‹‹አቤቱ÷ በመዓትህ አትቅሠፈኝ÷ በመቅሰፍትህም አትገሥጸኝ›› (መዝ. ፴፯፥፩)

እግዚአብሔር አምላክ በአሕዛብ ዘንድ ያለው ኃጢአት ከትዕግሥቱ ልክ በሚያልፍ ጊዜ ቁጣው ይበረታል፤ በሕዝቡ መካከል ያለውን ኃጢአትም አይታገሥም፡፡አሕዛብም የእግዚአብሔርን ትዕግሥት እና የተሰጣቸውንም የንስሓ ዕድል እየገፉ፣ የባሰ ክፋት ሲሠሩ በእግዚአብሔር ቁጣ ሥር ይወድቃሉ፡፡ ‹‹ከምድር ወገን ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ፤ ስለዚህ ስለ ኃጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ›› (አሞጽ ፫፥ ፪) በማለት በነቢይ አሞጽ አድሮ ይህን አስቀድሞ ተናግአል፡፡

ምድር በኃጢአት ዙሪያዋን በተከበበችበት በእንደዚህ ዓይነቱ ዘመን ሰዎች ከሚሠሩት ኃጢአት የተነሣ የእግዚአብሔር ቁጣ ይበዛል፤ ሕጉን በመተላለፍሥርዓቱንም በማፍረስ አምላክነቱን ሲጋፉ እና የእጁን ሥራዎችም ሲበድሉ የእግዚአብሔር ቁጣ ይነድዳል፣ ይቃጠልማል፡፡ በእነርሱም ላይ መዓትና መቅሰፍትም ይላካል፤ ሰደድ እሳት፣ ማዕበል፣ ልዩ ልዩ በሽታዎች የሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋሉ፡፡ ‹‹ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፥ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር›› እንዲል። (ሕዝ. ፳፪፥ ፴፩)

በዚህ ጊዜ ዓለም በገዳይ በሽታ እየተቀሰፈች እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች በሰዎች ዘንድ እየደረሱ ይገኛሉ፤ በሕክምና ውስጥ ያሉ ባለሞያዎች በሽታውን ኮሮና ቫይረስ ማለትም የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ እንደሆነና በእንስሶችም ላይ የሚከሰት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በሽታው የሰዎችን ሳንባ በማጥቃት ለከባድ ሥቃይ እንደሚዳርግ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከጥንት ጀምሮ ዓለም በእንደዚህ ዓይነት በሽታ ስትጠቃ እንደቆየች ታሪክ ምስክር ነው፤ እንደ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ቫይረስና የቅርብ ጊዜ ክስተት የሆኑት ኢቦላና ሳርስ በሽታዎች ሰዎችን በተለያዩ መንገድ በመያዝና በማሠቃየት ለሞት ዳርገዋል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም ከተጠቁት የዓለም ክፍላት ውስጥ አንዷ ናት፤ በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ሺዎችን አጥታለች፤ አሁንም እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ ያለው ኮሮና ቫይረስ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እንደገባ ምንጮች የሕክምና ማስረጃ ምንጮ ይፋ አድርገዋል፡፡

በዓለም ዙሩያ በሕክምናው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ለበሽታው መድኃኒት በማጣታቸው መንግሥታት ለዜጎቻቸው ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስጠንቅቀዋል፤ መከላከያ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሏቸውን መንገዶች አስታውቀዋል፡፡

ነገር ግን ቤተክርስቲያናችን ሰዎች በክፉ ደዌ ሲያዙ ፈውሰ ሥጋን የሚያገኙት በጸበል፤ በጾምና በጾሎት እንደሆነ ታስተምራለች፤ እንደነዚህ ዓይነቱ ተዛማች በሽታም የእግዚአብሔር ቁጣ መሆኑን ታስረዳለች፡፡ ልበ አምላክ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹አቤቱ÷ በመዓትህ አትቅሠፈኝ÷ በመቅሰፍትህም አትገሥጸኝ›› ሲል አምላኩን ተማጽኗል፡፡ (መዝ. ፴፯፥፩)

የእግዚአብሔር ቁጣ በግልፍተኝነትም አይደለም፤ በትዕግሥቱና በምሕረቱ ሰዎችን በንስሓ ወደ እርሱ እንዲመለሱ የንስሓ ጊዜ ይሰጣቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጥረታት ውስጥ ክብርን ሊያመጣም ሆነ  ሊሰጠው የሚበቃ፣ ለዚህም የሚመጥን አንድም የለም፤ በአምላክነቱ ክቡር በዙፋኑ ኃያል ሆኖ ይኖራል፤ ከፍጡሮቹ ይህ አይጎድልበትም፡፡ ፍጡሮቹ እርሱን ለማምለክ ከታደሉ ግን ክብሩን ተረድተው ይደነቃሉ፤ ይገዙለታልም፡፡

የእግዚአብሔር ቁጣ ቅድስናውንም ይገልጻል፤  እርሱ ምን ያህል ኃጢአትን እንደሚጸየፍ  የሚያመለክት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቁጣ ኃጢአተኞችን መቅጫ ሲሆን ለሚያመልኩት እና የእርሱ ለሆኑት ደግሞ የአምላክነቱ መገለጫ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቁጣ በሚበዛበት ጊዜ ሰዎች ፈጣሪያቸውን ያስባሉ፤ ወደ እርሱም ይጮሃሉ፡፡

በኃጢአታችን ምክንያት የሚመጣው የእግዚአብሔር ቁጣ ግዝፈት እጅግ ከባድ ነው፡፡ እርሱ ኃጢአትን ፈጽሞ እንደሚጠላ የሚያመለክት ነው፤ ኃጢአት መሥራት ከእግዚአብሔር እንድንርቅ፣ እርሱንም እንድናሳዝንና እንድናስቆጣ ስለሚያደርገን  እኛም እንደዚሁ ኃጢአትን ልንጠላና ልንንቅ ይገባናል፡፡

አባታችን አዳም ኃጢአትን ሠርቶ ማመጣው የሞት ቅጣት፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል መከራንና ሥቃይን እንደተቀበለ፣ በመስቀል እንደተሰቀልና እንደሞተ  መዘንጋት የለብንም፡፡

ኃጢአትን አቅልሎ ማሰብ የክርስቶስን መከራ አቅልሎ እንደማሰብ ይሆናል፤ እናም የእርሱን ክብርም አለማወቅ ነው፡፡

በእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣ ሥር የወደቀ ሰው፣ ኃጢአተኛ መሆኑ ያላሳሰበው፣ በወንጌል ያለውን ታላቅ የምሕረት መጽናናትና በክርስቶስ የተገለጠውን የጸጋ ብዛት ለማድነቅ ምንም ዕድል አይኖረውም። በመሆኑም ልበ አምላክ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹አቤቱ÷ በመዓትህ አትቅሠፈኝ÷ በመቅሰፍትህም አትገሥጸኝ›› ሲል አምላኩን እንደተማጸነው እኛም ወደ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር በመመለስ፣ ይቅርታና ምሕረትን በመለመንና ንስሓ በመግባት ቁጣውን ወደ ምሕረት እንዲለውጥልን መማጸን አለብን፡፡