ዝክረ ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ

ቅዱስ ያሬድ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ግንቦት  ቀን ፳፻፱ .

በየዓመቱ ግንቦት ፲፩ ቀን ከሚታወሱ ቅዱሳን መካከል የእመቤታችን እናት ቅድስት ሐና፣ ቅድስት ታውክልያ፣ ቅዱስ በፍኑትዩስ፣ አባ አሴር፣ ቅዱስ ያሬድ፣ ብፅዕት አርሴማ፣ ቅድስት ኤፎምያ፣ ቅድስት አናሲማ፣ ቅድስት ሶፍያ፣ አባ በኪሞስ፣ አባ አብላዲስ፣ አባ ዮልዮስ እና ስማቸውን ያልጠቀስናቸው ሌሎች በርካታ ቅዱሳንም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ‹የቤተ ክርስቲያን እንዚራ›፣ ‹የኢትዮጵያ ብርሃን› እየተባለ የሚጠራውን የቤተ ክርስቲያናችን ድምቀት፣ የአገራችን ኩራት የኾነውን የጥዑመ ልሳኑ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድን ታሪክ በአጭሩ ልናስታውሳችሁ ወደድን፤

ቅዱስ ያሬድ ሚያዝያ ፭ ቀን በ፭፻፭ ዓ.ም በአገራችን በኢትዮጵያ በአክሱም ከተማ ከአባቱ ከአብዩድ (ይስሐቅ) እና ከእናቱ ታውክልያ (ክርስቲና) ተወለደ፡፡ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ከአጎቱ ከአባ ጌዴዎን ዘንድ ትምህርት ሊማር ቢሔድም ለበርካታ ዓመታት ትምህርት ሊገባው አልቻለም ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ መምህሩ ይገርፉት፣ ይገሥፁት ነበር፡፡ እርሱም ከትምህርቱ ክብደት ባለፈ የመምህሩ ተግሣፅ ሲበረታበት ጊዜ ከአባ ጌዴዎን ቤት ወጥቶ በመሸሽ ላይ ሳለ ደክሞት ከአንድ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፡፡

ከዛፉ ሥር ተጠልሎ ሳለ አንድ ትል ፍሬውን ለመመገብ ወደ ዛፉ ሊወጣ ሲል መውጣት ስለ ተሳነው በተደጋጋሚ ሲወድቅ ቆይቶ ከብዙ ሙከራ በኋላ ከዛፉ ላይ ሲወጣ፤ ፍሬውንም ሲመገብ ይመለከታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ የትሉን ትጋት ከአየ በኋላ እርሱም በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግ የከበደው ምሥጢር እንደሚገለጽለት በማመን ወደ መምህሩ ተመልሶ ይቅርታ በመጠየቅ ትምህርቱን እንደ ገና መቀጠል ጀመረ፡፡ እግዚአብሔርን በጸሎት እየተማጸነ ትምህርቱን ሲከታተል ከቆየ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ልቡናው ብሩህ ኾኖለት የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ትርጓሜን አጠናቆ መዓርገ ዲቁና ተቀበለ፡፡

