ዕረፍቱ ለቅዱስ አትናቴዎስ

ግንቦት ፭ ቀን፤ ፳፻፲፬ ዓ.ም

ቅዱስ አትናቴዎስ የተወለደው ግብጽ ውስጥ እስክንድርያ ነው:: ሐናፊ ከሚባል የእስላም ነገድና ከአረማውያን ወገን በመሆኑ በልጅነቱ ክርስትናን መማር አልቻለም ነበር::

አንድ ቀን ግን ክርስቲያን ሕፃናት እርስ በእርሳቸው እየተጫወተ ተመለከተ። ጨዋታቸውም የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመሥራት ስለነበር ከመካከላቸው ዲያቆናትንና ኤጲስ ቆጶሳትን ሲመርጡ እንዲያጫውቱት ለመናቸው። ነገር ግን ‹‹አንተ አረማዊ ነህና ከእኛ ጋር አትደመርም›› በማለት ከለከሉት፡፡ አትናቴዎስም ‹‹ክርስቲያን እሆናለሁ›› ባላቸው ጊዜ ሕፃናቱ ደስ ተሰኝተው ማዕረጋቸውን ለመለየት ዕጣ ተጣጣሉ:: ለአንዱ ቄስ፣ ለአንዱም ዲያቆን መሆን ሲደርሳቸው ለአትናቴዎስ ፓትርያርክ መሆን ስለ ደረሰው ሌሎቹ ሕፃናት ይሰግዱለት ጀመር::

በወቅቱ ፓትርያርክ የነበሩት ቅዱስ አባ እለ እስክንድሮስ ሕፃናቱ ይጫወቱ በነበረበት ሥፍራ ሲያልፉ ተመለከቷቸው። በመገረምም ለሕፃኑ አትናቴዎስ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናገረለት፤‹‹ይህ ሕፃን ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች ሹመትን ይሾም ዘንድ አለው፡፡››

ከዚህ በኋላ የአትናቴዎስ አባቱ ሞት፤ በዚህም ጊዜ ሊቀ ጳጳሳት አባ እለ እስክንድሮስ የክርስትናን ጥምቀት አጥመቀው። እርሱም የአባቱን ገንዘብ ለድኆች ከሰጠ በኋላ አባ እለ እስክንድሮስ ዘንድ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርትና ሕግ እንዲሁም ሥርዓት ተማረ፤ ከእርሱም ጋር ኖረ። አባ እለ እስክንድሮስ ዲቁናን ሾመው፤ መንፈስ ቅዱስም በቅዱስ አትናቴዎስ ላይ አደረ፡፡

በዚያም ወራት አርዮስ ቤተ ክርስቲያንን በመረበሹ ኒቅያ ላይ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ ጸሐፊ አድርገው ሾሙት:: ቅዱስ አትናቴዎስም አርዮስን ተከራክሮ አሸነፈው:: ከሊቃውንቱ ጋር ሆኖ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ወልደ አምላክ እግዚአብሔር መሆኑን በዐደባባይ መሠከረ::

ከዚህ በኋላ ሊቀ ጳጳሳት አባ እለ እስክንድሮስ ዐረፈ። ስለዚህም ቅዱስ አትናቴዎስ የእስክንድርያ ፳ኛ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾመ። ለዐርባ ስምንት ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ብዙ መከራዎችን አሳለፈ:: ለአምስት ጊዜ ከመንበሩ አፈናቅለው ወደ በርሃ ሲያሳድዱት ከዐሥራ አምስት ዓመታት በላይ በስደት ኖሯል:: በእነዚህ ዘመናት በተሰደደባቸው ስፍራዎች ያላመኑትን አሳምኗል:: በመልካም እረኝነት የሚመጠብቃቸው በጎቹ እንዳይጠፉበት ደግሞ በደብዳቤ በመጻፍ ካሉበት ሆነው እንዲጸኑ ይረዳቸው ነበር:: በሃይማኖተ አበው መጽሐፍ የምናገኘው ቃለ ሃይማኖት በዚህ ዘመን የተጻፈ ነው::

በዚያም ዘመን ታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስን ሲያርፍ አርዮሳዊ ልጁ ቆስጠንጢኖስ አባቱን ተከትሎ ነገሠ:: በዚህም የተነሣ አርዮሳውን በዘመኑ በዙ፤ ንጉሡም ሃይማኖታቸው የቀና አባቶችንም ማሳደድ ሲጀምር ቅዱስ አትናቴዎስ አብሮ ተሰደደ:: በመንበሩም በእርሱ ፈንታ ጊዮርጊስ የተባለ ከሀዲ ተሾመ፡፡

ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በዘመኑ ብዙ ክርስቲያኖችን በግፍ አስገደለ። ቅዱስ አትናቴዎስ ደግሞ ለስድስት ዓመታት አሠቃየው:: በዚህ መከራና ሥቃይ መቀበልም ቅዱስ ሐዋርያ ተባለ። ይህም ቅዱስ ስለ ሃይማኖቱ ተዋግቶ ከብዙ ሥቃይ በኋላ በግንቦት ሰባት ቀን ዐርፏል::

አምላካችን እግዚአብሔር ከቅዱስ አትናቴዎስ በረከት ያሳትፈን፤ አሜን!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት