ሲመቱ ለሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕታት ቅዱስ እስጢፋኖስ

ጥቅምት ፲፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የስሙ ትርጓሜ ‹አክሊል› የሆነው በሕገ ወንጌል የመጀመሪያ ሊቀ ዲያቆናትና ቀዳማዊ ሰማዕት የተባለ ቅዱስ እስጢፋኖስ ‹‹ሊቀ ዲያቆናት›› ከመባሉ በፊትም በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነበር፤ ከዚያም ዲያቆን ሆኖ ተሾሟል፤ ይህም ጥቅምት ፲፯ ቀን ነው፡፡

በሐዋርያት ሥራ ላይ እንደተጠቀሰው ይህ ቅዱስ በመጀመሪያ ገማልያል በተባለ መምህር ትውፊትን፣ ኦሪትንና ነቢያቱን ተምሯል፡፡ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መዋዕለ ስብከት ወቅትም እርሱ በዋለበት እየዋለ ባደረበት እያደረ ወንጌልን ተማረ፤ ደቀ መዝሙሩም ሆነ፤ ጌታችንም ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ አደረገው፤ አጋንንትም ተገዙለት፡፡ (የሐዋ.፭፥፴፬፣፮፥፭-፲)

በበዓለ ሃምሳም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሰባ ሁለቱ አርድእት መካከል የእርሱን ያህል ልሳን የበዛለት ምሥጢርም የተገለጠለት አልነበረም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መሪነትም ወንግልን ሰብኳል፡፡ በቤተ ክርስቲያንም ፈተና ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ሰባት ዲያቆናት ሲመርጡ አንዱ እርሱ ነበር፡፡ የስድስቱ ዲያቆናት አለቃና የስምንት ሺህ ማኅበር መሪ ሆኗል፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ስምንት ሺህውን ማኅበረ እየመራ ወንጌልን እየሰበከ ቢጋደል ኦሪት እየጠፋች ወንጌል ደግሞ እየሰፋች ሄደች፡፡ (የሐዋ.፮፥፬)

ቅዱስ እስጢፋኖስም የእግዚአብሔር ጸጋና ኃይል ያደረበትና ታላቅ እንዲሁም ድንቅ ታምራትን የሚያደርግ ሰው ስለነበር በዚያን ጊዜ አይሁድ በምቀኝነት ተነሡበት፤ ከእርሱ ጋርም ክርክር ገጠሙ፤ ነገር ግን ሊያሸንፉት አልቻሉም፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አድሮበታልና በፈጣሪ ኃይል አሸነፋቸው፡፡

ከዚህም በኋላ በሐሰት ምስክር ‹‹ይህን ሰው በሙሴና በእግዚአብሔር ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል›› በማለት ወነጀሉት፤ እርሱ ግን ስለ እውነት መሰከረ እንጂ በጀ አላላቸውም፤ ሊቀ ካህናቱም በጠየቁት ጊዜ ስለ እግዚአብሔር አምላኩ መሰከረ፤ በመጨረሻም እንዲህ አላቸው፤ ‹‹እናንተ አንገታችሁ የደነደነ፥ ልባችሁም የተደፈነ፥ ጆሮአችሁም የደነቈረ፥ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ዘወትር ትቃወማላችሁ፡፡ አባቶቻችሁ ከነቢያት ያሳደዱት ማን አለ? ዛሬም እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና የገደላችሁትን የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን ገደሉአቸው፡፡ በመላእክትም ሥርዐት ኦሪትን ተቀብላችሁ አልጠበቃችሁም፡፡›› በዚህም ተበሳጭተው በድንጋይ ወግረው ገደሉት፡፡ በዚህም ምስክሩን ፈጽሞ የሰማዕታት አክሊልን በጥር ፩ ቀን ተቀዳጅቷል፤ በዚህም ቀዳሜ ሰማዕታት ይባላል፡፡(የሐዋ. ፯፥፶፩-፶፫)

አይሁድ ቅዱስ እስጢፋኖስን ለማጥፋት ቀንተው ሲገድሉት ጠላት ዲያብሎስ ደግሞ ክርስትናን ለማጥፋት እነርሱን ሰበብ አድርጎ ለሞቱም ተጠያቂ እንዲሆኑ አድርጎአቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ክርስትናን ለማጥፋት ጠላት በሰዎች ላይ እያደረ ክርስቲያኖችን ያስገድላል፤ ያስጨፈጭፋል፤ እንዲሁም ያሳድዳል፡፡ በየጊዜውም በተለያዩ ክፍለ ሀገራት በጅምላ የሚጨፈጨፉት ሕፃናት፣ አረጋዊያን እንዲሁም ወጣቶች ምንም በማያውቁት ምክንያት፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በመናገራቸው ሳቢያ፣ ቤተ ክርስቲያን ሄደው በዓላትን በማክበራቸውና ባህላቸውን ለማስጠበቅ በመፈለጋው ብቻ ነው፡፡ እነዚህ እርኩስ መንፈስ ያደረባቸው ሰዎች የጠላት ተገዢ ከመሆናቸው ባሻገር ለራሳቸውና ለሌሎች ጥፋት መንሥኤ በመሆናቸው እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ ሐሰተኞችን በመቃወም ለእውነት መመስከር ይገባናል፡፡ ለዚህም በሃይማኖት ጸንቶ መኖር ይጠበቃልና እንጽና!

የቅዱስ እስጢፋኖስ አማላጅነትና ተረዳኢነት አይለየን፤ አሜን፡፡