“እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።” (መዝ ፵፮ ፥፭)
ዕርገተ ክርስቶስ (The Ascension of Jesus Christ)
በቀሲስ ኃይሉ ብርሃኑ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትልቅ ቦታ ካላቸው 9 ዐበይት የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓላት መካከል አንዱ ነው።
“ዕርገት” የሚለው ቃል “ዐርገ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ከታች ወደ ላይ መውጣት፣ ከፍ ከፍ ማለት፣ ማረግ ማለት ነው፡፡ ዕርገት (Ascension) ሲባልም ማረግን፣ ወደ ላይ መውጣትን ያመለክታል፡፡ በዓለ ዕርገትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም የነበረውን የማዳኑን ሥራ ጨርሶ ወደ ላይ መውጣቱና በቀደመ ክብሩ በአብ ቀኝ መቀመጡ የሚከበርበት በዓል ነው፡፡ ለዚህም መሠረት እንዲሆን አርዮስን ለማውገዝ በኒቅያ የተሰበሰቡት ቅዱሳን አበው “ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ…/ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ…” ብለው ዕርገቱን በቅዱሳት መጻሕፍት ዋቢነት አስረግጠው ደንግገዋል፡፡
የክርስቶስ ጥንተ ዕርገቱ ግንቦት 8 ሐሙስ ቀን በ34 ዓ.ም በዘመነ ማርቆስ ነው፡፡ የዕርገት በዓል አከባበር እስከ 4ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ እንደዛሬው ሐሙስን ሳይጠብቅ በጥንተ ዕርገቱ ግንቦት 8 ቀን ብቻ ይከበር ነበር፡፡ በኋላ ግን ትንሣኤ በዋለ በ40ኛው ቀን ብቻ እንዲከበር ቅዱስ ዲሜጥሮስ በባሕረ ሐሳብ ቀመር ስሌት መሠረት ይከናወን ዘንድ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ተወስኖ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም እየተገለገለችበት ይገኛል።
ጌታችን ከተነሣ በኋላ ሐዋርያትን እያስተማረ ስለሚልክላቸው አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አስፈላጊውን ነገር እያስተካከለ አዕማደ ቤተ ክርስቲያንን በማቆም የሐዲስ ኪዳን ሕግና ሥርዓትን በማጽናት በቀደመው ኪዳን አምሳል ዐርባ ቀን ቆይቷል።
ያስተማራቸው ትምህርትም “ ኪዳን “ይባላል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዕርገቱ የመረጠው ቦታ በዓለም ሳለ ዘወትር ይጎበኘው የነበረውን ቦታ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ከቤተ መቅደስ በመለየት የተመረጠችውን ከተማ እንደተወ ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ በሚገኘው የደብረ ዘይት ተራራ ላይ ዐረፈ:: ክርስቶስም በተራራዋ ላይ ሆኖ ከተማዋን በርኅራኄ ዐይን ተመለከታት፤ በዚህም ተራራ ላይ የነበሩ ደኖችና ሽለቆዎች በክርስቶስ ተቀድሰዋል:: በዚህ ተራራ ጥግ ላይ በምትገኘው በቢታንያ ከተማ ነዋሪ በሆኑት በእነ አልዓዛር ቤት ብዙ ጊዜ ዐርፎ ነበር። በተራራው ግርጌ በምትገኘው የጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ውስጥም በብዙ ዕንባና ጩኸት ጸልዮአል:: የአይሁድ አለቆች ለመስቀል ሞት አሳልፈው ሊሰጡት በክፉ አገዳደልም ሊገደሉት ጌታን የያዙት በዚህ ስፍራ ነበር። በዚህ ዕለት ጌታ ተማሪዎቹን እየመራ ወደ ቢታንያ ወሰዳቸው፤ ደቀ መዛሙርቱ ከጌታቸው ጋር የሚገናኙበት ቀን ይህ ብቻ መሆኑን አላወቁም ነበር። ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ እንዲህ ዘግቦልናል። “ እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጁንም አንሥቶ ባረካቸው ።ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማያ ዐረገ” (ሉቃ ፳፬፥፶)
ቢታንያ ሲደርስ መሄዱን ትቶ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱም ከበውት ቆሙ ጌታም በፍቅር ዐይን አያቸው።
እጆቹንም አንሥቶ ከባረካቸው በኋላ ከመካከላቸው ተነሥቶ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ደቀ መዛሙርቱም ጌታቸውን ከዐይናቸው እስኪሰወርና ዐይኖቻቸው እስኪፈዙ ድረስ በአድናቆትና በፍቅር ወደ ላይ ተመለከቱ፤ ወዲያውኑ የክብር ደመና ከዐይናቸው ሰወረው የርቀት ያይደለ የርሕቀት ነው፤ ይህ ማለት መርቀቅ ሳይሆን መራቅ ነው። ለምሳሌ አውሮፕላን ከምድር ሲነሣ ቀስ እያለ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ አካሉ እያነሰ እያነሰ ይሄዳል በመጨረሻም ወፍ እስኪመስለን ድረስ ለዐይናችን ይርቃል፣ አምላካችንም ልክ እንደዚያ የሐዋርያት ዐይን ማየት እስከቻለበት መጠን ድረስ ከፍ ከፍ እያለ ወደ ሰማይ ዐርጓል:: መላእክትም የደመና ሰረገላም መስለው በተቀበሉት ጊዜ ቀደ መዛሙርቱ ጥዑም የሆነውን የመላእክትን ዝማሬ ሰምተዋል:: መላእክትም ትኩር ብለው የጌታን ዕርገት ለሚመለከቱ ሐዋርያት ‹‹እናንተ የገሊላ ሰዎች ወደ ሰማይ ሲወጣ ያያችሁት ተመልሶ ይመጣል›› የሚል ተስፋ አበሠሩአቸው:: ደቀ መዛሙርቱም ‹‹እነሆ እኔ እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ, ሲል የሰጣቸውን ተስፋ እያስታወሱ ከቢታንያ ተመለሱ::
ሊቁ እንዲህ አለ “እንዘ ይመስሕ ምስሌሆሙ በዓርብዐ ዕለት ነገሮሙ ወይቤሎሙ ሰላም ለክሙ አዓርግ ሰማየ ኀበ አቡየ ወአቡክሙ ወዘንተ ብሂሎ መሠጦ ደመና ወሠወሮ እምአዕይንቲሆሙ:: ሲመሽ በዐርባኛው ቀን ከእነርሱ ጋር አምሽቶ ነገራቸው እንዲህም አላቸው ሰላም ለእናንተ ይሁን ወደ ሰማይ ወደ አባቴ ወደ አባታችሁ ዐርጋለሁ፤ ይህን ብሎ ደመና ነጥቆ ከዐይኖቻቸው ሠወረው›› በማለት ጌታችን ደመና በተባለች በባሕርይ ክብሩ መቀመጡን ሊቁ መስክሯል:: ክርስቶስ ሲያርግ ያዩት ተማሪዎች ልባቸው አብሮ አርጓል:: ወደ ላይም መንፈሳቸው ተነጥቋል፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሀገራቸው በሰማይ ሆኗል፤ በምድር ላይ ሰማያዊ ኑሮን መኖር ጀምረዋል።
መላእክትም ያን ያህል ያደነቁትና እልል ያሉበት ምክንያት፣ ቀድሞ በምድር ዝቅ ብሎ የነበረው የሰው ሥጋ ዛሬ በመለኮት ክብር ወደ ሰማያት ሲያርግ በመመልከታቸው ነው።
