የአቡነ ተክለ ሃይማኖት በዓለ ዕረፍት

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸውን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው ባሻገር እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፤ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያችንም ነሐሴ ፳፬ ቀን የዕረፍታቸውን በዓል በትላቅ ደስታ ታከብራለች፡፡