የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፭

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

፩.፭ ሥርዓተ ተክሊል

ቅድስት ቤተ ክርስቲያ፣ አምነው ለሚመጡ ምእመናን ዂሉ ጸጋ እግዚአብሔርን በነጻ ታድላለች፡፡ ለምእመናን ጸጋ የምታድልባቸው መሣሪያዎችም ‹ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን› ተብለው ይጠራሉ፡፡ እነዚህም፡- ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቍርባን፣ ምሥጢረ ተክሊል፣ ምሥጢረ ክህነት፣ ምሥጢረ ንስሓና ምሥጢረ ቀንዲል ናቸው፡፡  ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መካከል አንዱ የኾነው ምሥጢረ ተክሊል፣ ክብራቸውን ጠብቀው የኖሩ ደናግል ጋብቻ ሲመሠርቱ የሚፈጸም ሥርዓት ነው፡፡ ክብረ ንጽሕናቸውን ጠብቀው የኖሩ ደናግል ከተጫጩና በፈቃዳቸው ለመጋባት ከተስማሙ በኋላ ጋብቻቸው በሥርዓተ ተክሊል ይፈጸማል፡፡

ከቃሉ ትርጓሜ ስንጀምር ‹ተክሊል› ማለት ‹መቀዳጀት› ማለት ነው፡፡ ይህም ሙሽራውና ሙሽራይቱ የጋብቻ ሥርዓታቸው በሚፈጸምላቸው ጊዜ እንደ ንጉሥና ንግሥት በራሳቸው ላይ አክሊል ደፍተው፣ የክብር ካባ ደርበው፣ በነጭ ልብስ ደምቀው መታየታቸውን ያመለክታል፡፡ ይኸውም ለሙሽሮች የሚፈጸመዉን ጸሎትና ቍርባን የሚያሳይ ሲኾን፣ አፈጻጸሙም ሥርዓተ ተክሊል ይባላል፡፡ ሥርዓተ ተክሊል ሲፈጸም ጸሎቱ፣ ልብሱ በጆሮ የሚሰማ፤ በዓይን የሚታይ ቢኾንም በሙሽሮቹና በዕለቱ በተገኙ ምእመናን ላይ የሚያድረው ጸጋና በረከት ግን በዓይን የማያዩት፤ በእጅም የማይዳስሱት፤ በጆሮም የማይሰሙት ረቂቅ ነውና ሥርዓቱ ምሥጢረ ተክሊል ይባላል፡፡

በሥርዓተ ተክሊል ጋብቻቸዉን የሚፈጽሙ ምእመናን እስከ ሞት ድረስ ላይለያዩ በፍጹም ፍቅር ይዋሓዳሉ፡፡ ሽንገላና ግብዝነት በሌለበት እውነተኛ ፍቅር ይጣመራሉ፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈሩና ወላጆቻቸውን የሚያከብሩ ልጆችንም ያፈራሉ፡፡ ጥንዶቹ የመከባበርና የመፈቃቀር፣ የመረዳዳትና የመተማመን፣ የመስማማትና የመተማመን ጸጋ ይታደላሉ፡፡ ፍቅራቸውም ወረተኛ ማለት ከጥቅማ ጥቅም ጋር የተሳሰረ ሳይኾን በመተሳሰብና በመደጋገፍ ላይ የተመሠረተ ይኾናል፡፡ በኑሯቸው የሚያጋጥሙ ፈተናዎችንም በጸሎትና በትዕግሥት የሚወጡበትን ጥበብ ይታደላሉ፡፡ ይህን ጸጋ በመገንዘብ በጋብቻ ሕይወት ለመኖር ዓላማውና ዕቅዱ ያለን ዂሉ በዘፈቀደ መንገድ ከመነዳትና ሰይጣናዊ ባህልን ተከትሎ ከመጥፋት ይልቅ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በመጠበቅና አንድ ለአንድ በመጽናት በዚህ ቅዱስ ሥርዓት ጋብቻችንን መመሥረት ይገባናል፡፡ በዚህም እኛ ተጠቅመን ለመጭው ትውልድም አርአያና ምሳሌ ለመኾን እንችላለን፡፡

ከላይ እንደ ተመለከትነው ምሥጢረ ተክሊል ለደናግል ማለትም ክብረ ንጽሕናቸውን ጠብቀው ለኖሩ ክርስቲያኖች ብቻ የሚፈጸም ሥርዓት ነው፡፡ ሥርዓቱ በዓላማ ጸንተው ክብራቸውን ጠብቀው ለቆዩ ዲያቆናትና ምእመናን ይፈጸማል፡፡ ከዚህ ላይ የዲያቆናት የጋብቻ ሥርዓት ከምእመናን የተለየ መኾኑን ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ምክንያቱም ወደ መዓርገ ቅስና የሚሸጋገሩበት አንዱ መሥፈርት ነውና፡፡ በሕግ የተወሰኑ ማለትም ትዳር የመሠረቱ ዲያቆናት (ቀሳውስት) በሞት ወይም በሌላ አስገዳጅ ምክንያት ከትዳር አጋራቸው ጋር ቢለያዩ ሁለተኛ ሚስት ማግባት አይፈቀድላቸውም፡፡ ካገቡም በመዓርገ ክህነት ማገልገል አይችሉም፡፡ ስለዚህም ዲያቆናት ሚስት በሚያጩበት ጊዜ ከምእመናን በተለየ መልኩ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

በእርግጥ ምእመናን እንዲሁ ሳይጠናኑ ይጋቡ ለማለት ሳይኾን የክህነት ሕይወት ከምእመንነት ሕይወት ስለሚለይ ዲያቆናት አስተውለው ወደ ሕይወቱ እንዲገቡ ለማስታዎስ ነው፡፡ ምእመናን ከትዳር አጋራቸው ጋር በሞት ወይም በሌላ ምክንያት ቢለያዩ ሁለተኛ ማግባት ይፈቀድላቸዋል፤ ዲያቆናት (ቀሳውስት) ግን ከአንድ ጊዜ በላይ ሚስት ማግባት አይችሉም፡፡ በክህነታቸው ለመቀጠል የግድ መመንኰስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕጉን ተላልፈው ወይም ፈቃደ ሥጋቸዉን ማሸነፍ አልችል ብለው ሁለተኛ ጋብቻ ከመሠረቱም ሥልጣነ ክህነታቸው ይያዛል (ይሰረዛል)፡፡ ከቀሳውስት (ዲያቆናት) በተለየ ሥርዓት ምእመናን ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ቢፋቱ የተለያዩበት ምክንያት ተጣርቶ ሁለተኛ ጋብቻ መመሥረት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሁለተኛ ጋብቻ በቍርባን እንጂ በተክሊል አይፈጸምም፡፡ ምክንያቱም ምሥጢረ ተክሊል ተጋቢዎቹ (ሁለቱም) ድንግልናቸውን አክብረው ከቆዩ ብቻ የሚፈጸምና የማይደገም ሥርዓት ነውና፡፡

፩.፮ ሕይወት በጋብቻ ወቅት

የጋብቻ ሕይወት፣ በእግዚአብሔር ፈቃድና በሰዎች ምርጫ የሚመሠረት የአንድነት ኑሮ ነው፡፡ በጋብቻ ከተዋሐድንበት ጊዜ ጀምሮ ያለው ወቅት ከነጠላነት ወደ ጥንድነት፣ ከብቸኝነት ወደ ሁለትነት ብሎም ወደ ሦስትነት (ልጅ ሲመጣ) የምንሸጋገርበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ከቀድሞው በበለጠ መልኩ በጾም በጸሎት መትጋት፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡ ይህ ወቅት ለራሳችን ብቻ ሳይኾን ለትዳር አጋራችን ብሎም ለልጆቻችን ሕይወት የምናስብበት የሓላፊነት ጊዜ ነውና፡፡ በመኾኑም ከቤት ጀምሮ እስከ ጎረቤት ያለን ማኅበራዊ ግንኙነት የጠነከረ፣ ፍቅራችንም የሠመረ መኾን ይገባዋል፡፡ ጋብቻ ከመሠረትን በኋላ ከትዳር አጋራችን ጋር ተቻችለን ሳይኾን ተስማምተን በፍቅርና በሰላም መኖር ይጠበቅብናል፡፡

በእርግጥ በኑሯችን ላይ ልዩ ልዩ ፈተናዎች ሊመጡብን ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ደዌ ሥጋ፣ ስንፈተ ሩካቤ ወይም በተፈጥሮ ሩካቤ ማድረግ አለመቻል፣ ሊፈወስ የማይችል በሽታ (ለምሳሌ ኤድስ)፣ የአባላዘር በሽታዎችና እነዚህን የመሰሉ ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር በአሉባልታ ወይም በሰዎች ጣልቃ ገብነት ለመግባባትና በአንድነት ለመቀጠል እንቅፋት የሚኾኑ ችግሮች ሊገጥሙን ይችላሉ፡፡ ለዚህም መፍትሔው ቢቻል ዂሉን ነገር ከመጋባት በፊት መወያየትና ለችግሮች መፍትሔ መስጠት ነው፡፡ የጤና እክሉ ወይም አለመግባባቱ ከጋብቻ በኋላ የመጣ ከኾነ ሕመሙን በጠበልና በሕክምና አለመግባባቱን ደግሞ በመወያየት፣ በጾምና በጸሎት መፍታት ይገባል፡፡ ከዚህ በተረፈ በየሰበቡ መጨቃጨቅም መናተረክም አስፈላጊ አይደለም፡፡

የባልና ሚስት ሕይወታቸው በአንድ አሳብ፣ በአንድ ልብ፣ በአንድ ምክርና የጋራ ፈቃድ ሊመራ ይገባዋል፡፡ እንደዚሁም በመፈቃቀር፣ በመከባበር፣ በመተሳሰብ፣ በመተዛዘንና በመደጋገፍ ሊኖሩ ያስፈልጋል፡፡ ልጆችን በክብካቤና በመንፈሳዊ ሥርዓት ማሳደግም ሌላው የባልና ሚስት ሓላፊነት ነው፡፡ በአጠቃላይ ባል ለሚስቱ፤ ሚስትም ለባሏ መታዘዝ የሕይወታቸው መርሕ መኾን አለበት፡፡ ከዚህም ባሻገር በቤት ውስጥም ኾነ ከቤት ውጪ ክርስቲያናዊ ምግባርን ገንዘብ በማድረግ ለልጆቻቸው መልካም አርአያ ሊኾኑ ይገባቸዋል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የባልና የሚስት ሕይወት እንዴት መቀጠል እንዳለበት ሲያስረዳ የሚከተለውን ትእዛዝ ከምሳሌያዊ ማብራሪያ ጋር ሰጥቷል፤ “ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ኾነ ባልም የሚስት ራስ ነውና፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በዂሉ ለባሎቻቸው ይገዙ፡፡ ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፡፡ ባሎች እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል፤ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፤” (ኤፌ. ፭፥፳፪-፴፫)፡፡

ከኃይለ ቃሉ እንደምንረዳው ባልና ሚስት ‹‹በአንተ ይብስ፤ በአንቺ ይብስ›› ተባብለው የጋራ ችግሮቻቸውን በጋራ በመፍታት፣ የሕይወት ምሥጢራቸውን በመጠበቅ በመንፈሳዊ ፍቅር መኖር ይገባቸዋል፡፡ በባልና በሚስት መካከል አንዱን የበላይ፣ ሌላውን የበታች የሚያደርግ ልዩነት ሊኖር አይገባም፡፡ ባል ስለ ሚስቱ፣ ሚስትም ስለ ባሏ ሰውነታቸዉን ለመከራ አሳልፈው እስከ መስጠት ድረስ በፍጹም ፍቅር መዋደድ ይገባቸዋል፡፡ ሁለቱም ከእናትና አባታቸው ተለይተው በአንድነት መኖር ጀምረዋልና (ዕዝራ ፬፥፳-፳፭)፡፡

ይቆየን

የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፬

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.

ለ. መባዛትና ዘርን መተካት

ሁለተኛው የጋብቻ ዓላማ ለመባዛትና ዘርን ለመተካት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አዳምና ሔዋንን ብዙ፤ ተባዙ፡፡ ምድርንም ሙሉአት፤ ግዙአትም” በማለት ዘራቸውን እየተኩ በምድር ይበዙ ዘንድ፣ ፍጥረታትንም ይገዙ ዘንድ አዝዟቸዋል (ዘፍ. ፩፥፳፪-፳፰፤ ፱፥፯)፡፡ በዚህ ሕግ መሠረት የሰው ልጅ መሰሉን እየተካና እየተባዛ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ትውልድ ይቀጥላል፡፡ ይህ ትእዛዝ ለእንስሳትም የተሰጠ ሕግ ቢኾንም የሰው ልጅ ግን ከፍጥረት ዂሉ የከበረ ነውና እንደ እንስሳት በዘፈቀደ ሳይኾን በሕግ ተወስኖ ይባዛና ዘሩን ይተካ ዘንድ የጋብቻ ሕግ ተሠርቶለታል፡፡ ከእንደዚህ ዓይነቱ ክቡር ጋብቻ የሚወለዱ ልጆችም የተባረኩና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ይኾናሉ፡፡ የቅኖች ትውልድ ትባረካለች” በማለት ቅዱስ ዳዊት እንደ ተናገረው (መዝ. ፻፲፪፥፪)፡፡

ሐ. ከዝሙት መጠበቅ

ሦስተኛው የጋብቻ ዓላማ ከዝሙት ፆር ለመጠበቅ ማለትም ፍትወተ ሥጋን ለመከላከል ወይም ለመቋቋም ነው፡፡ እንደሚታወቀው የሰው ልጆች መልአካዊና እንስሳዊ ባሕርያት አሉን፡፡ በመልአካዊ ባሕርያችን እንደ መላእክት ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያልን እግዚአብሔርን ማመስገን፣ ጾም፣ ጸሎት ይስማማናል፡፡ በእንስሳዊ ባሕርያችን ደግሞ መራብ፣ መጠማት፣ ፍትወተ ሥጋ ይሠለጥንብናል፡፡ የጋብቻ ሕይወት የዝሙትን ፆር ለማሸነፍ ከእግዚአብሔር የተሰጠን መከላከያ መንገድ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ጋብቻ የዝሙትን ጠንቅ ለመከላከል እንደሚያስችል ሲያስረዳ ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው፤ ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት” በማለት አስተምሯል (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፪-፱)፡፡ ፍትሐ ነገሥትም ሕግ ወደማፍረስ የሚያደርስ የፈቲው ፆር በብዙ ሰዎች ቢጸና ጋብቻ መፈጸም እንዲገባ ይናገራል (አንቀጽ ፳፬፣ ክፍል ፩)፡፡

በአጠቃላይ ጋብቻ፣ እንከብርበትና በጋራ እንኖርበት ዘንድ፤ እንደዚሁም ራሳችንን ከኃጢአት እንጠብቅበት ዘንድ እግዚአብሔር ያዘጋጀልን መንፈሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ ሦስቱ የጋብቻ ዓላማዎችም ከላይ የተጠቀሱት ናቸው፡፡ የጋብቻ ዓላማዎች ጠቢብ፣ ልዑል ከሚኾን ከፈጣሪ የተሰጡ ጸጋዎች፤ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅ፣ ከያዕቆብ የተገኙ ግብራት ናቸው፡፡ ከእነዚህ የተለየ የጋብቻ ዓላማ ሊኖር አይችልም፡፡ ወኢረከብነ አሐደ እምእሉ ዘይፈቅዳ ለሕገ አውስቦ ዘእንበለ ዘርእ ባሕቲቱ፤ ከነቢያት ከሐዋርያት አንዱ ስንኳ የግቢን ሥርዓት ‹ለዝሙት ትኹን› ብሎ ያስተማረ አላገኘንም፡፡ ልጅ ለመውለድ ብቻ ነው እንጂ” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ፍት. ነገ. አን. ፳፬፣ ቍ. ፷)፡፡

ከዚህ ላይ የጋብቻ አስፈላጊነቱ በሦስት ዓላማዎች ብቻ የተወሰነ አለመኾኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም በሦስቱ ዓላማዎች ውስጥ የሚካተቱ ብዙ ቁም ነገሮች ይኖራሉና፡፡ ለምሳሌ መረዳዳት በስሜት፣ በአሳብ፣ በገንዘብ፣ በመሳሰሉትና በሌሎችም ማኅበራዊ ዘርፎች መተጋገዝን ያጠቃልላል፡፡ ዘርን በመተካት ውስጥም ወልዶ መሳም፣ ዓይንን በዓይን ማየት፣ በወሊድ ጊዜ የሚደረግ ክብካቤና ሥርዓት ያለው የልጅ አስተዳደግ ተግባራት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ስለዚህ ጋብቻ ዓላማው በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ቢጠቀስም በእነዚህ ዓላማዎች ሥር ግን ሌሎች ቁም ነገሮችም ይካተታሉ፡፡

