ተዝካረ ዕረፍቱ ለአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ

መጋቢት ፪ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ተአምራቱና ትሩፋቱ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነው ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የዕረፍቱ ቀን መታሰቢያ መጋቢት ፭ ነው፡፡ ይህም ቅዱስ አባት በተወለደበት ቀን ድንቅ የሆነ ሥራን ሠራ፤ ተነሥቶ ከእናቱ እቅፍ ወርዶ “ከጨለማ ወደ ብርሃን ላወጣኸኝ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል” በማለት ሰግዷል፡፡

ሕፃኑም ሦስት ዓመት በሆነው ጊዜ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ሕፃኑን ከእናቱ እቅፍ አንሥቶ ብዙ ባሕታውያን ወዳሉበት ገዳም ወስዶ በደጅ አኖረው፤ ወደ አበምኔቱ ወደ አባ ዘመደ ብርሃንም ገብቶ ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ነገረው፡፡

በዚያን ጊዜም ነገሩ እውነት እንደሆነ ይረዳ ዘንድ አባ ዘመደ ብርሃን ተነሥቶ ወደ ደጅ ወጣ፡፡ መልአኩም እንደ ነገረው ሕፃኑ ከበር ተቀምጦ ፈገግታን ተመልቶ አገኘው፡፡ እጅግም ደስ ብሎት ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ ሕፃኑንም አንሥቶ ሳመው፤ ታቅፎም ወደ በዓቱ አስገባው፡፡ በፍቅር በሥነ ሥርዓት አሳደገው፡፡ የዳዊትን መዝሙርና ቤተ ክርስቲያን የምትቀበላቸውን መጻሕፍት ሁሉ ብሉይንና ሐዲስ አስተማረው፡፡

ከዚይ በኋላም ክህነተ ይሰጠው ዘንድ ስሙ አብርሃም ወደሚባል ጳጳስ ወሰደው፤ጳጳሱም በአየው ጊዜ ደስ አለው፡፡ የዲቁና ማዕረግንም ሾመው፤ እንደ ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስም ጸጋንና ሞገስን የተመላ ነው፡፡ ከጥቂት ቀኖች በኋላም በጌታችን ትእዛዝ ቅስና ተቀበለ፡፡ በጾም፣ በጸሎት፣በስግደት በብዙ ትጋትም እየተጋደለ በበረሀ ውስጥ ብቻውን ኖረ፡፡

በበረሀም ብዙ ዘመናትን ሲኖር ነፍሱን ‹‹ነፍስ ሆይ ዕወቂ፤ በእግዚአብሔር ፊት ራቁትሽን ትቆሚ ዘንድ እንዳለሽ እንግዲህስ ጽኚ፤በርቺ፤ታገሺ›› ይላት ነበር፡፡ ቆዳው ከአጥንቱ እስኪጣበቅ ያለ መብልና ያለ መጠጥ በእንዲህ ያለ ግብር በገድል ተጠምዶ ኖረ፡፡ ከዕፅዋት ፍሬዎች ወይም ከዕንጨት ሥሮች አልተመገበምና ለሥጋውም የሚጠቅም ምንም ምን ምክንያት አልፈለገም፡፡

ከብዙ ዘመናት በኋላም ለአባታችን ለገብረ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንዲህ አለው፤ ‹‹ከእንግዲህ በዓለም ካሉ ሰዎች ከካህናት፣ ከመነኰሳት ወይም ከምእመናን ሕዝቡ እንዳያውቅህ አደርግልሃለሁ፡፡ እንዳንተ ካሉ በቀር አንተ ራስህ ብትፈቅድ እንጂ መላእክትም ይጎበኙሃል፡፡ የብርሃን ሠረገላም ይሁንልህ፤መድረስ ወደምትሻበት ሁሉ ብረር እኔንም ማየትንም በፈለግህ ጊዜ ከአባቴና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ሦስትነቴ ታየኛለህ፤አሁንም ወደ ኢትዮጵያ ምድር ሂድ፤በዚያም ከደይን የምታወጣቸው ነፍሳት አለሁ፡፡›› ከዚህም በኋላ ስድሳ አንበሶች እና ስድሳ ነብሮች በፊት በኋላ አጅበውት ወደ ኢትዮጵያ ምድር ተጓዝ፡፡ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ቅዱስ ገብርኤልም ከአንበሶችና ከነብሮች ጋራ በነፋስ ሠረገላ አሳፍሮ ይመራው ነበር፡፡ ወደ ምድረ ከብድም አደረሰው፡፡ ከዚያም ወደ ልዩ ተራራ ወደ ደብረ ዝቋላ ወሰደው፡፡

