ልጆች ዘወትር ጸልዩ!

ጥቅምት ፱ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? እግዚአብሔር ይመስገን አላችሁ? መልካም፤ እግዚአብሔር አምላካችን የተመሰገነ ይሁን፡፡

ልጆች የዛሬ ትምህርታችን ስለጸሎት ነው፤ በመጀመሪያም የቃሉን ትርጉም እንመልከት፡፡

ጸሎት ‹‹ጸለየ›› ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ የቃሉ ፍችም  ለመነ፣ተማጸነ ማለት ሲሆን ጸሎት ማለት ልመና ወይንም መማጸን ማለት ነው፤ ጸሎት የሚቀርበው ለእግዚአብሔር ወይም ወደ እግዚአብሔር ነው፡፡

 ጸሎት ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ከብዙዎቹም ውስጥ ጥቂቶቹን እንደሚከተለው እንመለከታለን።

  1. እግዚአብሔርን ለማመስገን ይጠቅመናል፤
  2. በጸሎት በደላችንን እና ኃጢአታችንን ለእግዚአብሔር እንናዘዛለን (እንናገራለን) ይቅርታውንም እንለምናለን፤
  3. ከእግዚአብሔር ዘንድ የፈለግነውንና የጎደለንን ለማግኘትም ያስችለናል፤
  4. የእመቤታችንን እና የቅዱሳንን አማለጅነት ለመለመን እንጸልያለን
  5. መንፈሳዊ ኃይል እንድናገኝ ያስችለናል፡፡

እንግዲህ ጸሎት ይህን ያህል ጥቅም እንዳሉት ከተረዳን  አቡነ ዘበሰማያት (አባታችን ሆይ) በግእዝና በአማርኛ እንጸልያለን፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

አቡነ ዘበሰማያት በግእዝ

፩. አቡነ ዘበሰማያት! ይትቀደስ ስምከ፤ ትምጻእ መንግሥትከ፡፡ ወይኩን ፈቃድከ በከመ በሰማይ ከማሁ በምድር

፪. ሲሳየነ ዘለለ ዕለትነ ሀበነ ዮም

፫. ኅድግ ለነ አበሳነ ወጌጋየነ ከመ ንህነኒ ንኅድግ ለዘአበሰ ለነ፤

፬. ኢታብኣነ እግዚኦ ውስተ መንሱት፡፡ አላ አድኅነነ፥ ወባልሓነ እምኵሉ እኩይ

፭.እስመ ዚኣከ ይእቲ መንግሥት ኃይል፥ ወስብሐት፤ ለዓለመ ዓለም፡፡

በሰላመ ቅዱስ ገብርኤል መልአክ

፩. በሰላመ ገብርኤል መልአክ ኦ እግዝእትየ ማርያም ሰላም ለኪ ድንግል በሕሊናኪ፣ ወድንግል በሥጋኪ

፪. እመ እግዚአብሔር ጸባዖት ሰላም ለኪ

፫.ብሩክት አንቲ እምአንስት ወብሩክ፤ ፍሬ ከርሥኪ፤

፬.ተፈሥሒ ፍሥሕት ኦ ምልዕተ ጸጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ

፭. ሰአሊ ወጸልዪ ምሕረተ ኀበ ፍቁር ወልድኪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ይሥረይ ለነ ኃጣውኢነ።

አባታችን ሆይ በአማርኛ

1.  አባታችን ሆይ፥ በሰማይ የምትኖር፥ ስምህ ይቀደስ፥ መንግሥትህ ትምጣ፥ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ፣ እንዲሁም በምድር ይሁን፣

2.  የዕለት እንጀራችንን ስጠን ለዛሬ፥

3.  በደላችንን ይቅር በለን፥ እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል፥

4.   አቤቱ ወደ ፈተና አታግባን፥ ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ፥

5.   መንግሥት ያንተ ናትና፣ ኃይል፥ ክብር፥ ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን!

በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ

1.  እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ፥ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እንልሻለን። በሐሳብሽ ድንግል ነሽ፥ በሥጋሽም ድንግል ነሽ።

2.  የአሸናፊ የእግዚአብሔር እናት ሆይ ሰላምታ ላንቺ ይገባሻል።

3.  ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፥ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡

4.  ጸጋን የተመላሽ ሆይ! ደስ ይበልሽ፣ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና።

5.  ከተወደደው ልጅሽ ከጌታንችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይቅርታን ለምኝልን፤ ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ለዘለዓለሙ አሜን!

 

ልጆች! እስከ ዛሬ ጸሎት ያልጀመራችሁ ካላችሁ ዛሬውኑ ጀምራችሁ ዘወትር ጥዋት ከእንቅልፋችሁ ስትነሡ፣ ምግብ ከመመገባችሁ በፊትና ተመግባችሁ ስትጨርሱ እንዲሁም ከመኝታ በፊት ጸሎት አድርጉ፡፡ ጸሎት የጀመራችሁ ሕፃናት ደግሞ ሳታቋርጡ ዘወትር ጸልዩ! ይህንን ስታደርጉ አምላካችን እግዚአብሔር ይወዳችኋል፤ ከበሽታም ሁሉ ይጠብቃችኋል እሺ!

በመጨረሻም በቤተ ክርስቲያን ስትጸልዩ እንዴት መጸለይ እንዳለባችሁ በሚቀጥለው ትምህርታችን እናቀርብላችኋለን፤ እስኪዚያው መልካሙንና የተወደደውን ነገር ሁሉ እንመኝላችኋለን፤ ደኅና ሰንብቱ!

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