ቅድስት ኢየሉጣና ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ
ክፍል 2
ዲ/ን ደረሰ ተሾመ
በክፍል አንድ ጽሑፋችን እንገለጽነዉ በአረማዊው የሮም ንጉሥ በዲዮቅልጥያኖስ ዘመነ መንግሥት የተሾመው አረማዊው መኰንን እለእስክንድሮስ ክርስቲያኖችን ማሳደድና መግደል በጀመረ ጊዜ፣ ቅድስት ኢየሉጣ ልጇን ይዛ ወደ ጠርሴስ ብትሰደድም መኰንኑ ተከታትሎ በመምጣት ለጣዖት እንዲሰግዱና ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ አዘዛቸው።ቅዱሳኑ ግን በክርስቶስ ፍቅር ጸንተው እምነታቸውን አንክድም በማለታቸው በዓይንና በአፍንጫቸው ውስጥ ጨውና ሰናፍጭ ከመጨመር ጀምሮ፣ በጋሉ የብረት ችንካሮች መላ ሰውነታቸውን በማሠቃየት፣ እሳት በማንደድ፣ በመጋዝ በመሰንጠቅና በፈላ የጋን ውኃ ውስጥ በመጨመር በብዙ ዓይነት ጭካኔ የተሞላበት የሥቃይ መሣሪያዎች አሠቃይተዋቸዋል። (ስንክሳር ዘጥር ፲፭)
በዚህ ሁሉ መከራና ሥቃይ ውስጥ ግን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ በመምጣት ከሥቃያቸው ያድናቸው፣ የእሳቱንና የፈላውን ውኃ ኃይል ያቀዘቅዝላቸው ነበር። እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ በፈላው ውኃ ፊት በፈራች ጊዜም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ፦ «እናቴ ሆይ አትፍሪ፤ አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤልን ከእሳት ነበልባል ያዳናቸው እግዚአብሔር እኛንም ያድነናል» እያለ ያረጋጋትና በተጋድሎዋ እንድትጸና ያበረታት ነበር። ቅዱሳኑ ይህንን የመከራ መንገድ አልፈው በሰማዕትነት ካረፉ በኋላ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታላቅ ቃል ኪዳን ባለቤት ሆነዋል፤ ቤተ ክርስቲያናችንም በዓለ ክብራቸውን በዓመት ሁለት ጊዜ በድምቀት ታስባቸዋለች። አንደኛው ጥር ፲፭ ቀን በሰማዕትነት ያረፉበት ዋና በዓላቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሐምሌ ፲፱ ቀን ከፈላ ውኃና ከእሳት ነበልባል የዳኑበት፣ ቅዱስ ገብርኤል የተራዳቸውና ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ዕለት ነው።
ቅድስት ኢየሉጣ በጨካኙ መኰንን ፊት ስትቆም፣ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ደግሞ በሦስት ዓመቱ በእሳትና በፈላ ውኃ ፊት አልተናወጠም። ይህ ተጋድሎ ለዛሬው ትውልድ የሚያስተላልፈው ዋና ዋና መልእክቶች አሉ፣ለአብነትም፦
፩. ፈተናን በጽናት ማለፍ፦ ቅዱሳኑ መከራን በድል አልፈዋል። “እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።”እንዲል (የዮሐንስ ራእይ ፪፥፲) እውነተኛ ክርስቲያናዊ ማንነት በጊዜያዊ ችግር አይናወጥም።
