የቅዱስ ያሬድን ትሩፋት በዓለም የዕውቀት መድረክ ላይ ለማስተዋወቅ የምርምር ማእከላትን የማቋቋምና የዲጂታል ቅርስ አያያዝ ዘዴዎችን የመተግበር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።
በማኅበረ ቅዱሳን ባሕር ዳር ማእከል ከባሕር ዳር ሀገረ ስብከት እና ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቅዱስ ያሬድ አበርክቶ እና በቅዱስ ያሬድ ዜማ ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን የሚዳስስ የዐውደ ጥናት ጉባኤ ተካሄዷል።
በዐውደ ጥናት መርሐ ግብሩ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ኤፍሬም ሙሉዓለም፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መልአከ ብርሃን ፍሥሐ ጥላሁን፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የዐውደ ጥናት ጉባኤው ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ ተሳትፎ ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይና የምርምር ጉዳዮች ኮርፖሬት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ነጻነት ፈንታሁን ለጉባኤው ተሳታፊዎች የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት እና የመክፈቻ ንግግር አስተላልፈዋል።
ፕሮፌሰር ነጻነት በመልእክታቸው የቅዱስ ያሬድ የዜማና የድርሰት ጥበብ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የቅርስ ሀብት ነው ያሉ ሲሆን የሊቁ ቅዱስ ያሬድ አበርክቶት ለዘመናዊ የምርምር መስኮች ማለትም ለቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ፣ ለታሪክና ለነገረ መለኮት ጥናት ትልቅ መሠረት ሆኖ ዛሬም ድረስ የዓለም አቀፍ ምሁራንን ትኩረት እየሳበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር ነጻነት በተጨማሪም ዩነቨርሲቲው በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ቅርሶች በሳይንሳዊ መንገድ ለማጥናትና ለመጠበቅ በሰፊው እየሠራ መሆኑን በመግለጽ የቅዱስ ያሬድን ትሩፋት በዓለም የዕውቀት መድረክ ላይ ለማስተዋወቅ የምርምር ማዕከላትን የማቋቋምና የዲጂታል ቅርስ አያያዝ ዘዴዎችን የመተግበር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በዐውደ ጥናት ጉባኤው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ያሬድን ሥራ የሚገልጽ ያሬዳዊ መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን የቅዱስ ያሬድን አበርክቶ በተመለከተ በዶ/ር አሥራት አርአያ እና የቅዱስ ያሬድ ዜማ ተግዳሮቶች እና መፍትሔዎች በመምህር ኀይለ ማርያም ዘውዱ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
የማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮች ይቀላቀሉ
ቴሌግራም፡- http://t.me/mkpublicrelation
የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት፡- http://www.facebook.com/eotcmkidusan/
ድረገጽ፡- http://www.eotcmk.org
