ነገረ ድኅነት በመጽሐፍ ቅዱስ – ካለፈው የቀጠለ

በዳዊት አብርሃም

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ከዚህ ቀጥለን ደግሞ የጴጥሮስን እና የይሁዳን መልእክት እንመልከታለን፤

  • “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥ ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን ዐመድ እስኪኾኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ፥ ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፥ በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል” (፪ኛ ጴጥ. ፪፥፮)፡፡
  • “ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ፦ እነሆ፥ ጌታ በዂሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ዂሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ዂሉ ‹ኃጢአተኞችን ዂሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል› ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ” (ይሁዳ፣ ቍጥር ፲፬-፲፭)፡፡

እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ ጥቅሶች በብዛት አሉ፡፡ ይህን ዂሉ ከተመለከትን በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አንዲት ቦታ ላይ የጻፋትን አንዲት ጥቅስ ብቻ መዝዘን በመውሰድ ኃጢአትን “የሚያደርጉ ይጸድቃሉ” ወደሚል ስሕተት ከመውደቅ እንጠበቃለን፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ በሌላ ቦታ እንዲህ ሲል አስተምሯልና፤ “ወይስ ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢኾኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝራዎች ወይም ቀራጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌባዎች ወይም ገንዘብ የሚመኙ ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” (፩ኛ ቆሮ. ፮፥፱-፲)፡፡

በአንድ ጥቅስ መመርኮዝ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ አይደለም፡፡ በዚህ መልክ ድምዳሜ ላይ መድረስም ኦርቶዶክሳዊ መንገድ አይደለም፡፡ አንድ ጥቅስ አንሥቶ የኾነ ዐሳብ መሰንዘር የሚፈልግ ሰው ቢያጋጥም ጥቅሱ የቱንም ያህል ግልጽ መልእክት ያለው ቢኾን እንኳን “እንዲህ ለማለት ነው” ተብሎ ለመደምደም አያስችልም፡፡ ኦርቶዶክሳዊ የኾነ ሰውም በተነሣው ርእሰ ጉዳይ ላይ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምን እንደሚሉ ለማወቅ ይጥራል፡፡ ዐሳቡን የተሟላ የሚያደርጉት በጉዳዩ ላይ ሌሎች የቅዱደሳት መጻሕፍት ክፍሎች ተሟልተው ሲቀርቡ ነው፡፡ ሌሎች ጥቅሶች አንዱን ጥቅስ ግልጽና የማያሻማ እንደዚሁም የተሟላ ያደርጉታል፡፡

ይህንም በሚቀጥሉት ስለ ነገረ ድኅነት ከተጻፉት ጥቅሶች አንጻር እንመልከት፤ “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም” (ኤፌ. ፪፥፰-፱)፡፡ ይህ ኃይለ ቃል መልእክት “ሥራ አያስፈልግም፤ እምነትና ጸጋ ብቻቸውን ለመዳን በቂ ናቸው” የሚል ይመስላል፡፡ ነገር ግን ሳንቸኩል አንድ ቍጥር ወረድ ብለን ንባባችንን ብንቀጥል እንደዚህ የሚል መልእክት እገኛለን፤ “እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን” (ኤፌ. ፪፥፲)፡፡

ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት፤ “በጸጋ ከኾነ ግን ከሥራ መኾኑ ቀርቶአል፤ ጸጋ ያለዚያ ጸጋ መሆኑ ቀርቶአል” (ሮሜ. ፲፩፥፮)፡፡ አሁንም በዚህ ጥቅስ ሳንወሰን በዚያው ምዕራፍ ወረድ ብለን ንባባችንን እንቀጥል፤ “መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ፤ አንተም ከእምነት የተነሣ ቆመሃል፡፡ ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ፡፡ እግዚአብሔር እንደ ተፈጠሩት ለነበሩት ቅርንጫፎች የራራላቸው ካልኾነ ለአንተ ደግሞ አይራራልህምና፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ” (ሮሜ. ፲፩፥፳-፳፪)፡፡

ይህ ማለት ምን ማለት ነው? በክርስቶስ ደም ዂላችንም መዳንን አግኝተናል (ድነናል)፡፡ ኾኖም ከእርሱ ጋር ካልተጣበቅን ማለትም እስከ መጨረሻው ድረስ ከእርሱ ጋር እንድንኖር የሚያደርገንን የጽድቅ ሥራ መሥራት ካልቻልን የመቆረጥ ቅጣት ይደርስብናል፡፡ ከግንዱ ተቆርጦ ዕጣው መድረቅና መጠውለግ እንደ ኾነበት ቅርንጫፍ እንኾናለን፡፡

አሁንም ሦስተኛ ምሳሌ እንጨምር፤ “ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል፡፡ በየትኛው ሕግ ነው? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፥ በእምነት ሕግ ነው እንጂ። ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቈጥራለንና” (ሮሜ. ፫፥፳፯-፳፰)፡፡ ይህን ጥቅስ ስናነብ “ለመዳን ሥራ አያስፈልግም” ከሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ እንዳንቸኩል ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ሌላ ቦታ መሔድ ሳያስፈልገን ጥቂት ብቻ ዝቅ ብለን እናንብበው፤ “እንግዲህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? አይደለም፤ ሕግን እናጸናለን እንጂ” (ሮሜ. ፫፥፴፩)፡፡

አራተኛ ምሳሌ “ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚኾነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም” (ቲቶ ፫፥፬-፮)፡፡ ይህ ጥቅስ መዳን የሚገኘው በጥምቀትና በመንፈስ ቅዱስ ሥራ መኾኑን እንደሚገልጥ ልብ እንበል፡፡

ይህም መዳን “በእምነት ብቻ” የሚለውን ኑፋቄ የሚቃወም ዐሳብ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ሐዋርያው የሥራን አስፈላጊነት ሲገልጥ እንዲህ ይላል፤ “ቃሉ የታመነ ነው፤ እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፥ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ፡፡ ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው” (ቲቶ ፫፥፰)፡፡

አንድን ጥቅስ አንሥተን ስንናገር ያን ማድረጋችን ለጥቅማችን እንኳን ቢኾን በዚያ በአንዱ ጥቅስ ላይ ብቻ ልንመሠረት አይገባንም፡፡ ለምሳሌ “ጻድቅ እንደ ኾነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ዂሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ ዕወቁ” (፩ኛ ዮሐ. ፪፥፳፱) በሚለው ኃይለ ቃል ውስጥ ጽድቅን ማድረግ አስፈላጊ መኾኑ ተገልጧልና “ለመዳን ጽድቅ ማድረግ በቂ ስለ ኾነ እምነት፣ ጥምቀትና ሌሎች ምሥጢራት አያስፈልጉም” ወደሚል ጽንፈኛ አቋም ልንወድቅ አይገባም፡፡

ሐዋርያው በሌላ ቦታ ደግሞ ፍቅር ከሞት ወደ ሕይወት የሚመልሰን መኾኑን ያስተምራል፡፡ “እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ኾንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል” (፩ኛ ዮሐ. ፫፥፲፬)፡፡ በዚህ ጥቅስ ላይ ተመሥርተን ደግሞ “ለመዳን ወንድሞችን መውደድ በቂ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ብንደርስ አሁንም ልክ አይደለንም፡፡

ሐዋርያው ስለ ፍቅር ታላቅነት ደጋግሞ ሲያስተምር “እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል” በማለት አስተምሯል (፩ኛ ዮሐ. ፬፥፲፮)፡፡ ስለ ፍቅር ለማስተማር ብለን እንኳን ቢኾን በዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ልንመሠረትና ሌላውን ችላ ልንል  አይገባንም፡፡ ለምሳሌ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ፍቅር ሲያስተምር “ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ዂሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” ሲል ፍቅር ከእምነት እንደሚበልጥ ተናግሯል (፩ኛ ቆሮ. ፲፫፥፪)፡፡

በተመሳሳይ መልኩ “እንዲህም ከኾነ፥ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው” በማለት የፍቅርን ታላቅነት አስረድቷል (፩ኛ ቆሮ. ፲፫፥፲፫)፡፡ ስለዚህ “መዳን በእምነት ብቻ” የሚል ሰው እነዚህን ጥቅሶች ምን ሊያደርጋቸው ይችላል? በአንጻሩ በአንድ ጥቅስ ተወስኖ መደምደም የለመደ ሰው የፍቅርን ታላቅነት የሚያወሳውን ጥቅስ በመምዘዝ “መዳን በፍቅር ነው” ብሎ እንዳይስት መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡

ጌታችን ለወጣቱ ባለ ጸጋ “ወደ ሕይወት ልትገባ ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ” (ማቴ. ፲፱፥፲፯) ባለው ላይ ብቻ ተመሥርተን “ለመዳን መንገዱ ይሔ ብቻ ነው” ማለት ትልቅ ስሕተት ነው፡፡ ያለ እምነት የሚፈጸም መልካም ሥራ ብቻውን እንደማያድን አውቀን፣ “ለመዳን ሕግጋትን መጠበቅ ይበቃል” ከሚል ስሕተት ወጥተን፣ እንደዚሁም ስለ እምነትና በጸጋው ስለ መዳን በሚናገሩ አንዳንድ ጥቅሶች ላይ ብቻ ማተኮሩን ትተን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር በትዕግሥትና በጥንቃቄ ማጥናት እንዳንሳሳት ይረዳናል፡፡

ከዚሁ ዂሉ ጋርም “እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይኾን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንኾን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና፤ መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል” የሚለውን የሐዋርያውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል (፪ኛ ቆሮ. ፫፥፮)፡፡

የመዳንን ትምህርት ለመረዳት በፊደል ሳይኾን በመንፈስ ኾነን፣ በአንድ ጥቅስ ላይ ብቻ ሳንወሰን ወይም ጉዳዩን ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ሳንመለከት በስፋትና በጥልቀት የኾነውን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት በማወቅ መጽናት፣ ለሚጠይቁንም ምላሽ መስጠት ያስፈልገናል፡፡ በአንድ ጥቅስ ላይ ተመሥርቶ ነገረ ድኅነትን ለማወቅ መሞከር ከባድ ስሕተት ውስጥ እንደሚጥለን ለማወቅ አንድ ምሳሌ ተመልክተን ጽሑፋችንን እናጠቃልላለን፤

መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ቦታ “የጌታን ስም የሚጠራ ዂሉ ይድናል” ይላል (ሮሜ. ፲፥፲፮)፡፡ ይህን ጥቅስ መሠረት አድርገን “የጌታን ስም ስለ ጠራን ብቻ እንድናለን” ብለን ብናስብ ከሚከተለው ጥቅስ ጋር እንጋጫለን፤ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ዂሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” (ማቴ. ፯፥፳፩)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ነገረ ድኅነት በመጽሐፍ ቅዱስ – የመጀመሪያ ክፍል

በዳዊት አብርሃም

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ስለ ነገረ ድኅነትም ኾነ ስለማናቸውም ሃይማኖታዊ ጉዳይ ስናጠና አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ብቻ መመርኮዝ የለብንም፡፡ አንዲቷን ጥቅስ ከአጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዐሳብ ለይተንና ከሌሎች ጥቅሶች ነጥለን መመልከት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ያደርሳል፡፡ ኦርቶዶክሳዊውን የነገረ ድኅነት አስተምህሮ የሚቃወሙና በተቃራኒውም ስሕተት የኾነ ትምህርት በማስተማር የሚከራከሩ ወገኖች በዚህ ዓይነቱ ስሕተት ሊጠመዱ የቻሉበት አንዱ ምክንያት በአንዲት ነጠላ ጥቅስ ላይ ሙጥኝ ብለው ሌሎቹን ግን ችላ ማለት ስለሚቀናቸው ነው፡፡ ደካማ ሰው አንድን ጥቅስ ብቻ ነጥሎ በማንጠልጠል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሲደርስ ብልህ፣ ጠቢብና ዕውቀት ፈላጊ ሰው ግን አንዱን ከአንዱ ጋር እያነጻጸረ በማጥናት፣ በመታገሥ ምርምሩን ይቀጥላል፡፡ በዚህም ትክክለኛ ዕውቀት ላይ ይደርሳል፤ እውነትን ወደ ማወቅም ይመጣል፡፡

ከነገረ ድኅነት አስተምህሮ አንጻር ይህን ነገር በምሳሌ እንመልከት፤ “እነርሱም ‹በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ› አሉት” (ሐዋ. ፲፮፥፲፫)፡፡ አንዳንዶች ይህን ጥቅስ በመምዘዝ “ለመዳን ማመን ብቻ በቂ ነው” ይላሉ፡፡ ይህን ንግግር ቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ ሲላስ በፊልጵስዩስ የእስር ቤት ጠባቂ ለነበረው ሰው የተናገሩት ኀይለ ቃል ነው፡፡ “ጥቅሱ የተነገረው ለማን ነው? ለምን ተነገረ? ከዚያስ ወረድ ብሎ ምን ይላል? ከሌሎች ጥቅሶች ጋር ያለው ተዛምዶ ምን ይመስላል?” ብለው ሳይጠይቁ ለውሳኔ መቻኮል ትክክል አይደለም፡፡ እስኪ ጥቅሱን በእርጋታ እንመርምረው፤

፩ኛ. ይህ ቃል የተነገረው ከአሕዛብ ወገን ለኾነ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው እምነት የለሽ ነው፡፡ ስለዚህም ምንም ዓይነት በጎ ሥራ ቢሠራ ዋጋ አያገኝም፡፡ ለመዳን አስቀድሞ ማመን አለበትና፡፡ ሳያምን ወደ ሌላ በጎ ሥራ ቢጓዝ መዳንን አያገኝምና፡፡ ስለዚህም ጳውሎስ እና ሲላስ አስቀድመው የመዳን በር የኾነውን ቃል ነገሩት፤ ‹‹እመን›› አሉት፡፡ እምነት ለመዳን የመጀመሪያው ደረጃ ነው፤ ሌሎች ለመዳን ከሰው የሚጠበቁት ዂሉ ከማመን በኋላ የሚመጡ ናቸው፡፡

፪ኛ. መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ የመጀመሪያ ደረጃ ተግባርን የሒደቱን አጠቃላይ ኹኔታ የሚያሳይ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ለዚህም ዓይነተኛው ምሳሌ ስምዖን አረጋዊ ነው፡፡ ስምዖን አረጋዊ “ዓይኖቼ በሰዎች ዂሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋል” (ሉቃ. ፪፥፴-፴፩) በማለት የተናገረው ጌታ ተሰቅሎ፣ ሞቶ የሚፈጽመውን ማዳን አይቶ አይደለም፡፡ እርሱ ለማየት የቻለው የጌታን መወለድ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የጌታችን መወለድ የማዳን ሥራው አካል መኾኑን ስለተረዳ “እንግዲህ ባርያህን አሰናብተው” አለ፡፡ የጳውሎስ እና የሲላስ ዐሳብም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለእስር ቤቱ ጠባቂ “አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችኁ” ሲሉ የእርሱና የቤተሰቡ መዳን በእርሱ ማመን ብቻ ፍጻሜ ያገኛል ብለው አይደለም፡፡ ነገር ግን በምግባር፣ በተጋድሎ፣ ምሥጢራትን በመፈጸምና በሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ፍጻሜ የሚያገኘውን የመዳን ጉዞ በእምነት እንደሚጀምር መናገራቸው ነው፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘኬዎስ የተናገረው ኃይለ ቃልም ተመሳሳይ መልእክት ያለው ነው፤ “እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤” (ሉቃ. ፲፱፥፱)፡፡ ይህ ማለት የዘኬዎስ የመዳን ጉዞ ዛሬ ተጀመረ ማለት እንጂ ዘኬዎስ ጌታን በመኖሪያ ቤቱ ተቀብሎ ስላስተናገደው ብቻ መዳንን ወርሷል ወይም ድኗል ማለት አይደለም፡፡

፫ኛ. ጳውሎስና ሲላስም ይህን ሲሉ አሁን ባመንክበት ቅጽበት ትድናለህ ማለታቸው ሳይኾን የመዳኑን መንገድ ይዘኸዋል ማለታቸው መኾኑን የሚያረጋግጥ አንዱ አባባል “ትድናለህ” ብለው በትንቢት አንቀጽ መናገራቸው ነው፡፡

፬ኛ. ሌላው የእርሱ እምነት ለመዳኑ የመጀመሪያ ርምጃ መኾኑን የምናውቀው “ቤተሰቦችህ ይድናሉ” በሚለው የሐዋርት ንግግር ነው፡፡ “እርሱ ባመነው ቤተሰቦቹ እንዴት ይድናሉ?” የሚል ጥያቄ ብናነሣ ሐዋርያት የተናገሩት አሁን በዚያ ቅጽበት ለሚኾነው ሳይኾን ከዚያ ቅጽበት ለሚጀመረውና ወደፊት ለሚጠናቀቀው መዳን መኾኑን እንረዳለን፡፡ እርሱ ካመነ በኋላ ቤተሰቦቹን ሲያሳምን ደግሞ እነርሱም ልክ እንደ እርሱ የመዳንን ጉዞ አንድ ብለው ይጀምራሉ፡፡ ይህም ማመን ለመላው ቤተሰብ የመዳን ጉዞ የመጀመሪያ ምዕራፍ መኾኑን ይገልጣል፡፡

፭ኛ. ኃይለ ቃሉን ዝቅ ብለን ስናነብም ይህን የሚያጠናክር ማስረጃ እናገኛለን፤ “ለእርሱና በቤቱም ላሉት ዂሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሯቸው። በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፤ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተሰዎቹ ዂሉ ጋር ተጠመቀ፤” (ሐዋ. ፲፮፥፴፪-፴፫)፡፡

“እመን፤ ትድናለህ” የሚለውን ኃይለ ቃል ብቻ መዝዘን በማውጣት “ለመዳን የሚያስፈልገው ማመን ብቻ ነው” ከሚል ድምዳሜ ከደረስን በተጠቀሱት ስሕተቶች ላይ እንወድቃለን፡፡ ይህም የበለጠ ግልጽ እንዲኾንልን ሌላ ምሳሌ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት፤

አንድ ወጣት ወደ ጌታችን ቀርቦ “መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ?” ሲል ጠየቀው (ማቴ. ፲፱፥፲፮)፡፡ ጌታችን ሲመልስለትም “እመንና ትድናለህ” አላለውም፡፡ ነገር ግን “ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ” ነው ያለው (ማቴ. ፲፱፥፲፯)፡፡ ታዲያ ከዚህ የወንጌል ጥቅስ ተነሥተን “ትእዛዞችን መጠበቅ (ሕግጋቱን መጠበቅ) ብቻውን ለመዳን በቂ ነው” ብሎ መደምደም ይቻላል? በፍጹም አንችልም፡፡ አንድ ጥቅስ ብቻ አንጠልጥሎ ለመደምደም መቸኮል ግን ይህን ከመሰለው ስሕተት ላይ ሊጥለን እንደሚችል ልብ እንበል፡፡

