anoros gedam 5.jpg

አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ

መስከረም 13 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

anoros gedam 5.jpgአቡነ አኖሬዎስ በ13ኛው መ.ክ.ዘ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ናቸው፡፡ ትልቁ አኖሬዎስ ይሏቸዋል፡፡ የአቡነ ዜና ማርቆስ የእኅት ልጅ ናቸው፡፡ አባታቸው ቄስ ሰላማ እናታቸው ክርስቶስ ዘመዳ ሲባሉ የትውልድ ቦታቸው ምዕራብ ሸዋ ሙገር አካባቢ ልዩ ስሙ ማትጌ በሚባል ቦታ ነው፡፡ ገድለ ዜና ማርቆስ አባቱ ዘርዐ አብርሃም የተባለ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት ዘመድ ነበረ ይላል፡፡

ለአቡነ አኖሬዎስ ወላጆቻቸው ያወጡላቸው ስም ናርዶስ ሲሆን በሕፃንነታቸው የዳዊትን ንባብና የመጻሕፍትን ትርጓሜ ከተማሩ በኋላ በወቅቱ ከነበሩበት ግብፃዊ ጳጳስ ዲቁና ተቀበሉ፡፡ በወቅቱ ሐራንኪስ የተባለ የትርጓሜ መጻሕፍትና የዜማ ዐዋቂ በቤታቸው በእንግድነት ለብዙ ጊዜ በቆየበት ወቅት ለአቡነ አኖሬዎስ ዜማና ትርጓሜ መጻሕፍት በሚገባ አስተምሯቸዋል፡፡ በዚህም ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ ዜማና ትርጓሜ መጻሕፍት የበለጠ ለመረዳት ከነበራቸው ፍላጎት አንጻር ወደ ደብረ አስቦ (ደብረሊባኖስ) በመሔድ ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጋር ተገናኙ፡፡ በደብረ አስቦ (ደብረሊባኖስ) በገዳም ለረዥም ዓመታት ካገለገሉና ከተማሩ በኋላ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት እጅ መንኩሰው አባ አኖሬዎስ ተባሉ፡፡

የገዳሙ መነኮሳት በሊቀ ዲያቆንነት መርጠዋቸው ትርጓሜ መጻሕፍትና ዜማ ያስተምሯቸው ነበር፡፡  ትጋታቸውን ያዩት የገዳሙ መነኮሳትም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት በታች የገዳሙ መጋቢ አድረገው መረጧቸው፡፡ በዚያ ዘመን በገዳሙ ወንዶች እና ሴቶች መነኮሳዪያት በአንድነት ይኖሩ ነበር፡፡ ነገር ግን አቡነ አኖሬዎስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አማክረው የሴትና የወንድ ገዳም እንዲለይ አደረጉ፡፡ ከዚህ በኋላ በወቅቱ በነበሩት አቡነ ቄርሎስ ዘንድ ተልከው ቅስናን ተቀበሉ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካረፉ በኋላ ወደ ትግራይ ጸዐዳ አምባ ተጉዘው ከአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ጋር ቆዩ፡፡ ነገር ግን አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ወዲያው ስላረፉ ወደ ደብረ አስቦ ተመልሰው አበ ምኔቱን እጨጌ ፊልጶስን እየተራዱ ገዳሙን ማገለግሉ ጀመሩ፡፡

anoros gedam 7.jpgበ1317ዓ.ም ንጉሥ ዓምደ ጽዮን በዘመነ መንግሥቱ የስብከተ ወንጌልን መስፋፋት ሥራ አጠናከረ፡፡ ይኸውም ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ ሲያርፉ ወደ ግብፅ ልዑካንን ልኮ አቡነ ያዕቆብን አስመጣ፡፡ በዚህ ወቅት አቡነ ያዕቆብ ከአቡነ ፊልጶስ ጋር በመነጋገር “ኢትዮጵያ በአንድ ጳጳስ መወሰን የለባትም፡፡” በማለት እጨጌ አቡነ ፊልጶስን ኤጲስ ቆጶስነት ሰይመው ሐዋርያዊ አገልግሎት እንዲፈጽሙ ዐሥራ ሁለቱን ንቡራነ ዕድ ለስብከተ ወንጌል በመላዋ አገሪቱ ክርስትና እንዲስፋፋ አቡነ ያዕቆብ ባቀረበው ሀሳብ መሠረት ተሰማሩ፡፡ እነሱም አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ /ኤጲስ ቆጶስ/፣ አቡነ አኖሬዎስ ዘሞረት፣ አቡነ ማትያስ ዘፈጠጋር፣ አቡነ ሳሙኤል ዘወገግ፣አቡነ አኖሬዎስ ዘወረብ፣አቡነ ታዴዎስ ዘጽላልሽ፣አቡነ ገብረ ክርስቶስ ዘግድም፣ አቡነ መርቆሬዎስ ዘመርሐ ቤቴ፣ አቡነ አድኃኒ ዘዳሞት፣ አቡነ ቀውስጦስ ዘመሐግል፣ አቡነ ኢዮስያስ ዘወጅ፣ አቡነ ዮሴፍ ዘእናርያ ነበሩ፡፡

