አንቀጸ መድኃኒት ቤተ ክርስቲያን – ካለፈው የቀጠለ

የካቲት ፳፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

… ኵላዊት (ካቶሊክ፣ Universal) የሚለው አገላለጽ በምዕራባውያን (በካቶሊካውያን) አስተሳሰብ የተለየ ትርጕም አለው፡፡ በምዕራባውያን ዘንድ ለቤተ ክርስቲያን ኵላዊት መሆን ዋናው መሠረቱ ለሮሙ ፖፕ መታዘዝ ነው፡፡ በእነርሱ አስተሳሰብ መሠረት የማይሳሳትና የክርስቶስ ወኪል አድርገው ለሚቈጥሩት ለፖፑ የማትገዛ ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት አይደለችም፡፡ በምሥራቃውያንና በኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ኵላዊት የሚያሰኛት ሥላሴ በአንድነት በሦስትነት የሚመለኩባት፣ ከሐዋርያት ጀምሮ ባልተቋረጠ ክትትል ጳጳስ ያላትና የክርስቶስ ሥጋና ደም የሚፈተትባት መሆኗ ነው፡፡ ኵላዊትነት በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንድነት (በተለይም በቅዱስ ቊርባን) እንጂ በፖፕ አንድ መሆን አይደለምና፡፡

ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ ወደ ስሚርናስ በላከው መልእክቱ እንደተናገረው፥ ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት (ፍጽምት፣ ርትዕት፥ ሁሉንም የምትይዝ) የምትባለው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የሚፈተትባት በመሆኗ ነው፡፡ በዚህ ቅዱስ ምሥጢር አማካይነት በየትኛውም ሥፍራ የምንኖር ክርስቲያኖች (በግብፅም፣ በኢትዮጵያም፣ በሰማይም፣ በምድርም) አንድ ወደ መሆን፣ ወደ ፍጽምና፣ ወደ እውነት እንመጣለን፡፡ በመሆኑም ያለዚህ ምሥጢር ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት አትባልም፡፡ በዚህም የሐዋርያውያነ አበው ትምህርት መሠረት ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን አማናዊ አይደለም፤ አምሳል ነው የሚሉ ሰዎች ስብስባቸው ቤተ ክርስቲያን እንዳልሆነ እንረዳለን፡፡

. አንዲት

እግዚአብሔር አንድ ነው፤ የክርስቶስም ማዳን አንዲት ናት፤ ተስፋ የምናደርጋት መንግሥተ ሰማያት አንዲት ናት፤ የምንቀበለው የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደምም አንድ ነው፡፡ በአጭር አገላለጽ የተገለጠው እውነት ከነማብራሪያው አንድ ነው፡፡ ይህን የምታስተምር ቤተ ክርስቲያንም አንዲት ናት፡፡ የክርስቶስ አካል ስለሆነች አንዲት ናት፡፡ የክርስቶስ አካል አይከፈልምና ቤተ ክርስቲያን አንዲት እንጂ ብዙ አይደለችም፡፡ ይህቺ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ተአምኖዋ በአንድ እግዚአብሔር ስለሆነ መለያየት አይስማማትም፡፡ ምእመናኗም አንድ ትምህርት ይማራሉ፤ አንድ እምነት ያምናሉ፤ አንድ ጥምቀት ይጠመቃሉ፡፡ ሰዎች ወይም መላእክት ከእርሷ ውጪ ወጥተው በክሕደት በኃጢአት ሊሔዱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሌላ ቤተ ክርስቲያን ሊመሠርቱ አይችሉም፡፡ እንመሥርት ቢሉም የመሠረቱት ስብስብ ቤተ ክርስቲያን ተብለው ሊጠሩበት አይችሉም ምክንያቱም ከክርስቶስ የተለየች ቤተ ክርስቲያን የለችምና፡፡