ነቢዩ ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙር ፳፫ ፥፯-፰ — “አርኅው ኆኃተ መኳንንት ወይትረኃዋ ኆኃት እለ እም ፍጥረት ወይባእ ንጉሠ ስብሐት” መኳንንት ቅዳሴ መላእክት ኆኃተ ቅዳሴን ክፈቱ ከጥንት ጀምሮ ተከፍተው የማያውቁ ኆኃተ ቅዳሴ ይከፈቱ የክብር ባለቤት ጌታ በየማነ አብ (በአብ ቀኝ) በዘባነ ኪሩብ (በኪሩቤል ጀርባ) ይቀመጥ። በማለት ማር ያዕቆብ ዘሥሩግ መላእክት “ይህ ሥጋ ማን ነው?” ብለው እንደጠየቁ የገለጠውን ቅኔ፣ ይህ ጥቅስ በቀጥታ ያጸናዋል። ሰማያውያን መላእክት የክርስቶስን የሥጋ ዕርገት ሲያዩ በበሮቹ ላይ ያደረጉትን ድንጋጌና መደነቅ ያሳያል።
ቅዱስ ጳውሎስም በ፩ኛ ጢሞቴዎስ ፫፥፲፮ “በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ”በማለት ይገልጻል።
“ለመላእክት የታየ” የሚለው ቃል መላእክት በዕርገቱ ጊዜ አዲሱንና የከበረውን የሰው ልጅ ተፈጥሮ (ሥጋን) አይተው ማድነቃቸውን ያመለክታል።
ቅዱስ ዮሐንስም ይህን ሲያረጋግጥ በዮሐ ፫፥፲፫ — “ከሰማይም ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው”ብሏል።
ክርስቶስ ሥጋን ተዋሕዶ ወደ ምድር መውረዱንና ያንኑ ሥጋ ይዞ ሁሉን ይሞላ ዘንድ መዓርጉን ሳያናውጽ ማረጉን ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ በ ፬፥፱-፲ — “ይህም፦ ዐረገ ማለት ከምድር በታች ወደ አሉት ክፍሎች ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ያው እርሱ ነው” በማለት ገልጧል።
በአጠቃላይ የክርስቶስን ዕርገት በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ማየት ይቻላል።
ሀ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪኩ
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ (ከትንሣኤ ጀምሮ) ለ40 ቀናት ያህል ለደቀ መዛሙርቱ እየተገለጠ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተምሯቸዋል (ሐዋ. 1፥3)።
ቦታው፦ በ40ኛው ቀን ሐዋርያትን ይዟቸው ወደ ደብረ ዘይት (የወይራ ዘይት ተራራ) ወጣ።
ክስተቱ፦ እየባረካቸው ሳለ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውረችው።
* የመላእክት ብሥራት፦ ሐዋርያት ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ ሳለ፥ ነጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት ተገልጠው፦ “ይህ ከእግዚአብሔር ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲወጣ እንዳያችሁት እንዲሁ ይመጣል” ብለው የዳግም ምጽአቱን ነገር አረጋገጡላቸው (ሐዋ. 1፥11)።
ለ) ነገረ መለኮታዊ ትርጓሜው (Theological Meaning)
ዕርገት ዝም ብሎ የአንድ ስፍራ መቀየር ሳይሆን የሰው ልጅ ተፈጥሮ ትልቅ ክብር ያገኘበት ምሥጢር ነው።
የሰው ሥጋ ወደ ሰማይ መግባቱ፦
ክርስቶስ ወደ ሰማይ ያረገው በመለኮቱ ብቻሳይሆን በተዋሐደው ሥጋ ነው።
ይህም ለፈራሽና በስባሽ ለነበረ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ዘላለማዊ የሰማይ ክብርን ሰጥቷል።
በአብ ቀኝ መቀመጥ፦ “በአብ ቀኝ ተቀመጠ” ማለት ክርስቶስ በሥጋውም ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል ሥልጣን፣ ክብርና ጌትነት እንዳለው ያሳያል።