ሀገረ ስብከት ተሰጥቷቸው ለሐዋርያዊ ተልእኮ ተሰማሩ፡፡ ይህ የተቀናጀ የስብከተ ወንጌል ሥምሪት ሲደረግ ከተሰዓቱ ቅዱሳን በኋላ መጀመሪያና ትልቅ ለውጥ ያመጣ ነው፡፡ እነዚህ ዐሥራ ሁለቱ አበው “ንቡረ እድ” የሚል መጠርያ ኖሯቸው ክህነት ከመስጠት ውጭ ያለውን የኤጲስ ቆጶሱን ሥራ ይሠሩ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ለአቡነ አኖሬዎስ እንደ ግብጦን የተባለ ቦታ ደረሳቸው፡፡ ይህ ቦታ ከግንደ በረት እስከ ባሌ ያለውን አገር ያካትታል፡፡ እርሳቸውም ባሌ በመሄድ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ተክለው ክርስትናን አስፋፉ፡፡ የሐዋርያነት አገልግሎታቸው እስከ ኬንያ ድንበር ደርሶ ነበር፡፡

በአካባቢው ስብከተ ወንጌልን ካስፋፉ በኋላ ባርጋባን የተባለ የአካባቢው ሰው ደግነታቸውንና ትምህርታቸውን ተመልክቶ በጽጋጋ ገዳም (ደሴ አካባቢ) እንዲመሠርቱ ጋበዛቸው፡፡ ጽጋጋ እንደ ደረሱ መምለክያነ ጣዖታት በእጅጉ ተቃውመዋቸው ነበር፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በትምህርታቸውና በበርጋባን ረዳትነት ተቃውሞው በረደ፡፡ በርጋባንም በትምህርታቸው ይማረክ እንጂ ክርስቲያን አልነበረምና ተጠምቆ ዘካርያስ ተባለ፡፡ አቡነ አኖሬዎስም የአካባቢውን ሕዝብ ለማስተማር ካላቸው ፍላጎትና የምነና ሕይወትንም ለማጠናከር በጽጋጋ ገዳም መሠረቱ፡፡ በገዳሙ የሚሰበሰቡት መነኮሳትም ቁጥር በየቀኑ ይጨምር ነበር፡፡ ከትውልድ አካባቢያቸውም በየጊዜው ብዙዎች ይመጡ ነበር፡፡

አቡነ አኖሪዎስ ዘወረብ ተብለውም ይጠራሉ፡፡ ይህም ወረብ በሚባለው ሥፍራ በተጋድሎ የቆዩበት ቦታ በመሆኑና ዐፅማቸው በዚያ እንደተቀበረ ይነገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንድ የእስልምና ተከታይ ወረብ ከተባለው አካባቢ የአቡነ አኖሪዎስ ነው ብሎ ያመጣው መስቀል አሁን በጽጋግ ገዳማቸው ይገኛል፡፡

 አቡነ አኖሬዎስ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን 1297-1317 ዓ.ም የአባቱን ዕቁባት ማግባቱን ሰሙ በጉዳዩም እጅግ አዝነው እጨጌ አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ፣ አቡነ ናትናኤል፣ አባ እንድርያስ፣ አባ ድምያኖስ፣ አባ ዮሐንስ፣ አባ ገብረ ናዝራዊ፣ አባ ዘርዐ ክርስቶስ፣ አባ ገብረ አምላክ፣ አባ ብንያም፣ አባ አቡነ አሮን ዘደብረ ዳሬት ይዘው ወደ ንጉሡ ከተማ መጡ፡፡

