ነገረ ድኅነት በመጽሐፍ ቅዱስ – የመጀመሪያ ክፍል

በዳዊት አብርሃም

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ስለ ነገረ ድኅነትም ኾነ ስለማናቸውም ሃይማኖታዊ ጉዳይ ስናጠና አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ብቻ መመርኮዝ የለብንም፡፡ አንዲቷን ጥቅስ ከአጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዐሳብ ለይተንና ከሌሎች ጥቅሶች ነጥለን መመልከት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ያደርሳል፡፡ ኦርቶዶክሳዊውን የነገረ ድኅነት አስተምህሮ የሚቃወሙና በተቃራኒውም ስሕተት የኾነ ትምህርት በማስተማር የሚከራከሩ ወገኖች በዚህ ዓይነቱ ስሕተት ሊጠመዱ የቻሉበት አንዱ ምክንያት በአንዲት ነጠላ ጥቅስ ላይ ሙጥኝ ብለው ሌሎቹን ግን ችላ ማለት ስለሚቀናቸው ነው፡፡ ደካማ ሰው አንድን ጥቅስ ብቻ ነጥሎ በማንጠልጠል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሲደርስ ብልህ፣ ጠቢብና ዕውቀት ፈላጊ ሰው ግን አንዱን ከአንዱ ጋር እያነጻጸረ በማጥናት፣ በመታገሥ ምርምሩን ይቀጥላል፡፡ በዚህም ትክክለኛ ዕውቀት ላይ ይደርሳል፤ እውነትን ወደ ማወቅም ይመጣል፡፡

ከነገረ ድኅነት አስተምህሮ አንጻር ይህን ነገር በምሳሌ እንመልከት፤ “እነርሱም ‹በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ› አሉት” (ሐዋ. ፲፮፥፲፫)፡፡ አንዳንዶች ይህን ጥቅስ በመምዘዝ “ለመዳን ማመን ብቻ በቂ ነው” ይላሉ፡፡ ይህን ንግግር ቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ ሲላስ በፊልጵስዩስ የእስር ቤት ጠባቂ ለነበረው ሰው የተናገሩት ኀይለ ቃል ነው፡፡ “ጥቅሱ የተነገረው ለማን ነው? ለምን ተነገረ? ከዚያስ ወረድ ብሎ ምን ይላል? ከሌሎች ጥቅሶች ጋር ያለው ተዛምዶ ምን ይመስላል?” ብለው ሳይጠይቁ ለውሳኔ መቻኮል ትክክል አይደለም፡፡ እስኪ ጥቅሱን በእርጋታ እንመርምረው፤

፩ኛ. ይህ ቃል የተነገረው ከአሕዛብ ወገን ለኾነ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው እምነት የለሽ ነው፡፡ ስለዚህም ምንም ዓይነት በጎ ሥራ ቢሠራ ዋጋ አያገኝም፡፡ ለመዳን አስቀድሞ ማመን አለበትና፡፡ ሳያምን ወደ ሌላ በጎ ሥራ ቢጓዝ መዳንን አያገኝምና፡፡ ስለዚህም ጳውሎስ እና ሲላስ አስቀድመው የመዳን በር የኾነውን ቃል ነገሩት፤ ‹‹እመን›› አሉት፡፡ እምነት ለመዳን የመጀመሪያው ደረጃ ነው፤ ሌሎች ለመዳን ከሰው የሚጠበቁት ዂሉ ከማመን በኋላ የሚመጡ ናቸው፡፡

፪ኛ. መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ የመጀመሪያ ደረጃ ተግባርን የሒደቱን አጠቃላይ ኹኔታ የሚያሳይ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ለዚህም ዓይነተኛው ምሳሌ ስምዖን አረጋዊ ነው፡፡ ስምዖን አረጋዊ “ዓይኖቼ በሰዎች ዂሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋል” (ሉቃ. ፪፥፴-፴፩) በማለት የተናገረው ጌታ ተሰቅሎ፣ ሞቶ የሚፈጽመውን ማዳን አይቶ አይደለም፡፡ እርሱ ለማየት የቻለው የጌታን መወለድ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የጌታችን መወለድ የማዳን ሥራው አካል መኾኑን ስለተረዳ “እንግዲህ ባርያህን አሰናብተው” አለ፡፡ የጳውሎስ እና የሲላስ ዐሳብም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለእስር ቤቱ ጠባቂ “አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችኁ” ሲሉ የእርሱና የቤተሰቡ መዳን በእርሱ ማመን ብቻ ፍጻሜ ያገኛል ብለው አይደለም፡፡ ነገር ግን በምግባር፣ በተጋድሎ፣ ምሥጢራትን በመፈጸምና በሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ፍጻሜ የሚያገኘውን የመዳን ጉዞ በእምነት እንደሚጀምር መናገራቸው ነው፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘኬዎስ የተናገረው ኃይለ ቃልም ተመሳሳይ መልእክት ያለው ነው፤ “እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤” (ሉቃ. ፲፱፥፱)፡፡ ይህ ማለት የዘኬዎስ የመዳን ጉዞ ዛሬ ተጀመረ ማለት እንጂ ዘኬዎስ ጌታን በመኖሪያ ቤቱ ተቀብሎ ስላስተናገደው ብቻ መዳንን ወርሷል ወይም ድኗል ማለት አይደለም፡፡

