አብርሃም ርእየ ፫ተ እደወ፤ በዛቲ ዕለት ምሥጢረ ሥላሴ ዜነወ።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን!
አብርሃም ርእየ ፫ተ እደወ፤ በዛቲ ዕለት ምሥጢረ ሥላሴ ዜነወ።
“አብርሃም ሦስት ሰዎችን አየ፤ በዚያችም ቀን የቅድስት ሥላሴ ምሥጢር ተገለጠ።“
የቅድስት ሥላሴ በዓልን ስናከብር የምናስበው ታላቁን የእምነታችንን ምሥጢር ነው።
አብ፣ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኮት አንድ በአካል በግብር ሦስት ናቸው ።
አምላክ ውእቱ አብ፤ ወአምላክ ውእቱ ወልድ፤ ወአምላክ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ ወኢይትበሀሉ ፫ተ አማልክተ፡፡ አላ ፩ዱ አምላክ፡፡
አብ አምላክ ነው፤ወልድም አምላክ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው፡፡ ግን ሦስት አማልክት አይባሉም አንድ አምላክ እንጂ፡፡
“ወከመዝ ውእቱ እምነትነ በቅድስት ሥላሴ ዘይሴብሑ እምነ ኵሉ ዘውእቶሙ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወኢንትአመን በካልእ አምላክ እምእሉ ፫ቱ አካላት እለ ፍሉጣን በገጻት ወኢሂ ፍሉጣን በህላዌ መለኮት በከመ ይቤ ዐቢይ መምህር ባስልዮስ በድርሳኑ በእንተ ሃይማኖት ዘቅድስት ሥላሴ ዘውእቶሙ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ህላዌ ዘኢተገብረ ወሥልጣን ከሀሊ ለፈጽሞ ኵሉ ፍጥረታት፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ ዘአንጾኪያ
በሁሉ ዘንድ የሚመሰገኑ በቅድስት ሥላሴ የምናምነው እምነት እንዲህ ነው፤ እነዚህም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ናቸው፤ በገጽ ልዩ በባሕርየ መለኮት የማይለዩ ከሚሆኑ ከእነዚህ ከሦስቱ አካላት በቀር፤ በሌላ አምላክ አናምንም፤ በቅድስት ሥላሴ ስለማመን በተናገረበት ድርሳኑ፤ ደገኛው መምህር ባስልዮስ እንደተናገረ፤ እነዚህም ያልተፈጠረ ባሕርይ ፍጥረትንም ሁሉ ለመፍጠር፤ ለማሳለፍ የሚቻለው ሥልጣን (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ) ናቸው” ።
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም በአካል በግብር ሦስት በባሕርይ በሕልውናና በፈቃድ አንድነት ጽኑዓን (የጸኑ) ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ተገኙ፣ በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና፡፡ ቅድስት ሥላሴን የሰው አእምሮ አጥንቶ እና ተመራምሮ ሊደርስበት አይችልም ምክንያቱም ከዕውቀትና ከአእምሮ በላይ ስለሆነ ይህንንም ለማስረዳት ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ ዘአንጾኪያ
“ወበፈጢረ ኵሉ ፍጥረታት ቅድስት ሥላሴ ኅቡራነ መለኮት እለ ርሑቃን እምኵሉ ዓቅም ወኁልቊ፡፡ ቅዱስ አትንቴዎስ ዘአንጾኪያ
በከሀሊነት ፍጥረትን ሁሉ በመፍጠር ከአብ ከወልድ ጋር አንድ ነው፤ በመለኮት አንድ የሚሆኑ፤ ሦስት አካላት ከመወሰን፤ ከቊጥር ሕግ ሁሉ የራቁ ናቸው”፡፡ ሃይ.አበ ፻፰፡፪
እንዲህ ስለተባለ ግን ስለ ሥላሴ ማወቅና መማር አይቻልም ማለት አይደለም ምክንያቱም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደምናገኘውና አባቶቻችን እንዳስተማሩን ቅድስት ሥላሴ በባሕርያቸው የማይመረመሩ ቢሆንም ለእኛ ግን በምንችለውና በምንረዳው ልክ እንደ አቅማችን በተለያየ መንገድ ራሳቸውን ገልጸውልናል ሥላሴ እንደ እናት ርኅሩኀን ናቸውና በእናት ሥርዓት ‹‹ቅድስት ሥላሴ›› እንላቸዋለን፡፡ ይህንንም ሊቁ አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ ዘአንጾኪያ በሃይማኖተ አበውእንዲህ ሲል ይገልጸዋል
ወኢናንቀለቅል ለግሙራ ኀበ ካልእ ሃይማኖት በእንተ ቅድስት ሥላሴ ቅዱስ የሐንስ ዘአንጾኪያ
