የአቡነ ተክለ ሃይማኖት በዓለ ዕረፍት

ነሐሴ ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብ እና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኃረያ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፪፻፲፪ ዓ.ም በቡልጋ አውራጃ ኢቲሳ በሚባል ቦታ ተወለዱ፡፡  በተወለዱ በሦስተኛው ቀን እሑድ ከጠዋቱ በሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው‹‹አሐዱ  አብ  ቅዱስ  አሐዱ  ወልድ  ቅዱስ  አሐዱ  ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፤ አንዱ  አብ  ቅዱስ  ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ  ነው››በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ በተወለዱ በ፲፭ ዓመታቸው መዓርገ ዲቊናን፤ በ፳፪ ዓመታቸው ደግሞ መዓርገ ቅስናን ከግብጻዊው ጳጳስ አባ ጌርሎስ (ቄርሎስ) ተቀብለዋል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በመጀመሪያ በወላጆቻቸው የወጣላቸው ስም ፍሥሐ ጽዮን ነበር፡፡

በአንድ ወቅት በሕፃንነታቸውም ወደ ጫካ ለአደን በሔዱበት ጊዜ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ጸጋ መንፈስ ቅዱን አሳደረባቸው፡፡ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወንጌል ወዳልተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸውም አስረዳቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ከአውሬ አዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደ ተመረጡ፤ አጋንንትን የማውጣት፣ ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው፤ ስማቸውም ተክለ ሃይማኖት እንደሚባል፤ ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደሆነ አበሠራቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ያላቸውን ንብረት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው  ‹‹አቤቱ  ጌታዬ  ኢየሱስ  ክርስቶስ  ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደ ተከፈተ ተውኹልህ›› በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳንጸዋል፡፡

በደብረ ሊባኖስ ገዳምም (ገዳመ አስቦ) ዋሻ በመግባትም ሁለቱን በፊት፣ ሁለቱን በኋላ ሁለቱን በቀኝ፣ ሁለቱን በግራ ስምንት ጦሮችን ተክለው እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማም፣ ሞትና ነገረ መስቀል በማሰብ በተመስጦ ሌሊትና ቀን ያለ ማቋረጥ በጾም፣ በጸሎት ተወስነው ሲጋደሉ፤ ከቊመት ብዛት የተነሣ በ፺፪ኛ ዓመታቸው ጥር ፬ ቀን ፲፪፻፹፱ ዓ.ም አንዲቱ የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የመንፈሳዊ አባታቸውን ስባረ ዐፅም (የዐፅም ስባሪ) አክብረው በሥርዓት አኑረዋታል፡፡ እግራቸው እስኪሰበር የቆዩባቸው ዓመታትም ፳፪ ናቸው፡፡ ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው ቆመው ያለ ምግብና ያለ ውኃ በትኅርምት ሌሊትና ቀን እንደ ምሰሶ ጸንተው በትጋት ለሰው ዘር ዅሉ ድኅነትን ሲለምኑ ኖረዋል፡፡ ከሰባቱ ዓመታት ውስጥ ጥቂት ውኃ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ እንደ ነበረ መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡

አቡነ ተክለሃይማኖት ምድራዊ ሕይወታቸውን በተጋድሎና በሐዋርያዊ አገልግሎት ከፈጸሙ በኋላ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ የሚያልፉበት ቀን ተቃረበ፡፡ በዚህ ጊዜ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደ እርሳቸው በመምጣት የሚያርፉበት ዕለት መድረሱን ነገራቸው፡፡ የተጋድሏቸውን ጽናት አድንቆ በስማቸው መታሰቢያ ለሚያደርጉ፣ ለነዳያን ለሚመጸዉቱ ቤተ ክርስቲያን ለሚያሠሩ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ስለ ተጋድሏቸው ጽናትም  ‹‹በሰው  እጅ  የማይለካውን ይህንን የመንግሥት አዳራሽ ውሰድ››  በማለት የመለኮትን ነገር የሚናገር የእሳት አንደበት ያለው የጸጋ ልብስ አልብሷቸዋል፤ በመስቀል ምልክት ያጌጡ ሰባት የሕይወት አክሊላትንም አቀዳጅቷቸዋል፡፡

ጻደደቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት የዕረፍታቸው ጊዜ መቃረቡን ባወቁ ጊዜ የመንፈስ ልጆቻቸውን ጠርተው ጌታችን የነገራቸውን ሁሉ አስረድተው አባታዊ ምክርና ተግሣፅ ከሰጧቸው በኋላ ነሐሴ ፳፬ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውም ለአንድ ቅዱስ አባትና ካህን በሚገባ ሥርዓት በማኅሌት፣ በዝማሬና በምስጋና ቀብረዋቸዋል፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችንና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገልጾላቸዋል፤ነፍሳቸውንም ‹‹የጠራሽ፣ ንጽሕት ነፍስ ሆይ ወደ እኔ ነዪ›› ብሎ በክብር ተቀብሏታል፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዚህ ዓለም የኖሩበት ዕድሜ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከዐሥር ወር ከዐሥር ቀን ነው፡፡ በእናት አባታቸው ቤት ፳፪ ዓመት፤ በከተታ ፫ ዓመት፤ በይፋት ፱ ወር፤ በዳሞት ፲፪ ዓመት፤ በአማራ ፲ ዓመት፤ በሐይቅ ፲ ዓመት፤ በደብረ ዳሞ ፲፪ ዓመት፤ በትግራይና በኢየሩሳሌም ገዳማት ፩ ዓመት፤ ዳዳ በሚባል አገር ፩ ወር፤ በደብረ አስቦ ገዳም ፳፱ ዓመት ከ፲ ቀን መቆየታቸውን መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል (ገ.ተ.ሃ ፶፱፥፲፬-፲፭)፡፡

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸውን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደ ገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው ባሻገር እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፤ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያችንም ነሐሴ ፳፬ ቀን የዕረፍታቸውን በዓል በትላቅ ደስታ ታከብራለች፤ የጻድቁ በረከት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡መጽሐፈ ስንክሳር፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን፣ገድለ ተክለ ሃይማኖት፡፡