በዚሁ ጥቅስ ላይ ንባባችንን ስንቀጥል ጥያቄውን ያቀረበው ወጣት “እነዚህን ዂሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄያቸዋለሁ” ብሎ መለኮታዊውን ትእዛዝ መጠበቁን ሲያረጋግጥ እናገኘዋለን፡፡ እንግዲህ አስቀድሞ ጌታችን “ለመዳን መሥፈርቱ ትእዛዛትን መጠበቅ ነው” ብሎ የተናገረውን ይዘን አሁን ወጣቱ “‹ፈጽሜያቸዋለሁ› በሚል ምላሹ ምክንያት ድኗል” ብለን ልንደመድም አንችልም፡፡ ጌታችን ለወጣቱ “ፍጹም ልትኾን ብትወድ ሒድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፤ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ” በማለት ለመዳን ማድረግ የሚገባውን ዂሉ እንደ ነገረው መዘንጋት የለብንም (ማቴ. ፲፱፥፳፮)፡፡

ከዚህ ላይ ለመዳን እምነት ወይም ጸጋው አልተጠቀሰም፡፡ በዚህ ጥቅስ መሠረት ሕግጋትን መፈጸም ወይም በጎ መሥራት እንኳን ቢኾን በቂ አይደለም፡፡ ከዚያ ያለፈ ተግባር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በዚህ አንድ ጥቅስ ላይ ብቻ መመሥረትን የመረጠ ሰው “ያለውን ዂሉ ሸጦ ለችግረኞች አከፋፍሎ ጌታን ካልተከተሉ በቀር መዳን አይቻልም” ብሎ ለመደምደም ይገደዳል ማለት ነው፡፡

አንዳንድ ስሑታን ስለ ነገረ ድኅነት ሲከራከሩ የሚያነሡት ሌላው ጥቅስ “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ” የሚለው ኃይለ ቃል ነው (ሮሜ. ፭፥፩)፡፡ አንዳንዶች ይህን ጥቅስ እያነሡ “ከዚህ በላይ ማስረጃ ምን ትፈልጋለህ? በእምነት ብቻ እንደሚጸደቅ በግልጥ ተጽፏል፤ ይህን ጥቅስ ምን ታደርገዋለህ? ወይስ እንዴት ልትክደው ትችላለህ?” በሚል ዐሳብ ይከራከራሉ፡፡

የእኛ ምላሽም እንዲህ ነው፤ ይህንን ትምህርት አንክድም፤ አናስተባብልምም፡፡ ነገር ግን ለብቻው ነጥለን አንመለከተውም፡፡ እዚያው ከአጠገቡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጻፈው ሌላ ትምህርት አለና እርሱን አምጥተን አብረን እናጠናዋለን፡፡ ትምህርቱም እንዲህ የሚል ነው፤ “በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይደለም” (ሮሜ. ፪፥፲፫)፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ሐዋርያው ጽድቅ (መዳን) የሚገኘው ሕግን በማድረግ መኾኑን ያስተምረናል፡፡

ታዲያ በዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ተመሥርተን “መዳን ሕጉን በመተግበር ብቻ የሚገኝ ነው” ልንል እንችላለን? አንልም፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም የሐዋርያውን ጥቅሶች ሳንነጣጥል በአንድነት እንወስዳቸዋለን፡፡ ሐዋርያው በሁለቱም ቦታዎች በሮሜ. ፪፥፲፫ እና ፭፥፩ ላይ የጻፈልንን ለድኅነታችን አስፈላጊ የኾኑትን ተግባራት እንማራለን፡፡ በዚህ መሠረት ለመዳናችን ማመናችን የሚኖረውን ዋጋ መልካም ሥራ አይተካውም፤ እንደዚሁም መልካም ሥራ ለመዳናችን አስፈላጊ መኾኑ የእምነትን አስፈላጊነት አይሽረውም፡፡ “ሰው በእምነት ብቻ ሳይኾን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ፡፡ እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?” (ያዕ. ፪፥፳፬-፳፭) ተብሎ እንደ ተጻፈው ለመዳን ሁለቱንም እምነትንና ሥራን አዋሕደን መያዝ እንዳለብን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ሌላ ኃይለ ቃል ደግሞ እንመልከት፤ “ነገር ግን ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ኾኖ ይቈጠርለታል” (ሮሜ. ፬፥፭) በዚህ ኃይለ ቃል መነሻነት ሌሎቹን የትምህርት ዓይነቶች ወይም ኃይለ ቃሉን በምልዓት ለመረዳት ስንሞክር አንድ ሰው ኃጢአተኛ ኾኖ ሳለ፣ ኃጢአት መሥራቱንም ሳያይተው ወይም ንስሐ ሳይገባ “ይጸድቃል” ብለን መደምደም እንችላለን? ይህንን ኃይለ ቃል በትክክል ለመረዳት ጥቅሱን ግልጽ ሊያደርጉ የሚችሉ ሌሎች ነጥቦችን መረዳት ይኖርብናል፡፡

ለምሳሌ ከዚያው ከሮሜ መልእክት አንድ ሌላ ጥቅስ እንመልከት፤

  • “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ዂሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል” (ሮሜ. ፩፥፲፰)፡፡
  • “ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለ ጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ” (ሮሜ. ፪፥፭)፡፡

ይቆየን

የጌታችን መከራ በሊቃውንት አንደበት

መጋቢት ፳፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም 

‹‹ታመመ፤ ሞትን ከተቀበለበት ከሥጋ ተዋሕዶ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ለሥጋውያን ሞተ፣ ባሕርየ መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በማኅፀን ካደረ ጀምሮ ሥጋ ገንዘቡ እንደመሆኑ በሥጋ ይኸንን ሥርዓት ፈጸመ፡፡ ለማይመረመር ለመለኮቱ ባሕርይ እንደሚገባ ደግሞ እርሱ ኅብስት አበርክቶ ዂሉን ያጠግባል፡፡ አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም፤ አያንቀላፋም፤ አይታመምም፤ አይሞትም፤ ሕይወትን ለዂሉ ይሰጣል፡፡ ዳግመኛ በዚያ በሲኦል ተገዝተው ያሉ ነፍሳትን ያድን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወረደ፤ በመለኮቱም ሲኦልን በዘበዘ፤›› (የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ)፡፡

‹‹እጆቹን፤ እግሮቹን በተቸነከረባቸው ችንካሮች መወጋቱንም እናምናለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስእርሱ ደዌያችንን ወሰደሕማማችንንም ተሸከመ፤ እኛን ለማዳን ኃጢአታችንንም ለማስተስረይ መከራ ተቀበለእንዳለ፤ በባሕርዩ ሕማም የሌለበት ሲኾን በሥጋ የታመመ ነው፡፡ በእርሱ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ድነናል፡፡ በተገረፈና በተቸነከረም ጊዜ በመከራው መለኮትን ሕማም ተሰማው የሚል ሰው ቢኖር የተለየ የተወገዘ ይሁን፤›› (ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ)፡፡

‹‹እርሱ መቼም መች ከመለኮቱ ሳይለይ የሰውነትን ሥራ ገንዘቡ አደረገ፡፡ ይኸውም መራብ፣ መጠማት፣ መንገድ በመሔድ መድከም፣ በመስቀል ላይ መሰቀል፣ በብረት ችንካር መቸንከር ነው፡፡ በሰውነቱ መቸም መች ሰው ነው፤ በአምላክነቱም ሰውን የፈጠረ ነው፡፡ ነገር ግን ከማይከፈል ተዋሕዶ በኋላ መከፈል የለበትም፡፡ ሰው እንደ መኾኑ ስለ እኛ የታመመው፣ የሞተው እርሱ ነው፡፡ በመለኮቱ ግን መቸም መች አይታመምም፤ አይሞትም፡፡ ሕማምንና ሞትንም አይቀበልም፡፡ በሞቱ ሞትን ያጠፋው እርሱ ነው፡፡ ሲኦልንም የበዘበዘው እርሱ ነው፤›› (የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ዲዮናስዮስ)፡፡

‹‹ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ ያን ጊዜ በሲኦል ፈጥኖ ብርሃን ታየ፡፡ ጌታችን በአካለ ሥጋ ያይደለ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሔደ፡፡ ሲኦል ተነዋወጠች፤ መሠረቶቿም እፈርስ እፈርስ አሉ፡፡ ምድርን ያለ ጊዜዋ እንዳታልፍ ክብርት ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ፡፡ ከኅልፈት ጠበቃት በእርሷ ያለውንም ዂሉ ጠበቀ፡፡ ስለ ፍጥረት ሥጋውን በመስቀል እንደ ተሰቀለ ተወው፡፡ ነፍሱ ግን ወደ ሲኦል ወረደች ከዚያ ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አዳነች፤ ሲኦልንም በዘበዘች፡፡ ፍጥረትንም ዂሉ ገንዘብ አደረገች፡፡ ሥጋውም በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፤›› (የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስ)፡፡

‹‹ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፣ በባሕርዩ ከአባቱ ጋር አንድ የሚኾን፡፡ ዂሉ የተፈጠረበት፤ ያለ እርሱ ግን ምንም ምን የተፈጠረ የሌለ፤ በሰማይ በምድር ያለውም ቢኾን፡፡ እኛን ስለ ማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ኾነ፡፡ የሠላሳ ዘመንልማሳ ኾኖ በጲላጦስ የሹመት ዘመን ስለ እኛ ተሰቀለ፤ ስለ እኛም ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤›› (ሠለስቱ ምእት)፡፡

‹‹ምትሐት ያይደለ በእውነት ተራበ፤ ተጠማ፡፡ ዳግመኛም ከኃጥአን፣ ከመጸብሐን ጋር በላ፤ ጠጣ፡፡ ያቀረቡለትንም በላ፡፡ ራሱን አሳልፎ ለመስቀል ሰጠ፡፡ እጁን፣ እግሩን ተቸነከረ፤ ጐኑን በጦር ተወጋ፡፡ ከእርሱም ቅዱስ ምሥጢር የተገለጠበት ደምና ውኃ ፈሰሰ (ወጣ)›› (ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ)፡፡

‹‹የሚሠዋ በግ እርሱ ነው፤ የሚሠዋ ካህን እርሱ ነው፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው፡፡ በፈቃዱ መከራን በሥጋው የተቀበለ መከራንም የታገሠ እርሱ ነው፡፡ እንደ በግ ሊሠዋ መጣ፤ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንደማይናገር አልተናገረም፡፡ በአንደበቱ ሐሰት አልተገኘበትም፤›› (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ)፡፡

‹‹በሥጋ መወለድ፣ በመስቀል መከራ መቀበል፣ መሞት፣ መነሣት፣ ገንዘቡ የኾነ እርሱ እግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ስለዚህ በመስቀል ላይ ሳለ ከጥንት ጀምሮ በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤›› (ሰማዕቱ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ፊልክስ)፡፡

‹‹ሙሴም ሞትን ያጠፋ ዘንድ አልቻለም፤ እርሱንም ይዞ ገዛው እንጂ፡፡ ከእርሱም በኋላ የተነሡ ነቢያትንም ሞት ገዛቸው እንጂ፡፡ ክርስቶስ ግን በቸርነቱ ለዂሉ ሕይወትን ሰጠ፤›› (የሮማ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ አቡሊዲስ)፡፡

‹‹በመስቀል በሥጋ ተሰቅሎ ሳለ ለመለኮት ከሥጋ መለየት የለበትም፡፡ አንዲት ሰዓትም ቢሆን የዐይን ጥቅሻ ያህል ስንኳ ቢሆንም መለኮት ከትስብእት አልተለየም፣ በመቃብር ውስጥ በሰላም መለኮት ከትስብእት አልተለየም (የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አዮክንድዮስ)፡፡

‹‹ከአብ ጋር አንድ እንደ መኾንህ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፡፡ ከእኛ ጋር አንድ እንደ መኾንህ በፈቃድህ የሞትህ አንተ ነህ፡፡ በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፡፡ በኪሩቤል ላይ ያለህ አንተ ነህ፡፡ ከሙታን ጋር በመቃብር የነበርህ አንተ ነህ፡፡ በአንተ ሕማምና ሞትም ድኅነት ተሰጠ፡፡ ከሙታን ጋር የተቈጠርህ አንተ ነህ፡፡ ለሙታንም ትንሣኤን የምትሰጥ አንተ ነህ፡፡ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፡፡ በዘመኑ ዂሉ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምትኖር አንተ ነህ፡፡ በመለኮት ሕማም ሳይኖርብህ በሥጋ የታመምህ አካላዊ የእግዚአብሔር ቃል አንተ ነህ፤›› (የኪስኪስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤራቅሊስ)፡፡

‹‹ኃጢአታችንን ለማሥተስረይ በሥጋ እንዲህ ታመመ፤ እንደ ሞተ ከነፍሱም በተለየ ጊዜ ሥጋውን እንደ ገነዙ እናምናለን፤›› (የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ አለ)፡፡

‹‹ነቢይ ዳዊትነፍሴን በሲኦል አትተዋትም፤ የባሕርይ ልጅህንም ሙስና መቃብርን ያይ ዘንድ አሳልፈህ አትሰጠውም› አለ፡፡ ይህም ጌታ በተዋሐደው አካል ያለውን የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ያስረዳል፡፡ የቀና ልቡና ዕውቀት በእርሱ ጸንቶ ይኖር ዘንድ፡፡ ዳዊት እንደ ተናገረው እውነት ኾነ፤ ነፍስ መለኮትን ተዋሕዳ ወደ ሲኦል ወርዳለችና፡፡ ሥጋም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር ሳለ መለኮት ከሥጋ አልተለየም፤ አምላክ ሰው የመኾኑን እውነት ያስረዳ ዘንድ፡፡ መለኮት ነፍስን ተዋሕዶ በአካለ ነፍስ የሲኦል ምሥጢርን ገልጦ ፈጽሟልና በሲኦልም በቁራኝነት አልተያዘምና፤›› (የቆጵሮስ ደሴት ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ)፡፡ 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ፣ ሚያዝያ ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፯ .ም፡፡

ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – የመጨረሻ ክፍል

የካቲት ፴ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

፬. ነገረ ማርያም

፬.፩ አንጢዲቆማርያጦስ

እነዚህ መናፍቃን “አፅራረ ማርያም (የማርያም ጠላቶች)” ይባላሉ፡፡ መድኃኒታችንን ከወለደች በኋላ ከዮሴፍ ጋር በባልና ሚስት ልማድ ኖረች በማለት በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የጽርፈት ቃል የሚናገሩ መናፍቃን ናቸው፡፡ ለኑፋቄያቸው መነሻ ያደረጉት የበኵር ልጇን እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም የሚለው ንባብ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ይህ ንባብ እንዴት እንደሚፈታና እንዴት እንደሚተረጎም በማመሥጠር ለእነዚህ ዝንጉዓን መልስ ይሰጣቸዋል፡፡ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሕና፣ ቅድስናና ዘለዓለማዊ ድንግልና ቅዱሳት መጻሕፍትን በመጥቀስ ከተከራከራቸው በኋላ የመለኮትን አዳራሽ ሊቀርባት የሚችል የትኛው ሥጋዊ ነው? ምን ሰው ወደ መለኮት አዳራሽ ሊገባ ይችላል? በማለት ያሳፍራቸዋል፡፡ እኛ ግንድንግል ማርያምን የአምላክ እናት ናት፤ ከወለደችውም በኋላ ዘለዓለማዊት ድንግል ናት› እንላለን ይላል፡፡

፬.፪ “እመቤታችን በሩካቤ አልተወለደችም” ለሚሉ

አባ ጊዮርጊስ ለእነዚህ መናፍቃን መልስ ሲሰጥ “… መልአኩእነሆ ትፀንሻለሽ፤ ወልድንም ትወልጃለሽብሎ የምሥራች በነገራት ጊዜወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆንልኛል?› ብላ ያደነቀች እርሷን እንደምንበሩካቤ አልተወለደችምይሏታል? እናቷ እርሷን ያለ ሩካቤ ፀንሳት ቢሆን ኖሮ ድንግልወንድ ስለማላውቅ ይህ እንደምን ሆንልኛል?› ባላለች ነበር! በማለት አባቷ ኢያቄም እናቷም ሐና መሆኗን በመጥቀስ ያሳፍራቸዋል፡፡

፬.፫ ድንግል ማርያምና መስቀልን ለሚያበላልጡ

ሊቁ እነዚህን ስለ ማርያምና ስለመስቀል እንደሚክዱ በጆሯችን የገባ ወሬ አለ፡፡ እኩሌቶቹ የወለደችው ማርያም ከመስቀሉ ትበልጣለች ይላሉ፤ እኩሌቶቹም በሕማማቱ ደም የተቀደሰ መስቀል ይበልጣል ይላሉ፡፡ እኛ ግን ማርያም አምላክን የወለደች እንደሆነች እናምናለን፡፡ መስቀሉም መለኮት በተዋሐደው የትስብእት ደም የተቀደሰ የብርሃን ማዕተብ መሆኑን እናምናለን በማለት ይመልስላቸዋል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ከእነዚህም በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለማጣመም ለሚሞክሩ ሌሎች ስሑታንም መልስ ሰጥቷል፡፡ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል፡-

  • “ወደ ቤተ ክርስቲያን ኃይል አይወርድም፣ ኅብስቱም ወደ ክርስቶስ ሥጋነት፣ ወይኑም ደሙን ወደ መሆን አይለወጥም ለሚሉ ሊቁ ሲመልስ “‹ሰማየ ሰማያት የማይወስነው እግዚአብሔር አራት ጎኖቿ ባነሱ በሰው እጅ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት ያድራል?› የሚሉ አሉ፡፡ እኛ ግንበጽርሐ አርያም ያለ አኗኗሩ ሳይጎድል ይቀድሳት ዘንድ የመለኮት ኃይል በቤተ ክርስቲያን ያድራል› እንላለንይላል፡፡ በተጨማሪም “… ከከሐዲዎች መነሣሣት የተነሣ እንዳትነዋወጥ ኃይል ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃታል፡፡ የሚጠብቃት እርሱ ሲሆን ኃይልን ትሸከመዋለች፤ ኃይል ትጎናጸፋለች፤ ኃይልም ትታጠቃለች፤ ኃይላትም ይከቧታል፤ የሠራዊት ጌታ ሠረገላ አድርጓታልና በማለት ይመልስላቸዋል፡፡
  • ስለ ሥጋ ወደሙም “‹ኅብስቱ የክርስቶስን ሥጋ፣ ወይኑም ደሙን መሆን ይችላልን?የሚሉ አሉ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ በተቀደሰ ጊዜ ኅብስት ከልማዳዊ ኅብስትነት ሥጋውን ወደ መሆን ይለወጣል፤ ወይንም ከልማዳዊ ወይንነት ደሙን ወደ መሆን ይለወጣል በማለት ምሥጢረ ቍርባንን ያብራራል፡፡ ለድንግል የእግዚአብሔር ልጅ በመንፈስ ቅዱስ መምጣት ልጅ ሆናት፤ እርሷም በልዑል ኃይል እናት ሆነችው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ወደ እርሷ ባይመጣ፣ የልዑል ኃይልም ባይጋርዳት የልዑልን ልጅ ትሸከመው ዘንድ ባልተቻላት ነበር፡፡ ኅብስቱና ወይኑም እንዲሁ ካህኑ አቤቱ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋና ደም እንዲያደርገውበዚህ ኅብስትና ጽዋ ላይ ቅዱሱን ኃይል ትልክ ዘንድ እንለምንሃለን፤ እንማልድሃለንባለ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ መውረድ ሥጋና ደም ይሆናል በማለት ይመልሳል፡፡
  • ስለ ምሥጢረ ሥጋዌም የሚከተለውን ትምህርት ያስተምራል፤በማርያም ማኅፀን ፍጹም የሕይወት እንጀራ ተፀነሰ፡፡ ይኸውም ለተቀደሰች ምሥጢር የበረከት ፍሬ ሆኖ የተሰጠ ከአብርሃም ዘር የተገኘ ሥጋ ነው፡፡ ከባሕርይዋ ደምም በመንፈስ ቅዱስ መጐብኘት የወይን ፍሬ አፈራ፡፡ በአብም በመጋረዱ ኃይል የሚናገር የወይን ደም የመለኮትም ሥጋ ኅብስት ተፀነሰ፡፡ ስለዚህም መድኃኒታችንከሰማያት የወረደ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሥጋዬን የበላ የእኔን ሥጋ ስለበላ በሕይወት ይኖራል፤ ደሜንም የጠጣ ሞትን አይቀምስም› አለ፡፡ ዳግመኛምአብ ሕያው እንደሆነ እኔም የአብ ልጅ ስለሆንሁ ሕያው ነኝሥጋዬንም የበላ የእኔን ሥጋ ስለበላ በሕይወት ይኖራል› አለ፡፡ እንዲህ ያለውን ጸጋ አቃልለን እንደምን እንድናለን? እኛ ግን በመንበሩ ላይ ሆኖ በካህኑ እጆች የሚከብረው ኅብስትና ወይኑ ፍጹም የክርስቶስ ሥጋና ደም እንደሆነ እናምናለን፡፡