፩.፫ ሕይወት ከጋብቻ በፊት

የጋብቻ ሕይወት በዓላማ የተዘጋጀልን ሥርዓት ይኹን እንጂ ሰውነታቸውን መቈጣጠር የሚችሉ ቢኖሩ እንዲያገቡ አይገደዱም፡፡ ማግባትም አለማግትባም አንድም በእግዚአብሔር ፈቃድ አንድ በግል ፍላጎትና ስሜት ይፈጸማልና፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፤ አንዱ እንደዚህ፣ ሁለተኛውም እንደዚያ … ዂሉ እንደ ተጠራ እንዲሁ ይኑር” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፯-፳)፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው የፈቲውን ፆር ማሸነፍ ከቻለ እንዲያገባ አይገደድም ማለት ነው፡፡ ወእመሰ ኮንከ ዘኢትፈቅድ ብእሲተ ኢትኅሥሥ ኪያሃ፤ ሚስት ማግባት የማትሻ ከሆነ ሚስት ላግባ አትበል” እንዲል ፍትሐ ነገሥት፡፡ ሥርዓቱ ለሴቶችም ተመሳሳይ ነው፡፡

ጋብቻ የሚከልከልባቸው ኹኔታዎችም እንዳሉ ማወቅም ይገባናል፡፡ ለምሳሌ ሩካቤ ለመፈጸም የማያስችል (የሚከለክል) ደዌ ወይም ተፈጥሯዊ ችግር፣ ምንኵስና (ለመመንኰስ ቃል መግባት) ተተቃሾች ናቸው፡፡ ከተጋቡ በኋላ ጥላቻ እንዳይመጣ እንደዚህ ዓይነት የጤና ክሎችን አስቀድሞ ማወቅና መፍትሔ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ዂሉ ጋርም በእምነት መለያየት፣ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ ዝምድናም ጋብቻን የሚከለክሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ለመጋባት ከመስማማታችን በፊት በእምነት አንድ መኾናችንን፣ በዕድሜ መመጣጠናችንንና መዋደዳችንን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ የሁለቱ ተጋቢዎች ስምምነት፣ የቤተሰቦቻቸው ወይም የአሳዳጊዎቻቸው ፈቃድ ለጋብቻ ሕይወት አንደኛው ቅድመ ኹኔታ ነው፡፡ እንደዚሁም የሚያምኑ ከማያምኑ ጋር መጋባት የለባቸውም፡፡ ቢዋደዱም እንኳን ከመጋባት በፊት ያላመነውን (ችውን) ወደ ክርስትና ሃይማኖት መመለስና ማስጠመቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ለጋብቻ የተዘጋጁ ጥንዶች ዕድሜም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ይህም በልጅነት መንፈስ ቃል ከተጋቡ በኋላ ቃላቸውን እንዳያፈርሱ ሲባል ነው፡፡ ቃላቸውን ቢጠብቁም እንኳን ልጅ ለማሳደግና ቤተሰብን ለመምራት ሊከብዳቸው ይችላልና ነው፡፡

በዚህም ምክንያት ተገቢ ወዳልኾነ እርምጃ ማለትም ፅንስን ወደማስወረድ ዓይነት ተግባር ሊገቡ ይችላሉና የሚጋቡ ጥንዶች ለአካለ መጠን የደረሱ መኾን ይገባቸዋል፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለወደፊቱ በትዳር ተወስነን ለመኖር የምናስብ ከኾነም ጊዜው ደርሶ አጋራችንን እስክናገኝ ድረስ በትሕትና፣ በንጽሕናና በክርስቲያናዊ ሥነ ምጋባር ጸንተን ልንኖር ይገባናል፡፡ ይህንን ለማድረግም ኾነ ዕቅዳችንን ለማሳካት እንዲቻለን ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መጾም፣ መጸለይ፣ መማር፣ ቅዳሴ ማስቀደስና ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን መቀበል ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ውጪ ትዳር የመመሥረት ፍላጎትና አቅም ኖሯቸው ዕድሜያቸው ከፍ በማለቱ ምክንያት አፍረው ወይም ‹‹ሰው ምን ይለኝ›› በሚል ሥጋት ተይዘው ትዳር ያልመሠረቱ ሰዎች ካሉ በጋብቻ የመኖር ዕቅድ እስካላቸው ድረስ በመዘግየታቸው ምክንያት ሳይሳቀቁ ትዳር ሊመሠርቱ ይገባል፡፡ “‹ሲያረጁ አምባር ይዋጁ› ይሉኛል” ብሎ በመሳቀቅ ጋብቻን መሸሸ ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ያስተምራል፤ ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር የወደደውን ያድርግ፤ ቢያገባም ኀጢአት የለበትም፤ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል” (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፴፮)፡፡

፩.፬ የእጮኝነት ጊዜ

ጋብቻ ለመመሥረትና የትዳር አጋር ለመምረጥ የሚያስችል ዕድሜ ላይ የደረሱ ሰዎች ለጋብቻ ከተፈቃቀዱና ከተስማሙ በኋላ በቅድሚያ ለመምህረ ንስሓቸው ይነግራሉ፡፡ ከዚያም ለወላጆቻቸው (ለአሳዳጊዎቻቸው) ያሳውቃሉ፡፡ ጋብቻ የሚመሠረተው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ግንኙታቸው ወደ ኀጢአት እንዳይወስዳቸውና ከመጋባታቸው በፊት በሩካቤ ሥጋ እንዳይወድቁ መጠንቀቅ ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም እጮኛ መምረጥ ማለት መጋባት ማለት አይደለምና፡፡ የመተጫጨት ባህልና ሥርዓትን መጠበቅም ይገባል፡፡ ይህም ፈቃድና ስምምነትን፣ ዕድሜን፣ ዝምድናን፣ እንደዚሁም ሃይማኖትን ያገናዘበ መኾን ይኖርበታል፡፡

በመተጫጨት ጊዜ ሊታሰብበት የሚገባው ሌላኛው ጉዳይ የሚጋቡት ጥንዶች የዕድሜ ደረጃ ነው፡፡ የመተጫጫና የመጋቢያ ዕድሜም የወንዶች ከሃያ ወይም ከሃያ አምስት፤ የሴቶች ደግሞ ከዐሥራ አምስት ወይም ከዐሥራ ስምንት ዓመት በላይ ሊኾን እንደሚገባው በሕገ ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል (ፍት. ነገ. አን. ፳፬፣ ምዕ. ፫፣ ክፍ. ፪)፡፡ ተጋቢዎቹ በዕድሜ ብዙ የተራራቁ ከኾነ በጋብቻቸው ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተጋቢዎች መካከል ምንም ዓይነት ዝምድና እንዳይኖርም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሥጋዊና መንፈሳዊ ዝምድናን ለማስጠበቅ ሲባል እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ መጋባት አይፈቀድም፡፡

የእጮኝነት ጊዜ፣ ጋብቻ ከምንመሠረትበት ጊዜ በፊት ማለት ከቤተሰብ ወይም ከአሳዳጊ ጋር ከምናሳልፈው ጊዜ ጀምሮ ለዓቅመ አዳም (ሔዋን) እስከምንደርስበት ያለውን የወጣትነት የዕድሜ ክልል ያጠቃልላል፡፡ ከነጠላነት እስከ እጮኝነት ያለውን ይህን ወቅት ሕገ እግዚአብሔርንና ክብራችንን በመጠበቅ በንጽሕና ማሳለፍ ይኖርብናል፡፡ እንዲህ ካደረግን የወደፊቱ የጋብቻ ሕይወታችን የሠመረ፣ ፍቅር የሞላበትና በረከት የበዛበት ይኾንልናል፡፡ ይህን የዕድሜ ክልል ክርስቲያናዊ ባልኾነ፣ ሥርዓት በሌለው መንገድ ካሳለፍነው ግን ቀጣዩ ሕይወታችንም ፈተና የበዛበት ሊኾን ይችላል፡፡ ስለዚህ በኋላ እንዳንሰናከል አስቀድመን በጠንካራ መሠረት ላይ ልንታነጽ ይገባናል፡፡

ይቆየን

የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፫

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፫ ቀን ፳፻፲ .

፩.፩ የጋብቻ ክቡርነት እና ምሥጢር

እግዚአብሔር አምላካችን በብሉይ ኪዳን የአዳምንና የሔዋንን፤ የሌሎችንም አባቶች እና እናቶች ጋብቻ ባርኳል፡፡ በሐዲስ ኪዳንም በዶኪማስ ቤት ተገኝቶ፣ ውኃውን ወደ ወይን ቀይሮ ቤቱን በበረከት ሞልቶለታል፡፡ ይህም ጋብቻ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደና የከበረ ምሥጢር መኾኑን አመላካች ነው፡፡ ምክንያቱም አምላካችን ያልፈቀደዉን ሕይወት ባርኮ አይሰጥምና ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ባልና ሚስት አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” በማለት ማስተማሩም ጋብቻ የአንድነት ውጤትና ታላቅ ሥርዓት መኾኑን ያስረዳል (ማቴ. ፲፱፥፮፤ ዮሐ. ፪፥፩-፲፩)፡፡

በዚህም ሥርዓት በብሉይ ኪዳን፡- አዳምና ሔዋን፣ አብርሃምና ሣራ፣ ይስሐቅና ርብቃ፣ ያዕቆብና ራሔልን የመሰሉ፤ በሐዲስ ኪዳን፡- ኢያቄምና ሐና (የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆች)፣ ጸጋ ዘአብና እግዚእ ኀረያ (የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ወላ ጆች)፣ ኖኅና ታቦትን (የቅዱስ መርቆሬዎስ ወላጆች) የመሰሉ ደጋግ አባቶች ልጆችን አፍርተውበታል፤ ተጠቅመውበታልም፡፡ ለዚህም ነው “ጋብቻ በዂሉ ዘንድ ክቡር ነው፤ ለመኝታቸውም ርኵሰት የለበትም” ተብሎ የተነገረው (ዕብ. ፲፫፥፬)፡፡ በሥርዓት ከኖሩበት የሚያስከብር ሕይወት ነውና፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ “… ማርያም ድንግል ከብካብ ንጹሕ ወመርዓ ቅዱስ፤ ድንግል ማርያም ሙሽራዋ ንጹሕ የኾነ የሰርግ ቤት ናት፤” በማለት እመቤታችንን አመስግኗታል፡፡ ሊቁ እመቤታችንን በሰርግ ቤት መመሰሉ ጋብቻ ንጹሕ ሥርዓት መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህም ምሥጢራዊ ትርጕም አለው፤ በሰርግ ቤት ደስታ፣ ጨዋታ፣ መብልና መጠጥ፣ የሙሽራውና የሙሽሪት አንድነት ይከናወንበታል፤ የሙሽራውና የሙሽሪት ዘመዶች አንድ ይኾኑበታል፡፡ መብልና መጠጡ የትምህርተ ወንጌል (የሥጋ ወደሙ)፤ ደስታና ጨዋታው የተአምራት፤ የሙሽራውና የሙሽሪት ተዋሕዶ የትስብእትና የመለኮት አንድነት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በሰርግ የሙሽራውና የሙሽሪት ዘመዶች አንድ እንደሚኾኑባት ዂሉ፣ በድንግል ማርያምም ሰውና መላእክት፣ ሰውና እግዚአብሔር፣ ነፍስና ሥጋ፣ ሕዝብና አሕዛብ አንድ ኾነውባታል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ‹‹ሙሽራዋ ንጹሕ የሚኾን የሰርግ ቤት›› ይላታል (የረቡዕ ውዳሴ ማርያም፣ አንድምታ ትርጓሜ)፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም ዳግመኛም “ከመ ከብካብ ዘአልቦ ጥልቀት መንፈስ ቅዱስ ኀደረ ላዕሌኪ፤ እንደ ሰርግ ቤት አደፍ፣ ጉድፍ የሌለብሽ ኾነሽ ቢያገኝሽ መንፈስ ቅዱስ አድሮብሻል” በማለት እመቤታችንን ጋብቻ በሚፈጸምበት ንጹሕ የሰርግ ቤት መስሎ አመስግኗታል፡፡ ይህም በተመሳሳይ መልኩ የጋብቻን ክቡርነት የሚያመለክት ነው (ውዳሴ ዘቀዳሚት)፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ” በማለት ጋብቻ የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ተዋሕዶ ምሳሌ መኾኑን ያመሠጠረልን (ኤፌ. ፭፥፴፪)፡፡ በአጠቃላይ ጋብቻ፣ ይከብርበትና በጋራ ይኖርበት ዘንድ እንደዚሁም ራሱን ከኃጢአት ይጠብቅበት ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጅ ያዘጋጀው መንፈሳዊ ሥርዓት ነው፡፡

፩.፪ የጋብቻ አስፈላጊነትና ዓላማዎቹ

ሰው ኾነን የመፈጠራችን ዓላማው የእግዚአብሔርን ስም ለመቀደስ (ለማመስገን)፣ ክብሩን (መንግሥቱን) ለመውረስ እንደ ኾነው ዂሉ ጋብቻንም አምላካችን በዓላማ አዘጋጅቶልናል፡፡ የጋብቻ አስፈላጊነቱ ወይም ዓላማው እጅግ የጎላ ነው፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን እንደ ተገለጸው ጋብቻን የሚያሹ (የሚያስፈልጉ) ፈቃዳት ሦስት ናቸው፤ እሊህም ጠቢብ፣ ልዑል ከኾነው ከእግዚአብሔር የተሰጡ፤ እንደዚሁም ከአብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ የተወረሱ ግብራት ናቸው፡፡ ከሦስቱ ዓላማዎች የተለየ የጋብቻ ጥቅም (አስፈላጊነት) አይኖርም፡፡ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን “ከነቢያት ከሐዋርያት አንዱ ስንኳ ‹ጋብቻ ለዝሙት ትኹን› ብሎ ያስተማረ የለም፡፡ ልጅ ለመውለድ ብቻ ነው እንጂ” በማለት የጋብቻን ዓላማዎች ያስረዳሉ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፳፬፣ ቍ. ፷)፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት በማድረግ ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው ጋብቻ የሚከተሉት ሦስት መሠረታውያን ዓላማዎች አሉት፤

ሀ. መረዳዳት

ከጋብቻ ዓላማዎች አንደኛው እርስበርስ መረዳዳት ነው፡፡ መረዳዳት ማለት መተጋገዝ፣ መተሳሰብ፣ መደጋገፍ፣ መጠያየቅ፣ ለራሳችን ሊደረግልን የምንፈልገውን መልካም ነገር ዂሉ ለሌሎችም ማድረግ ማለት ነው፡፡ ጋብቻ ሁለት ጥንዶች በአንድነት የሚኖሩበትና እርስበርስ የሚረዳዱበት ሕይወት ነው፡፡ በጋብቻ ውስጥ የሚደረግ መረዳዳት በማኅ በራዊ፣ በሥነ ልቡና፣ በምጣኔ ሀብትና በቤተሰብ አስተዳደር መተጋገዝን፣ መተሳሰብን፣ በአንተ ይብስ፤ በአንቺ ይብስ መባባልን እንደዚሁም በስሜት መተዋወቅን ያጠቃልላል፡፡

በጋብቻ ሊኖር ስለሚገባው የመረዳዳት ዓላማ መነሻው “ሰው ብቻውን ይኾን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት” የሚለው አምላካዊ ቃል ነው (ዘፍ. ፪፥፲፰)፡፡ ስለዚህም በተቻላቸው አቅም ዂሉ ባል ለሚስቱ የሚገባትን፣ ሚስትም ለባሏ የሚገባውን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጋብቻ የአንድነት ሕይወት በመኾኑ ሚስት በራሷ፣ ባልም በራሱ ሥልጣን እንደሌላቸው ቅዱስ ጳውሎስ ይናገራል፡፡ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ማዘዝ እንደሚችሉም ያስረዳል፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም አንድ አካል ናቸውና (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፴፬)፡፡ በመኾኑም ባልና ሚስት እንደ ዓይን ብሌን ሊጠባበቁ፣ ሊከባበሩና አንዳቸው ለአንዳቸው ሊታዘዙ ይገባቸዋል፡፡ መረዳዳት ማለት አንዱ የሌላውን ስሜት መጠበቅ ነውና፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም በጋብቻ ሕይወት ውስጥ መኖር ስለሚገባው የመደጋገፍና የመረዳዳት ዓላማ ሲያስረዳ “እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ኾኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው፡፡ በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፤ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፤ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ኹኑ፡፡ ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፡፡ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታች ኋልና” ሲል በአጽንዖት አስተምሯል (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፩-፱)፡፡

በዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ ‹‹ደካማ ፍጥረት ስለ ኾኑ›› የሚለው ሐረግ ሴቶች በዕውቀት ወይም በዓቅም ዝቅተኛ ናቸው ለማለት አይደለም፡፡ በትዳር አጋሮቻቸው በሚደርስባቸው ጫና፣ ከውጪ በሚገጥማቸው ልዩ ልዩ ፈተና በቀላሉ የሚሰናከሉ መኾናቸዉን የመሚጠቁም ነው እንጂ፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚኾነን የሔዋን ጠባይዕ ነው፡፡ አዳምና ሔዋን በገነት በነበሩበት ወቅት የሰይጣን የማሰሳሳት ጥረት የተሳካው በሔዋን የመታለል ጠባይዕ ነበር፡፡ የሔዋን ውዳሴ ከንቱ (የማይጠቅም ምስጋና) የመውደድና በቀላሉ የመሸነፍ ስሜት አሁንም ድረስ በሴቶች ላይ ይስተዋላል፡፡ ሐዋርያው ድክመት ያለውም ይህንን ዓይነት የሴቶችን ጠባይዕ ነው እንጂ በተፈጥሮማ ሴቶችም በሥላሴ አርአያና አምሳል ነው የተፈጠሩት፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ በባልና በሚስት መካከል ሊኖር ስለሚገባው መልካም ግንኙነትና መተሳሰብ ሲያስረዳ ሣራ፣ አብርሃምን ትታዘዘው፤ ‹‹ጌታዬ›› ትለው እንደ ነበረው፤ በበጐ ሥራ ፍጹማን የኾኑ ልጆችን ይወልዱ ዘንድ ወንዶች ሚስቶቻቸውን እንዲያከብሩ ይመክራል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም በዲድስቅልያ “አእምራ አንስት ከመ ብእሲት እንተ ታፈቅር ምታ ትረክብ ክብረ በኀበ እግዚአብሔር፤ ሴቶች ሆይ፥ ባሏን የምትወድ ሚስት በእግዚአብሔር ዘንድ ክብርን እንደምታገኝ ዕወቁ” በማለት በባልና በሚስት መካከል ሊኖር ስለሚገባው መከባበርና መተጋገዝ፤ እንደዚሁም መከባበር ስለሚያስገኘው ጸጋ አስተምረዋል (ዲድስቅልያ፣ አን. ፫፣ ቍ. ፳፭)፡፡ በተአምረ ማርያምም “ከእናንተ ወገን ሚስት ያለችው ሰው ቢኖር እንደ ዓይን ብሌን ይጠብቃት፤ እግዚአብሔር ያስጠበቀው አደራ ናትና” ተብሎ ተጽፏል (፲፩ኛ ተአምር፣  ቍ. ፳፮)፡፡

በጋብቻ ሕይወት ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው መረዳዳት ቅዱሳት መጻሕፍት የሚናገሩትን ኃይለ ቃል ጠቅለል ስናደርገው ባልና ሚስት በመካከላቸው የራስ ወዳድነትና የትዕቢት መንፈስን በማስወገድ እንደ ዓይን ብሌን ሊጠባበቁ፣ ሊከባበሩና እርስበርስ ሊከባበሩ እንደሚገባቸው እንገነዘባለን፡፡ በየትኛውም ዓይነት ሕይወት ውስጥ መረዳዳት መኖሩ ተገቢ ነው፡፡ በጋብቻ ሕይወት ግን መረዳዳት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ጋብቻ ሁለት ሰዎች በአንድ ጣሪያ ሥር በአንድነት የሚኖሩበት ሕይወት ከመኾኑም ባሻገር ኑሮንም ስሜትንም በጋራ የሚመሩበት የአንድነት ተቋም ነውና፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የጋብቻን ሕይወት፣ ‹‹በቤት ውስጥ ያለች ትንሿ ቤተ ክርስቲያን›› በማለት የሚገልጸው፡፡

ይቆየን

የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፪

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ቅዱስ ጳውሎስ ጋብቻ የፈቃድ ሕግ መኾኑን ሲያስተምር ራሳቸውን መጠበቅ ለሚችሉ አለማግባት ቢቻልም ሰውነትን ለመጠበቅ ከአልተቻለ ግን ማግባት እንደሚሻል አስገንዝቧል፡፡ ሐዋርያው እንዳስተማረው ከሴት ጋር አለመገናኘት (ጋብቻ አለመምሥረት) ለሰው መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ወንድ አንድ ሚስት ሊኖረው፤ ለእያንዳንዲቱ ሴት ደግሞ አንድ ባል ሊኖራት ይገባል፡፡ ነገር ግን ሰው ዂሉ እግዚአብሔር እንዳደለው (እንደ ፈቀደለት) ይኑር፡፡

ላላገቡና ለመበለቶች ደግሞ የሚከተለዉን ትምህርት ሰጥቷል፤ “ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ፤ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ፤ በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና፡፡” ይኸውም “ሚስት የሌላቸው ወንዶች፣ ባል የሌላቸው ሴቶች እንደ እኔ ከሴት (ከወንድ) ርቆ፣ ንጽሕ ጠብቆ መኖር ይሻላቸዋል፡፡ ንጽሕ ጠብቆ፣ ከሴት (ከወንድ) ርቆ መኖር ባይቻላቸው አግብተው ይኑሩ፡፡ አንዲት ሴት (ባል) አግብታችሁ፣ በሕግ ተወስናችሁ ኑሩ ማለቴ ንጽሕ ጠብቆ፣ ከሴት ርቆ መኖር ለማይቻላቸው ሰዎች ነው፡፡ ‹እንደ እኔ ንጽሕ ጠብቃችሁ፣ ከሴት ርቃችሁ ኑሩ› ብዬ አላስገድዳችሁም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር እንዳደላችሁ ኑሩ፤” ማለቱ ነው (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፩-፱፣ አንድምታ ትርጓሜ)፡፡

ሐዋርያው፣ ቈነጃጅት ባል አግብተው፣ ልጆች ወልደው፣ ቤት፣ ንብረት ይዘው ቢኖሩ መልካም መኾኑን ጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን የማግባት ግዴታ እንደደሌለበትና የወደደውን ማድረግ እንደ ተፈቀደለት ማለትም ድንግልናውን ጠብቆ መኖር ከፈለገ በምንኵስና፤ ማግባት ከፈለገም በጋብቻ ሕይወት ጸንቶ መኖር እንደሚችል አስረድቷል፡፡ ትምህርቱም ወንዶችን ብቻ ሳይኾን ሴቶችንም የሚመለከት ነው (፩ኛ ቆሮ. ፯፥፴፯-፴፰)፡፡ ይህም ጋብቻ የፈቃድ እንጂ የግዴታ ሕግ አለመኾኑን ያመለክታል፡፡

ከትምህርቱ እንደምንረዳው ጋብቻ በሰው ፍላጎት ብቻ ሳይኾን በእግዚአሔር ፈቃድና ዕቅድ የተመሠረተ መንፈሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ ሕይወቱ ከምድራዊ አንድነት ባሻገር ለምሥጢረ ተዋሕዶም ምሳሌ ኾኖ ይጠቀሳል፡፡ “ዐቢይ ውእቱ ዝ ነገር አንሰ እብሎ ላዕለ ክርስቶስ ወላዕለ ቤተ ክርስቲያኑ፤ ይህም ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይህንኑ ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እናገረዋለሁ፤” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (ኤፌ. ፭፥፴፪)፡፡

የጋብቻ ክቡርነትና ምሥጢር ይህ ኾኖ ሳለ አንዳንዶቻችን ለጋብቻ የምንሰጠው ትርጕም ግን ዝቅ ያለ ይመስላል፡፡ በስውር ከጋብቻ ውጪ ፈቃዳቸዉን የሚፈጽሙ ምእመናን መኖራቸውም ከዚህ አመለካከት የመነጨ ነው፡፡ ከዚህ የተሳሳተ ግንዛቤ በመውጣትና ንጽሕናን በመጠበቅ አንድም ጋብቻ መመሥረት፤ ካለዚያም ራስን ጠብቆ በድንግልና ጸንቶ መኖር ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ ስለ ጋብቻ ሕይወት ሲነገር ከጋብቻ ዓላማዎች አንደኛው ከዝሙት ጠንቅ ለመሸሽ ነው፡፡ ይህም በሕጋዊ ሥርዓት ሩካቤ ሥጋን ለመፈጸም ያስችላል፡፡

ሩካቤ ሥጋ የተለየ ዓላማና ምሥጢር አለው፡፡ አፈጻጸሙም በሥርዓተ ተክሊል ወይም በሥርዓተ ቍርባን ይጸናል፡፡ በሕጋዊ ጋብቻ ተወስነን ካልኾነ በቀር ከጋብቻ በፊትም ኾነ በኋላ ካገኘነው ዂሉ ጋር ፆታዊ ግንኙነት መፈጸም ክቡራን ኾነን ተፈጥረን ሳለ በግብራችን ግን ከእንስሳት ጋር እንድንመሳሰል ያደርገናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ ወተመሰሎሙ፤ ሰውስ ክቡር ሳለ አላወቀም፤ ልብ እንደሌላቸው እንስሳትም መሰለ በማለት እንደ ተናገረው (መዝ. ፵፰፥፲፪)፡፡

በዓለማችን ላይ እንደምንሰማውና እንደምናስተውለው የሰው ልጅ ራሱን ከሚጥልባቸው መንገዶች አንደኛው ዝሙት ነው፡፡ ለዚህም ነው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች አስጸያፊ ፆታዊ ድርጊቶች ማለትም ከአንድ በላይ የትዳር አጋር መያዝ፣ ሴት አዳሪነት ብሎም የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ምእመናንን ሳይቀር እየተፈታተነ የሚገኘው፡፡ ይህም በሰው ልጆች ዘንድ የመንፈስ ዝለትና የዝሙት ስሜትን የመቈጣጠር ስንፍናን አመላካች ነው፡፡ ከእንደዚህ ዓይነት አጸያፊ የዝሙት ሥራ ራሳችንን እንድንጠብቅ ለማስጠንቀቅ፣ ጋብቻችንንም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ብቻ እንድንፈጽም ለመጠቆም እንደዚሁም ሩካቤ ሥጋ በሥርዓትና በሕግ እንደሚፈጸም ለማስገንዘብ ‹‹የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት›› በሚል ርእስ ይህን ትምህርት አዘጋጅተናል፡፡ በድጋሜ መልካም ንባብ!

፩. የጋብቻ ምንነትና አመሠራረት

ከቃሉ ትርጓሜ ስንጀምር ጋብቻ፡- መጣመር፣ መዋሐድ (አንድ መኾን)፣ በአንድ ጎጆ ውስጥ መኖር ማለት ነው፡፡ ቃሉ፣ የትዳር ሕይወትን ለመመሥረት የሚያስችል የሁለት ተቃራኒ ወይም ተፈላላጊ ፆታዎችን (ጥንዶችን) ዘላቂ ጥምረት (ግንኙነት) ያመለክታል፡፡ ‹ትዳር› የሚለው ቃልም ከጋብቻ ጋር በአቻነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይኸውም ባልና ሚስት በአንድ ጎጆ ጥላ ሥር የሚያከናውኑት ቤተሰብኣዊ ኑሮ ነው “በአንድ ልብ በእግዚአብሔር ቤት ተራመድን” በማለት ቅዱስ ዳዊት እንደ ተናገረው (መዝ. ፶፬፥፲፬)፡፡ ትዳር፣ ሁለቱም (ብልና ሚስት) በመስማማትና በመተሳሰብ በአንድነት መኖራቸውን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ ጋብቻ ወይም ትዳር ማለት በሁለት የማይተዋወቁና ባዕድ ተቃራኒ ጥንዶች (ፆታ) የሚመሠርቱት የአንድነት ሕይወት ነው፡፡

አመሠራረቱን ስንመለከት ጋብቻ የተመሠረተው በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በአዳምና ሔዋን አማካይነት ነው፡፡ ከአዳም በፊት የተፈጠሩ አራዊት፣ እንስሳትና አዕዋፍ በዝተው፣ ተባዝተው ይኖሩ ዘንድ የተፈጠሩት ጥንድ ጥንድ (ሴትና ወንድ) ኾነው ነበር፡፡ ለአዳም ግን ገና ሔዋን አልተሰጠችውም ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአራዊት፣ ለእንስሳትና ለአዕዋፍ ስም ያወጣላቸው ዘንድ ወደ አዳም በላካቸው ጊዜ እንስሳቱ ተባዕትና አንስት ኾነው መፈጠራቸዉን አዳም ተመልክቶ “ከእኔ በቀር ብቻውን የተፈጠረ የለም” ብሎ ማዘኑን የቤተ ክርስቲያን መተርጕማን ይናገራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር አምላካችን፣ “ኢኮነ ሠናየ ለእጓለ እመሕያው ይንበር ባሕቲቶ፤ አላ ንግበር ሎቱ ቢጸ ዘትረድኦ፤ ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም፤ የምትረዳውን ጓደኛ እንፍጠርለት እንጂ” አለ፡፡

ከዚህ በኋላ አዳም እንዲያንቀላፋ አደረገ፡፡ ከጎኑም አንድ አጥንት ነሥቶ (ወስዶ)፣ መልክ ከደም ግባት አስተባብራ የያዘችና ውብ አድርጎ፤ ዓይን፣ አፍንጫ፣ እጅ፣ እግር አውጥቶ፤ የሴት አካል ሰጥቶ ሔዋንን ፈጠረለት፡፡ ሔዋን ከአዳም ጎድን መፈጠሯም ባልና ሚስት ተከባብረው፣ ተቻችለውና ተመካክረው በእኩልነት እንዲኖሩ የሚያመለክት ምሥጢር አለው፡፡ ከዚህ ላይ የእግዚአብሔር ዓላማ ሴትንና ወንድን ማበላለጥ አለመኾኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እንደዚያ ቢኾን ኖሮ ሔዋንን አንድም ዝቅ ብሎ ከአዳም እግር፤ አንድም ከፍ ብሎ ከራሱ ሊፈጥራት ይችል እንደ ነበር መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሔዋን ከአዳም ጎን መፈጠሯ ባልና ሚስት እርስበርስ በመተጋገዝ፣ በመተሳሰብና በመደጋገፍ መኖር እንደሚገባቸው ያመላክታልና፡፡

አዳምም ከእንቅልፉ ሲነቃ ከጎኑ ሔዋንን በአገኘ ጊዜ “ይህቺ አጥንት የአጥንቴ ፍላጭ፣ ይህቺ ሥጋ የሥጋዬ ቁራጭ ናትና፤ ከኔ ከባሏ ተገኝታለችና ሚስት ትኹነኝ” በማለት ለሚስትነት እንደ ተሰጠችው አረጋግጦ ተናግሯል፡፡ ስለዚህም ወንድ አባትና እናቱን ትቶ ሚስቱን ተከትሎ ይሔዳል፡፡ ቈላ ብትወርድ፣ ደጋ ብትወጣ አብሯት ይወርዳል፤ ይወጣል፡፡ አንድ ክብር በመውረስና በመልበስ፤ እንደዚሁም በግብር (በሩካቤ ሥጋ) ሁለቱም አንድ አካል ይኾናሉ፡፡ ወንድ ቢወለድ ‹‹ያንተ ነው፤›› ሴት ብትወለድ ‹‹ያንቺ ናት›› አይባባሉምና፡፡ ዳግመኛም ሁለት ኾነው አንድ ልጅ ያስገኛሉና፤ እንደዚሁም ከእናት ደም፣ ከአባት ዘር ተከፍሎ አንድ ሰው እንዲወለድ ምክንያት ናቸውና እግዚአብሔር ‹‹አንድ አካል ይኾናሉ›› አለ (ዘፍ. ፩፥፳፰፤ ፪፥፳-፳፬)፡፡

ይቆየን

የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፩

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

መግቢያ

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ከዕለተ ትንሣኤ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ ድረስ ያለው ጊዜ ‹በዓለ ኀምሳ› ይባላል፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ተቀብሎ አዳምንና ልጆቹን ከሲኦል ነጻ ማውጣቱ፤ በሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱ፤ ከትንሣኤው በኋላ በልዩ ልዩ መንገድ ለደቀ መዛሙርቱ መገለጡ፤ መጽሐፈ ኪዳንን ለሐዋርያት እያስተማረ፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ ዐርባ ቀን በምድር ቆይቶ ወደ ሰማይ ማረጉ፤ ባረገ በዐሥረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት መላኩ፤ እንደዚሁም ዳግም ለፍርድ በግርማ የሚመጣ መኾኑ በስፋት የሚነገርበት ወቅት ነው፡፡ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን፣ እግዚአብሔር ያደረገልንን ውለታ በማሰብ ይህን ሰሙን በመንፈሳዊ ደስታ ልናከብረው እንደሚገባ የቤተ ክርስቲያን መምህራን ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡

ከዚህ ላይ መደሰት ማለት ሥርዓት በሌለው መልኩ ከመጠን በላይ መብላት መጠጣት ማለት አለመኾኑን ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቸርነት እያሰቡ በመጠን እየተመገቡ፣ ነዳያንንም እያሰቡ፣ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እየተቀበሉ መደሰት የክርስትና መገለጫ ነው፡፡ በዚህ ወቅት እያንዳንዱ ምእመን ሊጠብቀው የሚገባም ይህንኑ ሥርዓት ነው፡፡ ወቅቱ የደስታና የነጻነት ማለትም በክርስቶስ ቤዛነት የሰው ልጆች (ምእመናን) ከሰይጣን ባርነት ነጻ መውጣታችንን የምናስብበት ወቅት ነውና በዘመነ መርዓዊ እንደሚደረገው ዂሉ በዚህ ሰሙን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጋብቻ የሚፈጽሙ ምእመናን በርካቶች ናቸው፡፡ ዕቅዱ ላላቸውና ለተፈቀደላቸው ሰዎች ጋብቻ ከብቸኝነት ኑሮ ነጻ የሚወጡበት፣ የዝሙት ፆርን የሚከላከሉበት ሕይወት በመኾኑ በዚህ በነጻነት ወቅት (በበዓለ ኀምሳ) ይፈጸማል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የጋብቻን ታላቅነትና ልዩ ምሥጢር ባስተማረበት መልእክቱ “ይህም ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይህንኑ ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እናገረዋለሁ፤” በማለት የባልና የሚስት ጥምረት ወይም አንድነት የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ መኾኑን ይናገራል (ኤፌ. ፭፥፴፪)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ጋብቻ የመለኮት እና የትስብእት (የሰውነት) ምሳሌ መኾኑን መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ በዓለ ኀምሳ፣ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የመሠረታት የመድኀኒታችን ክርስቶስ ትንሣኤ የሚታሰብበት፣ ምሥጢረ ሥጋዌና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን በስፋት የሚሰበክበት ወቅት ከመኾኑ አኳያ በእርግጥም በዚህ የደስታ ሰሙን የተዋሕዶ ምሳሌ የኾነውን ጋብቻን በቤተ ክርስቲያን መፈጸም ለምሥጢር የተመቸ መልእክት አለው፡፡

የዛሬዉን ትምህርታዊ ጽሑፍ በጋብቻ ዙርያ ያደረግነው ወቅቱን ለመዋጀት በማሰብ ነው፡፡ በእርግጥ ስለ ጋብቻ በልዩ ልዩ መንገድ ብዙ ጊዜ ተምረናል፡፡ ኾኖም ጉዳዩ የሕይወት ጉዳይ ነውና ደጋግመን መማማሩ ይጠቅመናል፡፡ አንዳዶቹ በማወቅም፣ ባለማወቅም ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ጋብቻቸውን ሲፈጽሙ ይስተዋላል፡፡ ስለ ጋብቻ በተደጋጋሚ መማማራችንም በማወቅ ወይም በግድየለሽነት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ትዳር የሚመሠርቱ ምእመናንን ለመመለስና ሌሎችም እንዳይስቱ ለመጠቆም ይረዳናል፡፡ ስለዚህም በዚህ ዝግጅት ስለ ጋብቻ አመሠራረት፣ ክቡርነት፣ ምሥጢር እና ዓላማ የሚያትት ተከታታይ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን ትከታተሉ ዘንድ መንፈሳዊ ግብዣችንን እናስቀድማለን፡፡

መቅድም

የሰው ልጅ ወደዚህ ዓለም ከመጣ በኋላ ራሱን እስከሚችል ድረስ ሕይወቱ በእናት በአባቱ እጅ የተወሰነ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የወደፊት የኑሮ ዕጣውም በወላጆቹ አኗኗር ላይ የተመሠረተ ሊኾን ይችላል፡፡ በየትኛውም ዓይነት የአስተዳደግ ሥርዓት ብናልፍም ግን ዕድሜያችን እየገፋ ሲሔድ ራሳችንን መፈለግ እንጀምራለን፡፡ አንዳዶቻችን ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ሰባኪ፣ ዘማሪ፣ ወዘተ፤ ሌሎቻችን የአገር መሪ፣ አውሮላን አብራሪ፣ ተመራማሪ፣ ደራሲ፣ አርሶ አደር ወይም የተለየ ሰው የመሆን ርዕይ ሊኖረን ይችላል፡፡ ምንም ዓይነት ርዕይ የሌለን ሰዎችም ልንኖር እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ልንሸከመውና ልንወጣው በምንችልበት የኑሮ መስክ ያሰማራናል፡፡

በርዕይ ወይም ያለ ርዕይ ከአገኘነው ሥራ ወይም መዓርግ ባለፈ ሁለት ፈቃዳት ያስፈልጉናል፡፡ አንድም በድንግልና መኖር፤ አንድም በትዳር መወሰን፡፡ ሦስተኛው ግብር ግን ሰይጣናዊ ሲኾን፣ ይኸውም ዘማዊነት ነው፡፡ “ኦ ዘትቤ ንግበር ሎቱ፡፡ ለዕጓለ እመሕያው ቢጸ ከመ ኢይንበር ባሕቲቱ፡፡ እግዚአብሔር መጋቢ ወሠራዔ ዓለም በበሥርዓቱ፡፡ ሥርዐኒ ኀበ ፈቃድከ እምፆታ ፈቃዳት ክልኤቱ፡፡ ሣልሳዊሰ ግብር እምሰይጣን ውእቱ፤ ‹የሰው ልጅ (አዳም) ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም› በማለት የተናገርህ፤ ዓለምን በየሥርዓቱ ፈጥረህ የምትመግበው (የምታኖረው) እግዚአብሔር ሆይ፣ ከሁለቱ ፈቃዶች ውስጥ አንተ ወደ ወደድኸው ፈቃድ ምራኝ፡፡ ሦስተኛው ግብር (ሥራ) ግን ከሰይጣን የመጣ ነው፤” እንዳለ ደራሲ (ጠቢበ ጠቢባን)፡፡

ከሦስተኛው ፈቃድ ነጻ በመውጣት በምንኵስና ወይም በጋብቻ ለመኖርም ዋነኛውና መሠረታዊው ጉዳይ የእግዚአብሔር ፈቃድ ቢኾንም ከእርሱ ቀጥሎ የእያንዳንዳችን ፈቃድም ወሳኝነት አለው፡፡ ለመመንኰስም ትዳር ለመመሥረትም የሰውነታችንን ፈቃድ በትክክል መረዳት ይኖርብናልና፡፡ እንኳን ከገቡ ለማይወጡበት ለምንኵስና ሕይወት በልዩ ልዩ ምክንያት ሊቋረጥ ለሚችለው ለጋብቻ እንኳን ፈቃደኝነት ያስፈልጋል፡፡ የሁለቱ ጥንዶች የጋራ ስምምነት ደግሞ ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለቱ ተጋቢዎች ሳይስማሙ ማጋባት ተገቢ አይደለም፡፡

ምክንያቱም ሳይዋደዱ ከተጋቡ ኑሯቸው ጭቅጭቅና ጥርጣሬ የተሞላበት ሊኾን ይችላልና ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ጋብቻ ሕይወት ከመግባታችን በፊት ከአጋራችን ጋር በሙሉ ልብ መተማመንና መስማማት ይገባል፡፡ “ወኢይኩን ተዋስቦ ዘእንበለ በሥምረተ ክልኤሆሙ እለ ይትዋሰቡ ወበሥምረተ እሉ እሙንቱ ታሕተ ምግብናሆሙ ወዝንቱኒ ይከልእ እምአውስቦ …፤ በባልና ሚስት ፈቃድ ነው እንጂ ያለ ሁለቱ ፈቃድ ጋብቻ አይጸናም፤ አይፈጸምም፡፡ ወላጅ፣ ወይም አሳዳጊ ሳይፈቅድ ማጋባት አይገባም፤” እንዲል ፍትሐ ነገሥት (አን. ፳፬፣ ክፍል ፲፭)፡፡

በጋብቻ የመወሰን ፈቃድ እንደ ተሰጠን ዂሉ ፈቃደ ሥጋችንን ማሸነፍ እንደምንችል እርግጠኞች ከኾንን አለማግባትም ማለትም በድንግልና (በምንኵስና) መኖር እንችላለን፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር አምላክ የዝሙትን ፆር አርቆላቸው ከሴት ርቀው፣ ንጽሕ ጠብቀው በድንግልና (በምንኵስና) የሚኖሩ አባቶች እና እናቶች አብነቶቻችን ናቸው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባልና ሚስት ያለ ምክንያት መፋታት አመንዝራነት እንደ ኾነ ሲያስተምር ቅዱሳን ሐዋርያት “የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከኾነስ ማግባት መልካም አይደለም” አሉ። ጌታችንም “ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለዂሉ የሚቻል አይደለም፡፡ ከእናታቸው ማኅፀን እንዲሁ የተወለዱ፤ ሰዎች የሰለቧቸው፤ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ዣንደረቦች አሉ፡፡ መታገሥ የሚችልስ ይታገሥ” በማለት ስለ ጋብቻ እና ድንግልና ሕይወት አስረድቷቸዋል (ማቴ. ፲፱፥፲፩)፡፡ ይህ ኃይለ ቃል፣ ጋብቻም ኾነ ድንግልና በእግዚአብሔር ፈቃድ የሚመሠረት ሕይወት መኾኑን ያመላክታል፡፡

ይቆየን

ነገረ ትንሣኤ – ሦስተኛ ክፍል

በሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ

ሚያዝያ ቀን ፳፻፲ .

በዓለ ትንሣኤ፣ ‹ፋሲካ› እየተባለ የሚጠራበት ምክንያት

የፋሲካ በዓል በዕብራይስጥ ቋንቋ ፓሳህ› ይባላል፤ ትርጕሙም ማለፍ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በዓለ ትንሣኤ አንደኛ ሞት፣ ከእስራኤል መንደር ያለፈበት ስለ ኾነ ነው፤ ግብፅ በረሃብ እንዳትመታ ፈርዖናቸው ያደረገው ነገር ባይኖርም መጻተኛውና ወደ ወኅኒ የወረደው ዮሴፍ ግን የረሃብ ሞትን ወደ ግብፅ እንዳይገባ ከለከለው፡፡ ዳሩ ግን ዮሴፍ ሲያልፍ የዮሴፍን ታሪክ የማያውቅ ሌላ ፈርዖን ተሾመና በእስራኤል ላይ የሞት ሕግ አወጣ (ዘፀ. ፩፥፲፩)፡፡

‹‹በአንተና በሴቲቱ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፡፡ እርሱ ራስ ራስህን ይቀጠቅጣልአንተም ሰኰና ሰኰናውን ትነድፋለህ›› (ዘፍ. ፫፥፲፭) ተብሎ የተነገረለት ዲያብሎስ ራስ ራሱን የሚቀጠቅጥ ወንድ እንዳይወለድ በማሰቡ ሕፃናትን ከማኅፀን እያስቀረ፤ ለመቃብርም እያቀበለ እስከ ሙሴ ዘመን ደረሰ፡፡ ከሙሴ መምጣት በኋላ ሞት የእስራኤልን መንደር ለቅቆ ወደ ግብፃውያን መንደር እንዲገባ ምክንያት የኾነው ዕለትም ፋሲካ ይባላል፡፡ በዚህ በዓል ላይ እስራኤላውያን የበግ ጠቦት አርደው የቤታቸውን ጉበን የቀቡትን ደም የተመለከተው ሞት እነርሱን ትቶ የግብፃውያንን የበኵር ልጆች ገደለ፡፡ እስራኤላውያን ‹‹ቀሣፊያችን ተቀሠፈ›› ሲሉ በዓላቸውን ፋሲካ አሉት፡፡

እኛም በሐዲስ ኪዳን የጌታችንን ትንሣኤ ፋሲካ የምንለው ሞት ከእኛ ያለፈበት የመጀመሪያው በዓላችን በመሆኑ ነው፡፡ ስለ ብዙዎች ይቅርታ የፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም በግብፅ ከተሠዋው በግ ይልቅ የከበረ መሥዋዕት ነውና ያሉትን ከማዳኑም ባሻገር የሞቱትንም ከመቃብር አውጥቷል፡፡ በእርሱ ትንሣኤ ሞት ከእኛ ማለፉንና የሰው ባሕርይ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱንም ‹‹ለምንት ተኀሥሣሁ ለሕያው ምስለ ምዉታን፤ ሕያዉን ከሙታን ጋር ስለ ምን ትፈልጉታላችሁ›› ከሚለው ኃይለ ቃል እንረዳለን (ማቴ. ፳፰፥፮)፡፡ ምዉታን ያላቸውም አጋንንት ናቸው፡፡ በጌታችን ትንሣኤ ሰው ከሙታነ ሕሊና ከአጋንንት ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ ‹‹ኦ! አዳም መሬት አንተ ወትገብዕ ውስተ መሬት፤ አዳም ሆይ ቀድሞም መሬት ነህ፤ ወደ መሬትነትህም ትመለሳለህ›› የሚለው አዋጅ አሁን ተቀይሯል፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ከሚያረጀው ወደማያረጀው፣ ከሚበሰብሰው ወደማይበሰብሰው ሰውነት የተሸጋገርንበት በዓል ነው፡፡ ይህ ዂሉ መሸጋገር የተፈጸመው በፋሲካው በግ ምክንያት በመኾኑ ክርስቶስን ፋሲካችን እንለዋለን (፩ኛ ቆሮ. ፭፥፯)፡፡

ሁለተኛ ‹‹መሥዋዕተ ኦሪት አለፈ፤ መሥዋዕተ ወንጌል ደረሰ›› የምንልበት ወቅት ስለ ኾነ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ለደቀ መዛሙርቱ በሰጠበት ዕለት በፋሲካ የተጀመረችውን ሕግ በፋሲካ ይሽራት ዘንድ የሚያልፈውን መሥዋዕተ ኦሪት አስቀድሞ፣ የሚመጣውን መሥዋዕተ ወንጌል አስከትሎ ፋሲካን አደረገ፡፡ ለደቀ መዛሙርቱም ‹‹ዝ ውእቱ ደም ዘይትከአው ለሐዲስ ሥርዓት በእንተ ቤዛ ብዙኃን፤ ስለ ብዙዎች ይቅርታ የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው›› (ማቴ. ፳፮፥፳፰) በማለት ወደ ሐዲስ ኪዳን መግባታቸውን አስረግጦ ነግሯቸዋል፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ትንሣኤ አሮጌውን ትተን ወደ አዲስ ሕይወት የተሸጋገርንበት በዓል በመኾኑ ፋሲካ እንለዋለን፡፡

ሦስተኛ የደስታችን ማረጋገጫ ስለ ኾነ ነው፡፡ ፋሲካ ማለት በግእዝ ቋንቋ ደስታ ማለት ነው፡፡ ደስታችን የተረጋገጠው በጌታችን ትንሣኤ ሲኾን ፍጻሜውን የሚያገኘው ደግሞ በትንሣኤ ዘጉባኤ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጌታችን በዕለተ ዓርብ በቈረሰው ቅዱስ ሥጋውና ባፈሰሰው ክቡር ደሙ ተመሥርታለች፡፡ ምንም እንኳን በሕዝብና በአሕዛብ ፊት ደስታዋን የምትገልጥበት ጊዜ ገና ቢኾንም፣ በትንሣኤው ግን በዝግ ቤት ውስጥ ኾና የክርስቶስን ሰላምታ ተቀብላ ተደስታለች (ዮሐ. ፳፥፲፱)፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ፤ ተኀፂባ በደመ ክርስቶስ፤ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ደስ ትሰኛለች›› እያልን የምንዘምረው፡፡

ቤተ ክርስቲያን፣ ክርስቶስ የትንሣኤዋ በኵር ኾኖ ተነሥቶላታልና ሊገድሏት በሚጎትቷት ሰዎች ፊት ለሽልማት እንደ ተጠራ ብላቴና ደስ እያላት ትቀርባለች (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፳)፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደስታዋን በትንሣኤ ፍጹም እንደምታደርገውም ቅዱስ አርክዎስ በሃይማኖተ አበው ፱፥፩ ላይ ‹‹በዛቲ ዕለት ተፈጸመ ፍሥሐሃ ለቤተ ክርስቲያን፤ በዚች ቀን የቤተ ክርስቲያን ደስታ ፍጹም ›› በማለት ይመሰክርላታል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የጌታችን ትንሣኤ ፋሲካ ተብሎ ይጠራል፡፡

ጌታችን በኵረ ትንሣኤ የተባለበት ምክንያት

የመጀመሪያው አዳም ለሞትና ለኀጢአት በኵር ሆኖ ነበርና ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ ሞት ሲገዛን ኖሯል (ሮሜ. ፭፥፲)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ክርስቶስ ላንቀላፉት (ለሙታን) በኵራት ኖ ከሙታን ተነሥቶአል” በማለት ጌታችን የትንሣኤያችን በኵር መኾኑን ነግሮናል (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፳)፡፡ ከጌታችን በፊት የሞቱና ከሙታን የተነሡ አሉ፡፡ ነገር ግን የጌታችን ትንሣኤ ከሌሎች ትንሣኤ የተለየ ነውና በኵረ ትንሣኤ (የትንሣኤ መጀመሪያ) ይባላል፡፡ ጌታችን በኵረ ትንሣኤ መባሉም፡-

