ቅድስት ማርያም (ባለሽቶዋ) እንተ ዕረፍት

እግዚአብሔር ወልድ ተገልጦ በምድር ወንጌልን በሰበከበት በዘመነ ሥጋዌ  እስራኤላዊያን ወደ እርሱ እየቀረቡ ትምህርቱን በመስማት ጥያቆዎችን ያቀርቡለት፣ ምሕረትን ይማጸኑት፣ እንዲሁም የእጁን ተአምራቶችን በማየት ያደንቁት ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ጥያቄያቸውን በምሳሌ ይመልስ፣ ድውያንና በሽተኞችን ይፈውስ፣ ድንቅ ተአምራትን ያደርግ ነበር፡፡ ከሁሉ በላይ የእርሱን አምላክነት አምነው ነፍሳቸውን እንዲያድናላቸው ለለመኑት ድኀነትን አድርጓል፡፡ የእነዚህን ሰዎች ታሪክ ምሳሌ እንዲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቧልና እኛም ከእነዚህ ተምሳሌቶች ውስጥ አንዷ ስለሆነችው ቅድስት ማርያም እንተ ዕረፍት (ባለሽቶዋ) በየካቲት ፮ እናወሳለን፤ ይህም የዕረፍቷ ቀን ነው፡፡

ቅድስት ማርያም ቀደም ሲል ኑሮዋን በዝሙት ያሳለፈች ሴት ነበረች፡፡ ጎልማሶችንም ትማርክ የነበረው በጌጥ እየትሸለመችም ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ወደተለመደው ተግባሯ ለመሄድ ተሸልማ አጌጠች፤ ሽቶም ተቀባች፡፡ ፊቷን በመስታወት በማየት ለአንድ ሰዓት ያህል የጉንጯ ቅላትና ደም ግባት፤ የዓይኗ ወገግታና ጥራት ማማሩን በማየት አደነቀች፡፡ በዚህ ቅጽበት ግን በጎ ኀሳብ በአእምሮዋ መጣ፤ ያም ሞትንና ዓለምን ማሸነፍ ነበር፡፡ (ስንክሳር ዘወርኀ የካቲት ፮)

በዚያን ዘመን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን እንደሚቀበልና ኃጢአትን እንደሚያስተሰርይ ሲወራ በሰማች ጊዜ ገንዘቧን ሰብስባ የአልባስትሮን ሽቱ ገዛችበት፡፡ ‹‹እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደተቀመጠ ባወቀች ጊዜ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች፡፡›› (ሉቃ. ፯፥፴፯-፴፰) ጌታችንም በስምዖን ቤት እንደ ግብፃውያን አቀማመጥ እግሩን ወደኋላ አድርጎ  ነበር፤ አንድም ወንበሩ እንደ አፍርንጆች ወንበር እግር ወደኋላ የሚያደርግ ነው፤(ወንጌል ቅዱስ) እርሷም ከአጠገቡ ስትደርስ ከእግሩ በታች ከሰገደች በኋላ ‹‹በስተኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፤ በራስ ጠጉሯም ታብሰው፣ እግሩንም ትስመው፣ ሽቱም ትቀባው ነበረች፡፡›› (ሉቃ.፯፥፴፰-፴፱)

ጌታችንንም የጠራው ፈሪሳዊ ‹‹ይህስ ነቢይ ቢሆን ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደሆነች እንዴትስ እንደነበረች ባወቀ ነበር÷ ኃጢአተኛ ናትና›› ብሎ ተናገረ፡፡(ሉቃ.፯፥፴፱-፵) ጌታችን ኢየሱስም ይህን አውቆ ለስምዓን እንዲህ አለው፤ ‹‹ለአንድአበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት፤ በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት፤ በሁለተኛውም አምሳ፡፡ የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው፡፡ እንግዲህ ከሁለቱ አብልጦ የሚወደው ማንኛነው?›› ብሎ በጠየቀው ጊዜ ስምዖን መቶ ዲናር የተወለትን አብልጦ ሊወደው አንደሚገባ ለጌታ መለሰለት፤ ጌታችንም ትክክል እንደፈረደ ከነገረው በኋላ ወደ ሴቷ ዞሮ ስምዖንን እንዲህ አለው፤ ‹‹ይህችን ሴት ታያታለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ÷ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብክልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች፤ በጠጉርዋ አበሰች፡፡ አንተ አልሳምከኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም፡፡ አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች፡፤ ስለዚህ እልሃለሁ÷ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል፡፡ እርስዋንም ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል፤ አምነትሽም አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት፤›› (ሉቃ.፯፥፵-፶) ወንጌልም በሚሰበክበት ይህን ያደረገችውን እንዲአስቡ አዘዘ፡፡ (ስንክሳር ዘወርኀ የካቲት (ስንክሳር ዘወርኀ የካቲት ፮)

ምንጭ፤ ስንክሳር ዘወርኀ የካቲት፤ ወንጌል ቅዱስ