፬.፬ ሰዱቃውያን

ሰዱቃውያን ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ መናፍቃን ናቸው፡፡ ሊቁ ጌታችን በሥጋዌው ወራት በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም በማለት የመለሰላቸውን እየጠቀሰ መልስ ይሰጣቸዋል (ማቴ. ፳፪፡፴)፡፡

  • ነፍስ ከሥጋ ጋር ትሞታለች” ለሚለው፡- ይህ መናፍቅ ነፍስ ከሥጋ ጋር ትሞታለች፤ ሙታን በተነሡ ጊዜ ከሥጋ ጋር ትነሣለች የሚል ኑፋቄ ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ ሊቁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ላይ ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ በማለት የተናገረውን በመጥቀስ ነፍስ የማትሞት መሆኗን ይመልስለታል (ማቴ. ፲፡፳፰)፡፡ ነፍስ ከሥጋ ተለይታ በሲኦል ወይም በገነት እንደምትቆይ የአልዓዛርን ታሪክ ድሀውም ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት የሚለውን በመጥቀስ ያሳፍረዋል (ሉቃ. ፲፮፡፳፪)፡፡
  • “… በዐርባ ቀን እግዚአብሔር በሕፃኑ ፊት ላይ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ይልበታል፤ በእግዚአብሔርም እጅ ይፈጠራልበማለት የተሳሳተ ትምህርት ለሚያስተምሩ ዝንጉዓን፡ ሊቁ እግዚአብሔር የሕይወት እስትንፋስን በአዳም ላይ እፍ እንዳለ በሔዋን ፊት ላይ ግን የሕይወትን እስትንፋስ እፍ እንዳላለ እይ፤ ሕፃን ከእግዚአብሔር አፍ የሕይወትን እስትንፋስ መቀበል የሚገባው ቢሆን ሔዋን ከፈጣሪዋ ከእግዚአብሔር አፍ ዳግመኛ የሕይወትን አስትንፋስ መቀበል በተገባት ነበር በማለት ትክክለኛው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሕፃን ልጅ ከአባቱና ከእናቱ ዘር የማትሞት ነፍስን ይቀበላል የሚለው እንደሆነ ገለጸልን፡፡
  • “ኦሪት፣ ነቢያትና ሰንበት ተሽረዋልለሚሉ፡- በወንጌል መምጣት ኦሪት እንደ ቀረች፣ በሐዋርያትም ስብከት የነቢያት ትንቢት እንደጠፋ፣ ሰንበትም ትንሣኤ በሆነባት እሑድ እንደተሻረች የሚናገሩ አሉ፡፡ እኛ ግንኦሪት በወንጌል ስብከት ከበረች፤ ነቢያትም በሐዋርያት ትምህርት ከፍ ክፍ አሉ፤ ዓለምን ከመፍጠር ያረፈባት ሰንበትም የዓለም አዳኝ በተነሣባት በሰንበተ ክርስቲያን ዘውድን ተቀዳጀች› እንላለንበማለት ይመልስላቸዋል፡፡
  • አዳምና ነቢያት በሲኦል አልነበሩም ለሚሉ፡- አባ ጊዮርጊስ እንዲህ የሚሉትን መናፍቃን ነቢያት የተናገሩትን በመጥቀስ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ በሲኦል ስለመኖራቸው፣ ገነትም ተዘግታ በምትገለባበጥ የእሳት ሰይፍ እየተጠበቀች መቆየቷን በመግለጽ ይገሥጻቸዋል፡፡
  • “ኤዶም ገነትና ሲኦል በሰማያት ናቸው” ለሚሉ፡- የተወሰኑት ኤዶም ገነት በሰማያት ናት፤ በምድር አይደለችም” ሲሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ሲኦል በሰማያት ናት” ይላሉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ገነትና ሲኦል ቁጥራቸው ከዓለመ ምድር እንጂ ከሰማያት እንዳልሆኑ ገነትን የሚያጠጡ ወንዞችን፣ አዳም ወደ ገነት እንዳይገባ በሱራፊ መጠበቋን ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ መልስ ሰጥቷቸዋል፡፡

በአጠቃላይ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ምሥጢር መጽሐፉ የመናፍቃንን ስሕተትና የስሕተታቸውን ምክንያት ነቅሶ በማውጣትና መጽሐፋዊ የሆነ መልስ በመስጠት መናፍቃንንና ስሑታንን ገሥጿል፡፡ የመጽሐፉ ዋና ትኩረት ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌ ላይ ለተነሡ ኑፋቄዎች መልስ መስጠት ቢሆንም ሌሎችንም ጉዳዮች በማንሣት መልስ እንደ ሰጠ ከላይ ተመልክተናል፡፡ አዲስ መናፍቅ እንጂ አዲስ ኑፋቄ የለም እንደሚባለው በመጽሐፉ የተጠቀሱ መናፍቃን ትምህርቶች ዛሬም ድረስ በተለያዩ አካላት እንደ አዲስ ሲጠቀሱና ሲነገሩ እንሰማለን፡፡ በዘመናችን የተነሡ መናፍቃንና ግብረ አበሮቻቸው የሚያስተምሩትም ቤተ ክርስቲያን አውግዛ የለየችውና በየዘመናቱ የተነሡ ሊቃውንት መልስ የሰጡበት እንጂ አዲስ የተገለጠላቸው ትምህርት አለመሆኑን መረዳት ከክርስቲያኖች ይጠበቃል፡፡ ትምህርቷን ያልሰሙ አላዋቂዎች ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን እንደማትሰብክ አድርገው ይናገራሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን እንዴት እንደምትሰብከው በሚያስረዳው በሚከተለው የሊቁ ቃል ጽሑፋችንን እናጠቃልላን፤

ኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱሳን ሁሉ ንጉሥ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚጠራው ስሙ የጣፈጠ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያዳምጠው ቃሉ የጣፈጠ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚበላው ሥጋው የጣፈጠ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚጠጣው ደሙ የጣፈጠ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ዜናውን ለሚነግር መታሰቢያው የጣፈጠ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ የሰውም ልጅ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል ያለ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እትራቶቹ ከእርሱ ጋር መስቀሉም በፊቱ ያለ፣ የአንድነታችን አለቃ፣ የትምህርታችን አስተማሪ፣ የእረኞቻችን አለቃ፣ የካህኖቻችን ሊቅ ነው፡፡ እርሱ ሰማያዊ ከሚሆን ከቸር አባቱና ሕይወትን ከሚሰጥ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ከእኛ ጋር ይኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳም ድረ ገጽ ተከታታዮች! ይህ ትምህርት፣ ከጥር ፩ – ፲፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በታተመው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ በንቁ ዓምድ ሥር ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – ሦስተኛ ክፍል

የካቲት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

፪.፬ አርአያውን ወደ መስቀል አወጣ ለሚሉ መናፍቃን

ሥጋው የተቸነከረው በእውነት ካልሆነ ስለምን ከትንሣኤው በኋላ ቶማስንእጅህን አምጣና በመስቀል ችንካሮች የተጨነከሩትን እጆቼን ዳስስ፤ ጣቶችህንም አምጣወደ ጎኔም አስገባአለው በማለት ሊቁ ስንፍናቸውን ይገልጽባቸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዞ አባ ጊዮርጊስ እግዚአብሔር አይወልድም አይወለድም ለሚሉ መናፍቃን እነዚህን በምን እንከራከራቸዋለን፤የኦሪት ሕግ አለንይሉናል፡፡ የኦሪታቸው ቃል ከእኛ ኦሪት ጋር፣ የነቢዮቻቸውም ቃል ከእኛ ነቢያት ጋር አይተባበርምና የአንደበታቸው ቃል ሁሉ ሐሰተኛ ነው፤ መንገዳቸውም ክፉ መንገድ ነው …” በማለት ክሕደታቸውን ይገልጽልናል፡፡

፪.፭ አርሲስ

“አርሲስ” በሃይማኖተ አበው እንደተጠቀሰው ስመ መናፍቃን ነው፡፡ አርሲስ በነፍስና በሥጋ ወደ ሲኦል ወረደ ብለው የሚናገሩ መናፍቃን ናቸው፡፡ ሊቁ እነዚህን መናፍቃን እስኪ እናንተ አስቀድማችሁ ንገሩን? የእግዚአብሔርን ልጅሞተ› ትሉታላችሁ? ወይስአልሞተምትላላችሁ?ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ሞተ” ካሉ “የነፍስ ከሥጋ መለየት በቀር ሞት ምንድን ነው?” አልሞተም” ካሉ ደግሞ ሞት ሳይኖር ትንሣኤ እንዴት ነው?” እያለ ይሞግታቸዋል፡፡ በትምህርታቸው ክርስቶስን የሚሞትና የማይሞት ሁለት ሥጋ ያለው እንዳስመሰሉት በመንገር ይነቅፋቸዋል፡፡ እኛ ግንመለኮታዊ ቃል ከብቻዋ ከነፍስ ጋር ወደ ሲኦል ወረደ፤ ሥጋን ግን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል ላይ አውርደዋት በከፈን ጠቅልለው ከመቃብር ውስጥ ጨመሯት፡፡ ሥጋም ያለ ነፍስ እስከ ትንሣኤው ዕለት ለብቻዋ ቆየች፡፡ መለኮት ግን ከነፍሱ እና ከሥጋው አልተለየም› እንላለን” በማለት መልስ ያሰጣቸዋል፡፡

፪.፮ ፎጢኖስ

በሰርቢያ ግዛት ትገኝ በነበረች የሰርሚየም ሊቀ ጳጳስ የነበረው ፎጢኖስ ለፌ እማርያም ክዋኔሁ (ህላዌሁ) ለወልድየወልድ ህልውና ከማርያም ከተወለደ በኋላ ነው የሚል ኑፋቄ ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስም እኛ ግንህልውናው ከዘመናትና ከጊዜ፣ ከዕለታትና ከሰዓት አስቀድሞ ነው፣ በኋለኛው ዘመን ስለ እኛ ድኅነት ያለ ዘርዐ ብእሲ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆነ (በሥጋ ተገለጠ)› እንላለን በማለት ቅዱሳት መጻሕፍትን እያመሠጠረ መልስ ሰጥቶታል፡፡

፪.፯ የአብ ቃል ሰው ወደመሆን ተለወጠ ለሚሉ መናፍቃን

እነዚህ መናፍቃን አካላዊ ቃል ሥጋና ደም፣ አጥንትና ጠጉር፣ ሥሮችንም ወደ መሆን ተለወጠ፤ መለኮትም ሰውን ወደ መሆን ተለወጠ ብለው ይናገራሉ፡፡ ይህም ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነው ተለውጦ ነው ወይም ሰው በመሆኑ አምላክነቱ ጠፍቷል” የሚሉ ናቸው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን ሰው ሆነ ሲባል የጨው ሐውልት እንደሆነች እንደ ሎጥ ሚስት፣ የበርሃ አውሬ እንደሆነ እንደ ናቡከደነፆር ተለውጦ አይደለም ይላል፡፡ የመለኮት ኃይል ሰው ወደ መሆን ተለውጦ ቢሆን ኖሮ ሞትን ባልቀመሰ፣ ሞትንም ቢቀምስ ዓለምን የያዘው የመለኮት ኃይል ነውና፣ የሰማይ ጠፈር በፈረሰ፣ የምድርም መሠረታት በተበታተኑ ነበር፤ ሰውነት መለኮትን ወደ መሆን ተለውጦ ቢሆን መለኮት በእጅ አይነካም፣ ለዐይንም አይታይም፣ በሕሊናም አይመረመርምና ለሰቃዮች ባልተያዘ፣ በመስቀል ላይ እፍረትን ባልታገሠ ነበር በማለት ይዘልፋቸዋል፡፡ እኛ ግንያለጭማሪ ተዋሐደ እንጂ መለኮታዊ ቃል ከባሕርዩ አልተለወጠም፤ ያለመለወጥ የተዋሐደ ሆነእንላለን በማለት በተዐቅቦ እንደተገለጠ ይነግረናል፡፡

፪.፰ መንክዮስ

የክርስቶስ ሥጋ ምትሐት ነው፤ የሰው ልጅ ሥጋ አይደለም የሚል ኑፋቄ ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ የክርስቶስ ሥጋ ምትሐት አለመሆኑን፣ ፍጹም የሰው ሥጋ መሆኑን ከድንግል መወለዱን፣ ጡቶቿን እየጠባ ማደጉን፣ በዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ መዳሰሱን፣ በመስቀል ላይ መቸንከሩን በመጥቀስ መንክዮስ ሆይ! ስንፍናህን አደንቃለሁስለ ብዙዎች ቤዛ መገደሉን ካላመንክ አንተም በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት አልዳንህም በማለት ይዘልፈዋል፡፡ እኛ ግን የክርስቶስ ሰውነት ፍጹም የሚዳሰስ ሥጋን የሚያጸና አጥንት የሚፈስ ደም ሰውነትንን የሚያስሩ ጅማቶች፣ የራስ ጠጉርና ቅንድብ፣ የማትታይ ነፍስ የምታስተውልና የምትናገር የሕይወት እስትንፋስ፣ የእጆችና የእግሮች ቡቃያ ጥፍሮች አሉት እንላለን ይለናል፡፡

፪.፱ አውጣኪ

አውጣኪ ወይም አፍቲኪስ የክርስቶስ ሥጋ እንደኛ ሥጋ አይደለም፤ መከራንም አልተቀበለም፤ የክርስቶስ ሥጋ ከሰማይ የወረደ ነው በማለት ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ አውጣኪ ነገረ ተዋሕዶን ለማብራራት ሲሞክር ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ ነው” የሚለውን ትምህርት ቢቀበልም፣ በሥጋው ፍጹም ሰው መሆኑን ግን አልተቀበለም፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ተራበ፤ ተጠማ፤ ደከመ፤ መከራ ተቀበለ፤ ሞተ …” የሚሉትን ቃላት ለመጠቀም ይፈራል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ወደ ደረቱ ተጠግቶ የተቀመጠ ወዳጁ ዮሐንስ የክርስቶስን ሥጋ መድከም ለመናገር ካላፈረ፣ በፊቱ መስታወትነት ያልታየህ፣ ጣቶቹ ያልዳሰሱህ፣ ጣቶችህም ያልዳሰሱት አንተ እንዴት ታፍርበታልህ? በማለት የሚወቅሰው ስለዚህ ነው፡፡ እኛ ግን ክርስቶስ በሥጋው ደከመ፣ ወዛ፣ ተራበ፣ ተጠማ፣ ታመመ፣ ሞተ፤ ከኃጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ ሁሉ ሠራ እንላለን በማለት የቤተ ክርስቲያንን ቀጥተኛ አስተምህሮ በመግለጥ እኛን ስለማዳን ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ቅድስት ነፍሱ ከቅዱስ ሥጋው እስከተለየችበት ድረስ የተቀበለውን ፀዋትወ መከራ ያብራራል፡፡

በተጨማሪም አፍቲኪስ የክርስቶስ ሥጋ ከሰማይ ወረደ በማለት ለሚናገረው ኑፋቄው ሊቁ ሲመልስ እናንተ ሰነፎችና ልባችሁ ከማመን የዘገየአዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ› ብሎ መናገርን እንዳስቀደመ ከአዳም ዘር ሰው ሆኖ እንደተወለደ ዕወቁ፡፡ መድኃኒታችን ከለበሰው ከአዳም ሥጋ በቀር የአዳም እንደ እግዚአብሔር መሆኑ ምንድን ነው? በዚያችም ሥጋ በምድር ላይ ጉስቁልናን ለበሰ፤ ያችንም ሥጋ በሰማያት ጌትነትን አለበሳት፡፡ በሰማያት ሥጋ ካለ ከእርሷ ሰው ሆኖ ይወለድ ዘንድ ስለምን በድንግል ማኅፀን አደረ፣ ከሥጋው ጋር በድንግል ማኅፀን አደረ ካላችሁ፣ የሥጋ በሥጋ ውስጥ ማደር ጥቅሙ ምንድን ነው? ቀድሞውንም ሥጋ ካለው የቀደመ ሥጋው በበቃው፤ ከድንግል ሥጋ መወለድን ባልፈለገ ነበር ይላል፡፡ እኛ ግንየክርስቶስ ሥጋና ነፍሱ ከአዳም ባሕርይ ብቻዋን ንጽሕት ድንግል (ከሆነች) ማርያም ከተባለች የገሊላ ሴት ያለ ወንድ ዘር የነሣው ነው› እንላለን በማለት ይመልስለታል፡፡

አባ ጊዮርጊስ የክርስቶስን አምላክነት በመሰከረበት በዚህ አንቀጹ የሚከተለውን ትምህርት አስተምሯል፤ ስለ ትሕትና ነገር መናገርን እናስቀድም፤ ኃይል በሴት ማኅፀን አደረ፤ እሳትም በሥጋና በደም መጐናጸፊያ ተጠቀለለ፡፡ ሕፃናትንም የሚሥል በሕፃናት መልክ ተሣለ፤ የሔዋን አባት ከሔዋን ሴት ልጅ ተወለደ፤ በኪሩቤል ላይ የሚቀመጥ በጉልበት ታቀፈ፤ እሳት በተሣለባቸው በአራቱ እንሰሳ ላይ የሚጫን በላምና በአህያ መካከል ተኛ፡፡ ሥጋዊን ሁሉ የሚመግበው የጡት ወተትን ተመገበ፡፡ በጊዜና በዘመናት የሸመገለ በየጥቂቱ አደገ፤ በታናሽነታቸው ጊዜ ሕፃናትን የሚጠብቃቸው በሜዳ ላይ ዳኸ፤ ለዓመታቱ ቁጥር ጥንት የሌለው በሰው መጠን ጐለመሰ፤ ተራሮችን በኃይል የሚያቆማቸው ደከመ፣ ወዛም፡፡ ኪሩቤል ሊነኩት ሱራፌልም ሊዳስሱት የማይቻላቸው እግሮቹ በአመንዝራይቱ ሴት፣ ልብሶቹም ደም በሚፈስሳት ሴት ተዳሰሰ፡፡

፪.፲ የእለእስክንድርያው ታውዶስዮስና የሕንድክያው ሳዊሮስ

እነዚህ የእግዚአብሔር ልጅ በግድ መከራን ተቀበለ፤ ያለፈቃዱ ሞተ ብለው የተናገሩ መናፍቃን ናቸው፡፡ ሊቁ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት” ማለቱን፣ አትሙትብን” ያለውን ቅዱስ ጴጥሮስን መገሠጹን፣ ነፍሴን ላኖራት ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ” ማለቱን እየጠቀሰ ካሳፈራቸው በኋላ እኛ ግን በፈቃዱ መከራ ተቀብሎ ሞተ፣ በፈቃዱ በመለኮቱ ኃይል ተነሣ እንላለን ይላል፡፡ በፈቃዱ ስለሆነ መከራውና ሞቱም እርሱ ራሱ በፈቀደ አሰቃዩት፤ እርሱም በወደደ ገደሉት፤ እርሱ በፈቀደ በመስቀል ላይ በብረቶች ቸነከሩት፤ እርሱም በወደደ ሞትን በሥጋ ቀመሰ፤ እርሱ በፈቀደ ሆምጣጤ ከሐሞት ጋር ቀላቅለው አጠጡት፤ እርሱም በወደደ ነፍሱን ለአባቱ አደራ ሰጠ በማለት ይገልጽልናል፡፡

፪.፲፩ ፍላቭያኖስ

የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ የነበረና የመለኮትና የሰውነት ገጽ ሁለት ነው በማለት ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስም መለኮትና ትስብእት ካልተዋሐዱ ኢሳይያስ አማኑኤል ያለው ማንን ነው? ‹ሥጋዬን ካልበላችሁ ደሜንም ካልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም› ያለን ማን ነው? በጲላጦስ ፊት የቆመው፣ የተቸነከረውና የተሰቀለው፣ ዓለምን ያዳነው ማን ነው? በማለት ጥያቄውን በጥያቄ ይመልስለታል፡፡

፫. ነገረ መንፈስ ቅዱስ

፫.፩ መቅዶንዮስ

መንፈስ ቅዱስሕጹጽ› (ፍጡር) ነው” ያለ መናፍቅ ሲሆን በሁለተኛው ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ የተወገዘ ነው፡፡ ሊቁ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ያነሰ ቢሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲያዝዛቸውስታጠምቁ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁአለ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ያነሰ ከሆነ ስለምን በማይስተካከለው መጠመቅን አዘዘ? በማለት በጥያቄ ይመልስለታል፡፡

፫.፪ “የመንፈስ ቅዱስ ህላዌ ከክርስቶስ ጥምቀት ወዲህ ነው” ለሚሉ መናፍቃን

እነዚህ መናፍቃን ጌታችን አምላካችን መድኀኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት ጊዜ የመንፈስ ቅዱስን በርግብ አምሳል መገለጥ የህላዌው መጀመሪያ አድርገው መናገራቸው እንዴት ስሕተትና ኑፋቄ እንደሆነ የእግዚአብሔር መንፈስ በውኆች ላይ ሰፍፎ ነበር የሚለውን ቃል በመጥቀስና በማብራራት መልስ ይሰጣቸዋል፡፡ ሊቁ እኛ ግንመንፈስ ቅዱስ ቅድመ ዓለም የነበረ ለዘለዓለም የሚኖር ነው› እንላለን በማለት አማናዊውን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ይነግራቸዋል፡፡

ይቆየን

ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – ሁለተኛ ክፍል

የካቲት ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

፩.፪ አቡሊናርዮስ

አቡሊናርዮስ የሎዶቅያ ሊቀ ጳጳስ ነበረ፡፡ አባ ጊዮርጊስ አቡርዮስ” በማለት ይጠራዋል፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ለየራስ ናቸው በማለት ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ ሊቁ ለዚህ መናፍቅ ሲመልስ በአመክንዮ ይጀምራል አስቀድመህ በራስ ፍረድ፤ የሥላሴ ሥርዓት (ሥርዓተ ሥላሴ) ሦስት ከሆነ ማን ፈጠረህ? ማንስ አበጀህ? አብ ራሴን ፈጠረው፤ ወልድም እጄን አበጀው፤ መንፈስ ቅዱስም እግሬን አጸናው ትላለህን? በማለት ይወቅሰዋል፡፡ እንዲህ ካልህ የሥላሴን አንድነት እንደበተንህ የራስህንም አንድነት በተንህ፤የሥላሴን አንድነት እንደ አሕዛብ አማልክት ከፈልኸው፤ ጣዖት ከሚያመልኩ ጋር በሥርዓት ተባበርክ በማለት ይዘልፈዋል፡፡ እኛ ግንአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ መንግሥት፣ አንድ ፈቃድእንላለን በማለት የቤተ ክርስቲያንን ቀጥተኛ አስተምህሮ ይነግረዋል፡፡

የአቡሊናርዮስ ክሕደት የመለኮትንና የሥጋን ተዋሕዶ ሁለት ጊዜ እንደተፈጸመ ያደርገዋል፡፡ ይኸውም በፅንሰት ጊዜ በማኅፀን እና በሞት ተለያይተው የነበሩ ሥጋና መለኮት ከመቃብር በተነሣበት ጊዜ ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም የአቡሊናርዮስ ክሕደት የነፍስ ድኅነትን ያልተፈጸመ የሚያስመስል ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ነፍስን ካልነሣ ያልነሣውን አላደነምና ነፍስ አልዳነችም ያሰኛል፡፡ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ነፍስን አልነሣም፣ ስለ ልብና ነፍስ ፋንታ መለኮቱ ሆነው ብሎ ያስተማረም ራሱ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስም አንተ አቡሊናርዮስ ሆይ! ቀድሞ በጥርጥርህ አብና ወልድ መንፈስ ቅዱስም የተለያዩ ናቸው ብለህ ከአባቱ የተለየ ነው አልኸው፤ አሁን ደግሞ የክርስቶስ ሰውነት ነፍስና ልብ የለውም፣ መለኮቱም ስለ ነፍስና ልብ ሆነው አልህ፡፡ እንዴት እኮ እርሱ ራሱነፍሴን ፈጽሜ በፈቃዴ እሰጣለሁ› ያለ እንደዚህ ነፍስ የለውም ይባላል?ነፍስ ከሌለው መሞቱ እንደምን ይሆናል? ያለ ነፍስ ከሥጋ በመለየት ሞት የለምና በማለት አፉን ያስይዘዋል፡፡

፩.፫ ቢቱ

ከአባ ጊዮርጊስ ጋር በአንድ ዘመን የነበረ መናፍቅ ሲሆን ለኃጥአን ፍዳ፣ ለጻድቃን በጎ ዋጋ ለመክፈል ወልድ ከአባቱ ተለይቶ ይመጣልየሚል ኑፋቄ ያስተማረ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ቢቱን ሥጋን የለበሰ ሰይጣን፣ ሰው የሆነ ጋኔን ይለዋል፡፡ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይቀመጣሉ፤ ይመረምራሉ፤ ይፈርዳሉ እንዳለ፣ አባ ጊዮርጊስም ከብሉይና ከሐዲስ ማስረጃዎችን እየጠቀሰ ቢቱን መልስ አሳጥቶታል፡፡ እኛ ግንአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በሙታንና በሕያዋን ይፈርዱ ዘንድ በአንድ ዐደባባይ፣ በአንዲትም መወቃቀሻ ቦታ ይመጣሉ› እንላለን በማለት ይመልስለታል፡፡

፩.፬ አርዮስ

አርዮስ ወልድ ፍጡር በባሕርየ መለኮቱ፣ ሀሎ ዘመን አመ ኢሀሎ ወልድ፤ ወልድ በባሕርዩ ፍጡር ነው (ሎቱ ስብሐት) … ያልነበረበት ጊዜ ነበር ብሎ ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም አርዮስን ርእሰ መናፍቃን (የመናፍቃን አለቃ)” ትለዋለች፡፡ አባ ጊዮርጊስ አብ እና ወልድ በባሕርይ፣ በህልውና አንድ እንደሆኑ ከመጻሕፍት ከየወገኑ እየጠቀሰ አፉን ያስይዘዋል፡፡ የክሕደት ቡቃያ አርዮስ ሆይ!እኔና አብ አንድ ነን› ብሎ የተናገረውን የፍጥረታትን ፈጣሪ ፍጡር ትለዋለህን? ዳግመኛምእኔን ያየ አብን አይቷል፤ እኔን የሰማ የላከኝን ሰማው፤ እኔን የካደ የላከኝን ካደው፤ በእኔ ካልሆነ በቀር ወደ አብ መምጣት የሚቻለው የለም፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው›፤ በማለት የተናገረው ፍጡር ነውን? በማለት ፍጹም ሰው ሆኖ የተገለጠው ፍጹም አምላክ እንደሆነ ይመልስለታል፡፡

ስለ ህልውናቸውም የዐይን ጥቅሻ፣ የሽፋሽፍትንም መገለጥ ያህል እንኳ ቢሆን አብ ከወልድ በህልውና መቅደም የለውም በማለት የመለሰለት ሲሆን እኛ ግን ያልተሠራ፣ ያልተፈጠረ፣ ያልጎደለ፣ ያልተለየ እንደሆነ እንናገራለን ይላል፡፡ ፈጽሞ ያልተፈጠረ፣ ያልተሠራ፣ ከአባቱ አኗኗር ያልጎደለና ያልተለየ እንደሆነ እንናገራለን በማለት የወልድን አምላክነት ይመሰክራል፡፡ የአባ ጊዮርጊስ መልስ ዛሬም ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጡር ነው” ለማለት “አማላጅ” በሚል ቅጽል ለሚጠሩት ሁሉ መልስ መሆኑን አንብቦ መረዳት የሊቃውንቱንም መልስ የመስጠት መንፈሳዊ ፈሊጥ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

፩.፭ አርጌንስ

አርጌንስ (ኦሪገን) መዓርገ ርቀትን (‹ቀ› ይጠብቃል) ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ አብ ከወልድ እና ከመንፈስ ቅዱስ፣ ወልድም እንደዚሁ ከመንፈስ ቅዱስ እንደሚበልጥ አድርጎ ይናገራል፡፡ ዛሬም በዚህ ኑፋቄ የወደቁና አብ ይበልጠኛል፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ ብሏል በማለት ኢየሱስ ክርስቶስን ከአብ እንደሚያንስ አድርገው የሚናገሩ አሉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ እነዚህን ኀይለ ቃላት እንዲህ ይተረጉማቸዋል፡፡ ከዕርገቱ በፊትወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁያለው ለሰውነት የሚገባ ትሕትናን እያሳየ ነው፤ ለእነርሱ በጸጋ አባታቸው ነው፣ ለእርሱ ግን በእውነት የባሕርይ አባቱ ነው፡፡ ለእነርሱ በእውነት አምላካቸው ነው፤ ለእርሱ ግን ሰው ስለመሆኑ ነው፡፡ ለአርጌንስም እኛ ግን ‹በሥላሴ መዓርግ የመብለጥም ሆነ የማነስ ነገር የለም፤ በመለኮት አንድ ናቸው እንጂ› ብለን እናምናለን በማለት ይመልስለታል፡፡ አርጌንስ ከዚህም በተጨማሪ እግዚአብሔር እንዳይበሉ ከከለከላቸው ዛፍ በበሉ ቀን አዳምንና ሔዋንን ያለበሳቸው ለምድ በእኛ ላይ ያለው የቆዳ ልብስ ነው፤ የቁርበት ለምድ ልብስ አይደለም ማለቱን በመንቀፍ እኛ ግን ሥጋስ ቀድሞም በተፈጠሩ ጊዜ አላቸው፤ በኋላ እግዚአብሔር ያለበሳቸው ግን የቁርበት ልብስ ነው፤ ትእዛዙን ስላቃለሉ የነቀፋ ልብስ ነው እንላለን ብሎ ይመልስለታል፡፡

፪. ምሥጢረ ሥጋዌ (ነገረ ክርስቶስ)

፪.፩ ንስጥሮስ

ንስጥሮስ የቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳስ የነበረ ሲሆን የክርስቶስን አካልና ባሕርይ ለሁለት በመክፈል ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ በማለት ኅድረትን ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ወልድንከነቢያት አንዱ ነው፤ የዮሴፍ ልጅ ነው› ለማለት እንዴት ደፈርህ?” የሚለው ስለዚህ ነው፡፡ ንስጥሮስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የሰው እናት (Anthropothokos) እንጂ የአምላክ እናት (Theotokos) መባል የለባትም ያለ መናፍቅ ነው፡፡ በእርግጥ ያሻሻለ መስሎ የክርስቶስ እናት (Christotokos) እላታለሁ” ብሏል፡፡ ይህን ቢልም ግን ለንስጥሮስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ያደረበት ደግ ሰው እንጂ አምላክ አይደለም (ሎቱ ስብሐት)፡፡ ለዚህ ነው አባ ጊዮርጊስ ንስጥሮስን እመቤታችን ማርያምን መለኮት ያደረበትን ሰው የወለደች እንጂ የአምላክ እናት እንደማይሏት ስለ ልጆችህ ዜና ሰማን በማለት የሚዘልፈው፡፡

ሊቁ ለዚህ ኑፋቄው መልስ ሲሰጥ በእውነት ኢየሱስ ክርስቶስ ዐመጽ የሌለበት አምላክ፤ ኃጢአት የሌለበት ሰው፤ እድፍ የሌለበት ንጹሕ በግ፤ ነውር የሌለበት ፍሪዳ፤ ርኵሰት የሌለበት የበሰለ ኅብስት፤ አተላ የሌለው የጠራ የወይን ጭማቂ፤ የተወደደ ዕጣን፤ የሚያንጸባርቅ ሽቱ፤ የሕዝብን ኃጢአት ይቅር የሚል ኃጢአት የሌለበት ካህን፤ ፊት አይቶ ለሀብታም፣ ለደሀ የማያዳላ ንጉሥ ነው በማለት አምላክ ወሰብእ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ስለ እመቤታችንም ቀድሞ እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ እንደተወለደ፣ በኋለኛው ዘመን የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ከብቻዋ ከድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ በመጀመሪያ የማይታይ እርሱ ከማይታየው ተወለደ፤ በኋላም የማይያዝ የሕይወት እሳት፣ ከምትዳሰስ ሥጋ ተወለደ፡፡ በመጀመሪያ የሀልዎቱ መጀመሪያ ሳይታወቅ ተወለደ፤ በኋላም የዘመናት ፈጣሪ ዓመታትንም የሚወስን እርሱ ዕድሜዋ ዐሥራ አምስት ዓመት ከሆነ ከታናሽ ብላቴና ተወለደ፡፡ የመጀመሪያ ልደቱን ምሥጢር የኋለኛ ልደቱንም ድንቅ አደረገ በማለት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ መሆኗን በማስረዳት ከብሉያትና ከሐዲሳት እየጠቀሰ ያሳፍረዋል፡፡ ከሥጋዌ በኋላ ምንታዌ እንደሌለም የአርዮስን ክሕደት በዘለፈበት ድርሳኑ ሰው ከሆነ በኋላ በመለኮቱ የእግዚአብሔር ልጅ፣ በሰውነቱ የማርያም ልጅ አንለውምበማለት ይነግረናል፡፡

፪.፪ የሮሜ ሊቀ ጳጳስ ልዮን

ርጕም ልዮን በሦስተኛው ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ (ጉባኤ ኤፌሶን) ሁለት መቶ ሊቃነ ጳጳሳት ተሰብስበው ያወገዙትን የንስጥሮስን ክሕደት በማሻሻል አንድ አካል ሁለት ባሕርይ” የሚል ክሕደት የጀመረ መናፍቅ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን መከፈልም ተጠያቂ ነው፡፡ ልዮን ሥጋ ከመለኮት ያንሳል ይላል፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ” የተባለ አባ ጊዮርጊስ እኔ እና አብ አንድ ነን፤ ከሰማይ የወረደ ኅብስት እኔ ነኝ፤ ባለመድኃኒት ከሰማይ መጣ …” የሚሉትን ንባባት በመተርጎም እኛ ግን ‹ከተዋሕዶ በኋላ የክርስቶስ ትስብእት ከመለኮቱ አያንስም (አይጎድልም)› እንላለን፡፡ ባለመድኃኒት በድውዮች ሴት ልጅ ዘንድ አደረ፤ ከእርሷም ምድራዊት ሥጋን ተዋሐደ፡፡ ለድውዮችም ፈውስ በሚሆን ገንዘብ ከመለኮቱ ጋር አንድ አደረገው፡፡ ባለመድኃኒት ከሰማየ ሰማያት መጥቷልና የፈውስ እንጨት በዳዊት ቤት ተገኘ፡፡ ያለመለኮት ከሥጋ ጋር መዋሐድ ፈውስ እንደማይገኝ ባለመድኃኒቱ ዐወቀ፤ ስለዚህም ራሱን ሰው ለመሆን ሰጠ፡፡ ታማሚስ ለራሱ ፈውስን ያደርግ ዘንድ አይቻለውም፤ ነገር ግን በሚድንበት ገንዘብ መድኃኒት እንዲያደርግለት ባለመድኃኒቱን ይማልደዋል በማለት አፉን ያስይዘዋል፡፡

፪.፫ የኬልቄዶን ማኅበርተኞች

በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ጉባኤ ከለባት በመባል በሚጠራው በኬልቄዶን ጉባኤ የተሳተፉት ስድስት መቶ ሠላሳ ስድስት ኤጲስቆጶሳት ናቸው፡፡ እነዚህ ጉባኤተኞች መለኮትና ሥጋን በመለያየት ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ ናቸው” የሚል እንግዳ ትምህርት ያመጡ ናቸው፡፡ አባ ጊዮርጊስም መለኮት በሰውነት ሥጋ እንደሆነ፤ ሰውነትም በመለኮት አምላክ ሆነ፡፡ በመለኮቱ መቀየርን ስለ ሰውነቱም መለወጥን አናስብ፤ ስለ አንድነቱ መቀላቀልን፣ ስለ ባሕርይውም መለያየትን አናስብ፡፡ እርሱ በመለያየት ያልተከፈለ፣ በወንድማማችነትም ሁለት ያልሆነ ነው፡፡ በመለኮቱም በሰውነቱም አንድ እግዚአብሔር ነው በማለት መልስ ሰጥቷቸዋል፡፡ እኛ ግንከድንግል ማርያም ሰው የሆነ አንድ አካል አንድ ባሕርይ (ፈቃድ) ነውእንላለንበማለትም የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ አስረድቷቸዋል፡፡

