«ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው፤» (መዝ.፻፲፭፥፭)

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

«ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤ የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው»፤ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ስለሕዝቅያስ በተናገረው በዚህ ኃይለ ቃል ሊያስረዳን የፈለገው የነፍስ ከሥጋ መለየት ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም፣ ውጣ ውረድ፣ ድካም ካለበት ዓለም ውጣ ውረድ ድካም ወደሌለበት ዓለም መሄድ ነውና። ስለሆነም እንደ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ በዚህች ዕለት የቅዱሳን ዕረፍት ነው እየተባለ ይነገራል። ድካም ካለበት ድካም ወደሌለበት ስለሆነ ዐረፈ ወይም ዐረፈች እየተባለ ይነገራል። በነሐሴ ፳፬ በዓለ ዕረፍቱን የምናከብረው ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዐረፈ እንጂ ሞተ አይባልም፤ ሞቱ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነውና።

በዚህ ዕለት ቤተክርስቲያን የቅዱሱን በዓለ ዕረፍት ምክንያት በማድረግ እግዚአብሔርን ከምታመሰግንበት ያሬዳዊ ዜማ እንጥቀስ። «ሞቶሙሰ ለጻድቃን ሕይወቶሙ ውእቱ እስመ ለጻድቅ ይትሌዓል ቀርኑ በክብር ጻድቃን እለ አሥመርዎ ለእግዚኦሙ ምድረ ብርህተ ወጽዕዱተ ይወርሱ፤የጻድቃን ሞታቸው ሕይወታቸው ነው። የጻድቅ ክብሩ ከፍ ከፍ ይላልና። ጌታቸውን ደስ ያሰኙት ጻድቃን ብርህትና ጽዕዱት የሆነች ምድርን ይወርሳሉ» (ቅዱስ ያሬድ)።

እንግዲህ ከላይ በተጠቀሰው ቃለ እግዚአብሔር መሠረት ሞታቸው ሕይወታቸው ነው የተባለ በመጀመሪያ ደረጃ ሞተ ሥጋ እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ጻድቃን ሞተ ሥጋን እንጂ ሞተ ነፍስን ሊያዩ አይችሉም። ሞተ ነፍስን የሚያዩ ከሆነ ጥንቱኑ ጻድቃን ሊባሉም አይችሉም። ሞተ ሥጋቸው ግን ወደ ተሻለውና ወደሚበልጠው ዓለም የሚሄዱበት ስለሆነ ሕይወታቸው ነው ተባለ።

ሌላው ደግሞ የጻድቃን ሞት እንጂ የኃጥአን ሞት ሕይወት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ኃጥእን ምንም እንኳ ወደማያልፈው ዓለም የሚሄዱ ቢሆንም መከራ ወደ አለበት፣ ሥቃይ ወደሚበዛበት እንጂ ዕረፍት ወደአለበት መሄድ አይችሉም። መከራና ሥቃይ የሚበዛበት ዓለም መሄድ ደግሞ ሕይወት ሊባል አይችልም። እንዲያውም ነቢዩ ዳዊት «ሞቱ ለኃጥእ ጸዋግ፤የኃጥእ ሰው ሞት ክፉ ነው» (መዝ.፴፫፥፳፩) በማለት አስረድቷል። ጻድቃን ሞተ ሥጋን እንጂ ሞተ ነፍስን አያዩም። ኃጥኣን ግን ሞተ ሥጋም ሞተ ነፍስም ያገኛቸዋል። ስለዚህ ለኃጥእ ሰው ሞተ ሥጋውም ሆነ ሞተ ነፍሱ ክፉ እንጂ መልካም የሚባል አይደለም።

ሞት የሰው ልጅ የፈጣሪውን ትእዛዝ በመተላለፍ የሰለጠነበት ነው። «በሕይወታችሁ ስሕተት ለሞት አትቅኑ፤በእጃችሁም ሥራ ጥፋትን አታምጡ። እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና፤ የሕያዋንም ጥፋት ደስ አያሰኘውምና። ነዋሪ ይሆን ዘንድ ፍጥረቱን ፈጥሮአልና፣ የዓለም መፈጠርም ለድኅነት ነውና፣ በእነርሱም ዘንድ የጥፋት መርዝ አልነበረምና፣ ለሲኦልም በምድር ላይ ግዛት አልነበረውምና። ጽድቅ አትሞትምና። ክፉዎች ግን በእጃቸውና በቃላቸው ጠሩት ባልንጀራም አስመሰሉት። በእርሱም ጠፉ። የእርሱ ወገን መሆን ይገባቸዋልና ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረጉ» (ጥበ.፩፥፲፪-፲፯) በማለት መፍቀሬ ጥበብ ሰለሞን ነግሮናል።

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ሃይማኖትና ምግባር የማይነጣጠሉ እንደሆኑ በምሳሌ ሲያስተምር የጠቀሰው የነፍስና የሥጋን ህልውና ነው። «ከመ ሥጋ ዘአልቦ መንፈስ ምውት ውእቱ ከማሁ ሃይማኖትኒ እንተ አልባቲ ምግባረ ሠናይ ምውት ይእቲ ለሊሃ፤ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው» (ያዕ.፪፥፳፮) እንዲል፤ ስለዚህ ነፍስ ያለሥጋ ሥጋም ያለ ነፍስ ህልውና አይኖራቸውም። ይህ ማለት በሰውነት ህልውና እንጂ ነፍስና ሥጋ ተለያይተው ነፍስም በገነት  ወይም በሲኦል ሥጋም በመቃብር አይኖሩም ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም የሥጋ ሞት የሚባለው የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው። ይህ የነፍስ ከሥጋ መለየት የጻድቅ ከሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነው።

ነፍስ በባሕርይዋ የምትሞት አይደለችም፤ ሞተ ነፍስ የሚባለው የማትኖርበት ጊዜ ስላለ ሳይሆን ከምትኖርበት ሁኔታ አንጻር ነው። ይህ ማለት ነፍስ በሃይማኖት ጸንታ በምግባር ቀንታ ባለመኖሯ ወደ ሲኦል በኋላም ገሃነመ እሳት ትወርዳለች። የነፍስ ሞት ማለት ገነት በመግባት ፈንታ ሲኦል፣ መንግሥተ ሰማያት በመግባት ፈንታ ገሃነመ እሳት መግባት ነው። «ድል የነሣው ሁለተኛውን ሞት አያይም» (ራእ.፪፥፲፩) ተብሎ የተጻፈው ነፍስ ከሥጋ መለየትን ሳይሆን ገሃነመ እሳት መውረድን አያይም ለማለት ነው።

ሞት ማለት መለየት ነውና ነፍስ ከፈጣሪዋ ከእግዚአብሔር ተለይታ ካልፈጠራት ከዲያብሎስ ጋር መኖር ስትጀምር የነፍስ ሞት ይባላል። ሁለተኛ ሞት የተባለውም ፈጣሪ ያዘጋጀውን መንግሥተ ሰማያት አጥታ በኃጢአቷ ምክንያት ገሃነመ እሳት መውረድ ነውና «ድል የነሣው ሁለተኛውን ሞት አያይም» ማለት ከላይም እንደተገለጸው ገሃነመ እሳት አይገባም ማለት ነው።

በአጠቃላይ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት «የጻድቅ ሰው ሞት ክቡር ነው» ሲል ሞተ ሥጋን አያይም ማለት ሳይሆን ሞተ ነፍስን አያይም ማለት እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ደግሞ ሞተ ሥጋን መቅመስ የግድ ነውና ይህ እንደ ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት መንግሥተ ሰማያትን የሚወርስበት ሞት ክቡር ነው፤ሕይወት ነው፣ ዕረፍት ነው እያለ ይገልጸዋል፡፡ እኛም ንስሓ ገብተን ሥጋውን ደሙን በልተን እንደዚህ በእግዚአብሔር ዘንድ ክቡር ለተባለው ሞት እንዲያበቃን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የጻድቁ የተክለ ሃይማኖት ረድኤት በረከት አይለየን፤ አሜን።

በዘመናችን የቤተክርስቲያን ፈተናዎች

የተከበራችሁ አንባብያን ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በቤተክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ በተለይም ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጸመውን ግፍ የሚገልጽ ተከታታይ ጹሑፍ በማቅረብ ላይ መሆናችን ይታወቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ነጠቃ፤ የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎና የምእመናን ግድያ  ዋናዎቹ የግፍ ተግባራት ናቸው፤ ከባለፈው የቀጠለውንና የመጨረሻውን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡ መልካም ንባብ

በማርክሲዝም ሌሊዝንም አስተምሮ የተበረዘ ሰው ሁል ጊዜ ባላንጣና ጠላት በመፈለግ ጠላቱን ካላጠፋ መኖር እንደማችል ሲሰብክ የሚኖር መሆኑን በሙያው ምርምር ያደረጉ አካላት ይናገራሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ሃይማኖትም እየተጋባ መጥቷል፡፡ ከሃይማኖት ሰዎች የሚጠበቀው እናመልከዋለን የሚሉትን አምላክ በቃልም በምግባርም መግለጥ ነው፡፡ ሌላውን እያጠፉና  አማራጭ እያሳጡ እምነትን ማስፋፋት አይቻልም፡፡ ሌላውን አጥፍተው መኖር የሚፈልጉት የሚያደርጉት ምድራውያን ገዥዎች ናቸው፡፡ ስለሃይማኖት የሚያስተምሩ አካላት ከዚህ ዓለም የተለየ ዘለዓለማዊ ርስት እንዳለ የሚያምኑ በመሆናቸው ዘለዓለማዊ ርስት ማውረስ የሚችለውን አምላክ የሚያስደስቱበትን ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ ሰው በመግደልና ተቀናቃኝን በማጥፋት ተደስቶ የሚኖር የሚመሰለው ምድራዊ የሥጋ ፍላጎት ያለው ምድራዊ ገዥ እንጂ ዘለዓለማዊ መንግሥትን የሚሻ መንፈሳዊ ሰው አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወደ አሕዛብ የምትገባው ወንጌልን ይዛ እንጂ እንደ ቀኝ ገዥዎች በአንድ እጅ ወንጌል በሌላ የጦር መሣሪያ ይዛ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህን የምታደርገው ባለቤቱ በወንጌል እንዲያምኑ ያደረገው በፍቅር እንጅ በግዳጅ ባለመሆኑ ነው፡፡እንዲህ ያለው እኩይ ተግባር የቤተ ክርስቲያን አለመሆኑን መረዳት የሚገባውም ቤተ ክርስቲያን በሞት እንጂ በመግደል ጸንታ ስለማታውቅ ነው፡፡

ቤተክርስቲያን የገጠማት ፈተና ያላሳሰባቸው አካላት የሰጡት መግለጫ መንግሥትን በሚከተለው መንገድ  አሳስቧል፡፡ ሀገርና ሕዝብን ለመምራት የተቀመጠው መንግሥት  በየአካባቢው  እየደረሰ ባለው  የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎ፣ የኦርቶዶክሳውያንን መፈናቀል ፣ድብደባ ከዚያም ሲያልፍ አሰቃቂ ግድያ ላይ ያሳየው ቸልተኝነት የበርካታ ሚሊዮን አባሎቻችንን ልብ በእጅጉ የሰበረ ወደፊትም ቢሆን ለደኅንነታችን መጠበቅ ምንም አይነት ዋስትና እንደሌለን እንዲሰማን ያደረገ በመሆኑ የመንግሥትን ለዘብተኝነት በእጅጉ  እንቃወማለን ›› ይላል፡፡ አንድ መንግሥት ለዜጎቹ ዋስትና  ሲሰጥ ዜጎቹን በመንግስት እምነት  ማሳደር ብቻ  ሳይሆን  ለመንግሥትም  ጠበቃ ይሆናሉ፡፡ ምርጫ ቢደረግ ይመርጡታል፤ ቢናገር ይሰሙታል፡፡ ቢያዝዝ ይፈጽሙለታል፤ እንኳንም ተናግሮ ሳይናገርም ማድረግ የሚገባቸውን ይሠራሉ ፡፡ ክርስቲያኖች በዚህ ምድር ላይ ሲኖሩ በጌታ ለገዥዎቻችሁ ታዘዙ ›› የሚለውን  አምላዊ ቃል ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡ ወደ ፊትም ይፈጽሙታል፤ ይህ ማለት ግን በክርስቲያኖች ላይ በደል ሲፈጽም መንግሥትን አያሳስቡም ማለት አይደለም፡፡ ለገዥዎቻችን መታዘዝ እንዳለብን የሐዋርያውን ቃል አምነን እንሠራለን፡፡ አድሎአዊ ተግባር  ሲፈጸም ስናይ ደግሞ እንናገራለን፡፡ ነህምያ የኢየሩሳሌም መፍረስ ሲያሳስበው ስለኖረ ኃዘንና ትከዜው በፊቱ ላይ መነበብ በጀመረ ጊዜ የማረከው ንጉሥ ምን እንዳሳዘነው ጠየቀው ፡፡ ነህምያም ከዚህ በላይ መከራ አለመኖሩን በመረዳት አባቶቼ የሠሯት ኢየሩሳሌም ፈርሳ እንዴት ደስተኛ እሆናለሁ በማለት መለሰለት፡፡ በነህምያ መልስ ቅንነቱን ሲመለከት የኖረው ንጉሥ የሚያመልከው አምላክ የሚመለክበትን ቤተ መቅደስና ሙሉ ከተማዋን እንዲያንዱ ፈቃድ ሰጥቶ ሰደደው፡፡ በእኛ ዘመንም መፈጸም ያለበት እንዲህ ነው፡፡ አንተ ከፈርኦን አታንስ እኛም ከሙሴ አንበልጥ የሚለውን ንግግር ማሰብ ይገባል፡፡

