ማማተብ

በአስናቀች ታመነ

ሰላም ልጆች እንደምን አላችሁ? ደኅና ናችሁ? መቼም እግዚአብሔር ይመስገን እንዳላችሁ  ተሰፋ አደርጋለሁ፡፡ ልጆች ምንጊዜም ቢሆን እግዚአብሔርን ማመስገን መዘንጋት የለብንም እሺ?  ምክንያቱም እኛ ሰዎች የተፈጠርነው  ለምስጋና ስለሆነ ነው፡፡ ስለሆነም ልጆች በዚህ ክፍል በአጭሩ ሰለ ማማተብ እንማማራለን፡፡ እስኪ ስለማማተብ ምን ታውቃላችሁ ልጆች? የማማተብ ትርጉሙስ ምንድ ነው ትላላችሁ? እንግዲያውስ ዛሬ ስለማማተብ አጭር መርጃ ይዠላችው ቀርቤለሁ፤ መልካም ንባብ ይሁንላችሁ፡፡

ልጆች እኛ ኦርቶዶክሳዊያን ክርስቲያኖች ጠዋት ከእንቅልፋችን ስንነሣ እንዲሁም ጸሎት ስንጀምር ከሁሉ ነገር አስቀድመን እናማትባለን፡፡ በሌላ ሁኔታ ደግሞ ስንደነግጥ በተለይ ክፉ ነገር ሲገጥመን የእግዚአብሔርን ስም ጠርተን እናማትባለን፡፡ በምናማትብ ጊዜም የሚያስጨንቀን ነገር ሁሉ ይወገዳል፤ ኃይለ አጋንንትም ከእኛ ይርቃሉ፡፡

ለመሆኑ የማማተባችን ትርጉም ምንድን ነው ልጆች? ማማተብ ማለት የእጆቻችንን ጣት መስቀለኛ በማድርግ (የ ተ ምልክት) ከላይ ከግንባራችን ተነስተን ወደታች ወደደረታችን ከደረታችን ተነስተን ከግራ ትከሻ ወደ ቀኝ ትከሻችን የምናደርገው ሂደት ነው፡፡ ይህ ሂደትም የራሱ የሆነ ትርጉም አለው፡፡ ልጆች እስኪ ትርጉሙን እንመለክት ደግሞ፡-

1ኛ. ከግንባር (ከላይ ወደ ደረት (ታች) ስናደርግ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት መውረዱና ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን ያስረዳናል፡፡

2ኛ. ከግራ ትከሻ ወደቀኝ ትከሻ፣ ማድረጋችን ደግሞ አምላካችን እና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱና በርኅራኄው በድለው ሲዖል የነበሩ ነፍሳትን ወደ ገነት ያስገባበት ምሳሌ ነው፡፡

እንግዲህ ልጆች እጆቻችን መስቀለኛ በማድረግና በማማትብ ኃይለ አጋንንትን እያራቅን የእግዚአብሔርን ስም ከፍ አድርገን እየጠራን እንደሆነ መረዳት ይኖርባችኋል፡፡ ታዲያ ልጆች ትክክለኛውና ትርጉም ያለው ማማተብ የእጅ ጣትን መስቀለኛ (የ ተ ምልክት) የምናደርገው ነው፡፡ እንዳንድ ሰዎች አውራና ሌባ ጣቶቻችውን በመጠቀም ለየት ባለ ሁኔታ  ያማትባሉ፡፡ ይህ ታድያ ትክክለኛ የማማተብ ሂደት አይደለም፡፡

ልጆች አሁን ትክክለኛውን የማማተብ ሂደት የተረዳችሁ ይመስለኛል፡፡ ታዲያ ልጆች ያወቃችሁትን ላላወቁ ባልንጀሮቻችሁ እንድታካፍሉ በእግዚአብሔር ስም እጠይቃችኋለሁ፡፡ በሉ ልጆች በዚህ ክፍል ይዠላችሁ የቀርበኩት ትምህርት ይህንን ይመስል ነበር፡፡ በሌላ ጊዜ በሌላ ተመሳሳይ ትምህርት እስክንገናኝ ድረስ ደኅና ሁኑ ልጆች፡፡ እግዚአብሔር ሕፃናትንና ወላጆችን ከዘመኑ አስከፊ ወረርሽኝ ይጠብቅልን፡፡ አሜን!!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር