ሀልዎተ እግዚአብሔር

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ 

የካቲት ፳፮፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች!  እንዴት አላችሁልን? ትምህርት እንዴት ነው? የግማሽ ዓመት ትምህርት ተጀምሯልና በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት በነበረው የትምህርት ወቅት ደከም ያለ ውጤት ያስመዘገባችሁበትን ትምህርት በደንብ ትኩረት ሰጠታችሁ በመማር ማሻሻል ይገባል! ቤተ ክርስቲያን በመሄድም መንፈሳዊ ትምህርት መማርንም አትዘንጉ! ደግሞም ፳፻፲፮ ዓ.ም. (የሁለት ሺህ ዐሥራ ስድስት) ዐቢይ ጾም መጋቢት ሁለት ይጀምራልና ከምንጊዜውም በተለየ መልኩ በጸሎት መትጋት አለብን፡፡  ዕድሜያችን ከሰባት ዓመት በላይ የሆነን ደግሞ እንደ አቅማችን መጾም አለብን! መልካም!!!

ልጆች! አሁን ለዛሬ ወዳዘጋጀንላችሁ ትምህርት እናምራ! በባለፈው የትምህርት ክፍለ ጊዜያችን “ሃይማኖት” በሚል ርእስ ተምረን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ስለ “ሀልዎተ እግዚአብሔር” ማለትም ዓለምን ሁሉ የፈጠረ የአምላካችን የእግዚአብሔር መኖር በምን እንደሚታወቅ እንማራለን፤ ተከታተሉን!

“ሀልዎት” ማለት “መኖር” ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፫፻፸) ሀልዎተ እግዚአብሔር ስንል ደግሞ የእግዚአብሔር መኖር ማለታችን ነው፤ ባለፈው ትምህርታችን ላይ ሁሉን ያስገኘና የፈጠረ እግዚአብሔር መሆኑን ያወቅነው በሃይማኖት እንደሆነ እንደተማራችሁት ዛሬ ደግሞ “የእግዚአብሔር መኖር በምን ይታወቃል የሚለውን በተወሰነ መልኩ እንማማራለን፡፡

የአምላካችን የእግዚአብሔር መኖር ከሚታወቅባቸው ነገሮች አንዱ ሥነ ፍጥረት ነው፤ ለዚህ ዓለም ፈጣሪ (አስገኚ) አለው፤ የሚታየውን እንደገናም እኛ የማናያቸውን ፍጥረታት ሁሉ የፈጠረ እግዚአብሔር ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ጻድቁ ኢዮብ እንዲህ ሲል መስክሯል፤ ‹‹አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፤ ያስተምሩህማል፤ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፤ ይነግሩህማል፤ ወይንም ለምድር ተናገር፤ እርስዋም ታስተምርሃለች…፡፡›› (ኢዮብ ፲፪፥፯) አያችሁ ልጆች! እግዚአብሔር የሁሉ ፈጣሪ መሆኑን እንስሳትም እንኳን ምስክር ይሆነናሉ፡፡

ሌላው ደግሞ ልጆች! ነቢዩ ኢሳይያስ አምላካችን እግዚአብሔር ፍጥረታትን እንደፈጠረ እንዲህ ነግሮናል፤ ‹‹…ሠሪውም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ ስለሚመጣው ነገር ጠይቁኝ፤  …እኔ ምድርን ሠርቻለው፤ ሰውንም በእርሷ ላይ ፈጥሬአለሁ፤ እኔ በእጄ ሰማያትን ዘርግቻለው…፡፡››     (ኢሳ. ፵፭፥፲፩-፲፪)

ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስን ገና ስንገልጠው ባለው በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እንዲህ የሚል ቃል አለ፤ ‹‹በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ…፡፡›› (ዘፍ.፩፥፩) እንግዲህ ልጆች! እግዚአብሔር የዚህ ዓለም ፈጣሪ እንደ ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ማስረጃዎች አሉ፤ ለግንዛቤ ያህል ግን ይህን አቀረብን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እግዚአብሔር ለመኖሩ ሌላው ምስክር ደግሞ ፍጥረታትን ስንመለከት ሁሉም ሥርዓታቸውን ጠብቀው መንቀሳቀሳቸውን ስንረዳ ነው፡፡ ለምሳሌ ፀሐይን ብንወስድ ጠዋት ከምሥራቅ ወጥታ ማታ በምዕራብ ትጠልቃለች፤ ጨለማና ብርሃን፣ ሌሊትና ቀንም፣ ክረምትና በጋም ይፈራረቃሉ፤ የእነዚህ ፍጥረታት እንቅስቃሴ እግዚአብሔር እንዳለ ያስረዳሉ፤ እኛም የሰው ልጆች እግዚአብሔር እንዳለ ምስክሮች ነን፡፡