አባታችን በባሕሩ ቁሞ ምሥራቁን፣ ምዕራቡን ሰሜኑን፣ ደቡቡን ዐራቱን ማዕዘን ተመለከተ፡፡ የኢትዮጵያ ሰዎች የሚሠሩትን ኃጢአታቸውን በዐይኖቹ ፊት የተፈለጠ ሆኖ አየ፡፡ በራሱም ተዘቅዝቆ ተወርውሮ ወደ ባሕሩ ውስጥ ገባ፤ ‹‹እነዚህን የእጅህ ፍጥረቶች የሆኑትን ካልማርካቸው ከዚህ ባሕር እንዳልወጣ በእግሮቼም እንዳልቆም በሕያው ስምህ እምላለሁ›› እያለ ማለ፤ እንዲህም ሆኖ ዐርባ ቀን ዐርባ ሌሊት ኖረ፡፡ ‹‹ስምህን የጠራውን መታሰቢያህን ያደረገውን እምርልሃለሁ›› የሚል ቃል በመልአክ አማካኝነትም ወደ አባታችን መጣ፡፡

አባታችንም መልአኩን ‹‹መላውን የኢትዮጵያ ሰው ካልማረልኝ ከዚህ ባሕር አልወጣም›› አለው፡፡ መልአኩም ከአጠገቡ ሄደ፤ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስም በዚያ ባሕር ውስጥ መቶ ዓመት ኖረ፤ሥጋው ሁሉ አለቀ፤ ደሙም በባሕሩ ውስጥ ፈሰሰ፤ አጥንቶቹም እንደ በረዶ ነጭ ሁነው ታዩ፡፡ አጋንንትም ከዐራቱ ማእዘን በየቀኑ ሰባት መቶ ሺህ ሦስት መቶ ሽህ እየሆኑ በመምጣት በቀስታቸው ይነድፉታል፤እስከ መቶ ዓመትም አጥንቶቹን በሻፎ ድንጋይ ይፍቁታል፤ይህን ሁሉ መከራ በትዕግሥት ሲቀበል ኖረ፡፡

ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እርሱ መጥቶ ከባሕሩ ዳር ቆመ፤ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስንም ‹‹መላውን የኢትዮጵያን ሰው ምሬልሃለሁና ተነሥተህ ውጣ›› አለው፡፡ ያንጊዜም ወጣ፤ አጥንቶቹም እንደ ወንፊት ቀዳዳ የተበሳሱ ሁነው ተገኙ፤ጌታም ዳሠሠውና ጠነኛ አደረገው፤ ወደ ምዳረ ከብድም ሰደደው፡፡