፫ኛ. ጳውሎስና ሲላስም ይህን ሲሉ አሁን ባመንክበት ቅጽበት ትድናለህ ማለታቸው ሳይኾን የመዳኑን መንገድ ይዘኸዋል ማለታቸው መኾኑን የሚያረጋግጥ አንዱ አባባል “ትድናለህ” ብለው በትንቢት አንቀጽ መናገራቸው ነው፡፡

፬ኛ. ሌላው የእርሱ እምነት ለመዳኑ የመጀመሪያ ርምጃ መኾኑን የምናውቀው “ቤተሰቦችህ ይድናሉ” በሚለው የሐዋርት ንግግር ነው፡፡ “እርሱ ባመነው ቤተሰቦቹ እንዴት ይድናሉ?” የሚል ጥያቄ ብናነሣ ሐዋርያት የተናገሩት አሁን በዚያ ቅጽበት ለሚኾነው ሳይኾን ከዚያ ቅጽበት ለሚጀመረውና ወደፊት ለሚጠናቀቀው መዳን መኾኑን እንረዳለን፡፡ እርሱ ካመነ በኋላ ቤተሰቦቹን ሲያሳምን ደግሞ እነርሱም ልክ እንደ እርሱ የመዳንን ጉዞ አንድ ብለው ይጀምራሉ፡፡ ይህም ማመን ለመላው ቤተሰብ የመዳን ጉዞ የመጀመሪያ ምዕራፍ መኾኑን ይገልጣል፡፡

፭ኛ. ኃይለ ቃሉን ዝቅ ብለን ስናነብም ይህን የሚያጠናክር ማስረጃ እናገኛለን፤ “ለእርሱና በቤቱም ላሉት ዂሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሯቸው። በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፤ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተሰዎቹ ዂሉ ጋር ተጠመቀ፤” (ሐዋ. ፲፮፥፴፪-፴፫)፡፡

“እመን፤ ትድናለህ” የሚለውን ኃይለ ቃል ብቻ መዝዘን በማውጣት “ለመዳን የሚያስፈልገው ማመን ብቻ ነው” ከሚል ድምዳሜ ከደረስን በተጠቀሱት ስሕተቶች ላይ እንወድቃለን፡፡ ይህም የበለጠ ግልጽ እንዲኾንልን ሌላ ምሳሌ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት፤

አንድ ወጣት ወደ ጌታችን ቀርቦ “መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ?” ሲል ጠየቀው (ማቴ. ፲፱፥፲፮)፡፡ ጌታችን ሲመልስለትም “እመንና ትድናለህ” አላለውም፡፡ ነገር ግን “ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ” ነው ያለው (ማቴ. ፲፱፥፲፯)፡፡ ታዲያ ከዚህ የወንጌል ጥቅስ ተነሥተን “ትእዛዞችን መጠበቅ (ሕግጋቱን መጠበቅ) ብቻውን ለመዳን በቂ ነው” ብሎ መደምደም ይቻላል? በፍጹም አንችልም፡፡ አንድ ጥቅስ ብቻ አንጠልጥሎ ለመደምደም መቸኮል ግን ይህን ከመሰለው ስሕተት ላይ ሊጥለን እንደሚችል ልብ እንበል፡፡

በዚሁ ጥቅስ ላይ ንባባችንን ስንቀጥል ጥያቄውን ያቀረበው ወጣት “እነዚህን ዂሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄያቸዋለሁ” ብሎ መለኮታዊውን ትእዛዝ መጠበቁን ሲያረጋግጥ እናገኘዋለን፡፡ እንግዲህ አስቀድሞ ጌታችን “ለመዳን መሥፈርቱ ትእዛዛትን መጠበቅ ነው” ብሎ የተናገረውን ይዘን አሁን ወጣቱ “‹ፈጽሜያቸዋለሁ› በሚል ምላሹ ምክንያት ድኗል” ብለን ልንደመድም አንችልም፡፡ ጌታችን ለወጣቱ “ፍጹም ልትኾን ብትወድ ሒድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፤ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ” በማለት ለመዳን ማድረግ የሚገባውን ዂሉ እንደ ነገረው መዘንጋት የለብንም (ማቴ. ፲፱፥፳፮)፡፡

