እስመ ለመላእክቲሁ ይኤዝዞሙ በእንቲአከ/ መላእክቱን ስላንተ ያዛቸዋል. (መዝሙር ፺፥፲፩)
ዲ/ን ይትባረክ
ክፍል 1
ይህንን ቃል የተናገረው ቅዱስ ዳዊት ነው፡፡የቅዱሳን መላእክትን ተልእኮ ከቅዱሳን ሰዎች ጋራ ያላቸውን ግንኙነት፤አምላካችን እግዚአብሔር ስሙን ለሚጠሩ ስለ ስሙ ለሚጋደሉ በዐላውያን በመናፍቃን ዘንድ ሕያው ምስክር ሆነው መከራን የሚቀበሉ ሰዎችን ለመርዳት ለመታደግ ለማገልገል ለማጽናት ለማበርታት መላእክቱን እንደሚያዛቸው መላእክቱም እንደሚታዘዙ የታዘዙበትን ተልእኮም እንደሚወጡ ሰማዕታቱ በኀይለ እግዚአብሔር በእደ መላእክት ተደግፈው በክንፈ መላእክት ተጠልለው ለቅድስና ለክብረ ቅዱሳን እንደሚበቁ ለተስፋው ቃል ፍጻሜ እንደሚደርሱ የድል አክሊል እንደሚቀዳጁ ሲያመላክት…..
‹‹እስመ ለመላእክቲሁ ይኤዝዞሙ በእንቲአከ ከመ ይዕቀቡከ በኩሉ ፍናዊከ ወበእደዊሆሙ ያነሥኡከ ከመ ኢይትዐቀፍ በዕብን እግርከ….መላእክቱን ስላንተ ያዝዛቸዋልና በሥራህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ በእጃቸው ያነሱህ ዘንድ እግርህ በድንጋይ እንዳትሰናከል…›› ይላል፡፡ (መዝ ፺፥፲፩-፲፫፤ዘፀ ፳፫፥፳ ማቴ ፬፥፮)
መላእክት ስለ ሰው ልጆች የታዘዙበት ጥላ ከለላ የሆኑበት አቅፈው ደግፍው ለክብር ያበቁበት ስለ ሰው ልጆች ታዝዘው በመዓትም በምሕረትም በቁጣም በትሕትናም የተገለጹበት ወዳጅን ረድተው ጠላትን ቀጥተው የተገለጡበት ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ተጠቅሷል በብዙ ቅዱሳን ሕይወት ውስጥ ታይቷል፡፡(ዘፀ ፳፫፥፳ ማቴ ፬፥፮፤፩ኛ.መቃ ፲፫፥፳፩፤ኢያ ፭፥፲፫፤ኢሳ ፷፫፥፱…….)
በጣም ብዙ ምሳሌ መጥቀስ አስረጅ ታሪክ ማቅረብ የሚቻል ቢሆንም ለዛሬ ማንሳት የፈለግነው ግን ከመላእክት ወገን አንዱን በተራዳኢነቱ በመታዘዙ ለሰው ልጆች ባለው ቅርበትና አጋዥነት በብዙ ቅዱሳን ሰማዕታት የተጋድሎ የምስክርነት ሥራ ውስጥ በርኅራኄውና በቁጣው በፍቅሩና በአስፍሪነቱ የሚጠቀሰው ቅዱስ ገብርኤል ለቅዱስ ቂርቆስና ለእናቱ ለቅድስት ኢየሉጣ ያደረገውን ተራዳኢነት ነው፡፡
ይህ ገናና መልአክ ጥንት በሥነ ፍጥረት ዓለመ መላእክትን ያረጋጋ ነው፤ሦስቱን ሕፃናት ከእቶን እሳት ያወጣ መልአክ ነው ፤ይህ መልአክ ኤልሳቤጥን በእርጅናዋ ዘመን እንድትወልድ ያበሠረ ነው፤ይህ መልአክ ካህኑ ዘካርያስን አንደበቱን የዘጋ ነው፤ ይህ መልአክ ድንግል ማርያምን ለዛ ባለው ቃል በትሁት ማንነት ቀርቦ ያናገረ የልዑል ክርስቶስን መወለድ ያበሠረ የተስፋ ቃሉ ፍጻሜ መድረሱን ያስረዳ አብሣሬ ትስብእት ፍጡነ ረድኤት የሆነ መልአክ ነው፡፡