 ሀገራችን ክርስቲያኖችን እያጠፉ የሚደሰቱበት ክርስቲያኖች ደግሞ በኃዘን የሚኖሩባት መሆን የለባትም፡፡ ሁላችንም እኩል ደስታውንም ኃዘኑንም የምንካፍልባት መሆን ይኖርባታል፡፡በሃይማኖት ሰበብ የተቀሰቀሰ ግጭት ቶሎ ስለማይበርድ መፍትሔ መፈለግ ተገቢ ነው እንላለን፡፡

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተክርስቲያን ሠለስቱ ምእት የመቶ ሃያ ማኅበራት ኅብረት ደግሞ ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጅማ፣ በኢሉባቡር፣በከሚሴ፣በድሬድዋ፣በምሥራቅና በምዕራብ ሐረርጌ፣በፍቼ፣ሶማሌ (ጅጅጋ) ፣በባሌ፣ በአሩሲና በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ፤ ክርስቲያኖች እየተገደሉ፤ እየተሰደዱና ተገደው ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ እየተደረገ፤  ንብረታቸው እየተቀማና እየተቃጠለ የአብያተ ክርስቲያናት ይዞታዎች ጥምቀተ ባሕርን ጨምሮ እየተቀሙ እንደሆነ በተለያዩ ሚድያዎች የሰማነውና በአካልም በቦታው ተገኝተን ያየነው እውነታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለሀገር ባለውለታ መሆኗ ተረስቶ ቤተክርስቲያንና አማኞቿን የማይመጥን ስም እየተሰጣት እንዲህ ያሉ ጥቃቶች መንግሥት ባለበት ሀገር እየተፈጸሙ፤ ሰዎች በነፃነት የፈለጉትን የማምለክና በሰላም ወጥቶ የመግባት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ተነፍገው በስጋትና በመከራ ውስጥ በመሆናቸው የተሰማንን ጥልቅ ኃዘን እንገልጣለን›› ብለዋል፡፡ ሀገሪቱ የምትታወቅባቸው የመስህብ ቦታዎች የቤተክርስቲያኗ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ቤተክርስቲያንን አጥፍተን ሌላ እንመሥርት ካልተባለ በስተቀር እንዲህ አይነት ተግባር በየትም ተደርጎ አያውቅም፡፡እንዲህ አይነት ዘመኑን የማይመጥን  ጥፋትና አድሎአዊ አሠራር መቆም ይኖርበታል፡፡ሥልጣን ላይ ስንቀመጥ መልካም ብንሠራ እኛ ዘለዓለማዊ አይደለንምና ስንወርድ ደግሞ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንኖራለን፡፡ ሰዎች በመውረዳችን ያዝናሉ መልካም ተግባራችንን ሲዘክሩ ይኖራሉ እንጂ እንኳን ወረዱ አይሉንም፡፡ስለዚህ አጥፊዎች ከእኩይ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማድረግ አጥፊዎች እንወክለዋለን የሚሉትንም ሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያኖችን፤ አባቶችን አቅርቦ ማወያየትና ችግሩን በመለየት የማያዳግም እርምት መስጠት ይገባል፡፡

      ይቆየን

 ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፮ ዓመት ቁጥር ፲፯

 

በዘመናችን የቤተክርስቲያን ፈተናዎች

የተከበራችሁ አንባብያን ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በቤተክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ በተለይም ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጸመውን ግፍ የሚገልጽ ተከታታይ ጹሑፍ በማቅረብ ላይ መሆናችን ይታወቃል፡፡ የቤተክርስቲያን ይዞታ ነጠቃ፤ የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎና የምእመናን ግድያ ዋናዎቹ የግፍ ተግባራት ናቸው፤ ከባለፈው የቀጠለውን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡ መልካም ንባብ!

ክርስቲያኖች መከራ ቢገጥማቸውም ፈርተው ከእምነታቸው እንደማያፈገፍጉ፣ ከራሳቸው ሕይወት ይልቅ ለታቦታቱና ለንዋያተ ቅድሳቱ ቅድሚያ እንደሚሰጡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያነበብነው፤ በቅርብም ሲፈጸም ያየነው ተግባር ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከመከራ እንዲሰውራቸው ብቻ ሳይሆን በሰማዕትነት እንዲያበረታቸውም ይለምኑ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ለሁለት ሺህ ዘመናት ያልተፈተነችበት የመከራ አይነት፣ያልተፈጸመም ተአምር አለመኖሩን ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን አሕዛብም የሚመሰክሩት እውነታ ነው፡፡ አሕዛብ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ሲነሡ ክርስቲያኖች ታቦታትና ንዋያተ ቅድሳትን ይዘው እንዲሸሹ ከማድረግ በተጨማሪ  እግዚአብሔር አምላክ በማይታበል ቃሉ ታቦታቱም ሆኑ አብያተ ክርስቲያናቱ እንዲሰወሩ ሲያደርግ ኖሯል፡፡ በግብጽ የነበረ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ታቦት በእስላሞች በፈረሰ ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ ጽላቱን ሰውሮት ከብዙ ዘመን በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአባ ተክለ ሃይማኖት የትውልድ አካባቢ ጽላልሽ ቤተክርስቲያን ሲተከል  ታቦቱን ሰጥቷቸው አክብረውታል፡፡ እንዲህ አይነት ተአምራት በየዘመናቱ ተፈጽመዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ቤተክርስቲያንን ሊያቃጥሉ፤ ክርስቲያኖችን ሊገድሉ የተሰለፉ ወገኖች ሲጋፉት ለነበሩት ሃይማኖት ጠበቃ እንዲሆኑም አድርጓል፡፡ ከጥፋታቸው አልመለስ ካሉም ተቀስፈው እንዲሞቱ ሲያደርግ ኖሯል፡፡ ይህንን የምንጽፈው በአንድ በኩል በእምነት ያሉትን ለማጽናናት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ታሪክን መጥቀስ እንጂ ከታሪክ መማር የማይፈልጉ ወገኖች አንብበው እንዲጠቀሙበት በማሳብ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እየተሳደደች ትዕግሥቷን አሕዛብ አይተው እንዲማሩ ለማስተማር ጭምር ነው፡፡

የምዕራባውያን ተልእኮ አስፈፃሚ የሆኑ መናፍቃንና ግብረ አበሮቻቸው ኢትዮጵያውያንን የአስተሳሰብ ድሃ ለማድረግና የነጮችን  የበላይነት አምነው እንዳይቀበሉ እንቅፋት የሆነችባቸውንና የሰውን ልጅ  ለሁሉም እኩልነትን የምታስተምረውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን  ለመበቀል የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ ዝናራቸውን ቢያራግፉና ቀስታቸውን ቢጨርሱም ለማሸነፍ እንደማይችሉ እያወቁት ራሳቸውን የሚጎዳ ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ በዐድዋ በማይጨውና በሌሎች ከውጭ ወራሪዎች ጋር በተደረጉ ጦርነቶች የተሳተፉት ኦርቶዶክሳውያን ብቻ ባይሆኑም ቤተክርስቲያን ለሀገር መሞት ክብር መሆኑን በማወጅ፤ ምሕላ በመያዝ፤ ለዘማቾች የቁም ፍትሐት በማድረግ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በማሰብ መልካቸው እና ቋንቋቸው የሚመስሉንን አሠልጥነው ይልካሉ፡፡ ገንዘብ ማግኝት የሃይማኖተኝነት መስፈርት አስመስለው የዋሃንን ያሳስታሉና በቻሉት ሁሉ የቤተክርስቲያንን አስተዋጽኦ ከትውልድ አእምእሮ አጥበው ለማውጣት ብቻ ሳይሆን የፈጠራ ታሪክ እየፈበረኩ ጥላቻ ሲነዙ ይሰማሉ፡፡የሚያስፈልግውም ይህን የሐሰት ጽሑፍ እውነተኛ መረጃ ይዞ መንግሥት በፍርድ ቤትም መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡

ኅዳር ፯ እና ፰ በ፲፱፻፺፰ ዓ.ም ኮፈሌ አንሻ በተባለ ቦታ የእስልምና እምነት ተከታዮች ስድስት ክርስቲያኖችን ማረዳቸው እስልምና ባለበት ሀገር ሁሉ ተገዳዳሪያቸውን የማጥፋት ተግባራቸው ማሳያ ነው፡፡በምእመናን ብዛት ከፍተኛውን ቊጥር ያላትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ማጥቃት፤ ማዳከምና ምእመናንን አስገድዶ ማስለም የሚፈጸሙ ተግባራት ናቸው፡፡ በእምነት ስም የተደራጁ ቡድኖች እና የእምነቱ ተከታዮች ቤተክርስቲያንን ሲያጠቁ እና በተለያዩ ጊዜያት ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ ክርስቲያኖችን  አስገድዶ በማስለም፤ ፈቃደኛ ካልሆኑ ደግሞ የመግደል ተልኳቸውን ሲፈጽሙ ለደረሰው ጥፋት ክርስቲያኖች ለሚመለከተው አካል  አቤቱታ ሲያቀርቡ ፍትሕ አለመሰጠቱ ወደፊት መስተካከል ይርበታል፡፡ይህ ድርጊት በወቅቱና በጊዜው ካልታረመ መጨረሻ ለሌለው ብጥብጥ እንደሚዳረግ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

በቡርቃ ጉዲና እና በአዲስ ልማት ቀበሌዎች ከ፪፻ በላይ ክርስቲያን አባወራዎች ይኖሩ የነበሩ ሲሆን በ፳፻፲፩ ዓ.ም በተደረገው የክርስቲያኖች ቈጠራ ፻፹፭ ሆነዋል፡፡ ይህም የሆነው የክርስቲያኖች ግድያና ስደት ስለተባባሰና ድርጊቱ ሲፈጸም እየታየ ተው ባይ በመጥፋቱ ነው፡፡ ጥፋቱ ተጠናቅሮ በመቀጠሉም ከሚያዚያ ወር  መጀመሪያ እስካሁን ፲፭ አባወራዎች በጋሌ ሰረጡ ቅድስት ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ውስጥ ከቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ቄስ ጋር በድንኳን ተጠልለው እየኖሩ ነው፡፡ በክርስቲያኖችና በአብያተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋት ይቁም የምንለውም እንዲህ አይነት ኢሰብአዊ ተግባራት ሲፈጸሙ ሰለምንመለከት ነው፡፡ ሀገራችን ለውጥ ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ለውጡን ያልፈለጉት ወገኖች ኢትዮጵያውያን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ በማድረግ የሀገራችንን ገጽታ እያበላሹ መሆኑን ባንዘነጋውም በአንዳንድ አካባቢዎች ክርስቲያኖች ላይ ብቻ ያነጣጠረ ጥቃት ሥልጣን ላይ በተቀመጡ አካላት ጭምር ሲፈጸም መታየቱ ለሰላም ሳይሆን ለብጥብጥ  እየተሠራ ያስመስላልና መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል፡፡

የመንግሥት አካላት ሕዝብን ለማገልገል ኃላፊነት እንዳለባቸው ከተረዱ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዘር፣ቋንቋ፣ቀለም፤ ሃይማኖት፣ሳይለዩ ማገልገል ይኖርባቸዋል፡፡ለሚያልፍ ሥልጣን ታሪክ የማይረሳው ጠባሳ ትቶ ማለፍ ተገቢ አይደለም፡፡ በየቦታው ለሚከሠቱ ግጭቶች መፍትሔ ከመፈለግ ተቆጥበው ተረጋግቶ ለሥራ የተሰማራንና ስለሀገሩ የሚጸልይን ክርስቲያን መነካካት ጥፋት እንጂ ሰላምን አያመጣም፡፡

