• እንኳን በደኅና መጡ !

ዜናዎች፣ ወቅታዊ ክንውኖች እና ልዩ ልዩ ይዘቶች

የማኅበሩ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተራዘመ

ኅዳር 11 ቀን 2005 ዓ.ም. በእንዳለ ደምስስ የማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል በኢቢኤስ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ለመጀመር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በእኛ በኩል ዝግጅታችንን ለመጀመር ዝግጁ ሆነን እየተጠባበቅን የምንገኝ ሲሆን ከኢቢ ኤስ ቴሌቪዥን  በኢትዮጵያና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የጀመረው ስርጭት ከኅዳር 5 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ካልታወቀ አቅጣጫ በተደረገ ከፍተኛ የሳተላይት […]

mikeale

“በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ በፊትህ መልአክ እሰዳለሁ፤” ዘፀ.33፥1-3

ኅዳር 11 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ኢዮብ ይመኑ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ


mikealeበረሃብ ስደት ምክንያት ከከነዓን ወደ ግብፅ የመጡት ሰዎች ከዮሴፍ ጋር ሰባ ነበሩ፡፡ /ሐዋ.7/ በግብፅም በአባታቸው በያዕቆብ ምርቃት ቁጥራቸውም እጅግ በዛ፡፡ ይህም የቁጥራቸው መብዛት ከ1280-1445 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የተነሣውንና ዮሴፍን የማያውቀውን ንጉሥ አስፈራው፡፡ /ዘፀ.1፥8/ ንጉሡም ጠላት ይሆኑብናል ያም ባይሆን ጠላት ቢነሳብን አብረው ይወጉናል በሚል ፍርሃት አገዛዝ በማጥናት በቀን በሌሊት በከባድ ሥራ እየጠመደ በጭካኔ ጡብ እያስገነባ ፊቶም፣ ራምሴ፣ ዖንን የተባሉ ታላላቅ ከተሞችን እያሠራ ኖራ እያስወቀጠ ጭቃ እያስረገጠ በሥራ ደክመው ልጅ እንዳይወልዱና ጉልበታቸውን እየደከመ በጅራፍ አየገረፈ መከራ አጸናባቸው፡፡ ይህን ቢያደርግም ጉልበታቸው እየበረታ ከእርሱ መከራ የአባቶቻቸው ምርቃትና ቃል ኪዳን እየረታ አሁንም ሲበዙ ወንድ ሲወለድ በመግደል እስራኤልን ለመቆጣጠር ሞከረ፡፡ ግን የመከራው ብዛት የሕዝቡም ጩኸት የራሔልም እንባ እግዚአብሔርን፡- “የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ” አስብሎ በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት በሙሴ ጸሎት በግብፅ ምድር በ9 መቅሰፍቶች 10ኛ ሞተ በኩር  11ኛ ስጥመተ ባሕር የወጡት እስራኤል ከነዓን ገብተዋል፡፡ ይህም የኅዳር 12 መታሰቢያ በዓል መጽሐፍ ቅዱስ “በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ… በፊትህ መልአክ እሰዳለሁ፤” ዘፀ.33፥1-3 እንዳለ ከመከራ የወጡትን እስራኤል በጉዞአቸው ካለው መሰናከል እየጠበቀ “በመንገድ ላይ” እንዳይጠፉ እያማለደና በምሕረት እየታደገ ከጠላት ሲዋጉ አብሮ እየቀደመ ከዲያብሎስ ተንኮል እየሰወረ እግዚአብሔር ወዳዘጋጀላቸው ሥፍራ ያስገባው “መልአክ” የቅዱስ ሚካኤል መታሰቢያ በዓል ነው፡፡

 

ማእከላቱ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን አካሄዱ

ኅዳር 11 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን  ማኅበረ ቅዱሳን  የአሰላ፣ የአምቦ፣ የፍቼ፣ የደብረ ብርሃን፣ የወሊሶ እንዲሁም የወልቂጤ ማእከላት ከጥቅምት 25  እስከ ኅዳር 2 ቀን 2005 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ከወረዳ ማእከላት፣ ከግንኙነት ጣቢያዎች፣ ከግቢ ጉባኤያት የተወከሉ አባላት፣ የየሀገረ ስብከቱ ተወካዮች፣ የወረዳ ሊቃነ ካህናት፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች እና  የማኅበረ ቅዱሳን የዋናው ማእከልና የመሐል ማእከላት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ልዑካን በተገኙበት አካሂደዋል፡፡

 

