ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ማወቅ የችግሮች መፍትሔ መኾኑን ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ገለጡ

ነሐሴ ፲፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ዮሴፍ ይኵኖአምላክ

አቡነ ዲዮስቆሮስ

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው፣ ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይና የምሥራቃዊ ዞን አዲግራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ መመሪያዎችንና ደንቦችን ባለመረዳት በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማስወገድ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ማወቅ፣ ዐውቆም በተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባ ገለጡ፡፡

ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በጽ/ቤታቸው በሰጡት ቃለ መጠይቅ የካህናትና የምእመናን ድርሻ ምን መኾን እንዳለበት በቃለ ዐዋዲው በግልጽ መሥፈሩን አስታውቀው ‹‹ኹሉም ሕዝበ ክርስቲያን ክርስቲያናዊ መብትና ግዴታውን ዐውቆ እናት ቤተ ክርስቲያንን በፍቅር በማገልገል መንፈሳዊ አደራውን ሊወጣ ይገባል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ኹሉ ጋርም በኢትዮጵያውያን ምእመናን መካከል ለረጅም ጊዜ ተጠብቆ የቆየው እርስ በርስ የመፈቃቀርና የመደጋገፍ ባህል ለተከታዩ ትውልድ እንዲሻገር የኹሉንም ትኩረት እንደሚሻ ጠቅሰው ‹‹በቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት የታነጸው በጎ ሥርዓት በዘመን አመጣሽ ጎጂ ልማዶች እንዳይበከል ተግተን ልንሠራ ይገባል›› ብለዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያዊው ባህል አብሮ መብላት መጠጣት ብቻ ሳይኾን በችግርና በደስታ ጊዜ በአብሮነት መኖር ነው›› ያሉት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የአብሮነት ትሥሥሩን ከሚያጠፉ የባህል ወረራዎች ምእመናኑ ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም የእምነት ወረራ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ መኾኑን ያስታወሱት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ‹‹ምእመናንን ከነጣቂ ተኩላዎች ለመከላከል በስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተጠናከረ ሥራ መሠራት አለበት›› በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በልዩ ልዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ለዝግጅት ክፍላችን የሰጡትን ሙሉ ቃለ መጠይቅ ከነሐሴ ፩-፲፭ ቀን እና ከ፲፮-፴ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በሚታተመው የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በቤተ አብርሃም ዓምድ ትከታተሉ ዘንድ ከወዲሁ እንጋብዛለን፡፡

በዓለ ፍልሰታና ሻደይ

ነሐሴ ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በሰቆጣ ማእከል

ሻደይ

ልጃገረዶች የሻደይን በዓል ሲጫወቱ

በአገራችን ኢትዮጵያ በተለይ በሰሜኑ ክፍል ሕዝበ ክርስቲያኑ ለረጅም ዘመናት ሥርዓተ አምልኮ ሲፈጸሙባቸው የነበሩና አሁንም እየተፈጸመባቸው የሚገኙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ መንፈሳውያን ቅርሶች በርካቶች ናቸው። ከእነዚህ ቅርሶች መካከልም መንፈሳውያን በዓላት የሚከበሩበት ሥርዓት አንደኛው ነው፡፡ ከእነዚህ መንፈሳውያን በዓላት ውስጥ በዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ምእመናን ዘንድ የሚከበረው የሻደይ ምስጋና (ጨዋታ) ልጃገረዶች በአማረ ልብስ ደምቀው ‹‹አሸንድዬ›› በሚባል የቄጠማ ጉንጉን ወገባቸውን አሥረው እየተጫወቱ የሚያከብሩት በዓል ነው።

ከነሐሴ ፲፮ እስከ ነሐሴ ፳፩ ቀን ድረስ የሚከበረው ይህ በዓል በዋግ ኽምራ ‹‹ሻደይ››፣ በላስታ ‹‹አሸንድዬ››፣ በትግራይ ‹‹አሸንዳ››፣ በቆቦ አካባቢ ‹‹ሶለል››፣ በአክሱም አካባቢ ደግሞ ‹‹ዓይነ ዋሪ›› እየተባለ ይጠራል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የሻደይ በዓል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ አለው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና እንደሚናገሩት የአዳም ከገነት መባረር፣ የኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ፣ የዘመን መለወጫ፣ የመጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አንገት መቈረጥ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ (ፍልሰታ) እና የመሥፍኑ ዮፍታሔ ልጅ ታሪክ ከሻደይ በዓል ተያያዥነት ያላቸው ሲኾን በተለይ የእመቤታችን ትንሣኤ (በዓለ ፍልሰታ) ከሻደይ በዓል ጋር የጎላ ግንኙት እንዳለው የቤተ ክርስቲያን መምህራንና የአገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡ እያንዳንዱ ታሪክ ከሻደይ በዓል ጋር ያለውን ግንኙነት በአጭሩ እንመልከት፤

የአዳም ከገነት መባረር

አባታችን አዳም ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፉ ጸጋ እግዚአብሔር ርቆት እርቃኑን በኾነ ጊዜ አካሉን ለመሸፈን የበለስ ቅጠል ማገልደሙን ለማስታዎስና አዳምና ሔዋን ክብራቸውን ተገፈው ከገነት የተባረሩባትን ዕለት ለማሰብ በወቅቱ ያገለደሙትን ቅጠል በምልክትነት በመውሰድ ልጃገረዶች የሻደይ ቅጠልን በገመድ ላይ ጎንጉነው በወገባቸው አገልድመው ያሥራሉ፡፡ አዳምና ሔዋን ከገነት ከመውጣታቸው በፊት ግብረ ሥጋ ግንኙነት ያልጀመሩ ደናግላን ስለነበሩ ያንን በመከተልና በምሳሌነት በመውሰድ ያላገቡ የአገው ልጃገረዶች ተሰባስበው የሻደይ ጨዋታን መጫወት ወይም ማክበር እንደጀመሩ ይነገራል።

የሻደይ በዓልና የጥፋት ውኃ

በኖኅ ዘመን ከተላከው የጥፋት ውኃ በኋላ ውኃው መጕደሉንና አለመጕደሉን እንድታጣራ ኖኅ ርግብን በላካት ጊዜ በምድር ሰላም መኾኑን የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ በመምጣት ለኖኅ የምሥራች ነግራዋለች። ከዚሁ ጋር በተገናኘ በዓሉን ያንን ለምለም ቅጠል ወገባቸው ላይ በማሰር ከጨለማ ወደ ብርሃን ተሸጋገርን ሲሉ ማክበር እንደጀመሩ አበው ከታሪኩ ጋር አያይዘው ያስቀምጡታል።

የሻደይ በዓልና የመሥፍኑ ዮፍታሔ ልጅ ታሪክ

ዮፍታሔ ወደ ጦርነት በሔደ ጊዜ በድል ከተመለሰ ወደ ቤቱ ሲመለስ መጀመሪያ የሚቀበለውን ሰው እንደሚሠዋ ስእለት ተስሎ ነበር፡፡ ድል አድርጎ ሲመለስም ያለ ወትሮዋ ልጁ እየዘፈነች ልትቀበለው ወጣች፤ በዚህም በጣም አዘነ። ልጁም ለአምላኩ የገባውን ስእለት እንዳያስቀር ብላ ሁለት ወር ስለ ድንግልናዋ አልቅሳ ስእለቱን እንዲፈጽም ጠይቃው ከሁለት ወር በኋላ ልጁን ሠውቷታል፡፡ አባቷ የገባውን ቃል ኪዳን እንዳያጥፍ በማበረታታት በመሥዋዕትነት የቀረበችውን የዮፍታሔን ልጅ በማሰብ በየዓመቱ እየተሰባሰቡ ሙሾ ያወጣሉ፡፡

የልጃገረዶች የቡድን አመሠራረት

በሻደይ በዓል የልጃገረዶች የቡድን አመሠራረት ደብርን (አጥቢያን) መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የሻደይ ጨዋታ በዓል በሚያከብሩበት ጊዜ ልጃገረዶች የተለያዩ ባሕላዊ አልባሳትን ለብሰው ከበሮ እና ለምስጋና የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማሟላት ተጠራርተው በመጀመሪያ ወደ አጥቢያቸው በመሔድ የቤተ ክርስቲያኑን በር አልፈው ዘልቀው ጣዕመ ዝማሬ እያሰሙ ሦስት ጊዜ ይዞሩና ደጃፉን ተሳልመው በቅጥር ግቢው አመቺ ቦታ ፈልገው ምስጋናቸውን ይጀምራሉ፡፡

ከበሯቸውን እየመቱ፣ የታቦቱን ስም እየጠሩ በሚያምር ድምፃቸው፣ ሽብሻቦ፣ ውዝዋዜ፣ ጥልቅ መልእክትን በያዙ ግጥሞች፣ ለዚህ ያደረሳቸውን አምላክና ታቦት ያወድሳሉ፣ ያሞግሳሉ፣ ያከብራሉ፣ ያመሰግናሉ፡፡ ምስጋናው ለዚህ ዓመት ያደረሳቸውን አምላክ ቀጣዩ ዓመትም እንደዚሁ የሰላም፣ የጤና የተድላ እንዲኾን የሚማጸኑበት፣ ተስፋቸውን የሚገልጹበትና ስእለት የሚሳሉበት በመኾኑ ምስጋናቸውን ሞቅ፣ ደመቅ አድርገው በአንድነት፣ በፍቅር፣ በደስታ፣ በመተሳሰብና በሰላም ይጫወታሉ፡፡ ‹‹ለእግዚአብሔርና ለደብራችን ታቦት ያልኾነ›› እያሉ ጉልበታቸውን፣ ችሎታውንና ልምዳቸውን ሳይቈጥቡ በምስጋናው ይሳተፋሉ።

ከቤተ ክርስቲያን መልስ በአካባቢው ወዳሉት ታላላቅ አባቶች ዘንድ ሔደው በመዘመር ቡራኬ ይቀበላሉ። ከዚያም ተመልሰው ወደ ተራራማ ሥፍራ በመውጣት ክብ ሠርተው ይዘምራሉ፡፡ የዝማሬዎቻቸው ግጥሞችና ዜማዎችም መንፈሳዊ ይዘት ያላቸውና ከግለሰባዊ ስሜት ወይም ከግለሰብ ውዳሴ የራቁ ናቸው፡፡ አጥቢያቸውን እንደማያስደፍሩና እንደሚጠብቁ በምስጋናቸው ይገልጻሉ፡፡ የወከሉትን ደብር ታቦት ስም እየጠሩ ለአባት እናት፣ ለቤተሰብ ጤና፣ ጸጋ፣ ሀብት፣ ሰላም በአጠቃላይ መልካሙን ኹሉ እንዲያደርግላቸው እግዚአብሔርን ይማጸናሉ፡፡

