የጽዮን ምርኮ – ክፍል አንድ

ኅዳር ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በመምህር ብዙነህ ሺበሺ

በመጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ከምዕራፍ ፬ – ፯ ባለው ክፍል ከሚገኘው ታሪክ ውስጥ የምንረዳው ብዙ ቁም ነገር አለ፡፡ ታሪኩ የእግዚአብሔርን ኀይልና ምሕረት፣ የኀጢአትን አስከፊነት፣ የትዕቢተኞችን ውድቀት፣ የበጎዎችን በረከት፣ የደፋሮችን ጥፋት፣ ወዘተ ያስተምራል፡፡ ከዚህም በላይ ለሐዲስ ኪዳን የድኅነት ሥራ ምሳሌነት ያለው ትምህርትም ነው፡፡ ይህንን ታሪክ በአርእስት ከፋፍለን እንደሚከተለው እንመለከታለን፤

የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት (የታቦተ ጽዮን) መማረክ /፩ኛ ሳሙ. ፬፥፩-፳፪/

እስራኤላውያን ከፍልስጥኤማውያን ጋር በተዋጉ ጊዜ ድል ተነሱ፤ አራት ሺሕ ያህል እስራኤላውያንም ተገደሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሽማግሌዎችም እንዲህ ሲሉ መከሩ ‹‹እኛ ዛሬ በፍልስጥኤማውያን የተመታነችው የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ከእኛ ጋር አብራ ባለመውጣቷ ነው፡፡ ስለዚህ ፍልስጥኤማውያንን ድል እንድንነሳ ታቦተ ጽዮን ትምጣልን፡፡›› የካህኑ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስም ታቦተ ጽዮንን ይዘው መጡ፤ ታቦተ ጽዮን ወደ ሥፍራው ስትደርስም ታላቅ ደስታና ዕልልታ ተደረገ፡፡ የእግዚአብሔርን የኪዳን ታቦት ይዘው ሲወጡ ድል ያደርጉ ነበርና፡፡ ነገር ግን እነርሱ እንደ ጠበቁት ሳይኾን ቀርቶ ሠላሳ ሺሕ የሚሆኑ እስራኤላውያን በጦርነቱ ተገደሉ፤ ሁለቱ የሊቀ ካህናቱ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስም ሞቱ፤ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦትም ተማረከች፡፡ ከጦርነቱ ያመለጠ አንድ ሰው ወደ ከተማው ገብቶ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት እንደ ተማረከች፣ አፍኒንና ፊንሐስም እንደ ሞቱ፣ እጅግ ብዙ ኃያላነ እስራኤል በጦርነቱ እንደ ወደቁ ለካህኑ ዔሊ በነገረው ጊዜ ዔሊ በድንጋጤ ከተቀመጠበት ወንበር ወድቆ ሞተ፡፡ ምራቱም የፊንሐስ ሚስት አርግዛ ልትወልድ ተቃርባ ነበርና የአማትዋንና የባሏን ሞት በሰማች ጊዜ ምጥ ደረሰባት፤ ወንድ ልጅም ወለደች፡፡ ስሙንም ‹ኢካቦድ› ብላ ጠራችው፤ ትርጕሙም ‹‹ክብር ከእስራኤል ለቀቀ›› ማለት ነው፡፡

ከዚህ ታሪክ ብዙ ቁም ነገሮችን እንማራለን፤ አስቀድሞ እስራኤል ታቦተ ጽዮንን ይዘው የዮርዳኖስን ባሕር ከፍለው ተሻግረዋል፤ አሞናውያንን፣ ፌርዜዎናውያንን፣ ሞዓባውያንን ድል አድርገዋል፡፡ የኢያሪኮን ግንብ አፍርሰው ምድረ ርስትንም ወርሰዋል፡፡ ከዚህ ላይ ‹‹የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ከፊታቸው በማስቀደም እነዚህን ታላላቅ ተአምራት ያደረጉ እስራኤል በፍልስጥኤማውያን እንዴት ድል ተነሱ? የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦትስ እንዴት ተማረከች?›› የሚሉ ጥያቄዎች ከተነሡ ለታቦተ ጽዮን መማረክ፣ ለኃያላነ እስራኤል ድል መነሳት፣ ለካህኑ ዔሊ ሞት፣ እንዲሁም ለልጆቹ አፍኒንና ፊንሐስ በጦርነቱ መሞት ዋና ምክንያት የአፍኒንና ፊንሐስ ኃጢአት እንደዚሁም የዔሊ አለመታዘዝ ነው፡፡

የአፍኒንና ፊንሐስ ኀጢአት

፩ኛ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው መሥዋዕት ስቡ ሳይቃጠል አስቀድመው ሥጋ መብላታቸው

መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የዔሊ ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያውቁም ነበር›› ይላል /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፲፪/፡፡ እግዚአብሔርን አያውቁም ማለቱ ለአምላክነቱ የሚገባውን ክብር አይሰጡም ለማለት ነው እንጂ የሊቀ ካህን ልጆች ኾነው ስለ እግዚአብሔር ህልውና መግቦት፣ ገዥነት፣ ወዘተ አያውቁም ለማለት አይደለም፡፡ የአዋቂ አጥፊዎች እንደ ኾኑ ለመናገር ነው እንጂ፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ ለእግዚአብሔር የሚቃጠለው የስብ መሥዋዕት ሳይቀርብ አስቀድመው ጥሬ ሥጋ ሳይቀር ገና ሳይቀቀል ይወስዱ ነበር፡፡ እንኳን ለመሥዋዕት ከሚቀርበው ሥጋ መመገብ ከድካም ውጤት ዐሥራቱን፣ በኵራቱን፣ ቀዳምያቱን አለመስጠት በእግዚአብሔር ዘንድ ያስጠይቃል፡፡ ዐሥራት ከገንዘብ፤ በኵራት ከእንስሳት፤ ቀዳምያት ከአዝዕርት ከፍራፍሬ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ስጦታ ነው፤ ይህንን ማድረግም ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡

ስቡ ሳይቃጠል፣ መሥዋዕቱም ሳያርግ ለሆዳቸው ያደሩ አፍኒንና ፊንሐስ ሥጋ በመብላታቸው ምክንያት ‹‹ምናምንቴዎች›› እንደ ተባሉ፣ ዛሬም እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ የቤተ ክርስቲያንን ዕድገትና ልማት የሚናፍቁ ደጋግ ክርስቲያኖች የሚያስገቡትን ዐሥራት፣ በኵራት፣ ቀዳምያት በመዝረፍ ቤተ ክርስቲያንን የሚበድሉ ብዙ ምናምንቴዎች አይታጡም፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ ሲስገበገቡለት የነበረው ሥጋ አላዳናቸውም፡፡ እነርሱ ያለ ቀባሪ በጠላት ሰይፍ ተመተው እንደ ወደቁ ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን የሚዘርፉ፣ ሙዳየ ምጽዋት የሚገለብጡ ዅሉ ሥጋቸው በደዌ፣ በመቅሠፍት፤ ነፍሳቸውም በሲዖል መቀጣቱ አይቀርም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉት እኛ እንድንማርባቸው እንድንገሠፅባቸው ነውና ከዚህ ታሪክ ትምህርት ወስደን ሰማያዊውን ጸጋ በምድራዊው ጥቅም ለውጠን እንዳንጐዳ ሰውና እግዚአብሔርን ከሚያስቀይም መጥፎ ድርጊት ለመመለስ ዛሬውኑ መወሰን ይኖርብናል፡፡ ‹‹ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ /ሮሜ. ፰፥፮/፡፡

፪ኛ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር መሰሰናቸው

ዝሙት በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተጠላ፣ ሰውነትን ዅሉ የሚያረክስ ኃጢአት ነው፡፡ ሌሎቹ ኃጣውእ በአፍኣ ይሠራሉ፤ ዝሙት ግን በገዛ ሥጋ ላይ ስለሚሠራ ሰውነትን ዅሉ ያሳድፋል፡፡ ‹‹ከዝሙት ሽሹ፤ ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ዅሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙት የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአት ይሠራል፤›› /፩ኛ ቆሮ. ፮፥፲፰/ ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ይሰስኑ ነበር፡፡ የእነዚህን ሰዎች ኃጢአት እጅግ የከፋ የሚያደርገው በመገናኛው ድንኳኑ ውስጥ ዝሙት መፈጸማቸው ነው /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፪/፡፡ እግዚአብሔር ፍጹም ቅዱስ ነውና በቅድስና እንድናገለግለው ይፈልጋል፡፡ ‹‹ኩኑ ቅዱሳነ ወቀድሱ ርእሰክሙ እስመ ቅዱስ አነ እግዚአብሔር አምላክክሙ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ እንደ ኾንኩ እናንተም ቅዱሳን ኹኑ፤ ሰውነታችሁንም ቀድሱ›› /ዘሌ. ፲፩፥፵፬/ በማለት በሊቀ ነቢያቱ ቅዱስ ሙሴ አንደበት የተናገረው ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

ከእግዚአብሔር ውጭ በማንኛውም ነገር መመካት ወይም መታመን ዝሙት ነው፡፡ ሰው በወገን፣ በሥልጣን፣ በሀብት ወይም በዕውቀት እየታበየ የሚያቀርበው መባዕ፣ የሚጸልየው ጸሎት በአጠቃላይ መንፈሳዊ አገልግሎት ከንቱ ነው፡፡ መጀመሪያ እነዚህን ዝሙታት ማስወገድ አለበት፡፡ በእውነት የእኛስ አገልግሎታችን በንጽሕና በቅድስና የታጀበ ነውን? ብዙ ንጹሐን ቀሳውስትና መነኮሳት እንደዚሁም ዲያቆናት እንዳሉ ዅሉ ሥጋቸውን በዝሙት እያሳደፉ በድፍረት ማገልገል አለብኝ በማለት ማኅበረ ካህናቱና ሕዝበ ክርስቲያኑን የሚበጠብጡ እንዳሉ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በአፍኒንና ፊንሐስ የዝሙት ኀጢአት ምክንያት በአስራኤል ላይ ያደረሰው ቍጣና መቅሠፍት ዛሬም በረከሰ ሰውነታቸው ቤተ መቅደሱን በሚደፋፈሩ ሰዎች ምክንያት የምናጣው በረከትና የሚመጣው መቅሠፍት ቀላል አይኾንም፡፡

እስራኤል ከግብጽ ወጥተው ወደ ምድረ ርስት ሲጓዙ የአሕዛብን መንደሮች ያቋርጡ ነበር፡፡ በሰጢን መንደር በሰፈሩበት ጊዜ የእስራኤል ጐበዛዝት /ጐልማሶች/ በአሕዛብ ቈነጃጅት በዝሙት ተነደፉ፡፡ ከእስራኤል አንዱ ከምድያማዊቷ ሴት ጋር በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ተኛ፡፡ የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ለእግዚአብሔር ሕግ በመቅናት ሁለቱንም በአንድ ጦር ሆዳቸውን ወግቶ ገደላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ከቍጣው ተመለሰ፤ መቅሠፍቱም ቆመ፡፡ ስለዚህም ‹‹ለእርሱ፣ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘለዓለም ክህነት ቃል ኪዳን ይኾንለታል፤›› በማለት እግዚአብሔር አምላክ ለፊንሐስ ወልደ አልዓዛር ቃል ኪዳን እንደ ሰጠው በመጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል /ዘኊ. ፳፭፥፲፫/፡፡

ዛሬም በዝሙት ሰውነታቸውን እያረከሱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ካላገለገልን የሚሉትን እንደ አልዓዛር ልጅ እንደ ፊንሐስ በመንፈሳዊ ቅንዓት ተነሳሥተን ልንገሥፀቸው ይገባል፡፡ ራሳቸውን ያረከሱ አገልጋዮች በድፍረት ቤተ መቅደስ ሲገቡ ርኵሰታቸውን እያወቀ ዝም ብሎ የሚያይ ምእመን መልካም ሥራ መሥራት መልካም እንደ ኾነ እያወቀ ባለመሥራቱ ፍርድ ያገኘዋል፡፡ ሰዎች የእግዚአብሔር ቤተ መቅደሶች ናቸው፡፡ ወገኖቻችን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የኾነውን ሰውነታቸውን በዝሙት፣ በዘረኝነት፣ በትዕቢት፣ በስርቆት፣ በአጠቃላይ በኃጢአት ሲያረክሱ እያየን ዝም አንበል፡፡ ቢሰማን ያን ሰው እንጠቅመዋለን፤ ባይሰማንና በክፉ ሥራው ቢጸና ግን በራሱ ላይ የእሳት ፍሕም ያከማቻል /ምሳ. ፳፭፥፳፪/፡፡

፫ኛ ሌሊት ሲነድ የሚያድረውን እሳት ማጥፋታቸው

አፍኒንና ፊንሐስ ሌሊት በደብተራ ኦሪት ሲነድ የሚያድረውን ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የእሳት ቍርባን ያጠፉ ነበር /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፳፰/፡፡ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት ማስቀረት ክብር ይግባውና ባለቤቱን ማቃለል ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የሚያቃልለውን እንደሚያዋርድ፣ የሚያከብረውን እንደሚያከብር ራሱ እንዲህ በማለት ተናግሯል፤ ‹‹ያከበሩኝን አከብራለሁና፤ የናቁኝም ይናቃሉና፤›› /፩ኛ ሳሙ. ፪፥፴/፡፡ ቀደምት አባቶቻችን ለእግዚአብሔር ያቀርቡ የነበረውን ዐሥራት፣ በኵራት፣ ቀዳምያት እኛስ እያቀረብን ነውን?

ይቆየን፡፡

ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)

ኅዳር ፲፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጾመ ነቢያት በየዓመቱ ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እስከ በዓለ ልደት ዋዜማ ድረስ የሚጾም፤ ከሰባቱ አጽዋማት መካከል አንደኛው ጾም ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ለማዳን ሲል የሰውን ሥጋ ስለ መልበሱ፤ ወደ ግብጽ ስለ መሰደዱ፤ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለ መጠመቁ፤ በትምህርቱ ብርሃንነት ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፤ ለሰው ልጆች ድኅነት ልዩ ልዩ መከራን ስለ መቀበሉ፤ ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱና ዳግም ምጽአቱ በየዘመናቱ የተነሡ ቅዱሳን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ትንቢት ተናግረዋል፤ ትንቢቱ ደርሶ፣ ተፈጽሞ ለመመልከትም ‹‹አንሥእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሣ፤ እጅህን ላክ›› እያሉ በጾም በጸሎት ተወስነው አምላክ ሰው የሚኾንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት እያሰሉ ሲጠባበቁ ቆይተዋል፡፡

ይህ ጾም የእግዚአብሔርን ሰው መኾን ሲጠባበቁ የኖሩት የነቢያት ትንቢትና ጸሎት በጌታችን መወለድ ፍጻሜ ያገኘበት ወቅት በመኾኑ ‹‹ጾመ ነቢያት (የነቢያት ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ለአዳም የተነገረው የድኅት ተስፋ ስለ ተፈጸመበትም ‹‹ጾመ አዳም (የአዳም ጾም)›› ይባላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ሰው መኾን በስፋት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበት ወቅት በመኾኑም ‹‹ጾመ ስብከት (የስብከት ጾም)››፤ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመኾኑ ደግሞ ‹‹ጾመ ልደት (የልደት ጾም)›› በመባል ይታወቃል፡፡ እንደዚሁም ‹‹ጾመ ሐዋርያት›› ይባላል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹በዓለ ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብረዋለን፤ በዓለ ልደትንስ ምን አድርገን እናከብረዋለን?›› በማለት ነቢያት የጾሙትን ከልደተ ክርሰቶስ በፊት ያለውን ጾም ጾመዋልና፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ይህ ጾም ‹‹ጾመ ፊልጶስ (የፊልጶስ ጾም)›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ በአፍራቅያና አውራጃዋ ዅሉ እየተዘዋወረ በጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወንጌልን በማስተማር፣ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ብዙዎችን ወደ አሚነ እግዚአብሔር ሲመልስ ቆይቶ ትምህርቱን በማይቀበሉ የአፍራቅያ ሰዎች አማካይነት በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሥጋውን ሊቀብሩ ሲሉም ስለ ተሰወረባቸው የሐዋርያውን ሥጋ ይመልስላቸው ዘንድ ሱባዔ ይዘው፣ በጾም በጸሎት ተወስነው በለመኑት ጊዜ እግዚአብሔር ልመናቸውን ተቀብሎ በ፫ኛው ቀን መልሶላቸው ሥጋውን (አስከሬኑን) በክብር አሳርፈውታል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የሐዋርያውን ሥጋ ካገኙ በኋላ እስከ ጌታችን ልደት ድረስ ጾመዋል፡፡ ስለዚህም ጾመ ነቢያት ‹‹ጾመ ፊልጶስ›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ወልደ አምላክ ክርስቶስን በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደምትፀንሰው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ካበሠራት በኋላ እመቤታችን ‹‹ሰማይና ምድር የማይወስኑትን አምላክ ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ?›› በማለት ጌታችንን ከመውለዷ አስቀድማ ጾማዋለችና ይህ ጾም ‹‹ጾመ ማርያም›› በመባልም ይታወቃል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ በገና ጾም ነቢያትም ሐዋርያትም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም እንደ እነርሱ በረከትን እናገኝ ዘንድ ይህንን ጾም መጾም እንደሚገባን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሥርዐት ሠርተውልናል፡፡ በዚህም መሠረት የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን፤ መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ዅላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል፡፡

ምንጭ፡-

ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፣ አንቀጽ ፲፭፡፡

ጾምና ምጽዋት፣ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ፤ ገጽ ፵፯ -፶፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ዘመነ አስተምሕሮ

ኅዳር ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በቤተ ክርስቲያናችን የዘመን አከፋፈል መሠረት ከኅዳር ፮ ጀምሮ እስከ ታኀሣሥ ፲፫ ቀን ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምሕሮ ይባላል፡፡ ትርጕሙም ይቅርታ የመጠየቅ (የምልጃ) ዘመን ማለት ነው፡፡ ዘመኑ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምእመናንንም ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፤ ስለዚህም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ባሉት እሑዶች የሚገኙ ሰንበታት (እሑዶች) አስተምሕሮ፣ ቅድስት፣ ምኵራብ፣ መጻጉዕ እና ደብረ ዘይት በመባል ይጠራሉ፤ የመጀመሪያውን ሳምንት (የአስተምሕሮ) ትምህርትም እነሆ!

እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን /ማቴ.፮፥፲፪/፡፡

ይህ ቃል የተወሰደው ጌታችን በደቀ መዛሙርቱ በኩል እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚኖሩ (ዛሬም ላለን) ክርስቲያኖች እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ካስተማረው ጸሎት ነው፤ ‹‹በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፡፡ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ኾነች እንዲሁ በምድር ትኹን፡፡ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፡፡ እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፡፡ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፡፡ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለም አሜን፤›› /ማቴ.፮፥፱-፲፬/፡፡

ይህ ጸሎት በጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ሊቃውንት «የጌታ ጸሎት» ተብሎ ይጠራል፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን የጸሎቱን የመጀመሪያ ሐረግ በመያዝ «አባታችን ሆይ» ወይም በግእዝ «አቡነ ዘበሰማያት» እንለዋለን፡፡ ይህ ጸሎት ጌታችን ራሱ ያስተማረው በመኾኑ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ የሌሎች ጸሎታት ዅሉ ማሰሪያ (ማሳረጊያ) ኾኖም ያገለግላል፡፡ በውስጡም «አባታችን ሆይ» ከምትለው ከመጀመሪያዋ ሐረግ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ እጅግ ጥልቅ የኾኑና ነፍስን የሚያጠግቡ፣ ወደ ሰማይ ከፍ የሚያደርጉ መንፈሳዊና ነገረ መለኮታዊ መልእክቶችን ያዘለ ነው፡፡ ይህ የዘመነ አስተምሕሮ የመጀመሪያው ሳምንት ስለ ይቅርታ የሚሰበክበት ነውና በጸሎቱ ውስጥ ስለዚህ የሚናገረውን አንቀጽ መሠረት አድርገን እንማራለን፤

«እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን» ከሚለው ኃይለ ቃልም የሚከተሉትን ቁም ነገሮች እንረዳለን፤

፩. እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን እንደሚወድ

አምላካችን ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ባይወድ ኖሮ ይቅርታን እንድንጠይቅ አይነግረንም ነበር፡፡ አዎ፤ እኛ ከተመለስን ምንም ያህል በደለኛ ብንኾን ይቅር ሊለን፤ ምንም ያህል ብንቆሽሸ ሊያድነን ዝግጁ ነው፡፡ እንዲህ እያለ ይጠራናል፤ «እናንተ ሸክማችሁ የከበዳችሁ፤ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡» ስለዚህ በዚሀ ጸሎትም ላይ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጠይቀው አስተማረን፤ ይቅር ይለን ዘንድ፡፡

፪. ይቅር ለመባል ምን ማድረግ እንዳለብን

እግዚአብሔር ይቅር ሊለን ስለ ወደደም ይቅርታን ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን በዚሁ ቃል ነግሮናል፤ ማድረግ ያለብን ምንድን ነው?

ኀጢአታችንን ማወቅ (ማመን)

ጌታ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጸልይ ሲነግረን በመጀመሪያ ደረጃ በደለኛ እንደኾንን እያስታወስን (እንድናስታውስ እያደረገን) ነው፡፡ ዅልጊዜም በማሰብ፣ በመናገርና በማድረግ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የኾነውን ልባችንን (ኅሊናችንን) እና ሰውነታችንን እናቆሽሻለን፤ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የሞተለትን ማንነታችንን እናጎድፋለን፡፡ ይህም የሰው ልጆች በቅድስና እርሱን መስለን እንድንኖር በኋላም የተዘጋጀልንን የዘለዓለም መንግሥት እንድወርስ ብቻ ፈቃዱ የኾነውን እግዚአብሔርን ያሳዝናል፤ በአርአያውና በአምሳሉ ለክብር የፈጠረው ሰውነታችን መጉደፉ ያስቆጣዋል፤ ንጹሐ ባሕርይ የኾነ እርሱ ኀጢአት አይስማማውምና፡፡

እንግዲህ ይቅር ለመባል በመጀመሪያ እንዲህ ኀጢአት እየሠራን መሆኑን ማወቅና ማመን ያስፈልገናል፡፡ ወደዚህ ዕውቀት ለመድረስም የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል መማር የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ስሕተት የሚታወቀው ያለውን ኹኔታ (ድርጊታችንን ንግግራችንን፣ ሐሳባችንን…) መኾን ከነበረበት (ከትክክለኛው) ጋር በማነጻጸር በሚዛን ላይ በማስቀመጥ ነው፡፡ የማነጻጻሪያ ሚዛኖቻችን ደግሞ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉ ሕግጋትና ትእዛዛት ናቸው፡፡ እነዚህን ስናውቅ ጕድለቶቻችንና ድካሞቻችን ፍንተው ብለው ይታዩናል፡፡ ካለዚያ ግን እየበደለን ያልበደልን ሊመስለን ይችላል፡፡

የበደሉንን ይቅር ማለት

ጌታችን በዚህ ጸሎት ይቅርታ እንድንጠይቀው በማስተማር ይቅር ሊለን እንደሚወድ ቢነግረንም ይቅር ለመባል ግን እኛ የበደሉንን ይቅር ማለታችን የግድ እንደኾነ በግልጽ አስቀምጦልናል፤ «በደላችንን ይቅር በለን» ከማለታችን በፊት «እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል» እንድንል ያዘዘን እኛ ይቅርታ የምናገኘው ሌሎችን ይቅር ስንል ብቻ መኾኑን ለማመልከት ነው፡፡ በዚሁ በተራራው ስብከት ይኸው ጉዳይ ሁለት ጊዜ በጌታችን ትምህርት ተሰጥቶበታል፡፡ «እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል፤» /ማቴ.፯፥፪/፡፡

በሌላ ቦታም እንዲህ ሲል ይህንኑ ጉዳይ በምሳሌ አስተምሯል፤

 ‹‹መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ለመቈጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች፤ መቈጣጠርም በጀመረ ጊዜ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፡፡ ባለ እዳው ሰው የሚከፍለው ስላጣ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ንጉሡ አዘዘ፡፡ በዚህም ጊዜ ባርያው ወድቆ ሰገደለትና ጌታ ሆይ ታገሰኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው፡፡ የዚያም ባርያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፡፡ ይህ ባርያ ግን ወጥቶ ከባልጀሮቹ /እንደርሱ ባርያ ከኾኑት/ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው፡፡ ባልንጀራው ባርያም ወድቆ ታገሰኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤ ብሎ ለመነው፡፡ እርሱ ግን ሊተወው አልወደደም፡፡ ዕዳውን እስኪከፍልም በወኅኒ አኖረው፡፡ ይህንን ያዩ ሰዎችም አዘኑ፤ ሄደውም የኾነውን ለንጉሡ ተናገሩ፡፡ ከዚህ ወዲያ ንጉሡ ጠርቶ፣ አንተ ክፉ ባርያ ስለ ለመንከኝ ያን ዕዳ ዅሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህን የኾነውን ባርያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን አለው፡፡ ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን እስኪከፍለው ድረስ ለሚያሰቃዩት አሳልፎ ሰጠው፤» /ማቴ.፲፰፥፳፫-፴፭/፡፡

ጌታ ይህንን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ የምሳሌውን ትርጕም እንዲህ ሲል ገልጦታል፤ «ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል፡፡›› በአጠቃላይ ይቅር ለመባል ይቅር ማለት የግድ ነው፡፡ በእኛ ላይ የሚፈረድብን ፍርድ በእኛው እጅ ላይ ነው፡፡ ጌታችን በእነዚህ ትምህርቶች እንዲህ እያለን ነው «እኔ እናንተ ላይ የምፈርደው እናንተ በራሳችሁ ላይ በፈረዳችሁበት መንገድ ነው፡፡»

