se06

32ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እየተካሄደ ነው፡፡

 

ጥቅምት 6 ቀን 2006 ዓ.ም. 

በእንዳለ ደምስስ

 

32ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ጥቅምት 4 ቀን 2006 ዓም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ተጀምሯል፡፡se06

 

በመደበኛ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ የመምሪያ ሓላፊዎች፤ የየሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በመጀመሪያው ቀን ውሎም የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ካህናት ጸሎተ ወንጌል በማድረስ የተጀመረ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ የጉባኤውን መክፈቻ ቃለ በረከት አስተላልፈዋል፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የወላይታ ኮንታ እና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የ2005 ዓ.ም. የሥራ ክንውን አጠቃላይ ሪፖርት በማቅረብ ጉባኤው ቀጥሏል፡፡ ብፁዕነታቸው ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት ውይይት ተካሂዷል፡፡ እያንዳንዱ ሀገረ ስብከትም በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ሪፖርቱን አቅርቧል፡፡

 

የ32ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሁለተኛው ቀን ውሎውም የየሀገረ ስብከት ሪፖርት ሲያደምጥ ውሏል፡፡

 

32ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም. ይጠናቀቃል፡፡