የምስጋናቸው ዜማና ግጥም ተመሳሳይ ቢኾንም የወከሉትን ደብር ስም ብቻ በማቀያየር በተመሳሳይ ዜማ ማወደስ እና መማጸን በኹሉም የሻደይ ተጨዋች ቡድኖች ይስተዋላል፡፡ ልጃገረዶቹ በዚህ የምስጋና ጊዜ የሚሰበስቧቸውን ስጦታዎችም ለቤተ ክርስቲያን ያበረክታሉ።

የሻደይ በዓልና ፍልሰታ

የሻደይ በዓል አጀማመርን በተመለክተ ከላይ ከተቀመጡት ታሪኮች በተጨማሪ በአካባቢው ሕዝብና በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ተደጋግሞ የሚነሣው ታሪክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ በዓል ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአዳምና ሔዋን ከአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመት በኋላ ወደዚህ ዓለም አንድያ ልጁን ልኮ ከኀጢአት እሥራት ነጻ እንደሚያወጣቸው በገባላው ቃል ኪዳን መሠረት አምላክ የተወለደባት እና ትንቢቱ የተፈጸመባት፣ ከገነት የተባረረው የሰው ልጅ ወደ ገነት እንዲመለስ ምክንያት የኾነችው፣ የሰው ልጆች መመኪያ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም ድካም ካረፈች በኋላ ሞትን ድል አድርጋ ከመቃብር ተነሥታ ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡

በፍልሰታ ወቅት በዓሉ መከበሩም ለሻደይ ተጨዋቾች ተምሳሌትና የድንግልናቸው አርአያ የሚያደርጓት ድንግል ማርያም አካላዊ ሥጋዋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፤ እንደዚሁም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ምክንያት በማድረግ እንደኾነ የሚገልጹት የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል መምሪያ ሓላፊ መጋቤ ምሥጢር ገብረ ሕይወት ኪዳነ ማርያም ‹‹የሻደይ በዓል በልጃገረዶች ዘንድ ተወዳጅ የኾነው በሔዋን ምክንያት የተዘጋው ገነት በእመቤታችን አማካኝነት በመከፈቱ ነው። እመቤታችን መመኪያቸው ስለ ኾነች ልጃገረዶች በዓሉን በደስታ ያከብሩታል፤ ድንግልናቸውንም አደራ የሚሉት ለእርሷ ነው›› ሲሉ ይናገራሉ።

እመቤታችን በነሐሴ ፲፮ ቀን በቅዱሳን መላእክት ሽብሸባ፣ ዕልልታና ዝማሬ ታጅባ ከምድር ወደ ሰማይ ስታርግ ሐዋርያት በታላቅ ደስታ ይመለከቱ፣ ይደነቁም ነበር፡፡

ደናግልም ከቅዱሳን መላእክት ከተመለከቱት ሥርዓት በመነሣት ነጫጭ ልብሶችን ለብሰው፣ አምረውና አጊጠው፣ ረጃጅምና ለምለም ቅጠል በወገባቸው አሥረው  እንደ መላእክቱ አክናፍ ወገባቸውን ከግራ ወደ ቀኝ እያመላለሱ፣ እያዘዋወሩና እያሸበሸቡ፣ በአንደበታቸው እየዘመሩና በእጆቻቸው እያጨበጨቡ በአንድነት ተሰባሰባስበው በፍቅርና በሐሴት የወቅቱ መታሰቢያ የኾነውን የሻደይን በዓል ያከብራ፡፡

እናቶችና እኅቶች በዐደባባይ ወጥተው የድንግል ማርያምን ትንሣኤና ዕርገት እንደ ነጻነታቸው ቀን በመቍጠር ከበሮ አዘጋጅተው ‹‹አሸንድዬ›› የተባለውን ቄጠማ በወገባቸው ታጥቀው ምስጋና በማቅረብ በዓሉን ይዘክራሉ፡፡

በአጠቃላይ የሻደይ ጨዋታ የፍልሰታ በዓል መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በምእመኑ ዘንድ ለበርካታ ዓመታት እየተከበረ የኖረ ሃይማኖታዊ በዓል ነው፡፡ ይህንን ሃይማኖታዊ መሠረትነት ያለውን ትውፊት የመጠበቅና የማስጠበቅ ሓላፊነት ከኹላችንም ይጠበቃል። የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦትም›› /መዝ.፻፴፩፥፰/

ነሐሴ ፲፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በመ/ ሳሙኤል ተስፋዬ

St.Marry

የእመቤታችንን መቀብርና ከሞት ተነሥታ ማረጓን የሚሳይ ሥዕል

እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ስደትህን በስደቴ፣ ሞትህን በሞቴ አጥፍቼ፤ የቀደመ ክብርህን መልሼ ያጣኸውን ርስት፣ ገነትን (መንግሥተ ሰማያትን) አወርስሃለሁ›› በማለት ለአባታችን አዳም የገባው ቃል ኪዳን /ገላ.፬፥፬/ ፍጻሜው በደረሰ ጊዜ ለእግዚአብሔር ወልድ ማደሪያነት የተመረጠች፣ ለአዳም እና ለዘሩ መዳን ምክንያት የኾነች ‹‹የልጅ ልጅ›› የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዳ ፲፭ ዓመት ሲኾናት በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት የእግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ማደሪያ ኾነች፡፡ ልጇን በወለደች ወቅት የሰብአ ሰገልን ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ›› የሚለውን ዜና የሰማ ሄሮድስ ሕፃኑን ለመግደል ዐዋጅ ዐወጀ፡፡ እመቤታችንም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማዳን ወደ ግብጽ ይዛው ተሰደደች /ማቴ.፪፥፲፪/፡፡

የስደቱ ዘመን አልቆ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ በኋላም ኢየሱስ ክርስቶስ ፴ ዓመት ሲኾነው ስለ መንግሥተ ሰማያትና ስለ ሰው ልጆች ነጻነት ይሰብክ ጀመር፡፡ ከዚህ በኋላ የአዳምና የዘሩን ሞት ለማጥፋት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ፤ በሦስተኛው ቀን ተነሥቶ፣ ባርነትን አስወግዶ ለሰው ልጅ ነጻነትን ዐወጀ፡፡

በዚህ ኹሉ የድኅነት ጉዞ ውስጥ ያልተለየችና ምክንያተ ድኂን የኾነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደች በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ዐርፋለች፡፡ ይህን የእመቤታችን ሞት የሚያስደንቅ መኾኑን ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ «ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው ኹሉ የተገባ ነው፡፡ የማርያም ሞት ግን ኹሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችንን የከበረ ሥጋዋን ገንዘውና ከፍነው ለማሳረፍ ወደ ጌቴሴማኒ መካነ ዕረፍት (የመቃብር ቦታ) ይዘው ሲሔዱ አይሁድ በቅናት መንፈስ ተነሳሥተው «ቀድሞ ልጇን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ፤ በዐርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል›› እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ እርሷንም እንደ ልጇ ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን? ኑ! ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት» ብለው ተማከሩ፡፡

ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ የከበረ ሥጋዋን የተሸከሙበትን አጎበር (የአልጋ ሸንኮር) በድፍረት ያዘ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሰይፍ ሁለት እጆቹን ቆረጣቸው፡፡ እጆቹ ተንጠልጥለው ከቆዩ በኋላ በእውነት የአምላክ እናት ናት በማለት ስለ አመነ እጆቹ ተመልሰው እንደነበሩ ሆነውለታል፡፡ ከዚህ በኋላ መልአከ እግዚአብሔር የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ  ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ነጥቆ ወስዶ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሐዋርያት ሲመጣ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ በገነት መኖሩን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አግኝተው  ለመቅበር በነበራቸው ምኞትና ጉጉት ‹‹ዮሐንስ አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን? ብንጠየቅስ ምን እንመልሳለን?›› በማለት በነሐሴ አንድ ቀን ሱባኤ ጀምረው ሲጾሙና ሲጸልዩ ከሰነበቱ በኋላ በሁለተኛው ሱባዔ መጨረሻ (ነሐሴ ፲፬ ቀን) ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ የከበረ ሥጋ አምጥቶ ሰጥቷቸው በታላቅ ዝማሬና ውዳሴ በጌቴሴማኒ ቀብረውታል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዐት ሲፈጸም አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን  እንደ ልጇ ተነሥታ ስታርግ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቀድሞ የልጅሽን፣ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ›› ብሎ ቢያዝን እመቤታችን ከእርሱ በቀር ሌሎች ሐዋርያት ትንሣኤዋን እንዳላዩ ነግራ አጽናናችው፡፡ ወደ ምድር ወርዶ የኾነውን ኹሉ ለሐዋርያት እንዲነግራቸው አዝዛው፣ ለምልክት ይኾነው ዘንድም የተገነዘችበትን ሰበኗን ሰጥታው ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡

ቅዱስ ቶማስም ሐዋርያት ወደ አሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ «የእመቤታችን ነገር እነዴት ኾነ?»  ብሎ ቢጠይቃቸው፤ «እመቤታችንን እኮ ቀበርናት» ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም ዐውቆ ምሥጢሩን ደብቆ «አይደረግም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር  እንደምን ይሆናል?» አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ መጠራጠር ልማድህ ነው፡፡ ቀድሞ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንም›› ብሎ  የእመቤታችን መካነ መቃብር ሊያሳዩት ይዘውት ሔዱ፡፡ መቃብሩን ቢከፍቱ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አጡት፤ ደነገጡም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሥታ ዐርጋለች» ብሎ  የኾነውን ኹሉ ተረከላቸውና የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ እነርሱም ማረጓን አምነው ሰበኗን ለበረከት ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሔዱ፡፡ በየሀገረ ስበከታቸውም ሕሙማንን ሲፈውሱበትና ገቢረ ተአምር ሲያደርጉበት ኖረዋል፡፡

በዓመቱ ‹‹ቶማስ ትንሣኤዋን አይቶ እንዴት እኛ ይቅርብን?›› ብለው ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ ሱባዔ ገብተው ነሐሴ ፲፮ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልመናቸውን ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ (ረዳት) ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሠናይ (ዋና) ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ አቍርቧቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ እመቤታችንን ሐዋርያት በግልጽ ትንሣኤዋን ዕርገቷን እያዩዋት ከጌታችን ጋር በክብር በይባቤና በዝማሬ ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ «እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች በሰማይም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች» እንዳለ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት ትንሣኤ ጊዜያዊና ዘለዓለማዊ በመባል ይታወቃል፡፡ ጊዜያዊ ትንሣኤ የሚባለው የእግዚአብሔር ከሃሊነት የሚገለጽበት ተአምራዊ ሥራ ኾኖ በተወሰኑ ሰዎች ላይ የሚፈጸምና ዳግም ሞትን የሚያስከትል ነው፡፡ ለምሳሌ ኤልያስ ያስነሣውን ወልደ መበለት /፩ኛነገ. ፲፯፥፰-፳፬/፤ ዐፅመ ኤልሳዕ ያስነሣውን ሰው /፪ኛነገ. ፲፫፥፳-፳፩/፤ ወለተ ኢያኢሮስን /ማቴ.፱፥፰-፳፮/፤ በዕለተ ስቅለት ከመቃብር ወጥተው በቅድስት ከተማ የታዩ ሙታንን /ማቴ. ፳፯፥፶፪-፶፫/፤ በቅዱስ ጴጥሮስ ጸሎትና ምልጃ የተነሣችዋን ጣቢታን /ሐዋ.፱፥፴፮-፵፩/፤ እንደዚሁም ትንሣኤ አልዓዛርን መጥቀስ ይቻላል /ዮሐ.፲፩፥፵፫-፵፬/፡፡ እነዚህ ኹሉ ለጊዜው ከሞት ቢነሡም ቆይተው ግን ተመልሰው ዐርፈዋል፡፡ ወደፊትም ትንሣኤ ዘጉባኤ ይጠብቃቸዋል፡፡

የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ግን የክብርና የሕይወት ትንሣኤ ሲኾን ሁለተኛ ሞትን አያስከትልም፤ ትንሣኤ ዘጉባኤንም አይጠብቅም፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤያችን በኵር ኾኖ በሞተ በሦስተኛው  ቀን ተነሥቷል፡፡ እመቤታችንም በልጇ ሥልጣን፤  እንደ ልጇ ትንሣኤ በሦስተኛው ቀን ተነሥታ ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳትጠብቅ በክብር ዐርጋለች፡፡  እንደዚህ ያለውን ትንሣኤ ከእርሷ በቀር ሌሎች ቅዱሳን ወይም ነቢያትና ሐዋርያት አላገኙትም፡፡ በዚህም ኹኔታ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ከማናቸውም ትንሣኤ ልዩ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ትንሣኤ ዘለዓለማዊ የኾነ ከዳግም ሞተ ሥጋ ነጻ የኾነ ትንሣኤ ነው፡፡

ይህ የእመቤታችን ዕርገት በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው ከእነ ሄኖክና ኤልያስ ዕርገት የተለየ ነው፡፡ «ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም» ተብሎ እንደ ተጸፈ /ዕብ ፲፩፥፭/፣ ሄኖክ ወደ ሰማይ ያረገው በምድር ሳለ እግዚአብሔርን በእምነቱና በመልካም ሥራው ስላስደስተና በሥራውም ቅዱስ ኾኖ ስለ ተገኘ ሞትን እንዳያይ ሲኾን ወደፊትም ገና ሞት ይጠብቀዋል፤ ሞቶም ትንሣኤ ዘጉባኤ ያስፈልገዋል፡፡ ነቢዩ ኤልያስም በእሳት ሠረገላም ቢነጠቅም /፪ኛነገ.፪፥፲/ ወደፊት ሞት ይጠብቀዋል፤ ትንሣኤ ዘጉባኤም ያስፈልገዋል፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በትንቢቱ «ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅድስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦትም» /መዝ.፻፴፩፥፰/ በማለት አስቀድሞ የክርስቶስን ትንሣኤ ከገለጸ በኋላ ቀጥሎ የመቅደሱ ታቦት እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ከሞት እንደምትነሣ ተናግሯል /ማቴ.፭፥፴፭፤ ገላ.፬፥፳፮፤ ዕብ. ፲፪፥፳፪፤ ራእ.፫፥፲፪/፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ ‹‹በቃልዋ የታመነች፣ በሥራዋም የተወደደች ቅድስት ድንግል ማርያምን መላእክት እያመሰገኗትና በመንፈሳዊ ደስታ እያጀቧት ወደ ሰማይ አሳረጓት›› ሲል እንደ ገለጸው፣ በመጽሐፈ ስንክሳርም እንደ ተመዘገበው ቅዱስ ዳዊት ‹‹በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ፣ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች›› /መዝ.፵፬፥፱/ በማለት የተናገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ አባቷ ዳዊት በበገና፣ ነቢዩ ዕዝራ በመሰንቆው እያመሰገኗት፤ በቅዱሳን መላእክት፣ በቅዱሳን ነቢያትና ጻድቃን ዝማሬ በብሩህ ደመና ወደ ሰማይ ዐርጋ በክብር ተቀምጣለች፡፡ በዚያም ሥፍራ ሁለተኛ ሞት ወይም ኀዘን፣ ጩኸትና፣ ስቃይ የለም፡፡ የቀደመው ሥርዐት አልፏልና /ራእ.፳፩፥፬-፭/፡፡

ስለዚህም የእመቤታችን ዕረፍቷ፣ ትንሣኤዋና ዕርገቷ በሚታሰብበት በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት ምእመናንን ከአካባቢያቸው ራቅ ብለው በተለያዩ ገዳማትና አድባራት በመሔድ አለዚያም በየአጥቢያቸው በመሰባሰብ እመቤታችን በተለያዩ ጊዜያት ሞቷንና ትንሣኤዋን ለሐዋርያት የገለጸችበትን ኹኔታ ያስባሉ፡፡ በጾም በጸሎት ተወስነው የልጇን ቸርነት የድንግልን አማላጅነት በእምነት ኾነው ይማጸናሉ፡፡ እንደዚሁም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነሐሴ ፲፮ ቀን እናቱን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳዒ ካህን፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ ሐዋርያትንም እመቤታችንንም ማቍረቡን በመዘከር ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ሱባዔው ሲፈጸምም «በእውነት ተነሥታለች» እያሉ በደስታ የጾሙን ወቅት ይፈጽማሉ፡፡

የእመቤታችን አማላጅነት፣ የትንሣኤያችን በኲር የኾነው የአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት ከኹላችን ጋር ይኹን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

አስደናቂው የድንግል ማርያም ሞትና ትንሣኤ

ነሐሴ ፲፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ታደለ ፈንታው

St.Merry

እመቤታችን ከሙታን ተነሥታ በክብር እንዳረገች የሚያሳይ ሥዕል

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የጌታ ልደቱና ጥምቀቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱና ዳግመኛ መምጣቱ በነገረ ድኅነት ትምህርታችን እጅግ ጠቃሚ የኾኑ ምሥጢራት ናቸው፡፡ ቤተልሔም የሥጋዌውን ምሥጢር ሲያሳይ ዮርዳኖስ ቀዳማዊ ልደቱን ያሳያል፡፡ የመጀመርያው የእኛ ባሕርይ ሲኾን ሁለተኛው የጌታ የራሱ የባሕርይ ገንዘቡ የኾነ ነው፡፡ እርሱ የሰው ልጅ ኾነ፤ እኛ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች ኾንን፡፡ ይህ ኹሉ የተደረገው ከድንግል ማርያም በነሳው ሥጋ ነው፡፡ እርሱ የእኛን ተፈጠሮ ገንዘቡ ስላደረገ፤ እኛ ደግሞ የእርሱን ቅድስና ገንዘብ በማድረግ የመንግሥቱ ተካፋዮች ለመኾን በቃን፡፡ በእርሷ ምክንያት የእኛ የኾነው ኹሉ የእግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር የኾነው የእኛ ኾኗል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ እናደርገዋለን፤ ለዚህ ክብር በቅታ ያከበረችንን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያዛመደችንን እመቤታችንንም እናከብራታለን፡፡

እርስዋ ከኪሩቤል ትበልጣለች፤ ከሱራፌልም ትከብራለች፡፡ ጌታችን የሱራፌልን፣ የኪሩቤልን ባሕርይ ባሕርዩ አላደረገም፡፡ የመላእክትንም ባሕርይ እንደዚሁ፤ የእርሷን አካል ባሕርዩ አደረገ እንጂ፡፡ የእኛ መንፈሳዊ ልደት የተገኘው ጌታ በሥጋ ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው ልደት ነው፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን አምላክና የሰው ልጆች የተገናኙበት፤ አምላክና ሰው የተዋሐዱበት መካነ ምሕረት ነው፡፡ እግዚአብሔር ዙፋኑን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀናት የዘረጋበት መካነ ሰላም ነው፡፡ የእግዚአብሔር ዙፋን ፍጹም በማይናወጥና ጸጥታ በነገሠበት ሥፍራ የሚዘረጋ የክብር ዙፋን ነው፡፡ ይህም ዙፋን የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ነው፡፡

ድንግል ማርያም በአባት በእናቷ ቤት ሦስት ዓመት፤ በቤተ መቅደስ ዐሥራ ሁለት ዓመት፤ ከልጇ ጋር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር፤ ከጌታችን ስቅለት በኋላ ደግሞ ዐሥራ አምስት ዓመታት በምድር ኖራለች፡፡ ጌታን የፀነሰችበትን ወራት ስንጨምር በዚህ ዓለም በሥጋ የቆየችበት ጊዜ ስድሳ አራት ዓመት ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ አርጋኖን ድርሰቱ ‹‹ከሚያሰጥመው ባሕር ሞገድ የተነሣ የማትነቀነቅ፣ መልኅቆቿም በሦስቱ ሥላሴ ገመድ የተሸረቡ ናቸው ይህቺ ደግሞ ከነፋሳት ኃይል የተነሣ የማትናወጥ በጭንጫ ላይ ያለች የዕንቈ ባሕርይ ምሰሶ ናት፤ እርሷን የተጠጋ መውደቅ መሰናከል የለበትም›› የሚላት እመቤታችን ሞት አይቀርምና እርሷም እንደሰው የምትሞትበት ጊዜ ደርሶ ጥር ሃያ አንድ ቀን ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ዐርፋለች፡፡ እግዚአብሔር አያደላምና /ሮሜ.፪፥፲፩/፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያም የኃያሉ እግዚአብሔር እናቱ፣ መቅደሱ፣ ታቦቱ፣ መንበሩ ኾና እያለ ሞትን መቅመሷ በራሱ የሚያስገርም ምሥጢር ነው፡፡ የዚህ ከኅሊናት ኹሉ በላይ የኾነው የእመቤታችን ዕረፍትም እንዲህ ተብሎ ተገልጿል፤ ‹‹ለምንት ይዜኃር ኃያል በኃይሉ ወባዕል በብዝኃ ብዕሉ ኢያድለወ ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ፡፡ ኃይለኛ በኃይሉ ለምን ይታጀራል? ባለ ጸጋም በሀብቱ ብዛት፡፡ ክርስቶስ ለአካሉ አላደላም፡፡ ሞትስ ለሟች ይገባዋል፤ የእመቤታችን የቅድስት ማርያም ሞት ግን አስደናቂ ነው›› /መጽሐፈ ዚቅ/፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ ‹‹ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነይ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፤ ዝናሙም አልፎ ሔደ፡፡ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቍርዬም ቃል በምድር ላይ ተሰማ፤›› /መኃ.፪፥፲-፲፬/፡፡ ይህ ትንቢት የዚህ ዓለም ድካሟ ኹሉ መፈጸሙን ያስረዳል፡፡ ልጇን ይዛ ከአገር ወደ አገር በረሀብና ጥም የተንከራተተችበት ጊዜ አሁን አለፈ፡፡ ታናሽ ብላቴና ሳለች ልጇን አዝላ በግብጽ በረሃ የተቀበለችው መከራ ኹሉ ፍጻሜ አገኘ፡፡ ከእግረ መስቀል ሥር ወድቃ የልጇን የቈሰለ ገላ እየተመለከተች የደረሰባት ልብ የሚሰነጥቅ ኀዘን ወደ ደስታ ተለወጠ፡፡ ‹‹በነፍሷ ሰይፍ ያልፋል›› ተብሎ የተነገረው ልብ የሚሰነጥቅ መከራ እንደ ነቢዩ ቃል ትንቢት የሚቀጥልበት ጊዜ ተፈጸመ፡፡

