ትንሣኤ /ለሕፃናት/
ሚያዝያ 6/2004 ዓ.ም.
ሚያዝያ 6/2004 ዓ.ም.
ሚያዚያ 1/2004 ዓ.ም.
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? እንኳን ለሰሙነ ሕማማት በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ልጆች ሰሙነ ሕማማት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃላች? ሰሙነ ሕማማት ከትንሣኤ በፊት ያለውን ሳምንት ሲሆን በዚህ ሳምንት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን የሰው ልጆች ለማዳን ሲል የተቀበለውን መከራ ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ የምናስብበት ሳምንት ነው፡፡ ጌታችን በዚህ ሳምንት ውስጥ ባሉት ቀናት ውስጥ የተለያዩ ተግባራት አከናውኗል፡፡ እስኪ ልጆች ቀናቱንና በቀናቱ ውስጥ የተፈጸሙትን ተግባራት በዝርዝር እንመልከት፡-
1. እሑድ /ሆሣዕና/፡- በዚህ ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርቦ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ይከተሉት የነበሩት ሰዎች በተለይም ሕፃናት ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ብለው እየዘመሩ ጌታችንን አመስግነውታል፡፡
– ልጆች በዚህ ዕለት ማር.11÷12-19 እና ሉቃ.19÷45-46 ላይ የሚገኘውን የወንጌል ክፍል አንብቡ፡፡
– በዚህ ዕለት ዮሐ.18÷1-12፣ ሉቃ.22÷7-53፣ ማቴ.26÷17 ላይ የሚገኘውን የወንጌል ክፍል አንብቡ፡፡
መጋቢት 28/2004 ዓ.ም.
በልያ አበበ
ልጆች የዕረፍት ጊዜያችሁ ወይም የጨዋታ ሰዓት ሲደርስ በጣም ትደሰታላችሁ አይደል? እኔና ዘመዶቼ ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ሰዎችን በማገልገል እነርሱንና ዕቃዎቻቸው ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ ስንለፋ እና ስንደክም የምንኖር ቢሆንም በዓመቱ ውስጥ ግን ልክ እንደሰዎች እጅግ ተደስተንባቸው የምናሳለፋቸው በዓላት አሉ፡፡
አንደኛው በዓል የሁላችን ፈጣሪ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነው ለዚያ ቀን እርሱ ቤተልሔም በሚገኝ የዘመዶቻችን ቤት /በሰዎች አጠራር በረት/ ውስጥ ሲወለድ አንደኛ በትሕትና በእንስሳት ቤት ለመወለድ በመምረጡ ሁለተኛ እጅግ ብርዳማ በነበረው የልደቱ ዕለት የእኛ ዘመዶች የሰው ልጆች እንኳን ያላደረጉትን በትንፋሻቸው እንዲሞቀው ስላደረጉ በጣም ደስተኞች ነን፡፡
ስሜ ደስተኛዋ አህይት ነው፡፡ አሁን የምነግራችሁ በሕይወቴ እጅግ የተደሰትኩበትና እኔና ዘመዶቼ እስካሁን የምንወደውን ሌላኛውን ቀን ነው፡፡ ቀደም ብዬ የነገርኳችሁን የቤተልሔሙን ልደት የነገረችኝ አንደኛዋ አክስቴ አህያ ናት፡፡ ሁል ጊዜም ያንን ታሪክ እንደ አክስቴ እኔም በቤተልሔም በረት ውስጥ በነበርኩ እል ነበር፡፡
ያ ቤተልሔም በሚኖሩ ዘመዶቻችን ቤት የተወለደው የዓለም ሁሉ ፈጣሪ እኛ እንኖርበት በነበረው ሀገር ለ30 ዓመት ከኖረ በኋላ የሀገራችን ሰዎች ሁሉ ማስተማር ጀመረ፡፡
