ትንሣኤ ክርስቶስ በሊቃውንት – ካለፈው የቀጠለ

በመምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹‹በእርሱ ሞት ከብረናል፡፡ በመለኮቱ ሞት ሳይኖርበት በሥጋ ሞተ፤ ምንጊዜም ቢኾን እርሱ የሕይወት ልጅ ሕይወት ነው፡፡ ይኸውም ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ወደ ሕይወት ሥጋ ደፍሮ በመጣ ጊዜ ሞት እንዲህ ድል ተነሣ፤ መፍረስ መበስበስም በእርሱ (በክርስቶስ) እንዲህ ጠፋ፤ ሞትም ድል ተነሣ፤›› (ቅዱስ ቄርሎስ፣ ሃይ. አበ. ፸፪፥፲፪)፡፡

‹‹ሕማምን፣ ሞትን ገንዘብ አደረ፡፡ በሥጋው የሞተው የእኛን ባሕርይ በመዋሐዱ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ተዋሕዶውን አስረዳ፡፡ ሞት ሰው የመኾን ሥራ ነውና፡፡ ከሙታን ተለይቶ መነሣትም አምላክ የመኾን ሥራ ነውና፡፡ እነዚህ ሁለት ሥራዎችን (ሞትን እና ትንሣኤን) እናውቃለን፤›› (ዝኒ ከማሁ ፸፪፥፴፭)፡፡

‹‹በሥጋ ሞተ እንዳልን ዳግመኛ በሥጋ ተነሣ እንላለን፤ ስለ ትንሣኤም የእርሱ ገንዘብ እንደ ኾነ፤ ሙስና መቃብርም እንዳላገኘው ይነገራል፡፡ ይህ (መሞት፣ መነሣት) ለመለኮት አይነገርም፡፡ የተነሣው ሥጋው ነው እንጂ፤›› (ዝኒ ከማሁ ፸፱፥፱)፡፡

‹‹የሞትን ሥልጣን አጠፋ፤ ዲያብሎስንና ኃይሉን (ኃጢአትን) ሻረ፡፡ የብረት መዝጊያዎችን ሰበረ (ፍዳ፣ መርገምን አጠፋ)፡፡ ሲኦልን በዘበዘ፤ የጣዖት ቤቶችን አፈረሰ፡፡ የምሕረትን በር ከፈተ፡፡ ይህችውም በደሙ የከበረች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለዅሉ የዘለዓለም ሕይወት መገኛ የሚኾን ልጅነት የተገኘበት ሥጋውን ደሙን ሰጠን፤›› (ቅዱስ ቴዎዶስዮስ፣ ሃይ. አበ. ፹፫፥፮)፡፡

‹‹ለእኛስ እግዚአብሔር ቃል በባሕርየ መለኮቱ እንደ ታመመ፤ እንደ ሞተ፤ እንደ ተቀበረ ልንናገር አይገባንም፡፡ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ ሞት የሌለበት እንደ ኾነ፣ መድኃኒታችን በሚኾን በሞቱና በሦስተኛው ቀንም በመነሣቱ ትንሣኤን እንደ ሰጠን እናምናለን፡፡ የሞተ እርሱ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና፡፡ ዅሉን የሚችል እርሱ ካልተነሣ፣ የችሎታ ዅሉ ባለቤት እርሱ የሌለ ከኾነ፣ እንኪያስ ትንሣኤም ሐሰት ነዋ! ትንሣኤም ሐሰት ከኾነ ሃይማኖታችን ከንቱ ነው፡፡ እንኪያስ አይሁድንም እንመስላቸዋለን፡፡ ሰው እንደ መኾኑ በሥጋ ባይሞትስ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ እንደ መኾኑ ሞትን ባላጠፋ ነበር፡፡ የአዳም የዕዳ ደብዳቤም ከእግዚአብሔርና ከሰው መካከል ባልተደመሰሰም ነበር፤›› (ቅዱስ ሳዊሮስ፣ ሃይ. አበ. ፹፬፥፲፰-፳)፡፡

‹‹ፈጣሪያችን ክርስቶስ ለጌትነቱ እንደሚገባ ሥጋ መለወጥ የሌለበት እስኪኾን ድረስ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤ ሙስና መቃብርን አጥፍቷልና፤ በሥጋ በተቀበላቸው በሚያድኑ በእነዚህ ሕማማት ከጽኑ ሞት፣ ከዲያብሎስም ሥልጣን ያድነን ዘንድ፤ ወደ ቀደመ ቦታችንም ያገባን ዘንድ፤›› (ቅዱስ ዮሐንስ ዘአንጾኪያ፣ ሃይ. አበ. ፺፥፴፬)፡፡