የቤተ ክርስቲያን ትውፊት የድንግል ማርያም ሞት በሚከተሉት ምክንያቶች እንደ ኾነ ያስረዳል፤ የመጀመሪያው ‹‹ለመለኮት ማደርያ ለመኾን የበቃችው ኃይል አርያማዊት ብትኾን ነው እንጂ እንደ ምድራዊት ሴትማ እንደምን ሰማይና ምድር የማይችለውን አምላክ ልትሸከመው ይቻላታል?›› የሚሉ ወገኖች ነበሩና እግዚአብሔር ወልድ የተዋሐደው የሰው ልጆችን ሥጋ መኾኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲያስረዳ ‹‹እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፣ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፡፡ በሕይወታቸው ኹሉ ስለሞት ፍርሃት በባርነት ይታሠሩ የነበሩትን ኹሉ ነጻ እንዲያወጣ፣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም›› አለ /ዕብ.፪፥፲፬-፲፭/፡፡ በዚህም ድንግል ማርያም የአዳም ዘር መኾኗ ታወቀ፡፡ ሁለተኛው ቅዱስ ያሬድ እንደተናገረው ጌታችን በፍርዱ አድልዎ የሌለበት መኾኑ ይታወቅ ዘንድ ነው፡፡ ሥጋ የለበሰ ኹሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ የግድ ነውና፡፡

እመቤታችን ባረፈች ጊዜ ሐዋርያት ሊቀብሯት ሲሹም ከአይሁድ ክፋት የተነሣ ልጇ ሌላ ክብርን ደረበላት፡፡ ከጌቴሴማኒ ሥጋዋ ተነጥቆ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር እስከ ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን ለሁለት መቶ አምስት ቀናት ቆይታለች፡፡ ልጇ ወዳጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሥልጣኑ እንዳሸነፈ የልጇ መለኮታዊ ኃይል ሞትን አሸንፋ እንድትነሣ አደረጋት፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ስለ ትንሣኤዋ የተናገረው ቃል ተፈጸመ፡፡ ሊቁ ‹‹ለዛቲ ብእሲት ሠረቀ ላዕሌሃ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ ወአግዓዛ እምእኩይ ውስተ ሠናይ እሞት ውስተ ሕይወት፤ በድንግል ማርያም ላይ የአብ የባለጸግነቱ ብዛት ተገለጠ፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከክፉ ዓለም ወደ በጎ ዓለም አሸጋግሯታልና›› ሲል የተነጋረውም ይኼንን ምሥጢር የሚገልጽ ነው፡፡

ለአምላካችን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና ከሞት ወጥመድ በላይ እንኳን የኾነ ሌላ ኃይል አለ፤ ይኼውም ሞት ፈጽሞ ሊያሸንፈውና ሊገዳደረው የማይችል የእግዚአብሔር መለኮታዊ ኃይል ነው፡፡ ሕያው የኾነው እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነውና ሞት ሊያሸንፈው፣ ሊደርስበትም የማይችለውን ሕይወት ይሰጣል፡፡ ይህንን እርሱ የሚሰጠውን ሕይወት ሰይጣን በእጁ ሊነካው ከቶውንም አይችልም፡፡ ከሞት ሥልጣንና ኃይል በላይ የኾነው ይኸው የእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥልጣን የድንግል ማርያምን ሥጋ ለፍርድ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ በመቃብር ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይ፤ ፈርሶና በስብሶ በምድር ላይ እንዲቀር አላደረገም፡፡ ከሙታን መካከል ተለይታ ተነሥታለች፡፡ እንድትነሣም ያደረገ የእግዚአብሔር ኃይል ነው እንጂ በራሷ ሥልጣን የተነሣች አይደለችም፡፡ መንፈስ ቅዱስ በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷን በትንቢት እንዳናገረ ትንሣኤዋንም በትንቢት ሲያናግር ኖሯልና ይህ ታላቅ ምሥጢር በቅዱስ ዳዊት አንደበት ‹‹ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦትም›› ተብሎ ተገልጿል /መዝ.፻፴፩፥፰/፡፡

ቅዱስ ዳዊት በዚህ የትንቢት ክፍል ትንሣኤዋን አስረድቷል፡፡ ታቦት የጽላቱ ማደሪያ ነው፡፡ በታቦቱ ውስጥ የሚያድረው በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፈው ሕጉ ነው፡፡ ይህ እግዚአብሔር ያከበረው ነገር ኾኖ ሊመጣ ላለው ነገር ማሳያ ነው፡፡ እውነተኛዋ ታቦት ማርያም ናት፡፡ ሙሴ በተቀበለው ታቦት ውስጥ ያለው ጽላት በውስጡ የያዘው ሕጉን ነው፤ በድንግል ማርያም ላይ ያደረው ግን የሕጉ ባለቤት ነውና፡፡ ከፍጡራን ከፍ ከፍ የማለቷ ድንቅ ምሥጢርም ይህ ነውና፡፡ የእመቤታችን ትምክህቷም፣ ትውክልቷም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኾነ ወንጌላውያኑ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው መስክረውላታል፡፡ እርሷም ‹‹ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬ፣ በመድኃኒቴ ሐሤትን ታደርጋለች›› በማለት ተናግራለች /ሉቃ.፩፥፵፯/፡፡

እመቤታችን ባለችበት ሥፍራ የሕይወት ትንሣኤ ያላቸው ሰዎች ይኾኑ ዘንድ አስቀድማ ከሙታን ተለይታ በመነሣት የተጠበቀልን ተስፋ ማሳያ ኾነችን፡፡ ከእንግዲህ በኋላ ልጇ ሲንገላታ፣ ሲሰደድ፣ ሲገረፍ፣ ሲሰቀል፣ ሲቸነከር ያየችበት ዓለም አለፈ፡፡ አሁን የልጇን ልዕልና ከሚያደንቁ ጋር ታደንቃለች፤ ከፍ ከፍ ከሚያደርጉት ጋር ታከብረዋለች፡፡ ይኸውም ከገቡ የማይወጡበት፤ ኀዘን፣ መከራ፣ ችግር የሌለበት ሰማያዊ አገር ነው፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ስደት፣ መከራ፣ ኀዘን፣ ሰቆቃ፣ መገፋት፣ መግፋትም የለም፡፡ ቅዱሳን ሩጫቸውን ጨርሰው የድል አክሊልን የሚቀዳጁበት ሥፍራ ነው፡፡ በዚህም ከፍጡራን ኹሉ ከፍ ባለ በታላቅ ክብርና ጸጋ ለዘለዓለም እንደምትኖር እናምናለን፡፡ ልመናዋ፣ ክብሯ፣ ፍቅሯ፣ አማላጅነቷ፣ የልጇም ቸርነት በኹላችን ላይ አድሮ ይኑር፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡ሐመር ፲፰ ዓመት፣ ቍጥር

ደብረ ታቦርና ቡሄ

ነሐሴ ፲፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን በዓሉ ይከበራል፡፡ ይህ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ‹‹ቡሄ›› በመባል ይታወቃል፡፡

ቡሄ ማለት /መላጣ ፣ ገላጣ/ ማለት ነው፡፡ በአገራችን ክረምቱ፣ አፈናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት በዚሁ በዓል አካባቢ ስለኾነ ‹‹ቡሄ›› እንደ ተባለ ይገመታል፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት፣ ብርሃን የታየበት፣ ድምፀ መለኮት የተሰማበትና ችቦ የሚበራበት ዕለት ስለ ኾነ ደብረ ታቦር የብርሃን ወይም የቡሄ በዓል ይባላል፡፡

ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን፣ ወደ ጥቢ የሚያመራበት፣ ወደ መፀው የሚገባበት፣ ወገግታ የሚታይበት፣ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፣ የሚሸጋገርበት ወቅት በመኾኑ ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት አይኖርም፡፡ ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እንዲሉ፡፡በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የቡሄ ዕለት ማታ ምእመናን ችቦ ያበራሉ፡፡ ይህም በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ ነው፡፡

ሕፃናቱ ይህ በዓል ከመድረሱ በፊት ቀደም ብለው ጅራፍ ሲገምዱና ሲያጮኹ (ሲያኖጉ) ይሰነብታሉ፡፡ እናቶችም ለዚህ በዓል የሚኾን ዳቦ ለመጋገር ስንዴያቸውን ሲያጥቡ፣ ሲፈትጉ ይሰነብታሉ፡፡ በበዓሉ ዋዜማ (ነሐሴ ፲፪ ቀን) ሕፃናት በየቤቱ እየዞሩ ‹‹ቡሄ ና በሉ፤ ቡሄ በሉ፡፡ ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ፡፡ …›› እያሉ ይጫወታሉ፡፡ ‹‹ቡሄ›› ያሉት ዳቦውን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ እያነሡ ይሰጧቸዋል፡፡

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል፡፡ «ቡሄ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ የሚበራው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ ልጆችም ዳቧቸውን እየገመጡ ጅራፍ ሲገርፉ ይውላሉ፡፡ የጅራፉ መጮኽ የድምፀ መለኮት፣ ጅራፉ ሲጮኽ ማስደንገጡ ነቢያትና ሐዋርያት በድምፀ መለኮት መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን ያስታውሳል፡፡

በተጨማሪም ለክርስትና ልጅ፣ ለአማች፣ ለምራት፣ ለዘመድ አዝማድ ኹሉ የቡሄ ዳቦ ይሰጣል፡፡

ደብረ ታቦር ወይም ቡሄ በአብነት ተማሪዎች ‹‹ስለ ደብረ ታቦር›› እያሉ እህል፣ ጌሾ ከምእመናን በመለመንና ገንዘብ በማዋጣት ጠላውን ጠምቀው፣ ዳቦውን ጋግረው፣ ቆሎውን ቆልተው ለደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱ የመጡትን ምእመናን በመጋበዝ በታላቅ ድምቀት ያከብራሉ፡፡

መምህረ ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ተማሪዎቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ በደብረ ታቦር ምሥጢር መግለጡን በማስታዎስ የአብነት ተማሪዎች ከመምህራቸው ጋር በመኾን በዓለ ደብረ ታቦርን (ቡሄን) ያከብራሉ፤ ስሙን ይጠራሉ፡፡ ይህም እስከ አሁን ድረስ በትምህርት ቤቶች የሚሠራበት ነባር ትውፊት ነው፡፡

