በዓለ ፍልሰታና ሻደይ

ነሐሴ ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በሰቆጣ ማእከል

ሻደይ

ልጃገረዶች የሻደይን በዓል ሲጫወቱ

በአገራችን ኢትዮጵያ በተለይ በሰሜኑ ክፍል ሕዝበ ክርስቲያኑ ለረጅም ዘመናት ሥርዓተ አምልኮ ሲፈጸሙባቸው የነበሩና አሁንም እየተፈጸመባቸው የሚገኙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ መንፈሳውያን ቅርሶች በርካቶች ናቸው። ከእነዚህ ቅርሶች መካከልም መንፈሳውያን በዓላት የሚከበሩበት ሥርዓት አንደኛው ነው፡፡ ከእነዚህ መንፈሳውያን በዓላት ውስጥ በዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ምእመናን ዘንድ የሚከበረው የሻደይ ምስጋና (ጨዋታ) ልጃገረዶች በአማረ ልብስ ደምቀው ‹‹አሸንድዬ›› በሚባል የቄጠማ ጉንጉን ወገባቸውን አሥረው እየተጫወቱ የሚያከብሩት በዓል ነው።

ከነሐሴ ፲፮ እስከ ነሐሴ ፳፩ ቀን ድረስ የሚከበረው ይህ በዓል በዋግ ኽምራ ‹‹ሻደይ››፣ በላስታ ‹‹አሸንድዬ››፣ በትግራይ ‹‹አሸንዳ››፣ በቆቦ አካባቢ ‹‹ሶለል››፣ በአክሱም አካባቢ ደግሞ ‹‹ዓይነ ዋሪ›› እየተባለ ይጠራል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የሻደይ በዓል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መነሻ አለው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና እንደሚናገሩት የአዳም ከገነት መባረር፣ የኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ፣ የዘመን መለወጫ፣ የመጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አንገት መቈረጥ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ (ፍልሰታ) እና የመሥፍኑ ዮፍታሔ ልጅ ታሪክ ከሻደይ በዓል ተያያዥነት ያላቸው ሲኾን በተለይ የእመቤታችን ትንሣኤ (በዓለ ፍልሰታ) ከሻደይ በዓል ጋር የጎላ ግንኙት እንዳለው የቤተ ክርስቲያን መምህራንና የአገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ፡፡ እያንዳንዱ ታሪክ ከሻደይ በዓል ጋር ያለውን ግንኙነት በአጭሩ እንመልከት፤

የአዳም ከገነት መባረር

አባታችን አዳም ሕገ እግዚአብሔርን በመተላለፉ ጸጋ እግዚአብሔር ርቆት እርቃኑን በኾነ ጊዜ አካሉን ለመሸፈን የበለስ ቅጠል ማገልደሙን ለማስታዎስና አዳምና ሔዋን ክብራቸውን ተገፈው ከገነት የተባረሩባትን ዕለት ለማሰብ በወቅቱ ያገለደሙትን ቅጠል በምልክትነት በመውሰድ ልጃገረዶች የሻደይ ቅጠልን በገመድ ላይ ጎንጉነው በወገባቸው አገልድመው ያሥራሉ፡፡ አዳምና ሔዋን ከገነት ከመውጣታቸው በፊት ግብረ ሥጋ ግንኙነት ያልጀመሩ ደናግላን ስለነበሩ ያንን በመከተልና በምሳሌነት በመውሰድ ያላገቡ የአገው ልጃገረዶች ተሰባስበው የሻደይ ጨዋታን መጫወት ወይም ማክበር እንደጀመሩ ይነገራል።

የሻደይ በዓልና የጥፋት ውኃ

በኖኅ ዘመን ከተላከው የጥፋት ውኃ በኋላ ውኃው መጕደሉንና አለመጕደሉን እንድታጣራ ኖኅ ርግብን በላካት ጊዜ በምድር ሰላም መኾኑን የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ በመምጣት ለኖኅ የምሥራች ነግራዋለች። ከዚሁ ጋር በተገናኘ በዓሉን ያንን ለምለም ቅጠል ወገባቸው ላይ በማሰር ከጨለማ ወደ ብርሃን ተሸጋገርን ሲሉ ማክበር እንደጀመሩ አበው ከታሪኩ ጋር አያይዘው ያስቀምጡታል።