የመንፈስ ቅዱስ መውረድ ቅድመ–ሁኔታ፦ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል 16፥7 ላይ “እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ” እንዳለ፣ ዕርገቱ ለጰራቅሊጦስ (ለመንፈስ ቅዱስ) መውረድ መንገድ የከፈተ ነው።
የቤተክርስቲያን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሳኑ (በተለይም በመዝሙረ ዳዊት ትርጓሜውና በሃይማኖተ አበው ላይ በሰፈረው ትምህርቱ) ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት የክርስቶስ ዕርገት በገዛ አምላካዊ ሥልጣኑና ኃይሉ የተፈጸመ ፍጹም ልዩ ዕርገት መሆኑን በስፋት ያስተምራል።
የዕርገትን በዓል ታላቅነትና ረቂቅ ምሥጢር ሲያብራራም የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች ያነሳል፡
፩. በገዛ ሥልጣኑ ማረጉ (ከሌሎች ዕርገት መለየቱ)
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የጌታችንን ዕርገት ከነቢያት (ከነቢዩ ኤልያስና ከሄኖክ) ዕርገት ጋር በማነጻጸር የክርስቶስን አምላክነት ያስረዳባቸዋል፦
የኤልያስ ዕርገት፦ ነቢዩ ኤልያስ ወደ ሰማይ የወጣው በመላእክት ረዳትነትና በእሳት ሰረገላ ተጭኖ፣ ወደታዘዘበት ቦታ ተወስዶ ነው።
የጌታችን ዕርገት፦ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የመላእክት ፈጣሪ በመሆኑ፣ የማንም ርዳታ ወይም መሪ ሳይፈልግ በገዛ አምላካዊ ሥልጣኑ አርጓል።
መዝሙረኛው ዳዊት “እግዚአብሔር በእልልታ ዐረገ” አለ እንጂ “መላእክት አሳረጉት” አላለም በማለት ይተረጉማል። ወንጌላዊው ሉቃስም “ወደ ሰማይ ሲያርግ አዩ” አለ እንጂ “ተሸከሙት” አላለም፤ ምክንያቱም ያረገበት ሰማይ የገዛ ርስቱና ማደሪያው ነው።
፪. በተዋሐደው ሥጋ ማረጉ
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ክርስቶስ ወደ ሰማይ የወጣው ከእኛ በነሣው (በተዋሐደው) እውነተኛ ሥጋ መሆኑን ያረጋግጣል።
ከስቅለቱና ከትንሣኤው አስቀድሞ ግዙፍ ሥጋን እንደ ተዋሕደ በባሕር ላይ በተአምራት እንደተራመደ ሁሉ፣ ዛሬም ነፋሳትን ከፍሎ በተዋሐደው ሥጋ ወደ ሰማይ ሲያርግ ማንም ሊጠራጠር አይገባውም ይላል።
በዕርገቱ ጊዜ የክርስቶስ ሥጋ አልተለወጠም (መለኮት ሥጋን አልተወውም)፤ በዚያው በተዋሕደው ሥጋ ከፍ ከፍ አለ።
ሐ) ለሰው ልጅ የተሰጠ ታላቅ ክብር
በዚህ ድርሳን ላይ እንደተብራራው፣ የክርስቶስ ዕርገት ለሰው ልጅ የዘላለም ተስፋና ክብርን ያጎናጸፈ ነው፦
ቀድሞ በኃጢአት ምክንያት ከገነት ተባሮ የነበረው የሰው ልጅ ተፈጥሮ (ሥጋ)፣ በክርስቶስ ዕርገት አማካኝነት ከሰማያት በላይ ከፍ ብሎ አርጓል።
የሰው ባሕርይ ከጎሰቆለበት ተነሥቶ ከመላእክትና ከኃይላት ሁሉ በላይ የክብር ባለቤት ሆኗል።
መ) በዕርገቱ ሰይጣን ድል ተነሣ
በዕለተ ዕርገት መላእክት ሁሉ ሲዘምሩ፣ አንዳንዶቹ ከፊቱ ሲቀድሙና ከበውት ሲያርጉ፣ ሰይጣን ሙሉ በሙሉ ድል ስለተሣ ለምእመናን የደስታና የሐሴት ምንጭ ሆነ።
- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ዐረገ?