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር

ኅዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

ሊቀ ልሣናት ቀሲስ ከፍያለው ጥላሁን

ሥነ ምግባር፡- ማለት ደግነት፣ በጎነት፣ መልካም ጠባይ ማለት ሲሆን ክርስቲያን የሚለው ቃል ሲጨመርበት ደግሞ የተሟላና የተለየ ያደርገዋል፡፡ መልካም ጠባይ ማንም ሰው ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የተሟላ ዘላቂና የሁል ጊዜ ሆኖም ለሰማያዊ መንግሥት የሚያበቃው በክርስትና እምነት ሲኖሩ ነው፡፡

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፡- በምድር እያለን ሰማያዊ ኑሮ ኖረን ለሰማያዊ መንግሥት የምንበቃበት ሕይወት ነው፡፡ ሰውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ማስደሰት ነውና፡፡ በመሆኑም ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሚከተሉት ሕግጋት ሊለካ ይችላል፡፡

 

debr 10

ደብረሊባኖስ ገዳምን የሚታደጉ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ኅዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ማለደ ዋስይሁን

 

debr 10

የደብረ ሊባኖስ ገዳምን በሁለንተናዊ መልኩ ለማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የገዳሙ ጸባቴ አባ ኃይለ መስቀል ውቤ አስታወቁ፡፡ ኅዳር 9 2005 ዓ.ም በማኅበረ ቅዱሳን ጽሕፈት ቤት ከገዳሙ ወዳጆች ጋር በተደረገው የምክክር መርሐ ግብር ላይ ይፋ እንደተደረገው ገዳሙ ያሉበትን ችግሮች ቀርፎ በቀጣይም አርአያ ምሳሌ ወደሚሆንበት ደረጃ የሚያደርሱትን እንቅስቃሴዎች ከማኅበረ ቅዱሳን ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ለማከናወን መታቀዱን ጸባቴው ገልጸዋል፡፡

 

p 11

ኢትዮጵያ ትሴብሕ ወትዜምር ግብፅ……

ኅዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ማለደ ዋስይሁን

የግብ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ሂደት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ እንደ ምሳሌ

p 11

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊን ዕረፍት ተከትሎ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ስድስት ወራት ያህል ትኩረት የሰጠችው ተተኪ ፓትርያርኳን ለመምረጥ አስፈላጊውን ሁሉ መፈጸም ላይ ነበር፡፡ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወዲያ ውኑ ባደረገው ጉባኤ ለቤተ ክርስቲ ያኒቱ ዐቃቤ መንበር መሾም ሲሆን ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ ዘቤሔይራ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ሆነው ተሰይ መዋል፡፡ ከዚያ ተከትሎ ግብፅ እግዚአብሔር ያዘዘውን ፓትርያርኳን ለማግኘት ተገቢ የምትለውን  ቀኖናዊ እርምጃዎች ሁሉ መውሰዷን ቀጠለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የፓትርያርክ ምርጫ ሂደቱን ያከናወነችው እ.ኤ.አ በ1957 በወጣው ድንጋጌ መሠረት  ነው፡፡

 

የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ /ለሕፃናት/

ኅዳር 7 ቀን 2005 ዓ.ም.

በኪዳነማርያም


አባታችን አብርሃም እግዚአብሔርን በማያውቁ፣ ጣዖት በሚያመልኩ መንደር ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ አባቱ ጣዖት እየቀረጸ የሚሸጥ ነበር፡፡ አንድ ቀን አባቱ ሸጠህ ና! ያለውን ጣዖት ከረሀቡ ያስታግሰው ዘንድ አብላኝ ብሎ ቢጠይቀው አልሰማህ አለው፡፡ የጠየቀውን አልመልስልህ ሲለው ሰባብሮ ጣለው፡፡ ወደ ሰማይ አንጋጦ ጨረቃን ጠየቃት አልመለሰችም፣ ፀሐይን ጠየቀ አልመለሰችም፡፡ ተስፋው ሲሟጠጥ አምላከ ፀሐይ ተናበበኒ (የፀሐይ አምላክ አናገረኝ) አለ፡፡ እግዚአብሔርም ሰማው ከዘመዶችህ ተለይተህ እኔ ወደ ማሳይህ ስፍራ ውጣ አለው፡፡ አባታችን አብርሃምም እንደታዘዘው በመፈጸሙ እግዚአብሔር ቃልኪዳን ገባለት፡፡ ዘርህን እንደ ምድር አሸዋ አበዛዋለሁ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ አለው፡፡ አብርሃምም ከሣራ ይስሐቅን ወለደ፣ ይስሐቅም ታዛዥ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን አንድያ ልጅህን ሠዋልኝ ባለው ጊዜ አብርሃም ታዘዘ፡፡ ልጁ ይስሐቅም አባቱን ታዘዘ፡፡ አምላክህን ከምታሳዝነው እኔንም ዓይን ዓይኔን እያየህ ከምትራራ በጀርባዬ ሠዋኝ ብሎ አባቱን አበረታው፡፡ እግዚአብሔርም የአብርሃምን እምነት የልጁን ታዛዥነት ዓይቶ በይስሐቅ ፋንታ ነጭ በግ በዕፀ ሳቤቅ አዘጋጅቶ እንዲሠዋ አደረገ፡፡ የበጉም ምሳሌ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

 

ቤተ ጣዖቱ ተዘጋ! የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

ኅዳር 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

 

“በአርሲ ሀገረ ስብከት  በመርቲ ወረዳ ልዩ ስሙ ፈረቀሳ በተባለ ሥፍራ ከ120 አመታት በላይ የአርሲዋ እመቤት” በሚል የባዕድ አምልኮ ሥርዓት ሲፈጸምበት በነበረ ሥፍራ ላይ የባዕድ አምልኮ ሥርዓቱን በማጥፋት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ገብርኤልን ቤተ ክርስቲያን  ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ኅዳር 1 ቀን 2005 ዓ.ም. አኖሩ፡፡

 

ራሔል እንዘ ትበኪ በእንተ ውሉዳ፥ ራሔል ስለልጆችዋ አለቀሰች

ኅዳር 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ኀይለ ኢየሱስ ቢያ

“ራሔል ስለ ልጆችዋ ስታለቅስ ብዙ ልቅሶና ዋይታ በራማ ተሰማ፤ መጽናናትንም እንቢ አለች፤ ልጆችዋ የሉምና” ማቴ.2፥18

 

ይህ የግፍ ልቅሶ 3 ጊዜ ተፈጽሟል፡፡ይኸውም፡-

1ኛ. በንጉሥ ፈርዖን ዘመን እስራኤላውያን በግብፅ እያሉ ራሔል የተባለች የሮቤል/ ስምዖን ሚስት ነፍሰጡር ሆና ጭቃ ስትረግጥ የወለደቻቸውን መንታ ልጆች ከጭቃ ጋር እንድትረግጥ ተገዳ በመርገጧ “ኢሀሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እስራኤል” በማለት እንባዋን ወደ ሰማይ ረጭታለች ዘዳ.1፥15፡፡ እግዚአብሔርም ልመናዋን ሰምቶ፥ ሊቀ ነቢያት ሙሴን አስነሥቶ ከግብፅ ነፃ አወጣቸው (ዘፀ. 3፥7 ተመልከቱ)

 

ማኅበሩ የነጻ የትምህርት ዕድል መስጠት ሊጀምር ነው፡፡

ኅዳር 5 ቀን 2005 ዓ.ም.

ዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ

 

ማኅበረ ቅዱሳን ኅዳር 2 ቀን 2005 ዓ.ም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮችና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በተገኙበት በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በተደረገ የማስተዋወቂያ መርሐ ግብር ለአብነት ተማሪዎችና መምህራን የነጻ ትምህርት ዕድል ለመስጠት መዘጋጀቱን ገለጸ፡፡

 

በፌስቡክ የትስስር ገጽ ያግኙን

ስለ ማኅበረ ቅዱሳን መሰረታዊ መረጃዎች

ስያሜ

ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ያከበራቸው የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት በአጠቃላይ የቅዱሳን ገድል፣ ትሩፋትና አማላጅነት የሚዘከርበት በመሆኑ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› የሚል ስያሜውን አግኝቷል፡፡

የማኅበሩ ርእይ

ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ የመሪነት ሚናዋን ስትወጣ ማየት

ተልእኮ

ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ መሳካት እና ለሕልውናዋ የሚተጋ፣ የተደራጀ ፣ ምሉዕ ኦርቶዶክሳዊ፤ ርቱዕ ዘመናዊ፤ ሁለገብ መሪ ትውልድ ማፍራት እና ማሰማራት

እሴቶች

  • መንፈሳዊነት

    ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
  • አገልጋይነት

    የማኅበሩ አባላት አገልግሎትን የክርስቲያናዊ ሕይወታቸው መገለጫ አድርገው በመቀበል በበጎ ፈቃድ ሰማያዊውን ክብርና ጸጋ በመሻት፣ ምድራዊ ክብርና ውዳሴ ከንቱን ሳይፈልጉ፣ በትሕትና እና በክርስቲያናዊ ፍቅር በታማኝነት ያገለግላሉ::
  • የሐሳብ መሪነት

    ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን ዘላቂ አገልግሎት የሚያስፈልጉ፣ ኦርቶዶክሳዊ እሳቤን የተከተሉና ዘመኑን የዋጁ የመሪነት ሐሳቦችን በማፍለቅ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር በመመካከር ይሠራል::
  • ተባባሪነት

    ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሁሉም የቤተ ክርስትያን አካላት የወል ተግባር ነው ብሎ ያምናል:: በመሆኑም እንደየጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ባለ ድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በመግባባት፣ በመመካከር እና በቅንነት ለተልእኮ አንድነት ብዝኃ ጸጋን በማክበር አብሮ ይሠራል::
  • ሙያ አክባሪነት

    የማኅበሩ አባላት ባላቸው ልዩ ልዩ ሙያ /ዕውቀት/ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የተሰባሰቡ በመሆናቸው፣ በማኅበሩ አሠራሮች ሁሉ ከኦርቶዶክሳዊው ትምህርተ ሃይማኖት ጋር በማይጋጩ በእውነተኛ መረጃ ለሚደገፉ ሙያዊ ምክረ ሐሳቦች ተገቢውን ክብርና ቅድሚያ ይሰጣል:: በቤተ ክርስቲያንም ለመንፈሳዊ እና ለዘመናዊው (አስኳላ) ሙያ ተገቢው ክብር እንዲሰጥ ይሠራል::
  • ምክንያታዊ ሞጋችነት

    ማኅበሩ በእውነተኛ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ቤተ ክርስቲያንን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚፈትኑ አስተሳሰቦችን፣ አሠራሮችን፣ ልማዶችን እና ትርክቶችን በግልጽና በመንፈሳዊ ጥብዓት እና በእውነት እንዲሞገቱና መፍትሔ ላይ እንዲደረስ ይሠራል::
  • ተጠያቂነት

    የማኅበሩ አገልግሎት ግብ ሰማያዊ ዋጋ ማግኘት ስለሆነ ኀላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት በእግዚአብሔር እና በሰዎች ዘንድ የሚያስጠይቅ በመሆኑ በየትኛውም እርከን ላይ ያለ አባል እና አመራር በማኅበሩ አሠራር መሠረት በተሰጠው ኀላፊነት ተጠያቂ ይሆናል፡፡

ዓላማዎች

  • የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ አስተዳደር፣ የአሠራር ሥርዐትና አስተሳሰብ፣ በቴክኖሎጂ እና በልዩ ልዩ መንገዶች በመደገፍ ዘመኑን ለዋጀ ጠንካራ አገልግሎት ማብቃት፤
  • የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ሙሉ ሰብእናን የሚገነባ ሥርዐተ ትምህርት በማስተማር ዘመኑን የዋጁ ምሉዕ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር የሚያገለግሉ እንዲሁም በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ በፖለቲካዊ እና በሀገር አስተዳደር ጉዳዮች መሪ/ንቁ ተሳታፊ አገልጋዮችን ማፍራት እና ማሠማራት፤
  • የተተኪውን ትውልድ ምንጭ ለማጎልበት የሰ/ት/ቤቶችን አቅም በማጠናከር የሕጻናት እና የወጣቶችን የተተኪነት ሚና ማሳደግ፤
  • ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነትን በተግባር የሚገልጽ ቤተሰብ እና አንድነቱን የጠበቀ ኦርቶዶክሳዊ ማኅበረሰብ በመገንባት የተደራጀ እና የተናበበ አገልግሎት መስጠት፤
  • በተደራጀ እና ተደራሹን ማእከል ባደረገ መንገድ ስብከተ ወንጌልንና ሐዋርያዊ ተልእኮን ዘርፈ ብዙ በሆኑ መንገዶች በመላው ዓለም ማስፋፋት፤
  • በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚነዙትን የርእዮተ ዓለም፣ የሐሰት ትርክቶች እና የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን እንቅስቃሴ ጥናት እና ምርምር ላይ ተመርኩዞ መሞገት እና የተሳሳቱትን በማረም፣ በጠንካራ የዕቅበተ እምነት አገልግሎት የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ማስጠበቅ፤
  • በተመረጡ ገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች የልኅቀት ማእከል እና የተለየ ክርስቲያናዊ ተልእኮ የሚፈጽሙ እንዲሆኑ የሚያስችል ሁለገብ የአእምሮ ልማት ድጋፍ ማድረግ፤
  • ማኅበሩ ዘመኑን የዋጀ ተቋማዊ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ተልእኮውን ማሳካት የሚችልበት አቅም መፍጥር ( በአመራር፣ በሰው ኃይል፣ በመንፈሳዊነት፣ በግንኙነት፣ በዕውቀት፣በልማት፣ በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ)፤
  • ዓለም አቀፍ ግንኙነትና የትብብር አገልግሎትን መርሕ ያደረገ የኦርቶዶክሳውያን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማሳደግ፣

አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ
የሸዋ ሊቀ ጳጳስ ፲፱፻፴፪-፲፱፻፹፪ዓ.ም.

የማኅበሩ ህንጻ