እኔና እናቴ የምንኖረው ደብረ ዘይት ቤተ ፋጌ ከሚባለው ቦታ ጥቂት እንደተሔደ በምትገኘው ትንሽ መንደር ነበር፡፡ የእኛ ባለቤት የሆነው ሰው ፈጣሪያችን በትንሽዬዋ የእንስሳት ቤት ሲወለድ የተደረጉትን ነገሮች ማለቴ የእረኞችና የመላእክትን ዝማሬ የሦስቱ ነገሥታት ስጦታን ማምጣት ሰምቶ ስለነበር ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ቦታ ሁሉ እየሔደ ይማር እጅግም ይወደው ነበር፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ምን ሆነ መሰላችሁ፡፡ እናቴ ባለቤታችን አንድ ሁል ጊዜው ለብርቱ ሥራ ሊፈልገን ስለሚችል ብላ በጠዋት ቀሰቀሰችኝ፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ ሌላ ቀን ስትቀሰቅሰኝ ተኝቼ ማርፈድ የሚያምረኝ ቢሆንም የዚያን ቀን ወዲያውኑ ነበር የተነሣሁት፡፡ ፊቴን ከታጠብኩ እና ሰውነቴ ላይ ያለውን አቧራ ካራገፍኩ በኋላ ከእናቴ ጋር ሆነን ለዛ ቀን ያደረሰንን እና ጣፋጯን የጠዋት ፀሐይ እንድንሞቅ ላደረገው ፈጣሪያችን ጮክ ብለን እየጮህን ምስጋና አቀረብን፡፡
አሳዳሪያችን ከበረታችን አውጥቶ የቤቱ በር ላይ ባለ የእንጨት ምሰሶ ላይ አሰረንና ወደ ሌሎች ሥራዎች ተሰማራ፡፡ አሳዳሪያችን እንዲህ የሚያደርገው እርሱ ወደገበያ የማይወጣ እኛንም የሚያሥረን ሥራ ከሌለው ነው፡፡ እኔም እናቴም ቀኑን በሙሉ በማናውቀው ምክንያት ደስ ሲለን ዋለ፡፡
የሆነ ሰዓት ላይ ከሩቅ ሁለት ሰዎች ወደ እኛ መንደር ሲመጡ አየናቸው፡፡ ሰዎቹ እየቀረቡ መጡና እኛ ጋር ሲደርሱ አጎንብሰው የታሠርንበትን ገመድ ፈቱልን፡፡ ሰዎቹ ለጌታችን ፈጣሪያችን እንደሚፈልገን ነገሩን፡፡ እኛም በደስታ አብረናቸው ሔድን፡፡
ፈጣሪያችን ወደነበረበት ስንደርስ ምን እንደተደረገ ልንገራችሁ? ፈጣሪያችን በእኔ ላይ ልብስ ተነጥፎለት ተቀመጠና ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ ጀመርን፡፡ ምን ያህል እንደተደሰትኩ ልነግራችሁ አልችልም፡፡ በመንገድ የምናገኛቸው ሰዎች በሙሉ ሆሣዕና በአርያም እያሉ እየዘመሩ ልብሶቻቸውና የዘንባባ ዝንጣፊ በምናልፍበት መንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፡፡ ትንንሽ ሕፃናትም በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እያሉ ዘመሩ፡፡ ትልልቆቹ መምህራን ግን ልጆቹን ተቆጥተው ዝም በሉ አሏአቸው፡፡ ነገር ግን አንድ ተአምራዊ ነገር ተከሰተ፡፡ በመንገድ ላይ የነበሩ ድንጋዮች ሁሉ ልክ እንደ ሰው መዘመርና ፈጣሪያችንን ማመስገን ጀመሩ፡፡
ልጆች በዚያን ቀን ፈጣሪዬን በጀርባዬ ተሸክሜ 16 ምዕራፍ ያክል ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ወሰድኩት ታዲያ ይህንን ቀን እኛ አህዮችና ሌሎችም እንስሳት በታላቅ ደስታ እናከብረዋለን፡፡ ሆሣዕና ሕፃናት ፈጣሪያችንን ያመሰገኑበት ቀን ስለሆነ በቤተ ክርስቲያን ተገኝታችሁ አክብሩት እሺ ልጆች፡፡
መጋቢት 21 2004ዓ.ም
በቴዎድሮስ እሸቱ
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? መልካም ይኸው ዘወረደ ብለን በመጀመሪያው ሳምንት የጀመርነው ጾም ዛሬ ኒቆዲሞስ ላይ ደርሷል፡፡ ኒቆዲሞስ የ7ኛው ሳምንት መጠሪያ ነው፡፡
ልጆች የአይሁድ መምህር የሆነ አንድ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው ነበር፡፡ ይህ የአይሁድ መምህር ማታ ማታ እየመጣ ከክርስቶስ እግር ስር ቁጭ ብሎ ትምህርት ይማር ነበር፡፡ ልጆች ማታ ማታ እየመጣ የሚማረው ለምን መሰላችሁ፡፡
