የአዳማ ማእከል ለአባቶች የዓቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሰጠ

ነሐሴ ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በአዳማ ማእከል

Adama

አባቶች በሥልጠና ላይ

በማኅበረ ቅዱሳን አዳማ ማእከል ከምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ ከሙያ አገልግሎትና ዓቅም ማጐልበቻ ዋና ክፍል ጋር በመተባበር ለሀገረ ስብከቱ የየመምሪያ ሓላፊዎች፣ ለወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች፣ ለገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች በአጠቃላይ ፵ ለሚኾኑ አባቶች ከነሐሴ ፳፩-፳፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለሁለት ቀናት በሀገረ ስብከቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የዓቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ሰጠ፡፡

በሥልጠናውም የሥራ አመራር ጥበብ፤ የውሳኔ አሰጣጥና የግጭት አፈታት ዘዴ፤ ሕግጋተ ቤተ ክርስቲያንና ቃለ ዓዋዲ ከሥራ አመራር አንጻር፤ እንደዚሁም የፋይናንስ አስተዳደርና ሒሳብ አያያዝ የሚሉ አርእስት የተካተቱ ሲኾን በተጨማሪም የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን የተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ለሠልጣኞቹ ተደርጎላቸዋል፡፡

በሥልጠናው ማጠናቀቂያ መርሐ ግብር ላይ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ ቸርነት ሥልጠናው ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች መሰጠቱን አድንቀው ሥልጠናውን ያዘጋጀውን ማኅበረ ቅዱሳንን ካመሰገኑ በኋላ ‹‹ያገኛችሁትን ዕውቀት በተግባር ላይ በማዋል ብቁና ዘመናዊ አሠራርን የተላበሰ የሓላፊነት ሥራችሁን እንድትወጡ›› ሲሉ ለሠልጣኞቹ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ‹‹የወሰድነው ሥልጠና መንፈሳዊውን አስተዳደር ከዘመናዊ የሥራ አመራር ጥበብ ጋር በማጣጣም ቤተ ክርስቲያናችንን በአግባቡ ማገልገል እንደምንችል የተረዳንበት ሥልጠና ነው፡፡ በተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ዙሪያ የተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻም ቤተ ክርስቲያናችንን ነቅተን እንድንጠብቅና የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን በስፋት ለማዳረስ እንድንፋጠን አድርጎናል›› ብለዋል፡፡

የአዳማ ማእከል ሰብሳቢ መ/ር ጌትነት ዐሥራት ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ዕድገት በአንድነት ማገልገል የሚኖረውን ጠቀሜታ በመጥቀስ ማኅበሩ የራሳቸው መኾኑን ተገንዝበው በሚያስፈልገው ኹሉ ከማኅበሩ ጎን እንዲቆሙ፤ በምክርና በዐሳብም ድጋፍ እንዲያደርጉ አባቶችን አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም ለሥልጠናው መሳካት አስተዋጽዖና ድጋፍ ላደረጉት ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፤ ለሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ትፍሥሕት ሙሉጌታ ቸርነትና የየመምሪያ ሓላፊዎች፤ ለወረዳ ቤተ ክህነት፣ ለአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፤ እንደዚሁም ለአሠልጣኞችና ለበጎ አድራጊ ምእመናን መ/ር ጌትነት መንፈሳዊ ምስጋናቸውን በማኅበሩ ስም አቅርበዋል፡፡

ዐውደ ርእዩን በርካታ ምእመናን ጐበኙት

ነሐሴ ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በአሜሪካ ማእከል

Mini 3

ዐውደ ርእዩ በአባቶች ቡራኬ ሲከፈት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን በሚኒያ ፖሊስ ንዑስ ማእከል አዘጋጅነት ‹‹ማዕዶት ዘቤተ ጉባኤ ወገዳማት›› በሚል መሪ ቃል ከነሐሴ ፯-፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በሚኒያ ፖሊስ  ርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቅፅር ውስጥ የተካሔደውን ዐውደ ርእይ በርካታ ምእመናን እንደ ጐበኙት የሚኒያ ፖሊስ ንዑስ ማእከል አስታወቀ።

በዐውደ ርእዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የገዳማት ታሪክ፣ የአብነት ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርትና ችግሮቶች፣ የደቀ መዛሙርቱ የኑሮ ኹኔታ፣ ማኅበሩ በገዳማትና በአብነት ት/ቤቶች ላይ እየሰጠው ያለው አገልግሎትና የተመዘገቡ ውጤቶች፣ እንደዚሁም ወደፊት ምእመናን ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የሚያስገነዝቡ ነጥቦች በ፰ ክፍላተ ትዕይንት ተከፋፍለው ቀርበውበታል፡፡

ዐውደ ርእዩ በሚኒያ ፖሊስ ርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራልና የሴንት ፖል ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች መልአከ አርያም ቆሞስ አባ ኃይለ ሚካኤል ሙላት እና መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ዘርዐ ዳዊት ብርሃኔን ጨምሮ በአጥቢያዎቹ አገልጋይ ካህናትና ዲያቆናትም ተጐብኝቷል፡፡

Mini 4

ካህናትና ዲያቆናት የአብነት ሥርዓተ ትምህርትን ሲያሳዩ

የሚኒያ ፖሊስ ቅድስት ሥላሴ ካህናትና ዲያቆናት የአብነት ት/ት አሰጣጥ ሒደትን በክውን ትዕይንት መልክ ማቅረባቸው ለዐውደ ርእዩ ድምቀት ከመስጠቱ ባሻገር የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት በምን ዓይነት ሥርዓተ ት/ት አልፈው ለማዕረግ እንደሚደርሱ ጐብኚዎቹ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡

Mini

የዐውደ ርእዩ ጐብኚዎች በከፊል

ከጐብኚዎቹ መካከልም ጥቂት የማይባሉ ምእመናን በዐውደ ርእዩ መዘጋጀት የተሰማቸውን ደስታ በዕንባ ሲገልጹ የታዩ ሲኾን በአስተያየቶቻቸውም ማኅበሩ በየአገሩ እንደዚህ ዓይነት አስተማሪነት ያላቸውን መርሐ ግብራት ደጋግሞ እንዲያቀርብ አሳስበው ለዚህም የሚያስፈልገውን ኹሉ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ለዐውደ ርእዩ መሳካት በገለጻ፣ በማስተባበርና ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ አባቶችን፣ የሰበካ ጉባኤ አመራሮችን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችንና በጎ አድራጊ ምእመናንን ንዑስ ማእከሉ በማኅበረ ቅዱሳን ስም መንፈሳዊ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

