ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ

ዲያቆን ፋሲል በጋሻው

ነሐሴ ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ቶማስ ማለት የስሙ ትርጉም ፀሐይ ማለት ነው፡፡ በቶማስ  ስም የሚጠሩ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚታወቁ በርካታ ቅዱሳን አሉ፡፡ ከነዚህ መካከል ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ ናቸው፡፡ ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ ትሩፋትና ገድሉን ሰው ተናግሮ ሊፈጽመው አይችልም፤ እርሱ አስቀድሞ ከልጅነቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን የተማረ፣ ገና በወጣትነቱ መንኖ  ገዳም የኖረ፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በሰጊድ፣ ቀን እና ሌሊትም በመትጋት ለድኆችና ለምስኪኖችም በመራራት ተጠምዶ የኖረ ነበር፡፡ ቅዱስ ቶማስ ‹‹መርዓስ›› በምትባል አገር የወጣ የንጋት ኮከብ፣ ጻድቅ፣ ገዳማዊ፣ ጳጳስ፣ ሐዋርያ፣ ሰማዕትና ሊቅ ነው፡፡ የእርሱ ሕይወት ኦርቶዶክሳዊ የክርስትና ሕይወትና የጵጵስና የሹመት ሕይወት ምን እንደ ሆነ በትክክል የሚያሳይ ነው፡፡ መርዓስ በምትባል ሀገር ጳጳስ ሆኖ ተሹሞ በእረኝነት ያገለገል ዘንድ የክብር ባለቤት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መረጠው፤ መንጋውንም እንደ ሐዋርያት ጠበቀ፡፡

ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ብዙ አሕዛብን ወደ ክርስትና የመለሰ እና በዘመነ ሰማዕታት ብዙ መከራን የተቀበለ አባት ነው፡፡ ጨካኞቹ ቅዱሱን ለ፳፪ ዓመታት አካሉን እየቆራረጡ ለጣዖታቸው ያጥኑ ስለ ነበር ፪ እግሮቹ፣ ፪ እጆቹ፣ ፪ ጀሮዎቹ፣ ፪ አፍንጫዎቹ እና ፪ ዐይኖቹ አልነበሩም:: ነገር ግን እንዲህም ሆኖ አልሞተም እግዚአብሔርንም ማገልግል አልተወም ነበር፡፡ በመጨረሻም በዘመነ መናፍቃን አርዮስን ካወገዙት ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት አንዱ ለመሆን የበቃ ነበር፡፡

ከሃዲው ዲዮቅልጥያኖስ በነገሠ ጊዜ ክርስቲያኖቹን ሲያሰቃዩ በነበረበት ወቅት ከንጉሡ መኳንንት አንዱ ወደ መርዓስ ሄዶ ቶማስ ዘመርዓስን በጭፍሮቹ አስያዘው፤ ጭፍሮቹ እንደያዙት ደብድበው በምድር ላይ እየጎተቱት ደሙ እየፈሰሰ ወሰዱት፡፡

መኰንኑም ቅዱስ ቶማስን  ‹‹ለአማልክት ስገድ›› አለው፡፡ ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስም ‹‹እኔ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለረከሱ ጣዖታት አልሰግድም ለረከሱ ጣዖታት የሚሰግድ ሁሉ የተረገመ ነውና ከእግዚአብሔር በቀር የሚሰግዱለት አምላክ የለም›› አለው፡፡

መኰንኑም እጅግ የበዙ ጽኑ ሥቃዮችን አሠቃየው፡፡ የዘይት ድፍድፍ አፍልተው በሰውነቱ ላይ እንዲሁም በአፍና በአፍንጫው ውስጥ ጨመሩበት እስከ ብዙ ዘመናት ኖረ፡፡ እነዚህ ከሀድያን ልባቸው እንደ ደንጊያ የጸና ስለነበረ ቶሎ ብለው እንዲሞቱ ሳይሆን በሥቃይ ሆነው እንዲቆዩ በማድረግና ሌሎች ብዙዎች ሰዎችን ያስፈሩአቸው ዘንድ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ይክዱ ዘንድ የሥቃዩን ዘመን አስረዘሙት፡፡

ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ ግን በጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል የጸና ነውና ማሰቃየቱን ከሃዲያን በደከማቸው ጊዜ ስለስሕተታቸው ይዘልፋቸው ስለ ነበር ወደ ጨለማ  ቦታ ጣሉት በዚያም ለ፳፪ ዓመታት በጨለማ ውስጥ አስረው አሠቃዩት፡፡ ከሃድያኑም  በየዓመቱ ወደ እስር ቤቱ እየገቡ አንድ አካሉን ይቆርጣሉ፡፡

ከሃዲያኑ እጅና እግሩን በየተራ የቆራረጡትን የሰውነት አካላቱን አፍንጫውን፣ ከንፈሮቹን፣ ጆሮዎቹን ሁሉ በየተራ እየቆረጡ ለ፳፪ ዓመታት ጣዖታቸውን ሲያጥኑበት ኖረዋል፡፡