አንደኛ የአይሁድ መምህር ስለሆነ ሲማር እንዳያዩት ነው፡፡ ሲማር ካዩት ገና ሳይማር ነው እንዴ የሚያስተምረን እንዳይሉት፡፡ ሁለተኛ አይሁድ ክርስቶስን ያመነና የተከተለ ከሀገራችን /ከምኲራባችን/ ይባረራል ብለው ስለነበር እንዳይባረር ፈርቶ ሦስተኛ ደግሞ ሌሊት ሲማሩ ምንም የሚረብሽና ዐሳብን የሚሰርቅ ነገር ስለሌለ ትምህርት በደንብ ይበገባል ብሎ በማሰብ ነው፡፡ እናንተስ በሌሊት ትምህርታችሁን የምታጠኑት እንዲገባችሁ አይደል ልጆች? በሌሊት ዐሳባችሁ አይበተንም፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ማታ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ስለ ጥምቀት አስተማረው፡፡ “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔር መንግሥት ሊወርስ አይችልም” አለው፡፡ ኒቆዲሞስም “ሰው ከሸመገለ ካረጀ በኋላ እንዴት ድጋሚ ሊወለድ ይችላል” ብሎ ጠየቀ ክርስቶስ ዳግም ልደት ማለት ሰው በጥምቀት የሚያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት እንደሆነ ሰው ተጠምቆ የእግዚአብሔር ልጅ ካልሆነ መንግሥተ ሰማያትን እንደማይወርስ አስተማረው፡፡ ኒቆዲሞስም ስለ ጥምቀት በሚገባ ተረዳ፡፡
አያችሁ ልጆች እንግዲህ በዚህ ሳምንት ከሚነገረው ታሪክ በርካታ ቁም ነገሮችን እናገኛለን ለምሳሌ እኛ ልጆች የእግዚአብሔርን ቃል ቀን ከሌሊት ሳንል ሁል ጊዜ መማር እንዳለብን፤ ያልገባን ነገር ካለ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ጠይቀን መረዳት እንዳለብን ነው፡፡ እንደዚህ በማድረግ ስለ እምነታችን በቂ እውቀት ልንጨብጥ ይገባናል ማለት ነው፡፡ ለዛሬ አበቃሁ ደህና ሰንብቱ፡፡
መጋቢት 14/2004 ዓ.ም.
በቴዎድሮስ እሸቱ
ደህና ሰነበታችሁ ልጆች? እንዴት ናችሁ? በጾሙ እየበረታችሁ ነው አይደል? ጎበዞች፡፡ ዛሬ ስድስተኛው ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ ሳምንት ገብርኄር ይባላል፡፡ ገብርኄር ማለት ልጆች መልካም አገልጋይ ማለት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት በቤተ ክርስቲያናችን ክርስቶስ ስለመልካም አገልጋይ ያስተማረው ትምህርት ይነገራል፡፡ ይህን የተመለከተ ምስጋናም ይቀርባል፡፡
አንድ ባለጸጋ አገልጋዮቹን ያስጠራቸውና ለአንኛው 5 መክሊት ለሁለተኛው 2 መክሊት ለሦስተኛው ደግሞ 1 መክሊት ወርቅ ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚያም እኔ እስክመጣ በዚህ ወርቅ በመነገድ ተጠቀሙ ብሏቸው ወደሩቅ ሀገር ይሔዳል፡፡ ልጆች መክሊት የወርቅ መለኪያ /መስፈሪያ/ ነው፡፡
ይህም ባለጸጋ ከሔደበት ሀገረ ብዙ ከቆየ በኋላ ወደ ሀገሩ ይመለስና ወርቅ የሰጣቸውን ሰዎች በመጥራት ስለንግዳቸው ይጠይቃቸዋል፡፡ አምስት የተሰጠው አገልጋይ ሌላ አምስት መክሊት አትርፌአለሁ አለው፡፡ ጌታውም አንተ መልካም አገልጋይ ነህ ወርቁን ከነትርፉ ውሰድ ወደጌታህም ደስታ ግባ አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተሰጠውም ሌላ ሁለት መክሊት እንዳተረፈ ተናገረ ጌታው እሱንም አንተም መልካም አገልጋይ ነህ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሀለሁ ወደጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ በመጨረሻም አንድ መክሊት የተሰጠው አገልጋይ መጣ እንዲህም አለ “ጌታዬ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ ያልበተንከውን የምትሰበስብ ክፉ ጌታ መሆንህን አውቃለሁ ስለዚህ ሌቦች እንዳይሠርቁኝ አታላዮች እንዳይቀሙኝ ብዬ መክሊትህን ቀብሬ እስክትመጣ አስቀምጨዋለሁ አሁንም እንካ ይኸው አንድ መክሊትህ” ብሎ ሰጠው፡፡ ጌታውም “አንተ ክፉ አገልጋይ መቼ ነው እኔ ያልዘራሁትን ያጨድኩት፣ ያልበተንኩትን የሰበሰብኩት አሁን ወርቁን ተቀበሉትና ለባለ አምስት መክሊቱ ስጡት እሱን ደግሞ ወደ ዘለዓለም ሃዘንና መከራ ወዳለብት ወደጭለማው አውጥታችሁ ጣሉት” አላቸው፡፡ አገልጋዮችም ይህንን ክፉ አገልጋይ ወደ ጭለማው አውጥተው ጣሉት፡፡
ልጆች እንግዲህ በዚህ ሳምንት የሚነገረው ታሪክ ይህ ነው፡፡ እናንተ ክፉ አገልጋይ እንዳትባሉ ተግታችሁ ሥሩ በሃይማኖት ጠንክሩ እሺ! መልካም ደህና ሰንብቱ፡፡
መጋቢት 06/2004ዓ.ም
በቴዎድሮስ እሸቱ
ልጆች እንኳን ለጾመ እኩሌታው /ለደብረ ዘይት/ በሰላም አደረሳችሁ፡፡ ይህ አምስተኛው ሳምንት ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ የጾሙ እኩሌታ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ በዓል ነው፡፡ ልጆች በዚህ ቀን ጌታ በደብረ ዘይት ስለዳግም ምጽአቱ ያስተማረው ትምህርት ይነገራል፡፡ ጌታ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ለሁሉም እንደየሥራው ለመክፈል፣ በግርማ መንግሥቱ ይመጣል፡፡
በዚህ ዓለም ሰው ከአባት ከእናቱ ተወልዶ ሲወርድ ሲወጣ ኖሮ ይሞታል ሞቶ ግን አይቀርም በዳግም ምፅአት ጊዜ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ደጉ ደግነቱ ክፉውም ክፋቱን ይዞ ይነሣል፡፡ ወንዱ የሰላሳ ዓመት ጎልማሳ፣ ሴቷ የአሥራ አምስት ዓመት ኮረዳ ሆነው ጻድቃን ብርሃን ለብሰው ከፀሐይ 7 እጅ አብርተው፣ ኀጥአን ጨለማ ለብሰው ፍጹም ዲያብሎስን መስለው ይነሣሉ፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ጻድቃንን “ብራብ አብልታችሁኛል ብጠማ አጠጥታችሁኛል ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር ያዘጋጀሁላችሁን መንግሥቴን ውረሱ” ብሎ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸዋል፡፡ ኀጥአንን ደግሞ “ሒዱ ከእኔ ለሰይጣንና ለመልእክተኞቹ ወደተዘጋጀው ዘለዓለማዊ እሳት ግቡ” ብሎ ገሀነምን ያወርሳቸዋል፡፡ ጻድቃን ደስ ይላቸዋል፤ ኀጥአን ግን ያዝናሉ ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፤ እንባቸውን ያፈሳሉ ግን አይጠቅማቸውም፡፡
ልጆች እናንተም በዳግም ምጽአት ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን ከሚላቸው ከጻድቃን ወገን እንድትሆኑ ለተራበ አብሉ፤ አጠጡ፤ ደግ ደግ ሥራ ሥሩ፡፡ ሁላችንንም “ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን ብሎ ከሚጠራቸው ተርታ ያቁመን!