ሰዎች በተለያየ መንገድ ከአንዲቷ ማኅበር ቢወጡም ቤተ ክርስቲያን ተከፋፈለች አይባልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን አትከፈልም፤ አንዱ እንግዚአብሔር አይከፈልምና፡፡ አንዳንድ ወገኖች ለራሳቸው በየሰፈሩ “ቸርች” ብለው ይመሠርታሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ስብስባቸው ፈጽሞ ቤተ ክርስቲያን ሊባል እንደማይችል ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናትና፡፡ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ የተመሠረተች እንጂ ሰዎች ተሰብስበው የሚመሠርቷት አይደለችም፡፡ በሰዎች መሰባሰብ የተመሠረተች፣ እግዚአብሔር በአንድነት በሦስትነት የማይመለክባት፣ ምሥጢራት የማይፈጸሙባት በመሆኗ ድርጅት ወይም ተቋም እንጂ ቤተ ክርስቲያን አትባልም፡፡ በክርስቶስ ደም ወደተመሠረተችው ቤተ ክርስቲያን አንድነት መግባት የሚቻለው በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እንጂ በአንድነት ተሰብስቦ ስያሜ በመስጠት እንዳልሆነ ማወቅ ይገባናል፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የቤተ ክርስቲያን አንድነት፥ ክርስቲያኖች በእውነት አምነው በፍቅር ተመላልሰው ከእግዚአብሔር ጋር በሚፈጥሩት አንድነት የሚመዘን ነው፡፡ ይህን አንድነት ሰዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰብስበው ወይም የፍርድ ቤት ፈቃድ ይዘው ሊመሠርቱት አይችሉም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረታት እግዚአብሔር ነውና፡፡ ማንኛውም ሰው የቤተ ክርስቲያን አካል ሆኖ የሚኖረው ወይም ክርስቲያን ነው የሚባለውም በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እስካለ ድረስ ብቻ ነው፡፡ የአንድነታችን መሠረቱም በሥጋ ወደሙ የታተመው የክርስቶስ አካልነታችን ነው፤ ጌታ እንዲህ እንዳለ፡- “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በርሱ እኖራለሁ” (ዮሐ. ፮፡፶፮)፡፡ “አባት ሆይ፥ አንተ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ” (ዮሐ. ፲፯፡፳፩)፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ (Society) ሳትሆን የምእመናን አንድነት ናት፡፡ ጌታችንም የዚህች አንድነት ራስ ነው፡፡

በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን አሠረ ፍኖት ተከትላ የምትሔድና ክርስቶስን የምታምን እርሱ ራስ ሆኖላት አካሉና በእርሱ ውስጥ ያለች ናት፡፡ ክርስቲያኖች የዚች አንድነት አካል የሚሆኑት፣ በአንድነቱ ውስጥ ጸንተው የሚኖሩትና እግዚአብሔርን ወደ መምሰል የሚያድጉት በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ሲታመሙም (በኃጢአት ሲወድቁም) በእነዚህ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እየታከሙ አንድነታቸውን ያጸናሉ፡፡ ከእርስዋ ውጭ ድኅነት የሌለውም ለዚህ ነው፡፡ “ዋናው በክርስቶስ ማመናችን ነው” ብለው የሚወጡት ሰዎችም ድኅነት እንዳገኙ አድርገው መናገራቸው ከዚህ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ያፈነገጠ ከመሆኑም በላይ ስሕተት ነው፡፡

ክርስቲያኖች በዚህች አንዲት ቤተ ክርስቲያን ስንኖር ከእግዚአብሔር ጋር ያለን አንድነት እያደገ እየጠበቀ ይሔዳል፡፡ ይህ አንድነትም በጊዜ ሒደት፣ ወይም በተለያየ ቦታ በመሆን የሚቋረጥ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በውስጧ ቅዱሳን መላእክትን እንዲሁም በብሔረ ሕያዋን፣ በብሔረ ብፁዓን፣ በገነት፣ በዐጸደ ሥጋና በዐጸደ ነፍስ ያሉትን ምእመናን ሁሉ የምትይዝ አንዲት ኅብረት ናት ማለታችንም ስለዚሁ ነው (ዕብ. ፲፪፡፳፪-፳፬)፡፡ በዐጸደ ነፍስ ያሉት ምእመናን በንስሓ የተመላለሱ፣ ሩጫቸውን የጨረሱና ድል ያደረጉ ሲሆኑ፥ በዐጸደ ሥጋ ያለን ደግሞ ሩጫችንን ገና ያልጨረስንና በተጋድሎ ውስጥ የምንገኝ ነን፡፡ ሐዋርያው እንዲህ እንዳለ፡- “እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን” (ሮሜ. ፲፪፡፭)፡፡ ይህ ትምህርት የነገረ ሃይማኖት መሠረት ነው፡፡ እንዲህ የተባለበትም ምክንያት በቤተ ክርስቲያን ምንነትና ማንነት ላይ ያለን ልዩነት ለጠቅላላ ነገረ ሃይማኖት መለያየት ምክንያት ስለሚሆን ነው፡፡  ይህን የሚያስረዱ ሁለት ማሳያዎችን በማንሣት እንመልከት፡፡

