ወርኀ ጽጌ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ወርኀ ጽጌ
እንኳን አደረሳችሁ!
ክፍል ፩
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት በአንድ ዓመት ውስጥ ያሉት ፫፻፷፭/፮ ቀናት በ ፬ ወቅቶች ይከፈላሉ፡፡እነሱም፦
፩. ዘመነ መጸው (መከር) መስከረም ፳፮-ታኅሣሥ ፳፭
፪. ዘመነ ሐጋይ (በጋ) ከታኅሣሥ ፳፮-መጋቢት ፳፭
፫. ዘመነ ጸደይ (በልግ) ከመጋቢት ፳፮-ሰኔ ፳፭
፬. ዘመነ ክረምት ከሰኔ ፳፮-መስከረም ፳፭ ናቸው።
እነዚህ ወቅቶች እያንዳንዳቸው ፺ ቀናት ሲኖራቸው ዘመነ ክረምት ብቻ ፺፭/፺፮ ቀናት አሉት።
በዚህም መሠረት ከመስከረም ፳፮ ቀን እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ወቅት ‹‹ዘመነ መጸው››(መኸር) ይባላል፡፡
መጸው ማለት ‹‹መጸወ ፤ መጽለወ ጠወለገ›› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ወርኀ ነፋስ (የነፋስ ወቅት)ማለት ነው። ወቅቱም ከዘመነ ክረምት ቀጥሎ የሚገባና በክረምት ዝናብ የበቀሉ ዕፀዋት አዝርት የሚያብቡበትና ፍሬ የሚያፈሩበት እንዲሁም ወንዞችና ምንጮች የሚጠሩበት የአበባ፣የነፋስ፣ የፍሬ ወቅት ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን ይህን ሲገልጽ
‹‹እስመ ናሁ ክረምት ኀለፈ ወዝናም ገብአ ድኅሬሁ ጽጌ አስተርአየ በውስተ ምድርነ ጊዜ ገሚድ በጽሐ ቃለ ማዕነቅ ተሰምዐ በምድርነ በለስ አውፅአ ሠርጸ አውያን ጸገዩ ወወሀቡ መዓዛ፡ እነሆ ክረምት ዐለፈ፤ ዝናቡም ዐልፎ ሔደ፡፡ አበባ በምድር ላይ ታየ፤ የመከርም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጐመራ፤ ወይኖችም አበቡ፤ መዓዛቸውንም ሰጡ፤›› (መኃ. ፪፥፲፩-፲፫) በማለት ያስረዳል፡፡
በዘመነ መጸው ውስጥ ፭ ንዑሳን ክፍሎች አሉ።
እነሱም፡- ፩.ዘመነ ጽጌ ፬. ብርሃን እና
፪. አስተምህሮ ፭. ኖላዊ ናቸው ።
፫. ስብከት
ከእነዚህም መካከል ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ለ፵ቀናት ያህል የሚቆየው በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ የእመቤታችን ስደት የሚታወስበትና እጅግ ጥልቅ ምስጢር የያዘ ክፍል
ዘመነ ጽጌ(ወርኀ ጽጌ) ይባላል።
ጽጌ ማለት ‹ጸገየ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ‹አበበ፤ አፈራ፤ በውበት ተንቆጠቆጠ፤ በደም ግባት አጌጠ፤ የፍሬ ምልክት አሣየ› ማለት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በአበባ የተመሰለች እመቤታችንንና በፍሬ የተመሰለ ልጇን ከወቅቱ ጋር በማዛመድ የምናመሰግንበት ጊዜ ነው። በወርኃ ጽጌ በዋናነት እመቤታችን ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱስ ዮሴፍና ከቅድስት ሰሎሜ ጋር በሄሮድስ ምክንያት ወደ ምድረ ግብጽ መሰደዳቸውን በማስታወስና በቤተ ክርስቲያናችን ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በደረሱት ድርሰት (ማኅሌተ ጽጌና ሰቆቃወ ድንግል) በማኅሌት ይከበራል።
የስደትን ነገር ስናነሳ እንዲሁ እንደውሃ ፈሳሽ እንደ ወንዝ ደራሽ ሳይሆን አስቀድሞ በነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተጭኖ ወደ ግብጽ ይመጣል ኢሳ ፲፱፡፩ በማለት የተነገረ ነው።
የስደት ወቅት በምንመለከትበት ጊዜ ወደ ምድረ ግብጽ የተሰደዱት ግንቦት ፳፬ ነው። ታዲያ ስለምን ቤተክርስቲያናችን ወደ መስከረም ቀይራ ታከብራለች ? ቢሉ
ስለ ፪ ምክንያት ነው።
፩. የስደት መነሻቸው ግንቦት 24 የሚውለው በበዓለ ኀምሳ በመሆኑ በደስታ ወቅት የስደትን ነገር ማዘከር ስለማይገባ ነው።
፪. ዘመነ ጽጌን ፍለጋ ነው።ምክንያቱም አበባዎች ለእመቤታችን ለድንግል ማርያምና ለልጇ ምሳሌዎች ናቸውና ።ይህንን ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል።
ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች ከእርሷም አበባ ይገኛል።ኢሳ ፲፩፡፩በማለት እንደነገረን ምሳሌን ከምሥጢር ጋር አዋሕዶ ለማክበር ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ሰርተዋል።
ስለዚህ ኦርቶዶክሳውያን በዘመነ ጽጌ በሄሮድስ የተመሰሉ ከልባችን የክርስቶስን ፍቅር የሚያሳድዱ ቅናትንና ትዕቢት አስወግደን ዘወትር ሕፃኑንና እናቱን በልባችን ጽላት አንግሠን እንድንኖር አምላካችን ይርዳን።
የልባችን ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሰደድ አብራ ትሰደዳለችና። ድንግል ሆይ “እስከ ማእዜኑ ትሄልዊ በምድረ ነኪር ሀገረኪ ገሊላ እትዊ፤
እስከ መቼ ድረስ በባዕድ ሀገር ትኖሪአለሽ? ወደ ሀገርሽ ገሊላ ተመለሽ።”
የሰላም መገኛ ሰላማዊት ርግብ ሱላማጢስ ሆይ፥ ሰላምን ትሰጭን ዘንድ ወደ ዐሥራት ሀገርሽ ኢትዮጵያና ወደ ልቡናችን ጓዳ ተመለሽ በማለት መለመን ይገባል።
የእመቤታችን የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