ልጆች! ሃይማኖት ያለው ሰው እግዚአብሐር እንዳለ ያምናል፤ ይመሰክራልም፤ አንዴ ምን ሆነ መሰላችሁ? የእግዚአብሔር ወዳጅ አብርሃም አባታችን ቤተ ሰቦቹ ጣዖት የሚያመልኩ ነበሩ፡፡ ጣዖት ታውቃላችሁ አይደል ልጆች? ጣዖት ማለት ሰዎች ድንጋይ ጠርበው አልያም ደግሞ እንጨት አለዝበው የሚሠሩትና አምላክ ነው ብለው የሚያምኑት ማለት ነው፡፡ ታዲያ አብርሃም አባቱ ታራ የሠራውን ጣዖት እንዲሸጥ ወደ ገቢያ ላከው፡፡ አብርሃምም ዓይን እያለው የማያይ፣ ጆሮ እያለው የማይሰማ፣ እግር እያለው የማይሄድ ጣዖት የሚገዛ እያለ በገቢያ መሐል መዞር ጀመረ፡፡

ይገርማችኋል ልጆች! ሰው ሁሉ እርሱ ያላመነበትን እርሱ ያቃለለውን ማን ይገዛዋል እያሉ ሳይገዙት ቀሩ፤ አብርሃምም አባቱ እየሠራ የሚሸጠውን ጣዖት “አምላክ ከሆንክ አብላኝ፤ ርቦኛል፤ አጠጣኝ፤ ጠምቶኛል” አለው፤ ግን ምንም አልመለሰለትም፤ ግዑዝ ነገር (መናገር የማይችል) ነበርና፤ አብርሃምም ጣዖቱ አምላክ አለመሆኑን ተገነዘበ፡፡ ወዲያውኑ በደንጊያ ቀጠቀጠው፤ ከዚያም የሁሉን ፈጣሪ መፈለግ ጀመረ፤ነፋስን፣ እሳትን ፀሐይን፣ ጨረቃን ፣ ወንዙን፣ ተራራውን ሁሉ በየተራ እያፈራረቀ አምላክ መሆናቸውን ተመራመረ፡፡ አንዱ አንዱን ሲያሸንፈው፣ አንዱ በአንዱ ሲተከ ተመለከተ፡፡ የዚህን ጊዜ የእነዚህ ሁሉ ፈጣሪ እንዳለ ተገነዘበና “የፀሐይ አምላክ ተናገረኝ” ብሎ ለመነ ( ጸለየ)፡፡ እግዚአብሔርም ድምጹን አሰማው፤ ጣዖት ከሚመለክበትም ከተማ ተለይቶ እንዲወጣ ነገረው፡፡ አብርሃምም ከዚያ ከተማ እግዚአብሔር ወደ ነገረው ቦታ ሄደ፡፡ (ዘፍ.፲፩፥፳፰ አንድምታው)

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! እግዚአብሔርን በዓይናችን ማየት ባይቻለንም በሥነ ፍጥረቱ በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት፣ በውስጣችን ባለው ኅሊናችን መኖሩን እናውቃለን፡፡ ቀን ፀሐይን ያወጣልናል፤ በክረምት ዝናም ይሰጠናል፤ የተዘራው ዘር እንዲያድግ ፍሬን እንዲይዝ ያደርግልናል፡፡ ክረምትና በጋን ያፈራርቃል፡፡ እኛንም ይመግበናል፤ ከጠላታችን ዲያብሎስ ይጠብቀናል፤ ሁሉን የፈጠረ፣ ሁሉን የሚያውቅ እግዚአብሔር መኖሩን ማመን መልካም ሥራን በመሥራት፣ ሕጉን ትእዛዙን በመጠበቅ ልንኖርና ልንመሠክር ያስፈልጋል፤ እግዚአብሔር መኖሩን ለሰዎች መልካም በማድረግ፣ አታድርጉ የተባልነውን ባለማድረግ፣ አድርጉ ተብለን የታዘዝነውን መልካም ነገር ደግሞ በማድረግ በእግዚአብሔር ማመናችንን መመስከር አለብን ፤ ቸር ይግጠመን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

