“ባለፉት 34 ዓመታት በአገልግሎት የራቁትን ማቅረብ፣ የቀረቡትን ደግሞ ለንስሐ ሕይወት ለእግዚአብሔር መንግስት ማብቃት ትልቅ ነገር ነው።” ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሶማሌ ጅግጅጋና የምሥራቅ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል
ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሶማሌ ጅግጅጋና የምሥራቅ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፣ የምስካየ ኃዙናን መድኃኔዓለም አንድነት ገዳም የበላይ ኀላፊ ሊቀ ጳጳስ ተወካይ በጉባኤው ተገኝተው መመሪያ አስተላልፈዋል።
ብፀዕነታቸው ለ34ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ያሉ ሲሆን “ባለፉት 34 ዓመታት በአገልግሎት የራቁትን ማቅረብ፣ የቀረቡትን ደግሞ ለንስሐ ሕይወት ለእግዚአብሔር መንግስት ማብቃት ትልቅ ነገር ነው።” በማለት ተናግረዋል።
ብፁዕነታቸው አክለውም “ባለፉት ዓመታት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እየሠራ ምእመናንን ወንጌል በማስተማር በሃይማኖታቸው ጸንተው ፍጻሜያቸው እንዲያምር በማድረግ፣ በተለያዩ አካባቢዎች አብያተ ክርስቲያናትን በማስከፈት፣ አብነት ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋትና ሌሎች አገልግሎቶችን በማከናወን እዚህ መድረስ ትልቅ ነገር ነውና ከዚህ በበለጠ ደከመን ሰለቸን ሳትሉ እንደትናንትናው እንድታገለግሉ” ሲሉ አሳስበዋል።
በመርሐ ግብሩ ማኅበሩ ከምሥረታ ጀምሮ አሁን ያለበትን የአገልግሎት ሁኔታ ማኅበረ ቅዱሳንን ከመሠረቱት መካከል አንዱ በሆኑት ዲ/ን ዝናዬ ኃ/ማርያምና በቤተ ክርስቲያን 39 ዓመት የአገልግሎት ጊዜ ያላቸው እንዲሁም ወላይታ ማእከልን የመሠረቱት በወ/ሮ መታሰቢያ ለማ ልምድና የሕይወት ተሞክሮ ቀርቧል።
የማኀበረ ቅዱሳን ም/ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዲ/ን ደምሰው ጫላ ባለፉት 34 ዓመታት በትጋት እዚህ መድረስ ትልቅ ነገር ነውና ለምሥረታው በዓል እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለማከናወን የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ አዘጋጅታ ወደ ተግባር እየገባችበት ባለው በዚህ ጊዜ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት አገልግሎታችንን ከመቸውም ጊዜ በላይ ማጠናከርና በቁርጠኝነት መደገፍ አንዱ የማኅበረ ቅዱሳን ኃላፊነት በመሆኑ የማኅበሩን ሥልታዊ ዕቅድ ከቤተ ክርስቲያን መሪ ዕቅድ ጋር በማጣጣም ለማከናወን፣ የተናበበ እና ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ሁላችንም መዘጋጀት ይኖርብናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳንን 34ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል እያከበርን በምንገኝበት በዚህ ቀን ሁላችንም ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ″ሥራህን ሥራ″ በማለት የተናገሩትን ቃል የአገልግሎት መርሕ አድርገን ስንከተል በአገልግሎት መስዋዕትነት ጭምር ማገልገልን እንደምናስቀድም በማመን ነውና ዛሬም ይህንን ቃል እያሰብን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚያግዙ ተልእኮዋን የሚደግፉ አገልግሎቶችን ለማገልገል መትጋት አለብን በማለት ዲ/ን ደምሰው ጫላ አያይዘው ተናግረዋል።
በመጨረሻም ማኅበሩ ባለፉት ዓመታት በየደረጃው የሚገኙ አባቶቻችን፣ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ከማኅበራት፣ ከበጎ አድራጊ ምእመናንና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በርካታ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ያከናወነ ሲሆን በቀጣይ የቤተ ክርሰቲያን የዐሥር ዓመታት መሪ ዕቅድ ያስቀመጠቻቸውን የመንፈሳዊ ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ግቦችና ለዚህ ስኬት ድጋፍ ሊያደርግ የሚችለውን የማኅበራችን 5ኛውን ስልታዊ ዕቅድ ዓላማዎች ለማሳካት የተቻለንን ሁሉ እንናድርግ ሲሉጥሪአቅርበዋል።
ብፁዕ አቡነ ሚካኤል የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እንኳን ለማኅበሩ የምሥረታ በዓል አደረሳችሁ በማለት መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን ❝34 ዓመት በጣም ትንሽ ናት የተሠራው ሥራ ግን ከዚያ በላይ ነው❞ ብለዋል። አያይዘው አገልግሎታችሁን ከጠረፍ እስከ ጠረፍ ተደራሽ በማድረግ ከዚህ በላይ እንድትሠሩ ሲሉ አሳስበው ከጎናችሁ ነን በማለት አክለውተናግረዋል።
ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በበኩላቸው እንኳን አደረሳችሁ ያሉ ሲሆን እግዚአብሔርን በመያዝ ሳትሰለቹ እስከመጨረሻው ጠንክራችሁ አገልግሉ በማለት ቡራኬ ሰጥተው መርሐ ግብሩ ተጠናቅቋል።