ከዚያ በኋላ ወደ ላይ ወጥቶ ከፀሐይ በላይ ከሰማይ በታች እስከ ሰባት ዓመት ኖረ፡፡ ዳግመኛም ወደ ምድረ ከብድ ተልኮ እንደ ዓምድም የተተከለ ሆኑ ሳባት ዓመት ቁሞ ኖረ፡፡ ወደ ሰማይም ሲመለከት ቅንድቦቹን አልከደነም፤ራሱንም ወደ መሬት ዝቅ አላደረገም ነበር፤ እጆቹም ወደ ሰማይ ያንጋጠጡ ሁነው አገኛቸው፤ በራሱ ላይም ተቀምጦ ሁለቱን ዐይኖቹን አንቊሮ አሳወረው፡፡ እርሱ ግን ምንም ሳያጓድል እንደ ቀድሞው በመትጋት ሲጸልይ ኖረ፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል መጥተው በፊቱ ቆመው በሁለት ዐይኖቹ ላይ እፍ አሉበት፡፡ ብርሃንም ተሰጥቷቸው እንደ ቀድሞው አዩ፡፡ ‹‹ከሰማይ ታላቅ ኃይል ተሰጥቶሃልና ጠላቶችህን ትበቀላቸው ዘንድ ወደ ዝቋላ ሂድ›› አሉት፤ ከዚያም መላእክት ከአጠገቡ ሄዱ፡፡ እርሱም ተነሥቶ ወደ ዝቋላ ተጓዘ፤ በጎዳናም ሲጓዝ ሦስት ሽማግሌዎች ከዕንጨት ጥላ በታች ተቀምጠው አየ፤ አባታችንም በአያቸው ጊዜ ‹‹ልሠወራቸው›› ብሎ በልቡ አሰበ፡፡ እነርሱም ፈጥነው ‹‹በእግዚአብሔር ዙፋን ተማጥነናልና ሦስታችንንም በጀርባህ እያዘልክ አንዳንድ ምዕራፍ ሸኘን እንጂ አትተውን›› ብለው ተጣሩ፡፡ በመጣም ጊዜ ሁለመናቸውን ሽበት የከበባቸው የደከሙ ሽማግሌዎች ሁነው አገኛቸው፤ አንደኛውንም አንሥቶ በጀርባው አዘለው፤ ወደ አንድ ምዕራፍም አደረሰው፤ ሽማግሌውም ‹‹ከዚህ አሳርፈኝ፤ አንተ ደክመሃል፤ የማትበላ የማትጠጣ ስለሆንክ›› አለው፡፡ አባታችንም ‹‹ሽማግሌ ሆይ በምን ዐወቅከኝ?›› አለ፤ ሽማግሌውም ‹‹ሄደህ ባልንጀሮቼን አምጣልኝ›› አለው፤ ተመልሶ ሁለቱ ወዳለቡትም ደርሶ ሁለተኛውን ሽማግሌ በጀርባው አዝሎ ወደ ቀደመው ሽማግሌ አድርሶ አብሮ አስቀመጠው፤ ሦስተኛም ተመልሶ ሦስተኛውን ሽማግሌ አዝሎ ሁለቱ ወዳሉበት አድርሶ በአንድነት አኖረው፡፡

አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስም እነዚያን አረጋውያን ‹‹እናንተ ከወዴት ናችሁ? መዓዛችሁ ልብ ይመሥጣል፤እጅግም ደስ ይለኛል›› አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ተነሥተው ቆሙ፤ አንድ ሲሆኑ ሦስት ሦስት ሲሆኑ አንድ መሆናቸውን ገለጡለት፤ የአባቶች አለቃ አብርሃም እንዳየ፤ያንጊዜም የእግዚአብሔርን የጌትነቱን ክብር አየ፤የእነዚያ አረጋውያንም ፊታቸው ተንቦገቦገ፤ ከፀሐይና ከመብረቅ ብልጭታም ሰባት እጅ በራ፤ አባታችንም በምሥጢራተ ጎርፍ የተዋጠ ሆኖ ፈራ፤ተንቀጠቀጠ፤ በምድር ላይም ወደቀ፡፡ ሕልምን የሚአልምም መሰለው፤ ከዚያም ጌታችን አባታችንን አነቃውና ‹‹መቶ ዓመት ያህል ሥጋህን ሲነድፉህ አጥንቶችህን ሲፍቁህ የኖሩ አጋንንትን ታጠፋቸው ዘንድ ወደ ዝቋላ ተራራ ውጣ አለው፡፡ ‹‹እኔ እንደ ወሰድኩህ ባለማወቃቸው በባሕር ውስጥ አለ በማለት በትዕቢት ላይ ናቸው፤ሰባቱ ሊቃነ መላእክትም ይረዱሃል፤መባርቅትም በፊት በኋላ ሁነው ይከተሉሃል›› አለው፡፡