የሻደይ በዓልና የመሥፍኑ ዮፍታሔ ልጅ ታሪክ

ዮፍታሔ ወደ ጦርነት በሔደ ጊዜ በድል ከተመለሰ ወደ ቤቱ ሲመለስ መጀመሪያ የሚቀበለውን ሰው እንደሚሠዋ ስእለት ተስሎ ነበር፡፡ ድል አድርጎ ሲመለስም ያለ ወትሮዋ ልጁ እየዘፈነች ልትቀበለው ወጣች፤ በዚህም በጣም አዘነ። ልጁም ለአምላኩ የገባውን ስእለት እንዳያስቀር ብላ ሁለት ወር ስለ ድንግልናዋ አልቅሳ ስእለቱን እንዲፈጽም ጠይቃው ከሁለት ወር በኋላ ልጁን ሠውቷታል፡፡ አባቷ የገባውን ቃል ኪዳን እንዳያጥፍ በማበረታታት በመሥዋዕትነት የቀረበችውን የዮፍታሔን ልጅ በማሰብ በየዓመቱ እየተሰባሰቡ ሙሾ ያወጣሉ፡፡

የልጃገረዶች የቡድን አመሠራረት

በሻደይ በዓል የልጃገረዶች የቡድን አመሠራረት ደብርን (አጥቢያን) መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የሻደይ ጨዋታ በዓል በሚያከብሩበት ጊዜ ልጃገረዶች የተለያዩ ባሕላዊ አልባሳትን ለብሰው ከበሮ እና ለምስጋና የሚያስፈልጉ ነገሮችን በማሟላት ተጠራርተው በመጀመሪያ ወደ አጥቢያቸው በመሔድ የቤተ ክርስቲያኑን በር አልፈው ዘልቀው ጣዕመ ዝማሬ እያሰሙ ሦስት ጊዜ ይዞሩና ደጃፉን ተሳልመው በቅጥር ግቢው አመቺ ቦታ ፈልገው ምስጋናቸውን ይጀምራሉ፡፡

ከበሯቸውን እየመቱ፣ የታቦቱን ስም እየጠሩ በሚያምር ድምፃቸው፣ ሽብሻቦ፣ ውዝዋዜ፣ ጥልቅ መልእክትን በያዙ ግጥሞች፣ ለዚህ ያደረሳቸውን አምላክና ታቦት ያወድሳሉ፣ ያሞግሳሉ፣ ያከብራሉ፣ ያመሰግናሉ፡፡ ምስጋናው ለዚህ ዓመት ያደረሳቸውን አምላክ ቀጣዩ ዓመትም እንደዚሁ የሰላም፣ የጤና የተድላ እንዲኾን የሚማጸኑበት፣ ተስፋቸውን የሚገልጹበትና ስእለት የሚሳሉበት በመኾኑ ምስጋናቸውን ሞቅ፣ ደመቅ አድርገው በአንድነት፣ በፍቅር፣ በደስታ፣ በመተሳሰብና በሰላም ይጫወታሉ፡፡ ‹‹ለእግዚአብሔርና ለደብራችን ታቦት ያልኾነ›› እያሉ ጉልበታቸውን፣ ችሎታውንና ልምዳቸውን ሳይቈጥቡ በምስጋናው ይሳተፋሉ።

ከቤተ ክርስቲያን መልስ በአካባቢው ወዳሉት ታላላቅ አባቶች ዘንድ ሔደው በመዘመር ቡራኬ ይቀበላሉ። ከዚያም ተመልሰው ወደ ተራራማ ሥፍራ በመውጣት ክብ ሠርተው ይዘምራሉ፡፡ የዝማሬዎቻቸው ግጥሞችና ዜማዎችም መንፈሳዊ ይዘት ያላቸውና ከግለሰባዊ ስሜት ወይም ከግለሰብ ውዳሴ የራቁ ናቸው፡፡ አጥቢያቸውን እንደማያስደፍሩና እንደሚጠብቁ በምስጋናቸው ይገልጻሉ፡፡ የወከሉትን ደብር ታቦት ስም እየጠሩ ለአባት እናት፣ ለቤተሰብ ጤና፣ ጸጋ፣ ሀብት፣ ሰላም በአጠቃላይ መልካሙን ኹሉ እንዲያደርግላቸው እግዚአብሔርን ይማጸናሉ፡፡