መጋቢት1/2004 ዓ.ም.
እንደምን ሰነበታችሁ? ልጆች ደህና ናችሁ? መልካም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አሁን የአብይ ጾም አራተኛው ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ለቤተ ክርስቲያናችን ይህ ሳምንት መፃጒዕ ይባላል፡፡ በዚህ ሳንምንት በቤተ ክርስቲያን የሚቀርቡ ምስጋናዎች ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረጋችውን ድንቅ ድንቅ ተአምራት /ህሙም መፈወሱን፤ ሙት ማስነሣቱን/ የሚያዘክሩ ናቸው፡፡
መፃጒዕ ማለት ልጆች ድውይ፣ ሕመምተኛ ማለት ነው፡፡ በኢየሩሳሌም አንዲት ቤተሳይዳ ተብላ የምትጠራ የመጠመቂያ ቦታ ነበረች፡፡ ይህቺ የመጠመቂያ ቦታ ጠዋት ጠዋት የእግዚአብሔር መልአክ በክንፉ ያማታታል፣ ያናውጣታል፡፡ በዚህ ሰዓት ወዲያውኑ ገብቶ የተጠመቀ ካለበት በሽታ ሁሉ ይድናል፤ ይፈወሳል፡፡
በዚህች የመጠመቂያ ቦታ 38 ዓመት ሙሉ የተኛ በሽተኛ ነበር ከአልጋው መነሣት ስለማይችል መልአኩ ውኃውን ሲያማታው ቀድሞ መግባትና መጠመቅ አልቻለም ከዕለታት አንድ ቀን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ሲያልፍ ይህንን መፃጒዕ /ድውይ/ አየውና “ልትድን ትወዳለህን?” አለው ያም መፃጒዕ “ጌታ ሆይ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ሌላው ቀድሞኝ እየገባ ይፈወሳል፡፡ “አለው ጌታችንም ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ አለው ያም መፃጒዕ ዳነና 38 ዓመት ሙሉ ተኝቶባት የነበረችውን አልጋ ተሸክሞ ወደ ቤቱ ሔደ ዮሐ.5፥1-9
በሉ ልጆች በሚቀጥለው ሳምንት ስለተከታዩ የአብይ ጾም ሳምንት ይዤላችሁ እመጣለሁ እስከዚያው መልካም የጾም ሳምንት ደህና ሰንብቱ፡፡
የካቲት 8/2004 ዓ.ም.
ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ ከዚህ በታች ያለውን ተረት በደንብ አንብቡ በርካታ ቁም ነገሮችን ታገኙበታላችሁ መልካም ንባብ፡፡
ከእለታት አንድ ቀን በአንድ ሀገር የሚኖር ሰው ነበር ይህ ሰው ዘጠኝ ልጆች ሲኖሩት ሁሉም እርስ በራሳቸው የማይዋደዱ የማይስማሙ ነበሩ ሁሉም አባታቸው የሚያወርሳቸውን የራሳቸውን ድርሻ ይዘው ለብቻቸው መኖር ይፈልጉ ነበር፡፡ ከዚያም አንድ ቀን አባታቸው በጠና ታሞ አልጋ ላይ ተኛ ልጆቹንም ጠራቸውና አንድ ትእዛዝ አዘዛቸው ትእዛዙም “ሁላችሁም ሒዱና ለየራሳችሁ አንድ አንድ ጭራሮ ይዛችሁ ኑ” የሚል ነበር፡፡ ከዚያም ልጆቹ ወደውጪ ሔደው ለየራሳቸው አንድ አንድ ጭራሮ ይዘው ተመለሱ፡፡