የደቡብ ማእከላት ማስተባበሪያ ተተኪ መምህራንን አስመረቀ

ነሐሴ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በሐዋሳ ማእከል

Hawasa

በማኅበረ ቅዱሳን የደቡብ ማእከላት ማስተባበሪያ ከልዩ ልዩ ግቢ ጉባኤያት በመመልመል ለአንድ ወር ያሠለጠናቸውን ፶፮ የደረጃ ሁለት ተተኪ መምህራን የሲዳማ፣ ጌድዮ፣ አማሮና ቡርጂ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ የሐዋሳ ማእከል አባላት፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን በተገኙበት በሐዋሳ ደብረ ታቦር ቅዱስ ሩፋኤል የካህናት ማሠልጠኛ ተቋም ነሐሴ ፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም አስመረቀ፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ አባ ሀብተ ማርያም ‹‹እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል›› /ዮሐ.፫፥ ፴፬ / በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡

የዋናው ማእከል ተወካይ ዲ/ን ሙሉጌታ  ኃይለ ማርያም ባስተላለፉት መልእክት ምሩቃኑ ለአገልግሎት እንዲተጉና የተጣለባቸውን አደራ በትጋት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ሠልጣኞቹ ከወሰዷቸው ኮርሶች መካከል ትምህርተ ሃይማኖት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ሥርዓትና ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ነገረ ቅዱሳን፣ ትምህርተ ክርስትና፣ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፣ ሐዋርያዊ ተልእኮ፣ ትምህርተ አበው፣ ነገረ ማርያምና ኦርቶዶክሳዊ የጾታ ትምህርት የሚገኙ ሲኾን በተጨማሪም ስለ ኦርቶዶክሳውያን መዝሙራትና ሐራ ጥቃዎች በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ እያደረሱት ያለውን የተሐድሶ እንቅስቃሴ የሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡

ሚዲያ ክፍላችን ያነጋገራቸው አንዳድ ምሩቃን በሥልጠናው ጠቃሚ ዕውቀት እንደቀሰሙበትና በርካታ ቁም ነገሮችን እንዳገኙበት ገልጸው ለወደፊቱም ‹‹የየማእከላቱ ክትትልና ድጋፍ እንዳይለየን›› ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም የደቡብ ማእከላት ማስተባበሪያ ሓላፊ አቶ ዘሪሁን ከበደ የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን፣ የሀገረ ስብከቱና የወረዳ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎችን፣ የሐዋሳ ደብረ ታቦር ቅዱስ ሩፋኤል አስተደዳሪና ካህናትን፣ መምህራንን እንደዚሁም ሥልጠናው እንዲሳካ ልዩ ልዩ ድጋፍ ያደረጉ አካላትን በማኅበሩ ስም ካመሰገኑ በኋላ መርሐ ግብሩ በአባቶች ጸሎት ተጠናቋል፡፡

በጥናትና ምርምር ማእከል አዘጋጅነት የጥናት ጉባኤ ተካሔደ

ነሐሴ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በካሣኹን ለምለሙ

DSCN8791

የጉባኤው ተሳታዎች በከፊል

በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል አዘጋጅነት ‹‹ጥናትና ምርምር ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ አገልግሎት መጠናከር›› በሚል መሪ ቃል ፰ኛው ዓመታዊ የጥናት ጉባኤ ከነሐሴ ፳፩-፳፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በማኅበሩ ሕንጻ ፫ኛ ፎቅ አዳራሽ ተካሔደ፡፡

በጉባኤው ከቀረቡት ጥናቶች መካከልም ‹‹በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የአስኳላ ትምህርት መማር አስፈላጊነት››፤ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች የማቋቋም ሒደት›› እና ‹‹የግእዝ ቋንቋ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽዖ› የሚሉት ርእሰ ጉዳዮች ይገኙባቸዋል፡፡

DSCN8844

‹‹የአብነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የአስኳላ ትምህርት የመማር አስፈላጊነት›› በሚል ርእስ በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል የተዘጋጀውን ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የክፍሉ አባል የኾኑት አቶ ጌትነት ለወየው የአብነት ተማሪዎች ዘመናዊውን ትምህርት ቢማሩ ለቤተ ክርስቲያን ከሚሰጡት ውጤታማ አገልግሎት ባሻገር በታማኝነትና በሓላፊነት ከሙስና የጻዳ ሥራ በመሥራት ለአገር ዕድገትም የሚኖራቸው ኹለንተናዊ አስተዋጽዖ ከፍተኛ መኾኑን በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡

DSCN8805

‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች የማቋቋም ሒደት›› በሚለው ርእስ ላይ ጥናት ያቀረቡት ጠበቃና የሕግ አማካሪ ዲ/ን ፊልጶስ ዓይናለም በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ወቅት መንፈሳዊና ማኅበራዊ ግዴታዋን ከመወጣት አንጻር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ ጠቅሰው በሥሯ የሚገኙ አገልጋዮችንና ምእመናንን ለማስተዳደር ያመች ዘንድ የራሷ የኾነ መደበኛ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ሊኖራት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

‹‹የግእዝ ቋንቋ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ዕድገት ያበረከተው አስተዋጽዖ›› በሚል ርእሰ ጉዳይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ቋንቋዎች አካዳሚ ሓላፊና የሥነ ልሳን ረዳት ፕሮፌሰር ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም ደግሞ የግእዝ ቋንቋ ጥንታዊ መኾኑና በፊደል ቀረፃ፣ በትርጕም ሥራ፣ በቃላት ስያሜ፣ በመዝገበ ቃላት አገልግሎትና በመሳሰሉት ዘርፎች ለሌሎች ቋንቋዎች ሥነ ጽሑፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከቱ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ቋንቋዎች ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

በጥናት ጉባኤው ‹‹የክርስቶስ የማዳን ትምህርት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ዘንድ ያለው ግንዛቤና የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት››፤ ‹‹አውጣኪ፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስና የኬልቄዶን ጉባኤ››፤ ‹‹የመጽሐፈ መዋሥዕት ይዘት ትንታኔ››፤ ‹‹ባሕረ ሐሳብ ጥንታዊው የኢትዮጵያውያን ትምህርት፣ በዘመን አቈጣጠር፣ በሥነ ከዋክብት ጥናትና በአየር ትንበያ›› በሚሉ ርእሰ ጉዳዮችም በዘርፉ ምሁራን ተመሳሳይ ጥናቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች ላነሧቸው ልዩ ልዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በጥናት አቅራቢዎቹ ምላሾች ከተሰጡ በኋላ የጥናት ጉባኤው በጸሎት ተፈጽሟል፡፡

ተዝካረ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጻድቅ

ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዝግጅት ክፍሉ

Tkle

አቡነ ተክለ ሃይማኖት

በዛሬው ዝግጅታችን ነሐሴ ፳፬ ቀን የሚከበረውን በዓለ ዕረፍታቸውን ምክንያት በማድረግ ከቅዱሳን ጻድቃን መካከል አንዱ የኾኑትን፣ ‹‹ሐዲስ ሐዋርያ›› እየተባሉ የሚጠሩትን የቅዱስ ተክለ ሃይማኖትን ዜና ሕይወት በአጭሩ ይዘን ቀርበናል፤