ዕርገቱ ከምድር መለየት ብቻ ሳይሆን የተከናወኑበት ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡
፩.የመዳን ሥራ ለማጠናቀቅ: ምሥጢረ ሥጋዌን (ሰው መሆኑን) እና የቤዛነት ሥራውን ፈጽሞ ወደ ቀደመ ክብሩ፣ ወደ አባቱ ቀኝ ለመቀመጥ።
፪.መንፈስ ቅዱስን ለመላክ: ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን እንደማይተዋቸው ተስፋ የሰጠ ሲሆን፣ እርሱ ካላረገ በስተቀር አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ወደ ምድር አይመጣም ነበርና።
፫.ትንቢትን ለመፈጸም: «አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ» ተብሎ በመዝሙረ ዳዊት (መዝ. ፵፮፥፭) የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው。
፬.ቦታን ለማዘጋጀት: ምእመናን ከእርሱ ጋር ለሚኖሩበት ክብርና መንግሥት ስፍራን ለማዘጋጀት (ዮሐ. ፲፬፥፪) ዐረገ።
- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገቱን ለምን በተነሣ በ40ኛው ቀን አደረገ?
፩. አዳም በ40ኛ ቀን አግኝቶ ያጣትን ልጅነት እንደተመለሰለት ለማጠየቅ።
፪. አንድም ጌታ በረቀቀ ጥበቡ ተሸብሮ የነበረውን የሐዋርያትን ልቡና እያረጋጋና እያጽናና ለመቆየት።
፫. አንድም ለአይሁድ ምክንያት ለማሳጣት ነው፡፡ ዕርገቱን ከትንሣኤ አስከትሎ ወዲያው ቢያደርገው ዕርገቱን ምትሐት ናት እንዳይሉ በእርግጥ በሞቱ ሞትን ድል አድረጎ የተነሣው ወልደ እግዚአብሔር መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ መሆኑን እንዲረዱ እንዲገነዘቡ የጥርጣሬ መንፈስ በአእምሯቸው እንዳይሰርጽ ።
፬. አንድም ላላመኑት ለእስራኤላውያን (ለአይሁድ) የንስሐ ጊዜ ሲሰጣቸው ነው፡፡ ብዙዎች በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነው የተመለሱ አሉና፡፡
ስለዚህ እኛም ዕርገቱን መሠረተ ሃይማኖታችን በሆነው ጸሎተ ሃይማኖት ”በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ” ብለን ዘወትር እንጸልያለን፤ እንመሰክራለን።
ከሊቁ ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ጋር “አሁንም ከኛ ጋር በዓልን እንዲያደርጉ አባቶችን እንጥራቸው። ከሁሉ በፊት አዳምን እንጥራው፤ እነሆ እግዚአብሔር ከገነት በወጣህ ጊዜ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ያለው ተፈጸመ፤ እግዚአብሔር ሥጋን ከሴት ልጅህ ለበሰ፤ በአባቱም ቀኝ በሰማያት ተቀመጠ፤ ይህን የወደድኸውን አምላክነት ከሴት ልጅህ በተወለደ በመለኮት ሰው መሆን አገኘኸው እንበለው። የሕያዋን እናታቸው ስለሆንሽ ሕይወት የተባልሽ ሔዋን ሆይ በሴትልጅሽ ደስ ትሰኚ ዘንድ ነዪ፤ ሕይወትን አምጥተሻልና፤ በታተመ አፈ ማኅፀኗ የወለደችው እርሱ በረከትን ካገኙ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ቆማ እያየችው ወደ ሰማያዊው አባቱ ዐረገ” (መጽሐፈ ምሥ. ፳፰፥፲፬) እያልን እናክብር እናመስግን;
ከበዓለ ዕርገቱ ረድኤት በረከት ያሳትፈን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