ያንጊዜም አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ በመብረቅ ላያ ተጭኖ በረረ፤ እነዚያ አጋንንት ወዳለቡትም ወረደ፡፡ ደመናትም ከበቧቸው፤ መላእክትም በእሳት ሰይፍ መተሯቸው፤ በመብረቅም አጨዷቸው፡፡ አመድም ሁነው በነፋሱ በተኗቸው፡፡ የእነዚያም አጋንንት ቁጥራቸው ሰባት መቶ ሺህ እልፍ ከአንድ ሺህ ነበር፡፡

ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የካዱ ወዳሉበት ወደ ምዕራብ ሀገር ወሰደው፡፡ ነገሥታቱና መሳፍንቱ መኳንንቱም በሚወጡበትና በሚገቡበት ጐዳና ላይ አቆመው፤ ጌታችንም ‹‹በዚህች ጐዳና ብዙ መከራ ያገኝሃል፤ ግን በርታ፤ ታገሥ›› ብሎት በዚያ ተወው፡፡ በዚያን ጊዜም የዓረብ ንጉሥ ጣዖታትን አስይዞ መኳንንቱንና ሠራዊቱን አስከትሎ በዚያች ጐዳና መጣ፤ አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስን በጐዳና ውስጥ በተገናኙት ጊዜ ጣዖታቱ ወድቀው ተሰባበሩ፡፡ ንጉሡም አባታችንን በአየው ጊዜ ‹‹አንተ ጠጉር ለባሽ ምንድነህ? ሰው ነህን?›› አለው፡፡ አባታችንም ‹‹አዎን፤ ክብር ያለው የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያው የሆንኩ ሰው ነኝ››  ብሎ ለከሀዲው ንጉሥ መለሰለት፡፡ ንጉሡም ዳግመኛ አባታችንን ‹‹በዚያ አይሁድ በሰቀሉት ታምናለህን?›› አለው፡፡ ‹‹አባታችንም በሰው ፊት አምንበታለሁ፡፡ ስለ እኔ በተሰቀለው አላፍርበትም፤ ስለ እኔ ብቻ የተሰቀለ አይደለም፤ ስለ አንተና ከአንተ ጋር ስሏሉትም ነው እንጂ፤ ንጉሥ ሆይ፥ የዘለዓለም ሕይወትን ታገኛላችሁ፤ እመኑበት›› አለው፡፡ ንጉሡም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ተቆጣ፤ ሠራዊቱንም ጠርቶ ‹‹በፍጥነት እሳትን አንድዱ፤ለተሰቀለው ለናዝሬቱ ሰው ባሪያው ነኝ፤ የሚለውን ጠጉር ለባሽ ወስዳችሁ ጨምሩት›› አላቸው፡፡ የእሳቱም ነበልባል በረጅም ዛፍ መጠን ከፍ ከፍ እስከሚል አነደዱ፡፡ አባታችን ግን ንጉሡና ሠራዊቱ ሁሉ እያዩት አልፎ በፈቃዱ ወደ እሳቱ ገባ፡፡ እሳቱም እንደ ወንዝ ውኃ ሆነ፤ ሠራዊቱም እጅግ አደነቁ፤ እኩሌቶቹም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ፡፡