ነገር ግን በአንድ አካባቢዎች በተለይ በከተማ ዙሪያ በዓለ ደብረ ታቦር (ቡሄ) ሃይማኖታዊ ትውፊቱን የለቀቀ ይመስላል፡፡ ለዚህም ልጆች የሚጫወቱበት መዝሙር ግጥሙና ዜማው ዓለማዊ መለእክት የሚበዛበት መኾኑ፤ በወቅቱ ችቦ ከማብራት ይልቅ ርችት መተኮሱና በየመጠጥ ቤቱ እየሰከሩ መጮኹ፤ ወዘተ. የበዓሉን መንፈሳዊ ትውፊት ከሚያደበዝዙ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከዚሁ ኹሉ ጋርም በዚህ በዓል ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ የሚሽቀዳደሙ ነገር ግን የበዓሉን ታሪካዊ አመጣጥ የማያዉቁ ልጆችም ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ስለዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው የበዓለ ደብረ ታቦርን መንፈሳዊነት፣ የመዝሙሮቹን ያሬዳዊነትና አከባበሩን ከቤተ ክርስቲያን መምህራን በመጠየቅ ማስተማር፤ ልጆችም ከወላጆች ወይም ከመምህራን በመጠየቅ የበዓሉን አከባበር መረዳትና የዚህን በዓል መንፈሳዊ ትውፊት ሳይበረዝ ለትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ ነው እንላለን፡፡

በመጨረሻም በቡሄ በዓል ‹‹ድምፅህን ሰማና በብሩህ ደመና፤ የቡሄው ብርሃን ለእኛ በራልን፤ …›› የሚለውንና ይህን የሚመስሉ መንፈሳውያን መዝሙራትን እየዘመሩ በየቤቱ በመዞር የሚያገኙትን ዳቦና ገንዘብ ለነዳያንና ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ ልጆችን ማበረታታትና አርአያነታቸውን መከተል ይኖርብናል መልእክታችን ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ ፳፻፭ ዓ.ም፣ ገጽ ፫፻፲፭-፫፻፲፯፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፤ ፳፻፯ ዓ.ም፣ ገጽ ፻፲፩፡፡

አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር

ደደ

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት የታቦር ተራራ

ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

‹‹አስተርእዮ›› ሥርወ ቃሉ ‹‹አስተርአየ (አርአየ) = አሳየ፣ ገለጠ፣ ታየ፣ ተገለጠ›› የሚለው የግእዝ ግስ ሲኾን ትርጕሙም ‹‹መታየት፣ መገለጥ፣ ማሳየት፣ መግለጥ›› ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/፡፡ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር›› የሚለው ሐረግም ‹‹የእግዚአብሔር በታቦር ተራራ መገለጥ›› ወይም መታየት የሚል ትርጕም ያለው ሲኾን ይህም ከእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ጋር የተያያዘ እንደዚሁም ከምሥጢረ ሥጋዌና ከነገረ ድኅነት ጋር የተሳሰረ ታላቅ ምሥጢርን የያዘ መገለጥ ነው፡፡

ከዚህ ላይ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር›› ስንል የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ማለታችን መኾኑን ለማስታዎስ እንወዳለን፡፡ ‹‹እግዚአብሔር›› የሚለው ቃል ሦስቱም አካላት (ቅድስት ሥላሴ) በጋራ የሚጠሩበት መለኮታዊ ስያሜ ነውና፡፡ ‹‹አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ በአሐዱ ስም ሥሉሰ ያምልኩ፤ እኔ ‹እግዚአብሔር› በአልሁ ጊዜ ስለ አብም፣ ስለ ወልድም፣ ስለ መንፈስ ቅዱስም እናገራለሁ፤ (ምእመናን) በአንዱ ስም (በእግዚአብሔር) ሦስቱ አካላትን ያመልኩ ዘንድ›› እንዳለ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት /ሃይማኖተ አበው/፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እግዚአብሔር አምላክ በብሉይም ኾነ በሐዲስ ኪዳን በአንድነቱ በሦስትነቱ በግብር (በሥራ)፣ በራእይና በገቢረ ተአምራት በልዩ ልዩ መንገድ ለፍጡራኑ ተገልጧል፡፡ በብሉይ ኪዳን ልዩ ልዩ ምልክት በማሳየት፤ በቅዱሳን ነቢያትና በመሣፍንት፣ በነገሥታት፣ በካህናትና በነቢያት ላይ በማደር ወይም በራእይ በማነጋገር፤ በተጨማሪም በጻድቃኑ ላይ ቸርነቱን በማሳየት፣ በክፉ አድራጊዎች ላይ ደግሞ መቅሠፍቱን በመላክ ሲያደርጋቸው በነበሩ ተአምራቱና ሥራዎቹ ይገለጥ ነበር፡፡

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ለአዳምና ለልጆቹ በገባው ቃል መሠረት የሰውን ሥጋ ለብሶ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በአካለ ሥጋ ተገልጦ በገቢረ ተአምራቱ፣ በትንሣኤውና በዕርገቱ አምላክነቱን አሳይቷል፡፡ የብሉይ ኪዳኑ መገለጥ በምልክት፣ በራእይ፣ በድምፅና በመሳሰሉት መንገዶች የተደረገ መገለጥ ነበር፤ የሐዲስ ኪዳኑ መገለጥ ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹መቼም ቢኾን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው›› /ዮሐ.፩፥፲፰/ ሲል እንደ ገለጸው አምላካችንን በዓይነ ሥጋ ያየንበት አስተርእዮ ስለኾነ ከመገለጦች ኹሉ የተለየ ጥልቅ ምሥጢር አለው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በሐዲስ ኪዳን በአካለ ሥጋ ያደረገውን መገለጥ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከምሥጢረ ሥላሴ ጋር በማያያዝ በሦስት መንገድ ይገልጹታል፡፡ ይኸውም በእመቤታችን፣ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ላይ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹በላዕሌኪ ወበዮርዳኖስ ወበታቦር ሥልሰ ጊዜያተ ዘአልቦ ተውሳከ ወአልቦ ሕጸተ ለውሉደ ሰብእ ያርኢ ዘሥላሴሁ ገጻተ ጽጌኪ ድንግል ተአምሪሁ ከሠተ ወበፀዳሉ አብርሀ ጽልመተ›› እንዳለ ደራሲ /ማኅሌተ ጽጌ/፡፡ ትርጕሙ እግዚአብሔር አምላክ ጭማሬም ጉድለትም የሌለበትን ሦስትነቱን ለሰው ልጅ ያሳይ ዘንድ በእመቤታችን፣ በዮርዳኖስ እና በታቦር ሦስት ጊዜ ተአምራቱን መግለጡን፤ በብርሃነ መለኮቱም ጨለማውን ብርሃን ማድረጉን የሚያስረዳ ሲኾን ይህም ጌታችን በለበሰው ሥጋ በእመቤታችን ማኅፀን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተወስኖ ሲወለድ፤ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ዕለት እግዚአብሔር አብ ‹‹የምወደው ልጄ እርሱ ነው፤ እርሱን ስሙት›› ብሎ  ሲመሰክርና መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ራሱ ላይ ሲያርፍ፣ እንደዚሁም በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ መለኮታዊ አንድነቱና አካላዊ ሦስትነቱ መታወቁን ያመለክታል፡፡

በዛሬው ዝግጅታችን ወደምንመለከተው ትምህርት ስንመለስ ‹‹ደብረ ታቦር›› ማለት ‹‹የታቦር ተራራ›› ማለት ነው፤ ‹‹ደብር›› በግእዝ ቋንቋ ‹‹ተራራ ማለት ሲኾን ‹‹ታቦር›› ደግሞ የቦታው ስም ነው፡፡ ይኸውም ከኢያቦር ወገን በሚኾን ቦር በሚባል ሰው ስም የተሰየመ ቦታ ነው፡፡ ‹‹ታቦር›› ማለት ‹‹ትልቅ›› ማለት ሲኾን ተራራውን በ ‹‹ቦር›› ላይ ‹‹ታ››ን ጨምረው ‹‹ታቦር›› ብለው እንደ ጠሩት ይነገራል፡፡ ታቦር በፍልስጥኤም ግዛት ከገሊላ ባሕር በስተምዕራብ ደቡባዊ ክፍል የሚገኝ፤ ዕፀዋቱ መልካም መዓዛ የሚያመነጩበት፤ ከ፭፸፪ ሜትር በላይ ከፍታ ያለው ግዙፍ ተራራ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ነቢዪቱ ዲቦራ ከባርቅ ጋር በመኾን የከነዓናውያንን ንጉሥ፣ የጦር መሪው ሲሳራንና ኢያቢስን ድል አድርገውበታል፡፡ ነቢዪቱም ከድል በኋላ መሥዋዕት አቅርባበታለች /መሣ.፬፥፭-፳፬/፡፡ እንደዚሁም ነቢዩ ሳሙኤል ትንቢት ተናግሮበታል፡፡ ንጉሥ ሳኦልም ከሦስት ሰዎች ጋር ተገኝቶበታል /፩ኛ ሳሙ.፲፥፫/፡፡ ርእሰ አበው አብርሃምና ኖኅ በዚህ ተራራ ላይ ቀስተ ደመና ተተክሎ አይተዋል፡፡ ስለዚህም ኖኅ ‹‹መካነ ብርሃን፤ የብርሃን ቦታ›› ብሎ ጠርቶታል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በተወለደ በ፴፪ ዓመት ከ፯ ወር ከ፲፭ ቀን፣ በዘመነ ማቴዎስ፣ በወርኃ ነሐሴ በዕለተ እሑድ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ገልጧል /መር አፈወርቅ ተክሌ እንደ ጠቀሱት/፡፡

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው ጌታችን ‹‹ከስድስት ቀን በኋላ›› ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደዚህ ተራራ (ደብረ ታቦር) ወጥቷል /ማቴ.፲፯፥፩/፡፡ ከዚህ ላይ ‹‹ከስድስት ቀን በኋላ›› የሚለው ሐረግ ጌታችን ሐዋርያቱን በቂሣርያ ‹‹ሰዎች ክርስቶስን ማን ይሉታል?›› ብሎ ከጠየቀበት ከነሐሴ ፯ ቀን በኋላ ያሉትን ቀናት ያመለክታል፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠው ከተስእሎተ ቂሣርያ በ፮ኛው ቀን (ነሐሴ ፲፫ ቀን) ነውና /፯+፮=፲፫/፡፡ ሙሴ ከመቃብር ኤልያስም ከብሔረ ሕያዋን በተገኙበት በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱ በተገለጠ ጊዜ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም አጣቢ ሊያነጣው እስከማይችል ድረስ እንደ በረዶ ነጭ ኾነ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ›› እያለ ሲናገር ክርስቶስ በሰው እጅ የተሠራ ቤት የማያስፈልገው አምላከ ሰማይ ወምድር መኾኑ ይገለጥ ዘንድ ሰማያዊ ብሩህ ደመና ጋረደቻው፤ ከሰማይም ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› የሚል ቃል ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ መጣ፡፡ ‹‹እርሱን ስሙት›› ማለቱም ጌታችን ዓለምን ለማዳን እንደሚሞት ሲናገር ቅዱስ ጴጥሮ ‹‹አይኹንብህ›› ብሎት ነበርና ‹‹እሞታለሁ›› ቢላችሁ ‹‹አትሞትም›› አትበሉት ሲል ነው፡፡ ሙሴና ኤልያስም ከጌታችን ጋር ሲነጋገሩ ተሰሙ፤ ስለ ክርስቶስ የተናገሩት ትንቢትም በደብረ ታቦር ተረጋገጠ፡፡ በዚህ ጊዜ የፊቱን ግርማ ለማየትና የመለኮትን ድምፅ ለመስማት አልተቻላቸውምና ሙሴ ወደ መቃብሩ፣ ኤልያስም ወደ መጣበት ተመለሱ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም የመለኮትን ፊት አይተው መቆም አልተቻላቸውምና ደንግጠው ወደቁ፡፡

በብሉይ ኪዳን ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ቆይቶ ወደ ሕዝቡ ሲሔድ ፊቱ ያንጸባርቅ እንደ ነበርና የእስራኤላውያን ዓይን እንዳይጎዳ ሙሴ ፊቱን ይሸፍን እንደ ነበር ተጽፏል፡፡ ሙሴ የእግዚአብሔርን ድምፅ በመስማቱ ብቻ ፊቱ ያንጸባርቅ ከነበረ እግዚአብሔርንፊት ለፊት በዓይን ተመልክቶ ብርሃኑን መቋቋም ምን ያህል ከባድ ይኾን?