ይቅርታ መጠየቅ

ኀጢአታችንን ካወቅንና ካመንን፣ የበደሉንንም ከልብ ይቅር ካልን በኋላ ይቅር እንድንባል መጠየቅ (መለመን) አለብን ፡፡ ጌታችን «ይቅር በለን ብላችሁ ጸልዩ›› ብሎ ከማስተማሩም ይህንን እንረዳለን፡፡ ወደ ንስሐ አባት መሔድና ኀጢአትን ተናዞ ቀኖና መቀበል የሚገባው መጀመሪያ በዚህ መልኩ ስለ ኀጢአት ካለቀሱ በኋላ ነው፡፡ ከዚያም ቀኖና ተቀብለን ስንፈጽምም ይኸው ስለ ኀጢአት ይቅርታ መጠየቁ ይቀጥላል፡፡ ይቅርታ የምንጠይቀው አዳዲስ ስለ ሠራናቸውና ንስሐ ገና ስላልገባንባቸው ኀጢአቶቻችን ብቻ ሳይኾን ንስሐ ስለ ገባንባቸው ስለ ቀደሙት በደሎቻችንም ጭምር ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ዳዊት «የቀደመ በደላችንን አታስብብን፤ ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን፤» /መዝ.፸፰፥፰/ እያልን ሰለ ቀደመው በደላችንም እያሰብን በሕይወታችን ዘመን ዅሉ ይቅርታ መጠየቅ አለብን፡፡

እንደዚሁም ይቅርታ የምንጠይቀው ስለምናውቃቸው (ስለምናስተውላቸው) ኀጢአቶቻችን ብቻ ሳይኾን ስለ ማናስተውላቸውም መኾን አለበት፡፡ ስለዚህ «ይቅር ብለን» ስንል እኛ ካስተዋልናቸው መንገዶች ውጪ በብዙ መልኩ እርሱን እንደምንበድል አስበን ይቅርታ መጠየቅ አለብን፡፡ ስለዚህ ለጸሎት ከመቆማችንና ከመጸለያችን በፊት የበደሉንን ይቅር እንዳልን እርግጠኛ መኾን ይኖርብናል ማለት ነው፤ ‹‹እኛ የበደሉንን ይቅር እንዳልን …›› ልንል ነውና፡፡ «በደላችንን ይቅር በለን» ስንልም ከላይ ያየናቸውን ነገሮች ዅሉ እያሰብን፤ ይቅር ሊለን የወደደ አምላካችንንም እያመሰገንን መኾን አለበት፡፡

በእውነት ይህንን ጸሎት የምንጸልየው በዚህ መልኩ ነውን? ካልኾነ ልምምዱን ዛሬውኑ እንጀምረው፡፡ ይህንን ማድረግ እንችል ዘንደ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ

ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

mathew

ቅዱስ ማቴዎስ

የጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አምላካዊ ትእዛዝ ተቀብለው ወንጌልን ለመላው ዓለም በማብሠር መምለክያነ ጣዖትን ወደ አሚነ እግዚአብሔር፣ አሕዛብን ወደ ክርስትና ከመለሱ ቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ አንደኛው ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ አገሩ ናዝሬት፣ የዘር ሐረጉም ከይሳኮር ነገድ ሲኾን አባቱ እልፍዮስ (ዲቁ)፣ እናቱ ደግሞ ካሩትያስ ይባላሉ፡፡

ለደቀ መዝሙርነት ከመመረጡ በፊት ‹ሌዊ› ይባል ነበረ፤ ከተጠራ በኋላ ግን ‹ማቴዎስ› ተብሏል፡፡ ‹ማቴዎስ› ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹ጸጋ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ስጦታ)› ማለት ሲኾን ስሙን ያወጣለትም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለወንጌል አገልግሎት የተጠራውም በቅፍርናሆም ከተማ ከቀራጭነት ሥራ ላይ ነው /ማቴ. ፱፥፱-፲፫፤ ሉቃ. ፭፥፳፯-፴፪/፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ቍጥሩ ከ፲፪ቱ ሐዋርያት ሲኾን ከ፬ቱ ወንጌሎች አንደኛውን የጻፈው እርሱ በመኾኑ ‹ወንጌላዊ› እየተባለ ይጠራል፡፡ ወንጌሉን የጻፈውም ጌታችን ባረገ በ፰ኛው ዓመት መጨረሻ በ፵፩ /፵፪ ዓ.ም፣ ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በመጀመሪያው ዘመን በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው /ማቴ.፳፰፥፳/፡፡ ጽሕፈቱንም በፍልስጥኤም ጀምሮ በህንድ ፈጽሞታል፡፡

እንደ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ወንጌሉ በውስጡ ከ፻፶ በላይ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን ማካተቱ አይሁድን ለማሳመን የተጻፈ ለመኾኑ ማስረጃ ነው፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ከኦሪታዊ ይዘቱ አኳያ በመጀመሪያ ተቀመጠ እንጂ የተጻፈው ግን ከማርቆስ ወንጌል ቀጥሎ እንደኾነም መምህራን ይናገራሉ፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በሀገረ ስብከቱ በፍልስጥኤም ጌታችን ከፅንስ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ድረስ ያደረጋቸውን ተአምራት፣ ያስተማረውን ትምህርትና የሠራቸውን ትሩፋቶች ሲያስተምራቸው ብዙ አሕዛብ ከኦሪት ወደ ወንጌል፤ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመልሰዋል፡፡ ምእመናኑ ‹‹በቃል ያለ ይረሳል፤ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳልና ያስተማርኸንን ጻፍልን›› ብለውት፤ አንድም እንደ አባትነቱ ከራሱ አንቅቶ /አመንጭቶ/፤ አንድም አይሁድ ክርስቲያኖችን ‹‹ክርስቶስ ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም መኾኑን ሠፍራችሁ፣ ቈጥራችሁ አስረዱን›› ቢሏቸው ለማስረዳት የዕውቀት ማነስ ነበረባቸውና እርሱ ጽፎላቸዋል፡፡

ወንጌሉን ከጻፈ በኋላም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ አፓንጌ በሚባል አገር ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን በክርስቶስ አሳምኗል፡፡ የማቴዎስን ወንጌል ወንጌላዊው /ሐዋርያው/ ዮሐንስ በእልአንሳን፣ በህንድና በኢየሩሳሌም አገሮች እየተረጐመ አስተምሮታል፡፡ የእርሱ ስብከት በመጽሐፍ ቅዱስ አለመጠቀሱም መላ ሕይወቱን ለክርስቶስ አገልግሎት የሰጠ ሐዋርያ መኾኑን እንደሚያሳይ መምህራን ይመሰክራሉ፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ‹‹ወልደ ዳዊት፣ ወልደ አብርሃም›› በማለት የክርስቶስን ምድራዊ ልደት /ሰው መኾን/ ጽፏልና ከአራቱ የኪሩቤል ገጽ መካከል በአንደኛው በገጸ ሰብእ ይመሰላል፡፡ የኤፌሶን ወንዝ ፈለገ ሐሊብ ይባላል፤ ርስትነቱም ለሕፃናት ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም በዘር የሚወለዱ አበውን ልደት ጽፏልና፤ ዳግመኛም ሄሮድስ ስላስፈጃቸው ሕፃናት ተናግሯልና በኤፌሶን ወንዝ ይመሰላል፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልን አስተምሮ ብዙዎችን ወደ አሚነ እግዚአብሔር ከመለሰ በኋላ ጌታችን ወደ ካህናት አገር እንዲሔድና የካህን ልብስ ለብሶ፣ ፀጉሩንና ጺሙን ተላጭቶ፣ በቀኝ እጁ ዘንባባ ይዞ ወደ አገሩ ቅፅር እንዲገባ ስላዘዘው በደመና ተጭኖ ሔዶ ወደ ቤተ ጣዖታቱ ገብቶ በጸለየ ጊዜ መብረቅ የመሰለ ብርሃን ወረደ፡፡ የአምላክን ከሃሊነት ለመግለጥ በተከሠተው ርዕደ መሬትም የአገሩ ጣዖታት ኹሉ ወድቀው ተሰባበሩ፡፡ አርሚስ የሚባለው የጣዖቱ ካህንም ካየው አምላካዊ ብርሃንና ድንቅ ተአምር የተነሣ በክርስቶስ አምኖ ከተጠመቀ በኋላ የቅዱስ ማቴዎስ ረድእ ኾኗል፡፡

ይህ ክሥተትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙዎችን በክርስቶስ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል፡፡ ያማኞች ቍጥርም ፬ ሺሕ እንደ ነበረ በገድለ ሐዋርያት ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በኋላ የንጉሡ ልጅ በሞተ ጊዜ ቅዱስ ማቴዎስ ወደ እግዚአብሔር ጸልዮ ከሞት ቢያስነሣው ንጉሡ፣ ቤተሰቦቹና የአገሩ ሰዎች ኹሉ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው አጵሎን የተባለውን ጣዖት በእሳት አቃጥለው ቤተ ጣዖቱን የአምልኮተ እግዚአብሔር መፈጸሚያ ሥፍራ አድርገውታል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም አርሚስን ኤጲስ ቆጶስ በማድረግ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾሞላቸዋል፡፡

በገድለ ሐዋርያት እንደ ተጠቀሰው ቅዱስ ማቴዎስ ከማረፉ በፊት በደመና ተነጥቆ ብሔረ ብፁዓን ገብቷል፤ በዚያም ሄሮድስ በግፍ በጨፈጨፋቸው ሕፃናት ክብረ በዓል ጌታችን ወደ እነርሱ ሲመጣ፣ መላእክትም በዙሪያው ከበው ሲያመሰግኑት ያይ ነበር፡፡ ከዚያ ተመልሶም በየአገሩ እየዞረ ወንጌልን አስተምሯል፤ ካስተማረባቸው አገሮችም ፍልስጥኤም፣ ፋርስ፣ ባቢሎን፣ ኢትዮጵያና ዓረቢያ ይጠቀሳሉ፡፡ የማስተማር ተልእኮው የተከናወነውም በታንሿ እስያ ውስጥ ነው፡፡ ግሪካውያን አሕዛብ «አምላካችንን ሰደበብን» ብለው አሥረውት በነበረ ጊዜም ወኅኒ ቤት ኾኖ ይሰብክ ነበር፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በ፵ ዓ.ም በአገራችን በኢትዮጵያ እየተዘዋወረ ወንጌልን እንደ ሰበከና በዘመኑ የነበሩ ኦሪታውያን ነገሥታትን ጨምሮ በርካታ አሕዛብን አስተምሮ በማጥመቅ ወደ ክርስትና ሃይማኖት  እንደ መለሰ፤ እንደዚሁም ለምጻሞችን በማንጻት፣ አንካሶችን በማርታት፣ ሕሙማንን በመፈወስ፣ ሙታንን በማስነሣት ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እንዳደረገ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና በትግራይ ክልል በማኅበረ ጻድቃን ዴጌ ገዳም የሚገኙ የብራና መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

በአገልግሎቱ መጨረሻም በትርያ በምትባል አገር ሲያስተምር አገረ ገዥው አሠረው፡፡ በወኅኒ ቤቱም ጌታው ለንግድ የሰጠውን ገንዘብ ማዕበል ወስዶበት በዕዳ ምክንያት የሚያለቅስ አንድ እሥረኛ አገኘና አጽናንቶ መኰንኑ ገንዘቡን ከሕዝቡ ለምኖ እንዲከፍለው በመሻት ከእሥር እንደሚፈታው፤ ከባሕር ዳርቻም የወደቀ ወርቅ የተሞላ ከረጢት እንደሚያገኝ፤ ያንንም ለጌታው ከሰጠ በኋላ ከዕዳና ከእሥር ነጻ እንደሚኾን አስረዳው፡፡ ሰውየውም ቅዱስ ማቴዎስ የተናገረው ኹሉ ስለ ተፈጸመለት ለቅዱስ ማቴዎስ እየሰገደ፤ ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ›› እያለ ሃይማኖቱንና ደስታውን ገለጸ፡፡ ይህንን ድንቅ ተአምር የሰሙ ብዙ አሕዛብም በጌታችን አምነዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም አርያኖስ በሚባል ንጉሥ ትእዛዝ ጥቅምት ፲፪ ቀን አንገቱን በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ዐርፏል፤ ምእመናንም ሥጋውን በክብር ቀብረውታል፡፡ ትርጓሜ ወንጌል ደግሞ ብስባራ በምትባል አገር በደንጊያ ተወግሮ በሰማዕትነት ካረፈ በኋላ የቂሣርያ ክፍለ ዕጣ በምትኾን በቅርጣግና መቀበሩን ይናገራል፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ እኛንም በሐዋርያው በቅዱስ ማቴዎስ ጸሎት ይማረን፤ በረከቱም ይደርብን፡፡

