የግቢ ጉባኤ አባል (CGPA) 4.00 ነጥብ በማምጣት የዓመቱ የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነ።
በማኅበረ ቅዱሳን ባሌ ሮቤ ማእከል የጎባ ወረዳ ማእከል በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ግቢ ጉባኤ 82 ተማሪዎች በጎባ ደብረ ሰላም ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሰኔ 21 ቀን 2018 ዓ.ም በአባቶች ቡራኬ አሰመርቋል።
ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል በግቢ ጉባኤው በሥራ አሰፈጻሚነት ሲያገለግል የነበረው ተማሪ ቶልቻ ከበደ በነርሲንግ የትምህርት መስክ ከ39 ኮርሶች 25ቱን ‘A+’ እና ቀሪውን ‘A’ በማስመዝገብ አጠቃላይ (CGPA) 4.00 ነጥብ በማምጣት የዓመቱ የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
በተጨማሪም ተማሪ ሚኪያስ ገዛኸኝ (CGPA) 3.88 በክሊኒካል ፋርማሲ ከስኩል ኦፍሜዲሲን ከፍተኛውን ውጤት በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
ለዚህ ውጤት ያብቃኝ በግቢ ጉባኤ ውስጥ በጸሎት የእግዚአብሔርን እርዳታ፣ የቅድስት ድንጌል ማርያም ምልጃ እና እገዛ ነው ያለው የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚው ተማሪ ቶልቻ ከበደ ሲሆን በግቢ ጉባኤ ቆየታችን በዓለም እንዳንጠፋ እያስተማሩን ለዚህ ክብር ያበቁኝ የግቢ ጉባኤውን አመራሮች አመሰግናለው ብሏል።
ተማሪ ቶልቻ አክሎ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች ወደ ግቢ ጉባኤ ገብተው በመማር ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አለባቸው በማለት ምክሩን የለገሰ ሲሆን ተማሪው ከፍተኛ ውጤት በማምጣቱም የማስተርስ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል።
በማኅበረ ቅዱሳን ጎባ ወረዳ ማእከል የግቢ ጉባኤ ክፍል ተጠሪ መምህር ፍቃዱ “አዲሱን የሕይወት ጉዞ በምትጀምሩበት ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን አትለዩ። የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ የማስፈጸም ተስፋ እናንተ ናችሁ። የገባችሁትን ቃል ኪዳን አትርሱ። በመጪው ዘመን በሁሉም መልካም ሥራ እንድትበረቱ እንመኛለን። እናንተም እዚህ የምትቀሩ ደግሞ ከወንድሞቻችሁ መልካም አርአያ ውሰዱ።” ሲሉ የዕለቱን መልእክት አስተላልፈዋል።
በዕለቱም የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ሳህል ቀሲስ ዳኛቸው የተገኙ ሲሆን የስብከተ ወንጌል፣ የመዝሙር መርሐ ግብር ቀርቦ የአደራ መስቀል ለተመራቂዎች በመስጠት እና ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ግቢ ጉባኤ ሥጦታ ተበርክቶ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።
ዘገባው በማኅበረ ቅዱሳን የባሌ ሮቤ ማእከል ሚዲያ ነው።