ከዚህ በኋላ ሐዋርያት ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው የኾነው ክርስቶስ ሙሴን ከመቃብር አንሥቶ፤ ኤልያስንም ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ በደብረ ታቦር እንዳወጣቸው ዐወቁ፡፡ ጌታችንም ሐዋርያቱን አጽናንቶ ኃይሉን ብርታቱን ካሳደረባቸው በኋላ ከንቱ ውዳሴን የማይሻ አምላክ ነውና፤ ደግሞም መናፍቃን ምትሐት ነው ብለው እንዲሰናከሉበት አይፈልግምና ኹሉም በጊዜው እስኪለጥ ማለትም ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የክርስቶስን አምላክነቱን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን፣ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን ለዓለም እስኪሰብኩ ድረስ በደብረ ታቦር ያዩትንና የሰሙትን ለማንም እንዳይነግሩ አዝዟቸዋል /ማቴ.፲፯፥፩-፱፤ ማር.፱፥፪-፱/፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በዘመነ ኦሪት ከሙሴ ጋር ቃል በቃል በደመና በሚነጋገርበት ጊዜ ነቢዩ ሙሴ ‹‹… ጌትነትህን (ባሕርይህን) ግለጽልኝ›› ሲል እግዚአብሔርን ተማጽኖት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ለሙሴ ‹‹በባሕርዬ ፊቴን አይቶ የሚድን የለምና ፊቴን ማየት አይቻልህም፡፡ … እኔ በምገለጽልህ ቦታ ዋሻ አለና በብርሃን ሠረገላ ኾኜ እስካልፍ ድረስ በዋሻው ውስጥ ቁመህ ታየኛለህ፡፡ በባሕርዬ አይተህ ደንግጠህ እንዳትሞት በብርሃን ሠረገላ ኾኜ እስካልፍ ድረስ ቀዳዳ ባለው ዋሻ እሠውርሃለሁ፡፡ በብርሃን ሠረገላ ኾኜ ካለፍሁ በኋላ እጄን አንሥቼልህ ከወደ ኋላዬ ታየኛለህ እንጂ በባሕርዬ ግን ፊቴን ማየት አይቻልህም›› የሚል ምላሽ ሰጥቶት ነበር /ዘፀ.፴፫፥፲፫-፳፫/፡፡ ይህም በፊት የሚሔድ ሰው ኋላው እንጂ ፊቱ እንደማይታይ ጌታም በባሕርዩ አለመገለጡን ያስረዳል፡፡ ምሥጢሩም አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በደብረ ታቦር በባሕርዩ እስኪገለጥለት ድረስ ሙሴ በመቃብር ተወስኖ እንደሚቆይ ያጠይቃል /ትርጓሜ ኦሪት ዘፀአት/፡፡

በብሉይ ኪዳን ባሕርዩን ለሙሴ የሠወረ አምላክ በደብረ ታቦር በመለኮታዊ ባሕርዩ ተገልጧል፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረው የመገለጥ ተስፋ ተፈጽሞ ይኸው አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር ኾኗል፡፡ ‹‹ጀርባዬን ታያለህ›› ያለ እርሱ ለሙሴ በደብረ ታቦር በክበበ ትስብእት ታይቷል፡፡ ነቢዩ ሙሴ እንደ ተመኘው በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን በተመለከተ ጊዜም ‹‹ፊቴን ማየት አይቻልህም›› ያለው ቃሉ ይፈጸም ዘንድ የክርስቶስን ፊት ማየት ስላቃተው ‹‹ትኄይሰኒ መቃብርየ፤ መቃብሬ ትሻለኛለች›› ብሎ ወደ መቃብሩ ተመልሷል፡፡ ‹‹ሞትን አይቀምስም›› የተባለለት፣ ክርስቶስ ለፍርድ ከመምጣቱ አስቀድሞ ወንጌልን የሚሰብከው ኤልያስ ብርሃነ መለኮቱን በግልጥ ለመመልከት ችሏል፡፡ መለኮቱን አይቶ መቆም አልቻለው ቢልም ወደ ብሔረ ሕያዋን ተመልሷል፡፡ የክርስቶስን መሞት በሥጋዊ ስሜት ተረድቶ ‹‹አይሁንብህ›› ያለው ቅዱስ ጴጥሮስና መለኮታዊ ሥልጣንን የተመኙት ቅዱሳን ያዕቆብና ዮሐንስ አብሯቸው እየኖረ የማያውቁት ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መኾኑን ተረድተዋል፡፡ ተረድተውም ደንግጠው ወድቀዋል፡፡

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በተራራ የገለጠበት ምሥጢር

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በመንደር ሳይኾን በተራራ ያደረገው ስለምን ነው ቢሉ ተራራ የወንጌል ምሳሌ ነው፡፡ ተራራ ሲወጡት ያስቸግራል፤ ከወጡት በኋላ ግን ጭንጫውን፣ ግጫውን ሲያሳይ ደስ ያሰኛል፡፡ ወንጌልም ሲማሯት ታስቸግራለች፤ ጽድቅና ኀጢአትን ለይታ ስታሳውቅ ግን ደስ ታሰኛለችና በተራራ ትመሰላለች፡፡ ደግሞም ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፤ ተራራን በብዙ ፃዕር እንዲወጡት መንግሥተ ሰማይንም በብዙ መከራ ያገኟታልና፡፡ ‹‹እስመ በብዙኅ ፃማ ሀለወነ ንባኣ ለመንግሥተ እግዚአብሔር፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ አለን›› እንዲል /ሐዋ.፲፬፥፳፩-፳፪/፡፡

ትርጓሜ ወንጌል እንደሚያስረዳው ጌታችን መለኮቱን የገለጠበት ተራራ ታቦር መኾኑን ሐዋርያት በሲኖዶስ ጠቅሰውታል፡፡ ምሥጢሩን በሌላ ተራራ ሳይገልጥ ስለምን በደብረ ታቦር ገለጠ ቢሉ ትንቢቱ፣ ምሳሌው እንዲፈጸም ነው፡፡ ትንቢቱ፡- ‹‹ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ፤ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል›› የሚል ነው /መዝ.፹፰፥፲፪/፡፡ ይኸውም ጌታችን በደብረ ታቦር ባደረገው መገለጥ ተራሮች እንደ ሰው መደሰታቸውን፤ አንድም ልባቸው እንደ ተራራ በኑፋቄ የገዘፈ አይሁድና አሕዛብ ወይም መናፍቃን በተአምራቱ መማረካቸውን ያጠይቃል፡፡ ምሳሌው፡- በታቦር ተራራ ባርቅ ሲሳራን ድል ነስቶበታል /መሣ.፬፥፲፬-፲፮/፤ ጌታችንም በልበ ሐዋርያት (በልበ ምእመናን) ያደረ ሰይጣንን ድል የሚነሳበት ነውና ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር ገልጧል፡፡ አንድም ደብረ ታቦር የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናት፤ በደብረ ታቦር ነቢያትም ሐዋርያትም እንደ ተገኙ መንግሥተ ሰማያትንም በአንድነት ይወርሷታልና፡፡

ስለ ምን ከነቢያት ሁለቱን፣ ከሐዋርያት ሦስቱን ብቻ ወደ ተራራ ይዞ ወጣ?

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከነቢያት ሁለቱን፣ ከሐዋርያት ሦስቱን ብቻ ይዞ ወደ ደብረ ታቦር ይዞ የወጣበት ምሥጢር አንደኛ በብሉይ ኪዳን ሙሴ ‹‹ፊትህን አሳየኝ›› ብሎት ነበርና መለኮቱን ለሙሴ ለመግለጥ /ዘፀ.፴፫፥፲፫-፳፫/፤ ሁለተኛ ‹‹የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ›› ሲል የተናገረለት ኤልያስ በሕይወተ ሥጋ መኖሩን ለማሳየት /ማቴ.፲፮፥፳፰/፤ ደግሞም ኤልያስን ‹‹አንተሰ ስምዓ ትከውነኒ በደኃሪ መዋዕል፤ በኋለኛው ዘመን ምስክር ትኾነኛለህ›› /ሚል.፬፥፭/ ብሎት ነበርና የኤልያስን ምስክርነት ለማረጋገጥ፤ ሦስተኛ ጌታችን እንደሚሞት ሲናገር ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹አይኹንብህ›› ብሎት ነበርና ‹‹እርሱን ስሙት›› የሚለውን የእግዚአብሔርን አብ ምስክርነት ለማሰማት /ማቴ.፲፮፥፳፪፣ ፲፯፥፭/፤ አራተኛ አይሁድ ክርስቶስን ‹‹ከነቢያት አንዱ ነው›› /ማቴ.፲፮፥፲፬/ ይሉት ነበርና የነቢያት ጌታ መኾኑን ለማጠየቅ ነው፡፡

