የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንደቀጠለ ነው

 

ጥቅምት 8 ቀን 2006 ዓ.ም. 

በእንዳለ ደምስስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሦስተኛው ቀን ውሎው የስብከተ ወንጌል መምሪያ፤ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት፤ እንዲሁም በተለያዩ አኅጉራት የሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡

ከስዓት በኋላም የሃይማኖት መቻቻል በሚል ርዕስ ከፌደራል ጉዳዮች ተወክለው በመጡ ባለሙዎች ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ በሃይማኖት መቻቻል ዙሪያ በቀረበው ጥናት ላይ በመመርኮዝም ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በየሀገረ ስብከታቸው በተከሰቱና አሳሳቢ ናቸው ያሏቸውን ጥያቄዎች በማንሳት ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው? ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለቸው በ34 ዓ.ም. መሆኑን ነው የምናውቀው ያቀረባችሁት ከዚህ ጋር አይቃረንም ወይ? አክራሪዎች መረባቸውን ከላይ ዘርግተዋል መሬት ግን አልነኩም ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው? ቀድሞ መሬቱም ህዝቡም የዐፄው መንግሥት ነበር ብላችኋል አሁንስ የማነው? መቻቻል እስከምን ድረስ ነው? በወለጋ በ3 ወረዳዎች ምእመናን ከፍተኛ በደል እየደረሰባቸው መሆኑንና ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ክርስቲያኖች እየታሠሩ ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን፤ በሰንበት ቀን ካህኑ ብቻ ይቀድስ እናንተ ግን ውጡ ሥራ ሥሩ በማለት ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን እንዲወጡ እየተደረገ ስለመሆኑ፤ በወለጋ ጊምቢና መንዲ በሚባሉ ወረዳዎች ተማሪዎች በመምህራኖቻቸው እየተገደዱ የአንገት ማተባቸው እየተበጠሰ ስለመሆኑ፤ በጋሞጎፋ ሀገረ ስብከት በየዓመቱ የደመራ በዓል የሚከበርበት ቦታ ለሌሎች አሳልፎ በመስጠት በ2005 ዓ.ም. የደመራ በዓል ምእመናንን ሳያከብሩ ማሳለፋቸው፤ በሶማሌ ክልልም ምእመናን ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት የሚያቀርቡት ጥያቄ ውድቅ እየተደረገባቸው መቸገራቸውን፤ የቤተ ክርስቲያን ቃጠሎ በየቦታው እየተስፈፋፋ መምጣቱን፤ . . . የመሳሰሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ከፌደራል ጉዳዮች በመጡት ባለሙያዎችም ለጥያቄዎቹ ምላሸ ሰጥተዋል፡፡ 4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስትና በኢትዮጵያ በመንግሥት ደረጃ በኦፊሴል የታወቀበትና የተስፋፋበትን ለመግለጽ እንደሆነ ያብራሩት ተወካዮቹ በታሪክ ከዩኒቨርስቲ የተመረቁና የተለያዩ መጻሕፍትም ይህንኑ እንደሚያመለክቱ ተናግረዋል፡፡ መሬትን በተመለከተም የመንግሥትና የሕዝብ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በየክልሉና ሀገረ ስብከቶች ተፈጽመዋል ተብለው ስለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱም አንዳንዶቹ በመፈታት ላይ እንደሚገኙ፤ ያልተፈቱትም በመረጃ በማስደገፍ በየክልሉና ወረዳዎች ለሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል፡፡ መንግሥት ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር በቅርበት እየሥራ እንደሚገኝና በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩም ውይይቱ ጠቃሚ መሆኑን በመግልጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው በአራተኛ ቀን ውሎውም የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሪፖርቶች ቀርበዋል፡፡

ከስዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብርም አረንጓዴ ልማት በቤተ ክርስቲያን ትናትና ዛሬ ነገ፤ አነስተኛና ከፍተኛ የሥራ ፈጠራ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፤ እቅድ ክትትልና ግምገማ ለቤተ ክርስቲያን በሚሉ ርዕሰ ጉዳየች ላይ ያተኮሩ ሦስት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

ዝርዝሩን በቀጣይ እናቀርባለን፡፡