ይቆየን

ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – የመጀመሪያ ክፍል

የካቲት ፳፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ዕቅበተ እምነት የቤተ ክርስቲያን የዕለት ከዕለት አገልግሎት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በጎላና በተረዳ ለመናገር የዐቃብያነ እምነት ዘመን የሚባል ወቅት ቢኖርም ቤተ ክርስቲያን የዕቅበተ እምነት ተግባር ያልፈጸመችበት ጊዜ የለም፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በቃልም በመጽሐፍም የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ያስጠበቁ ብዙ ሊቃውንትን እናገኛለን፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ከእነዚህ ስመ ጥር ዐቃብያነ እምነት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በድርሰቱ ዳግማዊ ያሬድ”፣ በመንፈሳዊ ዕውቀቱ ዐምደ ሃይማኖት”፣ መናፍቃንን ተከራክሮ በመርታቱ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ” ተብሎ ይጠራል፡፡

ዜና ገድሉን የጻፈው ሊቁ ወልደ አብ እንደ ሙሴ የኦሪት መምህር፣ እንደ ሄኖክ የተሰወረውን የሚያይ፣ እንደ ኤልያስ ለአምላኩ ሕግ የሚቀና፣ እንደ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል (ቃሉ ከፍ ያለ)፣ ጎልያድን የገደለው ዐዲሱ ዳዊት፣ የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎችን የተቀበለ ጴጥሮስ፣ ከኢየሩሳሌም እስከ እልዋሪቆን ያስተማረ ልሳነ ዕፍረት ጳውሎስ፣ …” (ገድለ አባ ጊዮርስ ምዕራፍ ፩፡፲፮-፲፰) በማለት ክብሩን ልዕልናውን ይገልጸዋል፡፡ የሊቁን ዜና ዕረፍት በሰሙ ጊዜ ንጉሡና ሕዝበ ክርስቲያኑ ያለቀሱት ለቅሶ የአባ ጊዮርጊስን ጸጋና ተወዳጅነት የሚያስረዳ ነበር፡፡ አባ ቸር ጠባቂ፣ አባ የምስጋና ክቡር ዕቃ፣ አባ ዐዲሱ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ አባ ቀዩና አረንጓዴው ወርቅ፣ አባ ሰማያዊ ሰውና ምድራዊ መልአክ፣ አባ የማይዛባ የሃይማኖት ምሰሶ፣ አባ የኢትዮጵያ ብሩህ ፀሐይና በምልዐቱ የሚታይ ጨረቃ፣ አባ ሰማያዊ ኮከብ፣ በእውነት መለኮታዊ እሳት የተዋሐደውን ቅዱስ ቍርባን የዳሰሱ እጆችህ ደረቁን? እግሮችህስ በሞት መግነዝ ተገነዙን? አባ በእውነት ዐይኖችህ ተከደኑን? አፍንጮችህስ ተዘጉን? አፍና ከንፈሮችህስ ተከደኑን? …” በማለት ነበር ኀዘናቸውን የገለጹት፡፡

አባ ጊዮርጊስ በመጻሕፍት አዋቂነቱ እና በቅድስናው የተመሰከረለት አባት ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተነሡ የመናፍቃንን ጥያቄዎች በቃልም በመጽሐፍም በመመለስ ይታወቃል፡፡ በገድሉ ላይ ተጠቅሰው ከምናገኛቸው የቃል ክርክሮች አንዱ የአይሁዳዊው ታሪክ ነው፡፡ በአንድ ወቅት አንድ አይሁዳዊ ጌታችሁ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነአልዓዛርን የት ቀብራችሁት?› ብሎ ለምን ጠየቀ?” ብሎ በጠየቀ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እግዚአብሔር አብ በኦሪት ለምንአዳም ሆይ ወዴት ነህ?› ብሎ ጠየቀው? አብርሃምንስሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?› ብሎ ለምን ጠየቀው?” በማለት እንዳሳፈረው በገድሉ ተጽፏል፡፡

አባ ጊዮርጊስ ብዙ ድርሳናትን ደርሷል፤ የሚበዙት የምስጋና ድርሰቶች ናቸው፡፡ ከጻፋቸው ብዙ መጻሕፍት መካከል አንዱ መጽሐፈ ምሥጢር ነው፡፡ መጽሐፈ ምሥጢር በቤተ ክርስቲያናችን ከሚጠቀሱ የዕቅበተ እምነት መጻሕፍት ውስጥ አንዱ ሲሆን የአባ ጊዮርጊስ የነገረ ሃይማኖት ሊቅነቱ የተመሰከረበት መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ አባ ጊዮርጊስ በነገረ እግዚአብሔር ላይ ጽርፈት የተናገሩ መናፍቃንን ለመገሠጽና ለእነርሱ መልስ ለመስጠት የጻፈው መጽሐፍ ነው፡፡ በምን ዓይነት ቅንዐተ መንፈስ ቅዱስ ተነሣሥቶ መልስ እንደሰጠ ሲነግረን “… የቅዱሳንን ዜናቸውን ለመናገር ፍቅር ግድ ይለኛል፤ ቅንዐትም ከሐዲዎችን እነቅፋቸው ዘንድ ያስገድደኛል፤ ፍቅር ክርስቶስን እንዳመሰግነው ግድ ይለኛል፤ ቅንዐትም ሰይጣንን አወግዘው ዘንድ ያስገድደኛል፤ ፍቅር የክርስቶስን ሐዋርያት እንድከተላቸው ያስገድደኛል፤ ቅንዐትም ዝንጉዎችን እንድዘልፋቸው ግድ ይለያኛል፤ ፍቅር ሰማዕታትን አወድሳቸው ዘንድ ግድ ይለኛል፤ ቅንዐትም ጠንቋዮችን እንድዘልፋቸው ያስገድደኛልበማለት ይገልጽልናል፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በዚህ መንፈሳዊ ቅናቱ ምክንያት እግዚአብሔር የገለጠለትን ምሥጢር አምስት ጸሐፊዎችን ሰብስቦ እርሱ በቃል እየነገራቸው በሁለት ዕለታት ጽፈውታል፡፡ መጽሐፉ ሲያልቅ ጸሓፊዎቹ እጅግ አደነቁ፡፡ ምሥጢረ እግዚአብሔርን እየሰማ ያጻፈው አባ ጊዮርጊስም ጽሑፉን ተመልክቶ አደነቀ፤ እኔ የዚህን መጽሐፍ ቃል አልተናገርኩም፤ መንፈስ ቅዱስ በእኔ አንደበት ተናገረ እንጂ በማለት ተናግሯል፡፡ ይህንም መጽሐፍ የመለኮትን ነገር ይናገራልና መጽሐፈ ምሥጢር”  ሲል ሰየመው፡፡ መጽሐፉ በመጀመሪያ የተጻፈው በግእዝ ቋንቋ ሲሆን አሁን ግን ወደ አማርኛ ተተርጕሞ በብዙዎች እጅ ደርሷል፡፡

የመጽሐፈ ምሥጢር አጻጻፍ ወይም መልስ አሰጣጥ ስልትን ስንመለከት አባ ጊዮርጊስ በየምዕራፉ በምስጋና ይጀምራል፡፡ ከምስጋና ቀጥሎ መልስ የሚሰጣቸውን መናፍቃን ኑፋቄና ጥንተ ታሪክ ይገልጻል፡፡ ደርሰውበት የነበረውን የክህነት መዐርግ ጠቅሶ ከተናገሩት የክሕደት አዘቅት ጋር በማወዳደር ይወቅሳቸዋል፡፡ ከዚያም ለኑፋቄያቸው የተራቀቀ የነገረ ሃይማኖት ዕውቀቱን ተጠቅሞ ከብሉይና ከሐዲስ እየጠቀሰ መልስ ይሰጣል፡፡ በመልሱ ውስጥ በብሉይም ሆነ በሐዲስ የተነገሩ ትንቢትና ምሳሌዎችንም መንፈስ ቅዱስ በገለጠለት መሠረት ትርጉም ለአንባብያን ግልጥ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ለመናፍቃኑ መልስ በአብዛኛው የጠቀሰው ከብሉይና ከሐዲስ ነው፡፡ ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ለመናፍቃኑ መልስ የሰጠበትን ክፍል ዘለፋ፣ ወቀሳ” ይለዋል፡፡

ሊቁ በእግዚአብሔር ላይ የነቀፋ ቃል የተናገሩትን ይዘልፋቸዋል፣ ይገዝታቸዋል፣ ይረግማቸዋል፡፡ በሥላሴ ላይ የነቀፋ ቃል ባይናገሩም እንኳን የተሳሳተ ትምህርት ያስተማሩትን ደግሞ በጽድቅ ጎዳና ስላልቆሙ እንዘልፋቸዋለን፤ ርግማን ግን በሥላሴ ላይ ሐሰት ስላልተናገሩ አንረግማቸውም በማለት በተግሣጽ ያልፋቸዋል፡፡ በየአርእስቱ መጨረሻም በሃይማኖት አባቶቹን እንደሚመስል በምግባር ግን ደካማ እደሆነ በመጥቀስ አንባብያን በጸሎት እንዲያግዙት በመማጸን ያጠቃልላል፡፡ ይህም ቅዱስ ጴጥሮስ በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን በየዋሕነትና በፍርሃት ይሁን (፩ኛ ጴጥ. ፫፡፲፭) ያለውን ፍርሃትና የዋህነት የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤ ዳግም የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ፣ ስለ እኔ ለምኑ፤ ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆነው መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ በማለት እንዳስተማረው፡፡

አባ ጊዮርጊስ በመጽሐፉ ለአሕዛብ፣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለሚታወቁ መናፍቃንና በዘመኑ ለተነሡ እንደ ቢቱ ላሉ መናፍቃን መልስ ሰጥቷል፡፡ አጠቃላይ መልስ የሰጠባቸውን ርእሰ ጉዳዮች ስናይ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ ነገረ ክስቶስ፣ ነገረ መንፈስ ቅዱስ፣ ነገረ ማርያም ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ በአንድ ማሕቀፍ ሥር የማይጠቃለሉ ለሌሎች ልዩ ልዩ ጉዳዮችም መልስ ሰጥቷል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ መናፍቃንና ከሐዲያን  ላነሧቸው የኑፋቄ ትምህርቶች የሰጠዉን መልስ በማሳየት ምእመናን ከመሰል ክሕደቶች እንዲጠበቁ ማድረግ ነው፡፡ የእኛ ታሪክ አለማወቅ እንጂ አዲስ ኑፋቄም፤ አዲስ ትምህርትም አለመኖሩን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለሚያጠና በሦስቱ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት መልስ የተሰጠባቸውን ኑፋቄዎች አባ ጊዮርጊስ የጻፈውን መጽሐፈ ምሥጢር በቅርቡም መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ እና አለቃ አያሌው ተአምሩ የሰጧቸውን መልሶች ማየት ተገቢ ነው፡፡

ከሐዋርያት ጀምሮ እስከ ዘመነ ሊቃውንት ለተነሡት መናፍቃን የቤተ ክርስቲያን አባቶች መልስ ሰጥተዋል፡፡ ጉባኤ ዘርግተው፣ ተከራክረው መንፍቃንን አሳፍረው መልሰዋል፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ የቀደሙ አባቶችን አክሎና መስሎ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመተርጎምና የሊቃውቱን ቃል በማራቀቅ መልስ በመስጠቱ የአባቶቹ የግብር ልጅ መሆኑን አስመሰከረ፤ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፣ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው የሚለውንም አሳየን፡፡ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ ከሰጠው ትምህርት መካከልም የሚከተለው ኃይለ ቃል ተጠቃሽ ነው፤ አብ ብርሃን አንደሆነ ወልድም ለሰው ሁሉ የሚያበራ ብርሃን ነው፡፡ ወልድ ብርሃን እንደሆነ መንፈስ ቅዱስም ፍጹም በሆነ አንድ ጸዳል ያለ ብርሃን ነው፡፡ አብ የማይዳሰስ እሳት እንደሆነ ወልድም የማይያዝ እሳት ነው፡፡ ወልድ የማይያዝ  እሳት እንደሆነ መንፈስ ቅዱስም በሃይማኖት ሙቀት ቤተ ክርስቲያንን የሚያሞቃት እሳት ነው፡፡ አብ የማይታይ ኃይል እንደሆነ ወልድም ሰው በመሆኑ ካልሆነ በቀር የማይገለጥ ኃይል እንደሆነ መንፈስ ቅዱስም ከጥፋት ሰዎች መነሣሣት የተነሣ እንዳትናወጽ ቤተ ክርስቲያንን የሚጠብቃት ኃይል ነው፡፡ አብ ፍጹም አምላክ እንደሆነ ወልድም ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ወልድ ፍጹም አምላክ እንደሆነ መንፈስ ቅዱስም በአንድ ኅብር መልክእ ያለ ፍጹም አምላክ ነው፡፡

ከዚህ በመቀጠል መናፍቃን አንሥተዋቸው ሊቁ በመጽሐፈ ምሥጢር ኦርቶዶክሳዊ መልስ የሰጠባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች እናቀርባለን፡፡

፩. ምሥጢረ ሥላሴ

፩.፩ ሰባልዮስ

ሰባልዮስ በአባ ጊዮርጊስ አጠራር ሰብልያኖስ” ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣ መናፍቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ገጽ ነው፤ አንዱ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን አብ፣ በሐዲስ ኪዳን ወልድ፣ በበዓለ ኀምሳ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ ተገለጠይላል፡፡ በአጭሩአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ገጽ ነው የሚል የኑፋቄ ትምህርት ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ በሊቃውንቱ ቋንቋ የሰባልዮስ ኑፋቄ አንድ ገጽ (ሞናርኪያኒዝም) ሲባል ተከታዮች ደግሞ ሰባልዮሳውያን” ይባላሉ፡፡ የሥላሴን አካላት አንድ አድርገው በመናገራቸውም ሰቃልያነ አብ ይባላሉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ለሰባልዮስ ከብሉይ ከሐዲስ እየጠቀሰ መልስ ሰጥቷል፡፡ ሊቁ እኛ ግን ሦስት ገጽ አንድ ባሕርይ፣ ሦስት አካል አንድ አምላክ፣ ሦስት ስሞች አንድ እግዚአብሔር እንላለን በማለት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ይመሰክራል፡፡ ሰባልዮስንም ተጠራጣሪ ሆይ እንግዲህ ባንተ ያለውን ክሕደት ትተህ በሥላሴ እመን፤ ለሥላሴ ገጻትም ምስጋናን አቅርብ በማለት ይመክረዋል፡፡

ይቆየን

መጽሐፍ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ዐይን

የካቲት ፳፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ የታነፀች፣ ከሁሉ በላይ የሆነች አንዲትና ቅድስት አካለ ክርስቶስ ናት (ኤፌ. ፩፥፳፪፤ ኤፌ. ፪፥፳)፡፡ ‹‹ከሁሉ በላይ የሆነች›› የሚለው ሐረግ ሰማያዊ ሥልጣኗን እና ልዕልናዋን የሚገልጽ ነው፡፡ ይህም ማለት የትኛውም ቅዱስ መጽሐፍ ወይም ንዋይ በእርሷ ውስጥ ይሆናል እንጂ ከበላይዋ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የገለጸውን እውነት የያዘ እንጂ ከቤተ ክርስቲያን በላይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ስለሆነች ከክርስቶስ አካልነት በላይ የሆነ ስለሌለ ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን በላይ ያለ የቤተ ክርስቲያን ራስ ክርስቶስ ብቻ ነው (ቆላ. ፩፥፲፰)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የመጻሕፍት ሁሉ ራስ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ናት፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ቋንቋ የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ የተጻፈውም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ነው፡፡ ጸሓፊዎቹ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ናቸው፡፡ በቅድስናቸው ለእግዚአብሔር ቅሩባን ስለሆኑ የእግዚአብሔር ቃል ለሚላክላቸው አብያተ ክርስቲያናት በሚገባቸው ቋንቋ ጽፈዋል፡፡ መጻፋቸውም የእነርሱን ክብር ለመግለጽና ቤተ ክርስቲያን የምትመራበትን ሕግ ለመደንገግ ሳይሆን ቤተ ክረስቲያን የምታምነውን እምነት ለመመስከርና በመንፈሳዊ ሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ያሉ ምእመናን እንዲመከሩበት፣ እንዲገሠጹበት፣ ልባቸውን እንዲያቀኑበት ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የገለጠውን እውነትና ቤተ ክርስቲያን ስለ እግዚአብሔር የምታምነውን እምነት የያዘ እንጂ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ተሰፍሮና ተቈጠይሮ ሁሉ ነገር የተካተተበት ማለት አለመሆኑን መረዳት ይገባል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በማየት፣ በማድረግ፣ በቃል የሚተላለፍ ብዙ ሀብት አላት፡፡ እንዲያውም የተጻፈው በጣም ጥቂቱ ነው፡፡ ሆኖም በአንዳንድ የእምነት ድርጅቶች ዘንድ ነገረ ቤተ ክርስቲያንን በሙሉ ጠቅልሎ በመጽሐፍ ሥር የማድረግ የተሳሳተ አካሔድ አለ፡፡ ይህም በሉተራውያን ዘንድ “Sola Scriptura” ወይም “Only Bible” (መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ) ተብሎ የሚታወቀው ሲሆን ያልተጻፈው ቅዱስ ትውፊትም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የማይደግፈው ግለሰባዊ አሳብ እንጂ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት አይደለም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትን የምትቀበልበትን ሃይማኖታዊ እይታ በግልጽ ማሳየት ነው፡፡

የቅዱሳት መጻሕፍት ጥንተ ታሪክ

ፈጣሬ ኵሉ ዓለም እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ እጅግ አክብሮ የፈጠረው የሰው ልጅን ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይህን ክብሩን ሲገልጹ ሰውን “የፍጥረታት አክሊል – The Crown of Creation” ብለው ይጠሩታል፡፡ የፍጥረታት አክሊልነቱም በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ መፈጠሩ፣ ፍጥረታትን ሁሉ ከእግዚአብሔር በታች እንዲገዛ በፍጥረታት ላይ መሠልጠኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር “ሥሉጥ በላዕለ ኵሉ ፍጥረት፤ በፍጥረት ሁሉ ላይ የሠለጠነ (ሥልጣን ያለው)” እንደሆነ ሁሉ ሰውንም በጸጋ “ሥሉጥ በላዕለ ኵሉ ምድር፤ በምድር ሁሉ ላይ የሠለጠነ (ሥልጣን ያለው)” አድርጎታል፡፡ በጥንተ ተፈጥሮው የሰው ልጅ መጻሕፍትም ሆኑ መምህራን የማያስፈልጉት ዐዋቂ ፍጥረት ነበር፡፡ እንደ አባ ማቴዎስ በአእምሮ ጠባይዕ፣ እንደ አብርሃምና እንደ ሙሴ ጸሊም በሥነ ፍጥረት ተመራምሮ የሚያውቅ ማለት ነው (ትርጓሜ ወንጌለ ዮሐንስ)፡፡ በለባዊ አእምሮው ሥነ ፍጥረትን አንብቦና መርምሮ ረቂቁን እውነት የሚረዳ ከሃሊ ዘበጸጋ ነበር፡፡ የሰው የመጀመሪያ መጽሐፍም ሥነ ፍጥረት ነው፡፡ ለሰው የመጀመሪያ እውነተኛ መምህሩ መምህረ ኵሉ ዓለም እግዚአብሔር ነው፡፡

እግዚአብሔር ለአዳም ትእዛዛቱን አስተማረው፡፡ ከመጀመሪያ ትምህርቶቹም ዋናው “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና” (ዘፍ. ፪፥፲፮-፲፯) የሚለው ነበር፡፡ አዳም ግን እውነተኛ መምህሩን ትቶ የክፉ ፍጡር ትምህርትን ተማረ፤ “ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” (ዘፍ. ፫፥፬-፭) ብሎ ሰይጣን የነገረውን ሰማ፡፡ ተማሪው ከሁለቱ ትምህርቶች ሁለተኛውን መረጠና በፈተና ወደቀ፡፡ የመጀመሪያ መምህሩን ትምህርት ይረዳም ዘንድ ከዚያ በኋላ ብቁ ልቡና አልነበረውም፡፡ ወደ ታላቁ መምህር ለመመለስ ሌሎች መምህራን እንዲደግፉት ግድ ሆነ፡፡

ክፉው መምህር ካሳታቸው በኋላ አዳምና ሔዋን ያልተጻፈውን ፊደል አዩ፣ ያልተከተበውን አነበቡ፡፡ “ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች (ዘፍ. ፫፥፮) እንዲል፡፡ ከዚህም በኋላ ፍጥረታትን የሚያነቡ ሳይሆኑ ፍጥረታት የሚያስደነግጡአቸው ድንጉጦች ሆኑ፡፡ እግዚአብሔር ካደላቸው ከንጽሐ ጠባይ ደረጃ ስለወደቁና ወደ ቀደመ ክሂሎታቸው መመለስ ስላልቻሉ በሰውኛ ፊደል የተጻፉ መጻሕፍትን በማንበብ መመርኮዝ ግድ ሆነባቸው፡፡ የሰው ልጅ ፍጡር ባልሆነ ብርሃን ረቂቁንና የማይታየውን ዓለም ከማየት እና በማየት ከሚገኘው ዕውቀት ከመስማት ወደሚገኘውና ውስን ወደሆነው ዕውቀት በመውረዱ ምክንያት መጽሐፍ አስፈለገው፡፡ ስለዚህ መጻሕፍት የሰው የባሕርዩ መምህራን አይደሉም፡፡ ከውድቀቱ በኋላ የተሰጡት ደጋፊዎች እንጂ፡፡ ይህንም የቤተ ክርስቲያን መምህራን በሚከተለው ምሳሌ ይገልጹታል፤

ሰው የሚራመደው በሁለት እግሩ ነው፡፡ እግሩን ሲታመም ወይም ሲያረጅ በሁለት እግሩ መራመድ ስለሚያቅተው ምርኩዝ ይይዛል፡፡ ልክ እንደዚሁ ሰው በቅድመ ተፈጥሮው በራሱ መቆምና መራመድ የሚችል ነበር፡፡ ነገር ግን በኃጢአት ካረጀና ከታመመ በኋላ መቆምም መራመድም ይችል ዘንድ መጻሕፍትና መምህራን ምርኩዝ እንዲሆኑት ተሰጡት፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜው ይህን ይበልጥ ሲያብራራልን “በቀለም ከተቀረፁ የመጻሕፍት ቃላት ይልቅ በልቡናችን ያደረ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ይመራን ዘንድ እጅግ ንጹሕ ሕይወት ሊኖረን እንጂ የተጻፈ ነገር ሊያስፈልገን አይገባም ነበር” ብሏል፡፡ ይህን ካለ በኋላ ግን መጻሕፍትን በጥንቃቄ መያዝ እንደሚገባን ሲያስተምረን “ይህን ጸጋ ከእኛ እንዲርቅ አድርገናል፡፡ እንግዲህ ሁለተኛውን ታላቅ ስጦታ (መጻሕፍትን) አጥብቀን እንያዝ” ብሏል፡፡ ይህ ሁሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ከጊዜ በኋላ አስፈላጊ በመሆናቸው የተሰጡ እንጂ ሁሉ ነገር ከእነርሱ የጀመረ አለመሆኑን የሚያስረዳ  ነው፡፡

ወንጌል ከተጻፈውም በላይና የቀደመች እንደሆነች

ብዙ ጊዜ ወንጌል ስንል አራቱ የወንጌላውያን መጻሕፍት ብቻ ቀድመው ይታሰቡን ይሆናል፡፡ አንዳንድ “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚሉ የእምነት ድርጅቶች እንደሚሉትም የተጻፈው ብቻ ወንጌል የሚመስለንም እንኖር ይሆናል፡፡ የተጻፈውም ሆነ ያልተጻፈው ቅዱስ ትውፊት ግን ወንጌል በጽሑፍ ብቻ የተገደበ እንዳልሆነ ያስተምረናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤” ሲል አራቱ ወንጌላት ተጠቃለው አልተጻፉም ነበር (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፩)፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል” ብሎ ስለ ማርያም እንተ ዕፍረት በመሰከረ ጊዜ ማቴዎስም፣ ማርቆስም፣ ሉቃስም፣ ዮሐንስም ገና ወንጌልን አልጻፉም ነበር (ማቴ. ፳፮፥፲፫)፡፡ ይህ ቃል በተነገረ ጊዜ እንኳን ወንጌልን ሊጽፉ እምነታቸውም የተሟላ አልነበረም፡፡ ይህም በመከራው ጊዜ ከዮሐንስ በስተቀር ሁሉም በመሸሻቸው ተገልጧል፡፡ ስለዚህ ጌታ “ይህ ወንጌል” ሲል የተጻፈውን ብቻ የምናስብ ከሆነ ስሕተት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ወንጌል በቃልም፣ በመጽሐፍም፣ በሕይወትም የምትሰበክና የተሰበከች እንጂ በመጻሕፍት ተጠቃላና ተካትታ የተቀመጠች ብቻ አድርጎ ማሰብ ስሕተት ነው፡፡ ሐዋርያት በቃልም በመጽሐፍም ሰብከዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ በሕይወቱ ባገኘው መገለጥ ተሰብኳል (ሐዋ. ፱)፡፡ እንዲያውም የቅዱሳት መጻሕፍት ጸሐፍያን በጽሑፍ የተሰበከው ጥቂት መሆኑንና በቃል ብዙዎች እንደተሰበኩ ገልጸዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን ጽፎ ሲያጠቃልል “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” (ዮሐ. ፳፩፥፳፭) የሚለው ሁሉ ነገር አለመጻፉን ያስረዳል፡፡ ስለዚህ ከተጻፉት በላይ ቤተ ክርስቲያን በትውፊት ያቆየችልን ብዙ ነገር መኖሩን መረዳት ተገቢ ነው፡፡

ቅዱስ ሉቃስም ገና ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር ለሚጽፍለት ቴዎፍሎስ ለተባለው ሰው “የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ፥ ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን፥ በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ፥ እኔ ደግሞ ስለ ተማርከው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ” (ሉቃ. ፩፥፩-፬) ብሏል፡፡ ይህ በዓይን ያዩ፣ ወንጌልን ሳይጽፉ በቃል ወይም በሌሎች መጻሕፍት ያስተማሩና ለነቅዱስ ሉቃስም ያስተላለፉ መኖራቸውን በቅድሚያ ሲያስረዳ ወንጌሉ የተጻፈለት ቴዎፍሎስ እንኳን አስቀድሞ በቃል መማሩንም የሚያሳይ ነው፡፡ ቅዱስ ሉቃስም እርግጡን ያውቅ ዘንድ ወይም ያረጋግጥ ዘንድ ጻፈለት እንጂ ከዚያ በፊት ያልተማረ ስላልነበር ለማስተማርና ለማሳወቅ የጻፈለት አይደለም፡፡

ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቱ ይቀድማል?

ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ በፊት የነበረችና መጽሐፍ ቅዱስን የጻፈች፣ ከእግዚአብሔር የተቀበለችውን በመጽሐፍ የተቀመጠውን እውነት ጠብቃ ያስተላለፈች የእግዚአብሔር መንግሥት ናት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በቤተ ክርስቲያን ለቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ከተጻፉት መጻሕፍትም ውስጥ አምላካውያት የሆኑትን በቀኖና ለይታና ቀድሳ ለምእመናን የሕይወት ምግብነት የሰጠች መሆኗን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትቀድማለች፤ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ለመሆኑም ምስክሯ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የጻፈችውና የምትተረጉመው እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ያስገኘ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለአዋልድ መጻሕፍት ወላጃቸው ነው፡፡ ይህንም በብዙ ማስረጃና አመክንዮ እንደሚከተለው እናያለን፤

፩. መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የቤተ ክርስቲያንን ቀዳሚነት ይመሰክራል

የሚከተሉት ጥቅሶች ቅዱሳት መጻሕፍቱ ከመጻፋቸው በፊት ቤተ ክርስቲያን እንደነበረች በደንብ ያስረዳሉ፤

  • በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፥ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት (፩ኛ ቆሮ. ፩፥፪)፡፡

አንድ መልእክት (ደብዳቤ) ሲጻፍ ሦስት አካላት መኖራቸውን መረዳት ተገቢ ነው – ላኪው፣ መልእክቱና ተቀባዩ፡፡ ላኪውና ተቀባዩ በሌሉበት መልእክቱ ሊጻፍ አይችልም፡፡ የመልእክቱ ላኪ ቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡ ተቀባይዋ ደግሞ በቆሮንቶስ አገር ያለች የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ከመልእክቱ ላኪውና ተቀባዩ የሚቀድሙ ከሆነ መልእክቱን ለመቀበል ቅዱስ ጳውሎስንና ቤተ ክርስቲያንን በቅድምና መቀበል ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይህን ሲያስረዳ ቅዱስ ጳውሎስ ገና መልእክቱን ለመጻፍ ሲጀምርና ለማን እንደሚጽፍ ሲገልጽ “በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን” ማለቱ እርሱ መልእክቱን ከመጻፉ በፊት የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን እንደነበረች የሚያሳይ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ቀድማ መኖሯ ብቻ ሳይሆን ሰዎችን ስትቀድስም ነበር፡፡ በሌላ አገላለጽ ሰዎችን ለመቀደስ የግድ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈው መልእክት አላስፈለጋትም ነበር፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ የመልእክቱ ባለቤት “በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት” በማለት ገለጸ፡፡ ይህን የመሰሉና ተመሳሳይ እውነትን የሚመሰክሩ ብዙ ጥቅሶችን ማንሣት ይቻላል፡፡

  • በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ ወንድሙም ጢሞቴዎስ፥ በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፤” (፪ኛ ቆሮ. ፩፥፩)፡፡
  • “በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ፥ ወደ ገላትያ አብያተ ክርስቲያናት፤(ገላ. ፩፥፩)፡፡
  • ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር አብ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ (፩ኛ ተሰ. ፩፥፩)፡፡
  • እንዲሁም የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈሕ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊልድልፍያም ወደ ሎዶቅያም በእስያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ” (ራእ. ፩፥፲፩)፡፡ ባለራእዩ ቅዱስ ዮሐንስም በተመሳሳይ ራእዩን ካየ በኋላ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲጽፍ ተገለጸለት፡፡ ይህም ከመጽሐፉ በፊት አብያተ ክርስቲያናቱ እንደነበሩ የሚያስረዳ ነው፡፡ ዮሐንስም ራእዩን በማየት ይከብር ዘንድ መጽሐፍ አላስፈለገውም ነበር፡፡

፪. አመክንዮአዊ ማረጋገጫ

ከመጻሕፍት ሁሉ ቀድሞ የተጻፈው መጽሐፈ ሄኖክ ነው፡፡ መጽሐፈ ሄኖክ ከመጻፉ በፊት ሰው ከአንድ ሺሕ ዓመት በላይ ያለ መጽሐፍ ኖሯል፡፡ መጽሐፈ ኢዮብና አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት ከዚያ በመቀጠል ተጻፉ፡፡ የነቢያት መጻሕፍት ሺሕ ዓመታት ዘግይተው ክርስቶስ ሊወለድ በመቶዎች የሚቈጠሩ ዓመታት ሲቀሩት ተጻፉ፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ለመጀመሪያዎቹ ዐርባ ዓመታት መጻሕፍት አልተጻፉም፡፡ ከዚያ በኋላም የማቴዎስ ወንጌልንና የያዕቆብ መልእክትን የመሰሉት ቀድመው ተጻፉ እንጂ አብዛኞቹ የተጻፉት እስከ ፸ ዓ.ም. ድረስ ቆይተው ነው፡፡ የሐዲሳት መጻሕፍት የተጻፉት ደግሞ በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት መገባደጃ ነበር፡፡ ይህም የሚያስገነዝበው፡-

ሀ. ለጽድቅና ለድኅነት የሚያስፈልገው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ቢሆን ኖሮ መጽሐፉ በአንዴ አልቆና ተጠቃሎ ከአዳም ጀምሮ ላሉት ሁሉ ካለመድሎ መሰጠት አልነበረበትምን? መጽሐፍ ያልተሰጣቸውስ “እኛ በኃጢአት የወደቅነው መጽሐፍ ቅዱስ ስላልነበረን ነው” ብለው ምክንያት እንዲያቀርቡ ዕድል አይፈጥርላቸውም ነበርን? አምልኮን በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የምንገድበው ከሆነ ለሁሉም ሁሉንም መጻሕፍትን ባለ መስጠቱ የእግዚአብሔር ፈታሒነት ላይ ጥያቄ አያስነሣም ነበርን?

ለ. በጥንቱ ዘመን መጻሕፍት ለየተጻፉላቸው ሰዎች በጥቅል (Scroll) መልክ ይገኙ ነበር እንጂ አሁን እንዳለው ሁሉም በአንድነት ተጠርዘው በአንድ ሰው እጅ ማግኘት አይቻልም ነበር፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ባለው መልኩ ተሰብስቦ በአንድነት መገኘት የቻለው የማተሚያ ማሽን ከተሠራና በወረቀት ማተም ከተጀመረ በኋላ ነው፡፡ ምዕራፍና ቊጥር ወጥቶለት ለንባብ አመቺ የሆነው ደግሞ ከዐሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በኋላ ነው፡፡ በጥንቱ ዘመን እያንዳንዱ መጽሐፍ በየቦታው በጥቂት መጠን ብቻ ይገኝ ነበር፡፡ የሮሜ መልእክት የሚገኘው ሮማውያን ዘንድ፣ የቆሮንቶስ መልእክት ከቆሮንቶስ ሰዎች ዘንድ … ወዘተ እንጂ እንደዚህኛው ዘመን በአንድ ጊዜ ተባዝተው ሁሉም ዘንድ የሚገኙ አልነበረም፡፡ ለዐራት ሺሕ ዓመታት ያክል የተጻፉትን እነዚህን ቅዱሳት መጻሕፍት ከሐሰተኞቹ ለይታና በቀኖና ወስና “እነዚህን ተጠቀሙ” ያለችው ቤተ ክርስቲያን አይደለችምን?

ቤተ ክርስቲያን ይህን ባታደርግ እኛም ከመጽሐፍ ቅዱስ ፈጽሞ የማንገናኝ በሆንን ነበር፡፡ ወንጌላትን በጊዜው ብዙዎችን ያስቱ ከነበሩት “የይሁዳ ወንጌል”፣ “የበርናባስ ወንጌል” ከተባሉትና እነዚህን ከመሰሉት እንዲሁም “የማቴዎስ፣ የማርቆስ ወንጌል” ተብለው ብዙ ሐሰት ከተጨመሩባቸው ለይታ “መጻሕፍተ ወንጌላት ዐራቱ ብቻ ናቸው” ባትለን ኖሮ በብዙ ጥፋት ውስጥ የምንሆን አልነበርንምን? እርሷ በቀኖና ሰፍራ ቈጥራ የሰጠችውን መጽሐፍ ተቀብሎ ሰጪዋን ቤተ ክርስቲያንን አልቀበልም ማለትስ ስሕተት አይደለምን? በተመሳሳይ መልኩ ቀኖናን ሠርታ አዋልድ መጻሕፍትን ስትሰጥ አለመቀበልስ አለማወቅ አይደለምን?

ሐ. የቤተ ክርስቲያንን ከሁሉ በላይ መሆንና ፍጹም የሆነ ሥልጣኗን የምናውቅ አሥራው መጻፍት ተብለው የሚታወቁት መጻሕፍትን ሰብስቦ ሰማንያ አንድ ብቻ ናቸው ብሎ ማን ነገራችሁ? ብንባል “ቤተ ክርስቲያን” እንላለን፡፡ “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚሉት ወገኖች ግን “መጽሐፍ ቅዱስን ‘ስልሳ ስድስት’ ያላችሁ ማነው” ቢባሉ ማን ይሉ ይሆን? እንቀበላቸዋለን የሚሏቸው “ስልሳ ስድስትቱ መጻሕፍት” ራሳቸው “ስልሳ ስድስት ብቻ” ወይም “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” አይሉምና፡፡

፫. መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ አለመያዙን ያስረዳል

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ (ዮሐ. ፳፥፴) በማለት ክርስቶስ ያደረጋቸው ሁሉ የተጻፉ እንዳልሆነ አስረድቷል፡፡ እንዲያውም እርሱ ያደረገውን ሁሉንም እንጻፍ ማለት እንደማይቻል ሲገልጽ ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” ብሏል፡፡ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ታሪክ፣ ሁሉንም ሥርዐት … ወዘተ ጠቅልሎ እንዳላካተተ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህን ስንል ግን በጽሑፍ ደረጃ አልዘረዘረም ማለታችን እንጂ ከምሥጢር ምልዐት አንጻር የጎደለው ነገር አለው ማታችን አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሁሌም ምሉዕ ነውና የእግዚአብሔር ቃል የሚገኝበት መጽሐፍም ሕፀፅና ጉድለት የማይገኝበት ምሉዕ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ባነሣው ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መንፈሳዊ ዕውቀት የምንፈልግ ከሆነ የቀረው ነገር የት እንደሚገኝ አዋልድ መጻሕፍትን ጠቁሞናል እንጂ “ሁሉንም ጠቅልዬ ይዣለሁና እኔን ብቻ አንብቡ” አላለም፡፡ የሚከተሉት አሳቦችም ይህንኑ የሚያስረዱ ናቸው፡፡

  • የቀረውም ፊተኛውና ኋለኛው የሰሎሞን ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ፥ በሴሎናዊውም በአሒያ ትንቢት፥ ስለ ናባጥም ልጅ ስለ ኢዮርብዓም ባየው በባለ ራእዩ በአዶ ራእይ የተጻፈ አይደለምን?” (፪ኛ ዜና. ፱፥፳፱)፡፡
  • የቀረውም የሮብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?” (፩ኛ ነገ. ፲፬፥፳፱)፡፡
  • “የቀረውም የሰሎሞን ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ጥበቡም፥ እነሆ፥ በሰሎሞን ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል (፩ኛ ነገ. ፲፩፥፵፩)፡፡

ማጠቃለያ

መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ምንጭና ራስ ነው፡፡ ማንኛውም ትምህርት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ወይም ሥርዐት በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሰው ጋር የሚጋጭ ከሆነ በቤተ የቤተ ክርስቲያናችን ተቀባይነት የለውም፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን የትምህርተ ሃይማኖት ዋና ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የሥርዐትና የታሪክ ዋና ምንጭም መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዘውን የምትፈጽም፣ የምታስተምርና የምትኖር መጽሐፍ ቅዱሳዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስንም እንድናነበውና እንድንማርበት አዘጋጅታ የሰጠችን እርሷው ናት፡፡ ይሁንና አንዳንድ መናፍቃን መጽሐፍ ቅዱስን የሚከተሉ መስለው ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ያልሰበከች አስመስለው ስለሚያቀርቡ ተንኮላቸውን ተረድተን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የማይለውን እንደሚል አድርገው በማቅረብና አጣመው በመተርጎም የሚስቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ከሁሉ የምትቀድመውን ቤተ ክርስቲያን እየተቃወሙ እርሷ ለዓለም ሁሉ የሰጠችውን ቅዱስ መጽሐፍ የተቀበሉ የሚያስመስሉት፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከሚዋጉአት ክፍሎች ተሐድሶ ፕሮቴስታንቶች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ከሚያታልሉበት ፕሮቴስታንታዊ መንገድ አንዱ ደግሞ “መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚለው አስተምህሮ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም አመክንዮም የማይደግፉትን ይህን የስሕተት መንገድ በመያዝ ቤተ ክርስቲያንን ይከሳሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ቢሉም መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሰክርላትን ልዕልናዋን አይቀበሉም፡፡ የመረጡትን ይወስዳሉ፤ ያልተስማማቸውን ይተዋሉ፡፡ አስቀድመን እንዳየነው አንድ አማኝ ቤተ ክርስቲያን ሁሉን የምትይዝና ከሁሉ ይልቅ የበለጠች መሆኗን መረዳት ይገባዋል፡፡ አንድ ጥያቄ ቢፈጠርበት እንኳን በቤተ ክርስቲያ ውስጥ ካለ አይቸገርም፡፡ ምክንያቱም ዛሬ ያላወቀውን ነገ ያውቃል፤ ዛሬ ያልተረዳውን በሕይወትም፣ ከአባቶች ጠይቆም ይረዳል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ካላሳያችሁኝ የሚል አይሆንም፡፡ ይልቁንስ በመጽሐፍ ተጽፎ ያላገኘውን ከሁሉ ይልቅ ከፍ ካለችው ከቤተ ክርስቲያን ለማግኘት ይጥራል እንጂ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! ይህ ትምህርት፣ ከታኅሣሥ ፲፮ – ፴ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በታተመው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ በንቁ ዓምድ ሥር ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

አንቀጸ መድኃኒት ቤተ ክርስቲያን – ካለፈው የቀጠለ

የካቲት ፳፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

… ኵላዊት (ካቶሊክ፣ Universal) የሚለው አገላለጽ በምዕራባውያን (በካቶሊካውያን) አስተሳሰብ የተለየ ትርጕም አለው፡፡ በምዕራባውያን ዘንድ ለቤተ ክርስቲያን ኵላዊት መሆን ዋናው መሠረቱ ለሮሙ ፖፕ መታዘዝ ነው፡፡ በእነርሱ አስተሳሰብ መሠረት የማይሳሳትና የክርስቶስ ወኪል አድርገው ለሚቈጥሩት ለፖፑ የማትገዛ ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት አይደለችም፡፡ በምሥራቃውያንና በኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ኵላዊት የሚያሰኛት ሥላሴ በአንድነት በሦስትነት የሚመለኩባት፣ ከሐዋርያት ጀምሮ ባልተቋረጠ ክትትል ጳጳስ ያላትና የክርስቶስ ሥጋና ደም የሚፈተትባት መሆኗ ነው፡፡ ኵላዊትነት በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንድነት (በተለይም በቅዱስ ቊርባን) እንጂ በፖፕ አንድ መሆን አይደለምና፡፡

ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ ወደ ስሚርናስ በላከው መልእክቱ እንደተናገረው፥ ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት (ፍጽምት፣ ርትዕት፥ ሁሉንም የምትይዝ) የምትባለው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የሚፈተትባት በመሆኗ ነው፡፡ በዚህ ቅዱስ ምሥጢር አማካይነት በየትኛውም ሥፍራ የምንኖር ክርስቲያኖች (በግብፅም፣ በኢትዮጵያም፣ በሰማይም፣ በምድርም) አንድ ወደ መሆን፣ ወደ ፍጽምና፣ ወደ እውነት እንመጣለን፡፡ በመሆኑም ያለዚህ ምሥጢር ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት አትባልም፡፡ በዚህም የሐዋርያውያነ አበው ትምህርት መሠረት ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን አማናዊ አይደለም፤ አምሳል ነው የሚሉ ሰዎች ስብስባቸው ቤተ ክርስቲያን እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡

. አንዲት

እግዚአብሔር አንድ ነው፤ የክርስቶስም ማዳን አንዲት ናት፤ ተስፋ የምናደርጋት መንግሥተ ሰማያት አንዲት ናት፤ የምንቀበለው የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደምም አንድ ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ የተገለጠው እውነት ከነማብራሪያው አንድ ነው፡፡ ይህን የምታስተምር ቤተ ክርስቲያንም አንዲት ናት፡፡ የክርስቶስ አካል ስለሆነች አንዲት ናት፡፡ የክርስቶስ አካል አይከፈልምና ቤተ ክርስቲያን አንዲት እንጂ ብዙ አይደለችም፡፡ ይህቺ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ተአምኖዋ በአንድ እግዚአብሔር ስለሆነ መለያየት አይስማማትም፡፡ ምእመናኗም አንድ ትምህርት ይማራሉ፤ አንድ እምነት ያምናሉ፤ አንድ ጥምቀት ይጠመቃሉ፡፡ ሰዎች ወይም መላእክት ከእርሷ ውጪ ወጥተው በክሕደት በኃጢአት ሊሔዱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሌላ ቤተ ክርስቲያን ሊመሠርቱ አይችሉም፡፡ እንመሥርት ቢሉም የመሠረቱት ስብስብ ቤተ ክርስቲያን ተብለው ሊጠሩበት አይችሉም ምክንያቱም ከክርስቶስ የተለየች ቤተ ክርስቲያን የለችምና፡፡

ሰዎች በተለያየ መንገድ ከአንዲቷ ማኅበር ቢወጡም ቤተ ክርስቲያን ተከፋፈለች አይባልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን አትከፈልም፤ አንዱ እንግዚአብሔር አይከፈልምና፡፡ አንዳንድ ወገኖች ለራሳቸው በየሰፈሩ “ቸርች” ብለው ይመሠርታሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ስብስባቸው ፈጽሞ ቤተ ክርስቲያን ሊባል እንደማይችል ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናትና፡፡ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ የተመሠረተች እንጂ ሰዎች ተሰብስበው የሚመሠርቷት አይደለችም፡፡ በሰዎች መሰባሰብ የተመሠረተች፣ እግዚአብሔር በአንድነት በሦስትነት የማይመለክባት፣ ምሥጢራት የማይፈጸሙባት በመሆኗ ድርጅት ወይም ተቋም እንጂ ቤተ ክርስቲያን አትባልም፡፡ በክርስቶስ ደም ወደተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያን አንድነት መግባት የሚቻለው በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እንጂ በአንድነት ተሰብስቦ ስያሜ በመስጠት እንዳልሆነ ማወቅ ይገባናል፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የቤተ ክርስቲያን አንድነት፥ ክርስቲያኖች በእውነት አምነው በፍቅር ተመላልሰው ከእግዚአብሔር ጋር በሚፈጥሩት አንድነት የሚመዘን ነው፡፡ ይህን አንድነት ሰዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰብስበው ወይም የፍርድ ቤት ፈቃድ ይዘው ሊመሠርቱት አይችሉም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረታት እግዚአብሔር ነውና፡፡ ማንኛውም ሰው የቤተ ክርስቲያን አካል ሆኖ የሚኖረው ወይም ክርስቲያን ነው የሚባለውም በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እስካለ ድረስ ብቻ ነው፡፡ የአንድነታችን መሠረቱም በሥጋ ወደሙ የታተመው የክርስቶስ አካልነታችን ነው፤ ጌታ እንዲህ እንዳለ፡- “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በርሱ እኖራለሁ” (ዮሐ. ፮፡፶፮)፡፡ “አባት ሆይ፥ አንተ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ” (ዮሐ. ፲፯፡፳፩)፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ (Society) ሳትሆን የምእመናን አንድነት ናት፡፡ ጌታችንም የዚህች አንድነት ራስ ነው፡፡

በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን አሠረ ፍኖት ተከትላ የምትሔድና ክርስቶስን የምታምን እርሱ ራስ ሆኖላት አካሉና በእርሱ ውስጥ ያለች ናት፡፡ ክርስቲያኖች የዚች አንድነት አካል የሚሆኑት፣ በአንድነቱ ውስጥ ጸንተው የሚኖሩትና እግዚአብሔርን ወደ መምሰል የሚያድጉት በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ሲታመሙም (በኃጢአት ሲወድቁም) በእነዚህ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እየታከሙ አንድነታቸውን ያጸናሉ፡፡ ከእርስዋ ውጭ ድኅነት የሌለውም ለዚህ ነው፡፡ “ዋናው በክርስቶስ ማመናችን ነው” ብለው የሚወጡት ሰዎችም ድኅነት እንዳገኙ አድርገው መናገራቸው ከዚህ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ያፈነገጠ ከመሆኑም በላይ ስሕተት ነው፡፡

ክርስቲያኖች በዚህች አንዲት ቤተ ክርስቲያን ስንኖር ከእግዚአብሔር ጋር ያለን አንድነት እያደገ እየጠበቀ ይሔዳል፡፡ ይህ አንድነትም በጊዜ ሒደት፣ ወይም በተለያየ ቦታ በመሆን የሚቋረጥ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በውስጧ ቅዱሳን መላእክትን እንዲሁም በብሔረ ሕያዋን፣ በብሔረ ብፁዓን፣ በገነት፣ በዐጸደ ሥጋና በዐጸደ ነፍስ ያሉትን ምእመናን ሁሉ የምትይዝ አንዲት ኅብረት ናት ማለታችንም ስለዚሁ ነው (ዕብ. ፲፪፡፳፪-፳፬)፡፡ በዐጸደ ነፍስ ያሉት ምእመናን በንስሓ የተመላለሱ፣ ሩጫቸውን የጨረሱና ድል ያደረጉ ሲሆኑ፥ በዐጸደ ሥጋ ያለን ደግሞ ሩጫችንን ገና ያልጨረስንና በተጋድሎ ውስጥ የምንገኝ ነን፡፡ ሐዋርያው እንዲህ እንዳለ፡- “እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን” (ሮሜ. ፲፪፡፭)፡፡ ይህ ትምህርት የነገረ ሃይማኖት መሠረት ነው፡፡ እንዲህ የተባለበትም ምክንያት በቤተ ክርስቲያን ምንነትና ማንነት ላይ ያለን ልዩነት ለጠቅላላ ነገረ ሃይማኖት መለያየት ምክንያት ስለሚሆን ነው፡፡  ይህን የሚያስረዱ ሁለት ማሳያዎችን በማንሣት እንመልከት፡፡

፩. በካቶሊካውያን ዘንድ አንድ ሰው የፖፑን የክርስቶስ እንደራሴነት ካልተቀበለ የካቶሊክ ቤተ እምነት አባል አይሆንም፡፡ በኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ግን ቅዱሳን መላእክት እንዲሁም በብሔረ ሕያዋን፣ በብሔረ ብፁዓን፣ በገነት፣ በዐጸደ ሥጋ ያለንና በዐጸደ ነፍስ የሚኖሩ ምእመናን አንድ የምንሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ አካልነት ነው፡፡ ይህም በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ የምናገኘው ጸጋ ነው፡፡

፪. በፕሮቴስታንቱ ዓለም ያለውን ስንመለከት ደግሞ በዐጸደ ሥጋ ያሉትና በዐጸደ ነፍስ ያሉት አማኞች የተለያዩ ናቸው፤ እርስ በርሳቸው አይተዋወቁም፡፡ በሌላ አገላለጥ እንደ እነሱ አባባል “ቤተ ክርስቲያን የሚታዩ አባላት ብቻ ያሏት ተቋም ናት”፡፡ የቅዱሳንን ምልጃ የማይቀበሉትም ስለዚሁ ነው፡፡ ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ ከላይ ከነገረን (ዕብ. ፲፪፡፳፪-፳፬) የእውነት መሠረት የተለየ ትምህርት ነው፡፡ ዳግመኛም ይህ የፕሮቴስታንቶቹ አስተምህሮ (አይቻልም እንጂ)፥ ስሙ ይክበር ይመስገንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ያደረገንን የሚለያይ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ ሰው ቤተ ክርስቲያን መባሉን አጉልቶ በመስበክ የምእመናንን አንድነት የሚበታትን ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊው ትምህርት ይህ ፍጹም ስሕተት ነው፡፡ ሐዋርያዊት ከሆነችው ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያፈነገጠ በመሆኑም ተቀባይነት የለውም፡፡ እንዲያውም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከሚታየው የቤተ ክርስቲያን አካል የማይታየው ይበልጣል፡፡

የቤተ ክርስቲያን የአንድነቷ መሠረት ከላይ እንደገለጽነው ክርስቶስ እንጂ በአንድ ፖፕ ሥር መተዳደር ወይም በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ውስጥ አባል መሆን ስላልሆነ ቤተ ክርስቲያን ተቋም ወይም ድርጅት አይደለችም፡፡ ለአገልግሎት መፋጠን የፈጠረቻቸውን ተቋማት በማሰብ ድርጅት ወይም ተቋም የምትመስለን ካለን ተሳስተናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ራሷ ክርስቶስ የሆነላት በሰማይ ያሉ የድል ነሺዎች፣ በምድር ያሉ የክርስቲያኖች ኅብረት ወይም አንድነት ናት፡፡ ይህች አንድነት የሚታይና የማይታይ አካል አላት፡፡ የሚታይ አካል የተባለውም መዋቅሩ ሳይሆን እኛ ራሳችን ክርስቲያኖች እያንዳንዳችንና አንድነታችን ነው፡፡ የማይታየው አካሏ ደግሞ በሰማይ የሚኖሩ ቅዱሳንና እኛ የማናያቸው እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቃቸው የቤተ ክርስቲያን አካል የሆኑ ስውራን ናቸው፡፡ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ከምንም በፊት ይህን ኦርቶዶክሳዊ የነገረ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ማወቅና መረዳት አለበት፡፡

. ቅድስት

መሥራቿ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያንም ቅድስት ናት፡፡ የቤተ ክርስቲያን የቅድስና ምንጭ እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱስ ማለት የተለየ ማለት እንደሆነ፥ ቤተ ክርስቲያንም ከዓለም ተለይታ የእግዚአብሔርን ማዳን የምትመሰክር ናትና ቅድስት ናት፡፡ በሌላ አገላለጽ ደግሞ “እስመ ኢይትረከብ ነኪር በማዕከሌሃ – ባዕድ በመካከሏ አይገኝምና” እንዲል በሃይማኖት በምግባር የጸኑ ቅዱሳን መሰብሰቢያ ናትና ቅድስት ናት፡፡

እግዚአብሔር እጅግ ቸር ከመሆኑ የተነሣ፥ ሩጫችንን ያልጨረስን ክርስቲያኖች ኃጢአት ብንሠራ እንኳ በንስሓ እየተመላለስን ከምሥጢራቱ እንድንካፈል በማድረግ የድኅነት መንገዱን እንዳንለቅ ቀስ በቀስም ከአርአያ እግዚአብሔር ወደ አምሳለ እግዚአብሔር እንድናድግ አድርጎናል፡፡ ከበደላችን ተመልሰን ከምሥጢራቱ ስንካፈልም ከእግዚአብሔር ጋር እንዋሐዳለን፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ “የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ የንጉሡ ካህናት ቅዱስ ሕዝብ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ” ያለን (፩ኛ ጴጥ. ፪፡፱)፡፡ ዳግመኛም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ” (ሮሜ. ፩፡፯፣ ፩ኛ ቆሮ. ፩፡፪)ያለንም ስለዚሁ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ቅድስና የሚያርቀን ክሕደትና ኃጢአት ብቻ ነው ማለት ነው፡፡

አንድ ሰው ቅዱስ ሆኖ ለመኖር በዚህ አንድነት ውስጥ መኖር ይገባዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ማለትም ከክርስቶስ ውጪ ቅድስና የለምና ከዚህ አንድነት ከተለየ ምንም ያህል በጎ ምግባር ቢኖረውም ቅዱስ አይባልም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቅድስና ከመሥራቿ ከክርስቶስ ስለሆነ በሰዎች ኃጢአት ቅድስናዋን አታጣም፡፡ አንድ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ቢመላለስም በኃጢአት ውስጥ የሚኖር ከሆነ የቤተ ክርስቲያን አካል ነው ማለት አይቻለም፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ስለሆነች እርሱም የቅድስና ሥራ መሥራት ይገባዋልና፡፡ ለዚህ ነው በቅዳሴ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለተሰበሰቡት ሰዎች ዲያቆኑ “በንስሓ ውስጥ ያላችሁ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ” ሲል ካህኑ በሚያደርጉት ጸሎት ውስጥ “የቀደመ ሥራቸውን ይቅር ብለህ በሰላም ነፍሳቸውን አድን፤ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ አንድ አድርጋቸው፡፡ ተቀዳሚ ተከታይ በሌለው በአንድ ልጅህ በጌታችን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ በይቅርታውና በምሕረቱ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጨምራቸው” በማለት የሚጸልዩት፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ክርስቲያን ቅድስት ከሆነችው አንድነት እንዳይለይ ራሱን ሁልጊዜ በምሥጢራት መቀደስ አለበት ማለት ነው፡፡

. ሐዋርያዊት

ሐዋርያዊት የሚለው ቃል በውስጡ ሦስት መሠረታዊ መልእክታትን የያዘ ነው፡፡ አንደኛው ትርጕም ቤተ ክርስቲያን ሲባል የሐዋርያትን እምነት የሚያስረዳና በዚህም ከመናፍቃንና ከአረማውያን እምነት የተለየች መሆኗን የሚገልጽ ነው፡፡ ሁለተኛው ሐዋርያዊ ውርርስ (ቅብብሎሽ) እንዳላት የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህም ማለት አሁን ያለው እውነት ወደኋላ በሔድን ቊጥር ሳይዛነፍ፣ ሳይሸራረፍ፣ በመሀልም የሚቋረጥ መስመር ሳይኖረው ከሐዋርያት ዘንድ እንደሚያደርሰን ያሳያል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህን እምነት በጃንደረባው (ሐዋ. ፰፡፳፮-፵)፥ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ደግሞ በአኀት አብያተ ክርስቲያናት በኵል ተቀብላዋለች፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ ተልእኮዋን መናገር ነው፡፡ ይህም ማለት ቤተ ክርስቲያን “ሒዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ. ፳፰፡፲፱) የሚለውን ትርጕም የያዘ ነው፡፡

በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ሰውን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመማረክ ዋና ተልእኮዋ ነው፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ዋናው ዓላማ ሰዎችን ወደ ቀደመ ክብራቸው ለመመለስና ወደ ራሱ መንግሥት ለማምጣት ነው፡፡ ይህን ግብር ስለፈጸመም የሃይማኖታችን ሐዋርያ ተብሏል (ዕብ. ፫፡፩)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ተልኮ ወደዚህ ዓለም እንደመጣ ሁሉ፥ እርሱም ሐዋርያትን ወደ ዓለም ልኳቸዋል፡፡ “አብ እንደላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ” (ዮሐ. ፳፡፳፩-፳፪)፡፡ ሐዋርያት ወደ ዓለም ሁሉ በመሔድም የቤተ ክርስቲያንን መሠረት አስቀምጠዋል፡፡ ዳግመኛም በዚህ ምድራዊ አጥቢያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሰማያት ላለው የእግዚአብሔር መንግሥት በቃልና በገቢር ምስክር ትሆን ዘንድ ስለተላከች ሐዋርያዊት ትባላለች፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! ይህ ትምህርት፣ ከታኅሣሥ ፩ – ፲፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በታተመው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ በንቁ ዓምድ ሥር ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

አንቀጸ መድኃኒት ቤተ ክርስቲያን  – የመጀመሪያ ክፍል

የካቲት ፳፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ነገረ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቤተ ክርስቲያን ያለው ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ምን እንደ ሆነ የምንማርበት የትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ ምንም እንኳን ትምህርቱ እጅግ ጥልቅና ራሱን የቻለ መጽሐፍ የሚወጣውና ሰፊ አሳቦችን የያዘ ቢሆንም በዚህ ጽሑፍ ግን በተለያዩ አካላት ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚነሡ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያህል ብቻ በጥቂቱ ለማንሣት እንሞክራለን፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማም ቤተ ክርስቲያን ድርጅት (ተቋም) ዲኖሚኔሽን ናት፤ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ድኅነት ይገኛል፤ ለቤተ ክርስቲያን ስግደት አይገባም፤ ቤተ ክርስቲያን መሔድ አያስፈልግም፤ ቤተ ክርስቲያን ትሳሳታለች፣ ስለዚህ ትታደሳለች፤ ወዘተ” የሚሉ የተሳሳቱ አሳቦችን ለሚያነሡ አካላት መልስ መስጠት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ሦስት ዓይነት ሰዋስዋዊና ዘይቤአዊ ትርጕም አለው (አባ ጎርጎርዮስ ፲፱፻፸፰፣ ገጽ ፲፪-፲፯)፡፡

  • የመጀመሪያው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ያመለክታል፡፡ ይኸውም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- ወደ ማኅበር ስትሰበሰቡ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ እሰማለሁ (፩ኛ ቆሮ. ፲፩፡፲፰) እንዳለው የክርስቲያኖች ቤት፣ የክርስቲያኖች መኖሪያ ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ባወቀ የክርስቶስ ደም በነጠበበት የምትተከል፣ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሜሮን የከበረች፣ ሥላሴ በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገኑባት፣ የክርስቶስ ሥጋዌ የሚነገርባት፣ ሥጋውና ደሙ የሚፈተትባት ቅድስት መካን ቤተ ክርስቲያን ተብላ እንደተጠራች ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ይገልጻሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያን እንሒድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ (መዝ. ፻፳፩፡፩)፤ በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ” (ሐዋ. ፲፩፡፳፮) የሚሉት ንባቦች የቤተ ክርስቲያን አንደኛው ዘይቤአዊ ትርጕም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ዳግመኛም የእግዚአብሔር ቤት (ዘፍ. ፳፰፡፲፯)፣ በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ (መዝ. ፭፡፯)፣ የአባቴ ቤት (ሉቃ. ፪፡፵፱)፣ የእግዚአብሔር ቤት (ዕብ. ፲፡፳፩) የሚሉት ይህን የሚያስረዱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በተለይም ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ለወለደው ልጁ ለጢሞቴዎስ፡- ብዘገይ ግን፣ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፣ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው (፩ኛ ጢሞ. ፫፡፲፭) በማለት የገለጠው የእግዚአብሔር ቤት (ሕንፃ) ቤተ ክርስቲያን እንደሚባል ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡

  • ሁለተኛው ደግሞ እያንዳንዱ ምእመን (ክርስቲያን) ቤተ ክርስቲያን የሚባል መሆኑን የሚያስገነዝብ ትርጕም አለው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ (፩ኛ ቆሮ. ፫፡፲፮)፣ “… ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ (፩ኛ ቆሮ. ፮፡፲፱) በማለት የገለጸው ይህን ነው፡፡ ይኸውም በመንፈሳዊና በምሥጢራዊ ልደት ከክርስቶስ የተወለዱ፥ እርሱ አድሮባቸው የሚኖሩ፥ በቅዱስ ሜሮን የታተሙ (፩ኛ ዮሐ. ፪፡፳) እና ሥጋውንና ደሙን የተቀበሉ ምእመናንን ለማመልከት ነው፡፡
  • ሦስተኛው ትርጕም ደግሞ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል (፩ኛ ጴጥ. ፭፡፲፫) እንዲል የክርስቲያኖችን ኅብረት ወይም አንድነት (ማኅበረ ምእመናንን) የሚያመለክት ነው፡፡ በሰማይ ያሉ የድል ነሺዎች፣ በምድር ያሉ ከፍትወታት፣ ከኃጣውእና ከርኵሳን መናፍስት ጋር የሚጋደሉ የክርስቲያኖች አንድነትና ኅብረት ማለት ነው፡፡ ይህች ኅብረትና አንድነት ራሷ ክርስቶስ የሆነላት፣ የክርስቶስ አካል ናት፡፡ ኅብረታችንም በደስታ ከተሰበሰቡት አእላፋት መላእክት፣ በሰማያትም ከተጻፉ ከበኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ከሚሆን ከእግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ከሆኑት ከጻድቃን መንፈሶች (ዕብ. ፲፪፡፳፪-፳፬) ጋር እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ነግሮናል፡፡ እኛም በዚህ ክፍል ትኵረት የምናደርገው በዚሁ በሦስተኛው ትርጓሜ ላይ ነው፡፡

እኛ ኦርቶዶክሳውያን በግእዝ ቋንቋ ቤተ ክርስቲያን” የምንለውን ጽርዓውያን (ግሪካውያን) ኤክሌሲያ ይሉታል፡፡ ትርጓሜውም ለአንድነትና ለአንድ ልዩ ዓላማ የተጠሩ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው (፩ኛ ቆሮ. ፩፡፱) ብሎ ከገለጸው ጋር የተስማማ ነው፤ የቤተ ክርስቲያን ዓላማ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር አንድነትና ሰማያዊ ዓላማ በሃይማኖት መጥራት ነውና፡፡ ግሪኮች ኤክሌሲያ” የሚለውን ቃል መጀመሪያ አንድን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ወይም አስተዳደራዊ ችግር ለመፍታት ለተሰበሰቡ ሽማግሌዎች መጠሪያ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ በ፪፻፹፬ ከክርስቶስ ልደት በፊት ብሉይ ኪዳንን ከዕብራይስጥ ወደ ጽርዕ የተረጐሙት ሰብዓ ሊቃናት ግን ቀሃል የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል ኤክሌሲያ” ብለው ተርጕመውታል፡፡ ትርጕሙም የእስራኤልን ጉባኤ የሚገልጽ ነው፡፡ እንደ ምሳሌም የሚከተሉትን ኃይለ ቃላት እንመልከት፤

ማኅበሩንም ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስባቸው (ዘሌ. ፰፡፫)፡፡ እዚህ ላይ ማኅበሩ ተብሎ የተገለጠው በምሥጢር ስለዚህች ጉባኤ ነው፡፡ በዚህች ጉባኤም አሮን ሊቀ ካህን ሆኖ ተሾሟል (ዕብ. ፭፡፬)፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም እንዳስተማረው፥ ይህ የአይሁድ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያን አምሳል፣ መርገፍ ወይም ጥላ ነበር (The Catechetical Lectures of St. Cyril, Archbishop of Jerusalem, P. 335)፡፡ እንደ ሊቁ አስተምህሮ አብዛኞቹ አይሁዳውያን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ባለማመናቸው ምክንያት ከዚሁ ጉባኤ ቢወጡም ጉባኤው ግን አልተበታተነም፤ ሊበታተንም አይችልም፡፡ ይልቁንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- በዚህም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን (ጉባኤዬን) እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም (ማቴ. ፲፮፡፲፰) በማለት በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ጉባኤ አጸናት እንጂ፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም በሰዎች አመለካከት የተለያየ ዓይነት ስያሜ (እንደ አይሁዳውያኑና አሁን እንደምንሰማው ብዙ ስም) ቢሰጠውም ይህ የሰዎች የተሳሳተ ግንዛቤ የባሕርይ አምላክነቱን ሊለውጠው አይችልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የገሃነም ደጆች አይችሏትም የሚለው ኃይለ ቃልም ይህን ጥልቅ ነገረ ሃይማኖታዊ ጽንሰ ሐሳብ በውስጡ የያዘ ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ይህቺ ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያን) በቅድስት ሥላሴ ባለው እምነቷ ህልውናዋን የጀመረችው በዓለመ መላእክት ማለትም ሰው ከመፈጠሩ በፊት ነው፡፡ ከዚያም ከአቤል ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ድረስ በነበረው የደጋግ ሰዎች አንድነት ቀጠለች፡፡

በቅዳሴያችን እግዚአብሔር ይስማዕከ ኵሎ ዘሰአልከ ወይትወከፍ መሥዋዕተከ ወቊርባነከ ከመ መሥዋዕተ መልከ ጼዴቅ ወአሮን ወዘካርያስ ካህናተ ቤተ ክርስቲያኑ ለበኵር፤ እግዚአብሔር የለመንኸውን ሁሉ ይስማህ፤ የቀደመችዋ ቤተ ክርስቲያን ካህናት የሚሆኑ የመልከ ጼዴቅንና የአሮንን የዘካርያስንም መሥዋዕት እንደተቀበለ መሥዋዕትህን ቊርባንህንም ይቀበልልህ የሚለው ንባብ የቤተ ክርስቲያን ህልውና ግእዛን ያላቸው ፍጥረታት ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በመጨረሻ ከላይ እንደገለጥነው በክርስቶስ ደም ጸናች፡፡ አሁንም ይህ ጉባኤ ከሥላሴ ጋር ያለው ግንኙነት ዘወትር አይቋረጥም፡፡

ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ናት ሲባል ግን አንዳንዶች እንደሚሉት እንዲሁ የሰዎች ስብስብ ሳትሆን የምርጦች ስብስብ ናት፤ የተጠሩ ብዙ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና (ማቴ. ፳፡፲፮)፡፡ እነዚህ ጥቂትና የተመረጡትም የልጅነት ሥልጣን የተሰጣቸው (ዮሐ. ፩፡፲፫)፣ እግዚአብሔርን በአንድነቱና በሦስትነቱ የሚያመልኩ፣ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ (ማቴ.፲፮፡፲፮) በሚል ጽኑዕ መሠረት የታነፁ ናቸው እንጂ እንዲሁ በአንድ ቤት ውስጥ የተሰበሰቡ ሰዎች አይደሉም፡፡ ቤተ ክርስቲያን አካለ ክርስቶስና ሕያዊት ናት (ኤፌ. ፩፡፳፪-፳፫)፡፡ የክርስቶስ ሙሽራ (መኃ. ፭፡፩፣ ዮሐ. ፫፡፳፱፣ ራእ. ፳፩፡፱)፣  የእግዚአብሔር ሕያው ቤተ መቅደስ (ኤፌ. ፪፡፳፩)፣ የእውነት ዓምድና መሠረት (፩ኛ ጢሞ. ፫፡፲፭) ትባላለች፡፡

እነዚህ ስያሜዎች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መለወጥ የማይስማማው የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካል መሆኗን በግልጽ ያስረዳሉ፡፡ የክርስቶስ አካል ስለሆነች አትሳሳትም፣ አትለወጥም፡፡ ትምህርቷም ከአምላኳ ከእግዚአብሔር የተቀበለችውና በመንፈስ ቅዱስ የሚጠበቅ ስለሆነ ስሕተትና ነቅ አይገኝበትም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ትክክል ለመሆኗ ማስረጃችን መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ለመሆኑ ደግሞ ምስክሯ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ (ኤፌ. ፫፡፲) የሚለው የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ለዚህ ሁነኛ ማስረጃ ነው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ራሷ የሆነላት ቤተ ክርስቲያን አርጅታለች ትታደስ፣ ተሳስታለች ትመለስ አትባልም፡፡ እንዲህ ማለት ክርስቶስን ማረም፣ ክርስቶስን ማስተካከል ይሆናልና፡፡ አምላካችን ደግሞ መለወጥ የማይስማማው ፍጹም አምላክ መሆኑን በነቢዩ በሚልክያስ አድሮ እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም (ሚል. ፫፡፮) በማለት የነገረን ሲሆን፤ ቅዱስ ጳውሎስም ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘለዓለምም ያው ነው። ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ(ዕብ. ፲፫፡፰-፱) ብሎ በየጊዜው የሚሻሻል አዲስ ትምህርት እንደሌላት አስረግጦ ነግሮናል፡፡

ቅዱስ ያሬድ በድጓው አንቀጸ መድኃኒት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እምነ ይእቲ ንበላ በሐ ወይእቲ ትኩነነ መርሐቅድስት ቤተ ክርስቲያን የድኅነት በር ናት፤ እናታችን ናት፤ ለድኅነታችን መንገድ መሪ እንድትሆነን ሰላም እንበላት በማለት የድኅነት በር እንደሆነችና ለእርሷ ሰላምታ ማቅረብ እንደሚገባን ይነግረናል (ጾመ ድጓ ዘቅድስት)፡፡ በጾመ ድጓ ዘዘወረደም ላይ እንዲሁ አመ ኖኅ ይእቲ መድኃኒት እንተ ኮነት አንቀጸ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ቅድስትክብርት የምትሆን ቤተ ክርስቲያን ከኖኅ ዘመን ጀምሮ የሕይወት መንገድ (በር) ናት በማለት ብቸኛዋ የድኅነት በር እንደሆነች ያስረዳናል፡፡

በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፲ ላይ የተጠቀሰው በወንበዴዎች የተደበደበው ሰው የተወሰደባት የእንግዶች ማረፊያ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በደጉ ሳምራዊ የተመሰለው ክርስቶስ አዳምን ለማዳን የፈጸመውን ማዳን በምሥጢራት በማደል ሰዎችን ከቁስለ ኃጢአት እንድትፈውስ ሥልጣን የተሰጣት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ መድኃኒትነቷም የክርስቶስን ሥጋና ደም በመፈተትና በማቀበል ነው፡፡ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ከቤተ ክርስቲያን ውጪ አይፈጸሙም፡፡ ሰው ደግሞ ሳይጠመቅና ሥጋ ወደሙን ሳይቀበል የክርስቶስ አካል፣ የመንግሥተ ሰማያት አባል መሆን አይችልምና ቤተ ክርስቲያን መሔድ የግድ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው፡፡

ወደ ቤተ ክርስቲያን የምንሔደው እግዚአብሔር ሌላ ቦታ ሆነን ብንጸልይ ስለማይሰማን ሳይሆን ያለ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ድኅነት ተሳታፊ ስለማንሆንና እነዚህን ምሥጢራት ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ማግኘት ስለማንችል ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የምታምነውን ሳያምኑ፣ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ሳይሆኑ ድኅነት የለም፡፡ በአጠቃላይ ከክርስቶስ ውጪ የሆነች ቤተ ክርስቲያንን፣ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ የሚገኝ ድኅነት የለም፡፡

የቤተ ክርስቲያን ባሕርያት

ቤተ ክርስቲያን አራት ባሕርያት አሏት፡፡ እነዚህ ባሕርያቷ እንዲሁ የተጠራችባቸው ሳይሆኑ እጅግ ጥልቅ የሆነ የነገረ ሃይማኖትን ትምህርት የሚያስረዱ ናቸው፡፡ እነዚህም በጸሎተ ሃይማኖታችን ሁልጊዜ የምንመሰክራቸው ናቸው “… ከሁሉ በላይ (ኵላዊት) በምትሆን (፩) ሐዋርያት በሰበሰቧት (፪) በአንዲት (፫) ቅድስት (፬) ቤተ ክርስቲያን እናምናለን፡፡”

. ኵላዊት

ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት ናት ሲባል በብዙዎቻችን ልቡና የሚመጣው በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ስፍራ፣ ለሁሉም ሰው ያለች የሚል ትርጓሜው ነው፡፡ ርግጥ ነው ቤተ ክርስቲያን በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ስፍራ፣ ለሁሉም ሰው አለች፡፡ ነገር ግን በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት ናት ሲባል ከዚህ ያለፈ (የላቀ) ትርጓሜ አለው፡፡ ኵላዊት የሚለው ቃል ከብዛት ይልቅ ርቀትንና ምልዐትን፣ ርቱዕነትን፣ እውነተኛነትን፥ ፍጹምነትን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት ናት ስንል ፍጽምት ናት፤ ሁሉንም የምትይዝ ናት፤ ምንም የሚጐድላት ነገር የለም ማለታችን ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን እንደ አሁኑ በዓለም ሁሉ ከመስፋፋቷ በፊት እንኳን ኵላዊት ትባል ነበር፡፡ የኢየሩሳሌም የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የቆሮንቶስ፣ የሮም አብያተ ክርስቲያናት ኵላዊት ይባሉ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት መባሏ ከቦታ ወይም ከቊጥር አንጻር ሳይሆን የክርስቶስ አካል በመሆኗ ያገኘችው ነው፡፡ ዳግመኛም ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት የምትባለው ከእግዚአብሔር የተገኘች የሐዋርያት ትምህርታቸው፣ የክህነት ውርሳቸው (ቅብብሎሽ) ስላላት ነው፡፡ ኵላዊት ናት ስንል ምልዕትና ፍጽምት ናት ማለት ነው፡፡ የማትታደሰውም፣ የማትለወጠውም ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ክርስቶስ ራስ የሆነላት ሕያዊትና ፍጽምት አካሉ ናትና፤ እግዚአብሔር እንደማያረጅ እርስዋም አታረጅምና የሚገቡባትን ታድሳለች እንጂ አትታደስም፡፡

ይቆየን

ይህ ጽሑፍ፣ ከታኅሣሥ ፩ – ፲፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በታተመው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ በንቁ ዓምድ ሥር ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