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ፣ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት፤ ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፲፪፲፪ ዓ.ም. በቡልጋ አውራጃ በደብረ ጽላልሽ ኢቲሳ ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስተኛውም ቀን እሑድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው ‹‹አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፡- አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው›› በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ስማቸውን ‹‹ፍሥሐ ጽዮን›› ብለዋቸዋል፡፡ በተወለዱ በ፲፭ ዓመታቸው ዲቊናን፤ በ፳፪ ዓመታቸው ቅስናን ከግብፃዊው ጳጳስ ከአባ ጌርሎስ /ቄርሎስ/ ተቀብለዋል፡፡

አንድ ቀን ወደ ጫካ ለአደን በሔዱበት ዕለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱ ክርስቶስ ተገልጦላቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱን ካሰደረባቸው፤ እንደዚሁም ‹ሐዲስ ሐዋርያ› ብሎ ወንጌል ወዳተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸው ከነገራቸው፤ ቅዱስ ሚካኤልም ከአውሬ አዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደ ተመረጡና አጋንንትን የማውጣት፣ ተአምራትን የማድረግ ሥልጣን እንደ ተሰጣቸው፤ ስማቸውም ‹ተክለ ሃይማኖት› እንደሚባልና ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው›› እንደ ኾነ ካስረዳቸው በኋላ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ያላቸውን ንብረት ኹሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው ‹‹አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደ ተከፈተ ተውኩልህ›› በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ ብዙ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አንጸዋል፡፡

ከዚህ በኋላ በደብረ ሊባኖስ (ገዳመ አስቦ) ዋሻ በመግባትም ሁለቱን በፊት፣ ሁለቱን በኋላ ሁለቱን በቀኝ፣ ሁለቱን በግራ ስምንት ጦሮችን ተክለው እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማም፣ ሞትና ነገረ መስቀል በማሰብ በተመስጦ ሌሊትና ቀን ያለማቋረጥ በጾም፣ በጸሎት ተወስነው ሲጋደሉ፤ ከቊመት ብዛት የተነሣ በ፺፪ኛ ዓመታቸው ጥር ፬ ቀን ፲፪፹፱ ዓ.ም አንዲቱ የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የመንፈሳዊ አባታቸውን ስባረ ዐፅም አክብረው በሥርዓት አኑረዋታል፡፡ እግራቸው እስኪሰበር የቆዩባቸው ዓመታትም ፳፪ ናቸው፡፡ ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው ቆመው ያለ ምግብና ያለ ውኃ በትኅርምት ሌሊትና ቀን እንደ ምሰሶ ጸንተው በትጋት ለሰው ዘር ኹሉ ድኅነትን ሲለምኑ ኖረዋል፡፡

ከሰባቱ ዓመታት ውስጥ ጥቂት ውኃ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ እንደ ነበረ መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡ ጻድቁ አባታችን ምድራዊ ሕይወታቸውን በተጋድሎና በሐዋርያዊ አገልግሎት ከፈጸሙ በኋላ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ የሚያልፉበት ቀን በተቃረበ ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደእርሳቸው በመምጣት የሚያርፉበት ዕለት መድረሱን ነግሯቸው የተጋድሏቸውን ጽናት አድንቆ በስማቸው መታሰቢያ ለሚያደርጉ፣ ለነዳያን ለሚመጸዉቱ ቤተ ክርስቲያን ለሚያሠሩ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ ስለ ተጋድሏቸው ጽናትም ‹‹በሰው እጅ የማይለካውን ይህንን የመንግሥት አዳራሽ ውሰድ›› በማለት የመለኮትን ነገር የሚናገር የእሳት አንደበት ያለው የጸጋ ልብስ አልብሷቸዋል፤ በመስቀል ምልክት ያጌጡ ሰባት የሕይወት አክሊላትንም አቀዳጅቷቸዋል፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖትም የዕረፍታቸው ጊዜ መቃረቡን ባወቁ ጊዜ የመንፈስ ልጆቻቸውን ጠርተው ጌታችን የነገራቸውን ሁሉ አስረድተው አባታዊ ምክርና ተግሣፅ ከሰጧቸው በኋላ ነሐሴ ፳፬ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፉ፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውም ለአንድ ቅዱስ አባትና ካህን በሚገባ ሥርዓት በማኅሌት፣ በዝማሬና በምስጋና ቀበሯቸው፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችንና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገልጾ ታያቸው፤ ነፍሳቸውንም ‹‹የጠራሽ፣ ንጽሕት ነፍስ ሆይ ወደእኔ ነዪ›› ብሎ በክብር ተቀብሏታል፡፡ በመጽሐፈ ገድላቸው እንደተጠቀሰው ቅዱስ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዚህ ዓለም የኖሩበት ዕድሜ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከዐሥር ወር ከዐሥር ቀን ነው፡፡ ገድላቸው ዕድሜያቸውን በመከፋፈል፡- በእናት አባታቸው ቤት ፳፪ ዓመት፤ በከተታ ፫ ዓመት፤ በይፋት ፱ ወር፤ በዳሞት ፲፪ ዓመት፤ በአማራ ፲ ዓመት፤ በሐይቅ ፲ ዓመት፤ በደብረ ዳሞ ፲፪ ዓመት፤ በትግራይ ገዳማት በመዘዋወርና ወደ ኢየሩሳሌም በመመላለስ ፩ ዓመት፤ ዳዳ በሚባል አገር ፩ ወር፤ በደብረ አስቦ ገዳም ፳፱ ዓመት ከ፲ ቀን መቆየታቸውን ይናገራል /ገ.ተ.ሃ.፶፱፥፲፬-፲፭/፡፡

በአጠቃላይ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው በተጨማሪ እንደቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያችንም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፡፡ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከተናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ፤ ዋጋው አይጠፋበትም›› /ማቴ.፲፥፵-፵፪/ በማለት የተናገረውን መለኮታዊ ቃል ኪዳን መሠረት አድርጋ መጋቢት ፳፬ ቀን ፅንሰታቸውን፤ ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ልደታቸውን፤ ጥር ፳፬ ቀን ስባረ ዐፅማቸውን፤ ግንቦት ፲፪ ቀን ፍልሰተ ዐፅማቸውን ነሐሴ ፳፬ ቀን ዕረፍታቸውን በትላቅ ደስታ ታከብራለች፡፡

