በዓለ ልደቱ ለአቡነ አረጋዊ

ጥር ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የጻድቁ የአቡነ አረጋዊ አባት ይስሐቅ እናቱም እድና ይባላሉ፡፡ ሁለቱም እግዚአብሔርን የሚፈሩና የሚያከብሩ ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር አምላክም የተባረከውን ልጅ ሰጣቸው፤ይህም የሆነው በጥር ፲፬ ቀን ነው፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት፣ ሕገ ኦሪትን ትምህርተ ነቢያትንና ቅዱሳት መፃሕፍትን እያስተማሩ አሳደጉት፡፡ እርሱም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየጸና እየበረታ አደገ፡፡ ሚስት ያገባ ዘንድ አጩለት፡፡ ጻድቁ አባታችን አቡነ ዘሚካኤል(አረጋዊ) ፈጽሞ እምቢ አለ፡፡ ከብዙ ዘመን በኋላ ከሮም ወደ ግሪክ ሀገር አባ ጳኩሚስ የሚኖርበት ደውናስ ወደምትባል ገዳም የምንኩስናን ልብስ ይለብስ ዘንድ ሄደ፡፡ አባ ጳኩሚስንም አገኘው፡፡ አባ ጳኩሚስም ‹‹ልጄ ሆይ፥  አንተ የንጉሥ ልጅ እንደ መሆንህ መጠን የመንግሥቱ ወራሽ ነህና መንኰሰህ ለመኖር ይቻልሃልን?›› አለው፡፡ ብፁዕ አባታችንም ‹‹አባቴ ሆይ፥ የምድር መንግሥት ኃላፊ ጠፊ ነው፤ ነገር ግን የማታልፈውን የማትጠፋውን ዘለዓለማዊት መንግሥት እወርስ ዘንድ እፈልጋለሁ›› አለው፡፡ በፈተናም ከጸና በኋላ በዐሥራ ዐራት ዓመቱ በአባ ጳኩሚስ እጅ የምንኩስናውን ልብስ ለበሰ፡፡ ከአመነኮሰውም በኋላ ስሙን ዘሚካኤል ብሎ ሰየመው፡፡

ከአባ እንጦንስ ዐራተኛው የቆብ ልጅ ሲሆን እርሱን በቆብ የሚወልደው ደገኛውን የገዳም ሥርዓትን ከሠሩልን አበው አንዱ የሆነው ታላቁ ቅዱስ ጳኲሚስ ነው። ቀድሞም በአባ ጳኲሚስ ዘንድ መንኲሶ ለመኖር ሲመጣ የመጣው ከንጉሥ ቤት ነበርና አባ ጳኲሚስ ከማመንኰሱ በፊት ብዙ ፈትኖታል። በኋላም ገና ልጅ ሳለ በዐሥራ ዐራት ዓመቱ አመነኰሰው። የምንኲስና ስሙንም አባ ዘሚካኤል ብሎ ሰየመው። አረጋዊ የተባለው ገና ወጣ ሁኖ ሳለ ልባዌውና ግብሩ ሁሉ እንደሚያስተውል አረጋዊ ነውና ‹‹አንተስ አባታችን አረጋዊ ነህ›› ብለው ጠሩት።

በገድልም ተጸምዶ የሚኖር ሆነ። በኋላም ከሁለት ደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከተመለከታት በኋላ ወደ ሮም ተመልሶ ለወንድሞቹ ለስምንቱ ቅዱሳን ነገራቸውና እየመራ አብረው መጥተው በኢትዮጵያ መኖር ጀመሩ። በኋላ እነርሱ በአንድነት መኖራቸው ለወንጌልና ለምንኲስና መስፋት አይሆንም ነበርና ሀገሪቱን ተከፋፈሏት። በዚህም አባታችን አቡነ አረጋዊ ወደ ትግራይ በተለይም ወደ ደብረ ዳሞ መጦና በዚያ በዓታቸው ወሰኑ። በእሊህ ዘጠኝ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እጅግ ብዙ የሐዋርያዊ አገልግሎት እንዲሰፋ ሆኗል።

አባ አረጋዊም ወደ ደብረ ዳሞ ለመውጣት በአደዱ ጊዜ የታዘዘ ዘንዶ ከወገባቸው ይዞ አውጥቷቸዋል። በዚያም ሲጋደሉ ከኖሩ በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያንን ሠሩና መወጣጫውን ‹‹ዳህምሞ-አፍርሰው›› ብለው አስፈረሱት። በዚህም ዳሞ ተብላ እንደተጠራች ይነገራል። እርሳቸውም በገድል ተጸምደው ከኖሩ በኋላ በዚያችው ገዳማቸው ሳሉ ወደ ብሔረ ሕያዋን ተሠውረው ሄደዋል። እኒህ ደግ ጻድቅ ከቅዱስ ያሬድም ጋር የሚነገርላቸው ግሩም ዜና አላቸው።

የጻድቁ በረከት በሁላችንም ይደርብን። እግዚአብሔርም በጸሎታቸው ይማረን፤ ለዘላለሙ አሜን።

ምንጭ፥ ስንክሣር ዘወርኃ ጥቅምት፣ ገድለ አቡነ አረጋዊ