ሥርዓተ አምልኮ

አምላካችን እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ፍጥረት ሁሉ እንዲያመልከውና እንዲመሰግነው ነው፤ በአርአያውና በአምሳሉ የተፈጠርን ሰዎች ብቻም ሳይሆን በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀሱ እንስሳት ሳይቀር ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፡፡ በተለይም በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባልን ሰዎች የምናመልክበት የቅድስና ሕይወት ሰጥኖናል፡፡ ሕጉን ጠብቀን በሥርዓቱ ለምንኖር ለእኛ እርሱ ምሕረቱ የበዛ በመሆኑ በሕይወታችን ውስጥ ሊኖር ይወዳል፤ በቤቱም ስንገኝ ደስ ይሰኛል፡፡ እርሱን በዓይን ለማየት ባይቻለንም መኖሩን የምናውቀበትና የምናመሰግንበት፣ ለእርሱም የአምልኮት ስግደት የምናቀርብበትና የምናዜምበት በአጠቃላይ የምናመልክበት መንገድ ፈጥሮልናል፡፡ ለዚህም የከበረ ተግባር መፈጸሚያ ባርኮና ቀድሶ ንዋያተ ቅድሳትን ሰጥቶናል፡፡

ሥርዓተ አምልኮ

በዓላት ከማንኛውም ቀናት የበለጠ አምላካችን እግዚአብሔርን የምናመሰገንባቸውና የምናወድስባቸው፣ የተቀደሱትን ዕለታት በማሰብና በመዘከር በዝማሬ፣ በሽብሻቦና በእልልታ የምናከብርባቸው ናቸው፡፡ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው የሚወጡባቸውና ሕዝበ ክርስቲያኑን የሚባርኩባቸው ስለሆኑም በክብርና በድምቀት ይከበራሉ፡፡   

ሥርዓተ አምልኮ

በጸሎትና በስግደት እንዲሁም በምጽዋት የታገዘ ጾም በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ በመሆኑ ድኅነትን ማሰጠት ብቻም ሳይሆን በረከትን ያስገኛል፡፡ በዚህም የተነሣ ሥራችን፣ ትዳራችን እንዲሁም አገልግሎታችን ይባረክልናል፡፡

ሥርዓተ አምልኮ

ሥርዓት  “ሠርዐ” ሠራ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ደንብ፣ አሠራር፣ መርሐ ግብር ማለት ነው። በሃይማኖት ውስጥ የሚፈጸም የመንፈሳዊ አገልግሎትና አሠራር እንዲሁም ክርስቲያናዊ ሥርዓትን ያመለክታል።

 ሥርዓተ አምልኮት

የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮት ለአምላካችን እግዚአብሔር የሚቀርብ ሥርዓት ነው፡፡ ይህም ሥርዓተ ጸሎትን፣ ሥርዓተ ጾምን፣ ሥርዓተ ምጽዋት፣ ሥርዓተ ስግደትን፣ ሥርዓተ በዓላትን፣ ሥዕላትን፣ መስቀልንና ንዋያተ ቅድሳትን ያካትታል፡፡

ዕረፍተ ዘአበዊነ አብርሃም፣ይስሐቅ ወያዕቆብ

የአባቶቻችን የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብን መታሰቢያቸውን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶቻችን አዘውናል፤ ከእርሳቸው ዘለዓለም የሚኖር ርስትን ተቀብለናልና፡፡ የእነዚህንም አባቶች ገድላቸውን እንዘክር ዘንድ ተገቢ ነው፡፡

ሐዋርያው ይሁዳ

በስመ ይሁዳ የሚጠሩ በርካታ የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ ተጠቃሾች ቢኖሩም በሰኔ ፳፭ ቀን ቤተ ክርስቲያናችን የምታከብረው ሐዋርያው ይሁዳ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የሆነው የፀራቢው የዮሴፍ ልጅ እንዲሁም ያዕቆብ ለተባለው ሐዋርያ ወንድም ነው፡፡ አስቀድሞም ስሙ ታዴዎስ ይባል ነበር፡፡ ይህም ሐዋርያ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ያመነና በብዙ ሀገሮች የሰበከ ነው፤ ከእነርሱም መካከል በአንዲት ዴሰት ገብቶ በማስተማር በዚያ የነበሩትን ሰዎች በጌታችን ስም አሳምኖ ቤተ ክርስቲያን እንደሠራላቸውና በቀናች ሃይማኖትም አጽንቷቸዋል፡፡

