አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር

ደደ

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት የታቦር ተራራ

ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

‹‹አስተርእዮ›› ሥርወ ቃሉ ‹‹አስተርአየ (አርአየ) = አሳየ፣ ገለጠ፣ ታየ፣ ተገለጠ›› የሚለው የግእዝ ግስ ሲኾን ትርጕሙም ‹‹መታየት፣ መገለጥ፣ ማሳየት፣ መግለጥ›› ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/፡፡ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር›› የሚለው ሐረግም ‹‹የእግዚአብሔር በታቦር ተራራ መገለጥ›› ወይም መታየት የሚል ትርጕም ያለው ሲኾን ይህም ከእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ጋር የተያያዘ እንደዚሁም ከምሥጢረ ሥጋዌና ከነገረ ድኅነት ጋር የተሳሰረ ታላቅ ምሥጢርን የያዘ መገለጥ ነው፡፡

ከዚህ ላይ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር›› ስንል የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ማለታችን መኾኑን ለማስታዎስ እንወዳለን፡፡ ‹‹እግዚአብሔር›› የሚለው ቃል ሦስቱም አካላት (ቅድስት ሥላሴ) በጋራ የሚጠሩበት መለኮታዊ ስያሜ ነውና፡፡ ‹‹አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ በአሐዱ ስም ሥሉሰ ያምልኩ፤ እኔ ‹እግዚአብሔር› በአልሁ ጊዜ ስለ አብም፣ ስለ ወልድም፣ ስለ መንፈስ ቅዱስም እናገራለሁ፤ (ምእመናን) በአንዱ ስም (በእግዚአብሔር) ሦስቱ አካላትን ያመልኩ ዘንድ›› እንዳለ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት /ሃይማኖተ አበው/፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እግዚአብሔር አምላክ በብሉይም ኾነ በሐዲስ ኪዳን በአንድነቱ በሦስትነቱ በግብር (በሥራ)፣ በራእይና በገቢረ ተአምራት በልዩ ልዩ መንገድ ለፍጡራኑ ተገልጧል፡፡ በብሉይ ኪዳን ልዩ ልዩ ምልክት በማሳየት፤ በቅዱሳን ነቢያትና በመሣፍንት፣ በነገሥታት፣ በካህናትና በነቢያት ላይ በማደር ወይም በራእይ በማነጋገር፤ በተጨማሪም በጻድቃኑ ላይ ቸርነቱን በማሳየት፣ በክፉ አድራጊዎች ላይ ደግሞ መቅሠፍቱን በመላክ ሲያደርጋቸው በነበሩ ተአምራቱና ሥራዎቹ ይገለጥ ነበር፡፡

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ለአዳምና ለልጆቹ በገባው ቃል መሠረት የሰውን ሥጋ ለብሶ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በአካለ ሥጋ ተገልጦ በገቢረ ተአምራቱ፣ በትንሣኤውና በዕርገቱ አምላክነቱን አሳይቷል፡፡ የብሉይ ኪዳኑ መገለጥ በምልክት፣ በራእይ፣ በድምፅና በመሳሰሉት መንገዶች የተደረገ መገለጥ ነበር፤ የሐዲስ ኪዳኑ መገለጥ ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹መቼም ቢኾን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው›› /ዮሐ.፩፥፲፰/ ሲል እንደ ገለጸው አምላካችንን በዓይነ ሥጋ ያየንበት አስተርእዮ ስለኾነ ከመገለጦች ኹሉ የተለየ ጥልቅ ምሥጢር አለው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በሐዲስ ኪዳን በአካለ ሥጋ ያደረገውን መገለጥ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከምሥጢረ ሥላሴ ጋር በማያያዝ በሦስት መንገድ ይገልጹታል፡፡ ይኸውም በእመቤታችን፣ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ላይ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹በላዕሌኪ ወበዮርዳኖስ ወበታቦር ሥልሰ ጊዜያተ ዘአልቦ ተውሳከ ወአልቦ ሕጸተ ለውሉደ ሰብእ ያርኢ ዘሥላሴሁ ገጻተ ጽጌኪ ድንግል ተአምሪሁ ከሠተ ወበፀዳሉ አብርሀ ጽልመተ›› እንዳለ ደራሲ /ማኅሌተ ጽጌ/፡፡ ትርጕሙ እግዚአብሔር አምላክ ጭማሬም ጉድለትም የሌለበትን ሦስትነቱን ለሰው ልጅ ያሳይ ዘንድ በእመቤታችን፣ በዮርዳኖስ እና በታቦር ሦስት ጊዜ ተአምራቱን መግለጡን፤ በብርሃነ መለኮቱም ጨለማውን ብርሃን ማድረጉን የሚያስረዳ ሲኾን ይህም ጌታችን በለበሰው ሥጋ በእመቤታችን ማኅፀን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተወስኖ ሲወለድ፤ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ዕለት እግዚአብሔር አብ ‹‹የምወደው ልጄ እርሱ ነው፤ እርሱን ስሙት›› ብሎ  ሲመሰክርና መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ራሱ ላይ ሲያርፍ፣ እንደዚሁም በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ መለኮታዊ አንድነቱና አካላዊ ሦስትነቱ መታወቁን ያመለክታል፡፡