የምስጋናቸው ዜማና ግጥም ተመሳሳይ ቢኾንም የወከሉትን ደብር ስም ብቻ በማቀያየር በተመሳሳይ ዜማ ማወደስ እና መማጸን በኹሉም የሻደይ ተጨዋች ቡድኖች ይስተዋላል፡፡ ልጃገረዶቹ በዚህ የምስጋና ጊዜ የሚሰበስቧቸውን ስጦታዎችም ለቤተ ክርስቲያን ያበረክታሉ።

የሻደይ በዓልና ፍልሰታ

የሻደይ በዓል አጀማመርን በተመለክተ ከላይ ከተቀመጡት ታሪኮች በተጨማሪ በአካባቢው ሕዝብና በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ተደጋግሞ የሚነሣው ታሪክ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ በዓል ነው፡፡ እግዚአብሔር ለአዳምና ሔዋን ከአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመት በኋላ ወደዚህ ዓለም አንድያ ልጁን ልኮ ከኀጢአት እሥራት ነጻ እንደሚያወጣቸው በገባላው ቃል ኪዳን መሠረት አምላክ የተወለደባት እና ትንቢቱ የተፈጸመባት፣ ከገነት የተባረረው የሰው ልጅ ወደ ገነት እንዲመለስ ምክንያት የኾነችው፣ የሰው ልጆች መመኪያ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም ድካም ካረፈች በኋላ ሞትን ድል አድርጋ ከመቃብር ተነሥታ ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡

በፍልሰታ ወቅት በዓሉ መከበሩም ለሻደይ ተጨዋቾች ተምሳሌትና የድንግልናቸው አርአያ የሚያደርጓት ድንግል ማርያም አካላዊ ሥጋዋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፤ እንደዚሁም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ምክንያት በማድረግ እንደኾነ የሚገልጹት የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ስብከተ ወንጌል መምሪያ ሓላፊ መጋቤ ምሥጢር ገብረ ሕይወት ኪዳነ ማርያም ‹‹የሻደይ በዓል በልጃገረዶች ዘንድ ተወዳጅ የኾነው በሔዋን ምክንያት የተዘጋው ገነት በእመቤታችን አማካኝነት በመከፈቱ ነው። እመቤታችን መመኪያቸው ስለ ኾነች ልጃገረዶች በዓሉን በደስታ ያከብሩታል፤ ድንግልናቸውንም አደራ የሚሉት ለእርሷ ነው›› ሲሉ ይናገራሉ።

እመቤታችን በነሐሴ ፲፮ ቀን በቅዱሳን መላእክት ሽብሸባ፣ ዕልልታና ዝማሬ ታጅባ ከምድር ወደ ሰማይ ስታርግ ሐዋርያት በታላቅ ደስታ ይመለከቱ፣ ይደነቁም ነበር፡፡

ደናግልም ከቅዱሳን መላእክት ከተመለከቱት ሥርዓት በመነሣት ነጫጭ ልብሶችን ለብሰው፣ አምረውና አጊጠው፣ ረጃጅምና ለምለም ቅጠል በወገባቸው አሥረው  እንደ መላእክቱ አክናፍ ወገባቸውን ከግራ ወደ ቀኝ እያመላለሱ፣ እያዘዋወሩና እያሸበሸቡ፣ በአንደበታቸው እየዘመሩና በእጆቻቸው እያጨበጨቡ በአንድነት ተሰባሰባስበው በፍቅርና በሐሴት የወቅቱ መታሰቢያ የኾነውን የሻደይን በዓል ያከብራ፡፡

እናቶችና እኅቶች በዐደባባይ ወጥተው የድንግል ማርያምን ትንሣኤና ዕርገት እንደ ነጻነታቸው ቀን በመቍጠር ከበሮ አዘጋጅተው ‹‹አሸንድዬ›› የተባለውን ቄጠማ በወገባቸው ታጥቀው ምስጋና በማቅረብ በዓሉን ይዘክራሉ፡፡

በአጠቃላይ የሻደይ ጨዋታ የፍልሰታ በዓል መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ በምእመኑ ዘንድ ለበርካታ ዓመታት እየተከበረ የኖረ ሃይማኖታዊ በዓል ነው፡፡ ይህንን ሃይማኖታዊ መሠረትነት ያለውን ትውፊት የመጠበቅና የማስጠበቅ ሓላፊነት ከኹላችንም ይጠበቃል። የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