ሐምሌ ፲፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በባሌጎባ በተፈጠረ የሃይማኖት ግጭት ፭ ምእመናን ተገድለዋል፡፡ እንዲህ አይነት ጥፋቶች አሁንም ቀጥለዋል የሃይማኖት ግጭቶች ሲከሠቱ ግጭቶችን ማን እንዳስነሣቸው ማጣራትና ተገቢ የሆነ እርምጃ መስጠት ይገባል፡፡ እየታየ ያለው ግን እየተሰደዱ፣ እየተገደሉ ታቦታችሁን ይዛችሁ ውጡ የሚባሉትን ክርስቲያኖች መብታቸውን ሲጠይቁ ማሰርና ያለፍርድ ማጉላላት ነው፡፡ ይህን ተግባር ለማስታገስ በየአካባቢው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ ከሆነ የክርስቲያኖችን ችግር የፈጠረው ማን እንደሆነ፤ እነ ማን ያላግባብ እንደታሰሩ፤ ማን የሚባል ፖሊስ እንዳሰራቸው፤ ለምን ፍርድ ቤት እንዳላቀረባቸው፤ ፍርድ ቤት ለማቅረብ ጠበቃ የማግኘት መብታቸውን ማን እንዳስከለከለ መረጃውን አደራጅተው ለመንግሥት አካላትም በየደረጃው ለሚገኙ የቤተ ክህነት አገልጋዮችም ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥትንም በሕጋዊ መንገድ ለመጠየቅ ያግዛል፡፡ አጥፊዎች እናምንበታለን ከሚሉት  የእምነት ተቋማት ጋር ለመወያየትና አሳማኝ መረጃ ይዞ በፍርድ ቤት ለመጠየቅ ይጠቅማል፡፡ይህ ሁሉ እየተደረገ ጎን ለጎን መረሳት የሌለበት ጉዳይ እግዚአብሔር አምላክ፤ችግሩን እንዲያስወግደው በጾም በጸሎት መጠየቅ ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን በንጹሕ ልቡና ሆነን ከጠየቅነው የተፈጠረው ችግር ይርቃል፡፡ በኃጢአታችን ምክንያት ከመጣም ይቅር ይለናል፡፡ ለክብር ከሆነም ያጸናናል፡፡ በእምነት ጸንተን ብንሞት እንኳ ገዳዮቻችንን ማርኮ ያመጣል፡፡ የሰማዕትነት ደም ደርቆ አያውቅም የተባለው ሞታቸው አሕዛብን ማርኮ የሚያመጣ በመሆኑ ነው፡፡

 በክርስቲያኖችና በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥፋት አለመቆሙ ያሳሰበው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰ/ት/ቤት ወጣቶች፤ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና ምሩቃን እንዲሁም የመንፈሳዊ ማኅበራት ተወካዮች በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዩች ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ መግለጫው በአንድ በኩል አጥፊዎች ሕግና ሥርዓት ባለበት ሀገር ከእኩይ ድርጊታቸው እንዲታገሡ ጥፋታቸውን የደረስንበት መሆኑን እንዲረዱ የሚያሳስብ ሲሆን በሌላ በኩል መንግሥትም አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ  እንዳለበት ለማሳሰብ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ክርስቲያኖች አንድነትና ትብብር የሚያደርጉበትና ከፊት ይልቅ መትጋት የሚገባቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ያለችበት ሁኔታ ያሳሰበው የቤተክርስቲያን አካል የቅድስት ቤተክርስቲያናችን ውለታና እያደረገችው ያለው አስተዋጽኦ ተረስቶ ለሀገራዊ ጥፋት  ባለቤት ተደርጋ መኮነኗን በጽኑ እንቃወማለን፤ ቤተክርስቲያን ከትላንት እስከ ዛሬ የሰላም መልእክተኛ እንጂ አጥፊዎች የሐሰት ታሪክ ፈጥረው እንደሚያወሩት ሕዝብን ከሚያስጨፈጭፉ አካላት ጋር ተባብራ ያጠፋች አይደለችም፡፡ በእውነት ለመናገር ካስፈለገ  በደቡብ፤ በምሥራቅ፤ በኦሮምያም ጭምር ክርስትና ያበበው በሀገሩ ባህል ላይ መሆኑን  መረዳት አይሳነውም፡፡ በአንጻሩ ሌሎች እምነቶች በገቡበት ቦታ ግን ነባሩ ባሕል ተደምስሶ ሀገራችን እስከማይመስል ደርሷል፡፡ አስተዋይ አእምሮ ላለው ሰው በታሪክ ተወቃሽ የሚሆነው ነባሩን ባህል አስገድዶ ሃይማኖት ያስለወጠ እንጂ ባህላችሁን ጠብቃችሁ ዘላለማዊ ርስትን የምትወርሱበትን ወንጌልን መቀበል ትችላላችሁ  የምትለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሆን አይደለችም፡፡

ይቆየን

 ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፮ ዓመት ቁጥር ፲፯

 

በዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ፈተና

የተከበራችሁ አንባብያን እንደምን ሰነበታችሁ? ባለፉት ተከታታይ ጽሕፎች ላይ በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ፈተና በተለይ የቤተ ክርስቲያንን ቃጠሎና የይዞታ መነጠቅን በተመለከተ መጠነኛ መረጃ የሚሰጥ ጽሑፍ ማቅረባችን ይታወቃል፡፡ ቀጣዩን ደግሞ እንደማከተለው አቅርበነዋል፡፡

ሀገራችንን የምንወድና ሰላማውያን ከሆንን ቀርበን መወያየት፣ ጥፋተኞችን መገሠጽ፣ አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብና ለተፈጠረው ጥፋት ይቅርታ ጠይቆ ካሳ ካስፈለገ መክፈል ነው፡፡ በሃያ ሰባት ዓመታት በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን እንተውና ለውጥ ከመጣ በኋላ የጥፋት ኃይሎች የፈጸሙትን በመጠኑ ለማቅረብ እንሞክር ቢባል እንኳ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ‹‹ሚያዝያ ፳፻፲፩ ዓ.ም ሐረር ሳሮሙጢ በሚኖሩ በአራት ካህናትና በምእመናን ላይ የመግደል ሙከራ ተደርጐ ከባድ ድብደባ ቢፈጸምባቸውም በእግዚአብሔር ቸርነት ተርፈው ሆስፒታል ገብተዋል፡፡›› ይህ የሚያሳየው ጥፋቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው፡፡ ይህንን ጥፋት እየፈጸሙ ሰላማውያን ነን ቢሉን ማመን አንችልም፡፡ ሰላም የሚመጣው በተግባር እንጂ በቃል አይደለም፡፡ መንግሥት አጥፊዎችን ለሕግ ያቅርብልን፣ ወደ ፊትም ጉዳት እንዳይደርስብን ጥበቃ ያድርግልን የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ጥፋቱ አንድ ጊዘ ተፈጽሞ በመቆሙም አይደለም፡፡ በድሬዳዋ፣ በከሚሴ፣ በኤፍራታና ግድም፣ በሰሜን ሸዋ ሰላሌ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ ወሊሶ፡ በጅማ ሊሙኮሳ በተከታታይ የተፈጸመውን በማየት እንጂ፡፡

በድሬዳዋ ሀገረ ስብከት የተፈጸመውም ከዚህ ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡ በድሬዳዋ ከተማ ዳር የሚገኘውን ‹‹የመካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን ይዞታ እንወስዳለን በማለት ከመጋቢት ፳፻፲፩ ዓ.ም ጀምሮ ተደጋጋሚ ጥቃቶች በእስላሞች ተፈጽመዋል፡፡ የፖሊስ አባላቱ ችግር በተፈጠረበት ቦታ በሰዓቱ ቢደርሱም ጥቃት ፈጻሚዎቹን በመያዝና ወደ ሕግ በማቅረብ ፈንታ እንዲሸሹ ማድረጋቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ አናስነካም፣ ቤተ ክርስቲያን ጉዳት ሲደርስባት ቆመን አናይም ያሉ ወጣት ክርስቲያኖችን አስረው በመግረፍ የጥቃቱ ተባባሪ ሆነዋል፡፡››

ማኅበረ ቅዱሳን ወንጀል የሠሩ አካላት አይጠየቁ አላልንም፡፡ ጥፋተኛ ተለቅቆ፣ ተጎጂው የሚታሰርበትና የሚሰቃይበት አሠራር ይስተካከል በማለት ግን እንጠይቃለን፡፡ የፍትሕ አካላትም ከአንድ ወገን የሰሙትን ብቻ ይዘው ወደ ውሳኔ ከመግባት ይልቅ ከሃይማኖት ነፃ በሆነና የተቀመጡበትን ኃላፊነት ባገናዘበ መልኩ ሁለቱንም ወገን ፊት ለፊት አቅርቦ እውነቱን በማውጣት አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ለማለት ነው፡፡ በወቅቱ የቤተ ክርስቲያኑን ይዞታ ለመቀራመት አሰፍስፈው የነበሩ ወገኖች የምኒሊክ ሃይማኖት ይውጣልን በማለት ይጮኹ እንደነበር የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ ድርጊት የሰውን ልጅ የእምነት ነፃነት የሚፃረር ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ ለመቀራመትና ደኗን ጨፍጭፎ ለማውደም የተሰለፉ ወገኖች ቤተ ክርስቲያኗን ከምኒሊክ ጋር ለማያያዝ ምን ሞራላዊስ ሃይማሃታዊስ ችሎታ ይኖራቸዋል፡፡ ክርስትናም ጌታችን ለሐዋርያት ያስተማረው እንጂ በሰዎች የተፈጠረ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ምኒሊክ ከመነሣታቸው ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ፍጹም አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ወልድ ፍጹም ሰው በመሆን የመሠረተው፣ ዓለምን ከጨለማ ወደ ብርሃን ያመጣበት ሃይማኖት ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስን ሊገድሉ በለስ አልቀናቸው ያሉ አይሁድ የሮማውያን ሕግ የሰጣቸውን መብት በትክክል መጠቀም ሲገባቸው ሕጉን ጠምዝዘው ጳውሎስን ካልገደልን እህል አንበላም፣ ውኃም አነጠጣም ብለዋል፡፡ ታሰሮ የነበረውን ቅዱስ ጳውሎስ ወደ አደባባይ እንዲያወጣላቸው ሀገረ ገዥውን ሕጋውያን መስለው ጠይቀው የግል ጥላቻቸውን በሕግ ሽፋን ለመፈጸም ተማምለው እንደነበር ሁሉ ዛሬም እየተፈጸመ ያለው የጥንቱ ተመሳሳይ ክፍት ነው፡፡ ሕግ የሰጠውን መጠቀም መብት ነው፡፡ ሕግን ጠምዝዞ ግላዊ ፍላጐትን ለማሟላትና ሌላውን ለማጥፋት መሞከር ግን ወንጀል ነው፡፡ የማይገለጥ የተከደነ፣ የማይታወቅ የተሰወረ ጉዳይ ባለመኖሩ ተደብቀን ብናጠፋ ሁለት ቀን ሳናድር እውነቱ ይገለጣል፡፡ የአጥፊዎች አሳብ ታሪክ ምንም ይበል እኛ ብቻ ደኅና ካላሉና ሀገር ብትበተን ምን አገባን ካላሉ በስተቀር ያልተረዱት እውነታ ወደ ሌላው የወረወሩት ቀስት እነሱንም እንደሚወጋቸውና ለሌላው ያነደዱት እሳት ራሳቸውንም እንደሚያቃጥላቸው ነው፡፡