በዛሬው ዝግጅታችን ወደምንመለከተው ትምህርት ስንመለስ ‹‹ደብረ ታቦር›› ማለት ‹‹የታቦር ተራራ›› ማለት ነው፤ ‹‹ደብር›› በግእዝ ቋንቋ ‹‹ተራራ ማለት ሲኾን ‹‹ታቦር›› ደግሞ የቦታው ስም ነው፡፡ ይኸውም ከኢያቦር ወገን በሚኾን ቦር በሚባል ሰው ስም የተሰየመ ቦታ ነው፡፡ ‹‹ታቦር›› ማለት ‹‹ትልቅ›› ማለት ሲኾን ተራራውን በ ‹‹ቦር›› ላይ ‹‹ታ››ን ጨምረው ‹‹ታቦር›› ብለው እንደ ጠሩት ይነገራል፡፡ ታቦር በፍልስጥኤም ግዛት ከገሊላ ባሕር በስተምዕራብ ደቡባዊ ክፍል የሚገኝ፤ ዕፀዋቱ መልካም መዓዛ የሚያመነጩበት፤ ከ፭፸፪ ሜትር በላይ ከፍታ ያለው ግዙፍ ተራራ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ነቢዪቱ ዲቦራ ከባርቅ ጋር በመኾን የከነዓናውያንን ንጉሥ፣ የጦር መሪው ሲሳራንና ኢያቢስን ድል አድርገውበታል፡፡ ነቢዪቱም ከድል በኋላ መሥዋዕት አቅርባበታለች /መሣ.፬፥፭-፳፬/፡፡ እንደዚሁም ነቢዩ ሳሙኤል ትንቢት ተናግሮበታል፡፡ ንጉሥ ሳኦልም ከሦስት ሰዎች ጋር ተገኝቶበታል /፩ኛ ሳሙ.፲፥፫/፡፡ ርእሰ አበው አብርሃምና ኖኅ በዚህ ተራራ ላይ ቀስተ ደመና ተተክሎ አይተዋል፡፡ ስለዚህም ኖኅ ‹‹መካነ ብርሃን፤ የብርሃን ቦታ›› ብሎ ጠርቶታል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በተወለደ በ፴፪ ዓመት ከ፯ ወር ከ፲፭ ቀን፣ በዘመነ ማቴዎስ፣ በወርኃ ነሐሴ በዕለተ እሑድ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ገልጧል /መር አፈወርቅ ተክሌ እንደ ጠቀሱት/፡፡