አንደኛ ሞቱ፣ ሞትን ስላጠፋ ነው፡፡ የጌታችን ሞት ከሌሎች ሙታን የተለየ ነው፡፡ ሞትን በመግደል ድሩን ሳይኾን የችግሩን ምንጭ ሸረሪቱን አጥፍቶታል፡፡ ኀጢአት፣ ሞት፣ መቃብር እነዚህ ሦስቱ ተያያዥ ነገሮች ናቸው፡፡ ኀጢአት ከሌለ ሞት፣ ሞትም ከሌለ መቃብር አይኖርም፡፡ ሞት ሲሞት ሙታን ተነሡ፤ የሞት ጥላ ሲገፈፍ መቃብራት ተከፈቱ፡፡ በክርስቶስ ሞት ኀጢአት ከሥሯ እንደ ተነቀለች ዛፍ ላታፈራ፣ ላትለመልም ለዘለዓለም ተነቀለች፡፡ ሞትም ሙታንን ለቆ ጠፋ፤ መቃብርም ባዶ ኾኖ ተከፈተ፡፡ ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያናችን በቅዳሴዋ ‹‹ሞተ ዘቦአ ቀዳሚ ውስተ ዓለም በቅንዓተ ሰይጣን አብጠልከ በምጽአቱ ለዋሕድ ወልድከ መድኃኒነ፤ በሰይጣን ተንኮል ከልጅህ መምጣት አስቀድሞ ወደ ዓለም የገባ ሞትን በልጅህ ሰው መን አጠፋህ›› እያለች የምታመሰግነው (ሥርዓተ ቅዳሴ)፡፡

ጌታችን በኵረ ትንሣኤ የተባለበት ሁለተኛው ምክንያት የጌታችን ትንሣኤ የመጀመሪያው ሐዲስ ትንሣኤ ስለ ኾነ ነው፡፡ ከእርሱ በፊት ከሙታን የተነሡ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም በሚበሰብስ ሥጋ ተዘርቶ በማይበሰብስ ሥጋ መነሣት የቻለ ማንም አልነበረም፡፡ ሌሎቹ ሙታን ለዘለዓለም ሞትን ማሸነፍ በሚችል ሞት የተነሡ አልነበሩምና (፪ኛ ነገ. ፲፫፥፳፩)፡፡ ክርስቶስ ከመጣ በኋላ የተነሡት እንደነአልዓዛር ያሉትም ዳግመኛ መሞትና መነሣት አለባቸው፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ግን ዘለዓለማዊ ነው፡፡ እኛም ከትንሣኤ ዘጉባኤ በኋላ እንደ መላእክት ኾነን እንኖራለን፡፡ በሚፈርስ፣ በሚበሰብስ ሥጋ ተዘርተን (ሞተን)፣ በማይፈርስ፣ በማይበሰብስ ሥጋ እንነሣለን፡፡ የትንሣኤያችን በኵር ክርስቶስ ነውና፡፡

ጌታችን በኵረ ትንሣኤ የተባለበት ሦስተኛው ምክንያት፣ ትንሣኤው ስለ ዂላችንም ቤዛ የተደረገ ትንሣኤ ስለ ኾነ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ስለ ዂላችን (ለዓለም) የሞተ የለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እስመ ኵሉ ፆሮ ይፀውር፤ ዂሉም የራሱን ሸክም ይሸከማል›› ብሎ እንደ ተናገረው (ገላ. ፮፥፭)፣ አባቶቻችን በራሳቸው ዕዳ ሲሞቱ ምንም ዕዳና በደል የሌለበት ክርስቶስ ግን ለፍጥረት ዂሉ ዕዳ ሊደመስስ በፈቃዱ ሞተ፡፡ ሞቱ ስለ ዂላችን እንደ ኾነ ዂሉ ትንሣኤውም የዂላችን ሕይወት ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚኾነን የአይሁድ ፍርሃት ነው፡፡ አይሁድ ‹‹በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ ማለቱን ሰምተናል፤ ደቀ መዛሙርቱ ሌሊት መጥተው እንዳይሰርቁት፣ ተነሣም ብለው ለሕዝብ እንዳያስተምሩ ...›› ነበር ያሉት (ማቴ. ፳፯፥፷፪-፷፭)፡፡

ይህ የአይሁድ ፍርሃት የዲያብሎስም ጭንቀት ነው፡፡ ጌታችን ክብርት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በገዛ ሥልጣኑ ሲለያት ዲያብሎስ ነፍሱን በሲኦል ውጦ፣ ሥጋውን በመቃብር ረግጦ ማስቀረት እንዳልተቻለው ስለ ተረዳ አይሁድን እንዲህ እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ትንሣኤውን ዐይተው ያምኑ ዘንድ ይህን ማለታቸው የጌታ ፈቃድ ነበር፡፡ አምነው ባይጠቀሙበትም የጌታ ትንሣኤ ላመኑትም ላላመኑትም ሕይወት ነውና፡፡ ስለዚህ ነው የጌታችንን ትንሣኤ በኵረ ትንሣኤያችን የምናደርገው፡፡

ትንሣኤ ዘጉባኤ

በእሳት ተቃጥለው፣ በአራዊት ተበልተው ወደ መድነአፈርነት የተለወጡ ሰዎችበዕለተ ምጽአት ከሞት የሚነሡት እንዴት ነው? እንደ ገና ሰው ነው ይፈጠራሉ ማለት ነው?

በመጀመሪያ ካለመኖር ወደ መኖር እንድንመጣ ያደረገን ጥበበ እግዚአብሔር ነው፡፡ ያለዚያማ እንዴት ኾኖ ነው ከአባት የተከፈለው ዘር ከሴት ደም ጋር ተዋሕዶ፣ ብጥብጥ የነበረው ረግቶ፣ የአጥንት ምሰሶ የጅማት ማገር ተሠርቶለት ቅዱስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚኾነው? በእርግጥ እንዲህ ኾኖ የተጀመረው ህልውናችን በሞት ሲቋረጥ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ በመቃብር ውስጥ ቀልጦ ለመቅረት እንጂ ተመልሶ ለመብቀል አልነበረም፡፡ የሰው ልጅ እንደ አዝርዕት ከሞተና ከፈረሰ በኋላ አካል ኖሮት የሚነሣ ነው፡፡ ያለ ዝናም የአዝርዕት ምን ትንሣኤ አላቸው? ያለ ክርስቶስ ደም መፍሰስስ የሰው ልጅ ማን ከሞት ሊያስነሣው ይችላል? የጌታችን ደም ሲፈስ ግን መቃብራት ተከፈቱ፤ ዐለቶች ተሰነጣጠቁ፤ ከሙታን ወገን ብዙዎቹ ተነሡ፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቦኑ ለከንቱ ፈጠርኮ ለኵሉ እጓለ እመሕያው፤ በውኑ ሰውን ዂሉ ለከንቱ ነገር ፈጥረኸዋልን?›› የሚለው የአባቶቻችን ጥያቄ ምላሽ አገኘ (መዝ. ፹፰፥፵፯)፡፡

ሞት እንደ ገበሬ፣ መቃብር ደግሞ እንደ እርሻ ኾኖ የሰው ልጆች በዚህ ምድር በመበስበስ በመፍረስ እንዘራለን፡፡ እንዲህ ካልኾንን ትንሣኤ የለንም፡፡ በኋላም ተለውጠን በአዲስ ሥጋ እንነሣለን፡፡ ባሕርይ መልአካዊ፣ ባሕርይ ሥጋዊ፣ ባሕርይ እንስሳዊ ለዂላችንም በተፈጥሮ ይሰጡናል፡፡ ስንሞት ባሕርይ እንስሳዊ እና ባሕርይ ሥጋዊ ይለዩናል፡፡ ባሕርይ መልአካዊ ግን በባሕርዩ ሞት ስለ ሌለበት አብሮን ይኖራል፡፡ በምንም ዓይነት ሞት ብንሞትም ይህ የማይቀር ጉዳይ ነው (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፴፭-፵፬)፡፡ ትንሣኤ፣ የሰው ልጅ ፍሬ ሠላሳ፣ ስልሳና መቶ ፍሬ አፍርቶ የሚታይበት ወቅት ነው፡፡

ዕፅዋትና አዝርዕት ከፈረሱ፣ ከበሰበሱ በኋላ አንዱ በራሱ፣ ሌላው በጎኑ፣ ሌላው በሥሩ ያፈራል፡፡ ከሥሩ የሚያፈራው የባለ ሠላሳ፣ ከጎኑ የሚያፈራው የባለ ስልሳ፣ ከራሱ የሚያፈራው የባለ መቶ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያናችን ‹‹ዳግም ልደት›› ተብሎ ይጠራል፡፡  የሰው ልጅ ተፈጥሮዎች ሁለት ዓይነት ሲኾኑ፣ እነዚህም ጥንተ ተፍጥሮና ሐዲስ ተፈጥሮ ይባላሉ፡፡ ጥንተ ተፈጥሯችን በአዳም በኩል የተደረገው ተፈጥሯችን ሲኾን፣ ሐዲስ ተፈጥሮ የምንለው ደግሞ በክርስቶስ በኩል የተደረገውን የባሕርያችንን መታደስ ነው፡፡ ልደታችን ግን ሦስት ወገን ነው፡፡ አንደኛው ሥጋዊ፣ ሁለተኛው መንፈሳዊ፣ ሦስተኛው ደግሞ ትንሣኤ ዘጉባኤ ነው፡፡ ይህም “ልደተ ሙታን እመቃብር” ይባላል፡፡ ይኸውም የሙታን ከመቃብር መወለድ ማለት ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት ማለትም በትንሣኤ ዘጉባኤ ከሞት የምንነሣውም በዚህ መልኩ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ነገረ ትንሣኤ – ሁለተኛ ክፍል

በሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ

ሚያዝያቀን ፳፻፲ .

ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት

ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ሲገንዙት ጌታችን ‹‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት እያላችሁ ገንዙኝ›› ብሏቸዋል፡፡ ይህ ቃል አንደኛ ጌታችን የቀደመውን መርገም እንደ ሻረው የተረዳንበት ነው፡፡ በዘመነ ኦሪት የሞተ ሰው ብቻ ሳይሆን በድኑን የነካውም ርኩስ ነበር፡፡ ይህ ልማድ ለመሻሩ ማረጋገጫችን “ቅዱስ እግዚአብሔር” የሚለው ቃል ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ሞት አንዱ የሕይወት መንገድ እንጂ ለሲኦል እና ለመቃብር የሚያሰጥ ፍርድ አይደለም፡፡ ሁለተኛ ጌታችን መለኮታዊ ባሕርይው የተለየው መስሏቸው እንደ ነበር ያስረዳናል፡፡ በግዕ ነባቢ የተባለው ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው ለዘመናት አበው ያቀረቡትን የሕይወት ጥያቄ ለመመለስ ነው፡፡ ዮሴፍና ኒቆዲሞስም ፈጽሞ ሕይወት እንደ ተለየው በማሰብ ይገንዙት ነበርና ይህን ጥያቄአቸውን ለመመለስ በቃሉ አናግሯቸዋል፡፡ በሥጋ ቢሞት በመንፈስ ግን ሕያው ነውና፡፡

ሦስተኛ ኃጢአትን የሚያስተሠርይ እውነተኛ መሥዋዕት መኾኑን ለማስገንዘብ የተነገረ ቃል ነው፡፡ እስካሁን የቀረቡት መሥዋዕቶች ዂሉ ሞት የገዛቸው ነበሩ፡፡ ክርስቶስ ግን ከሞት አገዛዝ ውጪ በመኾኑ ከሞተ በኋላ ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር በሉኝ›› ብሎ ተናግሯል፡፡ ‹‹ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት›› እንዲሉት መናገሩም በሥጋው ቢሞት በመለኮቱ ግን ሕያው መኾኑን ለማስረዳት ነው፡፡ አራተኛ ባሕርየ መለኮቱ በሥጋው መከራ እንደ ተሳተፈ ለማሳወቅ ነው፡፡ መለኮት የሥጋን ውርደት፣ ሥጋም የመለኮትን ክብር ካልተሳተፈ የተዋሕዶ መገለጫው ምን ሊኾን ይችላል? ያለ ሥጋ እንዴት ኾኖ በድርብ በፍታ፣ በተልባ እግር ልብስ ሊሸፈን ይችላል? ያለ መለኮትስ ከሞት በኋላ እንዴት ሊናገር ይችላል? የሥጋ ሕይወት ነፍስ ናትና፡፡

የሙታን ሕይወታቸው፣ በመቃብር ላሉት ትንሣኤያቸው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና መቃብር ሊወስነው አይችልም፡፡ ደቀ መዛሙርቱን ሳይቀር ‹‹ሙታንን አንሡ›› ብሎ ሥልጣንን የሰጠ ጌታ እንዴት በሞት ግዛት ውስጥ ሊወሰን ይችላል? አይደለም! ‹‹በመቃብር አደረ›› እንላለን እንጅ ‹‹መቃብር ወሰነው›› አንልም፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹ውእቱ ውስተ መቃብር›› ካለ በኋላ ‹‹ውእቱ አፍኣ እመቃብር፤ እርሱ ከመቃብር ውጭም አለ›› ብሏል፡፡ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በድርብ በፍታ ሲገንዙት በሰማይ ደግሞ በባሕርይ ክብሩ ጸንቶ አለ፡፡ በምድር መከራ በሚያጸኑበት አይሁድ ፊት መከራን ይቀበላል፤ በሰማይ ደግሞ ከመላእክት ምስጋና ይቀርብለታል፡፡

እነዚህ ዂሉ መለኮት በሥጋ መሞቱንና መከራ መቀበሉን፤ ሥጋም በመለኮት ሕይወት፣ መድኃኒት መባሉን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ እንዲህ ስንል ግን ‹‹መለኮት ሞተ›› እንዳንል መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ‹‹በሥጋው ሞተ›› ትላለች እንጂ ‹‹በመለኮቱ ሞተ›› አትልም፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹ለእመ ትቤ መለኮት ሞተ አንተ ቀታሊሆሙ ለአብ ወመንፈስ ቅዱስ፤ መለኮት ሞተ የምትል ከነ የአብ የመንፈስ ቅዱስ ገዳይ አንተ ነህ›› ብሏል (ሃይ. አበ. ፲፩፥፲፫)፡፡ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ በባሕርይ አንድ ናቸውና፡፡ ስለዚህ ‹‹መለኮት በሥጋ ሞተ፤ ሥጋ በመለኮት ሕያው ›› የሃይማኖታችን ትምህርት ነው፡፡

ጌታችን በሥልጣኑ ከሙታን ተለይቶ ስለ መነሣቱ

መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞቱ አስቀድሞ ‹‹ነፍሴን ላኖራትም፣ ላነሣትም ሥልጣን አለኝ›› በማለት ተናግሯል (ዮሐ. ፲፥፲፯-፲፰)፡፡ በሐዋርያት ሥራ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው›› ተብሎ ተጽፏል (ሐዋ. ፪፥፲፭-፳፮)፡፡ ከዚህ ላይ ‹‹ጌታችን ከሙታን የተነሣው በራሱ ሥልጣን አይደለምን? እነዚህ ኃይለ ቃላትስ አይጋጩምን?›› የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ ወደ ምላሹ ስንመጣ ነገረ ክርስቶስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁለት ዓይነት አንድምታ አለው፡፡ ሐዋርያት ስለ እርሱ በጻፉት በሰበኩት ቃል ዂሉ ከሁለት አካል አንድ አካል፣ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ መኾኑን ለማስረዳት አንዳንድ ጊዜ ፍጹም ሰው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፍጹም አምላክ ሲያደርጉት እንመለከታለን፡፡

ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ፣ ‹‹የሚያበረታው መልአክ መጣከብርቱ ጩኸትና ልመና ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበእግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ጸሎቱ ተሰማለት›› (ዕብ. ፭፥፯) በማለት ጌታችንን ከአዳም ልጆች እንደ አንዱ በማስመሰል ደካማ ቃላትን ተናግሮለታል፡፡ በዚህም አምላካችን ክርስቶስ ድካማችንን ለማገዝ መድከሙን እንረዳበታለን፡፡ ኀይለኛውን ጠላታችንን አስሮ፣ ሲኦልን በርብሮ ነፍሳትን ነጻ እስኪያወጣ ድረስ ጌታችን ደክሞ ታይቷልና ደካማ ቃላት ተነገሩለት፡፡ ለመለኮትማ ከአንዱ ወደ አንዱ ይሔድ ዘንድ ጎዳና አለበት እንዴ? በእውነት ስለ ሥጋ ድካም ይህ ዂሉ ተባለ፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍትም ሰው መኾኑን እንደ ነገሩን ዂሉ ፍጹም አምላክ መኾኑንም ሲመሰክሩ ‹‹ተኀድገ ለከ ኃጢአትከ ፈቀድኩ ንጻሕ፤ ኀጢአትህ ተደመሰሰልህ፤ ፈቅጃለሁ፥ ንጻ›› እያለ በሥልጣኑ ኀጢአተኞችን ከበደል ነጻ እንደሚያደርግና ሕሙማንን እንደሚፈውስ ነግረውናል፡፡ ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ይህን ያደርግ ዘንድ ሥልጣን ያለው የለምና፡፡ በዚያውም ላይ ነፋሳትን ሲገሥፅ፣ አጋንንትን ሲያስደነግጥ ዐይተን፤ እንደ አምላክ ባለ ሟሎች በእግዚአብሔር ስም ሳይኾን በራሱ ስም ተአምራትን ሲያደርግ ስንመለከተው አምላክ መኾኑን  አወቅን፡፡ ስም አጠራሩን ስንመለከት አንዳንድ ጊዜ ‹‹ወልደ ዳዊት›› ሌላ ጊዜ ደግሞ ‹‹ወልደ እግዚአብሔር›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ‹‹ወልደ ዳዊት›› በመባሉ ምድራዊ ልደቱን፣ ‹‹ወልደ እግዚአብሔር›› በመባሉ ደግሞ ሰማያዊ ልደቱን ተረዳን፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ‹‹ወልደ ዳዊት›› እየተባለ የመጠራቱ ምሥጢርም እኛ ሰማያውያን እንሆን ዘንድ እሱ ምድራዊ መኾኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ክርስቶስ ሲነገር ማንኛውም ምእመን የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ ሊል ይገባል፤