እግዚአብሔርም የክብር መታሰቢያ ሊያቆምለት ወዷልና ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍን ልኮ በሰው አንደበት እንዲያናግሩት አደረጋቸው፡፡ እነርሱም ካናገሩት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አወጡትና በዚያም የሃያ አራቱን ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) ማኅሌት ተማረ፡፡ ወደ ምድርም ተመልሶ በአክሱም ጽዮን በሦስት ሰዓት ገብቶ በታላቅ ቃል፡- ‹‹ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ፤ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድ ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፡፡ የጽዮን ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ፡፡ ዳግመኛም እንዴት መሥራት እንዳለበት የድንኳንን አሠራር ለሙሴ አሳየው፤ አስተማረው፤›› እያለ በዜማ እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ የቅዱስ ያሬድን ድምፅ የሰሙ ዅሉ ጳጳሳቱና ነገሥታቱ ሳይቀሩ ካህናቱም ምእመናኑም ወደ እርሱ ተሰብስበው ሲሰሙት ዋሉ፡፡ ይህንንም ምስጋና ‹አርያም› ብሎ ሰየመው፤ ይኸውም በዜማ ትምህርት ቤት ከቃል ትምህርቶች አንደኛው ኾኖ በቤተ ክርስቲያን በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር ቅዱስ ያሬድን፡- አምሳሊሆሙ ለሱራፌል፤ የሱራፌል አምሳላቸው› ይለዋል፡፡ ከመላእክት ወገን የኾኑት ሱራፌል እግዚአብሔርን ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ በመንበሩ ፊት ቆመው እንደሚያመሰግኑ ዅሉ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያለ በመላእክት ቋንቋ እግዚአብሔርን አመስገኗልና፤ ደግሞም የተማረው ከእነርሱ ነውና የሱራፌል አምሳላቸው› ተባለ፡፡ እርሱም፡- ‹‹ሃሌ ሉያ ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ግናይ እንዘ ይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር መልዐ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሓቲከ፤ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይኹን! ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር፤ የምስጋናህ ስፋት ሰማይና ምድርን መላ፤›› እያሉ ሲያመሰግኑ ከመላእክት የሰማሁት ምስጋና ምንኛ ድንቅ ነው? በማለት ዜማውን የተማረው ከመላእክት መኾኑን በድርሰቱ መስክሯል (ኢሳ.፮፥፫)፡፡

ከዚያ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ከዓመት እስከ ዓመት ድረስ በየክፍለ ዘመኑ በክረምትና በበጋ፣ በመጸውና በጸደይ፣ በአጽዋማትና በሰንበታት፣ እንዲሁም በመላእክት፣ በጻድቃን፣ በሰማዕታት፣ በደናግል በዓላት የሚደረስ ቃለ እግዚአብሔር በሦስት ዜማዎች ማለትም በግእዝ፣ በዕዝልና በአራራይ ደረሰ፡፡ የሰው ንግግር፣ የአዕዋፍ፣ የእንስሳትና የአራዊት ጩኸት ዅሉ ከእነዚህ ከሦስቱ ዜማዎች እንደማይወጡ መጽሐፈ ስንክሳር ይናገራል፡፡ በዘመኑ የነበረው ንጉሥ ገብረ መስቀል በሊቁ ዜማ ረቂቅነት እና የድምፅ ማማር ከመመሰጡ የተነሣ የቅዱስ ያሬድን እግር በጦር መውጋቱም በመጽሐፈ ስንክሳር እንዲህ ተመዝግቧል፤

በአንዲት ዕለት ቅዱስ ያሬድ ከብሉይና ከሐዲስ፣ እንደዚሁም ከሊቃውንትና ከመነኮሳት የተውጣጣውን መንፈሳዊ ድርሰቱን ከንጉሡ ፊት ቆሞ ሲዘምር ንጉሡ በድምፁ በመማረኩ የተነሣ ልቡናው በተመስጦ ተሠውሮበት (የሚያደርገዉን ባለማወቁ) የቅዱስ ያሬድን እግር በጦር ወጋው፡፡ ከቅዱስ ያሬድ እግር ደምና ውኃ ቢፈስስም ነገር ግን ማኅሌቱን እስኪፈጽም ድረስ ሕመሙ አልተሰማውም ነበር፡፡ ንጉሡም ያደረገዉን ዅሉ ባወቀ ጊዜ ደነገጠ፤ ጦሩንም ከእግሩ ነቅሎ ‹‹ስለ ፈሰሰው ደምህ ዋጋ የምትፈልገዉን ዅሉ ለምነኝ›› እያለ ተማጸነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ላትከለክለኝ ማልልኝ›› ብሎ ቃል ካስገባው በኋላ ወደ ገዳም ሔዶ ይመነኵስ ዘንድ እንዲፈቅድለትና እንዲያሰናብተው ለመነው፡፡ ንጉሡም ከመኳንንቱ ጋር እጅግ አዘነ፤ ተከዘ፡፡ ከእርሱ እንዲለይ ባይፈልግም ነገር ግን መሐላዉን ማፍረስ ስለ ከበደው አሰናበተው፡፡