ንጉሡም ሲያደንቁ በአየ ጊዜ ፈጽሞ ተቆጣ፤ ከሰባ ሰባት አርበኞች ጋራ በቁጣ ተነሥቶ ያደነቁትንና ያመኑትን አንገታቸውን ቆረጠ፡፡ በዚያችም ቀን የተቆረጡት ዐርባ መቶ ሺህ ሁነው ተቆጠሩ፡፡ ንጉሡም የአባታችንን አንገት ሊቆርጥ ሰይፉን መዞ ተወርውሮ ሄደ፡፡ ያንጊዜም ከመብረቅና ከነጎድጓድ ጋራ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ፤ ንጉሡንም ከሠራዊቱ ጋራ አጠፋው፤ከከሀዲው ንጉሥ ጋራ የሞቱት ቁጥራቸው ዐራት ሺህ እልፍ ሆነ፡፡ ጌታችንም አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስን ‹‹ጠላቶችህንና የእኔንም ጠላቶች አጠፋሁልህ›› አለው፡፡  አባታችን ግን በመብረቅ የሞቱትን ሬሳቸውን ነፍሳቸውንም መላእክተ ጽልመት ወደ ሥቃይ ሲወስዷቸው በአየ ጊዜ መድኃኒታችንን ‹‹እነዚህን ስሑታን ማርልኝ፤ ሰው ስሑትና ከዳተኛ ነውና አቤቱ አንተ ግን መሐሪ፣ ይቅር ባይ ታጋሽም ነህ›› አለው፡፡ አባታችንም ይህን ሲናገር ጌታችን ተሠወረ፡፡

አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስም ከዚያ ሄደ፤ታላቅ ገደልም አገኘ፤ እግሮቹንም በገመድ ዐሥሮ በገደሉ ውስጥ ተዘቅዝቆ ተሰቀለ፡፡ ሰይጣንም መጥቶ ያቺን ገመድ ቆረጣት፤ ወደታችም ተወርውሮ ወረደ፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ቀድሞ አባታችንን ያዘው፤ ‹‹በእግርህ ላቁምህ ወይም በራስህ አለው፡፡ በራሴ እቆም ዘንድ ተወኝ›› አለው፡፡ ትቶት ሄደ፡፡ በዚያም በራሱ ቁሞ በጥርሶቹም ደንጊያ ነክሶ እስከ ሠላሳ ዓመት ኖረ፤ አንጀቱና ናለው ሁሉ እየፈሰሰ አልቆ መላ አካሉ እንደ እንጨት ቅርፊት ሆነ፡፡ ከሠላሳ ዓመትም በኋላ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባታችንን ‹‹ገብረ መንፈስ ቅዱስ›› እያለ ሦስት ጊዜ ጠራው፡፡ እርሱም ‹‹እነሆኝ ጌታዬ›› አለ፤ ጌታችንም ‹‹እነዚያን ከሀዲዎች ምሬልሃለሁ፤ ከዚህ ተነሣ›› አለው፡፡ ያንጊዜ የነከሰውን ደንጋይ ትቶ ተነሣ፡፡ ጥርሱም ተነቅሎ በደንጋይ ተተክሎ ቀረ፡፡ ክንፎቹም ተሰጥተውት እየበረረ ከእግዚአብሔር ፊት ደረሰ፤ ጌታውንም ‹‹ከማርክልኝ ከሥጋቸው ጋራ ተነሥተው በመጠመቅ ክርስቲያኖች ይሁኑ›› ብሎ ለመነው፡፡ መድኃኒታችንም ‹‹በሽተኞችን ልትፈውስ ሙታንን ልታስነሣ ሥልጣን ሰጥቼሃለሁ፤ አሁንም ወደተገደሉት ሄደህ በመስቀል ምልክት በላያቸው አማትብ፤ ሕይወት መድኃኒት በሆነ ስሜም አስነሣቸው›› አለው፡፡ ያንጊዜም በድኖቻቸው ወዳሉበት ሄዶ አስነሣቸው፤ አጥምቆም ክርስቲያኖች አደረጋቸው፤ ከእርሳቸውም ሄደ፡፡

ከዚህ ዓለም የሚለይበት በቀረበ ጊዜ እነሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነሆ ተገለጠለት፡፡ ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውንም ለሚያደርግ እስከ ዐሥራ አምስት ትውልድ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡የዕድሜውም ዘመናት አምስት መቶ ስድሳ ሁለት ሲሆን በሰላም በፍቅር ዐረፈ፤ጌታችንም ነፍሱን ተቀበለ፤ አቅፎም ሳማት፤ በመላእክትና በቅዱሳን ሁሉ ምስጋና አሳረጋት፡፡

የጸሎቱ ኃይል ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ይጠብቀን፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ መጋቢት