፩. በካቶሊካውያን ዘንድ አንድ ሰው የፖፑን የክርስቶስ እንደራሴነት ካልተቀበለ የካቶሊክ ቤተ እምነት አባል አይሆንም፡፡ በኦርቶዶክሳዊ ትምህርት ግን ቅዱሳን መላእክት እንዲሁም በብሔረ ሕያዋን፣ በብሔረ ብፁዓን፣ በገነት፣ በዐጸደ ሥጋ ያለንና በዐጸደ ነፍስ የሚኖሩ ምእመናን አንድ የምንሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ አካልነት ነው፡፡ ይህም በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ የምናገኘው ጸጋ ነው፡፡

፪. በፕሮቴስታንቱ ዓለም ያለውን ስንመለከት ደግሞ በዐጸደ ሥጋ ያሉትና በዐጸደ ነፍስ ያሉት አማኞች የተለያዩ ናቸው፤ እርስ በርሳቸው አይተዋወቁም፡፡ በሌላ አገላለጥ እንደ እነሱ አባባል “ቤተ ክርስቲያን የሚታዩ አባላት ብቻ ያሏት ተቋም ናት”፡፡ የቅዱሳንን ምልጃ የማይቀበሉትም ስለዚሁ ነው፡፡ ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ ከላይ ከነገረን (ዕብ. ፲፪፡፳፪-፳፬) የእውነት መሠረት የተለየ ትምህርት ነው፡፡ ዳግመኛም ይህ የፕሮቴስታንቶቹ አስተምህሮ (አይቻልም እንጂ)፥ ስሙ ይክበር ይመስገንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ያደረገንን የሚለያይ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ ሰው ቤተ ክርስቲያን መባሉን አጉልቶ በመስበክ የምእመናንን አንድነት የሚበታትን ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊው ትምህርት ይህ ፍጹም ስሕተት ነው፡፡ ሐዋርያዊት ከሆነችው ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ያፈነገጠ በመሆኑም ተቀባይነት የለውም፡፡ እንዲያውም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከሚታየው የቤተ ክርስቲያን አካል የማይታየው ይበልጣል፡፡

የቤተ ክርስቲያን የአንድነቷ መሠረት ከላይ እንደገለጽነው ክርስቶስ እንጂ በአንድ ፖፕ ሥር መተዳደር ወይም በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ውስጥ አባል መሆን ስላልሆነ ቤተ ክርስቲያን ተቋም ወይም ድርጅት አይደለችም፡፡ ለአገልግሎት መፋጠን የፈጠረቻቸውን ተቋማት በማሰብ ድርጅት ወይም ተቋም የምትመስለን ካለን ተሳስተናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ራሷ ክርስቶስ የሆነላት በሰማይ ያሉ የድል ነሺዎች፣ በምድር ያሉ የክርስቲያኖች ኅብረት ወይም አንድነት ናት፡፡ ይህች አንድነት የሚታይና የማይታይ አካል አላት፡፡ የሚታይ አካል የተባለውም መዋቅሩ ሳይሆን እኛ ራሳችን ክርስቲያኖች እያንዳንዳችንና አንድነታችን ነው፡፡ የማይታየው አካሏ ደግሞ በሰማይ የሚኖሩ ቅዱሳንና እኛ የማናያቸው እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቃቸው የቤተ ክርስቲያን አካል የሆኑ ስውራን ናቸው፡፡ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ከምንም በፊት ይህን ኦርቶዶክሳዊ የነገረ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ማወቅና መረዳት አለበት፡፡

. ቅድስት

መሥራቿ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያንም ቅድስት ናት፡፡ የቤተ ክርስቲያን የቅድስና ምንጭ እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱስ ማለት የተለየ ማለት እንደሆነ፥ ቤተ ክርስቲያንም ከዓለም ተለይታ የእግዚአብሔርን ማዳን የምትመሰክር ናትና ቅድስት ናት፡፡ በሌላ አገላለጽ ደግሞ “እስመ ኢይትረከብ ነኪር በማዕከሌሃ – ባዕድ በመካከሏ አይገኝምና” እንዲል በሃይማኖት በምግባር የጸኑ ቅዱሳን መሰብሰቢያ ናትና ቅድስት ናት፡፡

እግዚአብሔር እጅግ ቸር ከመሆኑ የተነሣ፥ ሩጫችንን ያልጨረስን ክርስቲያኖች ኃጢአት ብንሠራ እንኳ በንስሓ እየተመላለስን ከምሥጢራቱ እንድንካፈል በማድረግ የድኅነት መንገዱን እንዳንለቅ ቀስ በቀስም ከአርአያ እግዚአብሔር ወደ አምሳለ እግዚአብሔር እንድናድግ አድርጎናል፡፡ ከበደላችን ተመልሰን ከምሥጢራቱ ስንካፈልም ከእግዚአብሔር ጋር እንዋሐዳለን፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ “የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ የንጉሡ ካህናት ቅዱስ ሕዝብ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ” ያለን (፩ኛ ጴጥ. ፪፡፱)፡፡ ዳግመኛም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ” (ሮሜ. ፩፡፯፣ ፩ኛ ቆሮ. ፩፡፪)ያለንም ስለዚሁ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ቅድስና የሚያርቀን ክሕደትና ኃጢአት ብቻ ነው ማለት ነው፡፡

