በዓለ መስቀል
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
በዓለ መስቀል
ክፍል ፩
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አስተምህሮ መሠረት የዐደባባይ በዓላት ሁለት ናቸው፡፡ እነርሱም የመስቀልና የጥምቀት በዓላት ናቸው፡፡
ከእነዚህም ውስጥ ከጌታ ዘጠኙ ንኡሳን በዓላት ከሚባሉት አንዱ የመስቀል በዓል ነው።
በዓሉ የሚከበርበትም ምክንያት፡- መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ከተወለደ በኋላ በዚህ ዓለም ፴፫ ዓመት ወንጌልን ለሰው ልጆች እያስተማረ ከቆየ በኋላ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ የሰውን ልጅ ለማዳን በቀራንዮ በመስቀል ተሰቅሎ ላይ ሞቶ በ፫ኛው ቀን ከተነሣ በኋላ ሕሙማን ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀሉን እየዳሰሱ በመስቀሉ እየታሹ ከሥጋ ደዌ ይፈውሱ ጀመረ። ይህንን ያዩ አይሁድም በምቀኝነት መስቀሉን ከቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ በመቅበር የአካባቢው ሕዝብ ቆሻሻ በሙሉ እንዲጣልበት ተደረገ። በአይሁድ ማኅበረሰብ ዘንድም የተቀበረበትን ለማጥፋት ለብዙ ዓመታት የቆሻሻ ማጠራቀሚያ በማድረጋቸው ምክንያት ተራራ ሆኖ ነበረ። በዚህም ምክንያት ለ፫፻ ዓመታት ያህል ተዳፍኖ ቆይቷል።
በኋላ ላይ ግን በ፫፻፳፮ ዓ.ም የታላቁ ንጉሥ የቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ መስቀሉ ያለበትን ለማወቅና ለማውጣት ብዙ ከደከመች በኋላ በመጨረሻም ስሙ ኪርያኮስ የተባለ ታሪክ ዐዋቂ አረጋዊ ታሪኩን ይነግራት ዘንድ ጥበብ የተሞላበት መንገድ ተጠቅማ በነገራት መሠረት ደመራ አስደምራ ዕጣን በመጨመር በእሳት ብትለኩሰው(ስታነደው ) ጢሱ እንደ ቀስተ ደመና መስቀሉ ከተቀበረበት ተራራ ላይ ተተክሎ ያለበትን ቦታ እግዚአብሔር በጥበቡ አመልክቷታል።
ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ይህን ሲያስረዳ በድጓው “ዘእጣን አንጸረ ሰገደ ጢስ በጎልጎታ ዘቀበሩ አይሁድ ዮም ተረክበ ዕፀ መስቀል”በማለት ይገልጻል።
ሳትውል ሳታድር መስከረም ፲፯ ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት ፲ ቀን ሦስት መስቀሎች ተገኙ ።ሁለቱ በቀኝና በግራ የተሰቀሉት የጥጦስና የዳክረስ ሲሆኑ አንዱ ደግሞ የክርስቶስ ነው ። የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል፡፡
በኋላም ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ፫፻፳፯ዓ.ም መስከረም ፲፯ ቤተ ክርስቲያን በመሥራት ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ነው።
በሀገራችን በኢትዮጵያም የመስቀልን በዓል ደመራ በመደመርና ችቦ በማብራት፥ ቅዳሴ በመቀደስና ማኅሌት በመቆም የምናከብረው ለዚህ ነው።
ደመራ ማለት ደመረ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን መጨመር ፣አንድ ማድረግ፣ መጣመርንና ኅብረትን ያስረዳል።ይህም በወቅቱ ከእሳቱ ያሉትን የእንጨት ክምችንና አንድነት የሚገልጽ ሲሆን ፍጻሜው ግን ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ሰላም ፍቅር አንድነትን መስበኩን ይገልጻል።
መጋቢት ፲ ቤተ ክርስቲያናችን በዓል እንደሆነ ብትዘክርም በድምቀት መስከረም ፲፯ የምታከብርበት ምክንያት መጋቢት ፲ ሁልጊዜ ታላቁ የዓቢይ ጾም ስለሚውልና የደስታን በዓል በደስታ ለማክበር ሲባልና ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበትን በማሰብ ነው።
ስለዚህ ኦርቶዶክሳውያን ይህን የመስቀል በዓል ስናከብር ቅዱስ ጳውሎስ “ጥልን በመስቀሉ ገደለ” (ኤፌ ፪፡፲፮ )በማለት እንደነገረን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ እኛን የአዳም ልጆች ተይዘን ከነበርንበት የሰይጣን ባርነት ነጻ በማውጣት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውንም የጥል ግድግዳ አፍርሶ በመስቀሉ ሰላምን፣ፍቅርንና አንድነትን አውጆልናል። እርሱን አርአያ አድርገን በሰላም ፣በፍቅር፣ በአንድነትና በመተሳሰብ በዓሉን ልናከብር ይገባል።
ጥልን በመስቀሉ ገድሎ አንድነትና ሰላምን ያወጀልን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ለሀገራችን ፣ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሕዝቦቿ ሰላምና ፍቅር ያድለን። የመስቀሉ ክብርና ጸጋ ረድኤት አይለየን። አሜን።
👇👇👇👇👇👇👇
የማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮች ይቀላቀሉ
ቴሌግራም፡- http://t.me/mkpublicrelation
የማኅበረ ቅዱሳን ሕዝብ ግንኙነት:-https://www.facebook.com/mahiberekidusan.mkusa/
ድረገጽ፡- http://www.eotcmk.org
ዩ ቲዩብ፡- http://www.youtube.com/user/EOTCMK
:- https://www.youtube.com/@-zemawetibebzmk7905