በዚሁ በያዝነው ዓመት ባሳለፍነው የሚያዝያ ወር ሌላም ዘግናኝ ድርጊት በእስልምና እምነት ተከታዮች ጅማ ሀገረ ስብከት ሊሙኮሳ በሚባል ቦታ ተፈጽሟል፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው ‹‹ሚያዝያ አምስት ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም ለሚዘክረው አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጽዋ ጉዝጓዝ ቄጠማ ሊያጭድ በሔደበት ሚጡ ወንዝ ዳርቻ አቶ ልየው ጌትነት የተባለን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተ ክርስቲያን የእምነት ተከታይ አንገቱን ቀልተዉ በመጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ከጣሉት በኋላ በላዩ የከብት ፍግ ጨምረውበታል፡፡ የመጸዳጃ ጉድጓዱ ባለቤት አቶ መሐመድ ሃምዛ የተባሉ ግለሰብ ነው፡፡ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ቄጤማ ሊያጭድ ወጥቶ የቀረውን አቶ ልየው ፍለጋ ቢወጡ የደም ነጠብጣብ በማግኘታቸው ነጠብጣቡን ተከትለው ሲሔዱ ለማመን በሚከብድ ሁኔታ ገድለው ከአጨደው ቄጠማ ጋር መጸዳጃ ቤት ውስጥ ጥለውት ተገኝቷል፡፡›› ይህን ወንጀል የፈጸመው አካል ተጠርቶ ወደ ሕግ አልቀረበም፡፡ ከሁለት ዓመት ላላነሰ ጊዜ በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ግፍ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ድንኳን ተክለው መኖር ጀምረዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ስታስጠልል ዘርና ሃይማኖት እንደማትመርጥ የመካቆሪሾች አባርረዋቸው ለመጡት የመሐመድ ተከታዮች ክርስቲያኑ ንጉሥ አረማህ ተቀብሎ በሰላም እንዲኖሩ የፈቀደላቸው መሆኑን የምንመሰክረው እኛ ብቻ ሳንሆን ምዕራባውያን ጭምር ናቸው፡፡ ይህንንም ጉዳይ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ‹‹የእነሱ መንግሥታት (ምዕራባውያን) በ፳ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እኔን የመሰለ ስደተኛ በሀገሩ መቀበሉን እንደ ትልቅ ሰብአዊ ድርጊት ሲቆጥረው፤ የእኔ ሀገር ንጉሦች የጄኔቫ ኮንቬንሽን (ስምምነት)፣ ሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲ የሚባል ነገር በሰው ልጅ አእምሮ ባልታሰበበት ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በፊት በእምነታቸው ከዘመኑ የሀገራችን ሰዎች እምነት የተለዩ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች ጥገኝነት መስጠታቸውን፣ እነዚህን ስደተኞች መልሱልን በማለት ዓረቦች ለላኩት መልእክተኛ፣ ንጉሣችን በእያንዳንዱ ስደተኛ ክብደት የሚመዝን ወርቅ ብትሰጡኝ እንኳን አሳልፌ አልሰጣችሁም›› (አንዳርጋቸው፣፳፻፲፩፥፲፱) በማለት መመለሳቸውን ጽፈዋል፡፡

ስለዚህ ጉዳይ በጥልቅ ለማወቅ የፈለገ ሰው የእነ ጆን ሰፔንሰር ትሪሚንግሆምን እስላም ኢን ኢትዮጵያን እና የጎበዜ ጣፈጠን እስልምና በአፍሪካ ማንበብ ይጠቅመዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን እንግዳ ተቀባይነት በማቃለል ማጣጣል ተገቢ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ነገሥታት ጠብቀው ባቆዩዋት ሀገር እየኖሩ ነገሥታትን የሚተቹና ቤተ ክርስቲያንን ከነገሥታት ጋር እየደረቡ ለመምታት የሚፈልጉ ወገኖች እንደሚተርኩት ሳትሆን ትክክለኛ በመሆኗ በቅርቡ በለገጣፎም ሆነ በቡራዩ የተፈናቀሉ የእስልምናም የሌላ እምነት ተከታዮች እንጠጋ ብለው ሲመጡባት አታምኑብኝም የምትል ሳትሆን ልጆቼ ኑ ብላ እጇን ዘርግታ የምትቀበል መሆኗን አሳይታለች፡፡ ቤት ፈርሶባቸው ቤተ ክርስቲያን የተጠለሉ ወገኖች በኢሳት የቴሌቭዥን ጣቢያ ሲናገሩ ሰምተናልና፡፡

የሚጠቅመንም ካለፈው መጥፎ ታሪክ እየተጠነቀቅን መልካም ከሆነው ያለፈ ታሪካችን መማር ነው፡፡ ድሮ ተፈጽሟል እያሉ የሐሰት ታሪክ እየደረቱ የጥፋት ነጋሪት መምታት እልቂት እንጂ ሰላም ስለማያማጣ አጥፊዎች ደግመው ደጋግመው ተረጋግተው እንዲያስቡበት ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ መንግሥትም አጥፊዎችን እንዲያስታግሥልን ደግመን እንጠይቃለን፡፡ ይህንን ጽሑፍ የምንዘጋው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና ምሩቃን እንዲሁም የመንፈሳዊ ማኅበራት ተወካዮች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ ነው፡፡ እንዲህ ይላል ‹‹እስከ ዛሬ ሲፈጸሙ በኖሩ ጥቃቶች ላይ ከጥንስሱ ጀምሮ እጃቸውን የከተቱ፣ ያለ አንዳች ፍርሃት በአደባባይ ጭምር በክርስቲያኑ ሕዝብ ላይ ሲሳለቁ እና በል ሲላቸውም ዕልቂትን ሲያውጁ በከረሙና እያወጁ ባሉ ከመንግሥት ጭምር የፈረጠምን ነን ባይ ግለሰቦች እና ተቋማት መንግሥት ለፍርድ እንዲያቀርብልን እንጠይቃለን›› ይህ ቃል ሰላም ወዳድ ከሆነ አስተዋይ አካል የሚነገር ነው፡፡ ጥፋትን በጥፋት መመለስ ለሀገር አይጠቅምምና፡፡

 ይቆየን

 ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፮ ዓመት ቁጥር ፲፮

 

በዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ፈተና

የተከበራችሁ አንባብያን እንደምን ሰነበታችሁ? ባለፉት ተከታታይ ዕትሞች ላይ በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ፈተና በተለይ የቤተ ክርስቲያንን ቃጠሎና የይዞታ መነጠቅን በተመለከተ መጠነኛ መረጃ የሚሰጥ ጽሑፍ ማቅረባችን ይታወቃል፡፡ ቀጣዩን ደግሞ እንደማከተለው አቅርበነዋል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያለስሟ ስም፣ ያለ ግብሯ ግብር እየተሰጣትና ለማጥፋት ምክንያት እየተፈለገላት መሆኑ እየታየና እየተሰማ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ አጥቢያ በተዘረጋው መዋቅር መሥራት የሚገባትን፣ ማኅበራት፣ ዘማርያንና ሰባክያን መፈጸም የሚኖርባቸውን፣ ምእመናንና ምሁራን ማከናወን የሚጠበቅባቸውን ማሳወቅ ዘመኑ የማጠይቀው ተግባር ነው፡፡ በአንድ በኩል ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር መተባበር እና መረጃ በመለዋወጥ መሥራት የሚገባንን፣ በሌላ በኩል እየተፈጸመ ያለውን ጥፋት ለመንግሥት በማሳወቅ በአጥፊዎች ላይ እርምት እንዲወሰድ ማገዝ ይገባል፡፡ የአጥፊዎችን የተሳሳተ ትርክታቸውንና ለቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ጥላቻ እንዲያስወገዱ እንዲያደርግ ማሳሰብ ሲገባ በሌላ በኩል ደግሞ ከዛሬ ነገ ይማራሉ፣ በመረጃ የተደገፈ ትንታኔ በማቅረብ አስተማሪ የሆነ ጽሑፍ ያቀርባሉ ብለን ብንጠብቅም ዝም ማለታችንን እንደ ፍርሃት፣ አለመጻፋችንን እንደ አላዋቂነት ለሚቈጥሩ ወገኖች ሚዛኑን የጠበቀና ትክክለኛ መረጃ መስጠት ይገባል፡፡

ከትላንት እስከ ዛሬ የፈጸሙትን ጥፋት በማሳየት ማን ጥፋተኛ እንደሆነ አንባብያን የራሳቸውን ፍርድ እንዲሰጡ ማንቃትና ለተጨማሪ ንባብ መቀስቀስ ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል›› አካሔዳቸውን መግለጥ ባልቻልን ምንም እውነትን ብንይዝ ካልተገለጠ ጠቀሜታው ይደበዝዛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከአንዳንድ ባለሥልጣናት እየተጠጉ የሚፈጽሙትን ጥፋትም ማጋለጥ ያስፈልጋል፡፡ ሥራ አጥ ወጣቶች ሠርተው የሚበሉበት፣ ምሁራን ተመራምረው ሀገር የሚያበለጽጉበት ተግባር ከመፈጸም ይልቅ ሀገሪቱን ሁሉ ቤተ እምነት ካላደረግን፣ የሚያዩትን ባዶ ቦታ ሁሉ ካልሠራንበት የሚለው አካሔድ እንደ ሀገር አስማምቶ ሊያኖረን እንደማይችል ማስገንዘብ ይገባል፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ ሰማንያ በመቶ የሚሆነው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ያለው ቤተ እምነትና ፕሮቴስታንትና እስልምና ቢደመር ሃያ በመቶ ባይሆኑም እያንዳንዳቸው ያላቸው ቤተ እምነት ከኦርቶዶክሱ እጥፍ ሊሆን ምንም አይቀረው፡፡ ይህን እያወቅን እንኳ ያልጠየቅነው ከሁሉ በፊት ለሀገር ማሰብና ለሰላም መስፈን መሥራት ይገባል ብለን ስለምናምን ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያኗ ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥፋት ያሳሰበው ዜና ቤተ ክርስቲያን በጥቅምት ኅዳር ፳፻፲፩ ዓ.ም ዕትሙ ‹‹ለሁሉም በተሰጠው ገደብ የለሽ የእምነት ነፃነት መሠረት፣ ሁሉም የራሱን እምነት በሰላም ማራመድ ሲገባው በተቃራኒው ፀረ ኦርቶዶክስ ዘመቻ በሁለት ግንባር በመካሔድ ላይ ይገኛል፡፡ በአንድ በኩል ቀደም ሲል በዝርዝር እንደተገለጠው ፀረ ክርስትና አቋም ያለው ቡድን በአንዳንድ አካበቢዎች የሚገኙትን የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን እያቃጠለ ነው፡፡ ካህናትንና ምእመናንንም እያረደ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነ ፖስተር ኢዩ ጩፋን የመሳሰሉት የእነ ሬንሐርድ ቦነኬ ደቀመዛሙርት በቡድን ተሰማርተው ሕዝቡን በወንጌል ሳይሆን በመናፍስት በማስገደድና በካራቴ በማሳመን የእነርሱ ተከታይ ለማድረግ እየጣሩ ነው›› በማለት በርእሰ አንቀጹ ጽፎ ነበር፡፡

የሚገርመው ይህ ጥፋት በመቀነስ ፈንታ እየጨመረ፣ በመሻሻል ፈንታ እየባሰበት መምጣቱ ነው፡፡ የችግሩ መሞከሪያ፣ የጸጥታው ማስፈጸሚያ ቤተ ክርስቲያንና ክርስቲያኖች እስከሚመስሉ ድረስ በክርስቲያኖች ሞትና መከራ ላይ መከራ እየተደረገ ሀገር ትረጋጋለች ተብሎ ስምምነት ላይ የተደረሰ ያስመስላል፡፡ ይህ ጥፋት ሁል ጊዜ ሰበብ እየተፈለገ እንዲቀጥል አንፈልግም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል በግል የተፈጸመ፣ ክርስቲያኖች ሲገደሉ የግል ጠብ እየመሰለ መነገሩ በጀርባው ሌላ ተንኮል ያለ መሆኑን እየተገለጠልን መምጣቱን መረዳት ይገባል፡፡ ሀገር በጠባጫሪነትና ሁሉ ነገር ለእኔ በሚል መንፈስ መገንባት እንደማትችል የታወቀ ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን መረጃው እያለው እንደ ሌለው፣ ግልጽ አድልዎ እየተፈጸመ መሆኑን እያወቀ ዝም ያለው አጥፊዎችም አደብ ይገዛሉ፣ መንግሥትም እርምት ይወስዳል በማለት ነው፡፡ አሁን ግን የሚፈጸመው ጥፋት እየከፋ መጥቷል፡፡ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ማኅበር ለመዘከር የቤት ጉዝጓዝ ሊያጭድ የሔደን ክርስቲያን በገጀራ ከትክቶ ሽንት ቤት መክተት፣ በየቦታው ኦርቶዶክሶች እየተመረጡ አካባቢያቸውን እንዲለቁ መደረጉ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ይህ ሲደረግ መረጃው እንዳይወጣ መደበቁ እንደ ሀገርም እንደ ቤተ ክርስቲያንም መሠራት ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡

በቤተ ክርስቲያን እንዳይሠለስ እንዳይቀደስ ከማድረግ በተጨማሪ በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን የሚገኘው የመሎላሃ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጥምቀተ ባሕር ሥልጣን ላይ በተቀመጡ የፕሮቴስታንት ተከታዮች ለአውቶቢስ መናኽሪያ መሰጠቱና ታቦትና ንዋያተ ቅድሳታችሁን ይዛችሁ ውጡ ተብለው በእግራቸው ፻ ኪሎ ሜትር በላይ ታቦትና ንዋያተ ቅድሳት ይዘው መንከራተታቸው በፈጠረው የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ጫና የተደናገጡ ባለ ሥልጣናት ታቦቱ ወደ መንበሩ እንዲመለሰ ያደረጉበት ታሪክ የሦስት ወር ትዝታ ነው፡፡ እንዲስተካከል የምንፈልገውም እንዲህ አይነቱ መጥፎ ተግባር ነው፡፡ ሕሊናቸው የመራቸውን፣ መንግሥት የሰጣቸውን ኃላፊነት የሚወጡ የሌላ እምነት ተከታይ ወገኖች እንዳሉ ሁሉ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለጥፋት የሚጠቀሙ መኖራቸው፣ በጥፋት ላይ ጥፋት እያስከተለ በመሆኑ በቶሎ መታረም አለበት፡፡

በሶማሌ ክልል አሥር አብያተ ክርስቲያን እንዲቃጠሉና ከሃያ ሰባት በላይ ምእመናን እንዲገደሉ፣ ብዙዎችም እንዲቈስሉ የተደረገው በመንግሥት መዋቅር ነው፡፡ የዚህን ድርጊት ተገቢ አለመሆን የተረዳው አዲሱ የሶማሌ መንግሥት አመራር ቤተ ክርስቲያኗን ይቅርታ መጠየቁን ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የደሴ ከተማ ነዋሪዎችን ባወያዩ ጊዜ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ አጥፊዎች ከስሕተታቸው ቢመለሱና አስቀድመው ጥፋት ከመፈጸማቸው በፊት ደጋግመው ቢያስቡ መልካም ነው፡፡ ይህም ባይሆን ከተፈጸመ በኋላም ይቅርታ መጠየቃቸው የሚያሰመሰግን ነው፡፡ ይቅርታ መጠየቁ ብቻውን በቂ ባለመሆኑም ተጨማሪ ተግባራትን መፈጸም ይገባል፡፡ በያዘው ሥልጣን የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ እየነቀለ፣ ክርስቲያኖችን የገደለ በቃሉ ብቻ ይቅርታ በማለት እንዳይቀጥል ደንብና ገደብ ቢኖረው መልካም ነው፡፡ ይቅርታው ከስሕተት መታረሚያ፣ ዳግም ስሕተት ላለመፈጸም ቃል መግቢያ እንዲሆን መሥራት ይገባል፡፡ ይህንን ጉዳይ ወደ ፊት ሰፋ አድርገን ስላምናቀርበው በዚሁ እናቁምና በተለያዩ ቦታቸው የተፈጸሙ በምእመናን ላይ የደረሱትን ግድያዎች እናስከትላለን፡፡

ሐ. በምእመናን ላይ የደረሰ ግድያ፡-

ቤተ ክርስትያን ባለችበት ሁሉ ምእመናን አሉ፡፡ ምእመናን ቤተ ክርስቲያናቸው እየተቃጠለች ቆመው ማየት ስለማይችሉ ወይ አብረው ይቃጠላሉ ካልሆነም በአጥፊዎች ይገደላሉ፡፡ ይህም ፍርሃታቸውን ሳይሆን ጥብዓታቸውን፣ በመግደል ሳይሆን በመሞት አሸናፊዎች መሆናቸውን ማረጋገጣቸውን ያሳያል፡፡ በሊቢያ የሚገኘው አሸባሪው አይኤስአይኤስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖችን ብቻ መርጦ ለመግደል ሲወስዳቸው በሰማዕታቱ ላይ ይነበብ የነበረው በራስ መተማመን ወደ ሞት ሳይሆን ለንግሥና ታጭተው የሚሔዱ ይመስል ነበር፡፡ ብዙዎች የውጭ ሚዲያ ጋዜጠኞችና የማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ ጸሐፊዎች እንዲህ አይነት ምእመናንን በእምነት አንፃ የምታወጣ ቤተ ክርስቲያን አማኝ መሆን የሚያስገኘውን ክብር ሲገልጡ ነበር፡፡ በአንጻሩ በመግደል እናሸንፋለን ብለው ያሰቡ አሸባሪዎች የሚቀናባቸው ሳይሆን የሚጠቋቆምባቸው ቢያተርፉና የሚተቻቸው ቢያገኙ እንጂ የተስተካከለ አእምሮ ካለው ሰው ምስጋና አያገኙም፡፡ አራት ዓመት ቢያልፍም የክርስቲያኖች ጥብዓታቸው፣ ሞትን ለዘለዓለማዊ ሕይወት መውረሻ መሆኑን ስለአወቁ በደስታ መጓዛቸው ዛሬም ድረስ ይተረካል፡፡ ባለፈው ታኅሣሥ የሊቢያ መንግሥት በጅምላ ተገድለው የተቀበሩበትን ቦታ አግኝቶ ለኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚመልስ ሲናገር ክብራቸውን በመግለጥ ጭምር ነው፡፡

የክርስቲያኖች መገደል ተገቢ አለመሆኑን የምንገልጠው በዐዋጅ የሚፈጸም ስለሚመስል እንጂ እንደ ዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያኖችን የሚፈጅ መንግሥት ቢሆን ለምን ለማለት አይደለም፡፡ መንግሥት በውጭና በሀገር ውስጥ የነበሩትን አባቶች ማስማማቱ፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሀገር መሆኗን መግለጡ፣ በደርግ ተወስደው የነበሩ ቤቶችን መመለሱ መልካም ነው፡፡ ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም መሬታችን ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን እየሰበከ ሕዝቡ የሌላ እምነት ተከታይ እንዲሆን የሚሠሩ ስለአሉ ቆመን ማየት የለብንም፡፡ የአጥፊዎችን ድርጊት ይህንንም በገሀድም ሆነ በስውር የሚደግፉ ስለአሉ መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጥ ለማሳሰብ ነው፡፡ መንግሥትን ስናሳስብ የሰማዕትነትን ዋጋ ዘነግተን፣ ሰማዕትነትን ፈርተን ሳይሆን ዕለት ዕለት ሰማዕትነት እንደምንቀበል አምነን ዘመኑ የሚጠይቀውን ለመፈጸም የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ነው፡፡ ይህንንም መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹አይሁድ ስለ ጳውሎስ ከፊት ይልቅ አጥብቀህ እንደምትመረምር መስለህ ነገ ወደ ሸንጎ ታወርደው ዘንድ ሊለምኑህ ተስማምተዋል፡፡ እንግዲህ አንተ በጄ አትበላቸው፤ እስኪገድሉት ድረስ እንዳይበሉና እንዳይጠጡ ተማምለው ከእነሱ ከዐርባ የሚበዙት ሰዎች ያደቡበታልና፤ አሁንም የተዘጋጁ ናቸው፣ የአንተንም ምላሽ ይጠብቃሉ አለው፡፡›› (ሐዋ.ሥ ፳፫፥፳‐፳፪) በማለት የተገለጠውን ማስተዋል ይገባል፡፡ ጥፋትን የሚፈጽሙና የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ አካላት ፍትሐዊና ቀና የሆነውን አሠራርና ሕግ ለራሳቸው በሚመች መንገድ የሚጠቀሙበት መሆኑን ይህ ቃል ያስረዳል፡፡ ልንነቃ የሚገባው የአካሔዳቸውን መሠሪነት ነው፡፡ እነሱ ሐሰትን ታሪክ አስመስለው ሲጽፉ ሕሊናቸውን አየቆጠቁጠውም እንዲያውም ለአምላካቸው መብዓ ያቀረቡ የሚመስላቸው አካሔዳቸው ተገቢ አለመሆኑን የሚያስገነዝብ መልስ ሲሰጣቸው ደግሞ መረጃ ይዞ ተከራክሮ እውነቱን ከማውጣት ይልቅ ትክክለኛ ጉዳይ የጻፉትን አካላት ስም በማጥፋትና ጉዳዩን ሌላ መልክ በመስጠተ ሌሎች እንዳይጽፉ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ የተቀመጡበትን ወንበር መከታ አድርገው ሕዝብን በሕዝብ ላይ እንደማነሣሣት፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት እንደማጋጨት ይቈጥሩታል፡፡ መታወቅ የሚኖርበት ኦርቶዶክሳውያን ሲጽፉ ብቻ ጠብ አጫሪ መባል የማይገባቸው መሆኑን ነው፡፡ የሕዝብ ሰላም የሚያሳጣ፣ ከልማት ጥፋትን የሚያመጣ ተግባር ከፈጸሙ ለዚህ የጥፋት ተልእኮአቸው መልስ መስጠታችን፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን ማንቃታችን የማይቀር ነው፡፡ እውነተኞች ከሆኑ የምንለያይበትንና የምንጋጭበትን እየፈለፈሉ በማውጣት ተአማኒነት ያለው ጽሑፍ ማቅረብ ነው፡፡ በዚህ ፈንታ የሚመርጡት በለመዱበት መንገድ መንግሥት በተቀየረ ቊጥር እየተጠጉ ኦርቶዶክሳውያንን ማስጠላት ነው፡፡ ይህን የምንለው እየተፈጸመ ያለው ጉዳይ ለሀገር አንድነት የማይጠቅም በመሆኑ በሌላ በኩል እነሱ በሔዱበት መንገድ መሔድ የሚያደርሰውን ጥፋት በመገንዘብ ነው፡፡

ይቆየን

 ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፮ ዓመት ቁጥር ፲፮

ማእከለ ክረምት

ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

ዘመነ ክረምት የሚጋመስበት ወቅት ማዕከለ ክረምት ይባላል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ሁለት  ንኡስ ክፍል ይገኛሉ፤ እነርሱም ዕጒለ ቋዓት እና ደሰያት / ዐይነ ኩሉ/ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ይህም ወቅት ከነሐሴ ፲፩ – ፳፯ ቀን ድረስ ያለውን ፲፯ ዕለታት ያካትታል፡፡ ፍጥረታትና በባሕር የተከበቡ ደሴቶች የሚታወሱበት ወቅትም ነው፡፡

ዕጒለ ቋዓት- የሚለው ቃል ቁራን ያመለክታል፤ ቁራ ከእንቁላሉ ተቀፍቅፎ ሲወጣ ያለ ፀጉር በሥጋው ብቻ ይወጣል፡፡ እናትና አባቱም እነርሱን ባለመምሰሉ ደንግጠው ይሸሹታል፤ በዚህ ጊዜ የሚንከባከበው ሲያጣ እግዚአብሔር በረድኤት አፉን ከፍቶ ምግብ ሲሻ ተሐዋስያንን ብር ብር እያደረገ ከአፉ ያስገባለታል፡፡ (ኢዮ. ፴፰፥፵፩) «ለቁራ መብል የሚሰጠው ማን ነው?›› ብሎ እንደገለጸው እግዚአብሔር የሰጠውን እየተመገበ ቆይቶ ሲጠነክር እንደ እናትና አባቱ ያለ ፀጉር ያወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ግን አባቱና እናቱ ቀርበው ይንከባከቡታል፡፡ ቁራ በሥነ ፍጥረት አቆጣጠር በክንፍ ከሚበሩ አዕዋፍ ነው፡፡ ይህም አምላካችን እግዚአብሔር ለፍጥረቱ የሚያስብ በመሆኑ ይህን ዘመን ርኅራኄ ለተመላው ሥራው መታሰቢያ እንዲሆን ቤተክርስቲያን ዕለ ቋዓት በማለት ታስታውሳለች፡፡

ደሰያት – የሚለው ቃል በውኃ የተከበቡ ቦታዎችን ያመለክታል፡፡ እነዚህን ቦታዎች በውኃ እንዲሸፈኑ አድርጎ በውስጣቸው ያሉትን ሰዎች እንስሳት፤ አራዊትና አዕዋፍ ሁሉ የሚጠብቃቸው፣ በተስፋና በእምነት አበርትቶ የሚያኖራቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህም ሰዎች እግዚአብሔርን በዚህ ያመሰግኑታል፡፡ ደሴት የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፤ አንዲት ደሴት በውስጧ ብዙ ፍጥረታትን ትይዛለች፡፡ ከደሴት የተጠጉ ድኅነትን እንደሚያገኙ ሁሉ ወደ ቤተክርስቲያን የተጠጉ ሁሉ ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ ይጠበቃሉ፡፡