አባታቸውም ታላቁን ልጅ ጠርቶ የያዝከውን ጭራሮ ስበረው አለው ታላቁ ልጅም ጭራሮዋን ቀሽ አድርጎ ሰበራት እንዲህ እንዲህ እያሉ ሁሉም ልጆች የየራሳቸውን ጭራሮዎች ሰበሯቸው፡፡ ከዚያም አባትየው ትልቁን ልጅ ጠራውና የሁሉንም ወንድሞችህን ጭራሮ ሰብስብ አለው፡፡ታላቁ ልጅም የሁሉንም ጭራሮ ተቀብሎ ሰብስቦ ያዘ አባትየውም በል አሁን የያዝካቸውን ጭራሮ አንድ ላይ ስበራቸው አለው፡፡
ታላቁ ልጅም ቢሞክር ቢሞክር ቢታገል ጭራሮዎቹን ሊሰብራቸው አልቻለም ሁሉም ልጆች ቢሞክሩ አንድ ላይ የተሰበሰቡትን ጭራሮዎች ሊሰብሯቸው አልቻሉም ከዚያም አባትየው ልጆቹ ወደእርሱ እንዲጠጉ በምልክት ጠራቸውና እንዲህ ብሎ ነገራቸው፡፡
ልጆቼ በመጀመሪያ ሁላችሁም የያዛችኋቸውን ጭራሮዎች በቀላል ሰበራችኋቸው በኋላ ግን አንድ ላይ ሲሰበሰቡ ከእናንተ ውስጥ ማናችሁም ልትሰብሩ አልቻላችሁም፡፡ እናንተም የምትለያዩ ከሆነ አንድ ላይ የማትሆኑ ከሆነ ጠላት በቀላሉ ያጠፋችኋል ሌባ ይዘርፋችኋል፤ ጠንካራና ጎበዝ ልትሆኑ አትችሉም፡፡ አንድ ላይ ከሆናችሁ ግን ማንም አይደፍራችሁም፡፡ አሁን እኔ ልሞት ነው የማወርሳችሁን ሀብት በጋራ ተጠቀሙበት በመካከላችሁ መለያየት እንዳይኖር አደራ አላቸው፡፡ ከዚያም ትንሽ ቆይቶ ሞተ እነሱም ከዚያች ዕለት በኋላ ሳይጣሉ እርስ በእርስ በመዋደድ በፍቅር አንድ ላይ መኖር ጀመሩ ተባብረው ስለሚሠሩም ሀብታምና ጠንካሮች መሆን ቻሉ፡፡
ልጆቼ እነዚህ ወንድማማቾች ባይተባበሩ ኖሮ ጠንካሮች መሆን አይችሉም ጠላትም በቀላሉ ያጠቃቸዋል፡፡ እናንተም ከጓደኞቻችሁ በመጠየቅ ለጓደኞቻችሁ የምታውቁትን በማስረዳት ልትተባበሩ ይገባል በትብብር ስታጠኑ የሚከብዳችሁ ሁሉ ይቀላችኋል፡፡
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች ዛሬ ከ12ቱ አርድእት አንዱ ስለሆነው ስለ ቅዱስ በርናባስ ታሪክ በአጭሩ እጽፍላችኋለሁ፡፡
በርናባስ ማለት የስሙ ትርጉም ወልደ ፍስሐ የደስታ ልጅ ማለት ነው የተወለደው ቆጵሮስ በሚባል አገር ነው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአረገ በኋላ ሀብት ንብረቱን በመሸጥ ለሐዋርያት ሰጥቶአቸዋል፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ክርስትና ዓለም ሲጠራ ከሐዋርያት ጋር ያስተዋወቀው እርሱ ነው፡፡ ከቅዱስ ጳውሎስም ጋር በመሆን በልጥራን ያስተምሩ በነበረበት ወቅት አንድ ሕመምተኛ ፈወሱ፡፡ በዚህ ጊዜ የአካባቢው ነዋሪ አማልክት በሰው አምሳል ወደ እኛ ወረዱ ኑ መስዋእት እንሠዋላቸው ብለው ላም ይጎትቱ ጀመር፡፡ እነ ቅዱስ በርናባስም እኛ እንደ እናንተ የምንምት ሰዎች ነን ተው ብለው ከለከሏቸው የዚያ ሀገር ሰዎችም ስማቸውን ቀይረው ቅዱስ በርናባስን ድያ ጳውሎስን ሄርሜን ብለው ሰይመዋቸዋል፡፡