ስለ ምሥጢረ ሥላሴ ካመንነው እምነት ወደ ሌላ ሃይማኖት አንናወጥም በማለት ሥላሴን ቅድስት ሥላሴ ብሎ በሴት (በእናት) አንቀጽ ሲናገር እናያለን ስለዚህ ሥላሴ እኛ በምንረዳው ልክ በተለያየ አገላለጽ ተገልጸዋል ካልን ከተገለጹበት መንገድ አንዱ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ፲፰፡፩_፲፮ ተጽፎ እንደ ምናገኘው ለአባታችን ለቅዱስ አብርሃምና ለእናታችን ለቅድስት ሣራ የተገለጸበት መንገድ ነው ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ሰው የለም አባታችን ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና ስለዚህ ዛሬ የምናስበውና ምናከብረው ይህንን ነው ።
ይኸውም ታሪኩን ስንመለከተው ፡- አብርሃም በተመሳቀለ መንገድ በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት። ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፥ ወደ ምድርም ሰገደ፥እንዲህም አለ፦
አቤቱ፥ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፥ እግራችሁን ታጠቡ፥ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፥ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና። እነርሱም፦ እንዳልህ አድርግ አሉት። አብርሃምም ወደ ድንኳን ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ገባና፦ ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፥ ለውሺውም፥ እንጎቻም አድርጊ አላት።
አብርሃምም ወደ ላሞቹ ሮጠ፥ እጅግ የሰባም ታናሽ ጥጃ ያዘና ለብላቴናው ሰጠው፥ ያዘጋጅም ዘንድ ተቻኰለ። እርጎና ወተትም ያዘጋጀውንም ጥጃ አመጣ፥ በፊታቸውም አቀረበው እርሱም ከዛፉ በታች በፊታቸው ቆሞ ነበር፥ እነርሱም በሉ። እነርሱም፦ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? አሉት። እርሱም፦ በድንኳኑ ውስጥ ናት አላቸው። እርሱም፦ የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች አለ። ሣራም በድንኳን ደጃፍ በስተ ኋላው ሳለች ይህንን ሰማች።
አብርሃምና ሣራም በዕድሜአቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። ሣራም በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች፦ ካረጀሁ በኋላ በውኑ ፍትወት ይሆንልኛልን? ጌታዬም ፈጽሞ ሸምግሎአል።እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። ካረጀሁ በኋላ በውኑ እወልዳለሁን? ስትል ሣራ ለምን ሳቀች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ ሣራም ልጅን ታገኛለች። ሣራም ስለ ፈራች፦ አልሳቅሁም ስትል ካደች። እርሱም፦ አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ አላት ። ከታሪኩ እንደምረዳው በብሉይ ኪዳን ከሚገርሙ የሥላሴ ምሳሌዎች አንዱ በአብርሃም ቤት የተፈጸመው ነው ። ምክንያቱም የሠላሴ አንድነትና ሦስትነት የተገለጸበት ነውና
ይህ የአብርሃም መስተንግዶ ታላቅ ትምህርት አለው፤
- አብርሃም እንግዳን አክብሮ በመቀበሉ ሥሉስ ቅዱስን ለመቀበል በቃ እኛም እንደ አብርሃም እንግዳ ተቀባይ ብንሆን እንደ አብርሃም በጸጋ የእግዚአብሔር ማደሪያ እንሆናለን
- አብርሃም እንግዳን አክብሮ በመቀበሉ ከሥሉስ ቅዱስ ተስፋው ተነገረው እኛም እንደ አብርሃም እንግዳ ተቀባይ ብንሆን እንደ በዚህ ዓለም የጨለመብን ተስፋ በሥላሴ ይበራልናል ።
- አብርሃም እንግዳን አክብሮ በፍቅር በመቀበሉ የፍቅር ባለቤት የሆኑ ሥሉስ ቅዱስ ፍቅራቸውን ገለጹበት እኛም እንደ አብርሃም እንግዳን በፍቅር ተቀባይ ብንሆን እንደ አብርሃም ፍቅር ባለቤት ሥሉስ ቅዱስ ፍቅርን በጸጋ ያጎናጽፉናል
- አብርሃም እንግዳን አክብሮ በእምነት በመቀበሉ ከሥሉስ ቅዱስ የእምነቱን ዋጋ ተቀብሏል እኛም እንደ አብርሃም እንግዳን በእምነት ተቀባይ ብንሆን እንደ አብርሃም ሥሉስ ቅዱስ የእምነታችንን ዋጋ በመንግሥተ ሰማያት ይሰጡናል ።
በአጠቃላይ በዚህ በዓል የሥላሴ ፍቅር የአብርሃም እምነት የሣራ ትዕግሥት በአንድነት የታየበት ብዙ ትምህርት የምንማርበት በዓል ነው በፍቅር መኖር በእምነት መጽናት ትዕግስትን ገንዘብ ማድረግ ይገባናል ።
በምግባር በሃይማኖት ጸንተን እንደ አእምሮአችን ስፋት በምንችለው መጠን ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያልን በምስጋና ጸንተን የሥላሴን መንግሥት እንወርስ ዘንድ ሥሉስ ቅዱስ ጥበብ ምሥጢርን ይግለጹልን አሜን።
