ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ማወቅ የችግሮች መፍትሔ መኾኑን ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ገለጡ

ነሐሴ ፲፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ዮሴፍ ይኵኖአምላክ

አቡነ ዲዮስቆሮስ

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው፣ ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይና የምሥራቃዊ ዞን አዲግራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ መመሪያዎችንና ደንቦችን ባለመረዳት በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማስወገድ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ማወቅ፣ ዐውቆም በተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባ ገለጡ፡፡

ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ ለስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በጽ/ቤታቸው በሰጡት ቃለ መጠይቅ የካህናትና የምእመናን ድርሻ ምን መኾን እንዳለበት በቃለ ዐዋዲው በግልጽ መሥፈሩን አስታውቀው ‹‹ኹሉም ሕዝበ ክርስቲያን ክርስቲያናዊ መብትና ግዴታውን ዐውቆ እናት ቤተ ክርስቲያንን በፍቅር በማገልገል መንፈሳዊ አደራውን ሊወጣ ይገባል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ኹሉ ጋርም በኢትዮጵያውያን ምእመናን መካከል ለረጅም ጊዜ ተጠብቆ የቆየው እርስ በርስ የመፈቃቀርና የመደጋገፍ ባህል ለተከታዩ ትውልድ እንዲሻገር የኹሉንም ትኩረት እንደሚሻ ጠቅሰው ‹‹በቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርት የታነጸው በጎ ሥርዓት በዘመን አመጣሽ ጎጂ ልማዶች እንዳይበከል ተግተን ልንሠራ ይገባል›› ብለዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያዊው ባህል አብሮ መብላት መጠጣት ብቻ ሳይኾን በችግርና በደስታ ጊዜ በአብሮነት መኖር ነው›› ያሉት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የአብሮነት ትሥሥሩን ከሚያጠፉ የባህል ወረራዎች ምእመናኑ ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም የእምነት ወረራ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ መኾኑን ያስታወሱት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ‹‹ምእመናንን ከነጣቂ ተኩላዎች ለመከላከል በስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተጠናከረ ሥራ መሠራት አለበት›› በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በልዩ ልዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ለዝግጅት ክፍላችን የሰጡትን ሙሉ ቃለ መጠይቅ ከነሐሴ ፩-፲፭ ቀን እና ከ፲፮-፴ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በሚታተመው የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በቤተ አብርሃም ዓምድ ትከታተሉ ዘንድ ከወዲሁ እንጋብዛለን፡፡