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ጥቅምት ፲፪ ቀን፤

የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፤

የማቴዎስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ፤

ገድለ ሐዋርያት፡፡

ዘመነ ጽጌ

መስከረም ፳፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዝግጅት ክፍሉ

በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ በአገራችን በኢትዮጵያ የወቅቶች ሥርዓተ ዑደት መሠረት ከመስከረም ፳፮ ቀን ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ፺ ቀናትን የሚያጠቃልለው ጊዜ ‹‹ዘመነ መጸው›› ይባላል፡፡ ‹‹መጸው›› ማለት ወርኀ ነፋስ ማለት ሲኾን ይኸውም ‹‹መጸወ ባጀ፤ መጽለወ ጠወለገ›› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ዘመነ መጸው ከዘመነ ክረምት ቀጥሎ የሚብት (የሚገባ) የልምላሜ፣ አበባ፣ የፍሬ ወቅት ነው፡፡ በውስጡም አምስት ንዑሳን ክፍሎችን የሚያካትት ሲኾን እነዚህም፡- ዘመነ ጽጌ፣ ዘመነ አስተምህሮ፣ ዘመነ ስብከት፣ ዘመነ ብርሃን እና ዘመነ ኖላዊ ናቸው /ያሬድና ዜማው፣ ገጽ ፵፰-፵፱/፡፡

ከአምስቱ የዘመነ መጸው ክፍሎች መካከል የመጀመሪያው ክፍለ መጸው ዘመነ ጽጌ ተብሎ የሚጠራ ሲኾን ይህም ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ቀን ድረስ ያሉትን ፵ ቀናት ያጠቃልላል፡፡ ‹ጽጌ› ቃሉ ‹ጸገየ አበበ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም አባባ ማለት ነው፡፡ ‹ዘመነ ጽጌ› ደግሞ ‹የአበባ ወቅት፣ የአበባ ጊዜ፣ የአበባ ዘመን› ማለት ነው፡፡ ይህ ወቅት ዕፀዋት በአበባ የሚያጌጡበት፣ ምድር በአበቦች ኅብረ ቀለማት የምታሸበርቅበት፣ ወንዞች ንጹሕ የሚኾኑበት፣ ጥሩ አየር የሚነፍስበት፣ አዕዋፍ በዝማሬ የሚደሰቱበት፣ እኛም የሰው ልጆች ‹‹አሠርጎካ ለምድር በሥነ ጽጌያት፤ አቤቱ ምድርን በአበቦች ውበት አስጌጥሃት›› እያልን የዘመናት አስገኚና ባለቤት የኾነውን ልዑል እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት፤ ከዚህም ባሻገር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከገሊላ ወደ ግብጽ ምድር መሰደዷን የምናስብበት ወቅት ነው፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም በተወለደ ጊዜ የዘመኑ ንጉሥ ሄሮድስ ሥልጣኔን ይቀማኛል በሚል ቅናት ተነሣሥቶ ጌታችንን ለማስገደል አሰበ፡፡ ያንጊዜም ጌታችን በተአምራት መዳን ሲቻለው የትዕግሥት፣ የትሕትና አምላክ ነውና በለበሰው ሥጋ በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ በመልአኩ ተራዳኢነት፣ በአረጋዊው ዮሴፍ ጠባቂነትና በሰሎሜ ድጋፍ ከገሊላ ወደ ግብጽ ተሰዶ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቆይቷል፡፡ ሄሮድስም ጌታን የጋኘሁ መስሎት በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙ ሀለት ዓመት ከዚያ በታች የኾኑ አንድ መቶ ዐርባ አራት ሺሕ ሕፃናትን በግፍ አስፈጅቷል፡፡

በተአምረ ማርያምና በማኅሌተ ጽጌ ተጽፎ እንደሚገኘው ጌታችን በግብጽ ምድር በስደት ሳለ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም እናቱን እመቤታችንን የዘለፏትን ትዕማንና ኮቲባ የሚባሉ ሴቶችን ከሰውነት ወደ ውሻነት መቀየሩ፤ ውሃ በጠማቸው ጊዜ ውሃ እያፈለቀ ማጠጣቱና ይህንን ውሃ ክፉዎች እንዳይጠጡት መራራ ማድረጉ፤ ለችግረኞችና ለበሽተኞች ግን ጣፋጭ መጠጥና ፈዋሽ ጠበል ማድረጉ፤ ‹‹የሄሮድስ ጭፍሮች ደርሰው ልጅሽን ሊገድሉብሽ ነው›› ብሎ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ እመቤታችንን በማስደንገጡ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ድንጋይ ኾኖ እንዲቆይ ማድረጉ፤ መንገድ ላይ የተራዳቸው ሽፍታ ሰይፉ በተሰበረች ጊዜ እንደ ቀድሞው ደኅና እንድትኾን ማድረጉ፤ እንደዚሁም የግብጽ ጣዖታትን ቀጥቅጦ ማጥፋቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የጌታችንና የእመቤታችን የስደት ወቅት በወርኀ ግንቦት ነው፤ ነገር ግን ዘመነ ጽጌ የአበባና የፍሬ ወቅት በመኾኑ እመቤታችንን በአበባ፣ ጌታችንን ደግሞ በፍሬ እየመሰሉ ለማመስገንና ለማወደስ በሚያስችል ምሥጢር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የስደቱ ጊዜ በዘመነ ጽጌ እንዲዘከር አድርገዋል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዘለዓለሙ የማይደርቀውን የሕይወት ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን ንጽሕት የማትጠወልግ አበባ ናትና፡፡ ይህ የእመቤታችን አበባነትና የጌታችን ፍሬነትም እንደ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫና አባ ጽጌ ድንግል ባሉ ሊቃውንት ድርሰቶች በሰፊው ተገልጧል፡፡

በዘመነ ጽጌ በማኅሌትና በቅዳሴ ጊዜ የሚቀርቡ መዝሙራትና የሚሰጡ ትምህርቶችም ይህንኑ ምሥጢር የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት በሚገኙ ሰንበታትም ሊቃውንቱ ሌሊቱን ሙሉ ስለ እመቤታችን አበባነትና ስለ ጌታችን ፍሬነት የሚያትት ትምህርት የያዙትን ማኅሌተ ጽጌና፣ ሰቆቃወ ድንግልን ከቅዱስ ያሬድ ዚቅ ጋር በማስማማት ሲዘምሩ፣ ሲያሸበሽቡ ያድራሉ፡፡ ቅዳሴውም በአባ ሕርያቆስ የተደረሰውና ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ሥላሴንና ነገረ ማርያምን የሚተነትነው ቅዳሴ ማርያም ነው፡፡ ምንባባቱም ከዚሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ናቸው፡፡

በአጠቃላይ እመቤታችን በስደቷ የደረሰባትን መከራ በማስታዎስ ዘመነ ጽጌን በፈቃዳቸው የሚጾሙ ካህናትና ምእመናን ብዙዎች ናቸው፡፡ ኾኖም ግን የጽጌ ጾም የፈቃድ ጾም እንጂ ከሰባቱ አጽዋማት ጋር የሚመደብ ስላልኾነ ጽጌን የማይጾሙ አባቶች ካህናትንና ምእመናንን ልንነቅፋቸው አይገባም፡፡ አምላካችን በአበባ የሚመሰለው ሰውነታችን የጽድቅ ፍሬን ሳያፈራ በሞት እንዳንወሰድ መልካም ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

ብዙኃን ማርያም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፳ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

dscn9134

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ጋር (በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ውስጥ የሚገኝ ሥዕል)

በቤተ ክርስቲያናችን ከሚዘከሩ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓላት መካከል መስከረም ፳፩ ቀን የሚውለው በዓል ‹‹ብዙኃን ማርያም›› በመባል ይታወቃል፡፡ በዓሉ በሁለት ዐበይት ምክንያቶች ይከበራል፤ የመጀመሪያው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ለማዘጋጀት ከሩቅም ከቅርብም የተሰባበሰቡት ቀን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል በግሸን ደብረ ከርቤ የተቀመጠበት ዕለት መኾኑ ነው፡፡ ሁለቱንም ታሪኮች ከዚህ ቀጥለን እንመለከታቸዋለን፤

በ፫፻፳፭ ዓ.ም አርዮስ የሚባል መናፍቅ የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት አልቀበልም በሚል ክህደት እርሱ ተሰናክሎ ለሌሎችም መሰናክል ኾነ፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አርዮስ ክህደቱን እንዲተው ቢመክሩትም ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይህ የአርዮስ ክህደትም በሊቃውንቱ መካከል መለያየትን ፈጥሯል፡፡ ጊዜው ታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ‹‹አብያተ ጣዖታት ይትአጸዋ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኀዋ፤ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ! አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ!›› የሚል ዐዋጅ የነገረበት ወቅት ነበርና ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በአርዮስ ክህደት ምክንያት በኒቅያ የሃይማኖት ጉባኤ እንዲካሔድ በየአገሩ ላሉ ሊቃውንት መልእክት አስተላለፈ፡፡

በዚህም መሠረት ከሚያዝያ ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፩ ቀን ድረስ ፳፫፻፵፰ (ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንት) ሊቃውንት በኒቅያ ተሰበሰቡ፡፡ ኒቅያ ለዚህ ጉባኤ የተመረጠችበት ምክንያትም ጳጳሱን ከማኅበረ ካህናቱ፤ ንጉሡን ከሠራዊቱ ጋር አጠቃላ ለመያዝ የምትችል ሰፊና ምቹ ቦታ ከመኾኗ ባሻገር ለኹሉም አማካይ ሥፍራ ስለ ነበረች ነው፡፡ በጉባኤው ከተሰበሰቡ ሊቃውንት መካከልም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሙታንን ያስነሡ፣ ለምጽ ያነጹ፣ አንካሳ ያረቱ፣ የዕውራንን ዓይን ያበሩ ድውያንን የፈወሱ፣ ሌላም ልዩ ልዩ ተአምር ያደረጉ፤ እንደዚሁም ስለ ርትዕት ሃይማኖታቸው በመጋደል ዓይናቸው የፈረጠ፣ እጃቸው የተቈረጠ ይገኙበታል፡፡

ሊቃውንቱ ሱባዔ ይዘው በጸሎት ከቆዩ በኋላ ኅዳር ፱ ቀን በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት፣ በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት ጉባኤው ተጀመረ፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን ‹‹ስማችሁን፣ አገራችሁንና ሃይማኖታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ›› ባላቸው ጊዜም ከ፳፫፻፵፰ቱ መካከል ፫፻፲፰ (ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ) ሊቃውንት ሃይማኖታቸውን ሲገልጹ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና አንድ ነው›› ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ንጉሡም ‹‹ሃይማኖት እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ይኹን›› ብሎ ዐዋጅ አስነግሯል፡፡ እነዚህ ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሱት ፫፻፲፰ቱ የአብርሃም ብላቴኖች ምሳሌዎች ናቸው /ዘፍ.፲፬፥፲፬/፡፡

፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በጉባኤው አርዮስን አውግዘው በመለየት ‹‹ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን›› የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎችን ደንግገዋል፡፡ ሊቃውንቱ ጉባኤውን ያካሔዱት ኅዳር ፱ ቀን ይኹን እንጂ በአንድነት የተሰባሰቡት መስከረም ፳፩ ቀን ስለ ነበረ ይህ ዕለት ‹‹ብዙኃን ማርያም›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለሃይማኖታዊ ጉባኤ የተሳባሰቡበት ዕለት ነውና፡፡

በሌላ በኩል መስከረም ፳፩ ቀን የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በአምባሰል ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ የገባበትና በዓሉ የከበረበት ዕለት ነው፡፡ ታሪኩም በአጭሩ የሚከተለው ነው፤

ዐፄ ዳዊት መንፈሳዊና ደግ ንጉሥ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ቸነፈር ተከሥቶ ሕዝቡ ስለ ተሰቃየባቸው እጅግ አዘኑ፤ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላኩ ባሕታዊ መጥተው ‹‹የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል አስመጥተህ በአገርህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሠርተህ ብታስቀምጥ ረሃቡ፣ ቸነፈሩ ኹሉ ይታገሥልሃል›› አሏቸው፡፡ ዐፄ ዳዊትም ከብዙ ገጸ በረከት (ስጦታ) ጋር ‹‹የጌታችንን መስቀል ላኩልኝ›› የሚል መልእክት አስይዘው መልእክተኞችን ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱ፡፡ መልእክተኞቹም በታዘዙት መሠረት መስቀሉን ይዘው መምጣታቸውን ዐፄ ዳዊት ሲሰሙ ‹‹ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት›› ብለው መስቀሉን ለመቀበል ጉዞ ጀመሩ፡፡

