ማኅበረ ቅዱሳን እያስገነባ የሚገኘውን የልህቀት ማእከል የመጀመሪያ ዙር የፊኒሺንግ ሥራ ለማከናወን የገንዘብና የዐይነት ድጋፍ ማሰባሰብ መጀመሩን አስታወቀ
ማኅበረ ቅዱሳን ባለፉት 34 ዓመታት በርካታ መንፈሳዊ አገልግሎቶችን በስብከተ ወንጌል፣ በገዳማትና በአብነት ትምህርት ቤቶች፣ በጥናትና ምርምር፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (የዩንቨርስቲ/ኮሌጅ) ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን በማስተማር፣ 24 ሰዓታት የሚዲያ አገልግሎት በመስጠት፣ በመዝሙርና በኪነ ጥበባት፣ በሙያ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን እያከናወነ ይገኛል።
ይህን አገልግሎት በስፋት ተደራሽ ለማድረግ የልህቀት ማእከል እያስገነባ እንደሚገኝ በማኅበረ ቅዱሳን የልህቀት ማእከሉ ግንባታ ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ተሻለ ሞላ ተናግረዋል።
የዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢው አክለውም ትውልድ የሚያንጽበትን ባለ15 ወለል (2B+G+15+T) የልህቀት ማእከል ግንባታ የመጀመሪያ ዙር የፊኒሺግ ሥራ ለመጀመር ሲሚንቶ፣ አሸዋ፣ ብሎኬት፣ ኤሌክትሪክ ገመድ፣ ኮንዲዩትና ሌሎች ማቴሪያሎች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል።
በመጨረሻም የፊኒሺንግ ሥራው በቅርቡ እንደሚጀመር የገለጹት አቶ ተሻለ ሞላ አያይዘውም ይህን ለማከናወን “አንድ የፊኒሺንግ ዕቃ ለነገው ትውልድ” በሚል መሪ ቃል የገንዘብና የዐይነት ድጋፍ ማሰባሰብ የተጀመረ በመሆኑ ለዚህም አገልግሎት አባላትና ደጋፊ አካላት ከታች በተያያዘው ፎርም በመታገዝ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል። 👇👇👇 https://forms.gle/E87npdh8XnWWN3vV7
