ዐርባ ምንጭ ማእከል ተተኪ ሰባክያንን አስመረቀ

ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዐርባ ምንጭ ማእከል

DSC06070

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የዐርባ ምንጭ ማእከል ከጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት፣ ከኮንሶ ወረዳ ቤተ ክህነትና ከወረዳ ማእከሉ ጋር በመተባበር ለ፴ ቀናት ያሠለጠናቸውን፤ በአካባቢው ቋንቋዎች ወንጌልን ማስተማር የሚችሉ ከኮንሶ እና ከደራ ማሎ ወረዳዎች የተውጣጡ ፴፫ ተተኪ ሰባክያንን ሲቀላ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ደብር ቅፅር በሚገኘው የማኅበሩ ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ነሐሴ ፯ ቀን ፳፻፰ አስመርቋል፡፡

በምረቃ ሥርዓቱ ላይም የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከትና የኮንሶ ወረዳ ቤተ ክህነት ተወካዮች፣ የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል እና የደብረ መንክራት ቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ኃይለ ጊዮርጊስ ማሕጸንተ፣ ድጋፍ አድራጊ ምእመናንና የማእከሉ አባላት ተገኝተዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ተወካይ መምህር ዮሐንስ አሻግሬ ‹‹ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን በመላው ዓለም ዞረው ወንጌልን እንዲያስተምሩ እንደላካቸው ኹሉ፤ እናንተም በየአካባቢው ቋንቋ ወንጌልን በማስተማር አሕዛብን ከምእመናን ማኅበር እንድትጨምሯቸው አደራችንን እናስተላልፋለን›› ብለዋል፡፡

‹‹ምሩቃኑ ለስብከተ ወንጌል በምተሰማሩባቸው አካባቢዎች ኹሉ በሰበካ ጉባኤያት፣ በወረዳ ማእከላትና በሰ/ት/ቤቶች በአባልነት በመሳተፍ፣ ከካህናትና ከምእመናን ጋር በመግባባት ማገልገል ይጠበቅባችኋል›› ያሉት የማእከሉ ሰብሳቢ አቶ ደመላሽ ወንድማገኘሁ በበኩላቸው ለሰባክያኑ አገልግሎት ውጤታማነትም የሀገረ ስብከቱ፣ የወረዳ ቤተ ክህነቶችና የየአጥቢያ ሰበካ ጉባኤያት ክትትልና ድጋፍ እንዳይለያቸው አባቶችን አሳስበዋል፡፡

ሰብሳቢው አያይዘውም የጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከትን፣ የኮንሶ ወረዳ ቤተ ክህነትን፣ የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤትንና በጎ አድራጊ ምእመናንን ለሥልጠናው መሳካት ላበረከቱት አስተዋጽዖ በማእከሉ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የማእከሉ ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ሓላፊ አቶ እያያ ፍቃዴ በበኩላቸው ለሠልጣኞቹ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሐዋርያዊ ተልእኮ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ነገረ ማርያም፣ ነገረ ቅዱሳን፣ ነገረ ሃይማኖት እና የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና ከመሰጠቱ ባሻገር በተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ዙሪያም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንዲያገኙ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ልዩ ልዩ የትምህርተ ሃይማኖት መጻሕፍት ለምሩቃኑ ከተበረከቱ በኋላ በአባቶች ጸሎት የምረቃ ሥርዓቱ ተፈጽሟል፡፡

የዐርባ ምንጭ ማእከል በ፳፻፯ ዓ.ም በተመሳሳይ አርእስት ፳፮ ተተኪ ሰባክያንን አሠልጥኖ ለአገልግሎት እንዲሰማሩ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