የ32ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ ቀረበ

 

ጥቅምት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. 
ከጥቅምት 4 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሔድ የሰነበተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እየተገባደደ ነው፡፡ በዛሬው የከስዓት በፊት መርሐ ግብር ጉባኤው ሲወያይባቸው በሰነበተው ዝርዝር ጉዳዮች ቃለ ጉባኤ በንባብ ተሰምቷል፡፡ በቃለ ጉባኤው ከቀረቡት ዝርዝር የጉባኤው አካሔድ ዘገባ በተጨማሪ ጉባኤው የተስማማባቸውና ቅዱስ ሲኖዶስ ይወስነባቸው ዘንድ የቀረቡ ነጥቦች ተካተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቃለ ጉባኤው በንባብ ከተሰማ በኋላ እንደበፊቱ ጉባኤው ተወያይቶ ማሻሻያ አላደረገባቸውም፡፡ ለዚህም የተሰጠው ምክንያት የጊዜ እጥረት የሚል ሲሆን፤ የጉባኤው አባላትና ተሳታፊዎች በተሰማው ቃለ ጉባኤ ላይ ያላቸውን የማስተካከያና የማሻሻያ ሀሳቦች በጽሑፍ ለቃለ ጉባኤ አርቃቂ ኮሚቴው እንዲሰጡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

በመንበረ ፓትርያርኩ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ላለፉት ዘጠኝ ቀናት ሲካሔድ የሰነበተው ጉባኤ በተቀረጹት ልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ሲወያይ ሰንብቶ የአዳራሹን ጉባኤ ያጠናቀቀ ሲሆን፤ ነገ ጠዋት የጉባኤው አባላትና ተሳታፊዎች በየዓመቱ የሚደረገውን በአገልግሎት ቆይተው ላለፉ ብፁዓን አበው ጸሎተ ፍትሐት በማድረግ ያዘክራል፡፡ በእለቱ ምሽትም ማኅበረ ቅዱሳን በየዓመቱ ያለፉ አበውን ዝክር በማስመልከት ለጉባኤው አባላትና ተሳታፊዎች የእራት ግብዣ ያደርጋል፡፡ ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ. ም. ደግሞ የጉባኤው አባላትና ተሳታፊዎች በቅዱስ ሲኖዶስ መክፈቻ ጸሎት ላይ ተሳትፈው የጉባኤው ፍጻሜ ይሆናል፡፡