ከዚህ ላይ ለመዳን እምነት ወይም ጸጋው አልተጠቀሰም፡፡ በዚህ ጥቅስ መሠረት ሕግጋትን መፈጸም ወይም በጎ መሥራት እንኳን ቢኾን በቂ አይደለም፡፡ ከዚያ ያለፈ ተግባር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በዚህ አንድ ጥቅስ ላይ ብቻ መመሥረትን የመረጠ ሰው “ያለውን ዂሉ ሸጦ ለችግረኞች አከፋፍሎ ጌታን ካልተከተሉ በቀር መዳን አይቻልም” ብሎ ለመደምደም ይገደዳል ማለት ነው፡፡

አንዳንድ ስሑታን ስለ ነገረ ድኅነት ሲከራከሩ የሚያነሡት ሌላው ጥቅስ “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ” የሚለው ኃይለ ቃል ነው (ሮሜ. ፭፥፩)፡፡ አንዳንዶች ይህን ጥቅስ እያነሡ “ከዚህ በላይ ማስረጃ ምን ትፈልጋለህ? በእምነት ብቻ እንደሚጸደቅ በግልጥ ተጽፏል፤ ይህን ጥቅስ ምን ታደርገዋለህ? ወይስ እንዴት ልትክደው ትችላለህ?” በሚል ዐሳብ ይከራከራሉ፡፡

የእኛ ምላሽም እንዲህ ነው፤ ይህንን ትምህርት አንክድም፤ አናስተባብልምም፡፡ ነገር ግን ለብቻው ነጥለን አንመለከተውም፡፡ እዚያው ከአጠገቡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጻፈው ሌላ ትምህርት አለና እርሱን አምጥተን አብረን እናጠናዋለን፡፡ ትምህርቱም እንዲህ የሚል ነው፤ “በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይደለም” (ሮሜ. ፪፥፲፫)፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ሐዋርያው ጽድቅ (መዳን) የሚገኘው ሕግን በማድረግ መኾኑን ያስተምረናል፡፡

ታዲያ በዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ተመሥርተን “መዳን ሕጉን በመተግበር ብቻ የሚገኝ ነው” ልንል እንችላለን? አንልም፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም የሐዋርያውን ጥቅሶች ሳንነጣጥል በአንድነት እንወስዳቸዋለን፡፡ ሐዋርያው በሁለቱም ቦታዎች በሮሜ. ፪፥፲፫ እና ፭፥፩ ላይ የጻፈልንን ለድኅነታችን አስፈላጊ የኾኑትን ተግባራት እንማራለን፡፡ በዚህ መሠረት ለመዳናችን ማመናችን የሚኖረውን ዋጋ መልካም ሥራ አይተካውም፤ እንደዚሁም መልካም ሥራ ለመዳናችን አስፈላጊ መኾኑ የእምነትን አስፈላጊነት አይሽረውም፡፡ “ሰው በእምነት ብቻ ሳይኾን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ፡፡ እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?” (ያዕ. ፪፥፳፬-፳፭) ተብሎ እንደ ተጻፈው ለመዳን ሁለቱንም እምነትንና ሥራን አዋሕደን መያዝ እንዳለብን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ሌላ ኃይለ ቃል ደግሞ እንመልከት፤ “ነገር ግን ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ኾኖ ይቈጠርለታል” (ሮሜ. ፬፥፭) በዚህ ኃይለ ቃል መነሻነት ሌሎቹን የትምህርት ዓይነቶች ወይም ኃይለ ቃሉን በምልዓት ለመረዳት ስንሞክር አንድ ሰው ኃጢአተኛ ኾኖ ሳለ፣ ኃጢአት መሥራቱንም ሳያይተው ወይም ንስሐ ሳይገባ “ይጸድቃል” ብለን መደምደም እንችላለን? ይህንን ኃይለ ቃል በትክክል ለመረዳት ጥቅሱን ግልጽ ሊያደርጉ የሚችሉ ሌሎች ነጥቦችን መረዳት ይኖርብናል፡፡

ለምሳሌ ከዚያው ከሮሜ መልእክት አንድ ሌላ ጥቅስ እንመልከት፤

  • “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ዂሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል” (ሮሜ. ፩፥፲፰)፡፡
  • “ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለ ጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ” (ሮሜ. ፪፥፭)፡፡

ይቆየን