ዐፄ ዳዊት ስናር (ሱዳን) ደርሰው ከመልእክተኞቹ ጋር ተገናኝተው መስቀሉን በክብር አጅበው ወደ መካከል ኢትዮጵያ ለማስገባት ሲነሡም ከበቅሏቸው ወድቀው ጥቅምት ፱ ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ በዚህም ሠራዊታቸው ተደናግጠው የጌታችንን መስቀል እዚያው ትተው የዐፄ ዳዊትን አስከሬን ይዘው ተመለሱ፡፡ መስቀሉ በስናር ከቆየ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዘርዐ ያዕቆብ ሲነግሡ ወደ መሃል ኢትዮጵያ አምጥተው ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ለማስቀመጥ ቢያስቡም ምቹ ቦታ ግን ሊያገኙ አልቻሉም ነበር፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው ምቹ ቦታ ሲፈልጉ መስቀሉን በኤረር ተራራ፣ በደብረ ብርሃን፣ በመናገሻ ማርያም ዓምባ፣ በእንጦጦ ጋራ ብዙ ጊዜ አስቀምጠውት ቆይተዋል፡፡

መስቀሉ በእንጦጦ ጋራ ሳለ እግዚአብሔር አምላክ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ›› የሚል ቃል ለንጉሡ በራእይ ነገራቸው፡፡ መስቀሉን ወደ ወሎ ሀገረ ስብከት እንዲወስዱትም አዘዛቸው፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው በእግዚአብሔር መሪነት መስቀሉን ይዘው ወሎ ሲደርሱም ጌታችን ወደ አምባሰል እያመለከተ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ›› ይላቸው ነበር፤ ንጉሡ መስቀሉን ይዘው ወደ ቦታው ሲያመሩ መስቀለኛው የግሸን ተራራን አገኙ፤ በዚያም ቤተ ክርስቲያን አሠርተው በ፲፬፻፵፮ (1446) ዓ.ም የጌታችንን መስቀል በክብር አስቀምጠውታል፡፡

ከዚህ በኋላ ንጉሡ ‹‹መካከሏ ገነት፤ ዳሯ እሳት ይኹን! የበረረ ወፍ፣ የሠገረ ቆቅ አይታደንባት! በድንገት ሰው የገደለ፣ ቋንጃ የቈረጠ ወንጀለኛ አይያዝባት!›› ብለው ዐዋጅ ነግረዋል፡፡ የእመቤታችን ጽላትም አብሮ በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ ስለዚህም መስከረም ፳፩ ቀን በየዓመቱ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡ ኀጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሐ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ምእመናን ኹሉ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ጤፉት በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መ/ር አፈወርቅ ተክሌ፤ ፳፻፭ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፤ ገጽ ፫፶፬-፫፶፮፡፡

የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የክርስቶስ የመስቀሉ ኃይል፣ የአባቶቻችን ሊቃውንትና ነገሥታት በረከት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የደመራው ምሥጢር

መስከረም ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ

demera-3

እግዚአብሔር አምላካችን የሠራቸው ታላላቅ ሥራዎች በምልክት የተገለጡ ናቸው፤ ለምሳሌ የሙሴ መስፍንነት፣ የአሮን ሊቀ ካህንነት የተረጋገጠው በአሮን በትር ምልክትነት ነው፡፡ አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ሊሠዋ በታዘዘ ጊዜ የሞርያን ተራራ የመረጠው እግዚአብሔር በተራራው ላይ ካሳየው ብርሃን የተነሣ ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምና ቅዱስ መስቀልም የድኅነታችን ምልክቶች ናቸው፡፡ የአሮንና የሙሴ በትሮች፣ የይስሐቅ ቤዛ የሚኾን በግ የተገኘባት ዕፀ ሳቤቅ ደግሞ የእመቤታችንና የመስቀል ምልክቶች ነበሩ፡፡ ወደ ፊት የምንወርሰው መንግሥተ ሰማያት ክርስቶስ ነው፤ እርሱን ደግሞ ያገኘነው ከመስቀል ላይ ነው፡፡

ጥንተ ጠላት ሰይጣን ይህንን ስለሚያውቅ ቅዱስ መስቀሉን አጥብቆ ይቃወመዋል፤ ስለዚህም አይሁድን አነሳሥቶ ከ፫፻ ዓመታት በላይ ተቀብሮ እንዲቆይ አድርጓል፡፡ በመሠረቱ ለሰይጣን ምሥጢሩ ስለማይገባው ነው እንጂ የመስቀሉ ትክክለኛ መቀበሪያ ሥፍራ የምእመናን ልቡና ነው፡፡ ቀራንዮ ለመስቀሉ መትከያነት የተመረጠችውም ቀዳሜ ፍጥረት አዳም የተቀበረው በዚያ ስለ ነበረ ነው፡፡ ቦታው ‹‹የራስ ቅል ሥፍራ›› /ማቴ.፳፯፥፴፪/ መባሉም የኹላችን ራስ አዳም ዓፅሙ በዚያ ስላረፈ ነው፡፡ መስቀሉ በአዳማውያን ፍጥረታት አእምሮ ውስጥ እንጂ ከዚያ ውጪ የሚኖር ባለመኾኑ ተቀብሮ በቆየባቸው ዓመታት ውስጥም ፍቅሩ ከሰው ልጆች ልቡና አልወጣም፡፡

ጠላት በሠራው ተንኮል ተቀብሮ እንዳይቀር መስቀሉን እንድታወጣ መንፈስ ቅዱስ ንግሥት ዕሌኒን አስነሣት፡፡ ይህች ሴት ቤቷ በሀብት፣ በንብረት ሞልቶ በነበረበት ጊዜና በገረድ፣ በደንገጡር በምትንቀሳቀስበት ወቅት ምን እንደ ሠራች አልተመዘገበላትም ነበር፤ ከክብሯ ወርዳ በተጣለችበት ጊዜ ግን እግዚአብሔር ለሚፈልገው ሥራ ምቹ ኾና ተገኘች፡፡ እርሷ በተጣለችበት ባዕድ አገር ውስጥ ኾና የመስቀሉን ነገር ታስብ፤ ብርሃነ መስቀሉም ዘወትር በልቧ ያንጸባርቅ ነበር፡፡ ሐሳቧን እንዲያሳካላት የለመነችው አምላክም ኪራኮስ የተባለውን አይሁዳዊ ሽማግሌ ልኮ አቅጣጫውን አመላከታት፤ ኪራኮስ የጀመረውን ምሥጢርም መልአኩ ‹‹ደመራ ደምረሽ፣ ሰንድሮስ የሚባል ነጭ ዕጣን ጨምረሽ አቃጥዪው›› ብሎ ተረጐመላት፡፡ እርሷም መልአኩ እንደ ነገራት ብታደርግ ጢሱ ሰማይ ደርሶ ወደ ምድር ተመልሶ መስቀሉ ወደሚገኝበት ተራራ ሰገደ፡፡ በጢሱ ምልክትነት መስከረም ፲፯ ቀን የተጀመረው ቍፋሮ መጋቢት ፲ ቀን አልቆ ዕሌኒ መስቀሉን ከልበ ምድር ለማውጣት ችላለች፡፡

መስቀልና ደመራ እንዲህ ነበር የተገናኙት፡፡ ደመራው ለመስቀሉ መገኘት፣ መስቀሉም ለደመራው መሠራት ምክንያት ናቸው፡፡ በዚህ አንጻር መለኮትና ትስብእት በአንድነት መደመራቸው መስቀሉ እንዲሠራ ምክንያት ኾነዋል፡፡ አምላካችን ሥጋ ለብሶ ‹ክርስቶስ› በሚል የተዋሕዶ ስም ሲጠራ ለመከራ መዘጋጀቱን እንረዳለን፡፡ መስቀሉ የሥጋ ብቻ ነበረ፤ አሁን ግን መለኮትም በሥጋ ባሕርይ የመስቀሉ ተካፋይ ኾነ፡፡ ይህም የደመራው ውጤት ነው፡፡ መለኮት አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዘመን መስቀል የተሸከመ ሥጋን ሲዋሐድ መስቀሉን አስወግዶ አልነበረም፡፡ ይኸው በዕፀ በለስ ምክንያት የተሸከምነው መስቀል ነው፡፡ ሥጋ ዓቅም አጥቶ መስቀሉን ከትከሻው ላይ ሳያወርድ ለዘመናት የተጓዘውን ጕዞ መለኮት ኀይል ኾኖት ድካሙን ሳይለቅ ኀያል፤ ኀይሉን ሳይለቅ ደካማ ኾነ፡፡ መስቀል ትርጕሙ መከራ ቢኾነም ነገር ግን እግዚአብሔር ሲያመጣውና ሰው ሲያመጣው ግን ትርጕሙ ይለያያል፤ ሰው ያመጣው መስቀል ኹላችንን ለመከራ፣ ለሞት አሳልፎ ሰጥቶናል፡፡ የእግዚአብሔር መስቀል ግን መከራነቱ ለሰይጣን እንጂ ለእኛ ሕይወታችን ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም ‹‹መስቀል ብሂል ዕፀ ሕይወት ብሂል፤ መስቀል ማለት የሕይወት ዛፍ ማለት ነው›› በማለት የመስቀልን ትርጕም ነግሮናል፡፡

አዳም ከገነት ሲወጣ በመላእክት እንዲጠበቅ የተደረገው የሕይወት ዛፍ የክርስቶስ መስቀል ነው፡፡ በዕፀ በለስ ምክንያት ኹላችንም እንደ ተጎዳን በዕፀ ሕይወቱም ተጠቃሚዎች ኾነናል፤ አስቀድመን በአዳም መከራ እንደ ተባበርን አሁን ደግሞ በደስታው እንተባበራለን፡፡ ሞትም ሕይወትም አንድ አድርጎናል፡፡ የክርስቶስ መስቀል ኹሉንም በሕይወት አስተባብሯልና፡፡ በአንጻሩ ሰውና ዲያብሎስን ለያይቷል፡፡ የኀጢአት ቁራኝነትን አጥፍቷል፡፡ ጌታችን በማኅፀን ሲፀነስ ጀምሮ የእኛን መስቀል መሸከም ሲጀምር የእርሱ የኾነውን ለእኛ ስለ ሰጠን ከሰይጣን ጋር መለያየታችን በመስቀሉ ተረጋግጧል፡፡ የአምላካችን መስቀል ምልክቱ ደመራ መኾኑ የእኛን ወደ እርሱ መሰብሰብና የጠላታችንን መበተን የሚያረግጥልን ነው፡፡ ጌታችንም ‹‹ወብየ ካልዓትኒ አባግዕ እለ ኢኮና እምዝንቱ ዐፀድ ወኪያሆንሂ ሀለወኒ አምጽኦን ዝየ፤ ከዚህ በረት ያልኾኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ላመጣቸው ይገባኛል›› በማለት ሊሰበስበን እንደ መጣ ነግሮናል /ዮሐ.፲፥፲፮/፡፡ መስቀሉ ፍጥረት አንድ ደመራ ኾኖ የተሠራበት ስለ ኾነ በደመራ እንዲገለጥ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ኾነ፡፡

መስቀሉ አንድ ደመራ ያደረጋቸው ፍጥረታት

፩. ነቢያትና ሐዋርያት

ነቢያት የሚባሉት ከአዳም እስከ ዮሐንስ መጥምቅ ያሉ አባቶች ሲኾኑ፣ ከክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ጀምሮ ለቤተ ክርስቲያን የወንጌልን የምሥራች እንዲነግሩ የተላኩ አባቶች ደግሞ ሐዋርያት ይባላሉ፡፡ በእርግጥ ሐዋርያ የኾነ ነቢይ የለም እንጂ ነቢይ የኾነ ሐዋርያ አለ፡፡ ነቢያትና ሐዋርያት በዘመን፣ በክብር እና በግብር የማይገናኙ ፍጥረታት ናቸው፡፡ መንፈሰ ረድኤት የተሰጣቸው ነቢያት ለሐዋርያት የተሰጠውን መንፈሰ ልደት ለማግኘት አልተቻላቸውም፡፡ ሐዋርያት ግን ኹሉንም አንድ አድርገው ይዘዋል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ስለዚህ ሲመሰክር ‹‹በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጠን›› በማለት አጕልቶ የተናገረው /ዮሐ.፲፥፲፰/፡፡ ነቢያት በዚህ ምድር የእግዚአብሔርን መንግሥት በመፈለግ ብዙ ደክመዋል፡፡