አንዲት ደግ ክርስቲያናዊት ሴት ቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ የተጣለበትን ጉድጓድ አይታ ስለነበረ በድብቅ በሌሊት ተሰውራ እየሄደች ትመግበው ነበር፡፡ ደገኛውና ጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እስከ ነገሠና የቀናች የክርስቶስን ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖትን ክብር እስከ ገለጠበት ድረስ ቶማስ ዘመርዓስ ሲሠቃይ ቆየ፡፡

ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመታመኑ የታሠሩ እሥረኞችን ሁሉ በሀገሮች ሁሉ በወህኒ ቤት ያሉትን ይፈቷቸው ዘንድ አዋጅ አውጥቶ ሲያዝ ክርስቲያናዊቷ ሴት ሄዳ ስለ ቅዱስ ቶማስ ስለ እርሱ የሆነበትን ሃያ ሁለት ዓመት ተጥሎ እንደኖረ ለካህናቱ ነገረቻቸው በውስጡ ወደ ሚኖርበትም ቦታ መራቻቸው፡፡

ካህናቱም አንሥተው ተሸከሙት እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አደረሱት፤ በቤተ መቅደሱም ፊት ለፊት በወንበሩ ላይ አስቀመጡት፤ ምእመናንም ሁሉ ወደእርሱ እየመጡ ከእርሱ ይባረኩና የተቆረጡ አካላቱን ይሳለሙ ነበር፡፡

ቶማስ ዘመርዓስ ወደ ሠለስቱ ምእት ጉባኤ ሲሄድ ዞሮ እንዳያስተምር እግሩን፣ ጽፎ መልእክታት እንዳይልክ እጁን፣ አካሉ ቆራርጠውት ስለነበር ደቀ መዛሙርቱ በቅርጫት ውስጥ አድርገው በአህያ ጭነው ወደ ጉባኤ ኒቂያ ይዘውት ስሄዱ ከደረሱት ቦታ አርዮሳውያን ሌሊት ካደረበት አህዮቹን አንገት አንገታቸውን ቆርጠው ጥለዋቸው ስለነበር እርሱም በጸጋ አውቆ ጎህ ሳይቀድ ተነሥቶ ጫኑ አላቸው፡፡ ቢሄዱ ተቆራርጠው አገኟቸው ምኑን ጫነው እንዲህ አድርጎዋቸዋል አሉት፡፡ራሳቸውን ከአንገታቸው ግጠሙ አላቸው፤ ጨለማ ስለነበር አህዮቹን አንዲት ጥቁር አንዲቱ ነጭ ነበሩ የነጭነቱን ከጥቁሪቱን የጥቁሪቱ ከነጭቱ አድርገው ገጠሙት፤ ሲነጋ በብርሃን ሲያይዋቸው እንዲያውም ውበት ሆኖአቸዋል፤ ወዲያውም ቢባርካቸው ተነሥተዋል፡፡ (መዝገበ ታሪክ ፪ ገጽ ፻፵፱)

ንገሥ ቈስጠንጢኖስ የከበሩ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳቱን በኒቂያ ሀገር እንዲሰበሰቡ ሲያደርግ ይህ የከበረ ቶማስ ዘመርዓስ ከሊቃውንቱ አንዱ  ነበር፡፡ ከጉባኤው ሲደርሱ ንጉሡ ቈስጠንጢኖስ ወደ ጉባኤው ገብቶ ለቅዱሳን ሊቃውንቱ ሰላምታ ሰጣቸውና ከሊቃውንቱ ቡራኬ ተቀበለ፡፡  የዚህን ቅዱስ የቶማስ ዘመርዓስን ተጋድሎውን በነገሩት ጊዜ ወደ እርሱ ቀርቦ ሰገደለት፤ አካላቱም ከተቈራረጡበት ላይ ተሳለመው። ከዚያም አዝኖና እጅግም ተደንቆ አድንቆ አካላቱን ዳሠሠው ፊቱንና ዓይኖቹን አሻሸው ጽድቁንም ዐውቆ ‹‹አባቴ በረከትህ ትድረሰኝ›› በማለት ተባርኳል፡፡

ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ካጸና በኋላ ወደ ሀገረ መንበረ ሢመቱ ተመልሶ ካህናቱንና መንጋዎቹን ሁሉ ሰብስቦ ጸሎተ ሃይማኖትን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን አነበበላቸው ይህን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንም አጽንተው እንዲጠብቁት  አዘዛቸው፡፡ ጥቂት ዘመናትም ከኖረ በኋላ ቅዱስ ቶማስ ጵጵስና በተሾመ በ፵ ዓመቱ ነሐሴ ፳፬ አርፏል፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው›› ብሎ እንደተናገረው ከቅዱስ ቶማስ ዘመርዓስ ታሪክ እኛ ኦርቶዶክሳዊያን የምንማረው የእምነት ጽናት፣ የሰማዕትነት ክብርና መረዳት፣ እውነተኛ እረኛ መሆን እንዲሁም በተግባር የተገለጸ ሕይወት ከሊቅነት ጋር ነው፡፡ (ቆላ.፪፥፭፣፩ዮሐ.፭፥፲፣ዮሐ.፲ ፥፲፩)

የጻድቁ፣ የሰማዕቱ፣ የሐዋርያው በረከቱ ረድኤቱ አይለየን፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ፣ መዝገበ ቅዱሳን፣ መዝገበ ታሪክ ፪

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር