ትንሣኤ ክርስቶስ በሊቃውንት አንደበት – የመጀመሪያ ክፍል

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በየጊዜያቱና በየዘመናቱ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ከዚህ ቀጥሎ የተገለጠውን ትምህርትና ምስክርነት ሰጥተዋል፤

“ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶ ሲኦልን ረግጦ፣ በሞቱ ሞትን አጠፋው፤ በሦስተኛው ቀንም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ‹አባት ሆይ አመሰግንሃለሁ፥› ብሎ ሥግው ቃል አመሰገነ፤” (እልመስጦአግያ ዘሐዋርያት ፭፥፩)፡፡

“እንደ ሞተ እንዲሁ ተነሣ፤ ሙታንንም አስነሣ፡፡ እንደ ተነሣም እንዲሁ ሕያው ነው፤ አዳኝ ነው፡፡ በዚህ ዓለም እንደ ዘበቱበት፣ እንደ ሰደቡት እንዲሁ በሰማይ ያሉ ዂሉ ያከብሩታል፤ ያመሰግኑታል፡፡ ለሥጋ በሚስማማ ሕማም ተሰቀለ፤ በእግዚአብሔርነቱ ኃይል ተነሣ፡፡ ይኸውም መለኮቱ ነው፡፡ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ማረከ፤” (ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ ሃይ. አበ. ፯፥፳፰-፴፩)፡፡

“እንዲህ ሰው ኾኖም ሰውን ፈጽሞ ያድን ዘንድ ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤” (ዘሠለስቱ ምዕት ፲፱፥፳፬)፡፡

“ሞትን ያጠፋው፤ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ የሞት ሥልጣን የነበረው ዲያብሎስን የሻረው እርሱ ነው፡፡ ሰው የኾነ፤ በሰው ባሕርይ የተገለጠ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያደረበት ዕሩቅ ብእሲ አይደለም፡፡ ሰው የኾነ አምላክ ነው እንጂ፡፡ ፈጽሞ ለዘለዓለሙ በእውነት ምስጋና ይገባዋል፤” (ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ሃይ. አበ. ፳፭፥፵)፡፡

“ሥጋው በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፡፡ በዚያም ሰዓት የጌታችን ሥጋው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ መቃብራት ተከፈቱ፤ ገሃነምን የሚጠብቁ አጋንንትም ባዩት ጊዜ ሸሹ፡፡ የመዳብ ደጆች ተሰበሩ (ሊቃነ አጋንንት፣ ሠራዊተ አጋንንት ድል ተነሡ)፡፡ የብረት ቍልፎቿም ተቀጠቀጡ (ፍዳ መርገም ጠፋ)፡፡ ቅድስት ነፍሱ በሲኦል ተግዘው የነበሩ የጻድቃን ነፍሳትን ፈታች፤” (ዝኒ ከማሁ፣ ፳፮፥፳-፳፩)፡፡

“ሥጋ ከመለኮቱ ሳይለይ በመቃብር አደረ፡፡ ነፍሱም ከመለኮት ሳትለይ በገሃነም ተግዘው ለነበሩ ነፍሳት ደኅነትን ታበስር ዘንድ፤ ነጻም ታደርጋቸው ዘንድወደ ሲኦል ወረደች፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ተናገረው ቃል ዐፅም ሥጋ ወደ መኾን ፈጽሞ እንደ ተለወጠ የሚናገሩ የመናፍቃንን የአእምሮአቸውን ጕድለት ፈጽመን በዚህ ዐወቅን፡፡ ይህስ እውነት ከኾነ ሥጋ በመቃብር ባልተቀበረም ነበር፡፡ በሲኦል ላሉ ነፍሳት ነጻነትን ያበሥር ዘንድ ወደ ሲኦል በወረደ ነበር እንጂ፡፡ ነገር ግን ከነፍስና ከሥጋ ጋር የተዋሐደ ቃል ነው፡፡ እርሱ የሥጋ ሕይወት በምትኾን በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ለነፍሳት ነጻነትን ሰበከ፡፡ ሥጋው ግን በበፍታ እየገነዙት በጎልጎታ በዮሴፍ በኒቆዲሞስ ዘንድ ነበረ፤ ቅዱስ ወንጌል እንደ ተናገረ፡፡ አባቶቻችን ‹ሥጋ በባሕርዩ ቃል አይደለም፤ ቃል የነሣው ሥጋ ነው እንጂ› ብለው አስተማሩን፡፡ ይህን ሥጋም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ቶማስ ዳሠሠው፤ በሥጋው ሲቸነከር ቃል ታግሦ የተቀበለውን የችንካሩን እትራትም በእርሱ አየ፤” (ዝኒ ከማሁ፣ ፴፥፴፩-፴)፡፡

“አሁን እግዚአብሔር ‹ሞተ› ሲል ብትሰማ አትፍራ፤ ‹የማይሞተውን ሞተ ሊሉ አይገባም› ከሚሉ ዕውቀት ከሌላቸው፤ ሕማሙን፣ ሞቱን ከሚክዱ መናፍቃን የተነሣ አትደንግጥ፡፡ እኛ ግን በመለኮቱ ሞት እንደሌለበት፤ በሥጋ ቢሞትም በመለኮቱ ሥልጣን እንደ ተነሣ እናውቃለን፡፡ ሞት የሌለበት ባይኾንስ ኖሮ በሥጋ በሞተ ጊዜ ሥጋውን ባላስነሣም ነበር፤ ሥጋው እስከ ዓለም ፍጻሜ በመቃብር በኖረ ነበር እንጂ፤” (ቅዱስ ባስልዮስ፣ ሃይ. አበ. ፴፬፥፲፯-፲፰)፡፡

“ከመስቀሉ ወደ ሲኦል በመውረዱ አዳነን፤ በአባታቸው በአዳም በደል በሲኦል ተግዘው የነበሩ ጻድቃንን ፈታ፡፡ ከሙታን ተለይቶ አስቀድሞ በተነሣው በእውነተኛ ትንሣኤውም አስነሣን፤ የንስሐንም በር ከፈተልን፤” (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣፴፮፥፴)፡፡

“በአባታችን በአዳም በደል የተዘጋ የገነት ደጅን የከፈተልን፤ ዕፀ ሕይወትን የሚጠብቅ ኪሩብንም ያስወገደው፤ የእሳት ጦርን ከእጁ ያራቀ፤ ወደ ዕፀ ሕይወት ያደረሰን እርሱ ነው፡፡ ፍሬውንም (ሥጋውን፣ ደሙን) ተቀበልን፡፡ አባታችን አዳም ሊደርስበት ወዳልተቻለው፤ በራሱ ስሕተት ተከልክሎበት ወደ ነበረው መዓርግ ደረስን፡፡ ክፉዉንና በጎዉን ከሚያስታውቅ፤ ወደ ጥፋት ከሚወስድ፤ በአዳምና በልጆቹም ላይ ኃጢአት ከመጣበት ከዕፀ በለስ ፊታችንን መለስን፤” (ዝኒ ከማሁ ፴፮፥፴፰-፴፱)፡፡

“የሕይወታችን መገኛ የሚኾን የክርስቶስ ሞት የእኛን ሞት ወደ ትንሣኤ እንደ ለወጠ እናምናለን፡፡ ክርስቶስም ሞትን አጥፍቶ የማታልፍ ትንሣኤን ገለጠ፤ እንደ ተጻፈ፣ ከሰው ወገን ማንም ማን ሞትን ያጠፋ ዘንድ፣ ትንሣኤንም ይገልጣት ዘንድ አይችልም፡፡ ዳዊት ‹በሕያውነት የሚኖር፤ ሞትንም የማያያት ሰው ማነው? ነፍሱን ከሲኦል፤ ሥጋውን ከመቃብር የሚያድን ማን ነው?› ብሎ እንደ ተናገረ፤” (ቅዱስ አቡሊዲስ፣ ሃይ. አበ. ፵፪፥፮-፯)፡፡

