የሰማዕተ ጽድቅ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እና የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ መታሰቢያ መርሐ ግብር ተካሄደ
የሰማዕተ ጽድቅ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እና የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ መታሰቢያ መርሐ ግብር ሐምሌ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በማኅበሩ ሕንጻ 3ኛ ወለል ንቡረ እድ ዲሜጥሮስ አዳራሽ ተካሄዷል።
በመርሐ ግብሩ የማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አመራር አባል ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም፣ የአሐዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፣ አምባሳደር ዓለም ፀሐይ መሠረት፣ አርቲስት ተስፋዬ ሲማ፣ ዶ/ር ጌትነት ፈለቀ፣ አርቲስት ብርሃኑ ሽብሩ፣ የእዝራ ሱቱኤል የጥናትና ምርምር ማእከል ሥራ አስፈጻሚ ዲ/ን እዝራ ንጋቱ፣ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ወዳጆች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አባል ዲ/ን ተረፈ ወርቁ፣ ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች፣ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚዎች፣ መደበኛ አገልጋዮችና አባላት ተገኝተዋል።
የጉባኤው ዓላማ የሰማዕተ ጽድቅ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እና የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን ጽኑና ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው በመሆኑ የብፁዓን አበው የሕይወት ተጋድሎ፣ የሃይማኖት ጥንካሬና የሀገር ወዳድነትን በመዘከር ትውልዱ ከአባቶች እንዲማርና በጽናት እንዲያገለግል የተዘጋጀ መሆኑን በማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ኀላፊ ዲ/ን ማስተዋል ባየ ገልጸዋል።
መርሐ ግብሩ በጸሎት የተጀመረ ሲሆን መዝሙር ቀርቦ ትምህርተ ወንጌል በመልአከ ታቦር ኃይለየሱስ ፈንታሁን ተሰጥቷል።
የማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አመራር አባል ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን ብፁዕነታቸው ትውልዱን በመቅረፅ ወደ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለማሰማራት ያደረጉት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ወዳጆች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አባል ዲ/ን ተረፈ ወርቁ የቤተ ክርስቲያንና የሀገር መብራት የሆኑትን፣ ለእውነትና ለነፃነት ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የሰማዕተ ጽድቅ የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን ታሪክና ተጋድሎ አቅርበዋል።
በመርሐ ግብሩ በርካታ ሐሳቦች ተነሥተው ውይይት የተደረገ ሲሆን የአሐዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በበኩላቸው “ኢትዮጵያኒዝም ከእነዚህ ታላላቅ አባቶች የመጣ በመሆኑ ያባቶችን ታሪክ በመዘከር ትውልዱ እንዲያውቀውና እንዲማር ልናደርግ ይገባል” ብለዋል።