፪. የወላጅና የልጅ መንፈሳዊ ትስስር፦ ምንም እንኳን በሦስት ዓመት እንዲህ ያለ ጥብአት እና ገድል የተገኘው በፈቃደ እግዚአብሔር ቢሆንም እናት ልጇን በሃይማኖትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ማሳደጓ ለመንፈስ ቅዱስ የተዘጋጀ ቤተ መቅደስ አድርጋዋለች፣”በሕፃኑ ላይም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት ታላላቅ ድንቆችና ተአምራቶችንም አደረገ ብዙዎች በሽተኞችንም አዳናቸው” (ስንክሳር ዘወርኀ ሐምሌ 19)። ልጅ ደግሞ እናቱ በፈራች ጊዜ አባቶቻችንን ቸል ያላለ፣ ሰማዕታትን የታደገ እግዚአብሔር እኛንም አይዘነጋንም ብሎ አጸናት። ይህም በቤተሰብ ውስጥ እርስ በእርስ በመንፈስ የመደጋገፍን ጥቅም ያሳያል።
፫. ‘አይዞህ/ሽ” የሚል ትውልድ፦ ክርስትና ለብቻ የሚሮጡት የብቸኝነት መንገድ ሳይሆን በጋራ የሚቆሙበት፣በጸሎት የሚተሳሰቡበት የድኅነት በር ነው። ዛሬ በጭንቀት፣ በደዌና በችግር ሳለን ወንድማችንና እኅታችን “አይዞህ አትፍራ/አትፍሪ” በጸሎትህ/ሽ አስበኝ/አስቢኝ መባባልን ገንዘብ ማድረግ እንደሚገባን አስተምረውናል። ብንደጋገፍ የምናተርፈው ለራሳችን ነው፣ በክርስትና በሚመጣ መከራ እና ሥቃይ ውስጥ ብቻችንን ያለን ቢመስለን እንኳን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው። ዛሬ በብዙ መከራ ውስጥ በሞት አፋፍ ላሉ ሰዎች ድካም ከመሆን ይልቅ ብርታት ለመሆን አይዟችሁ ማለት የክርስትና ግዴታ ነው።
፬. የማይለየው የመላእክት ተራዳኢነት፦ በመከራቸው ሁሉ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል አልተለያቸውም። “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል” (መዝ. ፴፬፥፯) እንደተባለ፣ በእግዚአብሔር ለሚታመኑ ሁሉ የመላእክት ጥበቃ አይለያቸውም። እግዚአብሔርን በመፍራት ሕይወት መላእክት ከእኛ ጋር ናቸውና።
፭.መመኪያቸው እግዚአብሔር ነበር፦ ተሰደው በሰው አገር ወገን ዘመድ የሚሉት በሌለበት ቦታ እንኳን ተስፋቸው እና መመኪያቸው ያደረጉት እግዚአብሔርን ነበር። እኛም ዛሬ ከሥልጣን፣ ከዘመድ ከቋንቋ፣ ከዘር ከሀብትና ከዝና በላይ የሆነ እግዚአብሔርን መመኪያችን ልናደርገው ይገባል።”እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፥ አልፈራም..”(መዝሙረ ዳዊት ፻፲፰፥፮ / ዕብራውያን ፲፫፥፮) እንዲል።
በዚህ ውጣ ውረድ በተሞላው ዓለም ውስጥ እምነትን፣ ማንነትንና ሥነ ምግባርን አጽንቶ መያዝ ትልቅ ተጋድሎ በሆነበት ዘመን—የቅዱስ ቂርቆስና የቅድስት ኢየሉጣ ታሪክ ለእኛ ለዚህ ዘመን ትውልድ ታላቅ የሕይወት መብራት ነው።
የዚህ ዓለም ጊዜያዊ ጥቅምና ክብር የሚያልፍ ነው፤ የቅዱሳኑ ጽናት ግን ዘለዓለማዊ አክሊልን አጎናጽፏቸዋል። እኛም በቀንም በሌሊትም የቅዱሳኑን ጸሎትና የመልአኩን ምልጃ ተስፋ በማድረግ፦ “በተአምኖ ንሴፎ ትንባሌ ዚአከ መዓልተ ወሌሊተ ዕቀበኒ አንተ”(በእግዚአብሔር ታምነን በቀንም በሌሊትም የአንተን ልመና ተስፋ እናደርጋለን) እያልን በመንፈሳዊ ሕይወታችን ልንጸና ይገባል።
የሰማዕታቱ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ ጸሎትና በረከት፣ የቅዱስ ገብርኤል አማላጅነትና ጥበቃ አይለየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