አንድ ሰው ቅዱስ ሆኖ ለመኖር በዚህ አንድነት ውስጥ መኖር ይገባዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ማለትም ከክርስቶስ ውጪ ቅድስና የለምና ከዚህ አንድነት ከተለየ ምንም ያህል በጎ ምግባር ቢኖረውም ቅዱስ አይባልም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቅድስና ከመሥራቿ ከክርስቶስ ስለሆነ በሰዎች ኃጢአት ቅድስናዋን አታጣም፡፡ አንድ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን ቢመላለስም በኃጢአት ውስጥ የሚኖር ከሆነ የቤተ ክርስቲያን አካል ነው ማለት አይቻለም፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ስለሆነች እርሱም የቅድስና ሥራ መሥራት ይገባዋልና፡፡ ለዚህ ነው በቅዳሴ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለተሰበሰቡት ሰዎች ዲያቆኑ “በንስሓ ውስጥ ያላችሁ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ” ሲል ካህኑ በሚያደርጉት ጸሎት ውስጥ “የቀደመ ሥራቸውን ይቅር ብለህ በሰላም ነፍሳቸውን አድን፤ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያንህ አንድ አድርጋቸው፡፡ ተቀዳሚ ተከታይ በሌለው በአንድ ልጅህ በጌታችን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ በይቅርታውና በምሕረቱ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጨምራቸው” በማለት የሚጸልዩት፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ክርስቲያን ቅድስት ከሆነችው አንድነት እንዳይለይ ራሱን ሁልጊዜ በምሥጢራት መቀደስ አለበት ማለት ነው፡፡

. ሐዋርያዊት

ሐዋርያዊት የሚለው ቃል በውስጡ ሦስት መሠረታዊ መልእክታትን የያዘ ነው፡፡ አንደኛው ትርጕም ቤተ ክርስቲያን ሲባል የሐዋርያትን እምነት የሚያስረዳና በዚህም ከመናፍቃንና ከአረማውያን እምነት የተለየች መሆኗን የሚገልጽ ነው፡፡ ሁለተኛው ሐዋርያዊ ውርርስ (ቅብብሎሽ) እንዳላት የሚያስረዳ ነው፡፡ ይህም ማለት አሁን ያለው እውነት ወደኋላ በሔድን ቊጥር ሳይዛነፍ፣ ሳይሸራረፍ፣ በመሀልም የሚቋረጥ መስመር ሳይኖረው ከሐዋርያት ዘንድ እንደሚያደርሰን ያሳያል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህን እምነት በጃንደረባው (ሐዋ. ፰፡፳፮-፵)፥ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ደግሞ በአኀት አብያተ ክርስቲያናት በኵል ተቀብላዋለች፡፡ ሦስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ ተልእኮዋን መናገር ነው፡፡ ይህም ማለት ቤተ ክርስቲያን “ሒዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ. ፳፰፡፲፱) የሚለውን ትርጕም የያዘ ነው፡፡

በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ሰውን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመማረክ ዋና ተልእኮዋ ነው፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ዋናው ዓላማ ሰዎችን ወደ ቀደመ ክብራቸው ለመመለስና ወደ ራሱ መንግሥት ለማምጣት ነው፡፡ ይህን ግብር ስለፈጸመም የሃይማኖታችን ሐዋርያ ተብሏል (ዕብ. ፫፡፩)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ተልኮ ወደዚህ ዓለም እንደመጣ ሁሉ፥ እርሱም ሐዋርያትን ወደ ዓለም ልኳቸዋል፡፡ “አብ እንደላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ” (ዮሐ. ፳፡፳፩-፳፪)፡፡ ሐዋርያት ወደ ዓለም ሁሉ በመሔድም የቤተ ክርስቲያንን መሠረት አስቀምጠዋል፡፡ ዳግመኛም በዚህ ምድራዊ አጥቢያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን በሰማያት ላለው የእግዚአብሔር መንግሥት በቃልና በገቢር ምስክር ትሆን ዘንድ ስለተላከች ሐዋርያዊት ትባላለች፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! ይህ ትምህርት፣ ከታኅሣሥ ፩ – ፲፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በታተመው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ በንቁ ዓምድ ሥር ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