ቅዱሳን ጻድቃን በመንፈሳዊ አርአያነታቸው፣ በጸሎታቸውና በትምህርታቸው ከከበቡን የነፍስ ጠላቶች፤ ከርኲሳን መናፍስትና ከጨለማው ልጆች፣ ከክፉ ሰዎች ሽንገላና ተንኰል ለመሰወርና ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሥልጣን ምን ጊዜም ይሠራል፡፡ በጻድቃን መኖር ሀገር ከጥፋት ትድናለች፡፡ የጻድቃንን ስም ጠርቶ እግዚአብሔርን በመለመን በረከትና ረድኤት ይገኛል፡፡ ስለ ጻድቃን ብሎ እግዚአብሔርም ምሕረቱን ያድላል፡፡ ጻድቃንን ማሰብ ሥራቸውን መዘከር ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ያጐለምሳል፡፡ በነፍስ በሥጋ ይታደገናል፤ ይረባናል፤ ይጠቅመናል፡፡ ስለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቃንን እንድናስባቸው፣ በስማቸውም ለድሆችና ለጦም አዳሮች እንድንመጸውት መታሰቢያቸውን እንድናደርግ የምትመክረን፤ የምታስተምረን /ማቴ.፲፥፵፩-፵፪/፡፡ ጻድቃንን በሕይወተ ሥጋ ሳሉም ቢኾን፤ ከሞቱም በኋላ በዐጸደ ነፍስ በጸሎታቸው ለሚታመኑ፣ በቃል ኪዳናቸው ለሚማጸኑ፣ የድኅነተ ሥጋ፣ የድኅነት ነፍስ ምክንያቶች ናቸው፡፡

የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የኹሉም ጻድቃን ጸሎትና በረከት ረድኤትና ምልጃ በመላው ሕዝበ ክርስቲያን ላይ ጸንቶ ይኑር፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

መለከት መጽሔት ፲፰ኛ ዓመት፣ ቍጥር ፱፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን፡፡

ገድለ ተክለ ሃይማኖት፡፡

ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ የአንድነት ኑሮውን አበረታቱ

ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

IMG_0049

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ

‹‹ለቤተ ክርስቲያናችን ንዋያተ ቅድሳትን ብቻ ሳይኾን ሰውም እንስጥ›› በሚለው መሪ ቃሉ የሚታወቀው ጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናትና በርካታ ምእመናን በተገኙበት ነሐሴ ፳፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስብከተ ወንጌል አዳራሽ የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባኤ አካሒዷል፡፡

በዕለቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው፣ ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይና የምሥራቃዊ ዞን አዲግራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የአንድነት ኑሮው ከየብሔረሰቡ የተውጣጣጡ ሰባክያንን በማሠልጠን ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት የሚያደርገውን አስተዋጽዖ አድንቀው ‹‹በዚህ አገልግሎታችሁ በርቱ፤ እኛም ከጎናችሁ ነን›› ሲሉ የአንድነት ኑሮውን አበረታተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሰላማ የምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በበኩላቸው ‹‹እግዚአብሔር ንጹሕ ልብ፣ ንጹሕ ሰውነት ይፈልጋልና በንጽሕና ኾናችሁ እንድታገለግሉ እግዚአብሔር ይርዳችሁ፤ ማኅበራችሁን ያስፋላችሁ›› የሚል አባታዊ ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡

IMG_0073

ብፁዕ አቡነ ሰላማ

በተመሳሳይ መልኩ የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ታምሩ እሸቱ የሀገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስን ወክለው ‹‹እኛም ከጎናችሁ ኾነን የምንችለውን ኹሉ እናደርጋለን›› ብለዋል፡፡

በዕለቱ በቀሲስ እሸቱ ታደሰና በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲኾን፣ በተጨማሪም የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰንበት ት/ቤትና የአንድነት ኑሮው መዘምራን፣ እንደዚሁም የአንድነት ኑሮው ሠልጣኞች ያሬዳውያን ዝማሬያትን አቅርበዋል፡፡

በመቀጠልም የአንድነት ኑሮው መግለጫ በስብከተ ወንጌል ሥልጠና ኰሚቴው አባል በአቶ ማናየ አባተ የቀረበ ሲኾን በመግለጫውም ከአዲስ አበባ ከተማ በ፻፶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ የገጠር ቤተ ክርስቲያን ቆመው መሔድ የማይቻላቸው ካህን ታቦቱን አክብረው፤ ሌላ ጐልማሳ ደግሞ እርሳቸውን ተሸክሟቸው በበዓለ ጥምቀት ወደ ባሕረ ጥምቀት ሲወርዱ መታየታቸውን አስመልክቶ የቀረበው ዘገባ የጉባኤውን ተሳታፊዎች ያሳዘነ ነበር፡፡

IMG_0046

የጉባኤው ተሳፊዎች በከፊል

‹‹የአንድነት ኑሮው ዓላማና ተልእኮ ከመላው የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ማስተማር የሚችሉ ሰባክያነ ወንጌልን በማሠልጠን ወንጌልን ማዳረስና የአብነት ትምህርት በማስተማር በአገልጋይ ካህን እጦት ምክንያት የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ነው›› ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው ዲያቆን ሙሉጌታ ምትኩ የጉባኤው ዓላማም ለዚህ አገልግሎት ማስፈጸሚያ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡ አክለውም ኹሉም ሕዝበ ክርስቲያን ከአንድነት ኑሮው ጋር በመኾን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መጠናከር የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ሰላማ ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ የጉባኤው ፍጻሜ ኾኗል፡፡

‹‹ትርጓሜ ያሐዩ›› በሚል ኃይለ ቃል የውይይት መርሐ ግብር ተካሔደ

ነሐሴ ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዝግጅት ክፍሉ

በማበኅረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አዘጋጅነት ‹‹ትርጓሜ ያሐዩ፤ ትርጓሜ ያድናል›› በሚል ኃይለ ቃል ነሐሴ ፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በግዮን ሆቴል ብሉ ሳሎን አዳራሽ የውይይት መርሐ ግብር ተካሔደ፡፡

IMG_0012

የመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች በከፊል

በመርሐ ግብሩ ላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው ምእመናን የተገኙ ሲኾን የዋና ክፍሉ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ መሠረት ለተሳታፊዎች የእንኳን ደኅና መጣችሁ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የመርሐ ግብሩ ዓላማ የመጻሕፍት ትርጓሜ ቤቶችን አስተዋጽዖ በማስገንዘብ ጉባኤ ቤቶችን ለማስፋፋትና ተተኪ ሊቃውንትን ለማፍራት የሚያስችል ግንዛቤ ለማስጨበጥ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡

IMG_0002

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ

በዕለቱ የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኀኔ ዓለም የአራቱ ጉባኤያት ምስክር መምህርና የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ በአንድምታ ትርጕም ያዘጋጇቸው ትንቢተ ኢሳይያስ፣ ሃይማኖተ አበውና ድርሳነ ቄርሎስ ወጰላድዮስ ምስለ ተረፈ ቄርሎስ ተመርቀዋል፡፡

ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ መጻሕፍቱ ለጉባኤ ቤት መምህራንና ለደቀ መዛሙርት እንደዚሁም ለምእመናን የሚኖራቸው ጠቀሜታ የጎላ መኾኑን ጠቅሰው ‹‹መጻሕፍቱ በስሜ ቢዘጋጁም የመጻሕፍቱ ባለቤት ግን ጉባኤ ቤቱ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም›› ብለዋል፡፡ ከመጻሕፍቱ ሽያጭ የሚገኘውም ገቢም ሙሉ በሙሉ ለጉባኤ ቤታቸው መኾኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤልና በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ የትርጓሜ መጻሕፍትን ትውፊትና አስተዋጽዖ የሚዳስስ ጥናታዊ ጽሑፍ፤ እንደዚሁም የትርጓሜ መጻሕፍትን ታሪካዊ አመጣጥና የጉባኤ ቤቶችን ችግር የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም ከቀረበ በኋላ ሊቃውንቱንና ተጋባዥ እንግዶችን ያሳተፈ ጠቃሚ ውይይት ተካሒዷል፡፡

ከሰዓት በኋላ በዮድ አቢሲንያ የምግብ አዳራሽ በቀጠለው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብርም ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ‹‹የታቦር ጉባኤ›› በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል የሰጡ ሲኾን በትምህርታቸውም ከደብረ ታቦር ምሳሌዎች አንደኛው የመጻሕፍት ትርጓሜ ጉባኤ ቤት መኾኑን አስረድተዋል፡፡

IMG_0037

በዮድ አቢሲንያ አዳራሽ የተገኙ ሊቃውንትና ምእመናን በከፊል

ሊቀ ሊቃውንት በመቀጠልም የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኀኔ ዓለም የትርጓሜ መጻሕፍት ምስክር ቤት ደቀ መዛሙርትን እያስተማረ የሚገኘው በመቃብር ቤት መኾኑ ለሥርዓተ ትምህርቱ መሰናክል እንደ ኾነባቸው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ለጉባኤ ቤቱ አገልግሎት የሚሰጥ ኹለ ገብ ዘመናዊ ሕንጻ በጎንደር ከተማ ለመገንባት በ፳፻፰ ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ቢቀመጥም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሕንጻው እስከ አሁን ድረስ አለመገንባቱን አስታውሰው ይህን ሕንጻ ለመገንባት መላው ሕዝበ ክርስቲያን ከጎናቸው እንዲቆም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም በአባቶች ጸሎት የውይይት መርሐ ግብሩ ተፈጸሟል፡፡

ክብረ ድንግል ማርያም

ነሐሴ ፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ታደለ ፈንታው

mariam[1]

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ጋር

እግዚአብሔር ዘላለማዊ ኃይሉንና አምላክነቱን ለዓለም ከገለጸበት ታላቅ ሥራ መካከል በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የገለጸው ድንቅ ሥራው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ይህንን ኹኔታ ድንግል ማርያም ‹‹ብርቱ የኾነ እርሱ ታላቅ ሥራን በእኔ አድርጓል፤ ስለዚህም ፍጥረት ኹሉ ያመሰግኑኛል›› /ሉቃ.፩፥፵፱/ በማለት ገለጸችው፡፡

ቅድስት ኤልሳቤጥም ‹‹የጌታዬ እናት›› አለቻት /ሉቃ.፩፥፵፫/፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ›› አላት /ሉቃ.፩፥፳፰/፡፡ ቅዱስ ዳዊት ደግሞ ‹‹ልጄ›› ይላታል /መዝ.፵፬፥፱/፡፡ ሰሎሞንም ‹‹እኅቴ›› ይላታል /መኃ.፭፥፩/፡፡ ለወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም እናት ኾና ተሰጥታዋለች /ዮሐ.፲፱፥፳፮/፡፡ ይህን ድንቅ ምሥጢር ውስንና ደካማ የኾነ አእምሮ ሊገነዘበው ከሚችለው በላይ ነው፡፡

ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንደገለጸው ‹‹የቅድስት ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና፤ አማኑኤልን መውለዷና የማይሞተው ጌታ መሞቱ›› እነዚህ ሦስቱ ከዚህ ዓለም ጥበበኞችና ገዢዎች የተሰወሩ ምሥጢራት ናቸው፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹እነዚህ ድንቅ ምሥጢራት በራሳቸው ከንግግርና ከቋንቋዎች ኹሉ በላይ ኾነው የሚነገሩ በእግዚአብሔር የዝምታ መጐናጸፊያ የተጠቀለሉ ድብቅና ጣፋጭ ምሥጢሮች ናቸው›› ይላል፡፡

የእመቤታችን ምስጋናዋ የበዛለት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊም ‹‹አቤቱ መሰንቆ ልቡናዬን አነቃቃ፤ የልቤንም እንዚራ፡፡ ድምፁን ከፍ አድርጎ የዳዊት ልጅ የኾነችውን፣ የጌታውን እናት ድንግል ማርያምን ያመሰግናት ዘንድ፤ ለዓለም ሕይወት የሚሰጠውን የወለደች እናቱ የኾነች እርሷን ከፍ ከፍ ያደርጋት ዘንድ›› ብሏል፡፡ በሌላም አንቀጽ ደግሞ ‹‹ከሕሊናት ኹሉ በላይ ለኾነ ለዚህ ነገር አንክሮ ይገባል፡፡ ምድራዊት ሴት ፈጣሪዋን ወለደችው፤ እርሱም እናቱን ፈጠረ›› አለ፡፡ ስለእነዚህ ነገሮች ኹሉ ምን ማለትን እንችላለን? እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስለ ድንግል ማርያም ያልተናገረበት ጊዜ፤ ያላናገረው ቅዱስ እንደሌለ እንመለከታለን፡፡

‹‹በእግዚአብሔር፣ በመላእክትና በሰው ፊት የከበረ ሰው መታሰቢያው ለዘለዓለም ነው፡፡ በቤቱ በቅጥሩ የማይጠፋ የዘለዓለም ስምን ይቀበላልና›› /ኢሳ.፶፭፥፫/፡፡ ይህንን ታላቅ በረከት እንደሚሰጣቸው የተናገረው የማይዋሸው ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ወልድ እናት ከድንግል ማርያም የበለጠ በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ማንን ልንጠራ እንችላለን? እንደ እርሷስ ሊታሰብ፣ ሊከበርም የሚችል በቅድስና ሕይወት ያለፈ ማን ይኖራል?