ለካየተነገሩ ቃላት መኖራቸውን

በቅዱስ ወንጌል ‹‹አባቴ ላከኝ፤ ይህን ሥልጣን ከአባቴ ተቀብያለሁ›› የሚሉ ቃላት በተደጋጋሚ ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡ ያ ማለት ግን ምድራዊ አባት በልጁ፣ ልጅም ለአባቱ እንደሚያደርገው በአብ እና በወልድ መካከል ማዘዝ፣ መታዘዝ፣ መላክ፣ መላላክ ኖሮ አይደለም፡፡ ‹‹ኢይኤዝዞ አብ ለወልዱ በከዊነ አብ ወኢየቢ ወልድ በከዊነ ወልድ፤ አብ ልጁን አባት በመሆን አያዝዘውም፤ ወልድም ልጅ በመሆኑ እንቢ አይልም›› እንዳለ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፡፡ ታዲያ ለምን እንዲህ ይላል ያሉ እንደ ኾነ ቀዳማዊ አዳም ባለ መታዘዙ የመጣበት መከራ፣ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ እስከ መስቀል ድረስ ባደረገው መታዘዝ እንደ ተወገደለት ለማስረዳትና የአዳምን አለመታዘዝ በመታዘዝ ለመካሥ ነው፡፡

ኛ ጌታችን ፍጹም ሰው መኑን ለማስረዳት የተነገሩ ቃላት መኖራቸውን

ጌታችን ‹‹ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች›› ሲል ኀዘን የሚስማማው ሰውነትን እንደ ተዋሐደ ለማስረዳት ነው፡፡ ‹‹… ዋጋችሁ ብዙ ነውና ደስ ይበላችሁ›› እያለ የምሥራችን የሚሰብክ ጌታ እንዴት አዘነ ተብሎ ይነገርለታል?

የጠፉትን ለመፈለግ የተነገሩ ቃላት መኖራቸውን

ጌታ ‹‹አንሆይ፥ ውኃ አጠጭኝ›› ማለቱ ለሣምራዊቷ ሴት የሕይወትን ውኃ ለማጠጣት እንጂ እርሱ ውኃ ስለ ጠማው የተናገረው አይደለም፡፡ እንዲያማ ቢኾን ኖሮ በኋላ ውኃ ሲጠጣ ባየነው ነበር! ከዚያ ይልቅ ለሴቲቱ የሕይወትን ውኃ አጠጥቶ መሔዱን ስንመለከት ቃሉ የጠፋችውን ሴት ለመፈለግ የተነገረ መኾኑን እንረዳለን፡፡ ከላይ የተነሣው ጥያቄም ከእነዚህ ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ለመነሣት እንደ አልዓዛር፣ እንደ ወልደ መበለት ድምፅ የሚያሰማውና ከመቃብሩ በር ላይ ተንበርክኮ የሚጸልይለት ጻድቅ አያስፈልገውም፡፡ በገዛ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል እንጂ፡፡ ለዚህም ‹‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን አነሣዋለሁ›› ማለቱን ልብ ይሏል (ዮሐ. ፪፥፲፱)፡፡ በዚህም ሰውነቱን ከሞት እንደሚያነሣው ሥልጣን እንዳለው አሳይቶናል፡፡

በመሠረቱ ‹‹እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው›› (ሐዋ. ፪፥፲፭-፳፮) የሚለው ኃይለ ቃል፣ እግዚአብሔር እንዳስነሣው እንጂ አብ እንዳስነሣው የሚናገር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በሚለው ስም አብ ብቻ ሳይኾን ወልድና መንፈስ ቅዱስም ይጠሩበታል፡፡ አባቶቻችን የዚህን ኃይለ ቃል ምሥጢር ሲያስረዱ ‹‹እግዚአብሔርነቱ አስነሣው›› ብለው ይተረጕሙታል፡፡ ይኸውም ‹‹እግዚአብሔር›› የሚለው ስም ባሕርያዊ ስም እንጂ አካላዊ ስም ስላልኾነ ነው፡፡

አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹እግዚአብሔር አምላክህ ቀባህ እግዚአብሔርም የናዝሬቱን ኢየሱስን በኃይልና በመንፈስ ቀባው እግዚአብሔርም ከሙታን መካከል ለይቶ አስነሣው …›› ሲል ሲሰሙ የእምነት መሠረታቸው ይናወጥባቸዋል፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ በመጽሐፈ ምሳሌ ፰፥፲፪ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል ሲተረጕም ‹‹ጥበብ ጌታ ፈጠረኝ አለች እን አብ ፈጠረኝ አላለችም፤ ወልድ ስለ አባቱ መናገር በፈለገ ጊዜ አባቴ ብሎ ለይቶ የሚናገር አይደለምን?›› በማለት ለአርዮሳውያን የሰጠውን ምላሽ መመልከቱ ለዚህ ይጠቅማል (ሃይ. አበ. ፸፮፥፲፫)፡፡ ስለዚህ ‹‹አብ አነሣው›› ብለው ለሚሳሳቱ፣ ለሚያሳስቱ ወልድ በሥልጣኑ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ መኾኑን እንነግራቸዋለን፡፡

ሴቶች የጌታችንን ትንሣኤ የማየታቸው ምሥጢር

ቅዱስ ጳውሎስ ሴቶች በማኅበር መካከል መናገርና ማስተማር እንደማይገባቸው ተናግሯል (፩ኛ ቆሮ. ፲፬፥፴፭)፡፡ አንዳዶቹ ጌታችን ወደ መቃብሩ የሔዱትን ሴቶች ‹‹ወደ ገሊላ እንዲሔዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ›› ማለቱን በመጥቀስ ሴቶች ወንጌል ማስተማር ይችላሉ የሚል መከራከሪያ ያነሣሉ (ማቴ. ፳፰፥፩-፲)፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ለቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት የቀናን ይመስላቸውና ሲሳሳቱ እናያቸዋለን፡፡ የሴቶችን አለመስበክ ሲያስተዉሉ፣ ሴቶች የማይገቡባቸው ገዳማትን ሲያዩ እንደ መብት ጥሰት የሚቈጥሩት አሉ፡፡ አዳም ጥንት ሲፈጠር ያለ ሴት ብቻውን ለአንድ ሱባዔ ቆይቷል፡፡ ሴት የማይገባባቸው ገዳማት መኖራቸው ከሔዋን መገለጥ በፊት የነበረውን አዳም ለመግለጥ እንደ ሆነ መረዳት ይገባል፡፡

ጌታችን ቤተ ክርስቲያንን መሰብሰብ ሲጀምር ሠላሳ ስድስቱን ሴቶች እንዲኾኑ ማድረጉ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሴቶች ለወንጌል አገልግሎት መጠራታቸውን ልናምን ይገባናል፡፡ ከተጠሩት ቅዱሳት አንስት መካከልም ወንጌልን ሰብከው ብዙዎችን ወደ ማመን እንደ መለሷቸውና እንዳስጠመቋቸው የተረጋገጠ ነው፡፡ እንዲህ ስላልን ግን በጉባኤ ወጥተው ያስተምሩ ነበር ማለታችን አይደለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የከለከለውም ይህንኑ ነው፡፡ በእርግጥ ሴቶች፣ ሴቶችን ሰብስበው ያስተምሩ ነበር፡፡

ለማርያም መግደላዊት መጀመሪያ ትንሣኤውን የገለጠውና ‹‹ሒደሽ ለወንድሞቼ ንገሪያቸው›› ብሎ የላካት ለምንድን ነው? ከተባለ ሞት ወደ ዓለም ሲገባ የተሰበከው በሴት አንደበት ነበር፤ በሴት እጅ በተቈረጠ ዕፀ በለስ፣ በሴት አንደበት በተሰበከ ስብከት ሞት ወረሰን፡፡ በዚህም ምክንያት ሴቶቹ ርስት አይካፈሉም፤ ከቍጥር ገብተው አይቈጠሩም ነበር፡፡ እነዚህንና ሌሎችንም ችግሮች በእርሱ ቤዛነት እንዳስቀረላቸው ለማጠየቅ ጌታችን ለሴቶች ተገለጠ፡፡ ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ሴት፣ ሞትን በሰበከችበት አንደበቷ ትንሣኤውን እንድትነግር፤ ወደ ዕፀ በለስ በሮጠችባቸው እግሮቿ ወደ ሐዋርያት እንድትገሰግስ አደረገ፡፡ በዚያውም ላይ ቀዳማዊ አዳም ከእንቅልፉ ሲነቃ ከጎኑ ያገኛት ሔዋንን ነበር፡፡ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስም ከሞት በተነሣ ጊዜ ከመቃብሩ በአፍኣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶች ተገኝተዋል፡፡

ይቆየን

ነገረ ትንሣኤ – የመጀመሪያ ክፍል

በሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ

ሚያዝያ ፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ጌታችን የሞተው በሥጋው ወይስ በመለኮቱ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጌታችንን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ሲያበሥራት ‹‹እንደ ቃልህ ይንልኝ›› ባለችው ጊዜ መለኮትና ትስብእት ሁለትነትን አጥፍተው በአካልና በባሕርይ ተዋሐዱ፡፡ መለኮት ባሕርያዊ ታላቅነቱን ሳይለቅ በየጥቂቱ ማደግን ከሥጋ ገንዘብ አደረገ፤ ሥጋም ባሕርያዊ ታናሽነቱን ሳይለቅ ከሦስቱ አካላት እንደ አንዱ ኾነ (ዘፍ. ፫፥፳፪)፡፡ ይህ ተዋሕዶ አንዱን ለአንዱ ያስገዛ ተዋሕዶ ነው፤ መራብ፣ መጠማት፣ ሞት፣ ድህነትና እነዚህን የመሳሰሉት ዂሉ ያለ ተዋሕዶ ለመለኮት ሊስማሙ አይችሉም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ባለጠግነት፣ ሕይወት፣ ዘለዓለማዊት መንግሥት፣ የማነ አብ፣ ዘባነ ኪሩብና እነዚህን የመሳሰሉት ዂሉ ለሥጋ ይነገሩ ዘንድ የሚገባቸው አልነበሩም፤ ተዋሕዶ ምክንያት ኾኖ የመለኮትን ለሥጋ የሥጋን ለመለኮት ሰጥተን እንድንናገር አድርጎናል፡፡ ቅዱስ ቄርሎስም በድርሳኑ ‹‹እንቲአሁ ለሥጋ ኮነ ለቃል፤ ወእንቲአሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ፤ የሥጋ ገንዘብ ለቃል የቃልም ገንዘብ ለሥጋ ›› ብሎ መናገሩም ይህንን የተዋሕዶ ፍጹምነት ለመግለጥ ነው፡፡

ሊቁ ይህን ምሥጢር ለማስረዳት የተጠቀመበት ምሳሌ የብረትና የእሳት ተዋሕዶ ነው፤ ብረት ሠሪ ብረቱን ከእሳት ሲጨምረው ብረቱ የእሳትን ባሕርይ ገንዘብ ያደርጋል፡፡ በዚህ ጊዜ መልኩና ውዕየቱ የእሳት፤ ቅርፅና መጠኑ ደግሞ የብረት ይኾናል፡፡ ብረት ሠሪው በመዶሻ ብረቱን ሲቀጠቅጠው ሊያዝ የማይችለው እሳት ከብረት ጋር ተዋሕዶ ሲቀጠቀጥ እናያለን፡፡ ከብረቱ ጋር እሳት ባይዋሐድ ኖሮ ብረቱን ማስተካከል አይቻልም ነበር፡፡ መለኮት ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜም ሊይዙት ሊጨብጡት የማይቻል እሳተ መለኮት ተይዞ ተደበደበ፡፡ መለኮት በሥጋ መከራ ባይቀበል ኖሮ የሰው ባሕርይ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ እንደ ምን ይችል ነበር? ኀጢአት ያቀዘቀዘውን ባሕርያችንን ያስተካከለው መለኮት በሥጋ የተቀበለው መከራ ነው፡፡ እንደዚያማ ባይኾን ኖሮ ከአቤል ጀምሮ በግፍ የተገደሉ ብዙ ቅዱሳን መከራቸው ለምን አላስታረቀንም? የዕሩቅ ብእሲ ደም ሰውን ከኀጢአት ሊያነጻው ባለ መቻሉ ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን በገለጸበት ቅዳሴው ‹‹ኦ አእዳው እለ ለኃኳሁ ለአዳም ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል ኦ አእጋር እለ አንሶሰዋ ውስተ ገነት ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል ኦ አፍ ዘነፍሐ ውስተ ገጹ ለአዳም መንፈሰ ሕይወት ሰረበ ብሒአ፤ አዳምን የሠሩ እጆች በቀኖት ተቸነከሩበገነት የተመላለሱ እግሮች በቀኖት ተቸነከሩ፤ በአዳም ላይ የሕይወት እስትንፋስን እፍ ያለ አፍ መራራ ሐሞትን ጠጣ›› በማለት ያደንቃል፡፡ አዳምን የሠሩ የመለኮት እጆች ወይስ የትስብእት? በገነት ሲመላለሱ አዳም የሰማቸው እግሮች የመለኮት ወይስ የትስብእት? በአዳምስ ላይ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ብሎ ልጅነትን ያሳደረበት ማን ነው? ሥጋ ነው እንዳንል ሊቁ እየተናገረ ያለው ቅድመ ተዋሕዶ ስለ ተፈጸመ ታሪክ ነው፤ መለኮት ነው እንዳይባል የመለኮት እጅና እግር በችንካር የሚመታ፣ አፉም እንኳን መራራውን ጣፋጩን ሊጠጣ የማይችል ንጹሐ ባሕርይ ነው፡፡ የሊቁ ቃል ይመልሰንና መለኮት በሥጋ መከራን እንደ ተቀበለ ያስረዳናል፡፡ እንደ ሰውነቱ ‹‹ተቸነከረ መራራ ጠጣ›› እንላለን፡፡ እንደ አምላክነቱ ደግሞ የአዳም ፈጣሪ እንደ ኾነ እንናገራለን፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የተናገረው ቃል ቀዳማዊው ደኃራዊ፣ ደኃራዊው ቀዳማዊ መኾኑን የምንረዳበት አንቀጽ ነው፡፡ በጥንተ ፍጥረት ያልነበረ ሥጋ ፈጣሪነትን በተዋሕዶ ገንዘብ አድርጓል፡፡ ዓለምን የሠሩ መለኮታዊ እጆችም በሥጋ መከራን ተቀብለዋል፡፡ ስለዚህ የቀራንዮው መስቀል መለኮት ከትስብእት፣ ተስብእት ከመለኮት አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመኾኑ የተቀበለው እንጂ ለሥጋ ብቻ የሚሰጥ አይደለም፡፡ መከራ የተቀበለው መለኮት ለብቻው ቢኾን ኖሮ አይሁድ እንዴት አድርገው መስቀል ያሸክሙታል? በገጸ መለኮቱ ፊት ቆመው እንደ ምን ይሳለቁበታል? በብርሃን የተከበበ ፊቱን መላእክት፣ ሐዋርያት ስንኳን ሊያዩት አይቻላቸውምና (ማቴ. ፲፯፥፩-፱)፡፡ ለመለኮትስ መሥዋዕት በሚኾን ገንዘብ ሥጋና ደም አለውን? መለኮት ለብቻው ቢሰቀል ኖሮ ደም እንዴት ይፈሳል? ሥጋስ ከየት መጥቶ ‹‹እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው›› ልንባል እንችላለን? (ዕብ. ፲፥፩-፲፱)፡፡

ሞት በአዳም ምክንያት ወደ ዓለም እንደ ገባ፣ ሞትን የሚገድል ሞት ደግሞ በሁለተኛው አዳም በክርስቶስ በኩል ኾነ፡፡ መለኮት በሥጋው የሞተው ሞት እንጅ ሞትን የገደለው የዕሩቅ ብእሲ ሞት ብቻ አይደለም፡፡ የዕሩቅ ብእሲ ደም እንዴት ሥርየትን ሊሰጠን ይችላል? የዕሩቅ ብእሲ ሥጋስ እንዴት «ወሀቤ ሕይወት» ሊኾን ይችላል? ሞትን ያመጣ ሥጋ ዛሬ ግን ሕይወትን ለሙታን የሚያድል የሕይወት ምንጭ ኾነ (ዮሐ. ፬፥፲)፡፡ ዂሉን ይዞ የሞተው የአዳም ሥጋ ዛሬ ለዂሉ ሕይወትን ሰጠ፤ መቃብር የገዛው ባሕርያችን ዛሬ ዂሉን ከእግሩ በታች አድርጎ ገዛ፡፡ ለዚህ ዂሉ ምክንያቱ ምሥጢረ ተዋሕዶ ነው፡፡ ስለዚህ መለኮት በሥጋ ሞተ፤ ሥጋም በመለኮት ሕያው ኾነ ብለን እንናገራለን፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ሞተ በሥጋ ወሐይወ በመንፈስ፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ›› ብሎ መናገሩም ለዚህ ምስክር ነው (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፰)፡፡ መልክአ ኢየሱስም ‹‹ሰላም ለበድነ ሥጋከ እመለኮቱ ዘኢተፈልጠዓት አሐቲ ከመ ቅበተ ዐይን ኅዳጠ፤ ለዐይን ጥቅሻ ለምታክል ሰዓት ስንኳን ከመለኮቱ ያልተለየ በድነ ሥጋህን ሰላም እላለሁ›› ይላል፡፡

በዕለተ ዓርብ መስቀል ላይ የዋለው የክርስቶስ ሥጋ ከመለኮቱ አልተለየም፡፡ በእርግጥ የሥጋ ሕይወት ነፍስ ተለይታዋለችና ሥጋው ‹‹ምውት›› ወይም ‹‹በድን›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሆኖም ጌታችን በመለኮታዊ ባሕርዩ ሞት አያሰጋውም፤ አይስማማውም፡፡ ስለዚህም ሕያው ሥጋ ነው፡፡ ሕያው መኾኑንም ከሞተ በኋላ ለንጊኖስ በጦር በወጋው ጊዜ ደምና ውኃ ከጎኑ በመፍሰሱ እናረጋግጣለን፡፡ ከሞተ ሰው ደም ይወጣ ዘንድ የተፈጥሮ ሕግ አይደለምና፡፡ ምውትነቱን ደግሞ ‹‹አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ›› ብሎ በፈቃዱ ነፍሱን በመስጠቱ እናረጋግጣለን፡፡ በአጠቃላይ ቃል፣ ሥጋ መኾንን የወደደው የሥጋን ድካም ለማገዝና በሥጋ ድካም ጠንካራውን ጠላት ዲያብሎስን ለማሸነፍ ነው፡፡ በመኾኑም በአራት ዓለማት ውስጥ በሰው ላይ ይደርሱ የነበሩ ችግሮቹን በአካል ተገኝቶ አስወግዶለታል፤ እነዚህም ማኅፀነ አንስት፣ ምድር፣ መቃብርና ሲኦል ናቸው፡፡

መርከስ እንጀምርበት በነበረው ማኅፀን መቀደስን እንደ ጀመርን ማረጋገጫ ይኾነን ዘንድ በእመቤታችን ማኅፀን የመላእክት ቅዳሴ ይሰማ ነበር፡፡ የሴት ማኅፀን ርኵሰት የሚጀመርበት የሰው ልጆች ዓለም ነበረ፤ ዛሬ (ጌታችን ሲወለድ) ግን «ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ» ተብሎ የሚመሰገንበት ቦታ ኾነ፡፡ ሴቶች ከወለዷቸው ዂሉ ሕዝቡን ከኀጢአት ሊያድናቸው የተቻለው ማንም አልነበረም፤ ዛሬ ግን ከኃጢአት ንጹሕ ኾኖ ኃጢአትን የሚያርቅ ጌታ ተገኝቶበታል፡፡ ርኵሰታችን ከሚጀምርበት ከማኅፀን ጀምሮ የርኵሰታችን ዋጋ እስከ ኾነችው ሲኦል ድረስ በሔድንበት ሒዶ ችግራችንን አስወገደልን፡፡ ይህን ሲያደርግ ግን መለኮት ከሥጋ የተለየበት አንዳች እንኳን ጊዜ እንደ ሌለ እናምናለን፡፡

«ተራብሁ» (ሉቃ. ፬፥፪) ብሎ መናገር የሚስማማው ለሥጋ ብቻ ቢኾንም፣ መለኮትም በሥጋ እንደ ተራበ እንናገራለን፡፡ ኅብስት አበርክቶ መመገብ የሚቻለው ለባለ ጠጋው መለኮት ቢኾንም ለሥጋም ተገብቶታል፡፡ ጌታችን፣ ሣምራዊቷ ሴት ውኃ በከለከለችው ጊዜ ‹‹የሚለምንሽ ማን እንደ ነ ብታውቂስ ኖሮ አንች በለመንሽው፣ እርሱም ደግሞ የሕይወትን ውኃ በሰጠሽ ነበር›› ሲል የሰማነው በሥጋው ነው፡፡ ለራሱ የሌለው ሥጋ ለሌላው መስጠት ጀምሯልና፡፡ ሞትንም ስናነሣ ለሥጋ ብቻ ሳይኾን መለኮትም በሥጋ እንደ ሞተ፤ መለኮትም በሥጋ በመቃብር እንዳደረ እንናገራለን፡፡ ይህን የምንናገረው ግን እርሱ ሞቶ ለሙታን ሕይወትን የሚሰጥ መኾኑን ሳንረሳ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሊቁ ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹ውእቱ ውስተ መቃብር ወያነሥእ ሙታነ፤ እርሱ በመቃብር ያደረ ሲን ሙታንን ያስነሣል›› ሲል የሚናገረው (ሃይማኖተ አበው፣ ፲፩፥፬)፡፡

ይቆየን

ትንሣኤ ክርስቶስ በሊቃውንት አንደበት – ካለፈው የቀጠለ

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

“ሕማምን፣ ሞትን ገንዘብ አደረገ፤ በሥጋው የሞተው ሞትም የእኛን ባሕርይ በመዋሐዱ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ተዋሕዶውን አስረዳ፤ ሞት ሰው የመኾን ሥራ ነውና፡፡ ከሙታን ተለይቶ መነሣትም አምላክ የመኾን ሥራ ነውና፤ እነዚህ ሁለት ሥራዎችን /ሞትንና ትንሣኤን/ እናውቃለን፤” (ቅዱስ ቄርሎስ፣ ሃይ. አበ. ፸፪፥፴፭)፡፡

“በሥጋ ሞተ እንዳልን ዳግመኛ በሥጋ ተነሣ እንላለን፤ ስለ ትንሣኤም የእርሱ ገንዘብ እንደ ኾነ፤ ሙስና መቃብርም እንዳላገኘው ይነገራል፡፡ ይህ ለመለኮት አይነገርም፤ የተነሣው ሥጋው ነው እንጂ፤” (ዝኒ ከማሁ ፸፱፥፱)፡፡

“የሞትን ሥልጣን አጠፋ፤ ዲያብሎስንና ኃይሉን (ኃጢአትን) ሻረ፡፡ የብረት መዝጊያዎችን ሰበረ (ፍዳ መርገምን አጠፋ)፡፡ ሲኦልን በዘበዘ፡፡ የጣዖት ቤቶችን አፈረሰ፡፡ የምሕረትን በር ከፈተ፤ ይህችውም በደሙ የከበረች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለዂሉ የዘለዓለም ሕይወት መገኛ የሚኾን ልጅነት የተገኘበት ሥጋውን ደሙን ሰጠን፤” (ቅዱስ ቴዎዶስዮስ፣ ሃይ. አበ. ፹፫፥፮)፡፡

“ለእኛስ እግዚአብሔር ቃል በባሕርየ መለኮቱ እንደ ታመመ፤ እንደ ሞተ፤ እንደ ተቀበረ ልንናገር አይገባንም፡፡ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ ሞት የሌለበት እንደ ኾነ፤ መድኀኒታችን በሚኾን በሞቱና በሦስተኛው ቀንም በመነሣቱ ትንሣኤን እንደ ሰጠን እናምናለን፡፡ የሞተ እርሱ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና፡፡ ዂሉን የሚችል እርሱ ካልተነሣ፣ የችሎታ ዂሉ ባለቤት እርሱ የሌለ ከኾነ፣ እንኪያስ ትንሣኤም ሐሰት ነዋ! ትንሣኤም ሐሰት ከኾነ ሃይማኖታችን ከንቱ ነው፡፡ እንኪያስ አይሁድንም እንመስላቸዋለን፡፡ ሰው እንደ መኾኑ በሥጋ ባይሞትስ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ እንደ መኾኑ ሞትን ባላጠፋ ነበር፡፡ የአዳም የዕዳ ደብዳቤም ከእግዚአብሔርና ከሰው መካከል ባልተደመሰሰም ነበር፤” (ቅዱስ ሳዊሮስ፣ ሃይ. አበ. ፹፬፥፲፰-፳)፡፡

“ፈጣሪያችን ክርስቶስ ለጌትነቱ እንደሚገባ ሥጋ መለወጥ የሌለበት እስኪኾን ድረስ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤ ሙስና መቃብርን አጥፍቷልና፡፡ በሥጋ በተቀበላቸው በሚያድኑ በእነዚህ ሕማማት ከጽኑ ሞት፣ ከዲያብሎስም ሥልጣን ያድነን ዘንድ ወደ ቀደመ ቦታችንም ያገባን ዘንድ፤” (ቅዱስ ዮሐንስ ዘአንጾኪያ፣ ሃይ. አበ. ፺፥፴፬)፡፡

“ይታመም ዘንድ በተገባው በሥጋው፣ ነውር የሌለበትን ሕማም በፈቃዱ በእውነት ተቀበለ እንጂ በምትሐት እንዳልታመመ እናገራለሁ፡፡ እንደ ሕማሙ ሞትንም በመስቀል ላይ ተቀበለ፡፡ ለአምላክነቱ በሚገባ፣ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤውም የጌትነቱን ሥልጣን ገለጠ፡፡ ሥጋውንም የማይሞት አደረገ፡፡ ከኃጢአት በራቀ በንጹሕ ማኅፀን በተዋሐደው ጊዜ ለመለኮት ገንዘብ ስለኾነ በሥራው ዂሉ አይለወጥም፤” (ቅዱስ ቴዎዶስዮስ፣ ሃይ. አበ. ፺፪፥፲፭)፡፡

“ሕማም የማይስማማው እርሱ በሥጋ ሞትን ታገሠ፤ ብረት ወደ እሳት በገባ ጊዜ ዂለንተናው እሳት እንደ ኾነ እስኪታሰብ ድረስ በእሳት ዋዕይ እንዲግል፤ በመዶሻ በተመታ ጊዜ በመስፍሕ (መቀጥቀጫ) ላይ እንዲሳብ (እንዲቀጠቀጥ)፤ እሳትም ከብረት ጋር ተዋሕዶ ሳለ ፈጽሞ እርሱ እንዳይመታ፤ ከብረቱም እንዳይለይ ግን የመዶሻ ኃይል ሳያገኘው እንዲመታ፤ ለመዶሻ እንዲሰጥ፤ የሚያድን የጌታ ሕማም እንዲህ እንደ ኾነ ዕወቅ፡፡

በዚህ ትንሽ ምሳሌ በእሳትና በብረት ተዋሕዶ ምልክትነት ፍጹም ተዋሕዶን እንወቅ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ይህ መከራና ሕማምን የሚቀበል ሥጋን ተዋሕዶ በሞተ ጊዜም ከሦስት ቀን በኋላ አምላክነቱ በተገለጠበት ትንሣኤው ሞትን አጠፋው፡፡ ሥጋው በመቃብር በመቀበሩም በመቃብር ውስጥ የነበረ መፍረስን መበስበስን አጠፋልን፤ ከሥሩም ነቀለው፡፡ ይህንም የሚያስረዳ ከቅዱሳን ወገን ብዙ ሰዎች ተነሡ፤” (ቅዱስ ባስልዮስ፣ ሃይ. አበ. ፺፮፥፶-፶፪)፡፡

“ዳግመኛ እርሱ እንደ ሞተ፣ በሦስተኛውም ቀን እንደ ተነሣ፣ ስለ ተነሣም ሥጋው የማይፈርስ የማይበሰብስ፣ የማይታመም፣ የማይሞት እንደ ኾነ እናምናለን፡፡ ሥጋውም ከእርሱ ጋር አንድ ኾኖ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአርያም በልዑል ዙፋኑ ተቀመጠ፡፡ ዳግመኛም በሙታንና በሕያዋን ይፈርድ ዘንድ ዂሉ አንድ ኾኖ በሚነሣበት ጊዜ እርሱ በጌትነት ይመጣል፤ ለዂሉም እንደ ሥራው ይከፍለዋል፡፡ እኛ በእነዚህ ቃላት ሳናወላውል ጸንተን እንኖራለን፤” (ቅዱስ ዲዮናስዮስ፣ ሃይ. አበ. ፺፱፥፴፪)፡፡

“በፈቃዱ በሥጋው የእኛን ሕማም ታመመ፤ በእውነት የእኛን ሞት ሞተ፡፡ ይኸውም የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው፡፡ በፈቃዱ በተለየ አካሉ ሞትን ገንዘብ አደረገ፡፡ በሦስተኛውም ቀን በሥልጣኑ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱ ዕሪና ተቀመጠ፡፡ በኋለኛይቱ ቀንም በሙታን በሕያዋን ሊፈርድ ይመጣል፤” (ቅዱስ ፊላታዎስ፣ ሃይ. አበ. ፻፭፥፲፬)፡፡

“በሞቱ ሞትን ያጠፋው እርሱ ነው፤ በሦስተኛው ቀን በመነሣቱም ሲኦልን በዘበዘ፡፡ ለዂሉም ትንሣኤን ገለጠ፡፡ ፈጽሞ አልተለወጠም፡፡ ለዂሉ አምላክነቱን አስረዳ፡፡ ሙስና መቃብርን ከእኛ አጠፋ፡፡ በቀደመ ሰው በአባታችን በአዳም ትእዛዝ ማፍረስ ምክንያት ሠልጥኖብን ለነበረ ኃጢአት ከመገዛት አዳነን፤” (ቅዱስ ዲዮናስዮስ፣ ፻፲፩፥፲፫)፡፡

“እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ነፍሱን ከሥጋው አዋሕዶ በመለኮታዊ ኃይል ተነሣ፡፡ እርሱ ራሱ ‹ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ ልሰጥ፣ ሁለተኛም መልሼ ላዋሕዳት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልኩ› እንዳለ፡፡ በነጋም ጊዜ ለማርያም መግደላዊት ታያት፤ እጅ ልትነሣው በወደደች ጊዜም ‹አትንኪኝ› አላት፡፡ ‹ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና›፤ ስለዚህም ሥጋዊ አካሉ ከዚያን አስቀድሞ በአብ ቀኝ እንዳልተቀመጠ ዐወቅን፤” (አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈ ምሥጢር ዘትንሣኤ)፡፡

“ሞትን በሥጋ በቀመሰ ጊዜ መለኮቱ በመቃብር ውስጥ ያለ ነፍሱ ከበድኑ ጋር ነበር፡፡ በሲኦልም ውስጥ ያለ ሥጋው ከነፍሱ ጋር ህልው ነበር፡፡ በአባቱም ቀኝ ያለ ነፍስና ያለ ሥጋ ህልው ነበር፡፡ በትንሣኤውም ጊዜ ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋሕዶ አስቀድሞ ለአይሁድ ‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛው ቀን እሠራዋለሁ› ብሎ እንደ ተናገረ፡፡ አይሁድም ‹ይህ ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ያለቀው በዐርባ ሰባት ዓመት ነው፤ አንተ ግን ‹በሦስት ቀን እሠራዋለሁ› ትላለህ› አሉት፤ ይህንም የተናገረው ስለ ራሱ ሰውነት ነው፡፡

በተነሣም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንደ ተናገረ አሰቡ፡፡ በመጽሐፍና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም የተናገራቸውን ቃል አመኑ፡፡ ሁለተኛም ‹ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ልለያት መልሼም አዋሕጄ ላስነሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህንንም ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልኩ› ብሏል፡፡ ዳዊትም ‹አቤቱ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ› ይላል፡፡ ነቢዩ ‹አቤቱ አንተ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ› ለምን አለ? የመቅደሱ ታቦት ከኾነችው ከዳዊት ዘር ከነሣው ሥጋ ጋር በመለኮታዊ ኃይሉ ከሞት እንቅልፍ ከመንቃት በስተቀር የእግዚአብሔር መነሣት ምንድነው?” (አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽ. ምሥጢር ዘትንሣኤ)፡፡

“ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ከጲላጦስ ተካሰው ከመስቀል አውርደው፣ በድርብ በፍታ ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገብቶ በጽርሐ ጽዮን ታያቸው፤” (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ፣ ፩፥፱-፴፩)፡፡