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው ጌታችን ‹‹ከስድስት ቀን በኋላ›› ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደዚህ ተራራ (ደብረ ታቦር) ወጥቷል /ማቴ.፲፯፥፩/፡፡ ከዚህ ላይ ‹‹ከስድስት ቀን በኋላ›› የሚለው ሐረግ ጌታችን ሐዋርያቱን በቂሣርያ ‹‹ሰዎች ክርስቶስን ማን ይሉታል?›› ብሎ ከጠየቀበት ከነሐሴ ፯ ቀን በኋላ ያሉትን ቀናት ያመለክታል፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠው ከተስእሎተ ቂሣርያ በ፮ኛው ቀን (ነሐሴ ፲፫ ቀን) ነውና /፯+፮=፲፫/፡፡ ሙሴ ከመቃብር ኤልያስም ከብሔረ ሕያዋን በተገኙበት በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱ በተገለጠ ጊዜ ፊቱ እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም አጣቢ ሊያነጣው እስከማይችል ድረስ እንደ በረዶ ነጭ ኾነ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ›› እያለ ሲናገር ክርስቶስ በሰው እጅ የተሠራ ቤት የማያስፈልገው አምላከ ሰማይ ወምድር መኾኑ ይገለጥ ዘንድ ሰማያዊ ብሩህ ደመና ጋረደቻው፤ ከሰማይም ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት›› የሚል ቃል ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ መጣ፡፡ ‹‹እርሱን ስሙት›› ማለቱም ጌታችን ዓለምን ለማዳን እንደሚሞት ሲናገር ቅዱስ ጴጥሮ ‹‹አይኹንብህ›› ብሎት ነበርና ‹‹እሞታለሁ›› ቢላችሁ ‹‹አትሞትም›› አትበሉት ሲል ነው፡፡ ሙሴና ኤልያስም ከጌታችን ጋር ሲነጋገሩ ተሰሙ፤ ስለ ክርስቶስ የተናገሩት ትንቢትም በደብረ ታቦር ተረጋገጠ፡፡ በዚህ ጊዜ የፊቱን ግርማ ለማየትና የመለኮትን ድምፅ ለመስማት አልተቻላቸውምና ሙሴ ወደ መቃብሩ፣ ኤልያስም ወደ መጣበት ተመለሱ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም የመለኮትን ፊት አይተው መቆም አልተቻላቸውምና ደንግጠው ወደቁ፡፡

በብሉይ ኪዳን ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ቆይቶ ወደ ሕዝቡ ሲሔድ ፊቱ ያንጸባርቅ እንደ ነበርና የእስራኤላውያን ዓይን እንዳይጎዳ ሙሴ ፊቱን ይሸፍን እንደ ነበር ተጽፏል፡፡ ሙሴ የእግዚአብሔርን ድምፅ በመስማቱ ብቻ ፊቱ ያንጸባርቅ ከነበረ እግዚአብሔርንፊት ለፊት በዓይን ተመልክቶ ብርሃኑን መቋቋም ምን ያህል ከባድ ይኾን?

ከዚህ በኋላ ሐዋርያት ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው የኾነው ክርስቶስ ሙሴን ከመቃብር አንሥቶ፤ ኤልያስንም ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ በደብረ ታቦር እንዳወጣቸው ዐወቁ፡፡ ጌታችንም ሐዋርያቱን አጽናንቶ ኃይሉን ብርታቱን ካሳደረባቸው በኋላ ከንቱ ውዳሴን የማይሻ አምላክ ነውና፤ ደግሞም መናፍቃን ምትሐት ነው ብለው እንዲሰናከሉበት አይፈልግምና ኹሉም በጊዜው እስኪለጥ ማለትም ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የክርስቶስን አምላክነቱን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን፣ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን ለዓለም እስኪሰብኩ ድረስ በደብረ ታቦር ያዩትንና የሰሙትን ለማንም እንዳይነግሩ አዝዟቸዋል /ማቴ.፲፯፥፩-፱፤ ማር.፱፥፪-፱/፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በዘመነ ኦሪት ከሙሴ ጋር ቃል በቃል በደመና በሚነጋገርበት ጊዜ ነቢዩ ሙሴ ‹‹… ጌትነትህን (ባሕርይህን) ግለጽልኝ›› ሲል እግዚአብሔርን ተማጽኖት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ለሙሴ ‹‹በባሕርዬ ፊቴን አይቶ የሚድን የለምና ፊቴን ማየት አይቻልህም፡፡ … እኔ በምገለጽልህ ቦታ ዋሻ አለና በብርሃን ሠረገላ ኾኜ እስካልፍ ድረስ በዋሻው ውስጥ ቁመህ ታየኛለህ፡፡ በባሕርዬ አይተህ ደንግጠህ እንዳትሞት በብርሃን ሠረገላ ኾኜ እስካልፍ ድረስ ቀዳዳ ባለው ዋሻ እሠውርሃለሁ፡፡ በብርሃን ሠረገላ ኾኜ ካለፍሁ በኋላ እጄን አንሥቼልህ ከወደ ኋላዬ ታየኛለህ እንጂ በባሕርዬ ግን ፊቴን ማየት አይቻልህም›› የሚል ምላሽ ሰጥቶት ነበር /ዘፀ.፴፫፥፲፫-፳፫/፡፡ ይህም በፊት የሚሔድ ሰው ኋላው እንጂ ፊቱ እንደማይታይ ጌታም በባሕርዩ አለመገለጡን ያስረዳል፡፡ ምሥጢሩም አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በደብረ ታቦር በባሕርዩ እስኪገለጥለት ድረስ ሙሴ በመቃብር ተወስኖ እንደሚቆይ ያጠይቃል /ትርጓሜ ኦሪት ዘፀአት/፡፡