ቅዱስ እግዚአብሔር ፍጥረቱንና ዓለሙን ለማዳን የወሰነው ጊዜ በደረሰ ጊዜ ከድንግል ማርያም በድንግልና ተወለደ፡፡ አስቀድሞ በመልአኩ አፍ እንዳናገረ ክብሩ በእርሷ ላይ ታየ /ኢሳ.፷፥፪/፡፡ ማኅፀኗን ከተማ አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በእርስዋ አደረ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእመቤታችን ላይ የማደሩ ምሥጢር ያነጻቸው፤ ይቀድሳቸው፤ በሥጋም በነፍስም መርቶ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ያገባቸው ዘንድ በነቢያት፣ በሐዋርያት ላይ እንዳደረው ዓይነት አይደለም፡፡ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ (ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ) ከሥጋዋ ሥጋን፣ ከነፍስዋ ነፍስን ነስቶ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ ኾነ እንጂ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ይህን ዘለዓለማዊ እውነት ‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል፡፡ ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል›› በማለት ገልጾታል /ሉቃ.፩፥፵፭/፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ደራሲና ገጣሚ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም ‹‹የእስራኤል ንጉሥ በእስራኤል ልጅ አደረ፤ የዳዊት አምላክ ከዳዊት ልጅ ሥጋን ለበሰ፡፡ የዕብራውያን ጌታ በዕብራውያን ልጅ ማኅፀን ተወሰነ፡፡ ለአብርሃም የዕብራይስጥ ልሳን ያስተማረው ከቀድሞም ያልሰማውን ልሳን እንዲናገር አፉን ጆሮውን የከፈተለት ከዕብራዊት ድንግል ተወለደ፤ በድንግልና ወተት ጥቂት ጥቂት እያለ አደገ፡፡ የሕፃናትን ሥርዓት እንዳያጎድል አፉን የሚፈታባት ዘመን እስኪፈጸም ጥቂት ጥቂት እያለ በዕብራይስጥ ልሳን ሲናገር ኖረ፡፡ ለሙሴ በዕብራይስጥ ልሳን በጣቶቹ የተጻፉትን ዐሠርቱ ቃላትን የሰጠ የዕብራይስጥ ፊደል ለመማር ከመምህር እግር በታች ተቀመጠ፡፡ የባቢሎን አውራጃ በምትኾን ሰናዖርም የፍጥረትን ሁሉ ቋንቋ የበተነ እርሱ የአሕዛብን ቋንቋ እንደማያውቅ ኹሉ እናቱ አፍ በፈታችበት ልሳን በዕብራይስጥ ልሳን ሲናገር ኖረ፡፡ ጆሮ ይህንን ነገር ከመስማት የተነሣ የሚለመልምበት ይህ ነገር ዕፁብ ድንቅ ነው፡፡ ለዚህ አንክሮ ይገባል›› አለ፡፡ ይህ በሰው ጥበብ በብራናና በቀለም የተጻፈ እውነት ሳይኾን ለድኅነት በተጠሩ ሰዎች ሁሉ ልቡና በአምላክ ጥበብ የተጻፈ እውነት ነው፡፡

የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ይደርብን፤ የልጇ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክረስቶስ ጸጋ ይብዛልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ፳፰ ቤቶቿን አስመለሰች

ነሐሴ ፳ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

DSCN8710

መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ወጪ ካስገነባቻቸውና በደርግ ዘመነ መንግሥት በግፍ ከተወረሱባት በርካታ ቤቶቿ መካከል ፳፰ቱን ማስመለሷን የሕንጻዎችና ቤቶች አስመላሽ ኰሚቴ ሰብሳቢ አስታወቁ፡፡

በጠቅላይ ቤተ ክህነት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሓላፊ፣ የሕንጻዎችና ቤቶች አስመላሽ ኰሚቴ ሰብሳቢ መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም ለዝግጅት ክፍላችን እንደ ገለጹት አስመላሽ ኰሚቴው ባደረገው ያለሰለሰ ጥረት በሦስት ክፍለ ከተሞች ማለትም በልደታ ፲፰፤ በየካ ፭ እና በቂርቆስ ፭ በድምሩ ፳፰ ቤቶች ነሐሴ ፲፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለባለንብረቷ ለቤተ ክርስቲያን መመለሳቸው ተረጋግጧል፡፡

አስመላሽ ኰሚቴው ባደረገው የማጣራት ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ በየክፍለ ከተሞች በደርግ መንግሥት እንደ ተወረሱ የቀሩ ሁለት መቶ ሰማንያ ሦስት ሕንጻዎችና ቤቶች እንደሚገኙ፤ ከእነዚህ መካከልም አንድ መቶ ሠላሳ ሰባቱ ሕጋዊ ማረጋገጫ እንደ ተገኘላቸው የጠቆሙት የኰሚቴው ሰብሳቢ በአሁኑ ሰዓት ፳፰ቱ ቤቶች መመለሳቸውን አድንቀው ቀሪዎቹ አንድ መቶ ዘጠኙ ደግሞ እስከ ነሐሴ ወር ፳፻፰ ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ተመላሽ እንደሚኾኑ ጠቁመዋል፡፡

ለወደፊቱም ኹሉም ሕንፃዎችና ቤቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመለሱ ለማድረግ አስመላሽ ኰሚቴው ተግቶ እየሠራ መኾኑን ያስገነዘቡት ሰብሳቢው የተወረሱ ሕንፃዎችንና ቤቶችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት ልዩ ልዩ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት ኹሉ በቤተ ክርስቲያንና በአስመላሽ ኰሚቴው ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በዐሥር ሚሊዮን ዐርባ ዘጠኝ ሺሕ ብር ወጪ የተገዙ ዐሥር ዘመናዊ መኪኖች ሥራ መጀመራቸውን መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡

የመኪኖቹ ሙሉ ወጪ የቤተ ክርስቲያኗ መኾኑን የጠቀሱት መጋቤ ካህናት ዐሥሩም መኪኖች የመጓጓዣ እጥረት ላለባቸው አህጉረ ስብከትና የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎች አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጋቸውን አስታውሰው መኪኖቹ በአፋጣኝ ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉም የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ከዚህ ቀደሙ በተሻለ ኹኔታ እንዲከናወን ያደርጋል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም መኪኖቹ በፍጥነት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ድጋፍ ላደረጉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ በቤተ ክርስቲያኗ ስም ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ ለወደፊቱ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ለምታከናውናቸው ተግባራትና ንብረቶቿን ለማስመለስ ለምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውጤታማነት ‹‹መላው ሕዝበ ክርስቲያን በጸሎታቸውና በዐሳባቸው ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል›› ሲሉ ለምእመናን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዘመነ ክረምት ክፍል ሦስት

ነሐሴ ፳ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በክፍል ሁለት ዝግጅታችን ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፲ ቀን ድረስ ያለው ሁለተኛው ክፍለ ክረምት ‹‹መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል›› እንደሚባል፤ ይህ ክፍለ ጊዜ የመብረቅና የነጎድጓድ ድምፅ በብዛት የሚሰማበት፤ የባሕርና የወንዞች ሙላት የሚያይልበት፤ እንደዚሁም የምድር ልምላሜ የሚጨምርበት ወቅት እንደ ኾነ በማስታዎስ ሕይወታችንን ከወቅቱ ኹኔታ ጋር በማገናዘብ መንፈሳዊ ቁም ነገር የሚያስጨብጥ ትምህርት ማቅረባችን የሚታዎስ ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ቀጣዩንና ሦስተኛውን ክፍለ ክረምት የተመለከተ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!