“በመለኮትህ ሕማም፣ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፤ በሥጋ መከራ የተቀበልህ አንተ ነህ፤ ከአብ ጋር አንድ እንደ መኾንህ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፤ ከእኛም ጋር አንድ እንደ መኾንህ በፈቃድህ የሞትህ አንተ ነህ፡፡ በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፤ በኪሩቤል ላይ ያለህ አንተ ነህ፤ ከሙታን ጋር በመቃብር የነበርህ አንተ ነህ፡፡ በአንተ ሕማምና ሞትም ድኅነት ተሰጠ፡፡ ከሙታን ጋር የተቈጠርህ አንተ ነህ፤ ለሙታንም ትንሣኤን የምትሰጥ አንተ ነህ፤ ሦስት መዓልት፣ ሦስት ሌሊት በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፤ በዘመኑ ዂሉ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምትኖር አንተ ነህ፤ በመለኮት ሕማም ሳይኖርብህ በሥጋ የታመምክ አካላዊ እግዚአብሔር ቃል አንተ ነህ፤” (ቅዱስ ኤራቅሊስ፣ ፵፰፥፲፪-፲፫)፡፡

“እኛስ ኃጢአታችንን ለማስተስረይ በሥጋ እንደ ታመመ፤ እንደ ሞተ፤ ከነፍሱም በተለየ ጊዜ ሥጋውን እንደ ገነዙ፤ ከሙታንም ተለይቶ በእውነት እንደ ተነሣ፤ ከተነሣም በኋላ በእውነት ወደ ሰማይም እንደ ዐረገ እናምናለን፡፡ ኋላም እርሱ በሚመጣው ዓለም በሕያዋን፣ በሙታን ይፈርድ ዘንድ ይመጣል፡፡ የሰውን ወገኖች ዂሉ በሞቱበት፤ በተቀበሩበት ሥጋ ከሞት ያስነሣቸዋል፡፡ ከትንሣኤውም በኋላ ያለ መለወጥ ዂል ጊዜ ይኖራል፡፡ እርሱ በዚህ በሞተበት፤ በተገነዘበት ሥጋ ከሙታን አስቀድሞ እንደ ተነሣ፤” (ቅዱስ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም፣ ሃይ. አበ. ፶፪፥፲፩-፲፪)፡፡

“የሥጋን ሕማም ለመለኮት ገንዘብ በአደረገ ጊዜ የእግዚአብሔር አካል በባሕርዩ በግድ ሕማምን አልተቀበለም፤ ሕማም በሚስማማው ባሕርዩ ኃይል እንጂ፡፡ ሞትም በሥጋ ለእግዚአብሔር ቃል ገንዘብ በኾነ ጊዜ ሞትን አጠፋ፤ ከሞትም በኋላ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አጠፋ፤” (ቅዱስ ቴዎዶጦስ፣ ሃይ. አበ. ፶፫፥፳፯)፡፡

“መለኮት በሥጋ አካል በመቃብር ሳለ መለኮት የሥጋ ሕይወት በምትኾን በነፍስ አካል ወደ ሲኦል ወረደ፡፡ እንደዚህ ባለ ተዋሕዶ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ከትንሣኤ በኋላ አይያዝም፤ አይዳሰስም፤ በዝግ ቤት ገብቷልና፡፡ ነገር ግን ምትሐት እንዳይሉት ቶማስ ዳሠሠው፤ የተባለውን ከፈጸመ በኋላ ቶማስ አመነበት፤” (ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ሃይ. አበ. ፶፮፥፴፯-፴፰)፡፡