በብሉይ ኪዳን ባሕርዩን ለሙሴ የሠወረ አምላክ በደብረ ታቦር በመለኮታዊ ባሕርዩ ተገልጧል፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረው የመገለጥ ተስፋ ተፈጽሞ ይኸው አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር ኾኗል፡፡ ‹‹ጀርባዬን ታያለህ›› ያለ እርሱ ለሙሴ በደብረ ታቦር በክበበ ትስብእት ታይቷል፡፡ ነቢዩ ሙሴ እንደ ተመኘው በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን በተመለከተ ጊዜም ‹‹ፊቴን ማየት አይቻልህም›› ያለው ቃሉ ይፈጸም ዘንድ የክርስቶስን ፊት ማየት ስላቃተው ‹‹ትኄይሰኒ መቃብርየ፤ መቃብሬ ትሻለኛለች›› ብሎ ወደ መቃብሩ ተመልሷል፡፡ ‹‹ሞትን አይቀምስም›› የተባለለት፣ ክርስቶስ ለፍርድ ከመምጣቱ አስቀድሞ ወንጌልን የሚሰብከው ኤልያስ ብርሃነ መለኮቱን በግልጥ ለመመልከት ችሏል፡፡ መለኮቱን አይቶ መቆም አልቻለው ቢልም ወደ ብሔረ ሕያዋን ተመልሷል፡፡ የክርስቶስን መሞት በሥጋዊ ስሜት ተረድቶ ‹‹አይሁንብህ›› ያለው ቅዱስ ጴጥሮስና መለኮታዊ ሥልጣንን የተመኙት ቅዱሳን ያዕቆብና ዮሐንስ አብሯቸው እየኖረ የማያውቁት ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መኾኑን ተረድተዋል፡፡ ተረድተውም ደንግጠው ወድቀዋል፡፡

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በተራራ የገለጠበት ምሥጢር

ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በመንደር ሳይኾን በተራራ ያደረገው ስለምን ነው ቢሉ ተራራ የወንጌል ምሳሌ ነው፡፡ ተራራ ሲወጡት ያስቸግራል፤ ከወጡት በኋላ ግን ጭንጫውን፣ ግጫውን ሲያሳይ ደስ ያሰኛል፡፡ ወንጌልም ሲማሯት ታስቸግራለች፤ ጽድቅና ኀጢአትን ለይታ ስታሳውቅ ግን ደስ ታሰኛለችና በተራራ ትመሰላለች፡፡ ደግሞም ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፤ ተራራን በብዙ ፃዕር እንዲወጡት መንግሥተ ሰማይንም በብዙ መከራ ያገኟታልና፡፡ ‹‹እስመ በብዙኅ ፃማ ሀለወነ ንባኣ ለመንግሥተ እግዚአብሔር፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ አለን›› እንዲል /ሐዋ.፲፬፥፳፩-፳፪/፡፡