በዚህ ዕጒለ ቋዓትና ደሰያት ወቅት ክፍለ ክረምቱ እየተገባደደ፣ ውኃው እየጠራ፣ መሬቱ እየረጋ፣ ደመናውና ጉሙ እየተቃለለ፣ የወንዝ ሙላት እየቀነሰ፣ የክረምት ምግባቸውን ይዘው በየዋሻው የከረሙ ጭልፊቶችና አሞራዎች ድምጻቸውን እየሰሙ ምግብ ፍለጋ ሲወጡ የሚታይበት ወቅት ነው፡፡

‹‹ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት፣ ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት›› እንዳለው፤ ዝናብ ይቀንሳል፣ ምድሪቱም መቀዝቀዝና መጠንከር የምትጀምርበት ወቅት ነው፡፡

ቅድስት ቤተክርስቲያን በዚህ ወቅት እግዚአብሔር አምላክ ለሥጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ ምሕረቱም ለዘላለም የሆነውን የሰማይን አምላክ መሆኑንና ፍጥረታትም ሁሉ እርሱን ተስፋ የሚያደርጉ መሆናቸውን የሚገልጡ መዝሙራት፣ ትምህርት፣ ስብከት ይሰጣል፣ ይነበባል፡፡ (መዝ.፻፵፬፥፲፮-፲፯)

በተጨማሪ በዚህ በማእከለ ክረምት ‹‹ዕረፍተ አበው›› ከነሐሴ ፳፯ እስከ ነሐሴ ፳፱ ድረስ ባለው ጊዜ ይታሰባል፡፡ ከ፳፪ቱ አርዕስተ አበው አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ የቤተሰቦቻቸው ዕረፍት ይታሰባል፡፡ የአብርሃም ታዛዥነት እና የይስሐቅ ቤዛነት ይታሰባል፡፡ የተቀበሉትም ቃልኪዳን ‹‹ወተዘከረ ሣህሉ ዘለዓለም ዘሠርዓ ለአብርሃም መመሐለ ለይስሐቅ ወዐቀመ ስምዐ ለያዕቆብ ያረኁ ክረምተ ይገብር ምሕረተ እምሰማይ ይሁብ ወእምድር በረከተ ያጸግብ ነፍሰ ርኅብተ›› በማለት ይዘመራል፡፡

ጾመ ፍልሰታ/ጾመ ማርያም/

መጋቤ ሐዲስ ብርሃን አንለይ

ፍልሰታ ማለት ፈለሰ፤ተሰደደ፤ተጓዘ፤ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄደ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ «ፈለሰት ማርያም እምዘይበሊ ኀበኢይበሊ፤ ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም፣ ከምድር ሕይወት ወደ ሰማያዊ ሕይወት፣ ተሻገረች» በማለት ፍልሰታ የሚለውን ቃል ትርጓሜ አመሥጥሮ ገልጾታል፡፡

ጾመ ፍልሰታ ከእመቤታችን ድንግል ማርያም የዕረፍት ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እመቤታችን በዚህ ዓለም ፷፬ ዓመታትን በሕይወተ ሥጋ ከቆየች በኋላ ጌታችን የእናቱን ተድላ ነፍሷን እንጂ ተድላ ሥጋዋን አይወድምና ጥር ፳፩ ቀን ፵፱ ዓመተ ምሕርት አረፈች፡፡ ዕረፍቷም እንደሌላው ሰው በሕማምና በድካም አይደለም፡፡ በገነት ዕፀዋት መዓዛ ተመስጣ ቅድስት ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይታለች፡፡ ታሪኩ በነገረ ማርያም እንደተጻፈው ሐዋርያት እመቤታችንን በአጎበር አድርገው አክብረው ወደጌቴሴማኒ መካነ መቃብር ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉም ነበርና ቀድሞ ልጇን ተነሣ ዐረገ እያሉ ሲያውኩ ኖረዋል፤  እርሷን ደግሞ ተነሣች ዐረገች እያሉ ሊያውኩን ነውና «ኑ የማርያምን ሥጋ በእሳት እናቃጥለው» ብለው በምቀኝነት ተነሱ፡፡ ከመካከላቸው አንድ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ከሐዋርያት እጅ ለመንጠቅ ዘሎ ሄዶ የአልጋውን ሸንኮር ሲይዝ የታዘዘ መልአክ በረቂቅ ሰይፉ እጆቹን ቆረጠው፡፡ እጆቹም በአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡ የምሕረት እናት የሆነችው ድንግል ማርያም ቅዱስ ጴጥሮስ ጸልዮ እጆቹን እንዲመልስለት ነግራው እንደነበረ አድርጎለታል፡፡

የእመቤታችን ሥጋዋን መላእክት ከዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር ወስደው አስቀምጠውታል፡፡ ሥጋዋ ያለበትን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ አይቶ እነርሱ ባለማየታቸው እመቤታችን ባረፈች በ፮ኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን እስከ ፲፬ ቀን ድረስ ከጾሙ በኋላ በ፲፬ኛው ቀን ሥጋዋን እንደገና ከጌታ ተቀብለው በጌቴሴማኒ ባለው መቃብር ቀብረውታል፡፡ ከዚህ በኋላ እንደ ልጇ በ፫ኛው ቀን ተነሥታ መላእክት እየዘመሩላት ወደሰማያት ስታርግ፤ ሐዋርያው ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሰ ዕርገቷን በማየቱ መላእክት «እመቤትህ እርሷ ናት፤ስገድላት» አሉት፤ እርሱም «ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ ይላል፤ከደመናው ሊወድቅ ወደደ» ምክንያቱም ቀድሞ የልጇን ትንሣኤ፤ዛሬ ደግሞ የእርሷን ትንሣኤ ለማየት ብሎ ነው፡፡ እመቤታችንም «ትንሣኤየን ያየህ አንተ ነህ ሌሎቹ አላዩም» ብላ ሐዋርያት ገንዘው የቀበሩበትን የሐር ግምጃ ሰጥታ አጽናንታ ሰደደችው፡፡

ቅዱስ ቶማስ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የእመቤታችን ነገር እንዴት ሆነ ብሎ ጠየቃቸው፤እነርሱም አግኝተው እንደቀበሯት ነገሩት፤ እርሱም ያየውን ምሥጢር በልቡ ይዞ «ሞት በጥር፤ በነሐሴ መቃብር፤ ለሰሚውም አያምር፤ይህ እንዴት ይሆናል?»፤ ቢላቸው ቅዱስ ጴጥሮስ «ድሮም አንተ ተጠራጣሪ ነህ፤ማን ያርዳ የቀበረ፤ ማን ይናገር የነበረ እንዲሉ፤ ገንዘን የቀበረን እኛ እያለን እንዴት ትጠራጠራለህ» ብለው ወደ መቃብሯ ሄደው መቃብሯን ቢከፍቱት ባዶ ሆኖ አገኙት፡፡ በዚህ ተደናግጠው ተያዩ፤ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችን ተነሣች፤ዐረገች፤ ይኸው ምልክቱ» ብሎ ገንዘው የቀበሩበትን ሰበን አሳያቸው፤እነርሱም አምነው ሰበኗን ለበረከት ተካፈሉት፡፡

በዓመቱ ነሐሴ ፩ ቀን ሐዋርያት በመንፈሰዊ ቅናት ተነሳስተው «ቶማስ ትንሣኤዋን አይቶ እኛ ሳናይ እንዴት ይቀርብናል» በማለት ነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ጀምረው በ፲፮ኛው ቀን የሐዋርያትን ሱባኤ ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር ጴጥሮስን ተራዳኢ፣ ካህን እስጢፋኖስን ሠራዔ ዲያቆን አድርጉ ቀድሶ አቅርቧቸዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላም ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን  ጾመ ፍልሰታ ተብሎ ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ይጾመዋል፡፡ የጾሙና የትንሣኤዋ በረከት ተካፋይ ያድረገን፤አሜን

«ዕረፍተ ኅሊና»

                                                                                                                             

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

እውነተኛ ዕረፍት በጎ ኅሊና ነው፤ ይውም ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኝ ዘላለማዊ ዕረፍት ነው፤ክርስቲያን ዕረፍትን ለመፈለግ ሲል መከራ ሸሽቶ አይሔድም።ይልቁንም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ብሎ በሚደክመው ድካም ውስጥ እጅጉን ይደሰታል።በዚህ ወደ አምላኩ በሚወስደው መንገድ በመጓዝ በሚገጥመው ፈታኝ ጉዞ በሚደርስበት ሥጋዊ ድካም ውስጥ መንፈሳዊ ደስታ ያለበትን ምቾትን ያገኛል። ለዚህ ነው (ሲራክ ፮፥፳፫) ላይ «ልጄ ሆይ ስማኝ፤ በምክሬም ጽና፤ ምክሬን አታቃልል፡፡ እግሮችህን ወደ ቀንበርዋ አግባ፤ ዛንጅርዋንም ባንገትህ እሰር፡፡ጫንቃህን ዝቅ አድርገህ ተሸከማት። በእግር ብረትዋ አትበሳጭ፡፡ በፍጹም ነፍስህም ወደ እርሷ ተሰማራ፤ በፍጹም ኃይልህ መንገዷን ጠብቅ፤ ፍለጋዋንም ተከተል፤ ፈልጋት፤ ታገኛታለህም፤ በፍጻሜህም ዕረፍትን ታገኛለህ፤ደስታም ይሆንሃል»

የዳኞችን ፍርድ በገንዘብ ማስለወጥ ይቻላል፤ ኅሊና ግን ከዚህ ልዩ ነው፡፡ ማንንም የማይገባውን ቅጣት ቀጥቶ አያውቅም፤ አስፈጻሚዎቹ እጅና እግር እና ሌሎች አካሎቻችን ፍርዱን ስለሚያበላሹበት ከኅሊና ፈቃድ ውጪ አይንቀሳቀሱም፡፡ ኅሊናው ሁልጊዜ በሰው ላይ እንጅ በራሱ አልፈርድለት ካለ ይህ ሰው እንስሳ ሆኗል ማለት ነው፤ (መዝ. ፵፰÷፳)፡፡  «ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቅም፤ልብ እንደሌላቸው እንስሳትም ሆነ፤መሰላቸውም» ብሎናል፤ ቅዱስ ዳዊት ዕራቁቱን የሚሄደው ሰው መብዛቱ፤ ቅጥ የሌለው ኑሮ በብዙዎቹ ዘንድ እየተለመደ መምጣቱም የዚህ ምልክት ነው፡፡

የኑሮ ውድነት ዘወትር ሲወራ የኅሊና ዋጋ ክርስትና ከሆነ በብር ለምን ይለካል? የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ምግብ የሚያቀርብ ድርጅት ተመሠረተ፤ የኅሊና ዕረፍት ላጡ እና ሕሊናቸውን ሸጠው ሰውነታቸው መቃብር ለሆነባቸው ሰዎችስ ምን ይደረግ ትላላችሁ? እኔ ግን አንድ ነገር እላችኋለሁ፤ የአምላካችን ቅዱስ ቃል መቃብራትን ይከፍታል፡፡ መቃብር የሆነ ልቡናችሁን ይከፍት ዘንድ ቅረቡ፤ (ማቴ ፳፯፥፶፪)«መቃብሮችም ተከፈቱ፤ ተኝተው ከነበሩ ከቅዱሳን በድኖችም ብዙዎች ተነሡ፤ ይለናል” የሰው ልጅ በዓላማው፣ በአመለካከቱ፣ በመረዳት ችሎታው፣ በአኗኗር ዘይቤው፣ እንደሚለያይ ሁሉ በዓለም ሲኖር የሚገጥሙትን ሥጋዊና መንፈሳዊ ችግሮች የመቋቋምና በትክክለኛ መንገድ የመጓዝ ችሎታውም ይለያያል፡፡ ሰዎች ለነገሮች የሚኖራቸው እይታ የተለያየ ነው፡፡ አንዳንዱ የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች ቀለል አድርጎ ሲመለከታቸው ሌላው ደግሞ በጣም አክብዶና አጋኖ ሊመለከታቸው ይችላል፡፡ ሁለት ሰዎች አንድን ተመሳሳይ ክስተት የሚመለከቱበት ወይም የሚረዱበት መንገድ እንደሚለያይ ሁሉ የሚፈቱበት መንገድም ይለያያል፡፡ ለምሳሌ ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ደረጃ ያላቸው ሁለት ሰዎች ከሥራ ቢሰናበቱ አንደኛው መታገሥን መርጦ የነገን ሲያልም ሌላኛው ግን ጨለማ ውስጥ እንደገባ መሥሎ ሊታየው ይችላል፡፡የአእምሮ ውጥረትን የመቋቋም ችሎታ በአጭር ጊዜ የሚመጣ ክሂሎት ሳይሆን በረጅም ጊዜ ልምምድ የሚመጣ ክሂሎት ነው፡፡

በኤልያስ ዘመን ፫ ዓመት ከመንፈቅ ሰማይ የነጠፈው ምድርም የተራቆተው (፩ ነገ.፲፯፥፩)፤ በሌላም ጊዜ ውሃን በማዝነም ፈንታ እሳትን እና ዲንን ያዘነመው (ዘፍ.፲፱፥፳፬፣፪፣፳፩፥፲፪)፤ በንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመን በለኪሶን ሜዳ በአንድ ሌሊት አንድ መቶ ሰማንያ አምስት ሽህ ሬሳ የተገኘው(ኢሳ.፵፯፥፵፮) በሞዓብ ሜዳ ከነበረው ሕዝብ መካከል ፳፫ ሺህ ሬሳ በአንድ ቀን የተገኘው (፩ ቆሮ.፲፥፰) የሰው ልጅ ድንበር በማፍረሱም አይደል?