“ክርስቶስ የሙታን በኵር እንደ ምን ተባለ? እነሆ በናይን ያለች የደሀይቱን ልጅ አስቀድሞ አስነሣው፤ ዳግመኛም አልዓዛርን በሞተ በአራተኛው ቀን አስነሣው፡፡ ኤልያስም አንድ ምውት አስነሣ፤ ደቀ መዝሙሩ ኤልሣዕም ሁለት ሙታንን አስነሣ፤ አንዱን ሳይቀበር፤ ሁለተኛውን ከተቀበረ በኋላ ሥጋውን አስነሣ፡፡ እነዚያ ሙታን ቢነሡ ኋላ እንደ ሞቱ፤ እነርሱ ኋላ አንድ ኾነው የሚነሡበትን ትንሣኤ ዛሬ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሙታን ትንሣኤያቸው በኵር ነው፡፡ እንግዲህ ወዲህም ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ የተነሣ እርሱ ነው፡፡ ‹ዳግመኛም ሞት አያገኘውም› ተብሎ እንደ ተጻፈ፤” (ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ፶፯፥፫-፮)፡፡

“ቃል ሥጋውን በመቃብር አልተወም፤ በሲኦልም ካለች ከነፍሱ አልተለየም፡፡ ከነፍስ ከሥጋ በአንድነት ነበረ እንጂ፤ ለዘለዓለም ክብር ምስጋና ይግባው፤” (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ፣ ሃይ. አበ. ፷፥፳፱)፡፡

“ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ በትንሣኤ ‹ከእናንተ ጋር እስከምመጣበት ቀን ድረስ ከዚያ ወይን ጭማቂ አልጠጣም፤ በሐዲስ ግብር በምነሣበት ጊዜ የምታዩኝ እናንት ምስክሮቼ ናችሁ› ያለውን የማቴዎስን ወንጌል በተረጐመበት አንቀጽ እንዲህ አለ፤ ሐዲስ ያለው ይህ ነገር ምንድነው? ይህ ነገር ድንቅ ነው! መዋቲ ሥጋ እንዳለኝ ታያላችሁ፤ ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ የማይሞት ነው፤ አይለወጥም፡፡ ሥጋዊ መብልንም መሻት የለበትም፤ ከትንሣኤ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቢበላም ቢጠጣም መብልን ሽቶ አይደለም፤ እርሱ ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ ያምኑ ዘንድ በላ ጠጣ እንጂ፡፡ ይህ ድንቅ ሥራ ነው! ያለ መለወጥ ሰው የኾነ ቃል የተቸነከረበትን ምልክት (እትራት) አላጠፋምና፡፡ 

በሚሞቱ ሰዎች እጅ እንዲዳሠሥ አድርጎታልና፤ አምላክ የሆነ ሥጋ የሚታይበት ጊዜ ነውና አላስፈራም፤ እርሱ በዝግ ደጅ ገባ፤ ግዙፉ ረቂቅ እንደሆነ ሥራውን አስረዳ፤ ነገር ግን በትንሣኤው ያምኑ ዘንድ የተሰቀለው እርሱ እንደሆነ የተነሣውም ሌላ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ ይህን ሠራ፡፡ ስለዚህም ተነሣ፤ በሥጋውም የችንካሩን ምልክት /እትራት/ አላጠፋም፤ ዳግመኛም ከትንሣኤው አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱ ጧት ማታ ከእርሱ ጋር ይበሉ እንደነበረ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በላ፤ ስለዚህም በዐራቱ መዓዝነ ዓለም ትንሣኤውን አስረዱ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ያየነው ከእርሱም ጋር የበላን የጠጣንም እርሱ ነው ብለው አስረዱ፤” (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ሃይ. አበ. ፷፮፥፯-፲፪)፡፡

“በእርሱ ሞት ከብረናል፤ በመለኮቱ ሞት ሳይኖርበት በሥጋ ሞተ፤ ምንጊዜም ቢሆን እርሱ የሕይወት ልጅ ሕይወት ነው፤ ይኸውም ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ወደ ሕይወት ሥጋ ደፍሮ በመጣ ጊዜ ሞት እንዲህ ድል ተነሣ፤ መፍረስ መበስበስም በእርሱ /በክርስቶስ/ እንዲህ ጠፋ፤ ሞትም ድል ተነሣ፤” (ቅዱስ ቄርሎስ፣ ሃይ. አበ. ፸፪፥፲፪)፡፡

ይቆየን