ትርጓሜ ወንጌል እንደሚያስረዳው ጌታችን መለኮቱን የገለጠበት ተራራ ታቦር መኾኑን ሐዋርያት በሲኖዶስ ጠቅሰውታል፡፡ ምሥጢሩን በሌላ ተራራ ሳይገልጥ ስለምን በደብረ ታቦር ገለጠ ቢሉ ትንቢቱ፣ ምሳሌው እንዲፈጸም ነው፡፡ ትንቢቱ፡- ‹‹ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ፤ ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል›› የሚል ነው /መዝ.፹፰፥፲፪/፡፡ ይኸውም ጌታችን በደብረ ታቦር ባደረገው መገለጥ ተራሮች እንደ ሰው መደሰታቸውን፤ አንድም ልባቸው እንደ ተራራ በኑፋቄ የገዘፈ አይሁድና አሕዛብ ወይም መናፍቃን በተአምራቱ መማረካቸውን ያጠይቃል፡፡ ምሳሌው፡- በታቦር ተራራ ባርቅ ሲሳራን ድል ነስቶበታል /መሣ.፬፥፲፬-፲፮/፤ ጌታችንም በልበ ሐዋርያት (በልበ ምእመናን) ያደረ ሰይጣንን ድል የሚነሳበት ነውና ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር ገልጧል፡፡ አንድም ደብረ ታቦር የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናት፤ በደብረ ታቦር ነቢያትም ሐዋርያትም እንደ ተገኙ መንግሥተ ሰማያትንም በአንድነት ይወርሷታልና፡፡

ስለ ምን ከነቢያት ሁለቱን፣ ከሐዋርያት ሦስቱን ብቻ ወደ ተራራ ይዞ ወጣ?

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከነቢያት ሁለቱን፣ ከሐዋርያት ሦስቱን ብቻ ይዞ ወደ ደብረ ታቦር ይዞ የወጣበት ምሥጢር አንደኛ በብሉይ ኪዳን ሙሴ ‹‹ፊትህን አሳየኝ›› ብሎት ነበርና መለኮቱን ለሙሴ ለመግለጥ /ዘፀ.፴፫፥፲፫-፳፫/፤ ሁለተኛ ‹‹የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ›› ሲል የተናገረለት ኤልያስ በሕይወተ ሥጋ መኖሩን ለማሳየት /ማቴ.፲፮፥፳፰/፤ ደግሞም ኤልያስን ‹‹አንተሰ ስምዓ ትከውነኒ በደኃሪ መዋዕል፤ በኋለኛው ዘመን ምስክር ትኾነኛለህ›› /ሚል.፬፥፭/ ብሎት ነበርና የኤልያስን ምስክርነት ለማረጋገጥ፤ ሦስተኛ ጌታችን እንደሚሞት ሲናገር ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹አይኹንብህ›› ብሎት ነበርና ‹‹እርሱን ስሙት›› የሚለውን የእግዚአብሔርን አብ ምስክርነት ለማሰማት /ማቴ.፲፮፥፳፪፣ ፲፯፥፭/፤ አራተኛ አይሁድ ክርስቶስን ‹‹ከነቢያት አንዱ ነው›› /ማቴ.፲፮፥፲፬/ ይሉት ነበርና የነቢያት ጌታ መኾኑን ለማጠየቅ ነው፡፡

ከመዓስባን ሙሴን፣ ከደናግል ደግሞ ኤልያስን ማምጣቱም ደናግልም መዓስባንም መንግሥተ ሰማያትን በአንድነት እንደሚወርሱ ያጠይቃል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው›› ሲል መናገሩም ጌታችን በተአምራቱ ሲራቡ እያበላቸው፣ ሲጠሙ እያጠጣቸው፣ ሲታመሙ እየፈወሳቸው፣ ቢሞቱ እያነሣቸው፤ ሙሴም እንደ ቀድሞው ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላትን እየገደለ፤ ኤልያስ ደግሞ ሰማይን እየለጎመ፣ እሳት እያዘነመ፣ ዝናም እያቆመ በደብረ ታቦር ለመኖር መሻቱን ያመላክታል፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሦስት ጎጆ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ፤ አንዱን ለሙሴ፤ አንዱን ለኤልያስ›› በማለት የእርሱንና የሁለቱን ጎጆ ሳይጠቅስ አርቆ መናገሩ በአንድ በኩል ትሕትናውን ማለትም ‹‹ለእኛ›› ሳይል ነቢያቱን አስቀድሞ ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን አለመጥቀሱን፤ እንደዚሁም ከጌታችን ጋር ለመኖር ያለውን ተስፋ ሲያመለክት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቅዱስ ጴጥሮስን ድክመት ማለትም የክርስቶስን አምላክነት በሚገባ አለመረዳቱን ያሳያል፡፡ ጌታችንን በተራራ ላይ በሰው ሠራሽ ቤት ይኖር ዘንድ ጠይቆታልና፡፡