ዛሬስ ምድር በሰቆቃ የተሞላች መሆን፤ ለዓለማችን ፈውስ በሌለው ቁስል መመታትና በረከት ማጣት ተጠያቂው ማን ይሆን? ምን አልባት በአእምሮአችን ሌላ መልስ አስቀምጠን ይሆናል እንጅ ክፉውም ሆነ ደጉ ነገር የሥራችን ውጤት ነው፡፡ የፈርኦን ባሪያዎች በግብፅ ለተቃጣው መቅሠፍት ሁልጊዜ ተጠያቂ የሚያደርጉት ሙሴን ነበር እንጅ አንድም ቀን ይህ የኃጢአታችን ደምወዝ ነው ብለው አያውቁም(ዘፀ.፲፥፯)

ዛሬም ያለው ትውልድ ለአየር ንብረት መዛባት በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራትን ለታናናሽ ሀገራት የጦርነት ቀጠና መሆን፤ ኃያላን መንግሥታት ለድኃ ሀገራት አለመበልጸግ ቅኝ ገዥዎችን ምክንያት ማድረግ ልማዱ ነው(የእኛ ለእነርሱ የክፋት ድርጊት ራሳችንን አመቻችተን ማቅረባችንን አናስተውልም)፡፡ የሆነብንን ሁሉ እንደ ነቢይ አምነን ለምንቀበል ሰዎች ስለ ኃጢአታችንና ስለ በደላችን ይህ ሁሉ ሆነ ሳለ ያለ ሕግ የሚበድሉ ሁልጊዜም ያለሕግ ይቀጣሉና(ዳን. ፱፥፲፮-፲፯)፤

ይህን ገጽታውን በግልባጩ የተመለከትነው እንደሆነ ደግሞ ምድረ በዳ የሌለው የአጋንንት ማረፊያ ነው፤ (ማቴ. ፲፪፥፵፫) በጾም እና በጸሎት ከሰው ልጆች እንዲወጡ የተገደዱ አጋንንት ወደ ምድረ በዳው ይሰማራሉ፤ ማረፊያ የሌለው በመሆኑ ግን ተመልሰው ወደ መጡበት ቤት ይገባሉ፡፡ በእርግጥ አሁንም የሚሸጋገሩት ከምድረ በዳ ባዶ ወደሆነ ቤት ነው፡፡ ይህ ለእነርሱ ምቹና ባዶም በመሆኑ አጋንንት ያድሩበታል፡፡ የሥጋ ፍሬን ብቻ ስለሚያፈሩ የመንፈስ ፍሬን ረስተውታልና ስለዚህ ያድሩበታል፡፡ ሰው በገዛ ፈቃዱ ሕይወትን ትቶ የኮበለለ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን በሞት ወደ ተቀጣው የሰው ልጅ መጣ፡፡ የደከመውን የሰው ልጆች ባሕርይ ሊያበረታ መንገድ ከመሔድ ደክሞ ሊያርፍ ተቀመጠ ፤ ድካም ሳይኖርበት የሚታየውን እና የማይታየውን ዓለም የፈጠረ አምላክ ዛሬ ግን አዳምን ሊያድነው ወዶ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ለባሕርዩ የማይስማሙ ድካምና ሕማም የቃል ገንዘቦች ሆነው ተነገሩ፡፡«ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ» (ዮሐ.፬፥፮) ተብሎ ለኃያሉ አምላክ ሲነገርለት እንደምን ይገርማል፡፡ መላእክትን ያለ ዕረፍት ሌሊት እና ቀን እንዲያገለግሉ ኃይል የሆናቸው ጌታ እኮ ነው (ራዕ.፬፥፰) ዛሬ ግን ደከመ፤ በእርሱ ድካም ፍጥረት እንዲበረታ ይህ ሁሉ ሆነ፡፡ ያውም ጊዜው ቀትር ነበር፤ የሚያቃጥል ፍጥረት ሁሉ ጥግ ፍለጋ እንዲሸጐጥ የሚያደርግ አስቸጋሪ ሰዓት!ማንም ሰው በኃጢአቱ እንዲሞት የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም። (ሕዝ. ፲፰፥፴፪)

ክርስቲያን በእምነት ሕይወት ውስጥ ዕረፍትን ያገኛል እንዳለን ነቢዩ ኤርምያስ ፮፥፲፮ ላይ «በመንገድ ላይ ቁሙ፤ ተመልከቱ፤ የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች ዕወቁ፤በእርሷም ላይ ሒዱ፤ ለነፍሳችሁ ዕረፍትን ታገኛላችሁ»። እንዳለ እውነተኛ ዕረፍት የሚገኘው ከእግዚአብሔር ስለሆነ እኛም ወደ እርሱ በመቅረብ የማያቋርጥ ዕረፍትን እናገኛለን፡፡ እንዲሁም ለምናከናውነው ሥራ ሁሉ ስልቹ አንሆንም፤  ምክንያቱም የምናመልከው አምላክ ዘለዓማዊ ዕረፍትን ስለሚሰጠን ሥራን ሙሉ ለሙሉ በማቆም ማረፍ ሳይሆን መሰላቸትን በማቆም መንፈሳዊ ሥራንና ማኅበራዊ በጎ ሥራ በማከናወን ማረፍ ማለት ነው።

ልዑል እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ በሥርዓትና በሕግ እንዲመራ አድርጎታል። ለአኗኗሩ ሥርዓት አበጅቶለት ፍጥረታትን እንዲገዛ አዞና ሥልጣን ሰጥቶት በገነት እንዳስቀመጠው እውነት ነው። ስለሆነም የእግዚአብሔር ሕግ ስንልም ከእግዚአብሔር ፈቃድ የመነጨ፣ በእግዚአብሔር የተሰጠ፣ አምላካዊ ድንጋጌ ነው። በመጽሐፈ ሔኖክ ፲፱፥፳፪ ላይ የሰው ልጅ እንደ ንጹሐን መላእክት ሃይማኖቱን አውቆና ጠብቆ ፈጣሪውን በመፍራትና በማምለክ እንዲኖር ነው። በመዝሙር ፩፥፪ ላይ፤ «የእግዚአብሔር ሕግ ብቻ ፈቃዱ የሆነ፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያስብ፤ እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለች፤ ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ፤ ቅጠሏ እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፣ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል»

አስተውል! ያንተ ሕይወት ማለት እኮ እስከ ሞት የሚፋለም ባለቤት ያላት የናቡቴ ርስት ናት፡፡ ሕይወትህ በተቃራኒው የቆመች ምድረ በዳ ብትሆንብህም እንኳ አትፍራ፤እግዚአብሔር የምድረ በዳውም ፈጣሪ ነውና ለአርባ ዘመናት የመራውን ሕዝብ የውርጭ መና ከደመና አውርዶ የመገባቸው፤ውኃውንም ከዐለት ላይ አፍልቆ ያጠጣቸው፤ በምድረ በዳ መሆኑን አትርሳ፤ (መዝ ፸፯፥፳-፵) አንተም መናና ውኃ የተባለ የእግዚአብሔር ቃል ተመግበህና ጠጥተህ ምድረ በዳ የሆነ ሕይወትህን ልታለመልምበት ይገባል፡፡ ትናንት ከትምህርት ምድረ በዳ የነበረችውን የእነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን ሕይወትና የእነ ቅዱስ ያሬድን ሰውነት በልብህ ተመልከታት፤ትውልድ በልቶ የማይጨርሰው የዘለዓለም ስንቅ ተገኝቶባታልና፡፡

 

ምልአተ ባሕር

ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

የበአተ ክረምት ሁለተኛው ክፍል ምልአተ ባሕር ይባላል፡፡ ይህም ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፲ ድረስ ያለው ወቅት ሲሆን ዝናም ምድርን የሚያለመልምበት፤ የተዘራው የሚበቅልበት፤ በፀሐይ ሐሩር የደረቁ ዛፎች ሁሉ የሚያቆጠቁጡበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ከሐምሌ ፲፱ እስከ ሐምሌ ፳፱ መባርቅት የሚበርቁበት፤ ባሕርና አፍላጋት የሚሞሉበት ወቅት ነው፡፡

መብረቅና ነጎድጓድ

መብረቅ ማለት የእሳት ሰይፍ፤ የእሳት ፍላፃ፤ በዝናም ጊዜ ከደመና አፍ የሚመዘዝ የሚወረወር ነው፡፡ (ራእ ፬፥፭፤ ኤር ፲፥፲፫፤ ኢዮ. ፴፯፥፬) የመብረቅ ተፈጥሮ ውሃው በደመና አይበት ተቋጥሮ ሲመጣ በነፋስ ወደል ጋዝ ተጭኖ ፤ ደመናና ደመና በተጋጨ ጊዜ የሚፈጠር ነው፡፡ ወተት ሲገፋ ቅቤ እንደሚወጣው አይነት ማለት ነው፡፡

ነጎድጓድ ማለት ታላቅ ግሩም ድምፅ፤ የሚያስፈራ፤ የሚያስደነግጥና የሚያንቀጠቅጥ ሲሆን (መዝ. ፸፮፥፲፰፤ ኢዮ. ፵፥፬)፤ መብረቅ ከወረደ በኋላ የሚሰማ ድምፅም ነው፡፡ (ኢዮ. ፴፯፥፪-፭፤ መዝ. ፳፰፥፫) ነገር ግን ለማስደንገጥ ወይም ለመዓት ብቻ የተፈጠረ አይደልም፤ ማኅፀነ ምድርን በመክፈት ውኃው ሠርፆ እንዲገባና አዝርዕትና አትክልት እንዲበቅሉ፤ እንዲያብቡና እንዲያፈሩ የሚያደርግ ጭምር ነው፡፡(ሄኖ.፮፥፩)

የክረምትን ኃይልና ብርታት ጥግ አድርገው የሚከሠቱ የተፈጥሮ ኃይላት ዑደትም ይጸናበታል፡፡ መብረቅ፤ ነጎድጓድ፤ ባሕርና አፍላጋት (ወንዞች) ይሠለጥናሉ፡፡ጥልቅ የሆኑ ቦታዎች መጠናቸው ያድጋል፤ ምንጮች ይመነጫሉ፤  የወንዞች ሙላት ይጨምራል፡፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን በዚህ ክፍለ ክረምትና ንኡስ ክፍል ዘርዕን፤ ደመናን፤ ዝናምን የሚያዘክሩ እና የመብረቅን፤ የነጎድጓድን፤ የባሕርን፤ የአፍላጋትን፤ የጠልን ጠባይዓት የሚያመለክቱ መዝሙራት ይዘመራሉ፤ ምንባባት ይነበባሉ፤ ስብከት ይሰበካል፡፡

ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ያሬድም ይህን ወቅት አስመልክቶ በድጓው ላይ በገለጸው መሠረት ‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ነዳያን፤ ይጸግቡ ርኁባን ምድርኒ ርእየቶ ወአእኰተቶ ባሕርኒ ሰገደት ሎቱ፡፡ የዝናም ድምፅ ተሰማ፤ ዝናብም በዘነመ ጊዜ ድሆች ደስ ይሰኛሉ፤ ረኃብተኞችም ይጠግባሉ፤ ምድር አየችው፤ አመሰገነችውም፤ ባሕርም ሰገደችለት›› የሚለው ዜማ ይዜማል፡፡

ቅዱስ ዳዊት ደግሞ በመዝሙሩ ‹‹ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና፤ ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር፡፡ ዘያበቊል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡ ወሐመልማለ ለቅኔ እጓለ እመሕያው፡፡ ‹‹ሰማይን በደመና የሚሸፍን፤ ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ፣ ሣርን በተራሮች ላይ ልምላሜውንም ለሰው ልጆች አገልግሎት የሚያበቅል›› (መዝ.፻፵፮፥፰፤መዝ.፻፴፬፥፮፤መዝ.፸፮፥፲፰፤ መዝ.፷፬፥፱) ሲል ዘምሯል፡፡