“ሰውን ስለ መውደድህ ይህን ሁሉ አደረግህ፤ ከሙታን ተለይተህ ‹መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ› ሳትል ተነሣህ፡፡ ከእግረ መስቀል ሙታንን አስነሣህ ነፍሳትን ከሲኦል ማርከህ ለአባትህ አቀረብህ፤” (ቅዳሴ ያዕቆብ ዘሥሩግ፣ ፩፥፳፬)፡፡

“በታወቀች በተረዳች በሦስተኛይቱ ቀን ‹መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ› ሳይል ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገባ፡፡ የተወጋውን ጎኑን፣ የተቸነከረውን እጁን፣ እግሩን አሳያቸው፡፡ በዓለመ ነፍስ የኾነውን እያስተማራቸው ዐርባ ቀን ኖረ፤” (ቅዳሴ ሠለስቱ ምዕት፣ ፬፥፳፭)፡፡

“ሰማያት (ሰማያውያን መላእክት) የደስታ በዓልን ያደርጋሉ፤ ደመናት (ቅዱሳን) የደስታን በዓል ያደርጋሉ፡፡ ምድር (ምድራውያን ሰዎችም) በክርስቶስ ደም ታጥባ (ታጥበው) የፋሲካን በዓል ታደርጋለች (ያደርጋሉ)፡፡ ያከብራሉ (ታከብራለች)፡፡ ዛሬ በሰማያት (በመላእክት ዘንድ) ታላቅ ደስታ ኾነ፤ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ የፋሲካን የነጻነት በዓል ታደርጋለች፡፡ የትንሣኤያችን በኵር ክርስቶስ ከሙታን ሰዎች ዂሉ ተለይቶ ቀድሞ ተነሣ፤” (ድጓ ዘፋሲካ)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ትንሣኤ ክርስቶስ በሊቃውንት አንደበት – የመጀመሪያ ክፍል

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በየጊዜያቱና በየዘመናቱ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ከዚህ ቀጥሎ የተገለጠውን ትምህርትና ምስክርነት ሰጥተዋል፤

“ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶ ሲኦልን ረግጦ፣ በሞቱ ሞትን አጠፋው፤ በሦስተኛው ቀንም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ‹አባት ሆይ አመሰግንሃለሁ፥› ብሎ ሥግው ቃል አመሰገነ፤” (እልመስጦአግያ ዘሐዋርያት ፭፥፩)፡፡

“እንደ ሞተ እንዲሁ ተነሣ፤ ሙታንንም አስነሣ፡፡ እንደ ተነሣም እንዲሁ ሕያው ነው፤ አዳኝ ነው፡፡ በዚህ ዓለም እንደ ዘበቱበት፣ እንደ ሰደቡት እንዲሁ በሰማይ ያሉ ዂሉ ያከብሩታል፤ ያመሰግኑታል፡፡ ለሥጋ በሚስማማ ሕማም ተሰቀለ፤ በእግዚአብሔርነቱ ኃይል ተነሣ፡፡ ይኸውም መለኮቱ ነው፡፡ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ማረከ፤” (ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ ሃይ. አበ. ፯፥፳፰-፴፩)፡፡

“እንዲህ ሰው ኾኖም ሰውን ፈጽሞ ያድን ዘንድ ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤” (ዘሠለስቱ ምዕት ፲፱፥፳፬)፡፡

“ሞትን ያጠፋው፤ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ የሞት ሥልጣን የነበረው ዲያብሎስን የሻረው እርሱ ነው፡፡ ሰው የኾነ፤ በሰው ባሕርይ የተገለጠ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያደረበት ዕሩቅ ብእሲ አይደለም፡፡ ሰው የኾነ አምላክ ነው እንጂ፡፡ ፈጽሞ ለዘለዓለሙ በእውነት ምስጋና ይገባዋል፤” (ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ሃይ. አበ. ፳፭፥፵)፡፡

“ሥጋው በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፡፡ በዚያም ሰዓት የጌታችን ሥጋው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ መቃብራት ተከፈቱ፤ ገሃነምን የሚጠብቁ አጋንንትም ባዩት ጊዜ ሸሹ፡፡ የመዳብ ደጆች ተሰበሩ (ሊቃነ አጋንንት፣ ሠራዊተ አጋንንት ድል ተነሡ)፡፡ የብረት ቍልፎቿም ተቀጠቀጡ (ፍዳ መርገም ጠፋ)፡፡ ቅድስት ነፍሱ በሲኦል ተግዘው የነበሩ የጻድቃን ነፍሳትን ፈታች፤” (ዝኒ ከማሁ፣ ፳፮፥፳-፳፩)፡፡

“ሥጋ ከመለኮቱ ሳይለይ በመቃብር አደረ፡፡ ነፍሱም ከመለኮት ሳትለይ በገሃነም ተግዘው ለነበሩ ነፍሳት ደኅነትን ታበስር ዘንድ፤ ነጻም ታደርጋቸው ዘንድወደ ሲኦል ወረደች፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ተናገረው ቃል ዐፅም ሥጋ ወደ መኾን ፈጽሞ እንደ ተለወጠ የሚናገሩ የመናፍቃንን የአእምሮአቸውን ጕድለት ፈጽመን በዚህ ዐወቅን፡፡ ይህስ እውነት ከኾነ ሥጋ በመቃብር ባልተቀበረም ነበር፡፡ በሲኦል ላሉ ነፍሳት ነጻነትን ያበሥር ዘንድ ወደ ሲኦል በወረደ ነበር እንጂ፡፡ ነገር ግን ከነፍስና ከሥጋ ጋር የተዋሐደ ቃል ነው፡፡ እርሱ የሥጋ ሕይወት በምትኾን በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ለነፍሳት ነጻነትን ሰበከ፡፡ ሥጋው ግን በበፍታ እየገነዙት በጎልጎታ በዮሴፍ በኒቆዲሞስ ዘንድ ነበረ፤ ቅዱስ ወንጌል እንደ ተናገረ፡፡ አባቶቻችን ‹ሥጋ በባሕርዩ ቃል አይደለም፤ ቃል የነሣው ሥጋ ነው እንጂ› ብለው አስተማሩን፡፡ ይህን ሥጋም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ቶማስ ዳሠሠው፤ በሥጋው ሲቸነከር ቃል ታግሦ የተቀበለውን የችንካሩን እትራትም በእርሱ አየ፤” (ዝኒ ከማሁ፣ ፴፥፴፩-፴)፡፡

“አሁን እግዚአብሔር ‹ሞተ› ሲል ብትሰማ አትፍራ፤ ‹የማይሞተውን ሞተ ሊሉ አይገባም› ከሚሉ ዕውቀት ከሌላቸው፤ ሕማሙን፣ ሞቱን ከሚክዱ መናፍቃን የተነሣ አትደንግጥ፡፡ እኛ ግን በመለኮቱ ሞት እንደሌለበት፤ በሥጋ ቢሞትም በመለኮቱ ሥልጣን እንደ ተነሣ እናውቃለን፡፡ ሞት የሌለበት ባይኾንስ ኖሮ በሥጋ በሞተ ጊዜ ሥጋውን ባላስነሣም ነበር፤ ሥጋው እስከ ዓለም ፍጻሜ በመቃብር በኖረ ነበር እንጂ፤” (ቅዱስ ባስልዮስ፣ ሃይ. አበ. ፴፬፥፲፯-፲፰)፡፡

“ከመስቀሉ ወደ ሲኦል በመውረዱ አዳነን፤ በአባታቸው በአዳም በደል በሲኦል ተግዘው የነበሩ ጻድቃንን ፈታ፡፡ ከሙታን ተለይቶ አስቀድሞ በተነሣው በእውነተኛ ትንሣኤውም አስነሣን፤ የንስሐንም በር ከፈተልን፤” (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣፴፮፥፴)፡፡

“በአባታችን በአዳም በደል የተዘጋ የገነት ደጅን የከፈተልን፤ ዕፀ ሕይወትን የሚጠብቅ ኪሩብንም ያስወገደው፤ የእሳት ጦርን ከእጁ ያራቀ፤ ወደ ዕፀ ሕይወት ያደረሰን እርሱ ነው፡፡ ፍሬውንም (ሥጋውን፣ ደሙን) ተቀበልን፡፡ አባታችን አዳም ሊደርስበት ወዳልተቻለው፤ በራሱ ስሕተት ተከልክሎበት ወደ ነበረው መዓርግ ደረስን፡፡ ክፉዉንና በጎዉን ከሚያስታውቅ፤ ወደ ጥፋት ከሚወስድ፤ በአዳምና በልጆቹም ላይ ኃጢአት ከመጣበት ከዕፀ በለስ ፊታችንን መለስን፤” (ዝኒ ከማሁ ፴፮፥፴፰-፴፱)፡፡

“የሕይወታችን መገኛ የሚኾን የክርስቶስ ሞት የእኛን ሞት ወደ ትንሣኤ እንደ ለወጠ እናምናለን፡፡ ክርስቶስም ሞትን አጥፍቶ የማታልፍ ትንሣኤን ገለጠ፤ እንደ ተጻፈ፣ ከሰው ወገን ማንም ማን ሞትን ያጠፋ ዘንድ፣ ትንሣኤንም ይገልጣት ዘንድ አይችልም፡፡ ዳዊት ‹በሕያውነት የሚኖር፤ ሞትንም የማያያት ሰው ማነው? ነፍሱን ከሲኦል፤ ሥጋውን ከመቃብር የሚያድን ማን ነው?› ብሎ እንደ ተናገረ፤” (ቅዱስ አቡሊዲስ፣ ሃይ. አበ. ፵፪፥፮-፯)፡፡

“በመለኮትህ ሕማም፣ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፤ በሥጋ መከራ የተቀበልህ አንተ ነህ፤ ከአብ ጋር አንድ እንደ መኾንህ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፤ ከእኛም ጋር አንድ እንደ መኾንህ በፈቃድህ የሞትህ አንተ ነህ፡፡ በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፤ በኪሩቤል ላይ ያለህ አንተ ነህ፤ ከሙታን ጋር በመቃብር የነበርህ አንተ ነህ፡፡ በአንተ ሕማምና ሞትም ድኅነት ተሰጠ፡፡ ከሙታን ጋር የተቈጠርህ አንተ ነህ፤ ለሙታንም ትንሣኤን የምትሰጥ አንተ ነህ፤ ሦስት መዓልት፣ ሦስት ሌሊት በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፤ በዘመኑ ዂሉ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምትኖር አንተ ነህ፤ በመለኮት ሕማም ሳይኖርብህ በሥጋ የታመምክ አካላዊ እግዚአብሔር ቃል አንተ ነህ፤” (ቅዱስ ኤራቅሊስ፣ ፵፰፥፲፪-፲፫)፡፡

“እኛስ ኃጢአታችንን ለማስተስረይ በሥጋ እንደ ታመመ፤ እንደ ሞተ፤ ከነፍሱም በተለየ ጊዜ ሥጋውን እንደ ገነዙ፤ ከሙታንም ተለይቶ በእውነት እንደ ተነሣ፤ ከተነሣም በኋላ በእውነት ወደ ሰማይም እንደ ዐረገ እናምናለን፡፡ ኋላም እርሱ በሚመጣው ዓለም በሕያዋን፣ በሙታን ይፈርድ ዘንድ ይመጣል፡፡ የሰውን ወገኖች ዂሉ በሞቱበት፤ በተቀበሩበት ሥጋ ከሞት ያስነሣቸዋል፡፡ ከትንሣኤውም በኋላ ያለ መለወጥ ዂል ጊዜ ይኖራል፡፡ እርሱ በዚህ በሞተበት፤ በተገነዘበት ሥጋ ከሙታን አስቀድሞ እንደ ተነሣ፤” (ቅዱስ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም፣ ሃይ. አበ. ፶፪፥፲፩-፲፪)፡፡

“የሥጋን ሕማም ለመለኮት ገንዘብ በአደረገ ጊዜ የእግዚአብሔር አካል በባሕርዩ በግድ ሕማምን አልተቀበለም፤ ሕማም በሚስማማው ባሕርዩ ኃይል እንጂ፡፡ ሞትም በሥጋ ለእግዚአብሔር ቃል ገንዘብ በኾነ ጊዜ ሞትን አጠፋ፤ ከሞትም በኋላ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አጠፋ፤” (ቅዱስ ቴዎዶጦስ፣ ሃይ. አበ. ፶፫፥፳፯)፡፡

“መለኮት በሥጋ አካል በመቃብር ሳለ መለኮት የሥጋ ሕይወት በምትኾን በነፍስ አካል ወደ ሲኦል ወረደ፡፡ እንደዚህ ባለ ተዋሕዶ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ከትንሣኤ በኋላ አይያዝም፤ አይዳሰስም፤ በዝግ ቤት ገብቷልና፡፡ ነገር ግን ምትሐት እንዳይሉት ቶማስ ዳሠሠው፤ የተባለውን ከፈጸመ በኋላ ቶማስ አመነበት፤” (ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ሃይ. አበ. ፶፮፥፴፯-፴፰)፡፡

“ክርስቶስ የሙታን በኵር እንደ ምን ተባለ? እነሆ በናይን ያለች የደሀይቱን ልጅ አስቀድሞ አስነሣው፤ ዳግመኛም አልዓዛርን በሞተ በአራተኛው ቀን አስነሣው፡፡ ኤልያስም አንድ ምውት አስነሣ፤ ደቀ መዝሙሩ ኤልሣዕም ሁለት ሙታንን አስነሣ፤ አንዱን ሳይቀበር፤ ሁለተኛውን ከተቀበረ በኋላ ሥጋውን አስነሣ፡፡ እነዚያ ሙታን ቢነሡ ኋላ እንደ ሞቱ፤ እነርሱ ኋላ አንድ ኾነው የሚነሡበትን ትንሣኤ ዛሬ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሙታን ትንሣኤያቸው በኵር ነው፡፡ እንግዲህ ወዲህም ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ የተነሣ እርሱ ነው፡፡ ‹ዳግመኛም ሞት አያገኘውም› ተብሎ እንደ ተጻፈ፤” (ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ፶፯፥፫-፮)፡፡

“ቃል ሥጋውን በመቃብር አልተወም፤ በሲኦልም ካለች ከነፍሱ አልተለየም፡፡ ከነፍስ ከሥጋ በአንድነት ነበረ እንጂ፤ ለዘለዓለም ክብር ምስጋና ይግባው፤” (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ፣ ሃይ. አበ. ፷፥፳፱)፡፡

“ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ በትንሣኤ ‹ከእናንተ ጋር እስከምመጣበት ቀን ድረስ ከዚያ ወይን ጭማቂ አልጠጣም፤ በሐዲስ ግብር በምነሣበት ጊዜ የምታዩኝ እናንት ምስክሮቼ ናችሁ› ያለውን የማቴዎስን ወንጌል በተረጐመበት አንቀጽ እንዲህ አለ፤ ሐዲስ ያለው ይህ ነገር ምንድነው? ይህ ነገር ድንቅ ነው! መዋቲ ሥጋ እንዳለኝ ታያላችሁ፤ ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ የማይሞት ነው፤ አይለወጥም፡፡ ሥጋዊ መብልንም መሻት የለበትም፤ ከትንሣኤ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቢበላም ቢጠጣም መብልን ሽቶ አይደለም፤ እርሱ ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ ያምኑ ዘንድ በላ ጠጣ እንጂ፡፡ ይህ ድንቅ ሥራ ነው! ያለ መለወጥ ሰው የኾነ ቃል የተቸነከረበትን ምልክት (እትራት) አላጠፋምና፡፡ 

በሚሞቱ ሰዎች እጅ እንዲዳሠሥ አድርጎታልና፤ አምላክ የሆነ ሥጋ የሚታይበት ጊዜ ነውና አላስፈራም፤ እርሱ በዝግ ደጅ ገባ፤ ግዙፉ ረቂቅ እንደሆነ ሥራውን አስረዳ፤ ነገር ግን በትንሣኤው ያምኑ ዘንድ የተሰቀለው እርሱ እንደሆነ የተነሣውም ሌላ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ ይህን ሠራ፡፡ ስለዚህም ተነሣ፤ በሥጋውም የችንካሩን ምልክት /እትራት/ አላጠፋም፤ ዳግመኛም ከትንሣኤው አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱ ጧት ማታ ከእርሱ ጋር ይበሉ እንደነበረ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በላ፤ ስለዚህም በዐራቱ መዓዝነ ዓለም ትንሣኤውን አስረዱ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ያየነው ከእርሱም ጋር የበላን የጠጣንም እርሱ ነው ብለው አስረዱ፤” (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ሃይ. አበ. ፷፮፥፯-፲፪)፡፡

“በእርሱ ሞት ከብረናል፤ በመለኮቱ ሞት ሳይኖርበት በሥጋ ሞተ፤ ምንጊዜም ቢሆን እርሱ የሕይወት ልጅ ሕይወት ነው፤ ይኸውም ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ወደ ሕይወት ሥጋ ደፍሮ በመጣ ጊዜ ሞት እንዲህ ድል ተነሣ፤ መፍረስ መበስበስም በእርሱ /በክርስቶስ/ እንዲህ ጠፋ፤ ሞትም ድል ተነሣ፤” (ቅዱስ ቄርሎስ፣ ሃይ. አበ. ፸፪፥፲፪)፡፡

ይቆየን