ከዚያም ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ጽዮን ቤተ መቅደስ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ፡ ‹‹ቅድስት ወብፅዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን መዐርገ ሕይወት …፤ፈጽሞ የከበርሽና የተመሰገንሽ፣ ከፍ ከፍም ያልሽ፣ የብርሃን መውጫ የሕይወት ማዕረግ የኾንሽ …›› እያለ አንቀጸ ብርሃን የተሰኘውን የእመቤታችንን ምስጋና እስከ መጨረሻው ድረስ ደረሰ፡፡ ይህንን ጸሎት ሲያደርስም አንድ ክንድ ያህል ከመሬት ከፍ ብሎ ይታይ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን አገር ሔዶ (ሰሜን ተራሮች አካባቢ) በጾም በጸሎት ተወስኖ ሥጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያው ፈጸመ፡፡ እግዚአብሔርም ስሙን ለሚጠራ፣ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው፤ ከዚያም በሰላም ዐረፈ፡፡

(ምንጭ፡መጽሐፈ ስንክሳር፣ ግንቦት ፲፩ ቀን)፡፡

የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በገድለ ቅዱስ ያሬድ ላይ እና በመጽሐፈ ስንክሳር እንደ መዘገቡልን ግንቦት ፲፩ ቀን ቅዱስ ያሬድ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ያረፈበት ቀን ነው፤ እዚህ ላይ ግን አከራካሪ ጉዳይ አለ፤ ይኸውም አንደኛው ቅዱስ ያሬድ ሞቶ ተቀብሯል የሚል ሲኾን፣ ሌላኛው ደግሞ ቅዱስ ያሬድ እስከነነፍሱ ተሠወረ እንጂ አልሞተም የሚል ነው፡፡ በእርግጥ ቃሉን በትኩረት ለተመለከው ሰው ዐረፈ ማለት ሞትን ብቻ ሳይኾን እንደነሄኖክ ከዚህ ዓለም ጣጣ እና እንግልት ተለይቶ በሕይወት እያሉ (ሳይሞቱ) ተሠውሮ መኖርንም ያመለክታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መምህራን እንደሚያስተምሩን እነእገሌ ቀበሩት የሚል ቃል ስለማይገኝ ቅዱስ ያሬድ ተሠወረ እንጂ ሞተ ተብሎ አይነገርለትም፡፡ ለዚህም ማስረጃ እርሱ በተሠወረበት ተራራ አካባቢ እና በስሙ በተመሠረተው በደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ ገዳም እስከ አሁን ድረስ የከበሮ (የማኅሌት) ድምፅ ይሰማል፤ የዕጣን መዓዛም ይሸታል፡፡ ይህም ቅዱሱ ከሰው ዓይን ተሠውሮ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንደሚገኝ አመላካች ነው፡፡

በመጨረሻም የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ለአገርም ድንቅና ወደር የሌላቸው ሀብቶች መኾናውን ዅላችንም ልብ ልንለው ይገባል፡፡ በመኾኑም የዜማ ድርሰቶቹ (ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬ፣ መዋሥዕት) እንደ ሌሎቹ ቅርሶች ዅሉ በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ርብርብ በያደርጉ መልካም ነው፡፡ በቅዱስ ያሬድ ዜማ የሚደምቁት በዓለ ጥምቀት እና በዓለ መስቀል በዩኔስኮ ሲመዘገቡ ዜማውን ከበዓላቱ ለይቶ ማስቀረት አይገባምና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