‹‹ይታመም ዘንድ በተገባው በሥጋው፣ ነውር የሌለበትን ሕማም በፈቃዱ በእውነት ተቀበለ እንጂ በምትሐት እንዳልታመመ እናገራለሁ፡፡ እንደ ሕማሙ ሞትንም በመስቀል ላይ ተቀበለ፡፡ ለአምላክነቱ በሚገባ፣ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤውም የጌትነቱን ሥልጣን ገለጠ፡፡ ሥጋውንም የማይሞት አደረገ፡፡ ከኃጢአት በራቀ በንጹሕ ማኅፀን በተዋሐደው ጊዜ ለመለኮት ገንዘብ ስለኾነ በሥራው ዅሉ አይለወጥም፤›› (ቅዱስ ቴዎዶስዮስ፣ ሃይ. አበ. ፺፪፥፲፭)፡፡

‹‹ሕማም የማይስማማው እርሱ በሥጋ ሞትን ታገሠ፤ ብረት ወደ እሳት በገባ ጊዜ ዅለንተናው እሳት እንደኾነ እስኪታሰብ ድረስ በእሳት ዋዕይ እንዲግል፤ በመዶሻ በተመታ ጊዜ በመስፍሕ (መቀጥቀጫ) ላይ እንዲሳብ (እንዲቀጠቀጥ)፤ እሳትም ከብረት ጋር ተዋሕዶ ሳለ ፈጽሞ እርሱ እንዳይመታ፤ ከብረቱም እንዳይለይ፤ ግን የመዶሻ ኃይል ሳያገኘው እንዲመታ፤ ለመዶሻ እንዲሰጥ፤ የሚያድን የጌታ ሕማም እንዲህ እንደ ኾነ ዕወቅ፡፡ በዚህ ትንሽ ምሳሌ፤ በእሳትና በብረት ተዋሕዶ ምልክትነት ፍጹም ተዋሕዶን እንወቅ፤ የእግዚአብሔር ቃል ይህ መከራና ሕማምን የሚቀበል ሥጋን ተዋሕዶ በሞተ ጊዜም ከሦስት ቀን በኋላ አምላክነቱ በተገለጠበት ትንሣኤው ሞትን አጠፋው፡፡ ሥጋው በመቃብር በመቀበሩም በመቃብር ውስጥ የነበረ መፍረስ፣ መበስበስን አጠፋልን፤ ከሥሩም ነቀለው፡፡ ለዚህም ማስረጃ ከቅዱሳን ወገን ብዙ ሰዎች ተነሡ፤›› (ቅዱስ ባስልዮስ፣ ሃይ. አበ. ፺፮፥፶-፶፪)፡፡

‹‹ዳግመኛ እርሱ እንደ ሞተ፤ በሦስተኛውም ቀን እንደ ተነሣ፤ ስለ ተነሣም ሥጋው የማይፈርስ የማይበሰብስ፣ የማይታመም፣ የማይሞት እንደ ኾነ እናምናለን፡፡ ሥጋውም ከእርሱ ጋር አንድ ኾኖ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአርያም በልዑል ዙፋኑ ተቀመጠ፡፡ ዳግመኛም በሙታንና በሕያዋን ይፈርድ ዘንድ ዅሉ አንድ ኾኖ በሚነሣበት ጊዜ እርሱ በጌትነት ይመጣል፡፡ ለዅሉም እንደ ሥራው ይከፍለዋል፡፡ እኛ በእነዚህ ቃላት ሳናወላውል ጸንተን እንኖራለን፤›› (ቅዱስ ዲዮናስዮስ፣ ሃይ. አበ. ፺፱፥፴፪)፡፡

‹‹በፈቃዱ በሥጋው የእኛን ሕማም ታመመ፤ በእውነት የእኛን ሞት ሞተ፡፡ ይኸውም የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው፡፡ በፈቃዱ በተለየ አካሉ ሞትን ገንዘብ አደረገ፡፡ በሦስተኛውም ቀን በሥልጣኑ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱ ዕሪና ተቀመጠ፡፡ በኋለኛይቱ ቀንም በሙታንና በሕያዋን ሊፈርድ ይመጣል፤›› (ቅዱስ ፊላታዎስ፣ ሃይ. አበ. ፻፭፥፲፬)፡፡

‹‹በሞቱ ሞትን ያጠፋው እርሱ ነው፤ በሦስተኛው ቀን በመነሣቱም ሲኦልን በዘበዘ፣ ለዅሉም ትንሣኤን ገለጠ፡፡ ፈጽሞ አልተለወጠም፤ ለዅሉ አምላክነቱን አስረዳ፤ ሙስና መቃብርን ከእኛ አጠፋ፤ በቀደመ ሰው በአባታችን በአዳም ትእዛዝ ማፍረስ ምክንያት ሠልጥኖብን ለነበረ ኃጢአት ከመገዛት አዳነን፤›› (ቅዱስ ዲዮናስዮስ ፻፲፩፥፲፫)፡፡

‹‹እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ነፍሱን ከሥጋው አዋሕዶ በመለኮታዊ ኃይል ተነሣ፡፡ እርሱ ራሱ ‹ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ ልሰጥ፣ ሁለተኛም መልሼ ላዋሕዳት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ› እንዳለ፡፡ በነጋም ጊዜ ለማርያም መግደላዊት ታያት፤ እጅ ልትነሣው በወደደች ጊዜም ‹ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ› አላት፡፡ ስለዚህም ሥጋዊ አካሉ ከዚያን አስቀድሞ በአብ ቀኝ እንዳልተቀመጠ ዐወቅን፤›› (አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ መጽሐፈ ምሥጢር ዘትንሣኤ ፺፭)፡፡

‹‹ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ከጲላጦስ ተካሰው፣ ከመስቀል አውርደው፣ በድርብ በፍታ ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገብቶ በጽርሐ ጽዮን ታያቸው፤›› (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ፩፥፳፱-፴፩)፡፡

‹‹ሰውን ስለ መውደድህ ይህን ዅሉ አደረግህ፤ ከሙታን ተለይተህ መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ ሳትል ተነሣህ፡፡ ከእግረ መስቀል ሙታንን አስነሣህ፡፡ ነፍሳትን ከሲኦል ማርከህ ለአባትህ አቀረብህ፤›› (ቅዳሴ ያዕቆብ ዘስሩግ፣ ፩፥፳፬)፡፡

‹‹በታወቀች በተረዳች በሦስተኛይቱ ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገባ፡፡ የተወጋውን ጎኑን፣ የተቸነከረውን እጁን፣ እግሩን አሳያቸው፡፡ በዓለመ ነፍስ የኾነውን እያስተማራቸው ዐርባ ቀን ኖረ፤›› (ቅዳሴ ዘሠለስቱ ምዕት ፬፥፳፭-፳፯)፡፡

‹‹ሰማያት (ሰማያውያን መላእክት) የደስታ በዓልን ያደርጋሉ፤ ደመናት (ቅዱሳን) የደስታን በዓል ያደርጋሉ፡፡ ምድር (ምድራውያን ሰዎች) በክርስቶስ ደም ታጥባ (ታጥበው) የፋሲካን በዓል ታደርጋለች (ያደርጋሉ)፤ ያከብራሉ (ታከብራለች)፡፡ ዛሬ በሰማያት (በሰማያውያን መላእክት) ዘንድ ታላቅ ደስታ ኾነ፡፡ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ የፋሲካን የነጻነት በዓል ታደርጋለች፡፡ የትንሣኤያችን በኩር ክርስቶስ ከሙታን ሰዎች ዅሉ ተለይቶ ቀድሞ ተነሣ፤›› (ቅዱስ ያሬድ፣ ድጓ ዘፋሲካ)፡፡

‹‹ሞትን በሥጋ በቀመሰ ጊዜ መለኮቱ በመቃብር ውስጥ ያለነፍሱ ከበድኑ ጋር ነበር፡፡ በሲኦልም ውስጥ ያለ ሥጋው ከነፍሱ ጋር ህልው ነበር፡፡ በአባቱም ቀኝ ያለ ነፍስና ያለ ሥጋ ህልው ነበር፡፡ በትንሣኤውም ጊዜ ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋሕዶ አስቀድሞ ለአይሁድ ‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛው ቀን እሠራዋለሁ› ብሎ እንደ ተናገረ፡፡ አይሁድም ‹ይህ ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ያለቀው በዐርባ ሰባት ዓመት ነው፤ አንተ ግን በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ትላለህ› አሉት፤ ይህንንም የተናገረው ስለ ራሱ ሰውነት ነው፡፡ በተነሣም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንደ ተናገረ አሰቡ፡፡ በመጽሐፍና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም የተናገራቸውን ቃል አመኑ፤ ሁለተኛም ‹ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ልለያት መልሼም አዋሕጄ ላስነሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህንንም ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ› ብሏል፡፡ ዳዊትም ‹አቤቱ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ› ይላል፡፡ ነቢዩ ‹አቤቱ አንተ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ› ለምን አለ? የመቅደሱ ታቦት ከኾነችው ከዳዊት ዘር ከነሣው ሥጋ ጋር በመለኮታዊ ኃይሉ ከሞት እንቅልፍ ከመንቃት በስተቀር የእግዚአብሔር መነሣት ምንድን ነው?›› (አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽ. ምሥጢር ዘትንሣኤ ፸፯-፸፱)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