ደብረ ታቦርና ቡሄ

ነሐሴ ፲፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን በዓሉ ይከበራል፡፡ ይህ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ‹‹ቡሄ›› በመባል ይታወቃል፡፡

ቡሄ ማለት /መላጣ ፣ ገላጣ/ ማለት ነው፡፡ በአገራችን ክረምቱ፣ አፈናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት በዚሁ በዓል አካባቢ ስለኾነ ‹‹ቡሄ›› እንደ ተባለ ይገመታል፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት፣ ብርሃን የታየበት፣ ድምፀ መለኮት የተሰማበትና ችቦ የሚበራበት ዕለት ስለ ኾነ ደብረ ታቦር የብርሃን ወይም የቡሄ በዓል ይባላል፡፡

ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን፣ ወደ ጥቢ የሚያመራበት፣ ወደ መፀው የሚገባበት፣ ወገግታ የሚታይበት፣ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፣ የሚሸጋገርበት ወቅት በመኾኑ ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት አይኖርም፡፡ ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እንዲሉ፡፡በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች የቡሄ ዕለት ማታ ምእመናን ችቦ ያበራሉ፡፡ ይህም በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ ነው፡፡

ሕፃናቱ ይህ በዓል ከመድረሱ በፊት ቀደም ብለው ጅራፍ ሲገምዱና ሲያጮኹ (ሲያኖጉ) ይሰነብታሉ፡፡ እናቶችም ለዚህ በዓል የሚኾን ዳቦ ለመጋገር ስንዴያቸውን ሲያጥቡ፣ ሲፈትጉ ይሰነብታሉ፡፡ በበዓሉ ዋዜማ (ነሐሴ ፲፪ ቀን) ሕፃናት በየቤቱ እየዞሩ ‹‹ቡሄ ና በሉ፤ ቡሄ በሉ፡፡ ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ፡፡ …›› እያሉ ይጫወታሉ፡፡ ‹‹ቡሄ›› ያሉት ዳቦውን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ እያነሡ ይሰጧቸዋል፡፡

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል፡፡ «ቡሄ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ የሚበራው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ ልጆችም ዳቧቸውን እየገመጡ ጅራፍ ሲገርፉ ይውላሉ፡፡ የጅራፉ መጮኽ የድምፀ መለኮት፣ ጅራፉ ሲጮኽ ማስደንገጡ ነቢያትና ሐዋርያት በድምፀ መለኮት መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን ያስታውሳል፡፡

በተጨማሪም ለክርስትና ልጅ፣ ለአማች፣ ለምራት፣ ለዘመድ አዝማድ ኹሉ የቡሄ ዳቦ ይሰጣል፡፡

ደብረ ታቦር ወይም ቡሄ በአብነት ተማሪዎች ‹‹ስለ ደብረ ታቦር›› እያሉ እህል፣ ጌሾ ከምእመናን በመለመንና ገንዘብ በማዋጣት ጠላውን ጠምቀው፣ ዳቦውን ጋግረው፣ ቆሎውን ቆልተው ለደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱ የመጡትን ምእመናን በመጋበዝ በታላቅ ድምቀት ያከብራሉ፡፡

መምህረ ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ተማሪዎቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ በደብረ ታቦር ምሥጢር መግለጡን በማስታዎስ የአብነት ተማሪዎች ከመምህራቸው ጋር በመኾን በዓለ ደብረ ታቦርን (ቡሄን) ያከብራሉ፤ ስሙን ይጠራሉ፡፡ ይህም እስከ አሁን ድረስ በትምህርት ቤቶች የሚሠራበት ነባር ትውፊት ነው፡፡

ነገር ግን በአንድ አካባቢዎች በተለይ በከተማ ዙሪያ በዓለ ደብረ ታቦር (ቡሄ) ሃይማኖታዊ ትውፊቱን የለቀቀ ይመስላል፡፡ ለዚህም ልጆች የሚጫወቱበት መዝሙር ግጥሙና ዜማው ዓለማዊ መለእክት የሚበዛበት መኾኑ፤ በወቅቱ ችቦ ከማብራት ይልቅ ርችት መተኮሱና በየመጠጥ ቤቱ እየሰከሩ መጮኹ፤ ወዘተ. የበዓሉን መንፈሳዊ ትውፊት ከሚያደበዝዙ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከዚሁ ኹሉ ጋርም በዚህ በዓል ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ የሚሽቀዳደሙ ነገር ግን የበዓሉን ታሪካዊ አመጣጥ የማያዉቁ ልጆችም ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ስለዚህ ወላጆች ለልጆቻቸው የበዓለ ደብረ ታቦርን መንፈሳዊነት፣ የመዝሙሮቹን ያሬዳዊነትና አከባበሩን ከቤተ ክርስቲያን መምህራን በመጠየቅ ማስተማር፤ ልጆችም ከወላጆች ወይም ከመምህራን በመጠየቅ የበዓሉን አከባበር መረዳትና የዚህን በዓል መንፈሳዊ ትውፊት ሳይበረዝ ለትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ ነው እንላለን፡፡

በመጨረሻም በቡሄ በዓል ‹‹ድምፅህን ሰማና በብሩህ ደመና፤ የቡሄው ብርሃን ለእኛ በራልን፤ …›› የሚለውንና ይህን የሚመስሉ መንፈሳውያን መዝሙራትን እየዘመሩ በየቤቱ በመዞር የሚያገኙትን ዳቦና ገንዘብ ለነዳያንና ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ ልጆችን ማበረታታትና አርአያነታቸውን መከተል ይኖርብናል መልእክታችን ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ ፳፻፭ ዓ.ም፣ ገጽ ፫፻፲፭-፫፻፲፯፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፤ ፳፻፯ ዓ.ም፣ ገጽ ፻፲፩፡፡