‹‹እነሆ በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥም አገኘነው›› (መዝ.፻፴፩፥፮)

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለከበረው ጤንነታችሁ እንዴት አላችሁ! ነቢየ እግዚአብሔር ንጉሥ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹እነሆ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም፤ አያንቀላፋምም…›› (መዝ. ፻፳፩፥፬) በማለት እንደተናገረው ሁል ጊዜ ከክፉ የሚጠብቀን ፈጣያችን በቸርነቱ ለዚህ አድርሶናልና ምስጋና ይድረሰው አሜን!

ልጆች! ትምህርት እንዴት ነው? እየበረታችሁ ነውን? መልካም፤ በርቱ!

ልጆች! ወላጆቻችን ለትምህርት የሚያስፈልገወን ሁሉ አሟልተው፣ እንዳንራብና እንዳንጠማ በማለት የምንመገበውንም አዘጋጅተው፣ ልብስና ጫማውን ገዝተው በማልበስ ተማሪ ቤት የሚልኩን እኛ የማናውቀውን በትምህርት ዐውቀን በምድር ላይ ስንኖር በተማርነው ትምህርት መልካም እንድንሠራበት ነው፡፡ ስለዚህም በርቱና ተማሩ! መቼም ሁላችንም ስናድግ መሆን የምንፈልገው ነገር አለ፤ ያም ምኞታችን የሚሳካው ታዲያ ጠንክረን ስንማር ነውና ለትምህርታችን ትኩረት ሰጥተን እንማር!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በቀን ውስጥ ያሉንን ሰዓታት ብንከፋፍላቸው የትምህርት ጊዜ፣ ወደ ሰንብት ትምህርት ቤት የምንሄድበት ጊዜ፣ የጥናት ጊዜ፣ እንደ አቅማችን ቤተሰብ የምናግዝበት (ቤት ውስጥ ቀለል ያሉ ሥራዎችን) የምንሠራበት ጊዜ፣ መንፈሳዊ መጻሕፍት የምናነብበት ጊዜ ብለን ይገባናል፡፡፡፡ ይህ ለነገው ኑሮአችን ትልቅ ትምህርተ ይሆነናል፡፡ መልካም !!!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ዛሬ የምናስተምራችሁ ስለ ጌታችን አምላካችን ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነው፡፡ በጌታችን መወለድ ዓለም ሁሉ ከነበረበት የጨለማ ሕይወት ወጥቷል፤ ይገርማችኃል ልጆች! አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን በገነት ሲኖሩ እግዚአብሔር ‹‹አትብሉ!›› ብሎ ያዘዛቸወውን እፀ በለስ በሉ፤ ከዚያም ከገነት ወጡ፤ ጠላታችን ሰይጣንም መከራ ያደርስባቸው ጀመር፤ ከዘያም ልጆች አዳምና ሔዋን አለቀሱ፤ ‹‹ማርነን፣ ይቅር በለን›› ብለው እግዚአብሔርን ለመኑት፤ እግዚአበብሔርም አዘነላቸው፤ ከወጡበት ገነት ሊመልሳቸው ቃል ኪዳን ገባላችው፤ ከዚያም ለአዳም ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድናችኋለው ..›› ብሎ ተሰፋ ሰጠው፤ የሰጠው የተስፋ ቃልም መፈጸሚያው ቀኑ ሲደርስ ከእመቤታችን ከቅድስት ደንግል ማርያም ተወለደልንና አዳነን፤ ከጠላታችን ዲያቢሎስም እስራት ነጻ አደረገን፤ ዳግመኛ ልጆቼ አለን፡፡

ልጆች! ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው በቤተልሔም በኤፍራታ ነው፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን ጸንሳው በነበረ ጊዜ በሀገሩ ሕዝቡ እንዲቆጠር አዋጅ ታወጀ፡፡ ከዚያም እመቤታችን ከጻድቁ አገልጋይዋ ከቅዱስ ዮሴፍ ጋር ወደ ቤተልሔም ሄደች፡፡ እዚያም ሲደርሱ ከተለያየ ቦታ ብዙ ሕዝቦች መጥተው ስለነበር ከተማዋ ላይ ለማደሪያ የሚሆን ባዶ ቤት አጡ፡፡ ይገርማችኋል ልጆች! በእንግድነት የሚቀበላቸው ሰው ጠፋ፤ በጣም መሽቶ ስለነበር ቅዱስ ዮሴፍ ለማደሪያ የሚሆን ቦታ ፈልጎ አጣ፤ ከዚያ በኋላ ምን ተገኘ መሰላችሁ? በሬዎች፣ ላሞች፣ በጎች፣ አህያዎች የሚያድሩበት በረት ነበር፤ ሌሊቱ እስኪያልፍ ድረስ በጣም ደክሟቸውም ስለነበር እዚያ ገብተው አረፍ አሉ፤

አስተውሉ ልጆች! እመቤታችን ልጅ የምትወልድበት ጊዜ ደርሶ ስለነበር በበረት ውስጥ የዓለምን ፈጣሪ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችው፡፡ ትዝ ይላችኋል ልጆች? መዝሙር ስንዘምር፥

‹‹በበረት የተኛው ቅዱሱ ሕፃን
ልብስም አልለበሰ ነበር እርቃኑን
የምታለብሰው ልብስ ባታገኝ እናቱ
ትንፋሽ አለበሱት ከበው እንስሳቱ….››

ወቅቱ በጣም ይበርድ ነበርና እንሰሳቱ መጥተው በመክበብ ሙቀት እንዲያገኝ አደረጉ፡፡ የዚህን ጊዜ ታላቅ ብርሃን አካባቢውን አለበሰው፤ ከዚያም ከሰማይ ቅዱሳን መላእክት መጡ፤ ደስ እያላቸው አመሰገኑ፡፡

ልጆች! ጌታችን በተወለደ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገበርኤል ‹‹የምሥራች ደስ ይበላችሁ! የምሥራች!›› እያለ ተኝተው ለነበሩት እረኞች አበሠራቸው፤ እረኞቹ በጣም ደንገጠው ሲነሡ አካባቢው በብርሃን ተሞልቶ አዩ፡፡ ልጆች! ከዚያ ምን አደረጉ መሰላችሁ? መልአኩ እንደነገራቸው ተያይዘው ወደ ቤተልሔም ሄዱ፤ እዚያም ሲደርሱ ገብተው ተመለከቱ፤ እግዚአብሔር ስላደረገላቸው ነገር አመሰገኑ፤ መላእክትም ጌታችንን ‹‹ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ለእጓለ እመሕያው ሥምረቱ፤ ለእግዚአብሔር በሰማይ ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ለሰው ልጆች›› እያሉ አመሰገኑ፡፡
አያችሁ ልጆች! ይህ ሁሉ የተደረገልን ጌታችን በመወለዱ ነው፤ ዳግመኛ ልጆቹ ተባልን፤ ለዚህ እኮ ነው ስንጸልይ ‹‹አባታችን ሆይ..›› እያልን የምንጠራው፤ እርሱ አባታችን ነው፤ እኛ ደግሞ ልጆቹ ነን፤ እናም ልጆች! ጌታችን መወለዱ ለእኛ ደስታ ስለሆነ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገበርኤል ‹‹ደስ ይበላችሁ! ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ተወልዶላችኋል ..›› ብሎ አበሠረን፡፡ ከዚያም ነገሥታት ከተለያየ አገር መጡ ለተወለደው ለጌታችን ሰገዱለት፤ ያመጡትንም ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ ..ሌሎችንም ሥጦታዎች አበረከቱለት፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አምላካችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ ለዓለም ሁሉ ሰላም ሆነ፤ እኛም ታዲያ አባቶቻችን ባቆዩልን ሥርዓት መሠረት ነቢያት የጾሙትን ጾም በመጾም የጌታችንን የልደት በዓል እንቀበላለን፡፡ ታዲያ በዓሉን ስናከብር ካለችን ላይ ቀንሰን የተቸገሩ ወገኖቻችንን እንረዳለን፤ ያለንን እናካፍላለን፤ በጌታችን ልደት ጊዜ ቅዱሳን መላእክትና የሰው ልጆች አብረው ደስ ብሏቸው አመስግነዋል፡፡ ስለዚህ እኛም ይህንን በዓል ስናከብር ደስ ብሎን በትምህርት ቤት፣ በሰፈር ውስጥ ያስቀየምናቸው፣ የተጣላናቸው ልጆች ካሉ ታርቀን በፍቅር በሰላም ሆነን ማክበር አለብን፤ ምክንያቱም የጌታችን ልደት እኛ ይቅርታ ያገኘንበት ጠላታችን ዲያቢሎስ ያፈረበት ቀን ነውና፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ ነቢዩ ክቡር ዳዊት በትንቢት ‹‹..እነሆ በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥም አገኘነው…›› ብሎ እንደተናገረው እኛን ከወደቅንበት ሊያነሣን በትሕትና በቤተልሔም በኤፍራታ እንደተወለደንል እኛም እርሱን አርአያ አድርገን በሕይወታችን ታዛዦች፣ ለሰዎች የምናዝን፣ መልካም ነገርን የምናደርግ አስተዋይና ብልህ፣ ቅን ልጆች ልንሆን ይገባናል፤ አምላካችን ፈጣሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከበዓለ ልደቱ ረድኤት በረከቱን ይክፈለን (ይስጠን) አሜን!!! ቸር ይግጠመን !

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!