ከመዓስባን ሙሴን፣ ከደናግል ደግሞ ኤልያስን ማምጣቱም ደናግልም መዓስባንም መንግሥተ ሰማያትን በአንድነት እንደሚወርሱ ያጠይቃል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው›› ሲል መናገሩም ጌታችን በተአምራቱ ሲራቡ እያበላቸው፣ ሲጠሙ እያጠጣቸው፣ ሲታመሙ እየፈወሳቸው፣ ቢሞቱ እያነሣቸው፤ ሙሴም እንደ ቀድሞው ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላትን እየገደለ፤ ኤልያስ ደግሞ ሰማይን እየለጎመ፣ እሳት እያዘነመ፣ ዝናም እያቆመ በደብረ ታቦር ለመኖር መሻቱን ያመላክታል፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሦስት ጎጆ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፤ አንዱን ለሙሴ፤ አንዱን ለኤልያስ›› በማለት የእርሱንና የሁለቱን ጎጆ ሳይጠቅስ አርቆ መናገሩ በአንድ በኩል ትሕትናውን ማለትም ‹‹ለእኛ›› ሳይል ነቢያቱን አስቀድሞ ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን አለመጥቀሱን፤ እንደዚሁም ከጌታችን ጋር ለመኖር ያለውን ተስፋ ሲያመለክት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቅዱስ ጴጥሮስን ድክመት ማለትም የክርስቶስን አምላክነት በሚገባ አለመረዳቱን ያሳያል፡፡ ጌታችንን በተራራ ላይ በሰው ሠራሽ ቤት ይኖር ዘንድ ጠይቆታልና፡፡

ጌታችን ስምንቱን ከተራራው ሥር ትቶ (ይሁዳ ሳይቈጠር) ሦስቱን ሐዋርያት ወደ ተራራ ይዞ የወጣበት ምክንያት በአንድ በኩል ያዕቆብና ዮሐንስ ‹‹በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ፣ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን›› /ማር.፲፥፴፯/ ሲሉ መንግሥቱን ፈልገው ነበርና የልባቸውን መሻት ለመፈጸም ሲኾን በሌላ ምሥጢር ደግሞ ይሁዳን ወደ ተራራው ይዞ ለመውጣት ባለመሻቱ፤ ለይቶ እንዳይተወውም ‹‹ከምሥጢረ መንግሥቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት›› እንዳይለው (ምክንያት ለማሳጣት) ነው፡፡ ‹‹ያእትትዎ ለኀጥእ ከመ ኢይርአይ ስብሐተ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔርን ምስጋና (ክብር) እንዳያይ ኀጢአተኛውን ሰው አያስቀርቡት›› ተብሎ ትንቢት ተነግሮበታልና ይሁዳ የእግዚአብሔርን ክብር ለማየት አልበቃም፡፡ ኾኖም ግን በደብረ ታቦር የተገለጠው ምሥጢር ከተራራው በታች ለነበሩት ለስምንቱ ደቀ መዛሙርትም ተገልጦላቸዋል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ በደብረ ታቦር ጌታችን በዮርዳኖስ ሲጠመቅ የተገለጠው ምሥጢረ ሥላሴና የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ገሃድ ኾኗል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ የኾነችው ደብረ ታቦር ምሥጢረ ሥላሴ ተገልጦባታል፤ የክርስቶስ አምላክነት ተረጋግጦባታል፡፡ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱ እንደ ተገለጠና የእግዚአብሔር አብ ምስክርነት እንደ ተሰማ ኹሉ ዛሬም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ሥላሴ ሲነገር፣ የመለኮት ሥጋና ደም ሲታደል ይኖራል፡፡ በደብረ ታቦር ነቢያትም፣ ሐዋርያትም እንደ ተገኙ ኹሉ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ብሉይና ሐዲስ ኪዳን ይሰበካል፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴ የሚፈጽሙ ልዑካን አምስት መኾናቸውም በደብረ ታቦር የተገኙትን ሙሴን፣ ኤልያስን፣ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ያስታውሱናል፡፡ ዘወትር በቤተ መቅደሱ የሚፈተተው ኅብስትና የሚቀዳው ወይን ደግሞ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን የገለጠው የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡

ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በዓላት መካከል አንደኛው የኾነው በዓለ ደብረ ታቦር ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበትና ታላቅ የአስተርእዮ ምሥጢር የተፈጸመበት በዓል በመኾኑ ይህንን የመሥራቿን የክርስቶስን በዓል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን ‹‹አማን በአማን ተሰብሐ በደብረ ታቦር›› እያለች በድምቀት ታከብረዋለች፡፡ የአብነት ት/ቤት ደቀ መዛሙርት፣ በሰንበት ት/ቤትና በማኅበራት የሚያገለግሉ ምእመናንም ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠ አምላክ ብርሃነ ምሥጢሩን በየልቡናቸው እንዲገልጥላቸው ለመማጸን ጸበል ጸሪቅ አዘጋጅተው በዓሉን ይዘክሩታል፡፡ በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ከሙታን ተነሥቶ ከዘመናት በፊት የተመኘውን የአምላኩን ፊት ለማየት የታደለው ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተወለደውም በዚህች ዕለት ነው፡፡ እኛም እግዚአብሔር በደብረ ታቦር ያደረገውን አስተርእዮ ለማስታዎስ ይህንን ጽሑፍ አዘጋጀን፡፡

ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠ ጌታ በእያንዳንዳችን ልቡናም ማስተዋሉን፣ ምሥጢሩን፣ ጥበቡን ይሳልብን፤ ያሳድርብን፡፡ ከቅዱሳኑ ጋር መንግሥቱን እንዲያወርሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ነሐሴ ፲፫ ቀን፡፡

መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ በመ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ ገጽ ፫፻፲፬-፫፻፲፯ እና ፬፻፩፡፡

ትርጓሜ ወንጌለ ማቴዎስ፣ ምዕ.፲፯፥፩-፱፡፡

የአብነት ትምህርት ቤቶች ችግር አሳሳቢ መኾኑ ተገለጠ

ነሐሴ ፲፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በይብረሁ ይጥና

ኹሉም ሕዝበ ክርስቲያን የድርሻውን ተወጥቶ የአብነት ትምህርት ቤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ ካልተቻለ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማስቀጠል አሳሳቢ መኾኑ ተገለጠ፡፡

በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት የሚገኙ የአብነት ት/ቤቶችን ጉዳይ በሚመለከት ሐምሌ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በዮድ አቢሲኒያ የምግብ አዳራሽ በተካሔደው ውይይት የአብነት ትምህርት ቤቶች ችግር ካልተቀረፈ ወደፊት የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው ተብሏል፡፡

በዕለቱ የሰሜንና ደቡብ ጎንደር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ እና የምዕራብና ደቡብ ምዕራብ አውሮፓ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ የአብነት ትምህርት ቤቶችን መከባከብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ማስቀጠል መኾኑን በማስረዳት በመላው ዓለም የሚኖሩ ምእመናን በአንድነት ኾነው ለአብነት ት/ቤቶች መጠናከር የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

Gubae

በመርሐ ግብሩ ላይ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ኹኔታ የሚዳስስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶ/ር አበባው ምናዬ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ምንነትና ያሉባቸውን የምግብ፣ የቁሳቁስና የአልባሳት እጥረት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ችግሮች በመጥቀስ ችግሮቹ በዚህ ከቀጠሉ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እንደሚያደናቅፉ በጥናታቸው ጠቁመው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብራትን ማዘጋጀትና የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን ማከናወን ከችግሮቹ መፍትሔዎች መካከል የሚጠቀሱ ተግባራት መኾናቸውን አመላክተዋል፡፡

የጥናቱ አወያይ ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ በበኩላቸው ‹‹ቤተ ክርስቲያን የምትጠበቀው ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ቀጣይነት ሲኖራቸው ነው፡፡ እስካሁን የት ነበርን ብሎ ወደ ኋላ ከማሰብ ይልቅ ዛሬም ጊዜው ገና ነውና በመላው የአገራችን ክፍሎች ለሚገኙ የአብነት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የኾነ ሥራ በመሥራት ዘለቄታዊ መፍትሔ ማምጣት ይኖርብናል›› ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የአብነት ትምህርት ቤቶች የሚረዱበትን ኹኔታ የሚያመቻች ሰባት አባላት የተካተቱበት ዐቢይ ኰሚቴ ከተዋቀረ በኋላ የውይይት መርሐ ግብሩ በበብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ጸሎት ተፈጽሟል፡፡

ትምህርት ቤቱ በ፳፻፱ ዓ.ም ሥራ እንደሚጀምር ተገለጠ

ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በይብረሁ ይጥና

በምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ነቀምቴ ከተማ በምስካበ ቅዱሳን ዑራኤል ወሳሙኤል ገዳም ሀገረ ስብከቱና ማኅበረ ቅዱሳን በጋራ ያስገነቡት ትምህርት ቤት በ፳፻፱ ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሥራ እንደሚጀምር ተገለጠ፡፡

school

ሀገረ ስብከቱ ዘመናዊ ት/ቤት ሲገነባ የመጀመሪያው መኾኑን የጠቀሱት የምሥራቅና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ስምዖን ‹‹መረዳዳቱ፣ አንድነቱና መፈቃቀሩ ካለ ከዚህ የበለጠ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ ሌሎችንም የልማት ሥራዎችን መሥራት ይቻላል!›› ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በኵረ ትጉሃን ቀሲስ ገናናው አክሊሉ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በ፳፻፰ ዓ.ም ለመገንባት ዕቅድ ከያዘላቸው ፕሮጀክቶች መካከል ይህ የፈለገ ጥበብ መዋዕለ ሕፃናት ት/ቤት ፕሮጀክት አንዱ መኾኑን የገለጡት በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ዳይሬክተር ዲ/ን አእምሮ ይኄይስ የፕሮጀክቱ ግብ በሥነ ምግባር የበለጸገ የሰው ኃይል ማፍራትና ከት/ቤቱ በሚገኘው ገቢም የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

በድምሩ ፻፳ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችለው ትምህርት ቤቱ የመማሪያ፤ ለመምህራን ቢሮና ለሕፃናት ማረፊያ አገልግሎት የሚሰጡ ስድስት ክፍሎች፤ መጸዳጃ ቤትና የንጹሕ ውኃ ቧንቧዎች እንደ ተዘጋጁለት፤ ት/ቤቱን ለማስገንባትም ከአንድ ሚሊዮን ሰባ አምስት ሺሕ ብር በላይ ወጪ እንደ ተደረገና ከዚህ ውስጥ ከስምንት መቶ ሺሕ ብር በላይ የሚኾነው ወጪ በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል፤ ቀሪው ደግሞ በሀገረ ስብከቱ እንደ ተሸፈነ በምረቃው ዕለት ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዕለቱ ካነጋገርናቸው አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ላእከ ምእመናን ሽፈራው በቀለና ወ/ሮ መሠረት ታደሰ ቤተ ክርስቲያን የልማት ምሳሌና አርአያ መኾኗን ጠቅሰው ትምህርት ቤቱ በአካባቢያቸው መገንባቱ ልጆቻቸው በሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉና ለአገራቸው ጥሩ ዜጋ እንዲኾኑ በማስቻል ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ዐርባ ምንጭ ማእከል ተተኪ ሰባክያንን አስመረቀ

ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዐርባ ምንጭ ማእከል

DSC06070

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የዐርባ ምንጭ ማእከል ከጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት፣ ከኮንሶ ወረዳ ቤተ ክህነትና ከወረዳ ማእከሉ ጋር በመተባበር ለ፴ ቀናት ያሠለጠናቸውን፤ በአካባቢው ቋንቋዎች ወንጌልን ማስተማር የሚችሉ ከኮንሶ እና ከደራ ማሎ ወረዳዎች የተውጣጡ ፴፫ ተተኪ ሰባክያንን ሲቀላ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ደብር ቅፅር በሚገኘው የማኅበሩ ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ነሐሴ ፯ ቀን ፳፻፰ አስመርቋል፡፡