ንጉሥ ዓምደ ጽዮንም የአባቶችን ድንገት መምጣት አይቶ “ምን አመጣችሁ?” ብሎ ሲጠይቃቸው አቡነ አኖሬዎስ “የአባትህ ዕቁባት እናትህ ማለት ስለሆነች ማግባትህ አግባብ አይደለም፡፡ መኝታህን ማርከስህን ተው፡፡ ያለበለዝያ እንለይሃለን፤ ሥጋ ወደሙንም አናቀብልህም አሉት” ንጉሡም መነኮሳቱን አስደበደባቸው፡፡ ደማቸውም በአደባባይ ፈሰሰ፡፡ በዚያ ዕለት በከተማው እሳት ተነሥቶ እስከ ቤተ መንግሥቱ በመድረሱ ማስደብደቡን ትቶ በአማካሪዎቹ የቀረበለትን ሐሳብ በመቀበል ወደ ሩቅ አገር ለማጋዝ ወሰነ፡፡ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን ይህንን ተግሳጽ ከቁም ነገር አልቆጠረውም ነበር፡፡ ነገር ግን ሥጋወ ደሙ በድፍረት  ሊቀበል በቀረበ ጊዜ አባቶች “የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ” ተብሏል ብለው  ከለከሉት፤ እየተናደደ ወደ ቤተ መንግሥት ገባ፡፡ በቤተ መንግሥቱም ጳጳሱን፣ ንቡራነ እዱንና በአንድ ሐሳብ የጸኑ ሌሎች ሰባ ሁለት ካህናት አስጠርቶ አቡነ ያዕቆብ ከእኔ አያስጥላችሁም፡፡ በአስቸኳይ ወደ ሀገሩ(ግብፅ) እልከዋለሁ፡፡ ሲል በቁጣ ተናገራቸው፡፡ እነርሱ ግን “በቤተ ክርስቲያን ትምህርት መሠረት ኑር፣ የአባትህን ሚስት መፍታት ይገባሃል” ብለው ጸኑበት፡፡

በዚህ ምክንያት አባቶች እየተጋዙ በሰሜን በደቡብና በምዕራብ ኢትዮጵያ ተሰደዱ፡፡ ከእነርሱ ስደት በኋላ ብዙ ካህናትና መነኮሳት ወደ ንጉሡ መጡ፡፡ በድፍረትም ይገሥጹት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት መነኩሴ ወደ ከተማ እንዳይገባ እስከ መከልከል ደርሷል፡፡ በመጨረሻ አባ እንድርያስ የተባሉ አባት ወደ ንጉሡ መጥተው መክረው ንስሐ አስገብተው ወደ ቤተ ክርስቲያን መለሱት፡፡
አቡነ አኖሬዎስ ወደ ወለቃ /ደቡብ ወሎ ጋሥጫ አካባቢ/ ተጉዘው ለጥቂት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ዓምደ ጽዮን ዐረፈ፡፡ መንግሥቱንም ሰይፈ አርዕድ ወረሰ፡፡ ንጉሥ ሰይፈ አርዕድም የተጋዙት አባቶች በሙሉ እንዲመለሱ ዐወጀ፡፡ አቡነ አኖሬዎስም ወደ በኣታቸው ጽጋጋ ተመለሱ፡፡

ንጉሥ ሰይፈ አርዕድ እንደ አባቱ የአባቱን ዕቁባት ማግባቱን ሰሙ፡፡ ቀድሞ ንጉሥ ዓምደ ጽዮንን የገሰጹት እነዚያ ቅዱሳን አባቶች ተሰባስበው ወደ ንጉሡ መጡ፡፡ አቡነ አኖሬዎስ አፈ ጉባኤ ሆነው ንጉሡን ገሰጹት፡፡ ንጉሡም በወታደሮቹ አስደበደባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ከአፍ እና ከአፍንጫቸው ብዙ ደም ፈሰሰ፡፡ በኋላም ምድረ ጸወን ወደምትባል አገር /ደቡብ ወሎ፣ ቦረና/ ተጋዙ፡፡ በዚያም እጅግ ብዙ ተአምራት ማድረጋቸውና የንጉሡን ተግባር መቃወማቸው ስለተሰማ እንደገና ወደ ዝዋይ ደሴት ገማስቄ በምትባል ሥፍራ እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡

በዝዋይ እያሉም ነገረ ሠሪዎች ወደ ንጉሡ ቀርበው “አኖሬዎስ ሠራዊትህን ሁሉ ማርኮ ሊያመነኩሳቸው ነውና አንድ ነገር አድርግ፡፡” ብለው ስለ መከሩት አቡነ አኖሬዎስ የፊጥኝ በወታደሮች ታስረው እንዲመጡ አደረገና፡፡ ባሌ ግድሞ ወደ ተባለው አገር እንዲጋዙ አደረገ፡፡

እዚያም ለብዙ ዓመታት ገዳም መሥርተው በሐዋርያነት እያገለገሉ ከቆዩ በኋላ ወደ ጥንት በኣታቸው ጽጋጋ እንዲመለሱ ተፈቀደላቸው፡፡ በዚያም በማስተማርና በምነና ሕይወት ሲተጉ ኖሩ፡፡ ኋላም የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ዐፅም በደብረ ሊባኖስ ከሌሎች አበው መነኮሳት ጋር አፍልሰው ከቀበሩ በኋላ በተወለዱ በ104 ዓመታቸው መስከረም 18 ቀን 1471 ዓ.ም በጽጋጋ ገዳማቸው ዐረፉ፡፡ በረከታቸው በሁላችንም ይደር፤ አሜን፡፡

 

  • ምንጭ፡- ገድለ አቡነ አኖሬዎስ፣ ገድለ ተክለ ሃይማኖት፣ የቤተ ክርስቲያን መረጃዎች