ግልጽነትና መገማገም የቤተ ክርስቲያኗ ባሕል መሆን ይገባዋል ተባለ

 

ጥቅምት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. 
ያለንበት ዘመን የግልጽነትና የመገማገም ዘመን ስለሆነ በሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ አካላትና ደረጃዎች ሊለመድ የሚገባው ባሕል እንዲሆን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ገለጹ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ይህንን ያሉት 32ኛው የቤተ ክርስቲያኗ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ በመንበረ ፓትርያርክ ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ሲያካሔድ የነበረውን ጉባኤ የዕለት ውሎ ባጠናቀቀበት ጊዜ ነው፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ የጉባኤውን አጠቃላይ አካሔድ በገመገሙበት ንግግራቸው እንደገለጹት፤ ከወትሮው በተለየ በዘንድሮው ጉባኤ የታዩትን ግልጽ ውይይቶች አድንቀዋል፡፡ “እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ የነፃነት ኅሊና ሰጥቷል” ካሉ በኋላ “አንድ ሰው የፈለገውን እንዲናገር በሥልጣንና በገንዘብ ኃይል መታፈን የለበትም፡፡ ምክንያቱም ካልተናገረ ወደ ሌላ መጥፎ አዝማሚያ ይሔዳልና” በማለት በጉባኤው የነበረውን ግልጽነትና መገማገም አድንቀዋል፡፡ በተነገሩ ነገሮችም ሰዎች ቅሬታ እንዳይገባቸው መክረዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ሌላው ነጥብ በቤተ ክርስቲያኗ ሊስተካከሉ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ነው፡፡ “ሙስናና የገንዘብ ብክነት ይጥፋ፤ ሀቀኝነትና መልካም አስተዳደር ይስፋፋ” ያሉት ቅዱስነታቸው፤ ችግሮቹ በሁሉም ጥረት ካልተቀረፉ ጉዳዮቹ ከቤተ ክርስቲያኗ አልፎ ሀገርን የሚያጠፋ በመሆኑ ከላይ እስከታች ያለው የቤተ ክርሰቲያኗ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በጉባኤው የቀረቡትን ሪፖርቶች በዳሰሱበት የንግግር ክፍላቸውም በጣም አንገብጋቢና ቅዱስ ሲኖዶስ ሊመክርባቸው ይገባቸዋል ያሉትን ጠቃቅሰዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ በምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና በደል እንዲሁም በየአኅጉረ ስብከቱ ያሉ ካርታ አልባ ይዞታዎች በአፋጣኝ ስለሚያገኙበት ሁኔታ የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

“ስብከተ ወንጌል ካልተጠናከረ ቤተ ክርስቲያናችን ትራቆታለች” ያሉት ቅዱስነታቸው የቤተ ክርስቲያኗ ዐቢይ ተልእኮ የሆነው የወንጌል አገልግሎት በየቦታው መጠናከር አለበት ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን የደከሙትን አካላትና ተሳታፊዎች በማመስገን ንግግራቸውን ፈጽመዋል፡፡