ጌታችን ስምንቱን ከተራራው ሥር ትቶ (ይሁዳ ሳይቈጠር) ሦስቱን ሐዋርያት ወደ ተራራ ይዞ የወጣበት ምክንያት በአንድ በኩል ያዕቆብና ዮሐንስ ‹‹በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ፣ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን›› /ማር.፲፥፴፯/ ሲሉ መንግሥቱን ፈልገው ነበርና የልባቸውን መሻት ለመፈጸም ሲኾን በሌላ ምሥጢር ደግሞ ይሁዳን ወደ ተራራው ይዞ ለመውጣት ባለመሻቱ፤ ለይቶ እንዳይተወውም ‹‹ከምሥጢረ መንግሥቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት›› እንዳይለው (ምክንያት ለማሳጣት) ነው፡፡ ‹‹ያእትትዎ ለኀጥእ ከመ ኢይርአይ ስብሐተ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔርን ምስጋና (ክብር) እንዳያይ ኀጢአተኛውን ሰው አያስቀርቡት›› ተብሎ ትንቢት ተነግሮበታልና ይሁዳ የእግዚአብሔርን ክብር ለማየት አልበቃም፡፡ ኾኖም ግን በደብረ ታቦር የተገለጠው ምሥጢር ከተራራው በታች ለነበሩት ለስምንቱ ደቀ መዛሙርትም ተገልጦላቸዋል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ በደብረ ታቦር ጌታችን በዮርዳኖስ ሲጠመቅ የተገለጠው ምሥጢረ ሥላሴና የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት ገሃድ ኾኗል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ የኾነችው ደብረ ታቦር ምሥጢረ ሥላሴ ተገልጦባታል፤ የክርስቶስ አምላክነት ተረጋግጦባታል፡፡ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱ እንደ ተገለጠና የእግዚአብሔር አብ ምስክርነት እንደ ተሰማ ኹሉ ዛሬም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ሥላሴ ሲነገር፣ የመለኮት ሥጋና ደም ሲታደል ይኖራል፡፡ በደብረ ታቦር ነቢያትም፣ ሐዋርያትም እንደ ተገኙ ኹሉ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ብሉይና ሐዲስ ኪዳን ይሰበካል፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴ የሚፈጽሙ ልዑካን አምስት መኾናቸውም በደብረ ታቦር የተገኙትን ሙሴን፣ ኤልያስን፣ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ያስታውሱናል፡፡ ዘወትር በቤተ መቅደሱ የሚፈተተው ኅብስትና የሚቀዳው ወይን ደግሞ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን የገለጠው የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡

ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በዓላት መካከል አንደኛው የኾነው በዓለ ደብረ ታቦር ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበትና ታላቅ የአስተርእዮ ምሥጢር የተፈጸመበት በዓል በመኾኑ ይህንን የመሥራቿን የክርስቶስን በዓል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን ‹‹አማን በአማን ተሰብሐ በደብረ ታቦር›› እያለች በድምቀት ታከብረዋለች፡፡ የአብነት ት/ቤት ደቀ መዛሙርት፣ በሰንበት ት/ቤትና በማኅበራት የሚያገለግሉ ምእመናንም ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠ አምላክ ብርሃነ ምሥጢሩን በየልቡናቸው እንዲገልጥላቸው ለመማጸን ጸበል ጸሪቅ አዘጋጅተው በዓሉን ይዘክሩታል፡፡ በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ከሙታን ተነሥቶ ከዘመናት በፊት የተመኘውን የአምላኩን ፊት ለማየት የታደለው ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተወለደውም በዚህች ዕለት ነው፡፡ እኛም እግዚአብሔር በደብረ ታቦር ያደረገውን አስተርእዮ ለማስታዎስ ይህንን ጽሑፍ አዘጋጀን፡፡

ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጠ ጌታ በእያንዳንዳችን ልቡናም ማስተዋሉን፣ ምሥጢሩን፣ ጥበቡን ይሳልብን፤ ያሳድርብን፡፡ ከቅዱሳኑ ጋር መንግሥቱን እንዲያወርሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ነሐሴ ፲፫ ቀን፡፡

መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ በመ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ ገጽ ፫፻፲፬-፫፻፲፯ እና ፬፻፩፡፡

ትርጓሜ ወንጌለ ማቴዎስ፣ ምዕ.፲፯፥፩-፱፡፡