ቅዱስ በርናባስም እንዲህ ከሀገር ሀገር እየተዘዋወረ ሲያስተምር ኖሮ ሕዝበ ክርስቲያኑን ለመጎብኘት ቅዱስ ማርቆስን አስከትሎ ወደ ቆጵሮስ በመመለስ ማስተማር ጀመረ፡፡ ከቆጵሮስ በተጨማሪም ሶርያንና ዲልቅያን ጨምሮ ሲያስተምር አሕዛብ /የማያምኑ/ ጠልተው፤ ተመቅኝተው በድንጋይ በመውገር ነፍሱን ከሥጋው ከለዩ በኋላ ከእሳት ጣሉት፡፡ እሳቱ ግን ሥጋውን ሳያቃጥለው ቅዱስ ማርቆስ አንሥቶ ቀብሮታል፡፡
ጥር 29/2004 ዓ.ም
አንድ ቀን እግዚአብሔር ዮናስ ወደ ተባለ ሰው መጥቶ “ተነሥተህ ወደ ነነዌ ከተማ ሒድ፤ ሕዝቡ ኀጢአት ስለሠሩ ልቀጣቸው ነው፡፡ ነገር ግን አንተ ሔደህ ካስተማርካቸው እና እነሱም ከጥፋታቸው ከተመለሱ እምራቸዋለሁ፡፡” አለው ዮናስ ግን ወደ እነርሱ ሔዶ እግዚአብሔር የነገረውን ቢነግራቸው ይጎዱኛል ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ያዘዘውን መልእክት ላይናገር ወስኖ ተርሴስ ወደምትባል ሀገር ለመሸሽ ፈለገ፡፡ እግዚአብሔር እርሱን ፈልጎ እንደማያገኘውም አሰበ፡፡ ነገር ግን ማንም ከእግዚአብሔር መሸሽ አይችልም፡፡ ዮናስ ግን ይህን አላወቀም ነበር፡፡
ዮናስ በመርከቧ ላይ ሳለ ከባድ አውሎ ነፋስ ተነሣ፡፡ የመርከቧ ተሳፋሪዎች በሙሉ ተጨነቁ መርከቧ ከተገለበጠች እንዳይሞቱ አሰቡና እግዚአብሔር እንዲረዳቸው ጸለዩ፡፡ ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ሸሽቶ መምጣቱን አሰበ እሱን ወደ ውኃው ቢወረውሩት አውሎ ንፋሱ እንደሚቆም ነገራቸው፡፡ ሰዎቹ በጣም አዘኑ ነገር ግን መርከቧ እንዳትሰምጥባቸው ዮናስን ወደ ባሕሩ ወረወሩት፡፡ ዮናስ በውኃው ውስጥ እንዲሞት ግን እግዚአብሔር አልተወውም፡፡ ዮናስን ሳይጎዳው እንዲውጠው ዓሣ አንበሪ ላከ፡፡ ከሦስት ቀን በኋላ ዓሣ አንበሪው እየዋኘ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወጥቶ ዮናስን ተፋው፡፡ ከተፋው በኋላ እግዚአብሔር ዮናስ ወደ ነነዌ ሔዶ እንዲያስተምራቸው በድጋሚ ነገረው፡፡ ዮናስም ወደ ነነዌ ሔደ እግዚአብሔር የነገረውን ነገራቸው፡፡ ሰዎቹም ሰሙት፡፡ በነነዌ የነገሠው ንጉሥ የዮናስን ትምህርት በሰማ ጊዜ ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፡፡ ሕፃን፣ ሽማግሌ ሳይሉ እንስሳትም ሳይቀሩ ለሦስት ቀን እንዲጦሙ እና እንዲጸልዩ አዘዘ፡፡ ሕዝቡም ሁሉም ሦስት ቀን ጦሙ ጸለዩ፡፡ እግዚአብሔርም ሕዝቡ በጥፋታቸው ስለተጸጸቱ እና ስለጦሙ ከጥፋት አዳናቸው፡፡
ከታሪኩ የምንረዳው፡-