በምረቃ ሥርዓቱ ላይም የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከትና የኮንሶ ወረዳ ቤተ ክህነት ተወካዮች፣ የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል እና የደብረ መንክራት ቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ኃይለ ጊዮርጊስ ማሕጸንተ፣ ድጋፍ አድራጊ ምእመናንና የማእከሉ አባላት ተገኝተዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ተወካይ መምህር ዮሐንስ አሻግሬ ‹‹ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን በመላው ዓለም ዞረው ወንጌልን እንዲያስተምሩ እንደላካቸው ኹሉ፤ እናንተም በየአካባቢው ቋንቋ ወንጌልን በማስተማር አሕዛብን ከምእመናን ማኅበር እንድትጨምሯቸው አደራችንን እናስተላልፋለን›› ብለዋል፡፡

‹‹ምሩቃኑ ለስብከተ ወንጌል በምተሰማሩባቸው አካባቢዎች ኹሉ በሰበካ ጉባኤያት፣ በወረዳ ማእከላትና በሰ/ት/ቤቶች በአባልነት በመሳተፍ፣ ከካህናትና ከምእመናን ጋር በመግባባት ማገልገል ይጠበቅባችኋል›› ያሉት የማእከሉ ሰብሳቢ አቶ ደመላሽ ወንድማገኘሁ በበኩላቸው ለሰባክያኑ አገልግሎት ውጤታማነትም የሀገረ ስብከቱ፣ የወረዳ ቤተ ክህነቶችና የየአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያት ክትትልና ድጋፍ እንዳይለያቸው አባቶችን አሳስበዋል፡፡

ሰብሳቢው አያይዘውም የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከትን፣ የኮንሶ ወረዳ ቤተ ክህነትን፣ የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤትንና በጎ አድራጊ ምእመናንን ለሥልጠናው መሳካት ላበረከቱት አስተዋጽዖ በማእከሉ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የማእከሉ ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ሓላፊ አቶ እያያ ፍቃዴ በበኩላቸው ለሠልጣኞቹ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሐዋርያዊ ተልእኮ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ነገረ ማርያም፣ ነገረ ቅዱሳን፣ ነገረ ሃይማኖት እና የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና ከመሰጠቱ ባሻገር በተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ዙሪያም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንዲያገኙ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ልዩ ልዩ የትምህርተ ሃይማኖት መጻሕፍት ለምሩቃኑ ከተበረከቱ በኋላ በአባቶች ጸሎት የምረቃ ሥርዓቱ ተፈጽሟል፡፡

የዐርባ ምንጭ ማእከል በ፳፻፯ ዓ.ም በተመሳሳይ አርእስት ፳፮ ተተኪ ሰባክያንን አሠልጥኖ ለአገልግሎት እንዲሰማሩ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

የሊቀ ማእምራን ወመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝ አጭር የሕይወት ታሪክ

003

ነሐሴ ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

 

በኢሳይያስ ቦጋለ

የተወደዳችሁ የዝግጅታችን ተከታታዮች! የሊቀ ማእምራን ወመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝን ዜና ዕረፍት ባስነበብንበት ዕለት ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በገባነው ቃል መሠረት የሊቁን ሙሉ የሕይወት ታሪክ በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

ሊቀ ማእምራን ወመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝ ከአባታቸው ከአቶ ባይነሳኝ ላቀውና ከእናታቸው ከወ/ሮ በፍታ ተሾመ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በላስታ /ሙያጃ ወረዳ ልዩ ስሙ ዐሥራ ሁለት ተኹላ ደብረ ዘመዶ መዝገብ ዓምባ ማርያም በተባለው አካባቢ ሐምሌ ፳፩ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የመዝገብ ዓምባ ማርያም የቅዳሴ መምህር ከነበሩት ባሕታዊ አባ ኃይለ ማርያም ከፊደል ጀምሮ ንባብ፣ ሰዓታት፣ ቅዳሴ ከተማሩ በኋላ በ፲፱፻፵፪ ዓ.ም የወሎ ክፍለ ሀገር ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል ቀዳማዊ መዓርገ ዲቁና ተቀብለው በመዝገብ ዓምባ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ዓመት በላይ በዲቁና አገልግለዋል፡፡

ከዚያም ትምህርታቸውን በመቀጠል በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ወፍጫት መድኀኔ ዓለም ከመምህር መኰንን ሊበን እና ቀጋዎች ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከመምህር በጽሐ ቅኔ ከነአገባቡ ጠንቅቀው በመማር አስመስክረዋል፡፡ የቅኔ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በመቄት ወረዳ ገረገራ ጊዮርጊስ ከድጓው መምህሩ መ/ር አበባው አዳነ ድጓና ፀዋትወ ዜማ፤ ዱዳ ኪዳነ ምሕረት ከየኔታ ጌራ ወርቅ አቋቋም፤ በግምጃ ቤት መካነ ነገሥት ማርያም ከመምህር ክፍሌ ይመር የሐዲሳትን እና የሊቃውንትን ትርጓሜ ጠንቅቀው በመማር አስመስክረዋል፡፡

መጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት በመጋቤ ሐዲስ ክፍሌ ይመር፣ በንጉሡና በባለሥልጣናቱ ተመርጠው በወር ፶ ብር እየተከፈላቸው በግምጃ ቤት መካነ ነገሥት የሐዲሳት ትርጓሜ ቤት ከ፲፱፻፷፭-፲፱፻፸ ዓ.ም ድረስ ምክትል መምህር ኾነው ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በወቅቱ የጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ቀዳማዊ ትእዛዝ አሁን ‹‹ሐዋርያው ጳውሎስ የሕፃናት መርጃ ማእከል›› በመባል በሚታወቀው ጉባኤ ቤት ከሚያዝያ ወር ፲፱፻፸ ዓ.ም ጀምሮ የሐዲሳት ትርጓሜ መምህር ኾነው ለአንድ ዓመት ያህል አስተምረዋል፡፡

ሊቀ ማእምራን ወልደ ሰንበት መጋቤ ሐዲስ ክፍሌ ይመር ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩም ‹‹መጋቤ ሐዲስ›› በሚል መዓርግ የጎንደር ግምጃ ቤት መካነ ነገሥት ማርያም የመጻሕፍት ትርጓሜ ምስክር ጉባኤ ቤት የትርጓሜ መጻሕፍት መምህር ኾነው ተመድበዋል፡፡ በመምህርነት ከተመደቡበት ከ፲፱፻፸ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ትርጓሜ መጻሕፍትን በማስተማር በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር በልሉ ልዩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ የሚገኙ በርካታ የቤተ ክርስቲያን መምህራንን አፍርተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ብፁዕ አቡነ ያሬድ እና ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ይጠቀሳሉ፡፡

መጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት በ፲፱፻፹፭ ዓ.ም ለጉባኤ ወደ አዲስ አበባ በሔዱበት ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ‹‹እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ በተሻለ ደመወዝ እንመድብዎ›› የሚል ጥያቄ አቅርበውላቸው እንደ ነበርና እርሳቸው ግን ‹‹መካነ ነገሥት ጉባኤ ቤትን እንዳለቅ አደራ አለብኝ›› በማለት ወደ በዓታቸው እንደ ተመለሱ በወቅቱ የነበሩ አባቶች ይናገራሉ፡፡

ሊቀ ማእምራን በቃል ካስተማሩት ትምህርተ ወንጌል ባሻገር የማኅሌተ ጽጌን ዚቅ፤ የሊቃውንት አባቶችን ታሪክ፣ እንደዚሁም የመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ አዘጋጅተው በማሳተም ለንባብ ያበቁ ሲኾን ‹‹የአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን (ፍሬምናጦስ) እና የአብርሃ ወአጽብሃ ነገሥታት ታሪክ›› ደግሞ ያልታተሙ መጻሕፍቶቻቸው ናቸው፡፡

መጋቤ ሐዲስ ከመምህርነት ሙያቸው በተጨማሪ በብፁዕ አቡነ እንድርያስ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አማካይነት ‹‹ሊቀ ማእምራን›› በሚል መዓርግ ተሰይመው የመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት ኾነው ተሹመው ከ፲፱፻፺፯ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስ ካህናቱንና ሕዝበ ክርስቲያኑን በቅንነት፣ በትሕትና እና በአባታዊ ሥነ ምግባር ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ከዚሁ ኹሉ ጋርም ወጣቶችን በቤተ ክርስቲያን እየሰበሰቡ በማስተማርና መምህራንን በመመደብ በየቦታው የሰንበት ት/ቤት አገልግሎት እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡

በአጠቃላይ ሊቀ ማእምራን ወመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝ በጠባይዓቸው ዝምተኛ፣ ትዕግሥተኛና ባሕታዊ፤ ከቃለ እግዚአብሔር በስተቀር ሌላ ክፉ ቃል ከአንደበታቸው የማይወጣ፤ ከተማሪነታቸው ጀምሮ እስከ መምህርነታው ድረስ ከማንም ጋር ተቀያይመው የማያውቁና ከቂም በቀል የራቁ፤ ቀንም ሌሊትም ለአገር ሰላም፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገትና ለምእመናን አንድነት የሚጸልዩ፤ ከዓለማዊ ኑሮና ከውዳሴ ከንቱ የተለዩ፤ ከዚሁ ኹሉ ጋርም እንግዶችን መቀበል የሚወዱ፤ ከደመወዛቸውና ከዕለት ጕርሳቸው ቀንሰው ለተቸገሩ የሚሰጡ ርኅሩኅ፣ ደግና ታላቅ አባት ነበሩ፡፡

በመጨረሻም እኒህ ታላቅ ሊቅ ባደረባቸው ሥጋዊ ሕመም በልዩ ልዩ የሕክምና ተቋማት ሲረዱ ቆይተው ሊሻላቸው ባለመቻሉ በጉባኤ ቤታቸው እንዳሉ ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በተወለዱ በ፹ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ የሀገረ ስብከቱና የየወረዳ ቤተ ክህነት ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ ባልንጀሮቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ደቀ መዛርታቸውና የመንፈስ ልጆቻቸው፣ ማኅበረ ካህናትና በርካታ ምእመናን በተገኙበት በተማሩባትና ወንበር ተክለው፣ ጉባኤ ዘርግተው ትርጓሜ መሕፍትን በማስተማር በርካታ ሊቃውንትን ባፈሩባት በግምጃ ቤት መካነ ነገሥት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ተፈጽሟል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የእኒህን አባት በረከት በኹላችንም ያሳድርብን፤ እንደ እርሳቸው ያሉ ሊቃውንትንም አያሳጣን እያልን ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመንፈስ ልጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር::