የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ኅዳር ፳፰ ቀን ፳፻፲፬ .

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለተከበረው ጤንነታችሁ እንደምን አላችሁ? ነቢየ እግዚአብሔር ንገሥ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹… እግዚአብሔር ሕፃናትን ይጠብቃል…›› በማለት እንደተናገረው በእግዚአብሔር ጥበቃ በሰላምና በጤና እንደቆያችሁልን ተስፋችን የታመነ ነው፡፡ (መዝ.፻፲፬፥፮)

አዲሱ የትምህርት ዘመን እንዴት ነው? ከወዲሁ በርትታችሁ እየተማራችሁ ነውን? በመንፈሳዊም በሥጋዊም ዕውቀት ማደግ ይኖርባችኋልና በርቱ! በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ሆናችሁ ካደጋችሁ ለራሳችሁ፣ ለቤተሰብ፣ አልፎም ለሀገር ለወገን የምታገለግሉ ብርቱ ፣ጎበዝ ታማኝና አገር ወዳድ መሆን ይገባችኋል፡፡

ልጆች ዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስንመላለስ መፈጸም ስላለብን

‹‹ሥርዓተ  ቤተ ክርስቲያን (የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት)››  ነው፤   ቅድስት   ቤተ ክርስቲያን   ለምታከናውናቸው (ለምትፈጽማቸው) አገልግሎት ሁሉ ሥርዓት አላት፤ እነዚህም ደግሞ የራሳቸው የሆነ ምሥጢር፣ ምሳሌ፣ ምክንያት ያላቸው ናቸው፡፡ በዚህ ዓምዳችን (ርዕሰ ጉዳያችን) ስለ ሥርዓት ምንነት፣ በሥርዓት መመራት (ሕግን ማክበር) እንዳለብንና የሚያስገኝልንን በረከት እንማራለን፤ በአንጻሩ ደግሞ ሕግ ሥርዓት የማያከብሩ የሚደርስባቸውን ቅጣት፣ የሚገጥማቸውን መከራ ተገንዝበን እኛም ሥርዓትን ለመጠበቅ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መመራት ያስፈልገናል! መልካም ንባብ፡፡

ልጆች! ሥርዓት ማለት ምን ማለት ነው? ሥርዓት ማለት ደንብ፣ ሕግ፣ ብያኔ፣ መመሪያ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ማለታችን ደግም በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሠረተች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትመራበት ሕግ፣መመሪያ፣ደንብ ማለታችን ነው፡፡ ልጆች ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት መመራት ማለት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ማክበር ማለት ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ምን ማድረግ እንደሚገባን ሕፃናት፣ ወጣቱ፣ አዛውንቱ ሁላችንም እንደየ ዕድሜአችን ምን ምን መፈጸም እንዳለብን ሥርዓት አለን ማለት ነው፡፡

ልጆች! ሌላው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ማለት የጋራ አገልግሎት ማለት ነው፤  በቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት በአባቶች በካህናት፣ በዲያቆናት፣ በምእመናን (ሕፃን፣ ወጣት አዛውንቱ) በሁላችንም የሚፈጸም የጋራ አገልግሎት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በቅዳሴ ሥርዓት ጸሎት ካህናት አባቶች ጸሎቱን (ቅዳሴውን) ይመሩታል፡፡ ዲያቆናት ደግሞ ያስተባበራሉ፤ ይመራሉ፡፡ ምእመናንን ደግሞ ይሳተፋሉ፤ ይገለገላሉ፡፡ አያችሁ! በሁላችንም የሚፈጸም የጋራ አገልግሎት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሁላችንም የየራሳችን የአገልግሎት ድርሻ አለን፤ በአገልግሎቱ የሁላችንም ተሳትፎ ያስፈልጋል፤ ግን ደግሞ ሁላችንም ድርሻ ድርሻ አለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንግዲህ በጥቂቱ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ በሥርዓት እንድንመራ ያዘዘን ማነው የሚለውን እንመልከት፤ ሥርዓትን የሠራልን በዚህም እንድንመራ ያደረገው ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሲፈጥር ሁሉን በሥርዓትና በቅደም ተከተል ነው፡፡ የተፈጠሩት ፍጥረታት ሁሉ በሥርዓት ይኖራሉ፤ ሥርዓትን አለመጠበቅ እና ሕግን መተላለፍ እንደሌለብን ነቢዩ ንጉሥ ዳዊት መዝሙር እንዲህ ይመክረናል፤ ‹‹..ልጆቼ ግን ሕጌን ቢተው፣  በፍርዴም ባይሄዱ፣ ሥርዓቴንም ቢያረክሱ፣ ትእዛዜንም ባይጠብቁ ኃጢአታቸውን በበትር፣ በደላቸውንም በመቅሠፍት እጎበኛለሁ….›› (መዝ.፹፰፥፴) አያችሁ ልጆች! ሥርዓትን የሠራ እግዚአብሔር በሥርዓት እንድንመራ ያዘናል፤ ስለዚህ ሥርዓትን ጠብቀን በረከትን መቀበል ይገባናል እንጂ ከሥርዓት መውጣት የለብንም፡፡

በሥርዓት መመራት ለምን አስፈለገ? ምንስ ጥቅም አለው? የሚለውን ደግሞ በሚቀጥለው የትምህርት እንመለከታለን፡፡

ልጆች! በሚቀጥለው የትምህርት ክፍለ ጊዜ እስንክንገናኝ ቸር ሰንብቱ!