ሊቃውንቱ ነቢያትን በክረምት፣ ሐዋርያትን በበጋ ገበሬ ይመስሏቸዋል፡፡ የክረምት ገበሬ ላዩ ውሃ፣ ታቹ ውሃ ኾኖበት በጭቃ ወጥቶ በጭቃ ይመለሳል፡፡ ወደ ቤቱ ሲገባም ሚስቱ ጨምቃ ያቆየችለትን ጐመን በልቶ ደስ ሳይለው ይተኛል፡፡ ነቢያትም በዚህ ዓለም በጣዖት አምላኪ ነገሥታት፣ በነቢያተ ሐሰት ስብከት ሲንገላቱ ኖረው ሲሞቱም ሲዖል ይገባሉ እንጂ ገነትን አይወርሱም ነበር፡፡ የበጋ ገበሬ በደረቅ ወጥቶ፣ እሸት በልቶ፣ ተደስቶ ወደ ቤቱ ይመለሳል፤ ከቤቱ ሲገባም እንጀራው በሌማት፣ ጠላው በማቶት፣ ሲቀርብለት ደስ ብሎት ይበላል፤ ይጠጣል፡፡ ሐዋርያትም ልጅነትን አግኝተው ለማስተማር ተልከዋል፤ በሔዱበት ኹሉ ተአምራትን እንዲያደርጉ፣ ልጅነትንም እንዲሰጡ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሞታቸው ሲደርስም መንግሥተ ሰማያት ተከፍቶ ይጠብቃቸዋል፡፡

ቅዱስ ያሬድም ‹‹ኖትያት ነቢያት ራግናት ሐዋርያት›› በማለት ነቢያትን በዋናተኛ፣ ሐዋርያትን በጀልባ ቀዛፊ መስሎ ይናገራል፡፡ ከቀዛፊዎች ይልቅ ዋናተኞች ይደክማሉ፡፡ ዋናተኞች ውሃው አጥልቋቸው፣ መተንፈስ ተስኗቸው አንዳንዶቹ ከዳር ይደርሳሉ፤ አንዳንዶቹም በድካም በውሃ ውስጥ ሰጥመው ይቀራሉ፡፡ ቀዛፊዎች ግን ምናልባት ሞገድና ማዕበል ካላሰጋቸው በስተቀር ይህ ኹሉ ውጣ ውረድ የለባቸውም፤ በጀልባዋ የተመሰለችው ቤተ ክርስቲያን ለነቢያት በተስፋ እንጂ በአካላ አልተሰጠችም፡፡ ነቢያት ከእርሷ ሳይደርሱ ሞት ቀድሟቸዋል፡፡ ሐዋርያትም በነቢያት ድካም ገብተው ነቢያት የዘሩትን የትንቢት ዘር አጭደዋል፡፡ ወንጌል የነቢያት ዘር ናት፤ ዳሩ ግን ፍሬውን ለመብላት የታደሉት ሐዋርያት ናቸው፡፡ እሸቱ ሲደርስ የገበሬዎቹ የነቢያት ጌታ ክርስቶስ ዘሩን እንዲሰበስቡና እንዲያከማቹ ሐዋርያቱን በእርሻ መካከል ይዟቸው ገብቷል /ማቴ.፲፪፥፩/፡፡ በአበው ፋንታ ውሉድን ለመተካት የመጣው መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነቢያትንና ሐዋርያትን በመስቀሉ አንድ ማኅበር አደረጋቸው፡፡ ሐዋርያው መስቀሉን ‹‹ገባሬ ሰላም›› በማለት ይጠራዋል /ኤፌ.፪፥፲፫/፡፡ ነቢያትንና ሐዋርያትን አንድ አድርጎ የእግዚአብሔርን መንግሥት ያወረሰ የክርስቶስ መስቀል ነውና፡፡

፪. ሙታንና ሕያዋን

አዳም በዕፀ በለስ ምክንያት የተሸከመው መስቀል ሞትን አምጥቶብናል፤ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ድኅነት ሲል የተሸከመው መስቀል ግን ሞትን ገድሎ ሕይወትን ሰጥቶናል፡፡ በዚህ ምክንያት የሞት መውጊያ ሲሰበር፣ የመቃብር ስቃይ ሲቋረጥ፣ የጨለማ ኀይል ሲሻር ከመስቀሉ ሥር ብዙ ሙታን እንደ አሸን ብቅ ብቅ አሉ፡፡ ምድር እስከዚያች ቀን ድረስ ሙታንን ትቀበል ነበር እንጂ ሕያዋንን ማስገኘት አትችልም ነበር፡፡ ሙታንና ሕያዋን የተፈላለጉበት መስቀል የመጀመሪያው ቀን ነው፡፡ በመስቀል ሙታን ሕያዋንን ፍለጋ ከመቃብር ወጥተው ወደ ከተማ ገቡ፡፡ ከታደለው የሕይወት ስጦታ የተነሣ ሞት አካባቢውን ለቆ ስለጠፋ በሩ እንደ ተከፈተለት እሥረኛ ሙታን ከመቃብር እየወጡ ከተማውን ሞልተውታል፡፡ ይህ ዕለት ሙታንን ከሕያዋን ጋር አፍ ለአፍ ያነጋገረ ዕለት ነው፡፡ ደመራው ሙታንን ከሕያዋን የሚለይ አይደለም፤ ታላቅነቱም እስከ ሲዖል ድረስ የሚታይ ነው፡፡

፫. ጻድቃንና ኀጥአን

የአዳም በደል በሕይወት የሚኖሩ ወንድማማቾችን በሁለት ሐሳብ ከፋፍሏቸው ነበር፡፡ የክርስቶስ የጽድቅ መስቀል ግን አንድ ሐሳብ ፈጠረላቸው፡፡ ጻድቁ አቤል ሳይበድል በደል የደረሰበት፣ ሳይገድል የተገደለ መኾኑ ከክርስቶስ ጋር ቢያመሳስለውም ሞቱ ግን ለሰው ልጆች ድኅነት አልጠቀመም፤ የፍጡር ደም ከእግዚአብሔር ጋር ሊያስታርቀን አይችልምና ኹላችንም በመከራ ውስጥ ለመቆየት ተገደናል፡፡ የክርስቶስ ሞት ግን የድኅነታችን መሠረት ኾነልን፡፡ በቤት ውስጥ የሚዘጋጅ መብራት ከፍ ብሎ ሲቀመጥ ኹሉን እንዲያሳይ ከምድር ከፍ ብሎ የተሰቀለው ክርስቶስም ጻድቃነ ብሊትንና ጻድቃነ ሐዲስን በዓይን እንዲተያዩ አድርጓቸዋል፡፡ በመስቀል ላይ የተፈጸመው ዕርቅ የኀጥአንን በደል ደምስሶላቸዋል፤ የጻድቃንን ጽድቅ አረጋግጦላቸዋል፡፡ ጻድቃንም ኀጥአንም አንድ ኾነው መንግሥቱን በጸጋው ወረሱ፡፡ ኢያሱ በኢያሪኮ እንዳደረገው አሞራውያን ወጥተው እስራኤል ብቻ ምድሪቱን የወረሷት አይደሉም፡፡ መስቀሉ ለኹሉም አንድ መንግሥትን አውርሷቸዋል፤ ጊዜው የደመራ ነውና፡፡ በምድር ደምቆ የታየው ይህ ደመራ እስከ መንግሥተ ሰማያት ድረስም ይቀጥላል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ክብረ መስቀል በኢትዮጵያ

መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም 

በዝግጅት ክፍሉ

cross

‹መስቀል› ስንል ሦስት መሠረታዊ ቁም ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል፤ የመጀመሪያው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከሞተ ነፍስ ለማዳን ሲል የተቀበለው መከራና የከፈለው መሥዋዕትነት መስቀል ይባላል፡፡ ሁለተኛው በክርስትና ውስጥ የሚያጋጥም ልዩ ልዩ ዓይነት መከራም መስቀል ነው፡፡ ጌታችን ‹‹እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ›› /ማቴ.፲፮፥፳፬/ በማለት መናገሩም በክርስትና ሕይወት ውስጥ የሚደርሰውን ይህንኑ መከራ መታገሥ ተገቢ መኾኑን ሲያመለክተን ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ጌታችን የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል ሲኾን በሦስቱም ቁም ነገሮች ነገረ መስቀል (የመስቀሉ ነገር) ከክርስትና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ ስለ ክርስትና ሕይወት ሲነሣ ነገረ መስቀልም አብሮ ይታወሳል፡፡ ስለ ክርስትና ሲነገር ክርስቶስ የተቀበለው መከራ፣ የተሰቃየበትና ነፍሱን በፈቃዱ አሳልፎ የሰጠበት ዕፀ መስቀል፣ በክርስትና ሕይወት ውስጥ የሚከሠት ፈተና አብረው የሚነሡ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ስለ መስቀል ሲነገር ክርስቶስ ሰውን ለማዳን ሲል በሥጋው የተቀበለው ስቃይ፤ ሰማዕታት በሃይማኖታቸው ምክንያት የሚደርስባቸው ስደት፣ መከራና ሞት፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ በአረማውያንም በውስጥ ጠላቶችም የሚያጋጥማት የዘረፋና የቃጠሎ፣ እንደዚሁም የሰላም እጦትና የመልካም አስተዳደር እጥረት፤ በተጨማሪም በክርስትና ሕይወት ውስጥ የሚከሠቱ የኑሮ ውጣ ውረዶች መስቀልና ክርስትና የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ለመኾናቸው ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ከዚሁ ኹሉ ጋርም መስቀል ሲባል ክርስቶስ መከራ የተቀበለበት፣ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው የለየበት፣ ድንቅ ተአምራትን ያደረገበት፣ ከኹሉም በላይ ለአዳምና ለልጆቹ ነጻነትን ያወጀበት ዕፀ መስቀልም አንዱ የክርስትናችን አካል ነው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በጉልላቷና በሌሎችም ንዋያተ ቅድሳቷ መስቀልን እንደ ምልክት ትጠቀመዋለች፡፡ መሠረቷ፣ የልጆቿ መድኀኒት ክርስቶስ በመስቀል ላይ የከፈለው ዋጋ ነውና ሰንደቅ ዓላማዋ መስቀል ነው፡፡ አባቶች ካህናት ጸሎት ሲያደርጉ ‹‹ከመስቀሉ ዓላማ፣ ከወንጌሉ ከተማ አያውጣን›› እያሉ የሚመርቁትም ስለዚህ ነው፡፡ በእጃቸው ይዘውት የሚንቀሳቀሱት፣ እኛንም የሚባርኩትም በመስቀል ነው፡፡

መስቀል የጠላት ሰይጣን ተንኮል የከሸፈበት፣ የክርስቶስ ቤዛነት የተረጋገጠበት የድኅነት ኃይል ነውና፡፡ በየገዳማቱና በየአብነት ት/ቤቱ፤ እንደዚሁም በክርስቲያኖች መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በሚከናወኑ ተግባራት መስቀል ሰፊ ድርሻ አለው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ፣ በጠበል ቦታ፣ በጸሎት ጊዜያት፣ ወዘተ ቡራኬ የሚፈጸመው በመስቀል በማማተብ ነው፡፡ የመስቀሉን ምልክት ባዩ ጊዜ አጋንንት ይንቀጠቀጣሉ፤ ካደሩበት ሰው ላይም በፍጥነት ይወጣሉ፡፡ ምእመናን በመስቀሉ ስንዳሰስ ከልዩ ልዩ ደዌ እንፈወሳለን፡፡

ወደ አገራችን ክርስቲያናዊ ባህል ስንመለስ በኢትዮጵያ የመድኀኒታችን የክርስቶስ መስቀል በብዙ ተግባራት ላይ በምልክትነት ጥቅም ላይ ሲውል ይታያል፡፡ ለምሳሌ በቡልኮ፣ ጋቢ፣ ነጠላ፣ ቀሚስ ወዘተ የመሳሰሉ የሸማ ልብሶች፤ እንደዚሁም በጆሮ፣ በአንገት፣ በእጅና ሌሎችም ጌጣጌጦች ላይ የመስቀል ምልክት አለ፡፡ ክርስቲያን ልጃገረዶች (በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል) በግንባራቸው፣ በጉንጫቸው፣ በአንገታቸው፣ በደረታቸውና በእጃቸው ላይ በመስቀል ቅርፅ እየተነቀሱ ያጌጡበታል፡፡

ክርስቲያኖች ከዚህ ዓለም በሞት ስንለይም በመቃብር ሣጥናችን ወይም በሐውልቶቻችን ላይ የመስቀል ምልክት ይቀመጣል፡፡ በቤት ውስጥም ስንተኛና ከእንቅልፋችን ስንነቃ ፊታችንንና መላ ሰውነታችንን በትእምርተ መስቀል እናማትባለን፤ አባቶችና እናቶችም ውሃ ሲቀዱ፣ ሊጥ ሲያቦኩ፣ እንጀራ ሲጋግሩ፣ ምግብ ሲቈርሱ፣ ወዘተ በመስቀል አማትበው ነው፡፡ በአጠቃላይ መስቀል ብዙ ነገር ነው፤ መስቀል በክርስትና ሕይወት ውስጥ በሚደረጉ ተግባራት ኹሉ ያለው ድርሻ ጕልህ ነው፡፡ /ለተጨማሪ መረጃ ግሸን ደብረ ከርቤ የቃል ኪዳን አምባ፣ መስከረም ፲፱፻፺፮ ዓ.ም፤ ገጽ ፺፮-፻፪ ይመልከቱ/፡፡

ከዓለም ክርስቲያኖች በበለጠ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የተለየ እምነትና አክብሮት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ጌታችን ሰውን ለማዳን ሲል ብዙ ጸዋትወ መከራ የተቀበለበትንና ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ ያገኘንበት መስቀልን ለአፍታም ያህል የማያስታዉሱበት ቅፅበት ባይኖራቸውም በዓመት ለአምስት ጊዜያት ያህል በቤተ ክርስቲያንና በዐደባባይ ያከብሩታል፡፡

በዚህም መሠረት በዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ግማደ መስቀሉ ከእስክንድርያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን የመታሰቢያ በዓል በየዓመቱ መስከረም ፲ ቀን ቀደም ባለው ወቅት በነገሥታቱ፣ በመሳፍንቱና በመኳንንቱ ፊት በቤተ መንግሥት ያከብሩት ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከካህናትና ከምእመናን ጋር በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ያከብሩታል፡፡

እንደዚሁም በ፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ንግሥት ዕሌኒ በዕጣን ጢስ አመልካችነት መስቀሉን ከተቀበረበት ቦታ ለማውጣት ቍፋሮ ያስጀመረችበትን የመታሰቢያ በዓል በየዓመቱ መስከረም ፲፮ ቀን ደመራ ደምረው በመለኮስ በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዓት በዐደባባይ ያከብሩታል፡፡ በማግሥቱ መስከረም ፲፯ ቀንም ንግሥት ዕሌኒ ቅዳሴ ቤቱን ያከበረችበትን የመታሰቢያ በዓል ታቦት አውጥተው ዑደት በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ያከብሩታል፡፡

በማያያዝም መስከረም ፳፩ ቀን ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት በግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም በታላቅ በዓለ ንግሥ ያከብሩታል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ መስቀሉ ከተቀበረበት ተራራ ተቈፍሮ የወጣበት መጋቢት ፲ ቀንም በቤተ ክርስቲያን በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ /ምንጭ፡- የ፳፻፱ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓልን በማስመልከት በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የተዘጋጀ ልዩ ዕትም መጽሔት፣ ገጽ ፪/፡፡

በክርስቶስ ደም የተቀደሰው ይህ ክቡር መስቀል ለበርካታ ዓመታት በአይሁድ ምቀኝነት በጎልጎታ ተቀብሮ ከኖረ በኋላ በንግሥት ዕሌኒና በልጇ ቈስጠንጢኖስ ጥረት ከተቀበረበት ወጥቶ ከፀሐይ ብርሃን በላይ አብርቷል፤ ሙት በማስነሣት፣ ሕሙማንን በመፈወስ ብዙ ተአምራትን አሳይቷል፡፡ በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ደመራ ተደምሮ በዓሉ የሚከበረውም ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ለማግኘት ከእግዚአብሔር መልአክ በተሰጣት አቅጣጫ መሠረት ያነደደችውን ዕጣንና የመስቀሉን መገኛ የጠቆማትን ጢስ ለማስታዎስ ነው፡፡

እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን! በንጉሥ ዳዊትና በልጃቸው በዘርዐ ያዕቆብ አማካይነት ወደ አገራችን የመጣው የጌታችን መስቀል ቀኝ ክፍል በአገራችን ኢትዮጵያ በደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በግሸን ደብረ ከርቤ ይገኛል፡፡ ከቅዱስ መስቀሉና ከገዳሙ በረከት ለመሳተፍ ብዙ ምእመናን በየዓመቱ ቦታው ድረስ በመሔድ በዓለ መስቀልን ያከብራሉ፡፡

በዓለ መስቀል በቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን በየመንደሩና በየቤቱም ምእመናን ደመራ በመደመር፣ ጸበል ጸሪቅ በማዘጋጀት በድምቀት ያከብሩታል፡፡ በተለይ በደቡቡ የአገራችን ክፍል በዓለ መስቀል በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ይህም የቀደሙ አባቶቻችን ስለ በዓለ መስቀል ይሰጡት የነበረው ትምህርት ቁም ነገር ላይ መዋሉን የሚያስረዳ መንፈሳዊ ትውፊት ነው፡፡ የአከባበሩ ባህል ከቦታ ቦታ ይለያይ እንጂ በዓለ መስቀል በየዓመቱ በመስከረም አጋማሽ በመላው ኢትዮጵያ በልዩ ድምቀትና በመንፈሳዊ ሥርዓት ይከበራል፡፡

በአጠቃላይ በአገራችን ኢትዮጵያ መስቀልና ክርስትና እንዲህ ሳይነጣጠሉ ተሳስረው ይኖራሉ፡፡ እኛም አባቶቻችን እንዳስተማሩን ይህንን በክርስቶስ ደም የተቀደሰውን መስቀል በዘወትር ጸሎታችን ‹‹… መስቀል ኃይልነ መስቀል ጽንዕነ መስቀል ቤዛነ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ አይሁድ ክህዱ ንሕነሰ አመነ ወእለ አመነ በኃይለ መስቀሉ ድኅነ፤ … መስቀል ኀይላችን፣ ጽንዓችን፣ ቤዛችን፣ የነፍሳችን መዳኛ ነው፡፡ አይሁድ ይክዱታል፤ እኛ ግን እናምንበታለን፡፡ ያመነውም እኛ በመስቀሉ ኀይል እንድናለን፤ ድነናልም›› እያልን ለመስቀሉ ያለንን ክብር እንገልጻለን፤ በክርስቶስ መስቀል ኀይል መዳናችንንም ስንመሰክር እንኖራለን፡፡ ልዑል እግዚአብሔር በመስቀሉ ኃይል ኹላችንንም ከልዩ ልዩ ዓይነት መከራ ይጠብቀን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ጼዴንያ

መስከረም ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዝግጅት ክፍሉ

maryam

በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ መስከረም ፲ ቀን ከሚዘከሩ በዓላት መካከል የእመቤታችን በዓል አንደኛው ሲኾን ይኸውም ጼዴንያ በምትባል አገር ከሥዕሏ ተአምር የተደረገበት ዕለት ነው፡፡ በተአምረ ማርያምና በመጽሐፈ ስንክሳር እንደ ተመዘገበው ቅዱስ ሉቃስ ከሣላት ሥጋ የለበሰች ከምትመስል የእመቤታችን የሥዕል ሠሌዳ ቅባት ይንጠፈጠፍ ነበር፡፡

እመቤታችን ድንግል ማርያምን የምትወድና በሚቻላትም ኹሉ የምታገለግላት፣ ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች አንዲት ማርታ የምትባል ሴት ነበረች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አባ ቴዎድሮስ የሚባሉ መነኵሴ ከእርሷ ዘንድ በእንግድነት አድረው በማግሥቱ ከቤቷ ሲወጡ ማርታ የሚሔዱበትን አገር በጠየቀቻቸው ጊዜ  እርሳቸውም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው ቅዱሳት መካናትን እንደሚሳለሙ ነገሯት፡፡

ማርታም ከእርሷ ገንዘብ ወስደው የእመቤታችንን ሥዕል ገዝተው ይዘውላት እንዲመጡ ለመነቻቸው፡፡ መነኵሴውም በራሳቸው ገንዘብ ሥዕሉን ገዝተው እንደሚያመጡላት ቃል ገቡላት፡፡ አባ ቴዎድሮስ ኢየሩሳሌም ደርሰው ቅዱሳት መካናትን ከተሳለሙ በኋላ ሥዕሏን ሳይገዙ ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ ያን ጊዜም ‹‹ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ?›› የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰምተው ወደ ገበያ ተመልሰው መልኳ ያማረና የተወደደ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል ገዝተው በሐርና በንጹሕ ልብስ ጠቅልለው ይዘው እየተጓዙ ሳሉ ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ሲደርሱ ወንበዴዎች ተነሡባቸው፡፡ ሊሸሹ ሲሉም ‹‹መንገድህን ሒድ›› የሚል ቃል ከሥዕሏ ወጣ፤ መነኵሴውም መንገዳቸውን በሰላም ተጓዙ፡፡ ሁለተኛም አንበሳ ሊበላቸው በተነሣባቸው ጊዜ ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረላቸው፡፡

አባ ቴዎድሮስ ይህን ኹሉ ድንቅ ተአምር ባዩ ጊዜም ያቺን ሥዕል ለማርታ ከመስጠት ይልቅ ወደ አገራቸው ሊወስዷት ወደዱ፡፡ በመርከብ ተሳፍረው በሌላ አቅጣጫ ሲሔዱም ታላቅ ነፋስ ተነሥቶ ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያ ወሰዳቸው፡፡ ከመርከብም ወርደው ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ደረሱ፡፡ ነገር ግን ማንነታቸውን ለማርታ አልገለጡላትም፤ እርሷም አላወቀቻቸውም ነበር፡፡

በማግሥቱም ተሠውረው ወደ አገራቸው ሊሔዱ ሲሉ የቅፅሩ ደጃፍ ጠፍቶባቸው ሲፈልጉ ዋሉ፤ በመሸባቸው ጊዜም ወደ ማደሪያቸው ተመለሱ፡፡ ማታ ማታ በሩን ያዩታል፤ ነግቶ መሔድን ሲሹ ግን የበሩ መንገድ ይሠወርባቸዋል፡፡ እንዲህም ኾነው እስከ ሦስት ቀን ድረስ ቆዩ፡፡ ማርታም ‹‹አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን? ስትቅበዘበዝ አይሃለሁና ምን ኾነህ ነው?›› ሰትል ጠየቀቻችው፡፡ እርሳቸውም ከእመቤታችን ሥዕል የተደረገውን ተአምር ኹሉ ነገሯት፤ ራሳቸውንም ገለጡላትና ሥዕሏን ሰጧት፡፡ እርሷም የእመቤታችንን ሥዕል ተቀብላ የተጠቀለለችበትን ልብስ በፈታችው ጊዜ ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች፡፡ ከደስታዋ ብዛት የተነሣም የአባ ቴዎድሮስን እጃቸውንና እግራቸውን ሳመች፡፡

ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር አኖረቻት፡፡ ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስ መስኮትን ሠራችላት፡፡ በቀንና በሌሊትም የሚያበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች፤ ከመቅረዞች ውጭም የሐር መጋረጃን ጋረደች፡፡ ከሥዕሊቱ በታችም እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሠራ ወጭት አኖረች፡፡ እኒያ መነኰስም እስከሚሞቱበት ቀን ድረስ የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ሥዕል እያገለገሉ ኖሩ፡፡

የአገሩ ሊቀ ጳጳስም የእመቤታችን ሥዕል ሥጋ የለበሰች ኹና ባገኙና ተአምሯንም በተመለከቱ ጊዜ ከዚህ አምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ፡፡ ከሥዕሏ ከሚንጠባጠበው ቅባት ቀድተው ለበረከት ሲካፈሉም ወዲያውኑ በወጭቱ ውስጥ መላ፡፡ ሥዕሊቱን ወደ ሌላ ቦታም ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜም ንውጽውጽታ ኾኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ፡፡ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ ድረስ በዚያች አገር (በጼዴንያ) ትገኛለች፡፡

‹‹እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /መዝ.፷፯፥፴፭/ እግዚአብሔር አምላካችን በልዩ ልዩ መንገድ ለሰው ልጅ ተአምራቱን ይገልጣል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናገኘው እግዚአብሔር ከዓለት ላይ ውኃ እያፈለቀ ሕዝቡን ያጠጣል፡፡ ከግዑዝ ዓለት ውስጥ ውኃ የሚያፈልቅ አምላክ ከሥጋዋ ሥጋ፤ ከነፍሷ ነፍስ ተዋሕዶ ካከበራት ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ወዝ እንዲፈስ ቢያደርግ ምን ይሳነዋል? እንደዚሁም ቅዱሳን ሐዋርያት በቃላቸውም፣ በልብሳቸውም፣ በጥላቸውም ሙታንን በማስነሣት፤ ሕሙማንን በመፈወስ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላው፤ ቅዱስ ጳውሎስም በልብሱ ቅዳጅ ያደርጓቸው የነበሩ ተአምራትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሐዋርያት ከእግዚአብሔር ዘንድ በተሰጣቸው ጸጋ በልብሳቸውና በሰውነታቸው ጥላ ተአምራትን ማድረግ እንደ ተቻላቸው ኹሉ አምላክን በማኅፀኗ የተሸከመችው ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያምም በሥዕሏ ወዝ ብዙ ሕሙማንን መፈወስ ይቻላታል፡፡ ከቅዱሳን ልብስና ጥላ የእርሷ ሥዕል ይከብራልና፡፡ ስለዚህም ነው በየዓመቱ መስከረም ፲ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት የሚከበረው፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፤ የልጇ፣ የወዳጇ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ወርኀ ጳጕሜን አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት

ጳጕሜን ፬ ቀን ፳፻፰ .

የኢትዮጵያን የዘመን አቈጣጠር ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ‹ጳጕሜን› የምትባል 13ኛ ወር ስላለችን ነው፡፡ የቤት ኪራይና የወር ደመወዝ የማንከፍልባትና የማንቀበልባት፤ መብራትና ውኃ ግን ከነሐሴ ወር ጋር ጨምረው የሚያስከፍሉባት፤ ሲሻት አምስት፣ ሲያስፈልጋት ስድስት፣ ስትፈልግ ደግሞ ሰባት የምትኾን ወር ናት፡፡ ከዐሥራ ሁለቱ የኢትዮጵያ ወሮች መካከል ወርኀ ጳጕሜን በብዙ መንገድ የተለየች ናት፡፡

በአንድ በኩል በጣም ትንሿ ወር ናት፡፡ ሲቀጥልም ወርኃዊ በዓላት የማይውሉባት ወር ናት፡፡ ደግሞም ከሌሎች ወሮች በተለየ የቀኖቿ መጠን የሚቀያየሩ ብቸኛ ወር ናት፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወሮች በተለየም ስሟ ኢትዮጵያዊ ያልኾነ ወር ናት፡፡ በሁለት ዘመናት መካከል እንደ መሸጋገሪያ የምትታይ ወርም ናት፡፡

‹ጳጕሜ› ማለት በግሪክ ቋንቋ ‹ጭማሪ› ማለት ሲኾን ዓመቱ በሠላሳ ቀናት ሲከፈል የሚተርፉት ዕለታት ተሰባስበው የሚያስገኟት ተጨማሪ ወር ናት፡፡ ወይም በየዕለቱ በፀሐይና በጨረቃ አቈጣጠር መካከል የሚፈጠሩት ልዩነቶች ተሰባስበው የተከማቹባት ወር ትባላለች፡፡

ዓመቱ በዐውደ ፀሐይ ሲለካ 365 ቀናት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ሲኾን፣ በጨረቃ ሲለካ ደግሞ 354 ቀናት ከ22 ኬክሮስ፣ ከ1 ካልዒት፣ ከ36 ሣልሲት፣ ከ52 ራብዒት፣ ከ48 ኀምሲት ነው፡፡ በሁለቱ አቈጣጠር መካከል (በፀሐይና በጨረቃ) በዓመት ውስጥ ያለው ልዩነት 11 ቀናት ከ7 ኬክሮስ ይኾናል፡፡

በዘመን አቈጣጠራችን ውስጥ ከዕለት በታች የምንቈጥርባቸው ስድስት መለኪያዎች አሉ፡፡ እነዚህም ኬክሮስ፣ ካልዒት፣ ሣልሲት፣ ራብዒት፣ ኀምሲትና ሳድሲት ናቸው፡፡ 60 ሳድሲት 1 ኀምሲት፣ 60 ኀምሲት 1 ራብዒት፣ 60 ራብዒት 1 ሣልሲት፣ 60 ሣልሲት 1 ካልዒት፣ 60 ካልዒት ደግሞ 1 ኬክሮስ ይኾናል፡፡ 60 ኬክሮስ ደግሞ 1 ዕለት፤ 1 ኬክሮስ 24 ደቂቃ ነው፡፡ ወርኀ ጳጕሜንን ለማግኘት የሚረዳንም የየዕለቱን ልዩነታቸውን መመልከቱ ነው፡፡

በየዕለቱ በጨረቃና በፀሐይ መካከል 1 ኬክሮስ ከ52 ካልዒት ከ31 ሣልሲት ይኾናል፡፡ ይህም ማለት 5 ሰዓት ከ48 ደቂቃ ከ46 ካልዒት (ሴኮንድ?) ነው፤ ይህ ልዩነት በአንድ ወር ምን ያህል እንደሚደርስ ለማወቅ በ30 ብናበዛው 30 ኬክሮስ ከ1560 ካልዒት፣ ከ930 ሣልሲት ይኾናል፡፡ የዓመቱን ለማግኘት ደግሞ በ12 ብናበዛው 360 ኬክሮስ ከ18720 ካልዒት፣ ከ11160 ሣልሲት ይመጣል፡፡

ቀደም ብለን 60 ኬክሮስ አንድ ዕለት ይኾናል ባልነው መሠረት 360 ኬክሮስ ለ60 ሲካፈል 6 ዕለታትን ይሰጠናል፡፡ 18720 ካልዒትን በስድሳ በማካፈል 312 ኬክሮስን እናገኛለን፡፡ ያም ማለት ትርፉን 12 ኬክሮስ ትተን 300ውን ኬክሮስ ለ60 በማካፈል 5 ዕለት እናገኛለን ማለት  ነው፡፡ ይኼም 5 ዕለት ከ12 ኬክሮስ ይኾናል፡፡ 11160 ሣልሲትን ለ60 ብናካፍለው 186 ካልዒት ወይም ደግሞ 3 ኬክሮስና 6 ካልዒት ይኾናል ማለት ነው፡፡

ከላይ ኬክሮስን በዓመቱ ቀናት አባዝተን ያገኘነው 6 ዕለት ሕጸጽ ይባላል፡፡ ፀሐይና ጨረቃን እኩል መስከረም አንድ ላይ ዓመቱን ብናስጀምራቸው ፀሐይ የወሯ መጠን ምንጊዜም 30 ሲሆን ጨረቃ ግን በአንደኛው ወር 29 በሌላኛው ወር ደግሞ 30 ስለምትኾን ዓመቱ እኩል አያልቅም፤ የጨረቃ ዓመት የሚያልቀው ነሐሴ 24 ቀን ነው፡፡ ይህም ማለት ጨረቃ በሁለት ወር አንድ ጕድለት ታመጣለች ማለት ነው፡፡

ይህንን ነው ሊቃውንቱ ሕጸጽ (ጕድለት) ያሉት፡፡ በዚህም መሠረት ከላይ ኬክሮሱን በዓመቱ ቀናት አባዝተን ያገኘነውን 6 ዕለት ለጨረቃ ሕጸጽ ስንሰጠው የመስከረም /ጥቅምት 1፣ የጥቅምት /ኅዳር 2፣ የጥር /የካቲት 3፣ የመጋቢት /ሚያዝያ 4፣ የግንቦት /ሰኔ 5፣ የሐምሌ /ነሐሴ 6 ኾነው ተካፍለው ያልቃሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በጨረቃና በፀሐይ ዑደት መካከል በዓመት ያለው ልዩነት 11 ቀናት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ይኾናል፡፡ ስድስቱን ዕለታት ጨረቃ ለምታጋድልበት ሕጸጽ ብንሰጠው ቀሪ 5 ዕለት ይኖረናል፡፡ ወርኀ ጳጕሜን ማለት እነዚህ 5 ቀናት ናቸው፡፡

አሁን የዐሥራ አንዱን ዕለታት ከፈጸምን ሽርፍራፊዎቹን (15 ኬክሮስና 6 ካልዒት) እንመልከት፤
ከላይ እንደ ተመለከትነው በፀሐይና ጨረቃ ዓመታት መካከል የተፈጠሩትን 11 ቀናት ስድስቱ ለሕጸጽ ማሟያ ሲገቡ የቀሩት 5 ዕለታት ናቸው ጳጕሜን የምትባለውን ወር ያስገኟት፡፡

በጎርጎርዮሳውያኑ አቈጣጠር እነዚህ 5ቱ ዕለታት በጃንዋሪ፣ ማርች፣ ሜይ፣ ጁላይና ኦገስት ላይ ስለ ተጨመሩ ወሮቹ 31 ሊኾኑ ችለዋል፡፡ ይህንን የከፈለው በ46 ቅልክ የነበረው ዩልየስ ቄሣር ነው፡፡ ለአራቱ ወሮች 30 ቀን፣ ለአንዱ 28/29 (በየአራት ዓመቱ)፣ ለቀሩት ሰባት ወሮች ደግሞ 31 ቀን ሰጥቷቸዋል፤ ለአምስቱ ወሮች 31 ያደረጋቸው ከጳጕሜን ወስዶ ሲኾን ለሁለቱ ወሮች አንዳንድ ቀን የጨመረላቸው ደግሞ ከፌቡርዋሪ 2 ቀናት ወስዶ ወሩን 28 በማድረግ ነው፡፡

ከእንግዲህ የሚተርፉት ከላይ የየዕለቱን ልዩነት በዓመት ስናባዛ የቀሩት 15 ኬክሮስና 6 ካልዒት ናቸው፡፡ ሁለቱን ከላይ ያየናቸውን ስንደምራቸው (12 ኬክሮስ + 3 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት) 15 ኬክሮስ ከ 6 ካልዒት ይመጣሉ፡፡ 1 ዕለት 60 ኬክሮስ በመኾኑ 1 ዕለትን (60 ኬክሮስን) ለማግኘት ከላይ ያገኘነውን 15 ኬክሮስ በ4 ማባዛት ይኖርብናል፡፡

በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ጳጕሜን 6 ቀን የምትኾነውም እነዚህ በየዓመቱ የተሰባሰቡ 15 ኬክሮሶች አንድ ላይ መጥተው በአራት ዓመት አንድ ጊዜ አንድ ዕለት ስለሚኾኑ ነው፡፡ እርሷም ሠግር (leap year) ትባላለች፡፡ ጎርጎርዮሳውያኑ ይህቺን ሠግር በፌቡርዋሪ ወር ላይ ጨምረው ወሩን በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ 29 ቀን ያደርጉታል፡፡

15ቱ ኬክሮስ በአራት ዓመት ተደምረው አንድ ዕለት መጡና በአራት ዓመት አንድ ጳጕሜን ስድስት ቀን እንድትኾን አድርገዋታል፡፡ የቀረችው 6 ካልዒትስ የት ትግባ? ከተባለ ካልዒት አንዲት ዕለት ትኾን ዘንድ 3600 ካልዒት ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንን ያህል ካልዒት ለማግኘት 600 ዓመታት ያስፈልጉናል፡፡ ለዚህ ነው ጳጕሜን በየስድስት መቶ ዓመታት ሰባት የምትኾነው፡፡

ጳጕሜን 5 ቀን በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ‹ዕለተ ምርያ› ወይም ‹የተመረጠች ቀን› ትባላለች፡፡ ሊቃውንቱ የጌታችንን ልደት ሲያሰሉባት የቆየችው ዕለት በመኾኗ ነው ይህንን ስያሜ ያገኘችው፡፡ የጌታችንን ልደት ቀን የምትወስነው የጳጕሜን 5ኛዋ ቀን ናት፡፡ በዓለ ልደት የሚውለውም ጳጕሜን 5 በዋለበት ቀን ነው፡፡

ለምሳሌ ዘንድሮ (በ2008 ዓ.ም) ጳጕሜን 5 ቀን ቅዳሜ ነው የምትውለው፤ ስለዚህም በ2009 ዓ.ም በዓለ ልደት የሚውለው ቅዳሜ ነው ማለት ነው፡፡ በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ ጳጕሜን 6 ቀን ስትኾን ልደት በ28 የሚከበረው በዓለ ልደት ጳጕሜን 5 ቀንን (ዕለተ ምርያን) ስለማይለቅ ነው፡፡

በዘመነ ዮሐንስ ግን ስድስተኛዋ የጳጕሜን ቀን በዓለ ልደትን በአንድ ቀን ዝቅ ብሎ እንዲከበር ስለምታደርገው ልደትን ታኅሣሥ 28 ቀን እናከብራለን፡፡ ታድያ ምነው ጥምቀት፣ ግዝረትና ሌሎችም በዓላት አይለወጡም? ቢሉ ሊቃውንቱ የሚሰጡት ምላሽ ‹‹ትውልድ ሱባዔ እየቈጠረ በተስፋ የጠበቃት ዕለተ ልደትን ስለ ኾነ ነው፤ ሌሎቹ በዓላትም የመጡት በልደቱ ምክንያት ነው›› የሚል ነው፡፡

በጎርጎርዮሳውያንም ቢኾን በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዓለ ልደት ዝቅ ብሎ ይከበራል፡፡ የእነርሱ የማይታወቀው ጭማሪዋ ፌብርዋሪ ላይ ስለ ኾነች ነው፡፡ ያ ደግሞ አዲሱን ዓመት ካከበሩ በኋላ ስለሚመጣ ነው፡፡ የእኛ ግን የምትወድቀው ጳጕሜን መጨረሻ ላይ በመኾኗና ከአዲስ ዓመት በፊት ስለምትጨመር ቍጥሯ ጐልቶ ይታወቃል፡፡

እንግዲህ ጳጕሜን የምትባለው አስገራሚዋና ትንሿ ወራችን እንዲህ በስሌት የተሞላች፣ በሦስት ዓመታት አምስት ቀን ኾና ቆይታ በአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ ስድስት፣ በየስድስት መቶ ዓመት ደግሞ ሰባት ቀን የምትኾን ወር ናት፡፡ እንደዚሁም ታላላቆቹ ወሮች ምንም ሳይፈጥሩ የልደትን ቀን የምትወስን፣ የዓመቱን ሠግር የምታመጣ፣ ታሪከኛ ወር ናት፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡- የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገጽ፣ ፳፻፮ ዓ.ም (ከመጠነኛ ማስተካከያ ጋር)፡፡