ማኅበረ ቅዱሳን 34ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አከበረ
ማኅበረ ቅዱሳን 34ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በአበው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ ግንቦት 2 ቀን 2018 ዓ.ም በማኅበሩ ሕንጻ 3ኛ ወለል ንቡረ ዕድ ድሜጥሮስ አዳራሽ ከቀኑ 8 ሰዓት አክብሯል።
በመርሐ ግብሩ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ ካህናት አባቶች፣ የሥራ አመራር ጉባኤ አባላት፣ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት፣ የየማስተባበሪያ ኃላፊዎች፣ አባላትና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በጉባኤው መዝሙር በበኩረ መ/ን ኪነ ጥበብ እና በማኅበሩ መዘምራን የቀረበ ሲሆን ትምርተ ወንጌል በመ/ር ዲ/ን ዮሐንስ ጌታቸው ቀርቧል እንዲሁም ማኅበሩ ባለፉት 34 ዓመታት ያከናወናቸው ዋና ዋና አገልግሎቶችም ተዳሰዋል።
የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ ጸሐፊ ዲ/ን ብንያም አያሌው የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ማኅበሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ከተመሠረተበት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር ውስጥ 52 ማእከላት፣ 468 ወረዳ ማእከላት፣ 463 ግንኙነት ጣቢያዎች እና 459 ግቢ ጉባኤያት፤ እንዲሁም በውጪ ሀገር 7 ማእከላት፣ 27 ንኡሳን ማእከላት፣ 29 ግንኙነት ጣቢያዎች እንዲሁም 22 ግቢ ጉባኤያት መኖሩን ገልጸዋል።
ጸሐፊው አክለውም ማኅበሩ ባለፉት 34 ዓመታት ያከናወናቸውን የዋና ዋና ተግባራት ዘገባ ያቀረቡ ሲሆን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮዋን ለመደገፍ በወጣቶች የሰብእና ግንባታ ፣ በገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች ድጋፍ፣ በማኅበራዊ ድጋፍ፣ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት፣ በሚዲያ አገልግሎት እና በሌሎች በርካታ ዘርፎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷልም ብለዋል።