‹‹እግዚአብሔር ግን ለዘለዓለም ይኖራል›› (መዝ.፱፥፯)

ዘመን የማይቆጠርለት፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር፣ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው አምላካችን እግዚአብሔር ለዘለዓለም ይኖራል፡፡ በምድር ላይ ያሉ የምናያቸው አስደናቂና አስገራሚ የምንላቸው ነገሮች ሁሉ ያልፋሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን እነዚህን ሁሉ አሳልፎ የሚኖር ዘለዓለማዊ አምላክ ነው፡፡‹ ‹‹እምቅድመ ዓለም ወእስከለዓለም ሀሎ እግዚአብሔር በመንግሥቱ፤ ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት ዓለምን ከፈጠረ በኋላ ለዘለዓለም እግዚአብሔር በመንግሥቱ አለ›› እንዲል ቅዳሴ::

‹‹እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም›› (ዘዳ. ፴፫፥፳፮)

ከጠፈር በላይ ርቀቱ፣ ከባሕር በታች ጥልቀቱ፣ ከአድማስ እስከ ናጌብ ስፋቱ የማይታወቅ፣  ነፋሳት ሳይነፍሱ፣ አፍላጋት ሳይፈሱ፣ ብርሃናት ሳይመላለሱ፣ የመባርቅት ብልጭታ ሳይታይ፣ የነጎድጓድ ድምጽ ሳይሰማ፣ መላእክት ለቅዳሴ ከመፈጠራቸው አስቀድሞ፣ በአንድነቱ ሁለትነት፣ በሦስትነቱ አራትነት ሳይኖርበት፣ ለቀዳማዊነቱ ጥንት፣ ለማዕከላዊነቱ ዛሬ፣ ለደኃራዊነቱ ተፍጻሜት የሌለበት፣ በባሕርዩ ሞት፣ በሥልጣኑ ሽረት፣ በስጦታው ንፍገት የማይስማማው፣ የማይሾሙት ንጉሥ፣ የማይጨበጥ እሳት፣ የማይነጥፍ የፍቅር ጅረት፣ የነበረ ያለና የሚኖር፣ እንደ አምላካችን እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም፡፡

‹‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ›› (ዘፀ. ፮፥፪)

እግዚአብሔር አምላካችን ሰማይና ምድርን፣ መላእክትን፣ ሰውን እንዲሁም ፍጥረታትን በሙሉ የፈጠረ አምላክ ነው፡፡ ለፍጥረታቱም ህልውናውን እንደብቃታቸው ይገልጻል፤ በጥንተ ተፈጥሮ እግዚአብሔር አምላክ መላእክትን ለባውያን (አዋቂዎች) አድርጎ ከፈጠራቸው በኋላ በሰጣቸው ዕውቀት ተመራምረው ፈጣሪያቸውን ያመልኩት ዘንድ እንዲሁም ከባሕርዩ ፍጹም ርቀት የተነሣ በመካከላቸው ሳለ ተሰወረባቸው፡፡ መላእክትም ተፈጥሮአቸውንና ፈጣሪያቸውን መመርመር ጀመሩ፤ አንዱም ለአንዱ ‹‹አንተ ምንድን ነህ? ከየትስ መጣህ?›› ይባባሉ፣ እርስ በርሳቸውም እየተያዩ በተፈጥሮአቸው ይደነቁ ነበር፡፡ በኋላም ‹‹ማን ፈጠረን? ከየትስ መጣን?›› የሚለው የማኅበረ መላእክት ጥያቄ መበርታቱን የተረዳው ሳጥናኤል ሹመቱ ከሁሉ በላይ ነበርና አሻቅቦ ቢያይ ‹እኔ ነኝ ባይ› ድምጽ አጣ፤ ዝቅ ብሎም ቢያዳምጥ ከእርሱ በክብር ያነሱ መላእክት ይመራመራሉ፤ ‹ለምን እኔ ፈጠርኳችሁ ብዬ ፈጣሪነትን በእጄ አላስገባም› ብሎ አሰበ፤ ከዚያም ‹እኔ ፈጣሪያችሁ ነኝ› በማለት ተናገረ፡፡…