ከነሐሴ ፲ እስከ ፳፰ ቀን (ከማኅበር እስከ አብርሃም) ድረስ ያለው የዘመነ ክረምት ክፍለ ጊዜ ‹‹ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኲሉ›› ይባላል፡፡ ይኸውም የሰውን ልጅ ጨምሮ የሰማይ አዕዋፍ፣ የምድር አራዊትና እንስሳት ሳይቀሩ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርገው በደስታ መኖራቸው፤ በተጨማሪም በዝናም አማካይነት በዙሪያቸው ያለው የውሃ መጠን ከፍ ሲልላቸው ደሴቶች ኹሉ በልምላሜ ማሸብረቃቸው የሚነገርበት ክፍለ ክረምት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ኹሉ በእነዚህ ምሥጢራት ላይ ያተኰረ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥለን ስለ ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያትና ዓይነ ኲሉ በቅደም ተከተል አጭር ማብራሪያ ለመስጠት እንሞክራለን፤

ዕጕለ ቋዓት

‹‹ዕጕል፣ ዕጓል›› ማለት ‹‹ልጅ›› ማለት ሲኾን፣ ‹‹ቋዕ›› ደግሞ ‹‹ቍራ›› ማለት ነው፡፡ ‹‹ቋዕ›› የሚለው ቃል በብዙ ቍጥር ሲገለጽም ‹‹ቋዓት›› ይኾናል፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹ዕጕለ ቋዓት›› የሚለው የግእዝ ቃላት ጥምረትም ‹‹የቍራ ልጆች (ግልገሎች)›› የሚል ትርጕም አለው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን የቍራ ጫጩቶች አስተዳደግ ከምእመናን ሕይወት ጋር ተነጻጽሮ ይነገራል፡፡ ይህም እንዲህ ነው፤ ቍራ ከእንቁላሉ ፍሕም መስሎ ይወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ እናትና አባቱ ባዕድ ነገር መስሏቸው ትተውት ይሸሻሉ፡፡ እርሱም በራበው ጊዜ ምግብ ፍለጋ አፉን ሲከፍት እርጥበት የሚፈልጉ ተሐዋስያን ወደ አፉ ይገባሉ፡፡ ከዚያም አፉን በመግጠም ይመገባቸዋል፡፡ እንደዚሁም ተሐዋስያን በአጠገቡ ሲያልፉ በእስትንፋሱ (በትንፋሹ) እየሳበ ይመገባቸዋል፡፡ እስከ ፵ ቀን ድረስ እንደዚህ እያደረገ ከቆየ በኋላ ፀጕር ያበቅላል፤ በዚህ ጊዜ በመልክ እነርሱን ስለሚመስል እናት አባቱ ተመልሰው ይከባከቡታል፡፡ ይህ የቍራ ዕድገትና ለውጥም እግዚአብሔር ፍጡራኑን የማይረሳ አምላክ እንደ ኾነና ፍጥረቱንም በጥበቡ እየመገበ እንደሚያኖራቸው የሚያስገነዝብ ነው፡፡

ቅዱስ ዳዊት ይህንን የቍራ የዕድገት ደረጃና የእግዚአብሔርን መግቦት በተናገረበት መዝሙሩ ‹‹ወሐመልማለ ለቅኔ ዕጓለ እመሕያው ዘይሁቦሙ ሲሳዮሙ ለእንስሳ ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውእዎ፤ ለሰው ልጆች ጥቅም ለምለሙን የሚያበቅል፤ ለእንስሳትና ለሚለምኑት የቍራ ጫጩቶች ምግባቸውን የሚሰጣቸው እርሱ ነው›› ሲል ይዘምራል /መዝ.፻፵፮፥፱/፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በትርጓሜያቸው እንደ ገለጹት ይህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔር አምላክ ለእርሱ ለሚገዛው ለሰው ልጅ እኽህሉን፣ ተክሉን የሚያበቅልላቸው፤ ለእንስሳቱና ለአዕዋፍ (በቍራ አምሳል አዕዋፍን በመጥቀስ) ምግባቸውን የሚሰጣቸው እርሱ እንደ ኾነ ያስረዳል፡፡ ‹‹… ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውእዎ፤ … ለሚለምኑት ለቍራ ጫጩቶች›› የሚለው ሐረግም አዕዋፍ እግዚአብሔርን ምግብ እንዲያዘጋጅላቸው እንደሚለምኑትና እርሱም ልመናቸውን እንደሚቀበላቸው ያስገነዝበናል፡፡ በአንድምታው ትርጓሜ እንደ ተጠቀሰው ‹‹… ወለዕጕለ ቋዓት እለ ይጼውእዎ›› የሚለው ሐረግ ‹‹… እለ ኢይጼውእዎ›› ተብሎ ከተገለጸ የቍራ ጫጩቶች አፍ አውጥተው ባይነግሩት እንኳን እርሱ ፍላጎታቸውን ዐውቆ ምግባቸውን እንደሚሰጣቸው የሚያመለክት ምሥጢር አለው /ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት/፡፡

ምሥጢሩን ወደ እኛ ሕይወት ስናመጣውም እግዚአብሔር አምላክ ስሙን የሚጠሩትንም የማይጠሩትንም፤ ‹‹የዕለት እንጀራችንን ስጠን›› እያሉ የሚማጸኑትንም የማይጸልዩትንም በዝናም አብቅሎ፣ በፀሐይ አብስሎ ኹሉንም ሳያደላ በቸርነቱ እንደሚመግባቸው ያስተምረናል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የሰው ልጅ ለሚበላው፣ ለሚጠጣው መጨነቅ እንደማይገባው ሲናገር ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ትምህርት ሰጥቷል፡፡ እንዲህ ሲል፤ ‹‹ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፡፡ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና፡፡ ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱምም፡፡ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፡፡ እናንተ ከወፎች ትበልጡ የለምን? … አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም፤ አይፈትሉምም፡፡ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ኹሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም:: … ዛሬ ያለውን፣ ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የኾነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከኾነ፣ እናንተ እምነት የጐደላችሁ! እናንተንማ ይልቁን እንዴት? … የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፤ አታወላውሉም:: ይህንስ ኹሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፡፡ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል:: ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ፤ ይህም ኹሉ ይጨመርላችኋል፤›› /ሉቃ.፲፪፥፳፪-፴፩/፡፡

ስለዚህም አምላካችን እንዳስተማረን ስለምንበላውና ስለምንጠጣው ሳይኾን ስለ በጎ ምግባርና ስለ ዘለዓለማዊው መንግሥት መጨነቅ ይገባናል ማለት ነው፡፡ ራሳችንን ለገነት፣ ለመንግሥተ ሰማያት በሚያበቃ የጽድቅ ሥራ ካስገዛን የሚቀርብን ነገር አይኖርምና፡፡ ‹‹ዘእንበለ ንስአሎ ይሁብ ፍትወተነ፤ ሳንለምነው ልባችን የተመኘውን የሚሰጠን እርሱ ነው›› እንዲል /መጽሐፈ ኪዳን/፡፡ የየልባችንን መሻት ዐውቆ በረድኤቱ እየጠበቀ፤ በቸርነቱ እየመገበ የሚያኖረን አምላካችን እግዚአብሔር ስሙ ለዘለዓለሙ የተመሰገነ ይኹን፡፡

ደሰያት

በውሃ የተከበበ የብስ መሬት ‹‹ደሴት›› ይባላል፤ ‹‹ደሰያት›› ደግሞ ብዙ ቍጥርን አመላካች ነው፡፡ በዚህ ወቅት ስለ ደሴቶች ይነገራል፡፡ ምክንያቱም በዝናም አማካይነት በሚጨምረው የውሃ መጠን በድርቅ ብዛት የተጎዱ በደሴቶች የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ሳይኾኑ እንስሳትም አዕዋፍም በሚበቅለው እኽልና በሚያገኙት ምግብ የሚደሰቱበት ጊዜ በመኾኑ ነው፡፡ ደሴቶች በውሃ የተከበቡ መሬት እንደ መኾናቸው በዚህ ወቅት በልምላሜ ያጌጣሉ ቢባልም ዳሩ ግን በማዕበልና በሞገድ መቸገራቸውም አይቀርም፡፡ ይህም የቤተ ክርስቲያን (የምእመናን ሕይወት) እና የዓለም ምሳሌ ነው፡፡ ደሴቶች በውሃ መከበባቸው ቤተ ክርስቲያን (የምእመናን ሕይወት) በክርስቶስ ደም የተመሠረተች፤ በቃለ እግዚአብሔር የታነጸች ለመኾኗ፤ ደሴቶች በማዕበልና በሞገድ እንደ መናወጣቸው ደግሞ በዓለም ውስጥ የሚከሠቱ ረሃብ፣ ጥላቻ፣ ጦርነት፣ ወዘተ የመሳሰሉ ችግሮች፤ በተለይ ሰይጣን የሚያመጣው ልዩ ልዩ ኅብረ ኀጢአት የቤተ ክርስቲያንን (የምእመናንን) ህልውና የሚፈታተኑ መኾናቸውን ያጠይቃል፡፡

ዓለም ሞገድ የበዛባት የውሃ ክፍል ናት፤ የክርስትና ሕይወት ደግሞ በውሃ የተከበበች መሬት፡፡ በውሃ የተከበበ መሬት ሞገድ፣ ማዕበልና ስጥመት እንደሚያጋጥመው ኹሉ የክርስትና ሕይወትም በምድር ላይ ልዩ ልዩ መከራና ፈተና ሊያጋጥመው ይችላልና ሃይማኖታችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ከልዩ ልዩ ፈተና ይጠብቅልን ዘንድ ኹላችንም በፍጹም ሃይማኖት ኾነን እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ከስጥመት አድነን?›› እያልን እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ እርሱ በባሕር፣ በሞገድ፣ በማዕበልና በነፋስ የሚመሰሉ የዓለምን ውጣ ውረድና መከራ መገሠፅ፤ ሑከቱንም ጸጥ ማድረግ የሚቻለው አምላክ ነውና /ማቴ.፰፥፳፫-፳፯/፡፡

ዓይነ ኵሉ

‹‹ዓይነ ኵሉ›› በግእዝ ቋንቋ ‹‹የኹሉም ዓይን›› ማለት ነው፡፡ ይህም ፍጥረታት ኹሉ ወደ ፈጠራቸው ወደ እግዚአብሔር በማንጋጠጥ የዕለት ጕርስ፣ የዓመት ልብስ እንዳይከለክላቸው እንደሚማጸኑትና ዘወትር የእርሱን መግቦት ተስፋ በማድረግ እንደሚኖሩ ያስረዳል፡፡ ይህ ወቅትም ያለፈው እኽል ያለቀበት፤ የተዘራውም ያላፈራበት ገና የተክል ጊዜ በመኾኑ ፍጥረታት በሙሉ የፍሬውን ጊዜ በተስፋ የሚጠባበቁበት ስለ ኾነ ‹‹ዓይነ ኵሉ›› ተብሏል፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ዳዊት ‹‹ዐይነ ኵሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያከ አንተ ትሁቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ ትሰፍሕ የማነከ ወታጸግብ ለኵሉ እንስሳ ዘበሥርዓትከ›› ሲል የዘመረው /መዝ.፻፵፬፥፲፮/፡፡ ይኸውም የሰው ኹሉ ዓይን (ዓይን የተባለ ሰውነት ነው) እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጎ እንደሚኖር፤ እርሱም በዘር ጊዜ ዘሩን፣ በመከር ጊዜ መከሩን፣ በበልግ ጊዜ በልጉን እያዘጋጀ በየጊዜው ምግባቸውን እንደሚሰጣቸው፤ እንደዚሁም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ብቻ ሳይኾን በሰፊው እጁ (በማያልቅ ቸርነቱ) በሥርዓቱ ጸንተው ለሚኖሩ ለእንስሳት ጭምር ምግባቸውን እየሰጠ ደስ እንደሚያሰኛቸው የሚያስረዳ ነው /ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት/፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን መተርጕማን እንደሚያትቱት ከሰው ልጅ በቀር ከእግዚአብሔር ሥርዓት የወጣ እንስሳ የለም፤ ማለትም ሰው እንጂ እንስሳት ሕገ እግዚአብሔርን አልተላለፉም፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ አምላክነትን ተመኝቶ ‹‹አትብላ›› የተባለውን ዕፅ በመብላት ሕጉን፣ ትእዛዙን ተላልፏል፡፡ እግዚአብሔርም ይቅር ባይ አምላክ ነውና የሰውን ልጅ (የአዳምን) ንስሐ ተመልክቶ፣ ኀጢአቱን ይቅር ብሎ ሞቱን በሞቱ ሽሮ አድኖታል፡፡ እናም እግዚአብሔር በፍጡራኑ የማይጨክን፤ የለመኑትን የማይነሳ፤ የነገሩትንም የማይረሳ አምላክ መኾኑን በማስተዋልና ቸርነቱን ተስፋ በማድረግ በምድር በረከቱን እንዲሰጠን፤ ቅዱስ ሥጋውን ለመብላት፣ ክቡር ደሙን ለመጠጣ እንዲያበቃን፤ በሰማይም ዘለዓለማዊ መንግሥቱን እንዲያወርሰን በንጹሕ ልብ ኾነን ዘወትር ልንማጸነው ይገባናል፡፡ ‹‹አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /መዝ.፳፬፥፫/ እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ አያሳፍርምና፡፡ ደግሞም በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይበልጣልና፡፡

ይቆየን፡፡