ወደ መነሻ ታሪካችን ስንመለስ ሐምሌ 19 ቀን ይህ መልአክ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱን ቅድስት ኢየሉጣን ከእሳት ማዳኑ የሚዘከርበት ዕለት ነው፡፡ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ሀገሩ ሮም አንጌቤን ነው፡፡ አባቱ ቆዝሞስ እናቱ ኢየሉጣ ሲሆኑ ቅድስት ኢየሉጣ ከአዝማደ ነገሥት ነበረች፡፡ዲዮቅልጥያኖስ በነገሠ በ20 ዓመት (በ303 ዓ.ም) በአባ አባጋግዮስ ምክንያት ‹‹አብያተ ክርስቲያናት ይትዐጸዋ አብያተ ጣዖታት ይትረኃዋ ››የሚል አዋጅ ሲታወጅ ብዙ ክርስቲያኖች እንደ ሽንኩርት ተላጡ እንደ ጎመን ተቀረደዱ በሰይፍ ተቆረጡ በእሳት ተቃጠሉ ብዙ መከራ ደረሰ ብዙዎቹም ተሰደዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ የሦስት ዓመት ሕፃን ሆኖ ከናቱ ጋር ወደ ጠርሴስ ሸሹ፡፡
ይሁን እንጅ በዚያም መስፍነ ብሔሩ እለእስክንድሮስ ክርስቶስን ካጂ ለጣኦት ስገጂ አላት፡፡‹‹ዐይን እያለው ለማያይ ጆሮ እያለው ለማይሰማ በቃልህ አዝዘህ በእጅህ አበጅተህ ላቆምከው ምስል አልሰግድም እስኪ ይህንን ህፃን ጠይቀው›› አለችው፡፡መስፍኑም ቅዱስ ቂርቆስን ‹‹አንተ ሕፃን ብዙ ወርቅ እሰጥሃለሁ ለዚህ ጣዖት ስገድ›› አለው፡፡መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ነበርና ‹‹አንሰ ኢይሰግድ ለአማልክቲከ ርኩሳን ዘኢይክሉ አድኅኖ ርእሶሙ…ራሳቸውን ማዳን ለማይችሉ ርኩሳን ጣዖቶችህ አልሰግድም›› አለው፡፡(መዝገበ ታሪክ ክፍል 2)
በዚህ ጊዜ ተበሳጭቶ በብረት ጋን ውኃ አፍልታችሁ ዝፍት ተይ ጨምራችሁ በዚያ ጣሏቸው ብሎ አዘዘ፡፡ዝፍት ተይ ጨምረው በብረት ጋን ውኃ አፍልተው ‹‹ድምፃ ለጽሕርት ከመ ነጎድጓደ ክረምት ››ይላል የውኃው መፍለቅለቅ ፍላቱ እንደ ክረምት ነጎድጓድ እስከ 42 ምዕራፍ ድረስ እስኪሰማ ይጮህ ነበር ፡፡በዚያ ሊጥሏቸው ሲወስዷቸው ቅድስት ኢየሉጣ ልቧ ታወከ ፈራች ልጇ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን ‹‹ፍርሃቷን አርቅላት›› እያለ ለእናቱ ይጸልይ ነበር፡፡
እንዲህም አላት ‹‹ጥብዒኬ እምየ እምዝ ዳግመ ኢይረክበነ ሞት…ሁለተኛ ሞት አያገኘንምና እናቴ ሆይ በርች ጨክኚ..አናንያን አዛርያን ሚሳኤልን ያዳነ እኛንስ ያድነን የልምን ? ››እያለ አጽናናት፡፡በዚህ ጊዜ ጨክነው ተያይዝው በእሳት ወደፈላው የጋን ዉኃ ገብተዋል፡፡ቅዱስ ዳዊት መላእክቱን ስላንተ ያዝዛቸዋል ያለው እንደነሱ ላለው ሕያው ምስክሮቹ ነውና ከመላእክት አንዱ ፍጡነ ረድኤት ቅዱስ ገብርኤል ፈጥኖ መጣ በበትረ መስቀሉ እሳቱን ሲመታዉ 42 ምዕራፍ እስኪሰማ የፈላው ዉሃ እንደ ጥዋት ጤዛ ቀዘቀዘ ቅድስት ኢየሉጣና ሕፃኑ ቂርቆስ በሰላም ከእሳቱ ወጡ፡፡
‹‹መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኒሁ›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት ..እግዚአብሔር በቅዱስ ቂርቆስ እና በእናቱ ቅድስት እየሉጣ ላይ የሠራው ተአምር እጅግ የሚደንቅ ተአምር እንደሆነ እንረለልን፡፡
አምላከ ቅዱስ ቂርቆስ ወኢየሉጣ በእደ መልአኩ ይጠብቀን አሜን፡፡