እግዚአብሔር በነጎድጓድና በመብረቅ፤ በባሕርና በሐይቅ ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑን፤ የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታት ሁሉ የኃይሉ መገለጫዎች እንደሆኑ የሚያስተምሩ መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡ ምንባባትም ከቅዱስ ወንጌልና ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት እንዲሁም ከሐዋርያት ሥራ ክረምቱን በተመለከተ የተዘጋጁት ይነበባሉ፡፡

 

በአተ ክረምት

 ዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር ስሌት መሠረት ወቅቶች በአራት ይከፈላሉ፡፡ እነዚህም፡- ዘመነ መጸው (መከር)፣ ዘመነ ሐጋይ (በጋ)፣ ዘመነ ጸደይ (በልግ) እና ዘመነ ክረምት ይባላሉ፡፡ ከአራቱ ወቅቶች መካከልም ከሰኔ ፳፮ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ (አሁን የምንገኝበት ወቅት) ዘመነ ክረምት ተብሎ ይጠራል፡፡ ቃሉን ለማብራራት ያኽል፣ ‹ክረምት› የሚለው ቃል ‹ከረመ – ከረመ› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም የዝናም፣ የአዝርዕት፣ የአረም ጊዜ፣ እንደዚሁም ዕፀዋት፣ አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፀዋትና በልምላሜ የምታሸበርቅበት ወቅት ማለት ነው፡፡ ‹ዘመነ ክረምት› ማለትም ይኼንኑ ወቅት የሚያስገነዝብ ትርጉም አለው፡፡

በአተ ክረምት (ዘርዕ፣ ደመና)

ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ድረስ ያለው የመጀመሪያው የክረምት ክፍለ ጊዜ ‹በአተ ክረምት› ወይም ‹ዘርዕ፣ ደመና› ይባላል፡፡ ‹በአተ ክረምት› ማለት ‹የክረምት መግቢያ፣ መጀመሪያ› ማለት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን ስለ ክረምት መግባት፣ ስለ ዘርዕ፣ ስለ ደመና እና ስለ ዝናም የሚያዘክሩ መዝሙራትና ምንባባት ይዘመራሉ፣ ይነበባሉ፡፡ ይህ ወቅት ደመና ሰማዩን የሚሸፍንበት፣ የዝናም መጠን የሚያይልበትና መሬት በዝናም ረክታ ዘር የምታበቅልበት ጊዜ ነውና፡፡

ዘርዕ

ምድር ከሰማይ ዝናምን፣ ከምድርም ዘርን በምታገኝበት ወቅት ዘሩን አብቅላ ለፍሬ እንዲበቃ ታደርጋለች፡፡ በምድር የምንመሰል የሰው ልጆችም ከእግዚአብሔር ባገኘነው ጸጋ ተጠቅመን፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት እና ከመምህራነ ቤተ ክርስቲያን የምናገኘውን ቃለ እግዚአብሔር በተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባን ከምድር እንማራለን፡፡ ይህን ካደረግን ዋጋችን እጅግ የበዛ ይኾናል፣ ከዚህም አልፎ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንበቃለን፡፡ የተዘራብንን ዘር ለማብቀል ማለትም ቃሉን በተግባር ለማዋል ካልተጋን ግን በምድርም በሰማይም ይፈረድብናል፡፡ ‹‹ምድርም በእርስዋ የሚወርደውን ዝናብ ከጠጣች፣ ያን ጊዜ ስለ እርሱ ያረሱላትን መልካም ቡቃያ ታበቅላለች፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድም በረከትን ታገኛለች፡፡ እሾኽንና ኵርንችትን ብታወጣ ግን የተጣለች ናት፡፡ ለመርገምም የቀረበች ናት ፍጻሜዋም ለመቃጠል ይኾናል፣›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ገለጸው (ዕብ. ፮፥፯-፰)፡፡

በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ፲፫፥፩-፳፫ እንደ ተገለጸው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስትና ሕይወትን ከዘርና ፍሬ ጋር በማመሳሰል አስተምሯል፡፡ ይኸውም አንድ ገበሬ ዘር ሲዘራ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር ከመብቀሉ በፊት በወፎች እንደ ተበላ፣ በጭንጫ ላይ የተጣለውም ወዲያውኑ ቢበቅልም ነገር ግን ሥር መስድድ አልቻለምና፡፡ በፀሐይ ብርሃን እንደ ጠወለገ፤ በእሾኽ መካከል የወደቀው ደግሞ ሲበቅል በእሾኽ እንደ ታነቀ፣ ከሁሉም በተለየ መልኩ በመልካም መሬት ላይ የተጣለው ዘር ግን አድጎ መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ ፍሬ እንደ ሰጠ የሚያስረዳ ነው፡፡

ይህም ምሳሌ አለው፡፡ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ተረጐመው በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ የማያስተውል (ልብ የማይል) ክርስቲያን ምሳሌ ነው፣ እንደዚህ ዓይነቱ ምእመን ሙሉ እምነት ስለማይኖረው በመከራው ጊዜ አጋንንት ድል ያደርጉታል፡፡ በጭንጫ ላይ የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበል፣ ነገር ግን ተግባራዊ የማያደርግ (የማይተገብር) የክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ ይህ ምእመንም በጠንካራ እምነት ላይ የጸና አይደለምና በሃይማኖቱ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በደረሰበት ጊዜ ፈጥኖ ይክዳል፡፡ በእሾኽ መካከል የተዘራውም ቃሉን የሚሰማ ቢሰማም ግን በዚህ ዓለም ዐሳብና ባለ ጠግነት ተታሎ ቃሉን የማይተገብር ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡

በመልካም መሬት የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሰምቶ ተግባር ላይ የሚያውል ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምእመን በተማረው ትምህርት ጸንቶ ይኖራል፣ መልካም ሥራም ይሠራል፡፡ በመልካም መሬት የተዘራው ዘር ስለ አንዱ ፋንታ መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ እንደሚያፈራ ሁሉ በክርስቲያናዊ ግብር ጸንቶ የሚኖር ምእመንም ሥራውን በሦስት መንገድ ማለትም በወጣትነት፣ በማእከላዊነትና በፍጹምነት ደረጃ እንደሚፈጽም፣ ዋጋውንም በሥራው መጠን እንደሚያገኝ የሚያስረዳ ነው፡፡ በሌላ በኩል ባለ መቶ ፍሬ የሰማዕታት፣ ባለ ስድሳ የመነኮሳት፣ ባለ ሠላሳ በሕግ ተወስነው በዓለም የሚኖሩ ምእመናን ምሳሌ ነው፡፡ በተመሳሳይ ምሥጢር ሁሉም የፍሬ መጠን በሁሉም ጾታ ምእመናን ሕይወት ውስጥ እንደሚገኝ የትርጓሜ ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡ ስለዚህም በሰማዕትነትም፣ በምንኵስናም፣ በዓለማዊ ሕይወትም ውስጥ የሚኖሩ ምእመናን መልካም ግብራቸው እጅግ የበዛ ከሆነ በባለ መቶ ፍሬ፣ መካከለኛ ከሆነ በባለ ስድሳ፣ ከዚህ ዝቅ ያለ ከሆነ ደግሞ በባለ ሠላሳ ፍሬ ይመሰላል፡፡ (ትርጓሜ ወንጌለ ማቴዎስ፣ ማቴ. ፲፫፥፩-፳፫)፡፡

ደመና

እግዚአብሔር አምላካችን የውቅያኖስ እና የሐኖስ ድንበር ይሆን ዘንድ በውኃ መካከል ጠፈርን ፈጥሮ ከጠፈር በታች (በዚህ ዓለም) ያለው ውኃ በአንድ ቦታ እንዲወሰን አድርጎታል፡፡ ከዚያም ከምድር እስከ ብሩህ ሰማይ ድረስ የነበረውን ውኃ ከሦስት ከፍሎ ሢሶውን አርግቶ ጠፈር ብሎ ሰይሞታል፡፡ ከጠፈር በላይ ያለውን ሢሶውን የውኃ ክፍል ሐኖስ ብሎታል፡፡ ሢሶውንም ይህንን ዓለም ከሰባት ከፍሎ ሰባተኛውን ዕጣ አጐድጕዶ በዚያ ወስኖ ስሙን ውቅያኖስ ብሎ ጠርቶታል፡፡ የብሱን ክፍል ደግሞ ምድር ብሎ ሰይሞታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከደረቅ ምድር ደረቅ ጢስን፣ ከርጥብ ባሕር ርጥብ ጢስን አስወጥቶ እንደ ጉበት በለመለመች ምድር ላይ ደመናን አስገኝቷል (ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት፣ መዝ. ፻፴፬፥፯)፡፡

ደመና፣ ዝናምን የሚሸከም የማይጨበጥ፣ የማይዳሰስ ጢስ መሰል ፍጥረት ነው፡፡ በትነት አማካይነት፣ በደመና ተሸካሚነት ከውቅያኖሶች እና ከወንዞች እየተቀዳ ወደ ሰማይ ተወስዶ እንደ ገና ተመልሶ ወደ ምድር የሚጥለው ውኃ ዝናም ይባላል፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ጥበብ በደመና ወንፊትነት ተጣርቶ ለፍጡራን በሚመችና በሚጠቅም መጠን በሥርዓት ይወርዳል፡፡ ‹‹ያጸንዖ በፍኖተ በድው ከመ ይዝንም ብሔረ ኀበ አልቦ ሰብእ ወኢይነብሮ ዕጓለ እመሕያ፣ ዝናሙን ሰው በሌለበት በምድረ በዳ ያዘንመዋል፤›› እንዳለ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በቅዳሴው፡፡ ይህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔር በረዶውን በምድረ በዳ አፍስሶ የጠራውን ውኃ ሰው ወዳለበት እንዲዘንም ማድረጉን የሚያስረዳ መልእክት የያዘ ሲሆን፣ ምሥጢሩም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንበለ ዘርዐ ብእሲ (ያለ ወንድ ዘር) በልዩ ጥበቡ ተፀንሶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱንና በተዋሐደው ሥጋ በምድር ተመላልሶ ወንጌልን ማስተማሩን፣እንደዚሁም ‹‹ሑሩ ወመሀሩ፤ ሒዱና አስተምሩ›› ብሎ ቅዱሳን ሐዋርያትን በመላው ዓለም ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማሰማራቱን ያመለክታል (ትርጓሜ ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ፣ ፪፥፭-፮)፡፡

ዘመነ ክረምት ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት፤ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን (ምግብን) ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይ እና የሚያሳውቅ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት የውኃ ባሕርይ ይሠለጥናል፣ ውኃ አፈርን ያጥባል፣ እሳትን ያጠፋል፡፡ ሆኖም ግን ውኃ በብሩህነቱ ከእሳት፣ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፣ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር ይኖራል፡፡ ይህን ምሥጢር ከሕይወታችን ጋር አያይዘን ስንመለከተው ዘመነ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፡፡ በክረምት ወቅት ገበሬው ብርዱንና ዝናሙን ሳይሳቀቅ ለሥራ ይሰማራል፣ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሣል፡፡ ይህም ምእመናን በሰማያዊው ዓለም የምናገኘውን ተድላና ደስታ በማሰብ በምድር ቆይታችን ወቅት የሚደርስብንን ልዩ ልዩ መከራ በትዕግሥት ማሳለፍ እንደሚገባን ያስገነዝባል፡፡

በዘመነ ክረምት አዝርዕቱ በስብሰው ከበቀሉ፣ ካበቡና ካፈሩ በኋላ የሚጠቅሙት በሪቅ፣ በጎተራ እንደሚሰበሰቡ፣ እንክርዳዶቹ ደግሞ በእሳት እንደሚቃጠሉ ሁሉ እኛም ተወልደን፣ ተጠምቀን፤አድገን፣ ዘራችንን ተክተን እንደምንኖር፣ ዕድሜያችን ሲያበቃም እንደምንሞት፣ ሞተንም እንደምንነሣና መልካም ሥራ ከሠራን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደምንገባ፣ በኀጢአት ከኖርን ደግሞ በገሃነመ እሳት እንደምንጣል የምንማርበት ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም ሰይጣን በሚያዘንበው የኀጢአት ማዕበል እንዳንወሰድና በኋላም በጥልቁ የእሳት ባሕር እንዳንጣል ዅላችንም ቅዱሳት መጻሕፍትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጁልንን የቃለ እግዚአብሔር ዘር በእርሻ ልቡናችን በመዝራት (በመጻፍ) እንደየዓቅማችን አብበን፣ ያማረ ፍሬ አፍርተን መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር