‹‹ልበ ንጹሓን ብፁዓን ናቸው፤ እግዚእብሔርን ያዩታልና›› (ማቴ. ፭፥፲)

በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከናዝሬት ወደ ቅፍርናሆም በሔደ ጊዜ የገሊላ፣ የኢየሩሳሌም፣ የይሁዳ እና የዮርዳኖስ ሕዝብ ዝናውን ሰምተው ወደ እርሱ መጡ፡፡ በዚያም የመንግሥቱንም ወንጌል ሲሰብክ ‹‹……ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና…….ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤትንም አድርጉ፤ ዋጋችሁ በሰማያት ብዙ ነውና፤ ከእናንተ አስቀድሞ የነበሩ ነቢያትንም እንዲሁ አሳድደዋቸው ነበርና›› ብሎ አስተማራቸው፡፡ (ማቴ.፭፥፩-፲፪)

ጌታችን ነቢያት ያላቸው ጻድቃን እግዚአብሔር አምላካቸውን የሚያገለግሉ ነበሩና ጠላት ዲያብሎስ ሲያሳድዳቸውና ሲያሰቃያቸው ኖሯል፤ ሆኖም ፈጣሪያቸው ሁል ጊዜ ከእነርሱ ጋር  ስለነበር ጠላታቸውን አሸንፈውታል፡፡ በችግር እና መከራ ጊዜም እግዚአብሔር አምላክ  ያበረታቸው ነበር፤ በቃሉ አሰምቶ በፊታቸውም ተገልጦ አናግሯቸዋል፡፡ በኦሪት ዘጸአት ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፩ ላይ እንደተጻፈው እግዚአብሔር አምላክ የእስራኤልን ሕዝብ ነጻ እንዲያወጣ በወደደ ጊዜ ለነቢዩ ሙሴ ተገልጦ እንዲህ አለው፤ ‹‹አሁንም እነሆ÷ የእስራኤል ልጆች ጩኸት ወደ እኔ ደረሰ፤ ግብፃውያንም የሚያደርጉባቸውን ግፍ ደግሞ አየሁ፡፡ አሁንም ና፤ ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን እልክሃለሁ፡፡ ሕዝቤን የአስራኤልን ልጆች ከግብፅ ምድር ታወጣቸዋለህ››፡፡

ዳግምም ምስክሩን ለሚጠብቁ እርሱ በፈቀደ ይድኑ ዘንድ ለነቢዩ ዳዊት እንዲህ አለው፤ ‹‹ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁና፤ ልጆችህ ኪዳኔን÷ ይህንም የማስተምራቸውን ምስክሬን ቢጠብቁ፥ ልጆቻቸው ደግሞ በዙፋንህ ላይ ለዘለዓለም ይቀመጣሉ››፡፡ (መዝ. ፻፴፩፥፲፩) ነቢያት ልበ ንጹሐን ናቸውና አምላካቸውን አይተውታል፤ ለቃሉ ተገዝተው፣ በሕጉ ተመርተው በጾም በጸሎት ተግተው ስለኖሩ መንግሥተ ሰማያትን ወርሰዋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ቅን ልቡናን ይወዳል፤ ‹‹አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ›› ሲል ነቢዩ ዳዊት እንደተማጸነው (መዝ. ፶፥፲) ክርስትናን የተቀበለ ፍጡር በሙሉ ይህን ሊመኝ እና ልብን ንጹሕ ሊያደርግ ይገባል፡፡

የልብ ንጽሕና

ሰው ኃጢአትን ጨርሶ ሲጠላ፣ ኃጢአትንም ሁሉ ሲተውና ከልቡናው ፈጽሞ ሲያጠፋው የልብ ንጽሕናን ያገኛል፡፡ ሰው ኃጢአትን ጨርሶ መጥላቱ ሊታወቅ የሚችለው የሚከተሉትን ሲያደርግ ነው፡፡

. ከኃጢአት በመንፃት

ሀ) ሰው በናቃቸው ኃጢአቶች ሁሉ ላይ ንስሐ መግባት አለበት፤ ኃጢአትንም ሁሉ መተውና ከልቡናው ፈጽሞ ማጥፋት አለበት፤

ለ) ከኃጢአት መንፃት የምንችለውና ከንጽሕና ደረጃ የምንደርሰው ከእግዚአብሔር ጋር ስንሆን ነው፤ ‹‹እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ሰዎች በእኛ ላይ በተነሡ ጊዜ ቁጣቸውም በላያችን በነደደ ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ ሕያዋን ሳለን በዋጡን ነበር››(መዝ. ፻፳፫፥፪-፫)

ሐ) እግዚአብሔር በፀጋው ከልሎ በቸርነቱ ጠብቆ ከኃጢአቱ ሊያሳርፈን ይችላል፤ ይህም ንጽሓን ስለሆንን አይደለም፤

መ) ትላልቅ ሰዎች ከሕፃናት ይልቅ ስለሚፈተኑ በጦርነቱ ውስጥ ሆነው ተዋግተው ያልፋሉ፡፡ የኃጢአትንም ኃይል ተቃውመዋልና የድል አክሊል ያገኛሉ፡፡ የልብ ንጽሕና ፍጹም ንጽሕና ማግኘት ነው፤ ፍጹም ንጽሕና ከኃጢአት ሁሉ መንፃት ነውና፡፡

፪. ስለ ንጽሕና መፈተን

ሰው ንጹሕ ሊባል የሚችለው እጅግ ከባድ የሆነ የኃጢአት ፈታና ቢደርስበት እንኳ ሳይናወጥ የኃጢአትን ኃይል የተቋቋመ እንደሆነ ነው፡፡ ንጹሕ ልብ አለን የምንባለው በኃሳብ፣ በስሜት፣ በመናገር፣ በአካል እንዲሁም በማድረግ ከሚሠሩ ኃጢአቶች ሁሉ ልቡናችንን ያነፃን እንደሆነ ነው፤ እግዚአብሔር በሰጠው ፀጋ ታግዞ እነዚህን ሁሉ ኃጢአቶች ተዋግቶ ያሸነፈ ሰው ነው፡፡  እግዚአብሔርን የሚያየው ይህም የመጨረሻው የንጽሕና ምዕራፍ ነው፤ ‹‹ልበ ንጹሐን ብፁአን ናቸው፤ እግዚእብሔርን ያዩታል›› እንደተባለው፡፡ (ማቴ. ፭፥፲)    

. ከክፉ ሀሳብ መንፃት

ከሀሳብና ከግምት፣ ከመላምትም መንፃት ይገባል፡፡‹‹መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፤ ክፉም ሰው ከልቡ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል››(ሉቃ. ፯፥፵፭)፡፡ ሀሳባችን ክፉ ከሆነ ልባችን ገና አልነፃም፤ ልበ ንጹሑ የሆነ ሰው ምንጊዜም ቢሆን የሚያስበው መልካም ነገርን ነውና፡፡ አእምሮአችን ንጹሑንና ለንስሐ ሕይወት የሚሳማማውን ሀሳብ እንዲመዝገብ ይሆናል፤ ያኔ የሚያልመው ነገርም ንጹሕ ይሆናል፡፡

. ከማያስፈልጉ ነገሮች መንፃት

ከማያስፈልጉና ጥቅም ከሌላቸው ነገሮች መንፃት ማለት ነው፤ ለምሳሌ የሚሠሩ፣ የሚነበቡ፣ የሚታዩ፣ የሚደመጡ ሆነው ኃጢአትም ጽድቅም ያልሆኑ ነገሮች በመሆናቸው ጊዜያችንን ያባክንብናል፡፡ ‹‹አቤቱ ከንቱ ነገርን እንዳያዩ አይኖቼን መልስ››እንዲል፡፡ (መዝ. ፻፲፰፥፴፯)

. የንጽሕና ገጽታ

ንጹሕ ልብ የፍቅረ እግዚአብሔር ማደሪያ ነው፡፡ ንጹሕ ልብ ያላቸው ሰዎች የሚያደርጉትን ሁሉ እግዚአብሔርን በማፍቀር ያደርጋሉ እንጂ ስለታዘዙ አይደለም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ማለትም ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውኃት፣ ራስን መግዛት፣ በግልጽ ይታያሉ፡፡ እነዚህንም የሚከለክል ሕግ የለም፡፡ (ገላ. ፭፥፳፪) ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬን ለማግኘት መትጋት አለብን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ንጹሕ ልቡናን ይፈጥርልን እና በሕይወታችን ይኖር ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ የንስሓ ሕይወት መጽሐፍ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ፭የግብፅኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፤ ውርስ ትርጉም ቀሲስ እሸቱ ታደሰ ወንድምአገኘሁ